የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • bt ምዕ. 3 ገጽ 20-27
  • “በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ”
  • ‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “ሁሉም በአንድ ቦታ ተሰብስበው” (የሐዋርያት ሥራ 2:1-4)
  • ‘እያንዳንዱ ሰው በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ሰማ’ (የሐዋርያት ሥራ 2:5-13)
  • ‘ጴጥሮስ ተነስቶ ቆመ’ (የሐዋርያት ሥራ 2:14-37)
  • ‘እያንዳንዳችሁ ተጠመቁ’ (የሐዋርያት ሥራ 2:38-47)
  • ጴጥሮስ በጰንጠቆስጤ ዕለት ሰበከ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • የክርስትና እምነት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት አይሁዶች ተዳረሰ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • የአንባብያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • “ከየቋንቋው” የተውጣጡ ሰዎች ምሥራቹ ደረሳቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
ለተጨማሪ መረጃ
‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
bt ምዕ. 3 ገጽ 20-27

ምዕራፍ 3

“በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ”

በጴንጤቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ መውረዱ ያስገኘው ውጤት

በሐዋርያት ሥራ 2:1-47 ላይ የተመሠረተ

1. የጴንጤቆስጤ በዓል በሚከበርበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ ግለጽ።

የኢየሩሳሌም ጎዳናዎች በአድናቆት በተዋጡ ሰዎች ሁካታ ተሞልተዋል።a በቤተ መቅደሱ ከሚገኘው መሠዊያ ጭስ ወደ ላይ እየተትጎለጎለ ይወጣል፤ ሌዋውያኑም የሃሌል መዝሙሮችን (ከመዝሙር 113 እስከ 118) እየዘመሩ ሥነ ሥርዓቱን ያጅባሉ፤ ዝማሬው በቅብብሎሽ የሚዜም ሳይሆን አይቀርም። እንግዶች የከተማዋን ጎዳናዎች አጨናንቀዋቸዋል። እነዚህ ሰዎች የመጡት እንደ ኤላም፣ ሜሶጶጣሚያ፣ ቀጰዶቅያ፣ ጳንጦስ፣ ግብፅና ሮም ከመሳሰሉ ራቅ ያሉ ቦታዎች ነው።b ሰዎቹ በዚያ የተሰባሰቡት ለምንድን ነው? ለጴንጤቆስጤ በዓል ነው፤ “መጀመሪያ የሚደርሰው ፍሬ [የሚሰበሰብበት ቀን]” ተብሎም ይጠራል። (ዘኁ. 28:26) ይህ ዓመታዊ በዓል የገብስ መከር ተጠናቆ የስንዴ መከር መጀመሩን የሚያበስር ነው። በመሆኑም የደስታ ቀን ነው።

በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ምሥራቹን የሰሙት ሰዎች ከየትኞቹ አካባቢዎች እንደመጡ የሚያሳይ ካርታ። 1. አገሮች፦ ሊቢያ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ቢቲኒያ፣ ጳንጦስ፣ ቀጰዶቅያ፣ ይሁዳ፣ ሜሶጶጣሚያ፣ ባቢሎን፣ ኤላም፣ ሜዶን እና ጳርቴና። 2. ከተሞች፦ ሮም፣ እስክንድርያ፣ ሜምፊስ፣ አንጾኪያ (የሶርያ)፣ ኢየሩሳሌም እና ባቢሎን። 3. የውኃ አካላት፦ ሜድትራንያን ባሕር፣ ጥቁር ባሕር፣ ቀይ ባሕር፣ ካስፒያን ባሕር እና የፋርስ ባሕረ ሰላጤ።

ኢየሩሳሌም—የአይሁድ እምነት ማዕከል

በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፎች ላይ የተገለጹት አብዛኞቹ ክንውኖች የተፈጸሙት በኢየሩሳሌም ነው። ይህች ከተማ የምትገኘው በይሁዳ ማዕከላዊ ክፍል ባለ የተራራ ሰንሰለት ላይ ነው፤ ከሜድትራንያን ባሕር በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ 55 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ትገኛለች። በ1070 ዓ.ዓ. ንጉሥ ዳዊት በዚህ አካባቢ የሚገኘውን የጽዮን ተራራ ምሽግ ተቆጣጠረ፤ በምሽጉ ዙሪያ የተቆረቆረው ከተማ በኋላ ላይ የጥንቱ የእስራኤል ብሔር ዋና ከተማ ለመሆን በቃ።

በጽዮን ተራራ አቅራቢያ የሞሪያ ተራራ ይገኛል፤ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የተዘገቡት ክንውኖች ከመፈጸማቸው ከ1,900 ዓመታት ገደማ በፊት አብርሃም ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርበው የነበረው በዚህ ተራራ ላይ እንደነበር የጥንት አይሁዳውያን ወግ ይገልጻል። ሰለሞን የመጀመሪያውን የይሖዋ ቤተ መቅደስ በሞሪያ ተራራ አናት ላይ በገነባ ጊዜ ተራራው የከተማዋ ክፍል ሆነ። ይህ ዕፁብ ድንቅ ሕንፃ የአይሁዳውያን ሕይወትና አምልኮ ማዕከል ነበር።

ከመላው ምድር የሚመጡ ቀናተኛ አይሁዳውያን መሥዋዕት ለማቅረብ፣ አምላክን ለማምለክና በየወቅቱ የሚከበሩትን በዓላት ለማክበር ዘወትር የሚሰበሰቡት በይሖዋ ቤተ መቅደስ ነበር። ይህን የሚያደርጉት “በመካከልህ ያሉ ወንዶች ሁሉ በዓመት ሦስት ጊዜ . . . አምላክህ ይሖዋ በመረጠው ስፍራ ፊቱ ይቅረቡ” የሚለውን የአምላክን ትእዛዝ ለመፈጸም ነው። (ዘዳ. 16:16) በተጨማሪም ኢየሩሳሌም የታላቁ የሳንሄድሪን መቀመጫ ነበረች፤ ሳንሄድሪን የአይሁዳውያን ከፍተኛ የፍርድ ሸንጎና የብሔሩ የአስተዳደር ምክር ቤት ነው።

2. በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ምን አስደናቂ ነገሮች ተፈጸሙ?

2 በ33 ዓ.ም. የጸደይ ወቅት በዋለው በዚህ የጴንጤቆስጤ ዕለት፣ ጠዋት ሦስት ሰዓት ገደማ ላይ አንድ ክንውን ተፈጸመ፤ ከዚያ በኋላ ባሉት ዘመናት ሁሉ ሰዎችን ሲያስደንቅ የኖረ ተአምራዊ ክንውን! ድንገት “እንደ ኃይለኛ ነፋስ ያለ” ወይም “እንደ ብርቱ ዐውሎ ነፋስ ያለ” ድምፅ ከሰማይ መጣ። (ሥራ 2:2 አዲሱ መደበኛ ትርጉም) ይህ ኃይለኛ ድምፅ 120 ገደማ የሚሆኑ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ተሰብስበውበት የነበረውን ቤት ሞላው። ከዚያም አንድ አስደናቂ ነገር ተፈጸመ። የእሳት ምላሶች የሚመስሉ ታዩ፤ በእያንዳንዱ ደቀ መዝሙር ላይም አረፉ።c ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ “በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ”፤ በሌሎች ቋንቋዎች ይናገሩም ጀመር! ደቀ መዛሙርቱ ከቤት ከወጡ በኋላ በኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ላይ ያገኟቸውን እንግዶች በራሳቸው ቋንቋ ሲያነጋግሯቸው ሰዎቹ በአድናቆት ተዋጡ! አዎ፣ እያንዳንዱ ሰው ደቀ መዛሙርቱ “በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ” ሰማ።—ሥራ 2:1-6

3. (ሀ) በ33 ዓ.ም. የዋለው ጴንጤቆስጤ፣ በእውነተኛው አምልኮ ታሪክ ውስጥ ምዕራፍ ከፋች የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ጴጥሮስ ያቀረበው ንግግር “የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፎች” ከመጠቀም ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

3 ይህ ከእውነተኛው አምልኮ ጋር በተያያዘ ምዕራፍ ከፋች የሆነ ክንውን ነው፤ ምክንያቱም የመንፈሳዊ እስራኤል ብሔር ማለትም የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ መቋቋሙን የሚያበስር ነው። (ገላ. 6:16) ይህ ብቻም አይደለም። በዚያን ዕለት ጴጥሮስ ለተሰበሰበው ሕዝብ ንግግር ባቀረበበት ወቅት ከሦስቱ ‘የመንግሥተ ሰማያት ቁልፎች’ መካከል የመጀመሪያውን ተጠቀመ፤ እነዚህ ቁልፎች የተለያዩ ቡድኖች ልዩ በረከቶች የሚያገኙበትን አጋጣሚ የሚከፍቱ ነበሩ። (ማቴ. 16:18, 19) ይህ የመጀመሪያው ቁልፍ አይሁዶችና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ምሥራቹን ተቀብለው በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እንዲቀቡ በር የሚከፍት ነበር።d እነዚህ ሰዎች በዚህ መንገድ የመንፈሳዊው እስራኤል ክፍል ይሆናሉ፤ በመሆኑም በመሲሐዊው መንግሥት ውስጥ ነገሥታትና ካህናት የመሆን ተስፋ ይኖራቸዋል። (ራእይ 5:9, 10) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሳምራውያን፣ ከዚያም አሕዛብ ይህን መብት የማግኘት አጋጣሚ ይከፈትላቸዋል። ታዲያ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት ከተፈጸመው አስደናቂ ክንውን ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

“ሁሉም በአንድ ቦታ ተሰብስበው” (የሐዋርያት ሥራ 2:1-4)

4. በዘመናችን ያለው የክርስቲያን ጉባኤ፣ በ33 ዓ.ም. የተቋቋመው ጉባኤ የጀመረውን ሥራ ያስቀጠለው እንዴት ነው?

4 የክርስቲያን ጉባኤ በተቋቋመበት ወቅት “በአንድ ቦታ [ይኸውም በአንድ ደርብ ላይ] ተሰብስበው” የነበሩ በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ 120 ደቀ መዛሙርትን ያቀፈ ነበር። (ሥራ 2:1) በዚያን ዕለት መገባደጃ ላይ የጉባኤው የተጠመቁ አባላት ቁጥር በሺዎች የሚቆጠር ሆነ። እስከ ዛሬም ድረስ እየሰፋ በመሄድ ላይ ያለው ድርጅት እድገቱን ሀ ብሎ የጀመረው በዚህ ጊዜ ነበር! አዎ፣ በዘመናችን ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን ወንዶችና ሴቶች ያቀፈው የክርስቲያን ጉባኤ የዚህ ውጤት ነው፤ የሥርዓቱ መጨረሻ ከመምጣቱ በፊት “የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር” እየተሰበከ ያለው በዚህ ጉባኤ አማካኝነት ነው።—ማቴ. 24:14

5. በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ይሁን በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች ከጉባኤው ጋር መተባበራቸው ምን በረከት አስገኝቶላቸዋል?

5 ከዚህም በተጨማሪ የክርስቲያን ጉባኤ፣ ለአባላቱ ሁሉ መንፈሳዊ የብርታት ምንጭ ይሆናል፤ በመጀመሪያ ለቅቡዓኑ፣ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ‘ለሌሎች በጎችም’ ጭምር። (ዮሐ. 10:16) ጳውሎስ በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የጉባኤው አባላት አንዳቸው ለሌላው የሚያደርጉትን ድጋፍ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ገልጿል፤ እንዲህ ብሏል፦ “ለመጽናት የሚያስችላችሁን መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እጓጓለሁና፤ ይህን ስል እኔ በእናንተ እምነት እናንተም በእኔ እምነት እርስ በርሳችን እንድንበረታታ ነው።”—ሮም 1:11, 12

ሮም—የታላቅ ግዛት መዲና

በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የተዘገቡት ክንውኖች በተፈጸሙበት ጊዜ ሮም በወቅቱ ከዓለም ትልቋና ገናናዋ ከተማ ነበረች። የታላቅ ግዛት መዲና ነበረች፤ ይህ የሮም ኃያል መንግሥት በገናናነቱ ዘመን ከብሪታንያ እስከ ሰሜን አፍሪካ እንዲሁም ከአትላንቲክ ውቅያኖስ እስከ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ ድረስ ያስተዳድር ነበር።

ሮም የተለያየ ባሕል፣ ዘር፣ ቋንቋና አጉል እምነት ያላቸው ሰዎች የሞሉባት ከተማ ነበረች። በግዛቱ የሚኖሩ ሰዎችና ሸቀጣ ሸቀጦቻቸውን የጫኑ ነጋዴዎች በጥሩ ሁኔታ በተሠሩት በርካታ መንገዶች ከየአቅጣጫው ወደ ሮም ይተምሙ ነበር። በአቅራቢያው ያለው የኦስቲያ ወደብ ደግሞ ብዙ መርከቦችን ያስተናግዳል፤ መርከቦቹ ለሮም ያመጧቸውን የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦችና የቅንጦት ዕቃዎች የሚያራግፉት በዚሁ ወደብ ላይ ነው።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. በሮም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይኖሩ ነበር። ከነዋሪዎቹ መካከል ግማሽ የሚሆኑት ባሪያዎች ሳይሆኑ አይቀሩም፤ ከእነዚህም መካከል የተፈረደባቸው ወንጀለኞች፣ ወላጆቻቸው የሸጧቸው ወይም የጣሏቸው ልጆች እንዲሁም የሮም ሠራዊት የማረካቸው እስረኞች ይገኙበታል። ኢየሩሳሌም በ63 ዓ.ዓ. በጄኔራል ፖምፔ እጅ በወደቀች ጊዜ ከዚያ የተማረኩ አይሁዳውያንም ሮም ውስጥ ባሪያዎች ነበሩ።

ባሪያ ያልሆኑት አብዛኞቹ ነዋሪዎች፣ በተጨናነቁ ፎቆች ውስጥ የሚኖሩና መንግሥት ድጎማ የሚያደርግላቸው ድሆች ነበሩ። ይሁን እንጂ ንጉሠ ነገሥታቱ ዋና ከተማቸውን ወደር የለሽ በሆኑ ዕፁብ ድንቅ ሕንፃዎች አስውበዋት ነበር። ከሕንፃዎቹም መካከል ሕዝቡን ለማዝናናት ሲባል የተለያዩ ተውኔቶች፣ የትግል ግጥሚያዎችና የሠረገላ ውድድሮች በነፃ የሚቀርቡባቸው ቲያትር ቤቶችና ግዙፍ የሆኑ ስታዲየሞች ይገኛሉ።

6, 7. በዛሬው ጊዜ ያለው የክርስቲያን ጉባኤ ኢየሱስ ምሥራቹ ለሁሉም ብሔራት እንዲሰበክ የሰጠውን ተልእኮ እየተወጣ ያለው እንዴት ነው?

6 የክርስቲያን ጉባኤ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው ዓላማ ዛሬም አልተለወጠም። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ፈታኝ ሆኖም አስደሳች ሥራ ሰጥቷቸዋል። እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”—ማቴ. 28:19, 20

7 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ይህን ሥራ ለማከናወን እየተጠቀመ ያለው በይሖዋ ምሥክሮች የክርስቲያን ጉባኤ ነው። እርግጥ ነው፣ የተለያየ ቋንቋ ላላቸው ሰዎች መስበክ አስቸጋሪ ነው። ያም ሆኖ የይሖዋ ምሥክሮች ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እያዘጋጁ ነው። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ የምትገኝ እንዲሁም የመንግሥቱን መልእክት በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በትጋት የምትካፈል ከሆነ የምትደሰትበት በቂ ምክንያት አለህ። በምድር ላይ ስለ ይሖዋ ስም በሚገባ የመመሥከር መብት ከተሰጣቸው ጥቂቶች አንዱ ነህ!

8. ከክርስቲያን ጉባኤ ምን ጥቅም እናገኛለን?

8 በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ በደስታ እንድንጸና ለመርዳት ይሖዋ ዓለም አቀፋዊ የሆነ የወንድማማች ማኅበር ሰጥቶናል። ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች እንደሚከተለው ሲል ጽፏል፦ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት መሰብሰባችንን ቸል አንበል፤ ከዚህ ይልቅ እርስ በርስ እንበረታታ፤ ደግሞም ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ ይህን እናድርግ።” (ዕብ. 10:24, 25) የክርስቲያን ጉባኤ፣ ሌሎችን ማበረታታትና አንተም ራስህ መበረታታት የምትችልበት የይሖዋ ዝግጅት ነው። ከመንፈሳዊ ወንድሞችህና እህቶችህ አትራቅ። ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን ፈጽሞ ቸል አትበል!

‘እያንዳንዱ ሰው በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ሰማ’ (የሐዋርያት ሥራ 2:5-13)

የኢየሱስ ተከታዮች ሰው በሚበዛበት ጎዳና ላይ ለአይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት ለተለወጡ ሰዎች ሲሰብኩ።

“ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ በየቋንቋችን ሲናገሩ እየሰማናቸው ነው።”—የሐዋርያት ሥራ 2:11

9, 10. አንዳንዶች ሌላ ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች ምሥራቹን ለማድረስ ምን ጥረት እያደረጉ ነው?

9 በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል ላይ ተገኝተው የነበሩት አይሁዶችና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ምን ያህል ተደስተው ሊሆን እንደሚችል አስብ። እርግጥ ነው፣ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ የጋራ መግባቢያ የሆነ አንድ ቋንቋ (ምናልባትም ግሪክኛ ወይም ዕብራይስጥ) መናገር ይችሉ ይሆናል። አሁን ግን ‘እያንዳንዱ ሰው ደቀ መዛሙርቱ በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ሰማ።’ (ሥራ 2:6) እነዚያ ሰዎች ምሥራቹን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሲሰሙ ልባቸው እንደተነካ ጥርጥር የለውም። እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች በሌላ ቋንቋ የመናገር ተአምራዊ ስጦታ የላቸውም። ይሁን እንጂ ከሁሉም ብሔራት ለተውጣጡ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ለማድረስ ራሳቸውን ያቀረቡ ብዙዎች አሉ። እንዴት? አንዳንዶች በአቅራቢያቸው የሚገኝን በሌላ ቋንቋ የሚመራ ጉባኤ ለመርዳት አልፎ ተርፎም ወደ ሌላ አገር ሄደው ለማገልገል ሲሉ አዲስ ቋንቋ ለመማር ፈቃደኞች ሆነዋል። እነዚህ ወንድሞች ያደረጉት ጥረት ምሥራቹን የሚነግሯቸውን ሰዎች ያስደንቃቸዋል።

10 ክርስቲንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ከሌሎች ሰባት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር በመሆን የጉጅራቲ ቋንቋ ተማረች። ክርስቲን የሥራ ባልደረባዋ የሆነችን አንዲት የጉጅራቲ ቋንቋ ተናጋሪ ወጣት በአፍ መፍቻ ቋንቋዋ ሰላም አለቻት። ወጣቷ እጅግ በመደነቅ ክርስቲን እንደ ጉጅራቲ ያለ ከባድ ቋንቋ ለመማር ጥረት እያደረገች ያለችው ለምን እንደሆነ ጠየቀቻት። ክርስቲንም አጋጣሚውን ተጠቅማ ግሩም ምሥክርነት ሰጠቻት። ይህች ወጣት ክርስቲንን “በእርግጥም መልእክታችሁ እጅግ አስፈላጊ መሆን አለበት” አለቻት።

11. ሌላ ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ ዝግጅት ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

11 እርግጥ ነው፣ ሌላ ቋንቋ መማር የምንችለው ሁላችንም አይደለንም። ያም ሆኖ ሌላ ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ ዝግጅት ማድረግ እንችላለን። እንዴት? ለዚህ የሚረዳን አንዱ ነገር JW ላንግዌጅ የተባለው አፕሊኬሽን ነው፤ በዚህ አፕሊኬሽን በመጠቀም በአካባቢህ ብዙዎች በሚናገሩት ቋንቋ ሰላምታ መማር ትችላለህ። በዚህ ቋንቋ የምታነጋግራቸውን ሰዎች ትኩረት የሚስቡ አንዳንድ ቀለል ያሉ ዓረፍተ ነገሮችንም አፕሊኬሽኑ ላይ ታገኛለህ። ከ​jw.org ጋር አስተዋውቃቸው፤ ከተቻለም በድረ ገጹ ላይ በቋንቋቸው የሚገኙትን የተለያዩ ቪዲዮዎችና ጽሑፎች አሳያቸው። በአገልግሎት ላይ እንደነዚህ ባሉት መሣሪያዎች መጠቀም ደስታ ያስገኝልናል፤ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ወንድሞቻችን ከተለያዩ አገራት የመጡ ሰዎች ምሥራቹን ‘በገዛ ቋንቋቸው’ ሰምተው ሲደነቁ በማየት ያገኙትን ደስታ እኛም እንቀምሳለን።

በሜሶጶጣሚያ እና በግብፅ የሚኖሩ አይሁዳውያን

የአይሁድ ሕዝብ ታሪክ በኢየሱስ ክርስቶስ ዘመን (ከ175 ዓ.ዓ. እስከ 135 ዓ.ም.) የተባለው መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) እንዲህ ብሏል፦ “በአንድ ወቅት አሦራውያንና ባቢሎናውያን ከአሥሩ ነገድ [የእስራኤል] መንግሥት እንዲሁም ከይሁዳ መንግሥት በግዞት የወሰዷቸው ሰዎች የልጅ ልጆች በሜሶጶጣሚያ፣ በሜዶን እና በባቢሎን ይኖሩ ነበር።” ዕዝራ 2:64 ከባቢሎን ምርኮ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት እስራኤላውያን 42,360 ብቻ እንደነበሩ ይገልጻል። ይህ የሆነውም በ537 ዓ.ዓ. ነበር። ፍላቭየስ ጆሴፈስ እንደተናገረው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን “በባቢሎን አቅራቢያ ይኖሩ ነበር።” እነዚህ አይሁዳውያን ከሦስተኛው እስከ አምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ የባቢሎናውያን ታልሙድ የተባለውን ጽሑፍ አዘጋጅተዋል።

የጽሑፍ ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት ቢያንስ በስድስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. አይሁዳውያን በግብፅ ይኖሩ ነበር። በዚያን ዘመን ኤርምያስ፣ ሜምፊስን ጨምሮ ግብፅ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ለሚኖሩ አይሁዳውያን መልእክት ልኮ ነበር። (ኤር. 44:1 ግርጌ) የግሪክ ባሕል ተስፋፍቶ በነበረበት ዘመን በርካታ አይሁዳውያን ወደ ግብፅ እንደፈለሱ ይገመታል። ጆሴፈስ እንደተናገረው ከሆነ በእስክንድርያ መጀመሪያ ከሰፈሩት ሰዎች መካከል አይሁዳውያን ይገኙበታል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ከከተማዋ የተወሰነው ክፍል ለእነሱ ተሰጥቷል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ፊሎ የተባለው አይሁዳዊ ጸሐፊ፣ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ወገኖቹ “ከሊቢያ ጠረፍ አንስቶ እስከ ኢትዮጵያ ወሰን ድረስ” በመላው ግብፅ ይኖሩ እንደነበር ተናግሯል።

‘ጴጥሮስ ተነስቶ ቆመ’ (የሐዋርያት ሥራ 2:14-37)

12. (ሀ) ነቢዩ ኢዩኤል በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ከተፈጸመው ክንውን ጋር የሚያያዝ ምን ነገር ተናግሯል? (ለ) ደቀ መዛሙርቱ የኢዩኤል ትንቢት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ፍጻሜውን እንደሚያገኝ መጠበቃቸው ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

12 ጴጥሮስ ከተለያዩ አገራት ለመጣው ሕዝብ ንግግር ለማቅረብ ‘ተነስቶ ቆመ።’ (ሥራ 2:14) በልዩ ልዩ ቋንቋ የመናገር ተአምራዊ ችሎታ ያገኙት ከአምላክ እንደሆነና ይህም “በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ መንፈሴን አፈሳለሁ” የሚለው የኢዩኤል ትንቢት ፍጻሜ መሆኑን ለአድማጮቹ ገለጸላቸው። (ኢዩ. 2:28) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ “እኔም አብን እጠይቃለሁ፤ እሱም . . . ሌላ ረዳት ይሰጣችኋል” ብሏቸው ነበር፤ ኢየሱስ ይህን ረዳት “መንፈስ” ሲልም ጠርቶታል።—ዮሐ. 14:16, 17

13, 14. ጴጥሮስ የአድማጮቹን ልብ ለመንካት ጥረት ያደረገው እንዴት ነው? እኛስ እሱ የተጠቀመበትን ዘዴ መኮረጅ የምንችለው በምን መንገድ ነው?

13 ጴጥሮስ ለሕዝቡ ባቀረበው ንግግር መደምደሚያ ላይ የሚከተለውን ጠንከር ያለ ሐሳብ ተናገረ፤ “ይህን እናንተ በእንጨት ላይ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን አምላክ ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ቤት ሁሉ በእርግጥ ይወቅ” አላቸው። (ሥራ 2:36) እርግጥ ነው፣ ጴጥሮስን ያዳምጡት ከነበሩት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ በተገደለበት ወቅት በስፍራው አልነበሩም። ያም ሆኖ ለዚህ ድርጊት በብሔር ደረጃ ተጠያቂዎች ናቸው። ይሁንና ጴጥሮስ ወገኖቹ የሆኑትን አይሁዳውያን በአክብሮትና ልባቸውን በሚነካ መንገድ እንዳነጋገራቸው ልብ በል። የጴጥሮስ ዓላማ አድማጮቹን ማውገዝ ሳይሆን ንስሐ እንዲገቡ ማነሳሳት ነበር። ያዳምጡት የነበሩት ሰዎች ጴጥሮስ በተናገረው ነገር ቅር ተሰኝተው ይሆን? በፍጹም! እንዲያውም ሰዎቹ ‘ልባቸው እጅግ ተነካ።’ “ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻላል?” የሚል ጥያቄም አቀረቡ። ጴጥሮስ ሰዎቹን በአክብሮት ማነጋገሩ ብዙዎቹ ልባቸው እንዲነካና ንስሐ ለመግባት እንዲነሳሱ እንዳደረጋቸው ግልጽ ነው።—ሥራ 2:37

14 እኛም ጴጥሮስ የሰዎቹን ልብ ለመንካት የተጠቀመበትን ዘዴ መኮረጅ እንችላለን። ለሌሎች በምንሰብክበት ጊዜ የምናነጋግረው ሰው የሚሰነዝረውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ሐሳብ ሁሉ ለማረም ጥረት ማድረግ አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ በሚያስማሙን ነጥቦች ላይ ትኩረት ማድረጋችን የተሻለ ነው። በዚህ መንገድ በጋራ የሚያግባቡንን ነጥቦች ካነሳን በኋላ የአምላክን ቃል ተጠቅመን በዘዴ ልናስረዳው እንችላለን። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በዚህ መልኩ ከነገርናቸው ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በአብዛኛው ጥሩ ምላሽ ይሰጣሉ።

ክርስትና በጳንጦስ

በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት የጴጥሮስን ንግግር ካዳመጡት ሰዎች መካከል ከጳንጦስ የመጡ አይሁዳውያን ይገኙበታል፤ ጳንጦስ በትንሿ እስያ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኝ አውራጃ ነው። (ሥራ 2:9) ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹ ምሥራቹን ወደ ትውልድ አገራቸው ይዘው እንደተመለሱ ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም ጴጥሮስ የመጀመሪያ መልእክቱን የጻፈው እንደ ጳንጦስ ባሉ ቦታዎች “ተበትነው ለሚገኙ” አማኞች ጭምር ነው።g (1 ጴጥ. 1:1) ጴጥሮስ የጻፈው መልእክት እንደሚጠቁመው እነዚህ ክርስቲያኖች በእምነታቸው ምክንያት በሚደርሱባቸው “ልዩ ልዩ ፈተናዎች” ተጨንቀው ነበር። (1 ጴጥ. 1:6) ይህም ተቃውሞንና ስደትን ሊጨምር ይችላል።

የሮም ግዛት ክፍል የሆኑት የቢቲኒያና የጳንጦስ ገዢ የሆነው ትንሹ ፕሊኒ ለንጉሠ ነገሥት ትራጃን የጻፋቸው ደብዳቤዎች የጳንጦስ ክርስቲያኖች ስላጋጠሟቸው ፈተናዎች ተጨማሪ መረጃዎችን ይዘዋል። በ112 ዓ.ም. ገደማ ፕሊኒ ከጳንጦስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ የክርስትና “ወረርሽኝ” ፆታ፣ ዕድሜ ወይም ሥልጣን ሳይለይ በሁሉም ሰው ላይ ስጋት እንደፈጠረ ገልጿል። ፕሊኒ፣ ክርስቲያን እንደሆኑ ክስ የተሰነዘረባቸውን ሰዎች በመጀመሪያ ክርስትናን እንዲክዱ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል፤ ይህን ለማድረግ ፈቃደኞች ካልሆኑ ግን ያስገድላቸዋል። ክርስቶስን የረገመ ወይም ለጣዖታቱ አሊያም ለትራጃን ሐውልት ጸሎት ያቀረበ ማንኛውም ሰው ይለቀቅ ነበር። ሆኖም ‘እውነተኛዎቹ ክርስቲያኖች እነዚህን ነገሮች እንዲያደርጉ ማስገደድ እንዳልተቻለ’ ፕሊኒ በግልጽ ተናግሯል።

g እዚህ ላይ “ተበትነው ለሚገኙ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል “ዳያስፖራ” የሚል ትርጉም ካለው ግሪክኛ ቃል የተገኘ ነው። የቃሉ አገባብ በተለይ ከፓለስቲና ምድር ውጭ የሚኖሩ አይሁዳውያን ማኅበረሰቦችን ያመለክታል፤ ይህም ከመጀመሪያዎቹ የክርስትና አማኞች መካከል ብዙዎቹ ከአይሁድ ማኅበረሰብ የመጡ እንደሆኑ ይጠቁማል።

‘እያንዳንዳችሁ ተጠመቁ’ (የሐዋርያት ሥራ 2:38-47)

15. (ሀ) ጴጥሮስ ምን ተናገረ? በዚያ የነበሩት ሰዎችስ ምን ምላሽ ሰጡ? (ለ) በጴንጤቆስጤ ዕለት ምሥራቹን የሰሙት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዚያኑ ቀን ለመጠመቅ ብቁ የሆኑት ለምንድን ነው?

15 በ33 ዓ.ም. በዋለው በዚያ አስደሳች የጴንጤቆስጤ ዕለት ጴጥሮስ አዎንታዊ ምላሽ ለሰጡት አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች “ንስሐ ግቡ፤ እያንዳንዳችሁም . . . ተጠመቁ” አላቸው። (ሥራ 2:38) በውጤቱም 3,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች (በኢየሩሳሌም ወይም በኢየሩሳሌም አቅራቢያ በሚገኙ ኩሬዎች ውስጥ ሳይሆን አይቀርም) ተጠመቁ።e ይህ በስሜታዊነት የተወሰደ እርምጃ ነው? ይህ ዘገባ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጠኑ ሰዎች ወይም ክርስቲያን ወላጆች ያሏቸው ልጆች ዝግጁ ሳይሆኑ ቸኩለው እንዲጠመቁ ሰበብ ሊሆን ይችላል? በጭራሽ! በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት የተጠመቁት አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች የአምላክን ቃል በትጋት ያጠኑ እንደነበረ አስታውስ፤ ደግሞም ለይሖዋ የተወሰነ ብሔር አባላት ነበሩ። ከዚህም በተጨማሪ ቀናተኛ መሆናቸውን አስመሥክረዋል፤ ብዙ ርቀት ተጉዘው በዚህ ዓመታዊ በዓል ላይ መገኘታቸው ራሱ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል። ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ስለሚጫወተው ሚና የሚገልጹትን ወሳኝ እውነቶች አምነው ከተቀበሉ በኋላ አምላክን ማገልገላቸውን ለመቀጠል ዝግጁዎች ነበሩ፤ አሁን ግን አምላክን የሚያገለግሉት የተጠመቁ የክርስቶስ ተከታዮች ሆነው ነው።

ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች እነማን ነበሩ?

በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት የጴጥሮስን ስብከት ያዳመጡት “አይሁዶችና ወደ ይሁዲነት [የተለወጡ] ሰዎች” ነበሩ።—ሥራ 2:10

በየዕለቱ ይከናወን የነበረውን ምግብ የማከፋፈል “አስፈላጊ ጉዳይ” እንዲከታተሉ ከተሾሙት ብቃት ያላቸው ወንዶች መካከል ‘ወደ ይሁዲነት ተለውጦ የነበረው አንጾኪያዊው ኒቆላዎስ’ ይገኝበታል። (ሥራ 6:3-5) “ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች” የሚለው አገላለጽ የአይሁድን እምነት የተቀበሉ አሕዛብን ማለትም አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎችን ያመለክታል። እነዚህ ሰዎች ሙሉ በሙሉ አይሁዳዊ ተደርገው ይታዩ ነበር፤ ምክንያቱም የእስራኤላውያንን አምላክና የሙሴን ሕግ ተቀብለዋል፣ ሌሎች አማልክትን ማምለክ ትተዋል፣ ወንዶች ከሆኑ ተገርዘዋል፤ እንዲሁም የእስራኤል ብሔር አባል ሆነዋል።

አይሁዳውያን በ537 ዓ.ዓ. ከባቢሎን ግዞት ነፃ ከወጡ በኋላ ብዙዎቹ ከእስራኤል ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች የሰፈሩ ቢሆንም የአይሁድን እምነት መከተላቸውን አላቆሙም። በዚህም ምክንያት በጥንት ጊዜ በመካከለኛው ምሥራቅና ከዚያ ርቀው በሚገኙ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች ከአይሁድ እምነት ጋር መተዋወቅ ችለው ነበር። እንደ ሆራስና ሴኔካ ያሉ የጥንት ጸሐፊዎች እንደመሠከሩት በአይሁዳውያንና በእምነታቸው የተማረኩ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ እጅግ ብዙ ሰዎች ከአይሁድ ማኅበረሰብ ጋር ተቀላቅለዋል እንዲሁም ወደ ይሁዲነት ተለውጠዋል።

16. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ያሳዩት እንዴት ነበር?

16 ይሖዋ እነዚህን ሰዎች እንደባረካቸው በግልጽ ታይቷል። ዘገባው እንደሚከተለው ይላል፦ “ያመኑትም ሁሉ አብረው ነበሩ፤ ያላቸውም ነገር ሁሉ የጋራ ነበር፤ በተጨማሪም ያላቸውን ሀብትና ንብረት በመሸጥ ገንዘቡን ለሁሉም አከፋፈሉ። ለእያንዳንዱም ሰው የሚያስፈልገውን ያህል ሰጡ።”f (ሥራ 2:44, 45) እውነተኛ ክርስቲያኖች ሁሉ ይህን ዓይነቱን የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ፍቅር መኮረጅ እንደሚፈልጉ እሙን ነው።

17. አንድ ሰው ለመጠመቅ ብቁ እንዲሆን የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ ይኖርበታል?

17 አንድ ሰው ራሱን ለአምላክ ለመወሰንና ለመጠመቅ ሊወስዳቸው የሚገቡ በርካታ ቅዱስ ጽሑፋዊ እርምጃዎች አሉ። የአምላክን ቃል እውቀት መቅሰም አለበት። (ዮሐ. 17:3) እምነት ማዳበር እንዲሁም በቀድሞ ድርጊቱ ከልብ መጸጸቱን በማሳየት ንስሐ መግባት ይኖርበታል። (ሥራ 3:19) ከዚያም መለወጥ ወይም መመለስና ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማሙ ትክክለኛ ሥራዎችን መሥራት አለበት። (ሮም 12:2፤ ኤፌ. 4:23, 24) በመቀጠልም በጸሎት አማካኝነት ራሱን ለአምላክ መወሰን፣ ከዚያም መጠመቅ ይችላል።—ማቴ. 16:24፤ 1 ጴጥ. 3:21

18. የተጠመቁ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ምን መብት አላቸው?

18 ራስህን ለአምላክ ወስነህ የተጠመቅክ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ነህ? ከሆንክ ይህን መብት በማግኘትህ ደስ ሊልህ ይገባል። በመንፈስ ቅዱስ እንደተሞሉት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ደቀ መዛሙርት ሁሉ አንተም ለሌሎች በሚገባ በመመሥከርና የይሖዋን ፈቃድ በማድረግ አስደናቂ ነገሮችን ማከናወን ትችላለህ!

a “ኢየሩሳሌም—የአይሁድ እምነት ማዕከል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

b “ሮም—የታላቅ ግዛት መዲና” የሚለውን ሣጥን፣ “በሜሶጶጣሚያ እና በግብፅ የሚኖሩ አይሁዳውያን” የሚለውን ሣጥን እንዲሁም “ክርስትና በጳንጦስ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

c ‘ምላሶቹ’ ቃል በቃል የእሳት ነበልባል ሳይሆኑ “የእሳት ምላሶች የሚመስሉ” ነበሩ፤ ይህም መንፈስ ቅዱስ በእያንዳንዱ ደቀ መዝሙር ላይ መውረዱ የታየው የእሳት መልክ ባላቸው ነገሮች እንደሆነ የሚጠቁም አባባል ነው።

d “ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች እነማን ነበሩ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

e ለማነጻጸር ያህል፣ ነሐሴ 7, 1993 በኪየቭ፣ ዩክሬን በተደረገው ብሔራት አቀፍ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ በስድስት የመጠመቂያ ገንዳዎች ውስጥ 7,402 ሰዎች ተጠምቀው ነበር። ጠቅላላ የጥምቀት ሥርዓቱ ሁለት ሰዓት ከሩብ ፈጅቷል።

f ከሌሎች ቦታዎች የመጡት ሰዎች ተጨማሪ መንፈሳዊ እውቀት ለመቅሰም በኢየሩሳሌም ቆይተው ስለነበር ይህ ጊዜያዊ ዝግጅት በወቅቱ የሚያስፈልጋቸውን ለሟሟላት አስችሏል። ይህ በፈቃደኝነት የተደረገ ዝግጅት ነበር፤ በመሆኑም የኮሚኒዝም ርዕዮተ ዓለም ገጽታ እንደሆነ ተደርጎ መታየት የለበትም።—ሥራ 5:1-4

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ