-
ወደር የማይገኝለት አባትመጠበቂያ ግንብ—2008 | ጥር 1
-
-
በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጥቅምት ወር አካባቢ ኢየሱስ ለመጠመቅ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሄደ። መጽሐፍ ቅዱስ ሁኔታውን አስመልክቶ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “ኢየሱስም እንደ ተጠመቀ ከውሃው ወጣ፤ ወዲያውኑም ሰማይ ተከፍቶ የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድበት አየ። እነሆ፣ ‘በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው’ የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰማ።”a (ማቴዎስ 3:16, 17) ይሖዋ ራሱ የተናገራቸው እነዚህ አሳቢነት የተንጸባረቀባቸው ቃላት እሱ ምን ዓይነት አባት እንደሆነ ብዙ የሚነግሩን ነገር አለ። ይሖዋ ለልጁ የተናገራቸውን ሦስት ነገሮች ልብ በል።
በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይሖዋ “ልጄ ይህ ነው” ሲል ‘የአንተ አባት በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል’ በማለት የተናገረ ያህል ነበር። ልጆች በራሳቸው ማንነት መታወቅ እንዲሁም የሌሎችን ትኩረት ማግኘት ይፈልጋሉ፤ አሳቢ የሆነ አባት ደግሞ ይህን ፍላጎታቸውን ያሟላላቸዋል። ልጆች ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው የቤተሰቡ አባላት ተደርገው እንደሚቆጠሩ ማረጋገጫ ሊሰጣቸው ያስፈልጋል። ኢየሱስ ጎልማሳ ሆኖም እንኳ ከአባቱ ይህን የመሰለ እውቅና በማግኘቱ ምን ሊሰማው እንደሚችል ገምት!
በሁለተኛ ደረጃ፣ ይሖዋ “የምወደው” ብሎ ስለ ልጁ በመናገር ለኢየሱስ ያለውን ፍቅር በይፋ ገልጿል። ይሖዋ ይህንን ሲል ‘እወድሃለሁ’ ማለቱ ነበር። ጥሩ የሆነ አባት ልጆቹን በጣም እንደሚወዳቸው ይነግራቸዋል። እንደዚህ ያሉ ቃላት የፍቅር መግለጫ በሆኑ ድርጊቶች ሲደገፉ ልጆች በጥሩ ሁኔታ እንዲያድጉ ይረዷቸዋል። ኢየሱስ፣ አባቱ እንደሚወደው ሲናገር ሲሰማ ምን ያህል ልቡ ተነክቶ ይሆን?
በሦስተኛ ደረጃ፣ ይሖዋ “በእርሱ ደስ የሚለኝ” በማለት ለልጁ ያለውን አድናቆት ገልጿል። ይሖዋ ይህንን ሲል ‘ልጄ፣ ባደረግከው ነገር ተደስቻለሁ’ በማለት የተናገረ ያህል ነበር። አፍቃሪ የሆነ አባት ልጆቹ በሚናገሩት ወይም በሚያደርጉት መልካም ነገር መደሰቱን እንዲያውቁ ለማድረግ አጋጣሚዎችን ይፈልጋል። ልጆች፣ ወላጆቻቸው እንደሚያደንቋቸው መስማታቸው ብርታት የሚጨምርላቸው ከመሆኑም በላይ ደፋሮች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ኢየሱስ አባቱ ለእሱ ያለውን አድናቆት መስማቱ አበረታቶት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም!
-