-
“ተከታዬ ሁን”—ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር?“ተከታዬ ሁን”
-
-
ምዕራፍ አንድ
“ተከታዬ ሁን”—ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር?
“የዘላለም ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?”
1, 2. አንድ ሰው ሊቀርቡለት ከሚችሉት ግብዣዎች ሁሉ የላቀው የትኛው ነው? ራሳችንን ምን ብለን ልንጠይቅ እንችላለን?
እስከ ዛሬ ከቀረቡልህ ግብዣዎች ሁሉ እጅግ የተደሰትክበት የትኛው ነው? በአንድ ልዩ ዝግጅት ላይ ምናልባትም በጣም በምትወዳቸው ሁለት ሰዎች ሠርግ ላይ እንድትገኝ የተጋበዝክበትን ጊዜ ታስታውስ ይሆናል። ወይም ደግሞ ትልቅ ትርጉም ያለው ሥራ እንድትሠራ የተጠየቅክበት ቀን ትዝ ይልህ ይሆናል። እንዲህ ያሉ ግብዣዎች ቀርበውልህ ከነበረ ይህን አጋጣሚ በማግኘትህ በጣም እንደተደሰትክ አልፎ ተርፎም ክብር እንደተሰማህ ጥርጥር የለውም። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ከእነዚህ ሁሉ የላቀ አንድ ግብዣ ቀርቦልሃል። ይህ ግብዣ የቀረበው ለእያንዳንዳችን ነው። ለዚህ ግብዣ የምንሰጠው ምላሽ በሕይወታችን ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። እንዲሁም በሕይወታችን ውስጥ ከምናደርጋቸው ውሳኔዎች ሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠው ነው።
2 ለመሆኑ ይህ ግብዣ ምንድን ነው? ይህን ግብዣ ያቀረበው የሁሉን ቻዩ አምላክ የይሖዋ አንድያ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ግብዣው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። በማርቆስ 10:21 ላይ ኢየሱስ “ተከታዬ ሁን” የሚል ግብዣ አቅርቧል። ኢየሱስ ይህን ግብዣ ያቀረበው ለሁላችንም ነው ማለት ይቻላል። በመሆኑም ‘ለዚህ ግብዣ ምን ምላሽ እሰጣለሁ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። ‘ይሄማ መልሱ ግልጽ ነው’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ደግሞስ እንዲህ ያለውን ታላቅ ግብዣ ማን አልቀበልም ሊል ይችላል? የሚያስገርመው ግን አብዛኞቹ ሰዎች ይህን ግብዣ ለመቀበል ፈቃደኞች አይደሉም። ለምን?
3, 4. (ሀ) ኢየሱስን ስለ ዘላለም ሕይወት የጠየቀው ግለሰብ ብዙዎች በጣም የሚጓጉላቸው ምን ነገሮች ነበሩት? (ለ) ኢየሱስ ሀብታም የሆነው ወጣት አለቃ ምን ጥሩ ባሕርያት እንዳሉት አስተውሎ ሊሆን ይችላል?
3 ከ2,000 ዓመት ገደማ በፊት ይህ ግብዣ በግለሰብ ደረጃ የቀረበለትን አንድ ሰው እንደ ምሳሌ እንመልከት። ይህ ግለሰብ በጣም የተከበረ ሰው ነበር። ሰዎች ከፍ አድርገው የሚመለከቷቸው አልፎ ተርፎም በጣም የሚጓጉላቸው ቢያንስ ሦስት ነገሮች ማለትም ወጣትነት፣ ሀብትና ሥልጣን ነበሩት። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው ዘገባ ይህ ሰው ‘ወጣት፣’ “ሀብታም” እና ‘ከአይሁዳውያን አለቆች አንዱ’ እንደነበር ይገልጻል። (ማቴዎስ 19:20፤ ሉቃስ 18:18, 23) ይሁን እንጂ ይህ ወጣት ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ አንድ ሌላም ነገር ነበረው። ታላቅ አስተማሪ የሆነው ኢየሱስ የሚናገረውን ያዳመጠ ሲሆን በሰማውም ነገር ተደስቶ ነበር።
4 በዘመኑ የነበሩት አብዛኞቹ አለቆች ለኢየሱስ የሚገባውን አክብሮት አላሳዩትም። (ዮሐንስ 7:48፤ 12:42) ይሁንና ይህ አለቃ ከዚህ የተለየ ነገር አድርጓል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “[ኢየሱስ] ከዚያ ወጥቶ በመሄድ ላይ ሳለ አንድ ሰው እየሮጠ መጣ፤ በፊቱም በጉልበቱ ተንበርክኮ ‘ጥሩ መምህር ሆይ፣ የዘላለም ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?’ ሲል ጠየቀው።” (ማርቆስ 10:17) ይህ ሰው ከኢየሱስ ጋር ለመነጋገር ምን ያህል ጓጉቶ እንደነበር ልብ በል፤ ድሆችና ችግረኞች ያደርጉት እንደነበረው ሁሉ እሱም በአደባባይ ወደ ኢየሱስ እየሮጠ ሄዷል። በተጨማሪም አክብሮቱን ለመግለጽ በክርስቶስ ፊት ተንበርክኳል። በመሆኑም ይህ ሰው በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ትሑትና መንፈሳዊ ፍላጎቱን የሚያውቅ ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ላሉት ባሕርያት ከፍ ያለ ግምት ይሰጣል። (ማቴዎስ 5:3፤ 18:4) ከዚህ አንጻር “ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው” መባሉ ምንም አያስገርምም። (ማርቆስ 10:21) ኢየሱስ ወጣቱ ላቀረበው ጥያቄ መልስ የሰጠው እንዴት ነበር?
ወደር የማይገኝለት ግብዣ
5. ኢየሱስ ሀብታም ለሆነው ወጣት ምን ምላሽ ሰጠው? ይህ ሰው “አንድ ነገር” ጎድሎታል ሲል ድሃ መሆን አለበት ማለቱ ነበር? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
5 ኢየሱስ እንደገለጸው የዘላለም ሕይወት ማግኘት ስለሚቻልበት መንገድ ለሚነሳው ወሳኝ ጥያቄ፣ አባቱ ቀደም ብሎም ቢሆን አጥጋቢ መረጃ ሰጥቷል። ኢየሱስ ቅዱሳን መጻሕፍትን የጠቀሰ ሲሆን ወጣቱም የሙሴን ሕግ በሚገባ እንደሚጠብቅ አስረግጦ ተናግሯል። ሆኖም ኢየሱስ ልዩ የማስተዋል ችሎታ ስላለው በሰውየው ልብ ውስጥ ያለውን ነገር መገንዘብ ችሏል። (ዮሐንስ 2:25) ይህ አለቃ፣ አንድ ከባድ የሆነ መንፈሳዊ ችግር እንዳለበት ተረድቶ ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ “አንድ ነገር ይጎድልሃል” አለው። ይህ ሰው የጎደለው “አንድ ነገር” ምን ነበር? ኢየሱስ “ሂድና ያለህን ነገር ሁሉ ሸጠህ ገንዘቡን ለድሆች ስጥ” አለው። (ማርቆስ 10:21) ኢየሱስ እንዲህ ሲል ‘አንድ ሰው አምላክን ማገልገል ከፈለገ ቤሳ ቤስቲን የሌለው ድሃ መሆን አለበት’ ማለቱ ነበር? በፍጹም።a ክርስቶስ አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር ግልጽ እንዲሆን ማድረጉ ነበር።
6. ኢየሱስ ምን ግብዣ አቀረበ? ሀብታም የሆነው ወጣት አለቃ የሰጠው ምላሽ ስለ ልቡ ሁኔታ ምን ያሳያል?
6 ኢየሱስ ይህ ሰው የሚጎድለው ነገር ምን እንደሆነ ግልጽ እንዲሆንለት ሲል “መጥተህ ተከታዬ ሁን” በማለት ግሩም ግብዣ አቀረበለት። እስቲ አስበው፣ የልዑሉ አምላክ ልጅ ይህ ሰው እሱን እንዲከተለው ፊት ለፊት ግብዣ አቀረበለት! በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ሊገምተው ከሚችለው በላይ በረከት እንደሚያገኝ ቃል ገባለት። “በሰማይም ውድ ሀብት ታገኛለህ” አለው። ይህ ሀብታም አለቃ ይህን አጋጣሚ፣ ይህን ድንቅ ግብዣ ሳያቅማማ ተቀብሎ ይሆን? ዘገባው “ሰውየው ግን ይህን ሲሰማ አዘነ፤ ብዙ ንብረት ስለነበረውም እያዘነ ሄደ” ይላል። (ማርቆስ 10:21, 22) በመሆኑም ኢየሱስ ያቀረበው ያልተጠበቀ ሐሳብ በዚህ ሰው ልብ ውስጥ ያለው አንድ ችግር ይፋ እንዲወጣ አድርጓል። የሰውየው ሕይወት ከቁሳዊ ንብረቱ እንዲሁም ቁሳዊ ንብረቱ ከሚያስገኝለት ሥልጣንና ክብር ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነበር። የሚያሳዝነው ይህ ሰው ለእነዚህ ነገሮች ያለው ፍቅር ለክርስቶስ ካለው ፍቅር በለጠበት። ስለዚህ ሰውየው የጎደለው “አንድ ነገር” ለኢየሱስና ለይሖዋ ከልብ የመነጨና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ፍቅር ነው። ይህ ወጣት እንዲህ ዓይነት ፍቅር ስላልነበረው የቀረበለትን ወደር የሌለው ግብዣ ሳይቀበል ቀርቷል። ይሁንና ይህ ጉዳይ አንተንም የሚመለከተው እንዴት ነው?
7. ኢየሱስ ያቀረበው ግብዣ በዛሬው ጊዜ የምንገኘውን እኛንም እንደሚመለከት እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ ግብዣውን ያቀረበው ለዚህ ሰው ብቻ ወይም ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ አልነበረም። ኢየሱስ ‘ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ያለማቋረጥ ይከተለኝ’ ብሏል። (ሉቃስ 9:23) “ማንም” ሰው ከልቡ “የሚፈልግ” ከሆነ የክርስቶስ ተከታይ መሆን እንደሚችል ልብ በል። አምላክ እንዲህ ያሉትን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ ልጁ ይስባቸዋል። (ዮሐንስ 6:44) የኢየሱስ ግብዣ ለሀብታሞች፣ ለድሆች፣ የተወሰነ ዘር ወይም ብሔር ላላቸው ሰዎች አሊያም በዚያ ዘመን ይኖሩ ለነበሩ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለሰዎች ሁሉ የቀረበ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ “መጥተህ ተከታዬ ሁን” በማለት ያቀረበው ግብዣ አንተንም ይመለከታል። ክርስቶስን ለመከተል መምረጥህ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? ይህስ ምን ማድረግን ይጨምራል?
-
-
“ተከታዬ ሁን”—ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር?“ተከታዬ ሁን”
-
-
a ኢየሱስ የተከተሉትን ሰዎች ሁሉ፣ ያላቸውን ንብረት በሙሉ ለሌሎች እንዲሰጡ አልጠየቃቸውም። ለሀብታም ሰው ወደ አምላክ መንግሥት መግባት አስቸጋሪ እንደሚሆንበት ቢናገርም “በአምላክ ዘንድ ሁሉ ነገር ይቻላል” ብሏል። (ማርቆስ 10:23, 27) ደግሞም ባለጸጋ የሆኑ ጥቂት ሰዎች የክርስቶስ ተከታዮች ሆነዋል። እነዚህ ሰዎች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሀብትን በሚመለከት ቀጥተኛ ምክር የተሰጣቸው ቢሆንም ያላቸውን ሀብት ሁሉ ለድሆች እንዲሰጡ አልተጠየቁም።—1 ጢሞቴዎስ 6:17
-