የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 7/15 ገጽ 26-27
  • ያለ ነቀፋ በመመላለሳቸው ተክሰዋል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ያለ ነቀፋ በመመላለሳቸው ተክሰዋል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ያልተጠበቁ በረከቶች
  • የሚያስደስት ነገር
  • ዮሐንስ ተወለደ
  • በእጅጉ ተክሰዋል
  • ኤልሳቤጥ ልጅ ወለደች
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
  • መንገድ የሚያዘጋጅ ሰው ተወለደ
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
  • መንገድ ጠራጊው ተወለደ
    እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
  • የአንባብያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 7/15 ገጽ 26-27

ያለ ነቀፋ በመመላለሳቸው ተክሰዋል

ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ይባርካቸዋል፤ እንዲሁም ይክሳቸዋል። የአምላክ ዓላማዎች እንዴት ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ለማየት የተወሰነ ጊዜ መጠበቅ ይኖርባቸው ይሆናል። ሆኖም በረከቱ ሲገኝ የሚኖረው ደስታ ምንኛ ታላቅ ነው!

ወደ ሁለት ሺህ ከሚጠጉ ዓመታት በፊት የአሮን ዝርያ በሆኑት በአይሁዳዊው ካህን በዘካርያስና በሚስቱ በኤልሳቤጥ ላይ የደረሰው ነገር ለዚህ ግሩም ማስረጃ ነው። አምላክ እስራኤላውያን በታማኝነት ካገለገሉት ልጆችን በመስጠት እንደሚባርካቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር። ልጆች ስጦታ መሆናቸውን ተናግሯል። (ዘሌዋውያን 26:9፤ መዝሙር 127:3) ይሁን እንጂ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ልጅ አልነበራቸውም፤ ዕድሜያቸውም ገፍቶ ነበር።—ሉቃስ 1:1–7

ቅዱሳን ጽሑፎች ዘካርያስና ኤልሳቤጥ “ሁለቱም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ” በማለት ይናገራሉ። (ሉቃስ 1:6) አምላክን እጅግ ያፈቅሩት ስለነበረ የጽድቅን መንገድ መከተልና ትእዛዛቱን መጠበቅ ሸክም አልሆነባቸውም።—1 ዮሐንስ 5:3

ያልተጠበቁ በረከቶች

በ3 ከዘአበ ወደነበረው የጸደይ ወራት ማብቂያ ወይም የበጋ ወራት መጀመሪያ እስቲ መለስ እንበል። ታላቁ ሄሮድስ በይሁዳ ላይ ንጉሥ ሆኖ ይገዛ ነበር። አንድ ቀን ካህኑ ዘካርያስ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ ገባ። ሕዝቡ ከቤተ መቅደሱ ውጪ ተሰብስበው እየጸለዩ ሳለ ከወርቅ በተሠራው መሠዊያ ላይ ዕጣን ያጥን ነበር። በዕለት ውስጥ ከሚከናወኑት አገልግሎቶች ሁሉ ይኸኛው እጅግ ከፍተኛ ክብር ይሰጠው የነበረ ይመስላል። ይህ ይከናወን የነበረው መሥዋዕቱ ከቀረበ በኋላ ነበር። አንድ ካህን በሕይወት ዘመኑ ይህን መብት ሊያገኝ ይችል የነበረው አንድ ጊዜ ብቻ ነበር።

ዘካርያስ የሚያየውን ነገር ማመን አልቻለም። ለምንስ አይደነቅ፤ የይሖዋ መልአክ ዕጣን በሚታጠንበት መሥዋዕት በስተቀኝ በኩል ቆሟል። በዕድሜ የገፋው ካህን ተረበሸ፤ ፍርሃትም አደረበት። ሆኖም መልአኩ እንዲህ አለ፦ “ዘካርያስ ሆይ፣ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፣ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ።” አዎን፣ ይሖዋ የኤልሳቤጥንና የዘካርያስን ልባዊ ጸሎት ሰምቷል።—ሉቃስ 1:8–13

መልአኩ እንዲህ ሲል አክሎ ተናገረ፦ “ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፣ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፣ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል።” ዮሐንስ ዕድሜውን በሙሉ የአምላክ መንፈስ ቅዱስ የሞላበት ናዝራዊ ይሆናል ማለት ነበር። መልአኩ እንዲህ በማለት ቀጠለ፦ “ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል። እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ፣ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።”—ሉቃስ 1:14–17

ዘካርያስ “እኔ ሽማግሌ ነኝ ምስቴም በዕድሜዋ አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ?” ሲል ጠየቀው። መልአኩ እንዲህ በማለት መለሰለት፦ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፣ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፤ እነሆም፣ በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፣ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ድዳ ትሆናለህ መናገርም አትችልም።” ዘካርያስ ከቤተ መቅደሱ ሲወጣ መናገር አልቻለም። ሰዎቹ ተአምር እንዳየ ገባቸው። ሐሳቡን ለመግለጽ ማድረግ ይችል የነበረው በእጁ የተለያዩ ምልክቶችን ማሳየትና በሰውነት እንቅስቃሴዎች መጠቀም ነበር። ለሕዝብ ይሰጠው የነበረው አገልግሎት ሲያበቃ ወደ ቤቱ ተመለሰ።—ሉቃስ 1:18–23

የሚያስደስት ነገር

በተገባው ቃል መሠረት ኤልሳቤጥ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የምትደሰትበት ምክንያት ነበራት። ፀነሰችና መካንነት አስከትሎባት የነበረው ነቀፋ ተገፈፈላት። ዘመዷ ማርያምም እንደዚሁ ደስ አላት፤ ምክንያቱም ያው መልአክ ገብርኤል እንዲህ በማለት ነገራት፦ “እነሆም፣ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፣ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፣ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል።” ማርያም “የጌታ ባሪያ” የመሆንን ሚና ለመጫወት ፈቃደኛ ነበረች።—ሉቃስ 1:24–38

ማርያም ምንም ጊዜ ሳታጠፋ በተራራማው የይሁዳ አገር ወደሚገኘው የዘካርያስና የኤልሳቤጥ ቤት አቀናች። ማርያም ሰላምታ ስትሰጥ በኤልሳቤጥ ማኅፀን ውስጥ ያለው ሕፃን ዘለለ። በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ግፊት ኤልሳቤጥ እንዲህ ስትል ጮክ ብላ ተናገረች፦ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፣ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆ፣ የሰላምታሽ ድምፅ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት።” ማርያም የተሰማትን ከፍተኛ ደስታ ገለጸች። ከኤልሳቤጥ ጋር ለሦስት ወራት ያህል ቆየች።—ሉቃስ 1:39–56

ዮሐንስ ተወለደ

ጊዜው ሲደርስ በዕድሜ የገፉት ኤልሳቤጥና ዘካርያስ ወንድ ልጅ ተወለደላቸው። በስምንተኛው ቀን ሕፃኑ ተገረዘ። ዘመዶቻቸው ሕፃኑን ዘካርያስ ብለው ሊጠሩት ፈለጉ፤ ኤልሳቤጥ ግን “አይሆንም፣ ዮሐንስ ይባል እንጂ” አለች። በዚህም ወቅት ገና አፉ እንደተዘጋ ያለው ባልዋ በዚህ ይስማማ ይሆን? በብራና ላይ “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ። ወዲያውኑ ዘካርያስ አንደበቱ ተፈታ። ይሖዋን እየባረከ መናገር ጀመረ።—ሉቃስ 1:57–66

በደስታ የተፍለቀለቀው ካህን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ትንቢት ተናገረ። አሕዛብ ሁሉ ስለሚባረኩበት ዘር ከሚናገረው የአብርሃም ቃል ኪዳን ጋር በመስማማት ቃል የተገባለት አዳኝ ይኸውም “በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድ” እንደተነሣ አድርጎ ተናገረ። (ዘፍጥረት 22:15–18) ተአምራዊ በሆነ መንገድ የተወለደው የራሱ የዘካርያስ ልጅ የመሲሑ መንገድ ጠራጊ ሆኖ ‘በይሖዋ ፊት በመሄድ የመዳንን እውቀት ለሕዝብ ይሰጣል።’ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ዮሐንስ እያደገና በመንፈስ እየጠነከረ ሄደ።—ሉቃስ 1:67–80

በእጅጉ ተክሰዋል

ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ጥሩ የእምነትና የትዕግሥት ምሳሌዎች ናቸው። አምላክ የሚያደርገውን ነገር በትዕግሥት መጠበቅ የነበረባቸው ቢሆንም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። ያገኟቸው ታላላቅ በረከቶች የመጡላቸውም በዕድሜ በጣም በገፉባቸው ዓመታት ነው።

ሆኖም ኤልሳቤጥና ዘካርያስ አስደሳች በረከቶችን አግኝተዋል! በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት ሁለቱም ትንቢት ተናግረዋል። የመሲሑ መንገድ ጠራጊ የአጥማቂው ዮሐንስ ወላጆችና አስተማሪዎች የመሆን መብት አግኝተዋል። ከዚህም በላይ አምላክ እንደ ጻድቃን አድርጎ ተመልክቷቸዋል። ዛሬም እንደዚሁ አምላካዊ መንገድን የሚከተሉ በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም ሊያገኙ ይችላሉ። የይሖዋን ትእዛዛት በመጠበቅ ያለ ነቀፋ በመመላለሳቸውም ከፍተኛ ብድራት ያገኛሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ