የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖችና ዓለም
የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ገደመ እጅግ በጣም አስደናቂ የሆነ አንድ ነገር በመካከለኛው ምሥራቅ ተፈጸመ። የአምላክ አንድያ ልጅ ሰማያዊ መኖሪያውን ትቶ በሰው ልጆች ዓለም ውስጥ ለአጭር ጊዜ እንዲኖር ወደ ምድር ተላከ። አብዛኛው የሰው ልጅ እንዴት ተቀብሎት ይሆን? ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይመልስልናል፦ “[ኢየሱስ] በዓለም ነበረ፣ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፣ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው [ወደ እስራኤል] መጣ፣ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም።“—ዮሐንስ 1:10,11
ዓለም የአምላክ ልጅ የሆነውን ኢየሱስን አልተቀበለውም። ግን ለምን? ኢየሱስ አንዱን ምክንያት ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፦ “ዓለም . . . ሥራው ክፉ መሆኑን እመሰክርበታለሁና እኔን ይጠላኛል።“ (ዮሐንስ 7:7) በአንዳንድ የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች፣ በአንድ ኤዶማዊ ንጉሥና በአንድ ሮማዊ የፓለቲካ መሪ የተወከለው ያው ዓለም በመጨረሻ ኢየሱስን ገደለው። (ሉቃስ 22:66 እስከ 23:25፤ ሥራ 3:14,15፤ 4:24-28) ዓለም ለኢየሱስ ተከታዮችስ ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው? እነሱን ይቀበላቸው ይሆን? አልተቀበላቸውም። ኢየሱስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ “ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል“ በማለት ተከታዮቹን አስጠንቅቋቸው ነበር።—ዮሐንስ 15:19
በሐዋርያት ዘመን
ኢየሱስ የተናገረው ቃል በትክክል ተፈጽሟል። እርሱ ከሞተ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ሐዋርያቱ ተይዘው ታሠሩ፣ ተዛተባቸው እንዲሁም ተደበደቡ። (ሥራ 4:1-3፤ 5:17,18, 40) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ቀናተኛው እስጢፋኖስ ወደ አይሁዳውያን የሳንሄድሪን ሸንጎ ተጎትቶ ተወሰደና እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ተወገረ። (ሥራ 6:8-12፤ 7:54, 57, 58) ቆይቶም ሐዋርያው ያዕቆብ በቀዳማዊ ንጉሥ ሔሮድስ አግሪጳ ተገደለ። (ሥራ 12:1, 2) ጳውሎስም በሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት በአሕዛብ መካከል ተሰባጥረው ይኖሩ በነበሩ አይሁዳውያን አነሳሽነት ስደት ደርሶበታል።—ሥራ 13:50፤ 14:2, 19
የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት ተቃውሞ ሲደርስባቸው ምን አደረጉ? ገና ከጅምሩ ሃይማኖታዊ ባለ ሥልጣኖች በኢየሱስ ስም እንዳይሰብኩ በከለከሏቸው ጊዜ ሐዋርያት “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል“ በማለት አቋማቸውን ገለጹ። (ሥራ 4:19, 20፤ 5:29) ተቃውሞ በተነሳባቸው ጊዜ ሁሉ በዚሁ አቋማቸው ጸንተዋል። ያም ሆኖ ግን ሐዋርያው ጳውሎስ በሮማ ይገኙ የነበሩትን ክርስቲያኖች ’በበላይ ላሉት [መንግሥታዊ] ባለ ሥልጣኖች ተገዙ፤’ እንዲሁም “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ“ በማለት መክሯቸዋል። (ሮም 12:18፤ 13:1) በዚህ ምክንያት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ለውሳኔ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች መካከል ትክክለኛውን ሚዛን መጠበቅ ነበረባቸው። በአንድ በኩል አምላክን እንደ ዋናው ገዥያቸው አድርገው በመቀበል መታዘዝ አለባቸው በሌላው በኩል ደግሞ ለብሔራዊ ባለ ሥልጣኖች መገዛትና ከሁሉም ሰው ጋር በሰላም ለመኖር መሞከር ነበረባቸው።
በሮማው ዓለም ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች
በመጀመሪያው መቶ ዘመን በሮማ መንግሥት በሚተዳደረው ዓለም ውስት ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች የሮማ ጦር ሠራዊት ያስገኘው ፓክስ ሮማና ወይም የሮማ ሰላም ተጠቃሚዎች እንደነበሩ አያጠራጥርም። ሕግና ሥርዓት የተከበረበት የተረጋጋ ግዛት መኖሩ፣ ጥሩ ጥሩ መንገዶች መሠራታቸውና በመጠኑም ቢሆን ከስጋት ነፃ በሆነ መልኩ በመርከብ ለመጓዝ የሚቻል መሆኑ ለክርስትና መስፋፋት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ለኅብረተሰቡ ዕዳ እንዳለባቸው ተገንዝበው “የቄሣርን ለቄሣር . . . አስረክቡ“ የሚለውን የኢየሱስን ትዕዛዝ እንደተከተሉ ከአንዳንድ ሁኔታዎች በግልጽ መረዳት ይቻላል። (ማርቆስ 12:17) ሰማዕቱ ጀስቲን ለሮማው ንጉሠ ነገሥት አንቶኒስ ፓየስ (ከ138-161 እዘአ) በጻፈው ደብዳቤ ላይ ክርስቲያኖች ያለባቸውን ግብር “ከሰው ሁሉ ቀድመው“ ይከፍሉ ነበር ብሏል። (ፈረስት አፖሎጂ፣ ምዕራፍ 17) ክርስቲያኖች ያለባቸውን ግብር በጥንቃቄ ይከፍሉ ስለነበረ ተርቱልያን በ197 እዘአ ለሮማ ገዥዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ቀረጥ ሰብሳቢዎቻቸው “ክርስቲያኖችን የማመስገን ዕዳ እንዳለባቸው“ ጠቅሶላቸዋል። (አፖሎጂ፣ ምዕራፍ 42) ይህም ለበላይ ባለ ሥልጣኖች እንዲገዙ ጳውሎስ የሰጣቸውን ምክር የተከተሉበት አንዱ መንገድ ነበር።
ከዚህም በላይ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የክርስትና መሠረታዊ ሥርዓቶች እስከፈቀደላቸው ድረስ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በሰላም ለመኖር ይጥሩ ነበር። ሆኖም ይህ ቀላል አልነበረም። በዙሪያቸው የነበረው ዓለም እጅግ ሥነ ምግባር የጎደለው እንዲሁም በግሪካውያንና በሮማውያን የጣዖት አምልኮ የተዘፈቀ ነበር። ይህ የጣዖት አምልኮ ከጊዜ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱን ማምለክ የሚጨምር ሆኖ ነበር። በመሠረቱ የሮማ መንግሥት ሃይማኖት አረማዊነት ስለነበር ያንን ሃይማኖት የማይከተል ሰው የመንግሥት ጠላት እንደሆነ ተደርጎ ሊቆጠር ይችል ነበር። ታዲያ ክርስቲያኖች እንዴት ይሆኑ ይሆን?
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ኢ ጂ ሃርዲ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ተርቱሊያን ኅሊናውን የሚጠብቅ አንድ ክርስቲያን ከጣዖት አምልኮ ጋር ንክኪ አላቸው በማለት ሊፈጽማቸው የማይችላቸው በርካታ ነገሮች እንደነበሩ ዘርዝሯል። ለምሳሌ ያህል ውልን በመሐላ ማጽደቅ፣ በበዓላት ቀን በራቸውን በመብራት ማስጌጥ፣ አረማዊ በሆኑ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች መካፈል፣ አረማዊ በሆኑ ጨዋታዎችና የሰርከስ ትርኢቶች ላይ መገኘት፣ ዓለማዊ [የጥንት ግሪካውያንና ሮማውያን አረማዊ] የሥነ ጽሑፍ ትምህርቶችን ማስተማር፣ የውትድርና አገልግሎትና የሕዝብ ሹም መሆን።“-ክርስቲያኒቲ ኤንድ ዘ ሮማን ገቨርንመንት
አዎን፣ የክርስትናን እምነት ሳይክዱ በሮማዊው ዓለም ውስጥ መኖር አስቸጋሪ ነበር። የፈረንሳይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ደራሲ ኤ አሞን አንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “አንድ ክርስቲያን ከአምልኮ ጋር የተያያዘ ፈተና ሳያጋጥመው አንድ እርምጃ እንኳን መራመድ አይችልም ነበር። ክርስቲያናዊው አቋሙ በየዕለቱ ችግር ያመጣበታል። አኗኗሩ ከኅብረተሰቡ አመለካከት ጋር አይገጥምም። . . . በቤት፣ በመንገድ፣ በገበያ ሁሉ ተደጋጋሚ ችግሮች ያጋጥሙት ነበር። . . . ክርስቲያኑ ሮማዊ ዜጋ ሆነም አልሆነ በአንድ ቤተ መቅደስ ወይም ሐውልት አጠገብ ሲያልፍ ባርኔጣውን አውልቆ ሰላምታ መስጠት ነበረበት። ታዲያ አንድ ክርስቲያን ከዚህ ታቅቦ ከጥርጣሬ እንዴት ሊያመልጥ ይችላል? በሌላ በኩል ደግሞ የታማኝነት አቋሙን ካላፈረሰ እንዴት ይህን ግዴት ሊፈጽም ይችላል? ነጋዴ ከሆነና ገንዘብ ለመበደር ከፈለገ ለአበዳሪው ሰው በአማልክት ስም መማል ነበረበት። . . . በሕዝብ ላይ ቢሾምና ሹመቱን ቢቀበል መሥዋዕት እንዲያቀርብ ይጠበቅበት ነበር። ውትድርና ውስጥ ቢገባ ደግሞ መሐላ ከመፈጸምና በወታደታራዊ አገልግሎት ሥነ ሥርዓቶች ውስጥ ከመሳተፍ እንዴት ሊያመልጥ ይችላል?-ላ ቪ ኮቲዲየን ዴ ፕሬሚዬር ክሬቲየን (95 -197)(የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የዕለት ተዕለት ኑሮ፣ 95-197 እዘአ)
ጥሩ ዜጎች ቢሆኑም ስማቸው ይክፋፋ ነበር
በ60 ወይም በ61 እዘአ ገደማ ጳውሎስ የንጉሠ ነገሥት ኔሮች ፍርድ እየተጠባበቀ በሮም ባይኖር በነበረበት ጊዜ የአይሁድ መሪዎች የመጀመሪያዎቹን ክርስቲያኖች በተመለከተ “ይህ አንተ የምትከተለውን የሃይማኖት ክፍል በየቦታው ሰዎች እንደሚቃወሙት እናውቃለን“ ብለዋል። (ሥራ 28:22 የ1980 ትርጉም) የታሪክ መዛግብት እንደሚያሳዩት ሌሎች ሰዎች የክርስቲያኖችን ስም ያለ አግባብ ያክፋፉ ነበር። ዘ ራይዝ ኦቭ ክርስቲያኒቲ [የክርስትና እምነት አነሳስ] በተባለው መጽሐፋቸው ኢ ደብልዩ ባርንዝ እንዲህ ብለዋል፦ “በጥንቶቹ የክርስትና እምነት ጽሑፎች ክርስትና ንጹሕ ሥነ ምግባር ያለውና ሕግ አክባሪ እንቅስቃሴ ሆኖ ቀርቧል። አባላቱም ጥሩ ዜጎችና ታማኝ የመንግሥት ተገዚዎች ለመሆን ይፈልጉ ነበር። ከአረማውያን ጉድፈቶችና መጥፎ ምግባሮች የራቁ ነበሩ። በግል ሕይወታቸውም ሰላማዊ ጎረቤቶችና እምነት የሚጣልባቸው ወዳጆች ሆነው ለመገኘት ይጥሩ ነበር። ጭምቶች፣ ታታሪዎችና ንጹሖች እንዲሆኑ ትምህርት ይሰጣቸዋል። ምግባረ ብልሹነትና ልክስክስነት በተስፋፋበት አካባቢ ቢኖሩም ለቆሙላቸው መሠረታዊ እውነተኞች ነበሩ። የጾታ ሥነ ምግባራቸው ከፍተኛ በመሆኑ ጋብቻቸውን ያከብሩ ነበሩ፤ እንዲሁም ንጹሕ የቤተሰብ ኑሮ ነበራቸው። ይህን የመሰለ መልካም ሥነ ምግባር ስለነበራቸው በእነሱ ምክንያት ምንም ችግር ሊፈጠር አይችልም ብሎ የሚያስብ ሰው ይኖር ይሆናል። ሆኖም ለረጅም ጊዜ ተንቀዋል፤ ስማቸው ጠፍቷል እንዲሁም ተጠልተዋል።“
የጥንቱ ዓለም የኢየሱስን አቋም በመጥፎ እንደተረዳው ሁሉ የክርስቲያኖችም በትክክል አልተረዳላቸውም፤ በዚህም ምክንያት ይጠላቸው ነበር። ክርስቲያኖች ንጉሠ ነገሥቱንና አረማዊ አማልክትን አናመልክም ይሉ ስለነበር አምላክ የለም ትላላችሁ ተብለው ይወገዙ ነበር። አንድ ዓይነት የተፈጥሮ አደጋ ቢከሰት ይህ የደረሰው እናንተ አማልክትን በማስቆጣታቸው ምክንያት ነው ይባሉ ነበር። ብልግና የነበረባቸውን ቲያትሮች ወይም ደም አፋሳሽ የግላድያተር ትሪኢቶችን ስለማይመለከቱ የማኅበራዊ ኑሮ ጠላቶች አልፎ ተርፎም ’የሰውን ዘር የሚጠሉ’ ተብለው ይጠሩ ነበር። ጠላቶቻቸው “ኑፋቄ“ የሆነው የክርስትና እምነት ቤተሰብን የሚያፈራርስ በመሆኑ ለኅብረተሰቡ መረጋጋት አደገኛ ሃይማኖት ነው ይሉ ነበር። እንዲያውም ሚስቶቻቸው ክርስቲያኖች ከሚሆኑ ይልቅ ቢያመነዝሩ የሚሻላቸው አረማዊ ባሎች እንደነበሩ ተርቱሊያን ተናግራል።
ክርስቲያኖች በዚያን ጊዜ ተስፋፍቶ የነበረውን ፅንስ የማስወረድን ድርጊት ስለሚቃወሙ ይነቀፉ ነበር። ጠላቶቻቸው ግን ክርስቲያኖች ሕፃናትን ይገድላሉ በማለት ይወነጅሏቸው ነበር። የተሰው ሕፃናትን ደም በስብሰባዎቻቸው ጊዜ ይጠጣሉ እየተባለ ይወራባቸው ነበር። በሌላው በኩል ደግሞ ክርስቲያኖች ኅሊናቸው ደም እንዲበሉ እንደማይፈቅድላቸው እያወቁ ጠላቶቻቸው ግን ከደም የተሠሩ ምግቦችን እንዲበሉ ያስገድዷቸው ነበር። ስለዚህ እነዚህ ተቃዋሚዎች የሚያቀርቧቸው ክሶች እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ነበሩ።-በተርቱልያን የተጻፈው አፖሎጂ፣ ምዕርፍ 9
መጤዎች ናችሁ ተብለው ይናቁ ነበር
ታሪክ ጸሐፊው ኬኔት ስኮት ላትሬት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ክርስትና ከተቀናቃኞቹ [ከአይሁዶች እንዲሁም ከግሪካውያንና ከሮማውያን አረማዊ ሃይማኖቶች ጋር ሲነፃፀር ገና ትናንት የመጣ ነው በመባል መዘባበቻ ተደርጎ ነበር።“ (ኤ ሂስትሪ ኦቭ ኤክስፓንሽን ኦቭ ክርስቲያኒቲ፣ ጥራዝ 1፣ ገጽ 131) ሮማዊው ታሪክ ጸሐፊ ሲውቶኒየስ በሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ክርስትናን “አዲስ የመጣና ጎጂ የሆነ አጉል እምነት“ ሲል ጠርቶታል። ሌላው ቀርቶ ክርስቲያን የሚለው ስም ራሱ ይጠላ እንደነበረና ክርስቲያኖችም የተነቃፊ ሃይማኖት አባላት እንደነበሩ ተርቱሊያንም መስክሯል። ሮበርት ኤም ግራንት የሮማ መንግሥት ባለ ሥልጣኖች በሁለተኛው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩትን ክርስቲያኖች እንዴት ይመለከቷቸው እንደነበረ በመግለጽ “በመሠረቱ ክርስትና አላስፈላጊ እንደሆነ እንዲያውም ሊጎዳ የሚችል ሃይማኖት አድርገው ይመለከቱት ነበር“ ሲል ጽፈዋል።—ኸርሊ ክርስቲያኒቲ ኤንድ ሶሳይቲ
ተከታይ ለማፍራት ሕዝብን ይወርራሉ ይባሉ ነበር
የሶርቦን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ዣን በርናርዲ ሌ ፕርሚዬር ሲየክል ደ ሌግሊዝ (ቤተ ክርስቲያን ያሳለፈቻቸው የመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመናት) በተባለው መጸሐፋቸው ውስጥ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “[ክርስቲያኖች] በየቦታው እየሄዱ ላገኙት ሰው ሁሉ መናገር ነበረባቸው። በአውራ ጎዳናዎችና በከተሞች፣ ሕዝብ በሚበዛባቸው አደባባዮችና በየቤቱ እየሄዱ ለሚያገኟቸው ሰዎች ሁሉ መናገር ነበረባቸው። ተቀባይነት ቢያገኙም ባያገኙም ለድኾች፣ በሀብታቸው ለተጠላለፉት ባለ ጠጎች፣ ለዝቅተኛው የኅብረተሰቡ ክፍልና ለሮማ ክፍለ አገሮች አስተዳዳሪዎች ሁሉ መስበክ ነበረባቸው። . . . በእግር ወይም በመከብ እየተጓዙ እስከ ምድር ጫፍ ድረስ መሄድ ነበረባቸው።“
ታዲያ እንዲህ አድርገዋልን? እንዳደረጉ ማስረጃዎቹ ያሳያሉ። ፕሮፌሰር ሌኦን ኦሞ ክርስቲያኖች “በኃይለኛ ስብከታቸው“ ምክንያት ከሕዝብ ዘንድ የተቃውሞ አስተያየት ይሰነዘርባቸው እንደነበረ ተናግረዋል። ፕሮፌሰር ላቱሬትም አይሁዳውያን ተከታይ ለማፍራት የንበራቸው ቅንዓት እየከሰመ ሄደ፤ “ክርስቲያኖች ግን በሚስዮናዊነት ሥራቸው አካባቢውን ይወሩ ስለነበር የሕዝቡን ቁጣ አነሳስተዋል“ ሲሉ ተናግረዋል።
በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ ይኖር የነበረው ሮማዊ ፈላስፋ ሴልሰስ የክርስቲያኖችን የስብከት መንገዶች ነቅፏል። ክርስትና የመሃይማን ሃይማኖት እንደሆነና ሊያሳምን የሚችለውም ’ደንቆሮዎችን፣ ባሪያዎችን፣ ሴቶችንና ትንንሽ ልጆችን’ ነው ይል ነበር። ክርስቲያኖች “ሰዎቹ ነገሩን አስተውለው ሳይስቡበት እንዲያምኑ“ በማድረግ “የዋሆችን“ ይለውጣሉ ሲል ወንጅሏቸዋል። ለአዳዲሶቹ ደቀ መዛሙርት “ጥያቄ አትጠይቁ፤ ዝም ብላችሁ እመኑ“ ተብሎ ይነገራቸዋል ይል ነበር። ሆኖም ኦሪገን በጻፈው መሠረት ሴልሰስ ራሱ “በኢየሱስ መሠረተ ትምህርት በመመራት ሃይማኖቱን የተቀበሉት ተራ ሰዎች ብቻ አልነበሩም“ ሲል አምኗል።
ሃይማኖቶችን ለማዋሃድ የሚንቀሳቀሱ አልነበሩም
የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የእውነተኛው አንድ አምላክ እውነት ያለን እኛ ነን ይሉ ስለነበርም ተነቅፈዋል። ሃይማኖቶችን ለማዋሃድ ወይም ለማቀላቀል የሚደረገውን እንቅስቃሴ አይቀበሉም ነበር። ላቱሬት እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “[ክርስቲያኖች] በጊዜ ከነበሩት እምነቶች የተለየ አቋም በመያዝ ሌሎች ሃይማኖቶችን ይቃወሙ ነበር። . . . ሌሎቹ የሃይማኖት ቡድኖች ነገሮችን ችላ ብለው በዝምታ ያልፉ የነበረ ሲሆን እነሱ ግን ያለምንም መጠራጠር እውነቱን እንደያዙ ይገልጹ ነበር።“
በ202 እዘአ ንጉሠ ነገሥት ሰፕቴሚየስ ሰርቨረስ ክርሲያኖች ሰዎችን እያሳመኑ ሃይማኖታቸውን እንዳያስቀይሩ የሚከለክል አዋጅ አውጥቶ ነበር። ይህም ቢሆን ክርስቲያኖች ስለ እምነታቸው እንዳይመሰክሩ አላገዳቸውም። ላቱሬት ውጤቱን ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “[የመጀመሪያው ክርስትና] በጊዜ ከነበረው አረማዊነትና ከብዙዎቹ ማኅበራዊ ባሕሎች ጋር እንዲሁም በወቅቱ ከነበረው የሥነ ምግባር ልማድ ጋር ለመተባበር ሲል አቋሙን ለማላላት እምቢተኛ በመሆኑ በኅብረተሰቡ ዘንድ የተጠላ ቢሆንም በአቋሙ የሚጸና ድርጅት አቋቁሟል። የእምነት ተከታዮቹ የቀድሞ እምነታቸውን ለቅቀው መውጣታቸው ራሱ ማንኛውንም ስደት ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬና አዲስ አማኞችን ለማፍራት የሚያነሳሳ ቅንዓት የሚሰት ትልቅ ውስጣዊ እምነት ያድርባቸው ነበር።“
እንግዲያው ታሪክ የዘገበው ነገር ግልጽ ነው። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ጥሩ ዜጎች ለመሆንና ከሁሉም ሰዎች ጋር በሰላም ለመኖር ቢጥሩም ’የዓለም ክፍል’ ለመሆን ግን ባመዛኙ አሻፈረኝ ብለዋል። (ዮሐንስ 15:19) ባለ ሥልጣኖችን ያከብሩ ነበር። ቄሣር እንዳይሰብኩ ሲከለክላቸው ግን መስበካቸውን ከመቀጠል ሌላ ምንም አማራጭ አልነበራቸውም። ከሁሉም ሰዎች ጋር በሰላም ለመኖር ጥረት ያደርጉ የነበሩ ቢሆንም ሥነ ምግባራዊ አቋማቸውን ለማላላትና በአረማዊ የጣዖት አምልኮ ውስጥ ለመሳተፍ ግን እምቢተኞች ነበሩ። በዚህ ሁሉ ምክንያት ክርስቶስ ስለሚደርስባቸው ነገር አስቀድሞ እንደተናገረው ሁሉ ጠላቶቻቸው ይንቋቸው፣ ስማቸውን ያከፋፉ፣ ይጠሏጨውና ያሳድዷቸው ነበር።—ዮሐንስ 16:33
ከዓለም የተለዩ ሆነው ቀጠሉ ወይስ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ክርስቲያኖች ነን ይሉ የነበሩ ሰዎች በዚህ ነገር ላይ ያላቸውን አቋም ቀየሩ?
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ክርስቲያናዊ አቋሙ በየዕለቱ ችግር ያመጣበት ነበር፤ አኗኗሩ ከኅብረተሰቡ አመለካከት ጋር አይገጥምም ነበር”
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ክርስትና ከተቀናቃኞቹ . . . ጥንታዊነት ጋር ሲነፃፀር ገና ትናንት የመጣ ነው በመባል መዘባበቻ ተደርጎ ነበር“
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች የሮማን ንጉሠ ነገሥትና አረመኔያዊ አማልክትን አናመልክም ስላሉ አምላክ የለም ትላላችሁ ተብለው ይወገዙ ነበር
[ምንጭ]
Museo della Civiltà Romana, Roma
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
የመጀመሪያ መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የመንግሥቱ መልእክት ቀናተኛ ሰባኪዎች እንደሆኑ ተደርገው ይታወቁ ነበር
[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Cover: Alinari/Art Resource, N.Y.