የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 8/15 ገጽ 16-21
  • ‘ለአሕዛብ ሁሉ’ መመሥከር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘ለአሕዛብ ሁሉ’ መመሥከር
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የይሖዋ መንፈስና ምሥራቹ
  • ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ የሆኑ ሰዎች
  • ምሥራቹን ለማዳረስ የሚያስችሉ ስኬታማ መንገዶች
  • ክርስቲያናዊ ጠባይም ምሥክር ነው
  • የባርያው ክፍል ተስማሚ መሣሪያዎችን ያቀርባል
  • ሁላችንም ኃላፊነት አለብን
  • የይሖዋ ድርጅት በአገልግሎታችሁ ይደግፋችኋል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • የይሖዋ ምሥክሮች
    ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር
  • እውነትን እንዳገኘህ እርግጠኛ ነህ? ለምን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2014
  • ምሥራቹ አስቀድሞ መሰበክ አለበት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 8/15 ገጽ 16-21

‘ለአሕዛብ ሁሉ’ መመሥከር

“ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴዎስ 24:14

1. በማቴዎስ 24:14 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት ለተከታዮቹ ዱብ ዕዳ ሆነውባቸው መሆን ያለበት ለምንድን ነው?

ከላይ ያሉት የኢየሱስ ቃላት አይሁዳውያን ለሆኑት ደቀ መዛሙርቱ ምንኛ ዱብ ዕዳ ሆነውባቸው ይሆን! የተቀደሱት አይሁዶች “ርኩስ” የሆኑትን “አሕዛብ” ለማነጋገር ይሄዳሉ የሚለው ይህ ሐሳብ ለአንድ አይሁድ እንግዳና አልፎ ተርፎም በጣም ቀፋፊ ነበር።a ደንቡን በጥብቅ የሚከተል አንድ አይሁዳዊ ወደ አንድ ከአሕዛብ ወገን ወደሆነ ሰው ቤት ለመግባት እንኳ አይዳዳውም! እነዚህ አይሁዳውያን ደቀ መዛሙርት ስለ ኢየሱስ፣ ስለ ፍቅሩና ስለ ተልዕኮው ገና ብዙ የሚማሩት ነገር ነበር። ይሖዋ የማያዳላ ስለ መሆኑም ገና ብዙ የሚማሩት ነገር ነበር።—ሥራ 10:28, 34, 35, 45

2. (ሀ) የምሥክሮቹ አገልግሎት ምን ያህል ስፋት አለው? (ለ) ለምሥክሮቹ እድገት አስተዋጽኦ ያደረጉ ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ምንድን ናቸው?

2 የይሖዋ ምሥክሮች ዘመናዊቷን እስራኤል ጨምሮ በአሕዛብ መካከል የምሥራቹን ሲሰብኩ ቆይተዋል። በአሁኑ ጊዜም ከምን ጊዜውም በበለጠ በብዙ አገሮች ውስጥ ምሥራቹን በማወጅ ላይ ይገኛሉ። በ1994 ከአራት ሚልዮን ተኩል በላይ የሆኑ ምሥክሮች ወደ 230 በሚጠጉ አገሮች ውስጥ እየሰበኩ ነው። ፍላጎት ካሳዩ ሰዎች ጋር ከአራት ሚልዮን ተኩል በላይ የሆኑ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በመምራት ላይ ናቸው። ይህ እየተከናወነ ያለው ብዙውን ጊዜ ምሥክሮቹ ስለሚያስተምሩት ትምህርትና የሚያደርጓቸውን ነገሮች ከምን ዓላማ ተነሥተው እንደሚያደርጉ ካለማወቅ የመነጨ አግባብነት የሌለው ዓለም አቀፍ ጥላቻ እያለ ነው። ስለ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች የተባለው ነገር ስለ እነርሱም ሊባል ይችላል፦ “ስለዚህ ወገን በየስፍራው ሁሉ እንዲቃወሙ በእኛ ዘንድ ታውቆአልና።” (ሥራ 28:22) እንግዲያው በአገልግሎታቸው የተሳካ ውጤት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል ብለን የምንጠቅሰው ነገር ምንድን ነው? ለዕድገታቸው አስተዋጽኦ ያበረከቱ ቢያንስ ቢያንስ ሦስት ነገሮች አሉ። እነርሱም የይሖዋ መንፈስ ሥራውን መምራቱ፣ የክርስቶስን ተግባራዊ ዘዴዎች መከተላቸውና ሰዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማነጋገር በሚያስችሉ ተስማሚ ጽሑፎች መጠቀም ናቸው።

የይሖዋ መንፈስና ምሥራቹ

3. በተከናወነው ነገር መኩራራት የማንችለው ለምንድን ነው?

3 የይሖዋ ምሥክሮች ሥራቸው ሊሳካ የቻለው ልዩ ችሎታዎች ስላሉዋቸው እንደሆነ አድርገው በማሰብ ይኩራራሉን? በፍጹም፤ ምክንያቱም “የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ፦ የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፣ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት ለዚህ ሁኔታ ይሠራሉ። የይሖዋ ምሥክሮች በግለሰብ ደረጃ ያሉበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑና የተጠመቁ ክርስቲያኖች እንደመሆናቸው መጠን አምላክን የማገልገል ኃላፊነት በፈቃደኝነት ተቀብለዋል። ለአንዳንዶች ይህ ማለት ሚስዮናውያን ወይም በቅርንጫፍ ቢሮዎችና ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን ለማተም በሚያገለግሉ የሕትመት ተቋሞች ውስጥ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መሰማራት ማለት ሆኖአል። ሌሎች ደግሞ እንዲህ ዓይነቱ ክርስቲያናዊ ፈቃደኝነት በሃይማኖታዊ ሕንፃዎች የግንባታ ሥራ እንዲሳተፉ፣ አቅኚ አገልጋዮች ሆነው በሙሉ ጊዜ የስብከት ሥራ እንዲያገለግሉ ወይም በአካባቢያቸው በሚገኙ ጉባኤዎች ውስጥ የምሥራቹ አስፋፊዎች ሆነው ባሉአቸው ትርፍ ጊዜያት እንዲሰብኩ አድርጓቸዋል። “ልናደርገው የሚገባንን” ሥራ በመሥራታችን ማንኛችንም ብንሆን ልንኩራራ አንችልም።—ሉቃስ 17:10፤ 1 ቆሮንቶስ 9:16

4. በክርስቲያናዊው አገልግሎት ላይ የተነሣውን ዓለም አቀፍ ተቃውሞ መቋቋም የተቻለው እንዴት ነው?

4 ያገኘነው ማንኛውም የተሳካ ውጤት የተገኘው በይሖዋ መንፈስ ወይም በአንቀሳቃሽ ኃይሉ አማካኝነት ነው ልንል እንችላለን። “ለዘሩባቤል የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፦ በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” የሚለው አባባል በነቢዩ ዘካርያስ ዘመን ትክክል እንደነበረ ሁሉ ዛሬ ላለውም ሁኔታ ትክክለኛ አባባል ነው። ስለዚህ በምሥክሮቹ የስብከት ሥራ ላይ የሚደርሰውን ዓለም አቀፍ ተቃውሞ መቋቋም የተቻለው በሰው ጥረት ሳይሆን በይሖዋ አመራርና ጥበቃ ነው።—ዘካርያስ 4:6

5. የመንግሥቱ መልዕክት እንዲሰራጭ በሚደረገው ሥራ ይሖዋ ምን ሚና ይጫወታል?

5 ለመንግሥቱ መልዕክት አዎንታዊ ምላሽ ስለሚሰጡ ሰዎች ሲናገር ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአብ የሰማ የተማረም ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። . . . ከአብ የተሰጠው ካልሆነ ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም።” (ዮሐንስ 6:45, 65) ይሖዋ ልብንና አእምሮን ማየት ይችላል፤ ገና የማያውቁት ቢሆኑም እንኳ ለፍቅሩ አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡትን ሰዎች ያውቃል። ይህን ልዩ የሆነ አገልግሎት ለመምራትም በመላዕክቱ ይጠቀማል። ዮሐንስ በመጣለት ራእይ ላይ መላዕክት የሚያደርጉትን ተሳትፎ ያየውና “በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር አየሁ” ሲል የጻፈው ለዚህ ነው።—ራእይ 14:6

ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ የሆኑ ሰዎች

6. አንድ ሰው ለምሥራቹ አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጥ ምን መሠረታዊ አመለካከት ሊኖረው ይገባል?

6 ይሖዋ አንድ ሰው ምሥራቹን መቀበል የሚችልበትን አጋጣሚ የሚያመቻችለት ሌላው ምክንያት ምን እንደሆነ ኢየሱስ ገልጿል፦ “ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ የሆኑ ሁሉ ደስተኞች ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።” (ማቴዎስ 5:3 አዓት) ባለው አቋም የሚረካ ወይም እውነትን የማይፈልግ ሰው ለሚያስፈልጉት መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ ነው ሊባል አይችልም። እሱ ወይም እርሷ የሚያስቡት ከቁሳዊና ከሥጋዊ ነገሮች አንፃር ብቻ ነው። የጎደለኝ ነገር የለም የሚለው አስተሳሰባቸው እንቅፋት ሆኖባቸዋል። ስለዚህ ከቤት ወደ ቤት ስንሄድ የምናገኛቸው ብዙ ሰዎች መልዕክቱን አንቀበልም ቢሉ እንደዚያ ብለው እንዲመልሱ ያበቋቸውን የተለያዩ ምክንያቶች ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል።

7. ብዙዎች ለእውነት አዎንታዊ ምላሽ የማይሰጡት ለምንድን ነው?

7 ብዙዎች ማዳመጥ አይፈልጉም፤ ምክንያቱም ከዘር በወረሱት ሃይማኖት ላይ ድርቅ ያለ እምነት ስላላቸው ውይይት ለማድረግ ፈቃደኞች አይደሉም። ሌሎቹ ደግሞ ከጠባያቸው ጋር የሚስማማ ሃይማኖት ይማርካቸዋል። አንዳንዶች ምሥጢራዊና ከሰው የመረዳት ችሎታ በላይ የሆነ ሃይማኖት መከተል ይፈልጋሉ። ሌሎች ስሜታዊ የሆነ ነገር ያስደስታቸዋል። ሌሎቹ ደግሞ በቤተ ክርስቲያናቸው በሚካሄዱ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች የሚደሰቱ ሰዎች ናቸው። በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ከአምላክ የአቋም ደረጃዎች ጋር የሚጋጭ የአኗኗር ዘይቤን መርጠዋል። ምናልባትም “ፍላጎት የለኝም” ብለው እንዲናገሩ የሚያደርጋቸውን ብልሹ ኑሮ ይከተሉ ይሆናል። ተምረናል እንዲሁም በሳይንስ መጥቀናል የሚሉት ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ሀ ሁ ነው ብለው ያጣጥሉታል።—1 ቆሮንቶስ 6:9–11፤ 2 ቆሮንቶስ 4:3, 4

8. ሰዎች መልዕክቱን አልቀበልም ማለታቸው ቅንዓታችንን ሊያዳክምብን የማይገባው ለምንድን ነው? (ዮሐንስ 15:18–20)

8 አብዛኛዎቹ ሰዎች አንፈልግም ማለታቸው ሕይወት አድን በሆነው አገልግሎት ላይ ያለንን እምነትና ቅንዓት ሊያዳክምብን ይገባልን? ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች ከጻፋቸው ከሚከተሉት ቃላት መጽናኛ ማግኘት እንችላለን፦ “ታዲያ ምንድር ነው? የማያምኑ ቢኖሩ አለማመናቸው የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያስቀራልን? እንዲህ አይሁን፤ በቃልህ ትጸድቅ ዘንድ ወደ ፍርድ በገባህም ጊዜ ትረታ ዘንድ ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ሰው ሁሉ ውሸተኛ ከሆነ እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን።”—ሮሜ 3:3, 4

9, 10. በብዙ አገሮች ውስጥ ተቃውሞን መቋቋም እንደተቻለ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

9 አንዳችም ዓይነት አዎንታዊ ምላሽ የማያሳዩ ይመስሉ የነበሩ ከጊዜ በኋላ ግን የተገላቢጦሽ ሆነው ከተገኙት በዓለም ዙሪያ ያሉ አገሮች ብዙ ምሳሌዎች ማበረታቻ ማግኘት እንችላለን። ይሖዋና መላዕክቱ ቀና ልብ ያላቸው ሰዎች እንዳሉ ያውቁ ነበር። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች በአገልግሎታቸው በትዕግሥት መቀጠልና መጽናት ነበረባቸው። ለምሳሌ ያህል ከ50 ዓመት በፊት የካቶሊክ እምነት ሊወገድ የማይችል ጋሬጣ ሆኖ ይታይባቸው የነበሩትን እንደ አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ኮሎምቢያ፣ አየርላንድ፣ ጣሊያን፣ ሜክሲኮ፣ ፖርቱጋልና ስፔን ያሉ አንዳንድ አገሮችን እንውሰድ። ከብዙ ዓመታት በፊት ይኸውም በ1943 ምሥክሮቹ በጣም ጥቂት ነበሩ፤ በዓለም ዙሪያ ቁጥራቸው 126,000 ብቻ ነበር። ከዚህ ውስጥም 72,000ዎቹ የሚገኙት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ነበር። ምሥክሮቹ የገጠማቸው ሰዎች ስለ እነርሱ ያለማወቃቸው ችግርና አግባብነት የሌለው ጥላቻ ከጡብ እንደተሠራ ግድግዳ ፍንክች የማይል መስሎ ነበር። ዛሬ ግን በስብከቱ ሥራ ከተገኙት እጅግ ከፍተኛ ውጤቶች መካከል አንዳንዶቹ የተገኙት በእነዚህ አገሮች ውስጥ ነው። ቀደም ሲል ኮሙኒስት በነበሩ ብዙ አገሮች ውስጥም ያለው ሁኔታ እንደዚሁ ነው። በ1993 ዩክሬን ኪየቭ ውስጥ የተከናወነው 7,402 ሰዎች የተጠመቁበት የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ለዚህ ማስረጃ ይሆነናል።

10 ምሥክሮቹ ምሥራቹን ለጎረቤቶቻቸው ለመንገር ሲጠቀሙባቸው የቆዩት መንገዶች ምንድን ናቸው? አንዳንዶች ምንም ማስረጃ ሳይኖራቸው እንደሚናገሩት ምሥክሮቹ የሰዎችን እምነት ለማስለወጥ ቁሳዊ መደለያዎችን ሲጠቀሙ ቆይተዋልን? ሌሎቹ ደግሞ እንደሚሉት ምሥክሮቹ የሚያነጋግሩት ድሃውንና ያልተማረውን ኅብረተሰብ ብቻ ነውን?

ምሥራቹን ለማዳረስ የሚያስችሉ ስኬታማ መንገዶች

11. ኢየሱስ በአገልግሎቱ ምን ጥሩ ምሳሌ ትቷል? (ዮሐንስ 4:6–26ን ተመልከት።)

11 ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የይሖዋ ምሥክሮች እስከ ዛሬ ድረስ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራቸው የሚከተሉትን መንገድ ቀይሰዋል። ኢየሱስ ሀብታሞችም ይሁኑ ድሆች ሰዎች ወደነበሩበት ቦታ ሁሉ ይሄድ ነበር። ወደ ቤቶች፣ ወደ ሕዝብ መናኸሪያዎች፣ ወደ ሐይቅ ዳርቻዎች፣ ወደ ተራራ አጠገብ አልፎ ተርፎም ወደ ምኩራቦች ይሄድ ነበር።—ማቴዎስ 5:1, 2፤ 8:14፤ ማርቆስ 1:16፤ ሉቃስ 4:15

12, 13. (ሀ) ጳውሎስ ክርስቲያኖች ሊከተሉት የሚገባ ፈለግ የተወው እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች የጳውሎስን ምሳሌ የሚከተሉት እንዴት ነው?

12 ሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎቱን በተመለከተ እንዲህ ሲል በትክክል መናገር ችሏል፦ “ወደ እስያ ከገባሁበት ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ . . . ለጌታ እየተገዛሁ ዘመኑን ሁሉ ከእናንተ ጋር እንዴት እንደኖርሁ እናንተው ታውቃላችሁ፤ . . . በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ፣ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም።”—ሥራ 20:18–20

13 የይሖዋ ምሥክሮች የሐዋርያትን ፈለግ በመከተል ከቤት ወደ ቤት በሚያደርጉት አገልግሎት በዓለም ዙሪያ የታወቁ ናቸው። ከፍተኛ ወጪ በሚጠይቅ፣ እንደ ነገሩ በሚካሄድና ሰውን በግለሰብ ደረጃ ለማነጋገር በማያስችል የቴሌቪዥን ስብከት ላይ ከማተኮር ይልቅ ምሥክሮቹ ድሆችም ሆኑ ሀብታም ወደሆኑ ሰዎች ይሄዳሉ፤ ሰዎቹንም በግንባር አግኝተው ያነጋግሯቸዋል። ስለ አምላክና ስለቃሉ ሰዎችን ማወያየት ይፈልጋሉ።b የተለያዩ ዕቃዎችን በነፃ በማደል የዳቦ ክርስቲያኖችን ለማፍራት አይሞክሩም። የሚቀርብላቸውን ማስረጃ እያመዛዘኑ ለመወያየት ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ለሰው ልጆች ችግር ብቸኛዋ እውነተኛ መፍትሔ በምድራችን ላይ ያሉትን ችግሮች ወደተሻለ ሁኔታ የምትለውጠው የአምላክ መስተዳድር እንደሆነች ያስገነዝቧቸዋል።—ኢሳይያስ 65:17, 21–25፤ 2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:1–4

14. (ሀ)  ብዙ ሚስዮናውያንና አቅኚዎች ጠንካራ መሠረት የጣሉት እንዴት ነው? (ለ) በጃፓን ከሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ተሞክሮ ምን እንማራለን?

14 ሥራው በተቻለ መጠን በብዙ አገሮች ስኬታማ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ሚስዮናውያንና አቅኚዎች በብዙ አገሮች ውስጥ እግራቸውን ተከሉ። መንደርደሪያ የሚሆን ጥሩ መሠረት ጣሉ። ከዚያም የአገሩ ተወላጅ የሆኑ ምሥክሮች ግንባር ቀደም ሆነው መሥራት ጀመሩ። በመሆኑም የስብከቱ ሥራ እንዲቀጥልና በደንብ የተደራጀ ሆኖ እንዲዘልቅ ለማድረግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የውጪ አገር ምሥክሮች አላስፈለጉም። ለዚህ በዋነኛነት ከሚጠቀሱት አገሮች መካከል አንዷ ጃፓን ናት። ከብዙ ዓመታት በፊት በ19 40ዎቹ መገባደጃ ላይ ከመካከላቸው አብዛኛዎቹ አውስትራሊያውያንና እንግሊዛውያን የሆኑ ሚስዮናውያን ወደዚህች አገር ሄዱ፤ ቋንቋውን አጠኑ፤ በዚያ የጦርነት ማግሥት በነበረው ዘመን ከነበሩት ሁኔታዎች ጋር ራሳቸውን አስማምተው መኖር ጀመሩ፤ እንዲሁም ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ለመመሥከር ቆርጠው ተነሡ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጃፓን ውስጥ ምሥክሮቹ እገዳ ተጥሎባቸው ነበር፤ እንዲሁም ስደት ይደርስባቸው ነበር። ስለዚህ ሚስዮናውያኑ እዚያ ሲደርሱ ያገኟቸው በአገልግሎት በንቃት የሚሳተፉ ጃፓናውያን ምሥክሮች በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ። በዛሬው ጊዜ ግን ቁጥራቸው አድጎ ከ3,000 በሚልቁ ጉባኤዎች ውስጥ ከ187,000 በላይ አስፋፊዎች ሆነዋል! ገና ከጅምሩ ስኬታማ ሊሆኑ የቻሉበት ምሥጢሩ ምንድን ነው? በዚያ ቦታ ከ25 ዓመታት በላይ ያገለገለ አንድ ሚስዮናዊ እንዲህ ብሏል፦ “ከሰዉ ጋር መነጋገርንና መግባባትን መማሩ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነበር። ቋንቋቸውን በማወቅ ከእነርሱ ጋር ልብ ለልብ መተዋወቅ፣ የአኗኗር መንገዳቸውን ለመረዳትና ለማድነቅ ችለን ነበር። ጃፓናውያኑን እንደምንወዳቸው ማሳየት ነበረብን። ክርስቲያናዊ የአቋም ደረጃዎቻችንን ዝቅ ሳናደርግ የአካባቢው ማኅበረሰብ ክፍል ለመሆን በትህትና ጥረት እናደርግ ነበር።”

ክርስቲያናዊ ጠባይም ምሥክር ነው

15. ምሥክሮቹ ክርስቲያናዊ ጠባይን በሥራ የሚያሳዩት እንዴት ነው?

15 ይሁን እንጂ ሰዎች አዎንታዊ ምላሽ የሚያሳዩት ለመጽሐፍ ቅዱስ መልዕክት ብቻ አይደለም። ክርስቲያናዊነትም በተግባር ሲውል ተመልክተዋል። የእርስ በርስ ጦርነትን፣ የጎሳ ግጭቶችንና የዘር ጥላቻን በመሰሉ እጅግ ፈታኝ በሆኑ ጊዜያትም ጭምር ምሥክሮቹ ያላቸውን ፍቅር፣ ስምምነትና አንድነት አስተውለዋል። ምሥክሮቹ በሁሉም ግጭቶች የማያወላዳ ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋም ጠብቀዋል፤ የሚከተሉትን የኢየሱስ ቃላትም ፈጽመዋል፦ “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፣ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በእርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በእርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።”—ዮሐንስ 13:34, 35

16. ተግባራዊ የሆነ ክርስቲያናዊ ፍቅርን የሚያሳየው የትኛው ተሞክሮ ነው?

16 ጎረቤታዊ ፍቅር ስለ “አንድ ደግ ባልና ሚስት” ለአንድ የአካባቢው ጋዜጣ በጻፉ አረጋዊ ሰው ሁኔታ ላይ ታይቷል። አዛውንቱ ባለቤታቸው ሲሞቱ ጎረቤታቸው የሆኑ ባልና ሚስት ውለታ እንደዋሉላቸው ገልጸዋል። “እርሷ ከሞተችበት ጊዜ ጀምሮ . . . ያደረጉልኝን ነገር ልነግራችሁ አልችልም” ሲሉ ጽፈዋል። “ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሁሉንም ዓይነት ሥራዎች በመሥራትና የ74 ዓመትን ጡረተኛ ችግሮች ለመፍታት እርዳታ በማድረግ . . . ‘እንደ ቤተሰባቸው አድርገው ይዘውኛል።’ ይህን ሁኔታ እጅግ ልዩ የሚያደርገው እነርሱ ጥቁሮች ሲሆኑ እኔ ነጭ መሆኔ ነው። እነርሱ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። እኔ ከአባልነት ራሴን ያገለልኩ ካቶሊክ ነኝ።”

17. የትኛውን መንገድ ከመከተል መራቅ ይኖርብናል?

17 ይህ ተሞክሮ በየዕለቱ የምናሳየውን ጠባይ ጨምሮ በብዙ መንገዶች ምሥክርነት መስጠት እንደምንችል ያሳያል። እንዲያውም ጠባያችን ልክ እንደ ክርስቶስ ካልሆነ አገልግሎታችን ፈሪሳዊነት ይሆናል፤ እርባናም አይኖረውም። ኢየሱስ “ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም፣ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ” ሲል እንደገለጻቸው ሰዎች መሆን አንፈልግም።—ማቴዎስ 22:37–39፤ 23:3

የባርያው ክፍል ተስማሚ መሣሪያዎችን ያቀርባል

18. መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ለመርዳት የሚያስታጥቁን እንዴት ነው?

18 ምሥራቹን ለአሕዛብ ሁሉ በመስበክ ረገድ ሌላው እጅግ ጠቃሚ ሆኖ የተገኘው ነገር በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር እየታተሙ የሚወጡት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች መኖራቸው ነው። ለማንኛውም በቅን ልቦና ጥያቄ ለሚያነሣ ሰው ሁሉ አጥጋቢ መልስ መስጠት የሚችሉ መጻሕፍት፣ ብሮሹሮች፣ ትራክቶችና መጽሔቶች አሉን ማለት ይቻላል። አንድ እስላም፣ ሂንዱ፣ ቡድሂስት፣ የታኦይዝም እምነት ተከታይ ወይም አይሁድ ቢያጋጥመን ውይይት ለመክፈትና ምናልባትም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሰው ዘር አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ወይም የተለያዩ ትራክቶችንና ቡክሌቶችን መጠቀም እንችላለን። አንድ የዝግመተ ለውጥ አማኝ ስለ ፍጥረት ቢጠይቀን ሕይወት እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ መጠቀም እንችላለን። አንድ ወጣት ‘የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው?’ ብሎ ቢጠይቀን ወጣትነትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት የተባለውን መጽሐፍ ልንጠቁመው እንችላለን። አንድ ሰው እንደ መንፈስ ጭንቀት፣ ከባድ የድካም ስሜት፣ ተገዶ መነወር፣ ፍቺ በመሳሰሉ የግል ችግሮች በእጅጉ የሚሰቃይ ከሆነ እነዚህን ችግሮች ተግባራዊ በሆነ መንገድ እንዴት መወጣት እንደሚቻል የሚያብራሩ መጽሔቶች አሉን። እውነትም ኢየሱስ “ምግባቸውን በጊዜው” ይሰጣቸዋል ሲል የተነበየለት የታማኙ ባሪያ ክፍል የሥራ ድርሻውን እየተወጣ ነው።—ማቴዎስ 24:45–47

19, 20. በአልባኒያ ውስጥ የመንግሥቱ ሥራ እየተፋጠነ ያለው እንዴት ነው?

19 ሆኖም መልዕክቱን ለአሕዛብ ለማዳረስ እነዚህን ጽሑፎች በብዙ ልሳኖች ማዘጋጀቱ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ጽሑፎችን ከ200 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች መተርጎም የተቻለው እንዴት ነው? አልባኒያን በአጭሩ እንደ ምሳሌ አድርገን መመልከታችን ብዙ ከባድ ችግሮች እያሉና ወዲያውኑ የተለያዩ ቋንቋዎችን የመናገር ችሎታ የሚያስገኝ ዘመናዊ ጰንጠቆስጤ ሳይኖር የታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል ምሥራቹን እንዴት ማስፋፋት እንደቻለ በግልጽ ያሳየናል።—ሥራ 2:1–11

20 እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ አልባኒያ በአምላክ መኖር የማታምን ኮምኒስት መሆኗን ያወጀች ብቸኛዋ አገር ተደርጋ ትታይ ነበር። ናሽናል ጂኦግራፊክ የተባለው መጽሔት “አልባኒያ በ1967 ‘በዓለም ላይ የመጀመሪያዋ በአምላክ የማላምን አገር’ ነኝ ብላ በማወጅ [ሃይማኖትን] አግዳለች። . . . የአልባኒያ አዲስ ትውልድ የሚያውቀው ነገር አምላክ የለም የሚለውን እምነት ብቻ ነው” በማለት በ1980 አትቶ ነበር። አሁን ያ ኮምኒዝም ተንኮታኩቷል። መንፈሳዊ ነገር እንደሚያስፈልጋቸው የተገነዘቡ የአልባኒያ ሰዎች በይሖዋ ምሥክሮች እየተከናወነ ላለው ስብከት አዎንታዊ ምላሽ እየሰጡ ነው። በ1992 በቲራና ውስጥ የጣሊያንኛና የእንግሊዝኛ እውቀት ያላቸው ወጣት ምሥክሮችን ያቀፈ አነስተኛ የትርጉም ቡድን ተመሥርቷል። ከሌሎች አገሮች መጥተው የጎበኙአቸው ብቃት ያላቸው ወንድሞች በአልባኒያ ቋንቋ ለመጻፍ በቀላሉ ከቦታ ወደ ቦታ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ ኮምፒውተሮችን እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ አስተማሯቸው። ትራክቶችንና የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት መተርጎም ጀመሩ። ልምድ ሲያገኙ ደግሞ ሌሎች እጅግ ጠቃሚ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችን የመተርጎሙን ሥራ ተያያዙት። በዚያች (3,262,000 ሕዝብ ባላት) አነስተኛ አገር ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ወደ 200 የሚጠጉ ምሥክሮች አሉ። 1,984 ሰዎችም በ1994 የመታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝተዋል።

ሁላችንም ኃላፊነት አለብን

21. የምንኖረው በምን ዓይነት ዘመን ውስጥ ነው?

21 በዓለም ላይ እየተከናወኑ ያሉት ነገሮች ወደ ፍጻሜያቸው እየገሰገሱ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም እያየሉ በመጡት ወንጀልና ዓመጽ፣ በእርስ በእርስ ጦርነቶች በሚካሄደው መጨፋጨፍና አስገድዶ የመድፈር ድርጊት፣ በጊዜያችን የተለመደ በሆነው ልቅ ሥነ ምግባርና የዚህ ፍሬዎች በሆኑት በጾታ ግንኙነት በሚተላለፉ በሽታዎች እንዲሁም ለሕጋዊ ሥልጣን አክብሮት ባለማሳየት የተነሣ ዓለም ሥርዓት አልባና ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ መጥቷል። በዘፍጥረት ላይ የተገለጸውን ከውኃ ጥፋት በፊት የነበረውን ጊዜ በሚመስል ዘመን ላይ እንገኛለን፦ “እግዚአብሔርም የሰው ክፋት በምድር ላይ እንደ በዛ፣ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደሆነ አየ። እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፣ በልቡም አዘነ።”—ዘፍጥረት 6:5, 6፤ ማቴዎስ 24:37–39

22. የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ ምን ክርስቲያናዊ ኃላፊነት አለባቸው?

22 ይሖዋ በኖህ ዘመን እንዳደረገው አሁንም እርምጃ ይወስዳል። ነገር ግን ከፍትሑና ከፍቅሩ የተነሣ አስቀድሞ የምሥራቹና የማስጠንቀቂያው መልዕክት ለአሕዛብ ሁሉ እንዲሰበክ ይፈልጋል። (ማርቆስ 13:10) በዚህ ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ ሰላም የሚገባቸውን የመፈለግና የእርሱን የሰላም መንገዶች የማስተማር ኃላፊነት አለባቸው። በቅርቡ አምላክ በወሰነው ጊዜ የስብከቱ ተልእኮ ስኬታማ በሆነ መንገድ ይጠናቀቃል። “በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴዎስ 10:12, 13፤ 24:14፤ 28:19, 20

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አሕዛብን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል በተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ጥራዝ ሁለት ገጽ 472–4 ያለውን “Nations” (“አሕዛብ”) የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

b ክርስቲያናዊ አገልግሎትን በተመለከተ ተግባራዊ የሆኑ ሐሳቦችን ለማግኘት 8–105 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 13 ላይ ያለውን “በጥሩ ዘዴ የሚጠቀም አገልጋይ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለውንና ገጽ 16 ላይ ያለውን “ተጨማሪ ደቀ መዛሙርት የሚያስገኝ ውጤታማ አገልግሎት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

ታስታውሳለህን?

◻ በዘመናችን ያሉ ክርስቲያኖች በአገልግሎታቸው ምን የተሳካ ውጤት አግኝተዋል?

◻ ብዙዎች ክርስቲያናዊውን መልዕክት የማይቀበሉት ለምንድን ነው?

◻ ምሥክሮቹ የሚጠቀሙት የትኛውን ሐዋርያዊ የስብከት መንገድ ነው?

◻ ለውጤታማ አገልግሎት የሚረዱ ምን መሣሪያዎች አሉን?

◻ ሁላችንም ከማርቆስ 13:10 ጋር በመስማማት ምን ማድረግ አለብን?

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አገር በ1943 የነበሩ ምሥክሮች በ1943

አርጀንቲና 374 102,043

ብራዚል 430 366,297

ቺሊ 72 44,668

ኮሎምቢያ  ?? 60,854

ፈረንሳይ 2ኛው የዓለም ጦርነት—አይታወቅም 122,254

አየርላንድ 150? 4,224

ጣሊያን 2ኛው የዓለም ጦርነት—አይታወቅም 201,440

ሜክሲኮ 1,565 380,201

ፔሩ የተመዘገበ ነገር የለም 45,363

ፊሊፒንስ 2ኛው የዓለም ጦርነት—አይታወቅም 116,576

ፖላንድ 2ኛው የዓለም ጦርነት—አይታወቅም 113,551

ፖርቱጋል የተመዘገበ ነገር የለም 41,842

ስፔን የተመዘገበ ነገር የለም 97,595

ኡራጓይ 22 9,144

ቬንዙዌላ የተመዘገበ ነገር የለም 64,081

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች እንደ ስፔን በመሰሉ ብዙ የካቶሊኮች አገሮች ውስጥ ቁጥራቸው እየጨመረ ነው

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች በምድር ዙሪያ ባሉ አገሮች ውስጥ በትጋት ያገለግላሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ