የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ሰዎች ችግርና መከራ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
    • ምዕራፍ 26. በጭንቀት የተዋጡ ወላጆች ልጃቸው ከተኛበት የሆስፒታል አልጋ አጠገብ ቁጭ ብለው

      ምዕራፍ 26

      ሰዎች ችግርና መከራ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?

      ሰዎች አሳዛኝ ነገር ሲደርስባቸው “ለምን?” ብለው መጠየቃቸው የተለመደ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የማያሻማ መልስ እንደሚሰጥ ማወቃችን ምንኛ የሚያስደስት ነው!

      1. ሰይጣን በዓለም ላይ ለሚታየው መጥፎ ነገር መንስኤ የሆነው እንዴት ነው?

      ሰይጣን ዲያብሎስ በአምላክ ላይ ዓምጿል። በሌሎች ላይ የበላይ ሆኖ መግዛት ስለፈለገ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ማለትም አዳምና ሔዋን ከእሱ ጋር አብረው እንዲያምፁ አድርጓል። ሰይጣን ይህን ያደረገው ለሔዋን ውሸት በመንገር ነው። (ዘፍጥረት 3:1-5) ይሖዋ ጥሩ ነገር እንደነፈጋት እንዲሰማት አደረገ። ሰዎች የአምላክን ትእዛዝ ቢጥሱ ይበልጥ ደስተኛ እንደሚሆኑ የሚጠቁም ሐሳብ ሰነዘረ። ሰይጣን ለሔዋን እንደማትሞት በመግለጽ የመጀመሪያውን ውሸት ተናገረ። በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣንን “ውሸታምና የውሸት አባት” በማለት ይጠራዋል።—ዮሐንስ 8:44

      2. አዳምና ሔዋን ምን ለማድረግ መረጡ?

      ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን ብዙ ነገሮችን ሰጥቷቸዋል። ከአንድ ዛፍ በቀር በኤደን ገነት ውስጥ ከሚገኙት ዛፎች ሁሉ መብላት እንደሚችሉ ነግሯቸው ነበር። (ዘፍጥረት 2:15-17) ያም ሆኖ ግን አዳምና ሔዋን ከዚያ ዛፍ ፍሬ ለመብላት መረጡ። ሔዋን “ከዛፉ ፍሬ ወስዳ በላች።” በኋላ ደግሞ ‘አዳምም በላ።’ (ዘፍጥረት 3:6) ሁለቱም የአምላክን ትእዛዝ ጣሱ። አዳምና ሔዋን ፍጹም ወይም ከኃጢአት ነፃ ስለነበሩ ትክክል የሆነውን ማድረግ ይቀልላቸው ነበር። ሆኖም ሆን ብለው የአምላክን ትእዛዝ በመጣስ ኃጢአት የሠሩ ከመሆኑም ሌላ የእሱን አገዛዝ ለመቀበል አሻፈረኝ አሉ። ይህ ውሳኔ ከባድ መከራ አስከትሎባቸዋል።—ዘፍጥረት 3:16-19

      3. አዳምና ሔዋን ያደረጉት ውሳኔ በእኛ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል?

      አዳምና ሔዋን ኃጢአት ሲሠሩ ፍጽምና የጎደላቸው ሆኑ፤ ከዚያም ኃጢአትን ለዘሮቻቸው ሁሉ አወረሱ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አዳም ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።”—ሮም 5:12

      ታዲያ መከራ የሚደርስብን ለምንድን ነው? በተለያዩ ምክንያቶች መከራ ሊደርስብን ይችላል። አንዳንዴ እኛ ራሳችን ባደረግነው መጥፎ ውሳኔ ምክንያት ለመከራ ልንዳረግ እንችላለን። ሌሎች ባደረጉት መጥፎ ውሳኔ ምክንያት መከራ የሚደርስብን ጊዜም አለ። ባልተጠበቁ ክስተቶችም ምክንያት መከራ ሊደርስብን ይችላል።—መክብብ 9:11⁠ን አንብብ።

      ጠለቅ ያለ ጥናት

      አምላክ በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ለሚታየው ችግርና መከራ ተጠያቂ አይደለም የምንለው ለምን እንደሆነና መከራ ሲደርስብን ምን እንደሚሰማው እንመለከታለን።

      4. ለሚደርስብን መከራ ተጠያቂው ማን ነው?

      ብዙ ሰዎች መላውን ዓለም የሚገዛው አምላክ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይህ እውነት ነው? ቪዲዮውን ተመልከቱ።

      ቪዲዮ፦ ዓለምን የሚገዛው ማን ነው? (1:24)

      ያዕቆብ 1:13⁠ን እና 1 ዮሐንስ 5:19⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • ለሚደርስብን ችግርና መከራ ተጠያቂው አምላክ ነው?

      5. የሰይጣን አገዛዝ ምን ውጤት አስከትሏል?

      ቪዲዮውን ተመልከቱ።

      ቪዲዮ፦ አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?—ተቀንጭቦ የተወሰደ (3:07)

      ዘፍጥረት 3:1-6⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      • ሰይጣን ምን ውሸት ተናግሯል?—ቁጥር 4 እና 5⁠ን ተመልከት።

      • ሰይጣን፣ ይሖዋ የሰው ልጆችን ጥሩ ነገር እንደሚነፍጋቸው የሚጠቁም ምን ሐሳብ ተናግሯል?

      • ሰይጣን፣ ሰዎች ደስተኛ ለመሆን በይሖዋ አገዛዝ ሥር መሆን እንደማያስፈልጋቸው የጠቆመው እንዴት ነው?

      መክብብ 8:9⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • ይሖዋ ምድርን ባልገዛባቸው ጊዜያት በዓለማችን ላይ ምን ነገሮች ተከስተዋል?

      ምድር ከተፈጠረችበት ጊዜ አንስቶ ወደፊት ገነት እስከምትሆንበት ጊዜ ድረስ ያለውን ሁኔታ የሚያሳዩ ሥዕሎች፦ ሀ. የሚያማምሩ አትክልት የሞሉባት ገነት ለ. ላለፉት መቶ ዓመታት የዘለቀው የሰዎች አገዛዝ ምድር በሐሰት ሃይማኖት፣ በክፍፍል፣ በጦርነትና በብክለት የተሞላች እንድትሆን አድርጓል። በሥዕሉ ላይ ከሚታዩት አንዳንድ ኃያል መንግሥታት መካከል ሮም፣ ታላቋ ብሪታንያ፣ ቻይና፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ግሪክና ግብፅ ይገኙበታል። ሐ. መልሳ ገነት በሆነችው ምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች
      1. ሀ. አዳምና ሔዋን ከኃጢአት ነፃ ነበሩ፤ የሚኖሩትም ገነት ውስጥ ነበር። ሆኖም ሰይጣንን ሰምተው በይሖዋ ላይ ዓመፁ

      2. ለ. በአምላክ ላይ ካመፁ በኋላ ምድራችን በኃጢአት፣ በመከራና በሞት ተሞላች

      3. ሐ. ወደፊት ይሖዋ ኃጢአትን፣ መከራንና ሞትን ያስወግዳል። ሰዎች እንደ ድሮው ከኃጢአት ነፃ ሆነው በገነት ውስጥ ይኖራሉ

      6. ይሖዋ በእኛ ላይ የሚደርሰው መከራ ያሳስበዋል

      አምላክ በእኛ ላይ የሚደርሰው መከራ ምንም ግድ አይሰጠውም? ንጉሥ ዳዊትና ሐዋርያው ጴጥሮስ ምን ብለው እንደጻፉ ተመልከት። መዝሙር 31:7⁠ን እና 1 ጴጥሮስ 5:7⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • ይሖዋ በእኛ ላይ የሚደርሰውን መከራ እንደሚመለከትና ሁኔታችን እንደሚያሳስበው ማወቅህ ምን ስሜት ያሳድርብሃል?

      7. አምላክ በሰዎች ላይ የሚደርሰውን መከራ በሙሉ ያስወግዳል

      ኢሳይያስ 65:17⁠ን እና ራእይ 21:3, 4⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ተወያዩ፦

      • ይሖዋ በሰው ልጆች ላይ የደረሱት መጥፎ ነገሮች ያስከተሉትን ጉዳት ሙሉ በሙሉ እንደሚያስተካክል ማወቅህ የሚያጽናናህ ለምንድን ነው?

      ይህን ታውቅ ነበር?

      ሰይጣን የመጀመሪያውን ውሸት ሲናገር የይሖዋን ስም አጥፍቷል። ይሖዋ ፍትሐዊና አፍቃሪ ገዢ እንዳልሆነ የሚያስመስል ሐሳብ በመሰንዘር ስሙን አጉድፏል። በቅርቡ ይሖዋ በሰው ልጆች ላይ የደረሰውን ጉዳት ሙሉ በሙሉ በማስተካከል መልካም ስሙን ያድሳል። በሌላ አባባል የእሱ አገዛዝ ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ ያሳያል። የይሖዋ ስም መቀደስ ወይም ከነቀፋ ነፃ መሆን በጽንፈ ዓለም ውስጥ ተቀዳሚ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።—ማቴዎስ 6:9, 10

      አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “የተፈጠርነው ለመከራ ነው።”

      • አንተ ምን ትላለህ?

      ማጠቃለያ

      በዓለም ላይ ለሚታየው መጥፎ ነገር በዋነኝነት ተጠያቂ የሆኑት ሰይጣን ዲያብሎስና የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ናቸው። ይሖዋ የሚደርስብን መከራ በጣም ያሳስበዋል፤ በቅርቡ ደግሞ የደረሰብንን ጉዳት በሙሉ ያስተካክላል።

      ክለሳ

      • ሰይጣን ዲያብሎስ ለሔዋን ምን ውሸት ነግሯታል?

      • የአዳምና የሔዋን ዓመፅ በእኛ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል?

      • ይሖዋ የሚደርስብን መከራ እንደሚያሳስበው በምን እናውቃለን?

      ግብ

      ምርምር አድርግ

      ኃጢአት ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ ይሰጣል?

      “ኃጢአት ምንድን ነው?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

      ሰይጣን ዲያብሎስ በኤደን ገነት ስላስነሳው አወዛጋቢ ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ይህን ርዕስ አንብብ።

      “አምላክ መከራና ሥቃይ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?” (መጠበቂያ ግንብ ጥር 1, 2014)

      ብዙዎች ለሚያነሱት ከባድ ጥያቄ የተሰጠውን የሚያጽናና መልስ አንብብ።

      “ናዚዎች ያደረሱት እልቂት የተከሰተው ለምንድን ነው? አምላክ ጣልቃ ገብቶ ያላስቆመውስ ለምንድን ነው?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

      አንድ ሰው በዙሪያው የሚያየውን ችግር በተመለከተ ምን ተገንዝቧል?

      ከአሁን በኋላ ብቻዬን አይደለሁም (5:09)

  • የኢየሱስ ሞት የሚያድነን እንዴት ነው?
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
    • የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ማለትም አዳምና ሔዋን አምላክን ባለመታዘዛቸው ለኃጢአት፣ ለመከራና ለሞት ተዳርገናል።a ታዲያ ምንም ተስፋ የለንም ማለት ነው? በፍጹም! ይሖዋ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ከኃጢአትና ከሞት ነፃ የምንወጣበት ዝግጅት አድርጎልናል። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት ቤዛ እንደከፈለ ይናገራል። ቤዛ ማለት አንድን ሰው ነፃ ለማውጣት የሚከፈል ዋጋ ነው። ኢየሱስ የከፈለው ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ነው። (ማቴዎስ 20:28⁠ን አንብብ።) ኢየሱስ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚውን በፈቃደኝነት አሳልፎ በመስጠት አዳምና ሔዋን ያጡትን ነገር በሙሉ መልሰን የምናገኝበት መንገድ ከፍቶልናል። በተጨማሪም ኢየሱስ እሱና ይሖዋ ለእኛ ምን ያህል ጥልቅ ፍቅር እንዳላቸው አሳይቷል። ይህ ምዕራፍ ኢየሱስ ለአንተ ላደረገው ነገር ያለህን አድናቆት ያሳድግልሃል።

      1. የኢየሱስ ሞት በዛሬው ጊዜ የሚጠቅመን እንዴት ነው?

      ኃጢአተኞች ስለሆንን ይሖዋን የሚያሳዝኑ ብዙ ነገሮችን እናደርጋለን። ሆኖም በሠራነው ኃጢአት ከልብ ካዘንን፣ ይሖዋ ይቅር እንዲለን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከለመንንና ስህተታችንን ላለመድገም የቻልነውን ሁሉ ካደረግን ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት እንችላለን። (1 ዮሐንስ 2:1) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ጻድቅ የሆነው ክርስቶስ እንኳ ለዓመፀኞች ሲል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመሞት ከኃጢአት ነፃ አውጥቷቸዋልና። ይህን ያደረገው እናንተን ወደ አምላክ ለመምራት ነው።”—1 ጴጥሮስ 3:18

      2. የኢየሱስ ሞት ወደፊት የሚጠቅመን እንዴት ነው?

      ይሖዋ ኢየሱስን ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን እንዲሰጥ ልኮታል። ይህን ያደረገው በኢየሱስ “የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል” ነው። (ዮሐንስ 3:16) ኢየሱስ ባደረገው ነገር የተነሳ ይሖዋ የአዳም አለመታዘዝ ያስከተለውን ጉዳት በሙሉ በቅርቡ ያስተካክላል። በመሆኑም በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ እምነት እንዳለን ካሳየን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እናገኛለን!—ኢሳይያስ 65:21-23

      ጠለቅ ያለ ጥናት

      ኢየሱስ ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠው ለምን እንደሆነ በስፋት እንመለከታለን፤ በተጨማሪም የኢየሱስ መሥዋዕት ለአንተ የሚጠቅምህ እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።

      3. የኢየሱስ ሞት ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ያወጣናል

      ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      ቪዲዮ፦ ኢየሱስ የሞተው ለምንድን ነው?—ክፍል 1 (2:01)

      • አዳም አምላክን ባለመታዘዙ ምን አጋጣሚ አጥቷል?

      ሮም 5:12⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • አዳም ኃጢአት መሥራቱ በአንተ ላይ ምን ውጤት አስከትሏል?

      ዮሐንስ 3:16⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • ይሖዋ ልጁን ወደ ምድር የላከው ለምንድን ነው?

      1. አዳም በአምላክ ላይ ካመፀ በኋላ 2. ለቀስተኞች የሬሳ ሳጥን ተሸክመው ሲሄዱ ሀ. አዳም በአምላክ ላይ ካመፀ በኋላ ለ. ኢየሱስ ክርስቶስ ለ. 1. ኢየሱስ ክርስቶስ 2. የተለያየ ዕድሜ፣ ዘር፣ ባሕልና አስተዳደግ ያላቸው ሰዎች
      1. ሀ. ፍጹም ሰው የነበረው አዳም አምላክን ባለመታዘዙ የሰው ልጆችን ለኃጢአትና ለሞት ዳርጓቸዋል

      2. ለ. ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ አምላክን ስለታዘዘ የሰው ልጆች ፍጽምና ላይ መድረስና የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችሉበት መንገድ ከፍቷል

      4. የኢየሱስ ሞት ለሁሉም ሰው ጥቅም ያስገኛል

      ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      ቪዲዮ፦ ኢየሱስ የሞተው ለምንድን ነው?—ክፍል 2 (2:00)

      • የአንድ ሰው ሞት ሁሉንም ሰዎች ሊጠቅም የሚችለው እንዴት ነው?

      አንደኛ ጢሞቴዎስ 2:5, 6⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • ፍጹም ሰው የነበረው አዳም የሰው ልጆችን ለኃጢአትና ለሞት ዳርጓቸዋል። ኢየሱስም ፍጹም ሰው ነበር። ከዚህ አንጻር “ተመጣጣኝ ቤዛ” ሊከፍል የቻለው እንዴት ነው?

      5. ቤዛው ይሖዋ ለአንተ የሰጠው ስጦታ ነው

      የይሖዋ ወዳጆች ቤዛው ለእነሱ በግል የተሰጠ ስጦታ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይህን የሚያሳይ ምሳሌ ለመመልከት ገላትያ 2:20⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • ሐዋርያው ጳውሎስ ቤዛውን ለእሱ በግሉ እንደተሰጠው ስጦታ አድርጎ ይቆጥር እንደነበር በምን እናውቃለን?

      አዳም በሠራው ኃጢአት የተነሳ እሱም ሆነ ዘሮቹ ሞት ተፈርዶባቸዋል። ይሖዋ ግን ልጁን ለእኛ ሲል እንዲሞት በመላክ የዘላለም ሕይወት የምታገኝበት መንገድ ከፍቶልሃል።

      ቀጣዮቹ ጥቅሶች ሲነበቡ ይሖዋ ልጁ ሲሠቃይ ምን እንደተሰማው በዓይነ ሕሊናህ ለመሣል ሞክር። ዮሐንስ 19:1-7⁠ን እና 16-18⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • ይሖዋና ኢየሱስ ስላደረጉልህ ነገር ስታስብ ምን ይሰማሃል?

      አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢጠይቅህስ? “የአንድ ሰው ሞት ሁሉንም ሰዎች ሊያድን የሚችለው እንዴት ነው?”

      • ምን ብለህ ትመልሳለህ?

      ማጠቃለያ

      የኢየሱስ ሞት ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር የሚልበት መሠረት እንዲኖረው አድርጓል፤ እንዲሁም ለዘላለም በደስታ የምንኖርበት መንገድ ከፍቶልናል።

      ክለሳ

      • ኢየሱስ የሞተው ለምንድን ነው?

      • የኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ተመጣጣኝ ቤዛ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

      • የኢየሱስ ሞት ለአንተ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?

      ግብ

      ምርምር አድርግ

      የኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ‘ቤዛ’ ተብሎ የሚጠራው ለምንድን ነው?

      “የኢየሱስ መሥዋዕት ‘ለብዙዎች ቤዛ’ የሆነው እንዴት ነው?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

      ለመዳን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

      “ኢየሱስ ያድናል—እንዴት?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

      ይሖዋ ከባድ ኃጢአቶችን ጭምር ይቅር ይላል?

      “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው” (መጠበቂያ ግንብ ግንቦት 1, 2013)

      አንድ ሰው ስለ ክርስቶስ መሥዋዕት ማወቁ በማንነቱ ላይ ለውጥ እንዲያደርግ የረዳው እንዴት ነው?

      “አሁን የዓመፅ ባሪያ አይደለሁም” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

      a ኃጢአት የሚለው ቃል ትክክል ያልሆነ ነገር ማድረግን ብቻ የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከአዳምና ከሔዋን የወረስነውን ወደተሳሳተ አቅጣጫ የሚመራ ዝንባሌም ያመለክታል።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ