-
ከውጥረት እፎይታ ለማግኘት የሚረዳ ተግባራዊ መፍትሔመጠበቂያ ግንብ—2001 | ታኅሣሥ 15
-
-
ቀንበሩን መሸከም
9, 10. በጥንት ጊዜ ቀንበር ምንን ለማመልከት ያገለግል ነበር? ኢየሱስ ቀንበሩን በላያቸው እንዲሸከሙ ለሰዎች ግብዣ ያቀረበው ለምን ነበር?
9 በማቴዎስ 11:28, 29 ላይ በሚገኙት ቃላት ውስጥ ኢየሱስ “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ” እንዳለ አስተውለሃል? በዚያ ዘመን ይኖር የነበረ አንድ ተራ ሰው ቀንበር ተሸክሞ የሚሠራ ያህል ሊሰማው ይችላል። ከጥንት ጊዜ አንስቶ ሰዎች ቀንበር የሚለውን ቃል ባርነትን ወይም ጭቆናን ለማመልከት ሲጠቀሙበት ኖረዋል። (ዘፍጥረት 27:40፤ ዘሌዋውያን 26:13፤ ዘዳግም 28:48) ኢየሱስ ያገኛቸው ብዙዎቹ የቀን ሠራተኞች ቃል በቃል በትከሻቸው ላይ ቀንበር ተሸክመው ከባድ ዕቃዎችን ያጓጉዙ ነበር። እንደ ቀንበሩ ቅርጽ አንዳንዱ የሚመች ሌላው ደግሞ አንገትና ትከሻን እየፈገፈገ የሚያሳምም ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ አናጢ የነበረ እንደመሆኑ መጠን ቀንበር ሠርቶ ሊሆን ይችላል። ከሆነ ደግሞ “ልዝብ” የሆነ የሚመች ቀንበር እንዴት መሥራት እንደሚቻል ያውቃል። ቀንበሩ የሚመችና የማይቆረቁር እንዲሆን አንገትና ትከሻ ላይ የሚያርፈውን ክፍል በቆዳ ወይም በጨርቅ ይጠቀልለው ይሆናል።
10 ኢየሱስ “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ” ብሎ ሲናገር ራሱን ለአንድ ሠራተኛ አንገትና ትከሻ የሚመች ‘ልዝብ’ ቀንበር ከሚሠራ ሰው ጋር አመሳስሎ መናገሩ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ኢየሱስ “ሸክሜም ቀሊል ነውና” በማለት ተናግሯል። ይህም ቀንበሩ ለሸክም የማይቆረቁርና ሥራውም ቢሆን አድካሚ አለመሆኑን ያመለክታል። እርግጥ ነው ኢየሱስ ቀንበሩን እንዲሸከሙ አድማጮቹን ሲጋብዝ በዚያን ጊዜ ይደርስባቸው ከነበረው ጭቆና በሙሉ ወዲያው እንደሚገላገሉ መናገሩ አልነበረም። ያም ሆኖ ግን ነገሮችን ከተለየ አቅጣጫ እንዲያዩ ማድረጉ ራሱ ትልቅ እረፍት ያስገኝላቸዋል። በአኗኗራቸውና ነገሮችን በሚያከናውኑበት መንገድ ላይ የሚያደርጉት ማስተካከያም እፎይታ ያመጣላቸዋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ብሩህና ጠንካራ የሆነ ተስፋ ማግኘታቸው ያለባቸውን ውጥረት ያቃልልላቸዋል።
አንተም እረፍት ማግኘት ትችላለህ
11. ኢየሱስ አንድን ቀንበር በሌላ ቀንበር ስለ መቀየር ያልተናገረው ለምንድን ነው?
11 ኢየሱስ ሕዝቡ በላያቸው ላይ ያለውን ቀንበር በሌላ ቀንበር እንዲቀይሩት እንዳልተናገረ ልብ በል። በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች የሚኖሩበትን አገር የሚያስተዳድሩ መንግሥታት እንዳሉ ሁሉ በዚያን ጊዜም የሮም መንግሥት አገሪቱን ይገዛ ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሮማውያን ከሚያስከፍሉት ቀረጥ ነፃ መሆን አይቻልም። የጤናና የኢኮኖሚ ችግሮች አልተወገዱም። አለፍጽምና እና ኃጢአት በሰዎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ቀጥለው ነበር። ቢሆንም ዛሬ እኛ እፎይታ ማግኘት እንደምንችለው ሁሉ የኢየሱስን ትምህርት ተቀብለው በሥራ ላይ በማዋል እረፍት ማግኘት ይችሉ ነበር።
12, 13. እረፍት ያመጣል በማለት ኢየሱስ ጎላ አድርጎ የገለጸው ምንድን ነው? አንዳንዶችስ ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው?
12 ኢየሱስ ስለ ቀንበር የተናገረው ምሳሌ ይበልጥ የሚሠራው ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ በተመለከተ ነው። የኢየሱስ ዋነኛ ሥራ በአምላክ መንግሥት ላይ ይበልጥ በማተኮር ሰዎችን ማስተማር እንደነበር የተረጋገጠ ነው። (ማቴዎስ 4:23) ስለዚህ ኢየሱስ “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ” ብሎ ሲናገር የእሱን ፈለግ በመከተል በዚህ ሥራ መካፈልን እንደሚጨምር ግልጽ ነው። ሥራ ማግኘት ብዙ ሰዎችን የሚያሳስብ ጉዳይ ቢሆንም እንኳ ኢየሱስ ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች ይተዳደሩበት የነበረውን ሥራ እንዲቀይሩ እንዳነሳሳቸው የወንጌል ዘገባዎች ያሳያሉ። ኢየሱስ “በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ” በማለት ለጴጥሮስ፣ ለእንድርያስ፣ ለያዕቆብ እና ለዮሐንስ ያቀረበላቸውን ጥሪ አስታውስ። (ማርቆስ 1:16-20) እነዚህ ዓሣ አጥማጆች እሱ በሚሰጣቸው መመሪያና እርዳታ በመታገዝ እርሱ በሕይወቱ ውስጥ ቅድሚያ ሰጥቶ እያከናወነ ያለውን ሥራ ቢያከናውኑ ከፍተኛ እርካታ እንደሚያገኙ ገለጸላቸው።
13 አንዳንድ አይሁድ አድማጮቹ መልእክቱ ገብቷቸው በሕይወታቸው ተግባራዊ አድርገውታል። በሉቃስ 5:1-11 ላይ የምናነበውን በባሕር ዳርቻ የተከናወነ ትዕይንት በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። አራት ዓሣ አጥማጆች ሌሊቱን ሙሉ ሲለፉ ቢያድሩም አንድም ዓሣ አልያዙም ነበር። በድንገት ግን መረባቸው በዓሦች ተሞላ! ይህ እንዲሁ በአጋጣሚ የተከሰተ አልነበረም፤ የኢየሱስ እጅ ነበረበት። ዓይናቸውን አቅንተው ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሲመለከቱ የኢየሱስን ትምህርቶች ለማዳመጥ ጓጉተው የተሰበሰቡ እጅግ ብዙ ሰዎች ተመለከቱ። ይህም ኢየሱስ ለእነዚህ ለአራቱ ‘ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምዱ ትሆናላችሁ’ በማለት የነገራቸው ምን እንደሆነ ማስተዋል አስችሏል። እነርሱስ የሰጡት ምላሽ ምን ነበር? “ታንኳዎችንም ወደ ምድር አድርሰው ሁሉን ትተው ተከተሉት።”
14. (ሀ) በዛሬው ጊዜ እረፍት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ያወጀው እረፍት የሚያስገኝ ምሥራች ምንድን ነው?
14 አንተም ተመሳሳይ ምላሽ መስጠት ትችላለህ። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሰዎች የማስተማሩ ሥራ አሁንም በመከናወን ላይ ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ስድስት ሚልዮን የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ‘ቀንበሩን በላያቸው እንዲሸከሙ’ ኢየሱስ ያቀረበውን ግብዣ በመቀበል “ሰዎችን አጥማጆች” ሆነዋል። (ማቴዎስ 4:19) አንዳንዶች ይህንን የሙሉ ጊዜ ሥራቸው አድርገው የያዙት ሲሆን ሌሎች ደግሞ የተቻላቸውን ያህል ጊዜያቸውን ለዚህ ሥራ ያውላሉ። ይህ ሥራ ለሁሉም እረፍት ያስገኘላቸው ሲሆን በሕይወታቸው ውስጥ ያለባቸውን ውጥረት ቀንሶላቸዋል። ይህም ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ ምሥራች ለሌሎች መንገር ማለትም የሚያስደስት ሥራ መሥራትንም ይጨምራል። (ማቴዎስ 4:23) ምሥራች መናገር በተለይ ደግሞ ይህን ምሥራች መናገር ምንጊዜም ቢሆን የሚያስደስት ነው። ብዙዎች ያለባቸውን ውጥረት ማቃለል እንደሚችሉ ለማሳመን የሚረዱን መሠረታዊ ትምህርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረው እናገኛለን።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
15. ኢየሱስ ሕይወታችንን ስለምንመራበት መንገድ ከሰጠው ትምህርት ጥቅም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?
15 ስለ አምላክ መንግሥት ገና መማር የጀመሩ ሰዎችም እንኳ ሕይወታቸውን እንዴት መምራት እንደሚችሉ ከኢየሱስ ትምህርቶች የተወሰነ ጥቅም አግኝተዋል። የኢየሱስ ትምህርቶች እረፍት እንደሰጣቸውና ሕይወታቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲለውጡ እንደረዳቸው ብዙዎች በእርግጠኝነት ሊናገሩ ይችላሉ። በተለይ ማቴዎስ፣ ማርቆስ እና ሉቃስ የጻፏቸውን በወንጌሎች ውስጥ የሚገኙትን ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የሚገልጹትን አንዳንዶቹን መሠረታዊ ሥርዓቶች በመመርመር ይህንን በራስህ ሕይወት ልታረጋግጥ ትችላለህ።
እረፍት የሚገኝበት መንገድ
16, 17. (ሀ) ኢየሱስ ያስተማራቸውን አንዳንዶቹን ቁልፍ ትምህርቶች የት ልታገኛቸው ትችላለህ? (ለ) የኢየሱስን ትምህርቶች በሥራ ላይ በማዋል እረፍት ለማግኘት ምን ማድረግ ያስፈልጋል?
16 በ31 እዘአ የጸደይ ወራት ኢየሱስ እስከ ዛሬ ድረስ በሰዎች ዘንድ ሰፊ እውቅና ያተረፈ አንድ ንግግር አቀረበ። አብዛኛውን ጊዜ የተራራው ስብከት በመባል ይታወቃል። ይህ ስብከት ከማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ ምዕራፍ 7 እና በሉቃስ ምዕራፍ 6 ላይ ሰፍሮ የሚገኝ ሲሆን አብዛኞቹን የኢየሱስ ትምህርቶች ጠቅለል አድርጎ ይዟል። ኢየሱስ ያስተማራቸውን ሌሎች ትምህርቶች በወንጌሎች ውስጥ በሌሎች ቦታዎችም ላይ ማግኘት ትችላለህ። አብዛኞቹ ትምህርቶች በጣም ግልጽ ቢሆኑም በሥራ ማዋሉ ግን እንደመናገሩ ቀላል አይደለም። እነዚህን ምዕራፎች ለምን ጊዜ ወስደህ በጥንቃቄ አታነብባቸውም? ትምህርቶቹ ያላቸው ኃይል አስተሳሰብህንና ዝንባሌህን እንዲቀርጹ ፍቀድ።
17 እርግጥ ነው የኢየሱስን ትምህርቶች በተለያዩ መንገዶች መከፋፈል ይቻላል። በወር ውስጥ በየቀኑ ቁልፍ በሆነ አንድ ትምህርት ላይ ለመሥራት ግብ ማውጣት ትችል ዘንድ እነዚህን ትምህርቶች እንከፋፍላቸው። እንዴት? ትምህርቶቹን እንዲሁ ገረፍ ገረፍ አድርገህ ብቻ አትለፋቸው። “የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?” በማለት ኢየሱስ ክርስቶስን የጠየቀውን ባለጠጋ አለቃ አስታውስ። ኢየሱስ የአምላክ ሕግ የሚጠይቃቸውን በጣም አስፈላጊ የሆኑ ብቃቶች በጠቀሰ ጊዜ ሰውዬው እነዚህን ብቃቶች ቀደም ሲልም ይፈጽማቸው እንደነበረ ገለጸ። ቢሆንም ገና ሊያደርገው የሚገባ ነገር እንዳለ ተገነዘበ። ኢየሱስም ሰውዬው ንቁ ደቀ መዝሙር ለመሆን የአምላክን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በሆነ መንገድ በሕይወቱ ውስጥ በሥራ ላይ ለማዋል ከፍተኛ ጥረት እንዲያደርግ ጠየቀው። ሰውዬው ግን ይህን ለማድረግ የተዘጋጀ አይመስልም ነበር። (ሉቃስ 18:18-23) ስለሆነም ዛሬ የኢየሱስን ትምህርቶች ለመማር የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በኢየሱስ ትምህርቶች እንደሚስማማ በመግለጽና ትምህርቶቹን አጥብቆ በመያዝ መካከል ልዩነት እንዳለ ማስታወስ ይኖርበታል። ውጥረትን ማቅለል የሚቻለው በዚህ መንገድ ነው።
18. ከዚህ ጥናት ጋር የቀረበውን ሣጥን ጠቃሚ በሆነ መንገድ እንዴት ልትጠቀምበት እንደምትችል ግለጽ።
18 የኢየሱስን ትምህርቶች መመርመርና በሥራ ላይ ማዋል ትችል ዘንድ በመጀመሪያ ከዚህ ርዕስ ጋር በቀረበው ሣጥን ውስጥ የሚገኘውን አንደኛ ነጥብ ተመልከት። ማቴዎስ 5:3-9ን ይጠቅሳል። ማናችንም ብንሆን በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ በሚገኙት ግሩም ምክሮች ላይ ረዘም ላለ ሰዓት ማሰላሰል እንደምንችል የታወቀ ነው። ሆኖም እንዲያው በጥቅሉ ስትመለከታቸው ባሕርይን በሚመለከት ምን ብለህ ልትደመድም ትችላለህ? ከልክ ያለፈ ውጥረት በሕይወትህ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በእርግጥ ማሸነፍ የምትፈልግ ከሆነ ምን ሊረዳህ ይችላል? ትኩረት ሰጥተህ በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ በማሰላሰል ያለህበትን ሁኔታ ማሻሻል የምትችለው እንዴት ነው? ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ተጨማሪ ትኩረት መስጠት ትችል ዘንድ በሕይወትህ ውስጥ ያን ያህል ትልቅ ቦታ ሊሰጣቸው የማይገቡ አንዳንድ ጉዳዮች ይኖሩ ይሆን? እንደዚያ ካደረግህ ደስታህ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ይጨምራል።
19. ተጨማሪ ማስተዋልና እውቀት ለማግኘት ምን ልታደርግ ትችላለህ?
19 አሁን ደግሞ ልትወስደው የሚገባ ሌላ ተጨማሪ እርምጃ እንመልከት። እነዚህን ጥቅሶች ከአንድ የአምላክ አገልጋይ ምናልባትም ከትዳር ጓደኛህ፣ ከቅርብ ዘመድህ ወይም ከጓደኛህ ጋር ለምን አትወያይባቸውም? (ምሳሌ 18:24፤ 20:5) ባለጠጋው አለቃ አስፈላጊ ስለሆነ አንድ ጉዳይ ሌላ ሰው ማለትም ኢየሱስን እንደጠየቀ ልብ በል። የተሰጠው ምላሽ ደስታውን ሊጨምርለትና ቀሪ ሕይወቱን ብሩህ ሊያደርግለት ይችል ነበር። እነዚህን ጥቅሶች የምታወያየው የእምነት ባልደረባህ ከኢየሱስ ጋር እንደማይተካከል እሙን ነው፤ ሆኖም በኢየሱስ ትምህርቶች ላይ የምታደርጉት ውይይት ሁለታችሁንም ይጠቅማችኋል። ለምን አሁኑኑ እንዲህ ማድረግ አትጀምርም።
20, 21. ስለ ኢየሱስ ትምህርቶች ለመማር ምን ዓይነት ፕሮግራም ልትከተል ትችላለህ? ያደረግኸውን እድገት መገምገም የምትችለውስ እንዴት ነው?
20 አሁንም “አንተን ለመርዳት የተዘጋጁ ትምህርቶች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት። ትምህርቶቹ በየቀኑ ቢያንስ አንድ ጥቅስ መመርመር በሚያስችልህ መንገድ ተዘጋጅተዋል። በመጀመሪያ በተጠቀሱት ጥቅሶች ውስጥ ኢየሱስ የተናገረውን ልታነብ ትችላለህ። ከዚያም ስለ ቃላቱ አስብ። በሕይወትህ እንዴት በሥራ ላይ ልታውላቸው እንደምትችል አሰላስል። እየሠራህበት ያለኸው ነገር እንደሆነ ከተሰማህ ከዚህ መለኮታዊ ትምህርት ጋር ተስማምተህ ለመኖር ምን ተጨማሪ ነገር ልታደርግ እንደምትችል አሰላስል። በዚያው ዕለት ትምህርቱን በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት አድርግ። ትምህርቱን መረዳት ወይም እንዴት በሥራ ላይ እንደምታውለው ማወቅ ከተቸገርህ ሌላ አንድ ቀን ጨምር። ይሁን እንጂ በዚህ ትምህርት እስካልተሳካልህ ድረስ ወደ ሌላ ትምህርት ማለፍ እንደማትችል አድርገህ አታስብ። በሚቀጥለው ቀን ሌላ ትምህርት ልትመረምር ትችላለህ። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ አራቱን ወይም አምስቱን የኢየሱስ ትምህርቶች በሥራ ላይ በማዋል ረገድ ምን ያህል እንደተሳካልህ ልትከልስ ትችላለህ። በሁለተኛውም ሳምንት በየቀኑ እንዲሁ አድርግ። ያለፉትን አንዳንድ ትምህርቶች በሥራ ላይ ማዋል ብትቸገር ተስፋ አትቁረጥ። ሁሉም ክርስቲያኖች እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። (2 ዜና መዋዕል 6:36፤ መዝሙር 130:3፤ መክብብ 7:20፤ ያዕቆብ 3:8) ትምህርቶቹን በሦስተኛውም በአራተኛውም ሳምንት በሥራ ላይ ማዋልህን ቀጥል።
21 በአንድ ወር ወይም ከዚያ ብዙም በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ሠላሳ አንዱንም ነጥቦች ሸፍነህ ትጨርስ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ በመጨረሻ ምን ይሰማሃል? ውጥረትህ ቀለል እንደሚልልህና ይበልጥ ደስተኛ ልትሆን እንደምትችል አይሰማህም? ያደረግኸው መሻሻል አነስተኛ ቢሆንም እንኳ ያለብህ ውጥረት እንደሚቀንስ የታወቀ ነው፤ ሌላው ቢቀር ያለብህን ውጥረት በተሻለ መንገድ መቋቋም ትችላለህ። በዚሁ መቀጠል የሚያስችል ዘዴም ታገኛለህ። በዚህ ዝርዝር ውስጥ ያልተካተቱ ግሩም የሆኑ ሌሎች የኢየሱስ ትምህርቶች እንዳሉ አትዘንጋ። አንዳንዶቹን በመመርመር ለምን በሥራ ላይ ለማዋል አትሞክርም?—ፊልጵስዩስ 3:16
22. የኢየሱስን ትምህርቶች መከተል ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል? ይሁን እንጂ ልንመረምረው የሚገባን ሌላ ምን ተጨማሪ ገጽታ አለ?
22 የኢየሱስ ቀንበር ምንም ክብደት የሌለው ነው ባይባልም እንኳ ልዝብ እንደሆነ ልትመለከት ትችላለህ። ትምህርቱም ሆነ የእርሱ ደቀ መዝሙር መሆን ለመሸከም የሚከብድ አይደለም። የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅ የነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ 60 ለሚያክሉ ዓመታት በራሱ ሕይወት ላይ ከተመለከተው ተሞክሮ በመነሳት “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም” በማለት ይህን ሐቅ መስክሯል። (1 ዮሐንስ 5:3) አንተም ተመሳሳይ የሆነ ትምክህት ሊያድርብህ ይችላል። የኢየሱስን ትምህርቶች ይበልጥ በሥራ ላይ እያዋልክ በሄድክ መጠን በአሁን ጊዜ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ሕይወታቸው በውጥረት እንዲሞላ ያደረጉት ነገሮች በአንተ ላይ ያን ያህል ጭንቀት የሚፈጥሩ እንደማይሆኑ የበለጠ ግልጽ እየሆነልህ ይሄዳል። ከፍተኛ እፎይታ እንዳመጣልህም መገንዘብ ትችላለህ። (መዝሙር 34:8) ሆኖም የኢየሱስን ልዝብ ቀንበር በሚመለከት ልትመረምረው የሚገባ ሌላ ገጽታም አለ። ኢየሱስ ‘የዋህና በልቡም ትሑት እንደሆነ’ ተናግሯል። ይህ የኢየሱስን ትምህርት ከመማራችንና የእርሱን ምሳሌ ከመከተላችን ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ይህን እንመረምራለን።—ማቴዎስ 11:29
-
-
‘ከእኔ ተማሩ’መጠበቂያ ግንብ—2001 | ታኅሣሥ 15
-
-
‘ከእኔ ተማሩ’
“ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ።”—ማቴዎስ 11:29
1. ከኢየሱስ መማር አስደሳች የሚሆንልንና ሕይወታችንን ይበልጥ ትርጉም ያለው የሚያደርገው ለምንድን ነው?
ኢየሱስ ክርስቶስ አሳቡ፣ ትምህርቱና ድርጊቱ በጠቅላላ ሁልጊዜ ቀና ነበር። በምድር ላይ የቆየባቸው ጊዜያት አጭር ቢሆኑም እንኳ አርኪ የሆነ ሥራ ከማከናወኑም በላይ ምንጊዜም ደስተኛ ነበር። ደቀ መዛሙርትን ሰብስቦ አምላክን እንዴት ማምለክ እንደሚችሉ፣ የሰውን ዘር እንዴት እንደሚወድዱና ዓለምን እንዴት ማሸነፍ እንደሚችሉ አስተምሯቸዋል። (ዮሐንስ 16:33) ልባቸው በተስፋ እንዲሞላ ከማድረጉም በላይ “በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቶአል።” (2 ጢሞቴዎስ 1:10) አንተም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ከሆንክ ደቀ መዝሙርነት ለአንተ ምን ትርጉም አለው? ኢየሱስ ስለ ደቀ መዝሙርነት የተናገራቸውን ቃላት በመመርመር ሕይወታችንን ይበልጥ ትርጉም ያለው ማድረግ ስለምንችልበት መንገድ ልንማር እንችላለን። ይህም የእርሱ ዓይነት አመለካከት ማዳበርንና አንዳንድ ዋና ዋና መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ ማዋልን ይጨምራል።—ማቴዎስ 10:24, 25፤ ሉቃስ 14:26, 27፤ ዮሐንስ 8:31, 32፤ 13:35፤ 15:8
2, 3. (ሀ) የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ማለት ምን ማለት ነው? (ለ) ‘እኔ የማን ደቀ መዝሙር ነኝ’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
2 በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ደቀ መዝሙር” ተብሎ የተተረጎመው ቃል አንድን ነገር በትኩረት የሚከታተል ወይም የሚማር የሚል መሠረታዊ ትርጉም አለው። የጭብጡ ጥቅሳችን በሆነው በማቴዎስ 11:29 ላይ ከዚህ ጋር የሚዛመድ አንድ ቃል አለ። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) አዎን፣ ደቀ መዝሙር ተማሪ ነው። ብዙውን ጊዜ ወንጌሎች “ደቀ መዝሙር” የሚለውን ቃል ከኢየሱስ ጋር ይሰብኩና የእርሱን መመሪያ ይከተሉ የነበሩትን የኢየሱስን የቅርብ ተከታዮች ለማመልከት ይጠቀሙበታል። የኢየሱስን ትምህርቶች በምሥጢር የተቀበሉ ሰዎችም ነበሩ። (ሉቃስ 6:17፤ ዮሐንስ 19:38) የወንጌል ጸሐፊዎችም “የዮሐንስ [መጥምቁ] እና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት” በማለት ዘግበዋል። (ማርቆስ 2:18) ኢየሱስ ተከታዮቹን “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት” እንዲጠበቁ አስጠንቅቋቸው ስለነበረ ‘እኔ የማን ደቀ መዝሙር ነኝ?’ ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን።—ማቴዎስ 16:12
3 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ማለትም ከእርሱ የተማርን ከሆንን ሌሎች ከእኛ ጋር በሚሆኑበት ጊዜ መንፈሳዊ እረፍት ያገኛሉ። የዋሆችና በልባችን ትሑታን እንደሆንን መመልከት መቻል ይኖርባቸዋል። በሥራ ቦታ አስተዳደራዊ ኃላፊነት ካለን፣ ወላጅ ከሆንን ወይም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የእረኝነት ኃላፊነት የተጣለብን ከሆንን በሥራችን ያሉ ሰዎች ኢየሱስ በእርሱ ሥር የነበሩትን ሰዎች በያዘበት መንገድ እንደምንይዛቸው ይሰማቸዋል?
ኢየሱስ ሰዎችን ይይዝ የነበረበት መንገድ
4, 5. (ሀ) ኢየሱስ ችግር የነበረባቸውን ሰዎች እንዴት ይይዝ እንደነበረ ማወቁ አስቸጋሪ የማይሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ በአንድ ፈሪሳዊ ቤት ተጋብዞ ሳለ ምን አጋጠመው?
4 ኢየሱስ ሰዎችን በተለይ ደግሞ ሥር የሰደደ ችግር የነበረባቸውን ሰዎች እንዴት ይይዝ እንደነበረ ማወቅ ይኖርብናል። ይህን መማር አስቸጋሪ ሊሆንብን አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ መከራ የደረሰባቸውን አንዳንድ ሰዎች ጨምሮ ኢየሱስ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ስለነበረው ግንኙነት የሚገልጹ በርካታ ዘገባዎችን ይዟል። ከዚያም የሃይማኖት መሪዎች በተለይ ደግሞ ፈሪሳውያን ተመሳሳይ ችግር ለገጠማቸው ሰዎች ያንጸባርቁ የነበረውን አመለካከት እናያለን። ሁለቱን ማነጻጸሩ እውቀታችንን የሚጨምርልን ሆኖ እናገኘዋለን።
5 በ31 እዘአ ኢየሱስ በገሊላ ምድር እየተዘዋወረ ይሰብክ በነበረበት ጊዜ “ከፈሪሳውያንም አንድ ከእርሱ ጋር ይበላ ዘንድ [ኢየሱስን] ለመነው።” ኢየሱስም ግብዣውን ሳያመነታ ተቀበለ። “በፈሪሳዊው ቤትም ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ። እነሆም በዚያች ከተማ ኃጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት፤ በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደ ተቀመጠ ባወቀች ጊዜ፣ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ አመጣች። በስተ ኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፣ በራስ ጠጒርዋም ታብሰው እግሩንም ትስመው ሽቱም ትቀባው ነበረች።”—ሉቃስ 7:36-38
6. አንዲት “ኃጢአተኛ” ሴት በአንድ ፈሪሳዊ ቤት የተገኘችው ለምን ሊሆን ይችላል?
6 ይህን ትዕይንት በዓይነ ሕሊናህ መመልከት ትችላለህ? አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ በማለት ሁኔታውን ገልጿል:- “ችግረኞች ጥቂት ፍርፋሪ ለማግኘት ግብዣ ወዳለበት ቦታ ይሄዱ ስለነበር ይህችም ሴት (ቁ.37) የአካባቢውን ልማድ ተከትላ ወደዚያው ሄዳለች።” አንድ ሰው ሳይጋበዝ እንዲህ ባለ ግብዣ ላይ ሊገኝ የሚችለው በዚህ ምክንያት መሆን አለበት። ግብዣው ካለቀ በኋላ የተራረፉ ምግቦችን ለማግኘት የተኮለኮሉ ሌሎች ሰዎችም ሳይኖሩ አይቀርም። ሆኖም ይህች ሴት ያሳየችው ጠባይ ፈጽሞ የተለየ ነበር። ግብዣው እስኪያልቅ ድረስ ጥግ ተቀምጣ አልጠበቀችም። “ኃጢአተኛ” የሚል መጥፎ ስም አትርፋ የነበረ ሲሆን ኢየሱስም ‘ብዙ ኃጢአት’ ያለባት መሆኗን እንደሚያውቅ ተናግሯል።—ሉቃስ 7:47
7, 8. (ሀ) በሉቃስ 7:36-38 ላይ ሰፍሮ እንደሚገኘው ዓይነት ሁኔታ ቢገጥመን ምን ምላሽ ልንሰጥ እንችላለን? (ለ) ስምዖን ምን ተሰማው?
7 በዚያን ዘመን ትኖር እንደነበርና ራስህን በኢየሱስ ቦታ እንዳለህ አድርገህ አስብ። ምን ታደርግ ነበር? ይህች ሴት ወደ አንተ ስትቀርብ ስትመለከት ትሸማቀቅ ነበር? እንዲህ ያለው ሁኔታ ምን ዓይነት ስሜት ያሳድርብህ ይሆን? (ሉቃስ 7:45) ትጸየፋት ነበር?
8 ከሌሎቹ እንግዶች አንዱ ብትሆን ኖሮ አንተም በተወሰነ መጠን ፈሪሳዊው ስምዖን የነበረው ዓይነት አመለካከት ይኖርህ ነበር? “[ኢየሱስን] የጠራው ፈሪሳዊም አይቶ:- ይህስ ነቢይ ቢሆን፣ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፣ ኃጢአተኛ ናትና ብሎ በልቡ አሰበ።” (ሉቃስ 7:39) በተቃራኒው ግን ኢየሱስ ከአንጀቱ የሚራራ ሰው ነበር። ሴትዮዋ ያለችበትን ሁኔታና ጭንቀት ተረድቷል። በኃጢአተኝነት ኑሮ ውስጥ እንዴት ልትገባ እንደቻለች አናውቅም። በእርግጥ ዝሙት አዳሪ ከነበረች በከተማው የሚኖሩ ቀናተኛ አይሁዳውያን ያደረጉላት እርዳታ አልነበረም ለማለት ይቻላል።
9. ኢየሱስ ምን ብሎ መለሰ? ምንስ ውጤት ተገኝቶ ሊሆን ይችላል?
9 ሆኖም ኢየሱስ ሊረዳት ፈለገ። “ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል” አላት። ከዚያም “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ” በማለት ጨምሮ ተናገረ። (ሉቃስ 7:48-50) ዘገባው እዚህ ላይ ያበቃል። አንድ ሰው ኢየሱስ ብዙም ያደረገላት ነገር የለም ብሎ ያስብ ይሆናል። በመሠረቱ ኢየሱስ ያሰናበታት ባርኮ ነው። ይህች ሴት ወደ ቀድሞ አሳዛኝ አኗኗሯ ተመልሳለች ብለህ ታስባለህ? በእርግጠኝነት መናገር ባንችልም ሉቃስ ቀጥሎ የተናገረውን ልብ በል። ኢየሱስ “እየሰበከና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች እየተናገረ በየከተማይቱ በየመንደሩም ያልፍ” እንደነበር የተናገረ ሲሆን ‘በገንዘባቸው የሚያገለግሉ’ ‘ብዙ ሌሎች ሴቶች’ ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደነበሩም ዘግቧል። ንስሐ የገባችውና አመስጋኝ የነበረችው ይህች ሴት በንጹሕ ሕሊና፣ በአዲስ ዓላማና ለአምላክ የበለጠ ጥልቅ ፍቅር በማዳበር እርሱን በሚያስከብር አኗኗር ከእነዚህ ሴቶች ጎን ተሰልፋ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው።—ሉቃስ 8:1-3
በኢየሱስና በፈሪሳውያን መካከል የነበረው ልዩነት
10. ስለ ኢየሱስና በስምዖን ቤት ስለነበረችው ሴት የሚናገረውን ዘገባ መመርመሩ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
10 ከዚህ ሕያው ዘገባ ምን ልንማር እንችላለን? ይህ ታሪክ ስሜታችንን በጥልቅ እንደሚነካው የተረጋገጠ ነው፣ አይደለም እንዴ? በስምዖን ቤት እንዳለህ አድርገህ አስብ። ምን ዓይነት ስሜት ያድርብህ ነበር? እንደ ኢየሱስ ታደርግ ነበር ወይስ ትንሽም ቢሆን እንደጋባዡ ፈሪሳዊ ይሰማህ ነበር? ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደ መሆኑ መጠን ልክ እንደ እርሱ ማሰብና ማድረግ እንደማንችል የታወቀ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የፈሪሳዊው ስምዖን ዓይነት ስሜት ማንጸባረቅ እንደማንፈልግ ግልጽ ነው። እንደ ፈሪሳውያን መሆን የሚያስደስታቸው ጥቂት ሰዎች ይኖሩ ይሆናል።
11. ከፈሪሳውያን ወገን መመደብ የማንፈልገው ለምንድን ነው?
11 መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠው መግለጫና ከምሁራን አስተያየት በመነሣት ፈሪሳውያን ለማኅበረሰቡ ብልጽግናና ብሔራዊ ደህንነት ካለ እነርሱ ተቆርቋሪ እንደሌለ አድርገው ያስቡ እንደነበር ማወቅ እንችላለን። የአምላክ ቃል ግልጽና ለመረዳት የማያስቸግር መሆኑ ደስ አያሰኛቸውም ነበር። ሕጉ በግልጽ በማይናገርበት ጊዜ ጉዳዩን ለሕሊና ከመተው ይልቅ ሕጉን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል የሚያብራሩ ተጨማሪ ሐሳቦችን ያካትቱ ነበር። እነዚህ ሃይማኖታዊ መሪዎች ጥቃቅን በሆኑ ጉዳዮች እንኳን ሳይቀር ለሁሉም ዓይነት የኑሮ ዘርፍ መመሪያ የሚሆኑ ደንቦችን ያወጡ ነበር።a
12. ፈሪሳውያን ስለ ራሳቸው ምን ዓይነት አመለካከት ነበራቸው?
12 የመጀመሪያው መቶ ዘመን ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ ፈሪሳውያን ራሳቸውን ደጎች፣ ጨዋዎች፣ የማያዳሉና የተሰጣቸውን ሥራ በብቃት የሚወጡ እንደሆኑ አድርገው ይመለከቱ እንደነበር ገልጿል። አንዳንዶቹ እነዚህ ባሕርያት እንደነበሯቸው አይካድም። ምናልባት ኒቆዲሞስ ወደ አእምሮህ ይመጣ ይሆናል። (ዮሐንስ 3:1, 2፤ 7:50, 51) ከጊዜ በኋላ አንዳንዶቹ የክርስትናን መንገድ ተቀብለዋል። (ሥራ 15:5) ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ ፈሪሳውያንን ስለመሳሰሉ አንዳንድ የአይሁድ ሰዎች ሲጽፍ “በእውቀት አይቅኑ እንጂ ለእግዚአብሔር እንዲቀኑ እመሰክርላቸዋለሁና” ብሏል። (ሮሜ 10:2) ይሁን እንጂ ተራው ሕዝብ የሚመለከታቸው ኩራተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተመጻዳቂዎች፣ ስህተት ለቃቃሚዎች፣ ኮናኞችና ሌሎችን የሚንቁ እንደሆኑ አድርጎ እንደነበር የወንጌል ዘገባዎች ይገልጻሉ።
ኢየሱስ የነበረው አመለካከት
13. ኢየሱስ ስለ ፈሪሳውያን ምን ብሎ ለመናገር ተገድዷል?
13 ኢየሱስ ጻፎችና ፈሪሳውያን ግብዞች እንደሆኑ በመግለጽ ክፉኛ ነቅፏቸዋል። “ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፣ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም።” አዎን፣ ሸክሙ ከባድ ነበር፤ በሕዝቡ ላይ የተጫነው ቀንበርም የሚያሠቃይ ነበር። ኢየሱስ ጻፎችንና ፈሪሳውያንን “ደንቆሮዎች [“ሰነፎች፣” NW ]” በማለት ጠርቷቸዋል። ሰነፍ ሰው የኅብረተሰብ ጠንቅ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ ጻፎችንና ፈሪሳውያንን “ዕውሮች መሪዎች” በማለት የጠራቸው ሲሆን ‘ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፣ በሕግ ያለውን ዋና ነገር የምትተዉ’ በማለት አስረግጦ ተናግሯል። ኢየሱስ እንደ ፈሪሳውያን አድርጎ እንዲመለከተው የሚፈልግ ማን አለ?—ማቴዎስ 23:1-4, 16, 17, 23
14, 15. (ሀ) ኢየሱስ ከማቴዎስ ሌዊ ጋር ካደረገው ውይይት ስለ ፈሪሳውያን ምን ነገር ያስገነዝበናል? (ለ) ከዚህ ዘገባ ምን ጠቃሚ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?
14 የወንጌል ዘገባዎችን የሚያነብ ማንኛውም ሰው ለማለት ይቻላል ብዙዎቹ ፈሪሳውያን የነበረባቸውን ጉልህ ችግር ማየት ይችላል። ኢየሱስ ቀረጥ ሰብሳቢ የነበረውን ማቴዎስ ሌዊን ደቀ መዝሙሩ እንዲሆን ከጋበዘው በኋላ ሌዊ ትልቅ ግብዣ አደረገለት። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “ፈሪሳውያንና ጻፎቻቸውም በደቀ መዛሙርቱ ላይ:- ስለ ምን ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ትበላላችሁ ትጠጡማላችሁ? ብለው አንጐራጐሩ። ኢየሱስም መልሶ:- . . . ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም አላቸው።”—ሉቃስ 5:27-32
15 በዚያን ወቅት ሌዊ ከኢየሱስ አነጋገር የተገነዘበው ሌላም ነገር ነበር። ኢየሱስ “ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደ ሆነ ተማሩ” በማለት ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 9:13) ፈሪሳውያን ዕብራውያን ነቢያት የጻፏቸውን ጽሑፎች እንደሚያምኑባቸው ቢናገሩም በሆሴዕ 6:6 ላይ የተነገረውን ይህን ቃል ግን አይቀበሉም ነበር። ያወጡትን ወግ እስካልተላለፉ ድረስ ምንም ዓይነት ስህተት እንደፈጸሙ ሆኖ አይሰማቸውም ነበር። ስለዚህ እያንዳንዳችን ራሳችንን እንዲህ እያልን ልንጠይቅ እንችላለን:- ‘ሌሎች የሚመለከቱኝ የግል አመለካከትን በሚጠይቁ ወይም ማንኛውም ሰው ሊገምት በሚችላቸው ጉዳዮች ረገድ የሚወጡ ደንቦችን በተመለከተ ድርቅ ያለ አቋም እንዳለኝ አድርገው ነው? ወይስ ይበልጥ ጎልቶ የሚታያቸው መሐሪና ደግ መሆኔ ነው?’
16. የፈሪሳውያን መንገድ ምን ነበር? እንደ እነርሱ ከመሆን መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?
16 ፈሪሳውያን ስህተት መለቃቀም ይወድዱ ነበር። ተፈጽሟል ብለው የሚያስቡትም ይሁን በእውነት የተፈጸመ ምንም የሚያልፉት ስህተት አልነበረም። ፈሪሳውያን ሰዎች ተሸማቅቀውና ዘወትር ድክመቶቻቸውን እያሰቡ እንዲኖሩ አድርገዋል። ፈሪሳውያን እንደ አዝሙድ፣ እንስላልና ከሙን ያሉ ትናንሽ ተክሎችን አሥራት አድርገው ማውጣታቸው በጣም ያኩራራቸው ነበር። በአለባበሳቸው ሃይማኖተኛ መስለው ለመታየት ይሞክሩ የነበረ ሲሆን ሕዝቡንም ለመምራት ይፈልጉ ነበር። በእርግጥም ድርጊታችን ኢየሱስ ከተወልን ምሳሌ ጋር የሚስማማ እንዲሆን ከፈለግን በሰዎች ላይ ስህተት ከመለቃቀምና የሌሎችን እንከን ከማጋነን መታቀብ ይገባናል።
ኢየሱስ ችግሮችን ይፈታ የነበረው እንዴት ነው?
17-19. (ሀ) ኢየሱስ ከባድ ችግር ሊፈጥር ይችል ለነበረ አንድ ሁኔታ እንዴት መፍትሔ እንዳስገኘ ግለጽ። (ለ) ሁኔታውን የሚያስጨንቅና የማያስደስት ያደረገው ምንድን ነው? (ሐ) ሴትዮዋ ወደ ኢየሱስ ስትቀርብ አንተ እዚያ ኖረህ ቢሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?
17 ኢየሱስ ችግሮችን ይፈታ የነበረበት መንገድ ከፈሪሳውያን ፈጽሞ የተለየ ነበር። ኢየሱስ ከባድ ችግር ሊፈጥር ይችል የነበረን አንድ ሁኔታ እንዴት እንደያዘ ተመልከት። ጉዳዩ ለ12 ዓመታት ደም ይፈሳት የነበረችን አንዲት ሴት የሚመለከት ነው። ታሪኩን በሉቃስ 8:42-48 ላይ ማንበብ ትችላለህ።
18 የማርቆስ ዘገባ ሴትዮዋ ‘በፍርሃት ትንቀጠቀጥ’ እንደነበር ይገልጻል። (ማርቆስ 5:33) ለምን? ምክንያቱም የአምላክን ሕግ እንደጣሰች ታውቅ ስለነበር ነው። በዘሌዋውያን 15:25-28 መሠረት ከተፈጥሮ ውጭ ደም የሚፈስሳት አንዲት ሴት ደሙ መፍሰሱን እስኪያቆም ብሎም ከዚያ በኋላ አንድ ሳምንት እስኪያልፍ ድረስ ርኩስ ትሆናለች። የነካችው ማንኛውም ዕቃ ሆነ ሰው ርኩስ ይሆናል። ይህች ሴት ወደ ኢየሱስ ለመቅረብ በሕዝቡ መካከል ተሹለክሉካ ማለፍ ነበረባት። ከ2, 000 ዓመት በፊት የተጻፈውን ይህ ታሪክ ስናነብ ሴትዮዋ የነበረችበትን ሁኔታ በማሰብ ከልብ እንደምናዝን የታወቀ ነው።
19 በዚያን ዕለት ኖረህ ቢሆን ኖሮ ሁኔታውን እንዴት ትመለከተው ነበር? ምንስ ትናገር ነበር? ኢየሱስ ችግር እንደፈጠረች አድርጎ ከመናገር ይልቅ ሴትዮዋን በደግነት፣ በፍቅርና በአሳቢነት እንደያዛት ልብ በል።—ማርቆስ 5:34
20. ዘሌዋውያን 15:25-28 በጊዜያችን የሚሠራ ሕግ ቢሆን ኖሮ ምን ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ ከፊታችን ይጋረጥብን ነበር?
20 ከዚህ ክስተት ልንማር የምንችለው ነገር ይኖር ይሆን? በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆነህ የምታገለግል ነህ እንበል። እንዲሁም በዘሌዋውያን 15:25-28 ላይ የሚገኘው ሕግ በክርስቲያኖች ላይ እንደሚሠራና አንዲት ክርስቲያን ሴት ይህን ሕግ በመተላለፏ ምክንያት ከፍተኛ ጭንቀትና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት እንዳደረባት አድርገህ አስብ። ምን ታደርግ ነበር? በሕዝብ ፊት በመገሠጽ ታዋርዳት ነበር? “ኧረ በጭራሽ፣ እንዴት እንዲህ አደርጋለሁ! የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ደግ፣ አፍቃሪ፣ አስተዋይና አሳቢ ለመሆን የተቻለኝን ሁሉ እጥራለሁ” ብለህ ታስብ ይሆናል። በጣም ጥሩ ነው! ችግሩ ግን የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ተግባራዊ ማድረጉ ላይ ነው።
21. ሕጉን በሚመለከት ኢየሱስ ለሰዎች ያስተማረው ምንድን ነው?
21 ሰዎች ከኢየሱስ መነቃቃትን፣ መበረታታትንና እፎይታን አግኝተዋል። የአምላክ ሕግ የሚለው ነገር ቁርጥ ያለ ትእዛዝ በሚሆንበት ጊዜ ሕጉ የሚለውን መፈጸም ይገባ ነበር። ብዙ ነገሮችን የሚያካትት በሚሆንበት ጊዜ ግን በሕሊናቸው ተጠቅመው ውሳኔ በማድረግ ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር ማሳየት ይችሉ ነበር። ሕጉ እንደ አስፈላጊነቱ የሚለዋወጥ እንጂ መፈናፈኛ የሚያሳጣ አልነበረም። (ማርቆስ 2:27, 28) አምላክ ሕዝቡን ይወድዳል፣ ሁልጊዜ የሚጠቅማቸውን ያደርግላቸዋል፣ በሚሳሳቱበት ጊዜም ይምራቸዋል። ኢየሱስም እንደዚህ ነበር።—ዮሐንስ 14:9
-