የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 11/15 ገጽ 26-28
  • “ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን ክፈሉ”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን ክፈሉ”
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መመሪያ የሚሆኑ አምስት መሠረታዊ ሥርዓቶች
  • አምላክን የሚያስከብር ስም አትርፍ
  • ግብር “የሠለጠነ ኅብረተሰብ” እንዲኖር ሲባል የሚከፈል ነው?
    ንቁ!—2004
  • ግብር መክፈል ይኖርብሃል?
    ንቁ!—2004
  • ቀረጥ መክፈል ይኖርብሃል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • ግብርን በተመለከተ የሚሰማው ቅሬታ እየጨመረ መጥቷል
    ንቁ!—2004
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 11/15 ገጽ 26-28

“ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን ክፈሉ”

“በዚህ ዓለም ላይ የማይቀሩ ነገሮች ሞትና ቀረጥ ናቸው።” ይህን የተናገሩት የታወቁት የ18ኛው መቶ ዘመን አሜሪካዊ የፖለቲካና የፈጠራ ሰው ቤንጃሚን ፍራንክሊን ናቸው። ብዙ ጊዜ የሚጠቀሰው ይህ አባባላቸው ቀረጥ የማይቀር ነገር መሆኑን ብቻ ሳይሆን የሚያስከትለውን ፍርሃት ጭምር የሚገልጽ ነው። ቀረጥ መክፈል ለብዙ ሰዎች የሞትን ያክል የሚያስጠላ ነገር ነው።

ምንም እንኳን ቀረጥ መክፈል ደስ የማያሰኝ ነገር ሊሆን ቢችልም እውነተኛ ክርስቲያኖች በቁም ነገር ሊመለከቱት የሚገባ ግዴታ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለሚገኘው የክርስቲያን ጉባኤ “ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፣ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፣ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፣ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ” ሲል ጽፎ ነበር። (ሮሜ 13:7) ኢየሱስ ክርስቶስም “የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” ብሎ በተናገረ ጊዜ በተለይ ቀረጥን መጥቀሱ ነበር።—ማርቆስ 12:14, 17

ይሖዋ መንግሥታዊ ‘የበላይ ባለ ሥልጣኖች’ እንዲኖሩ ፈቅዷል፤ እንዲሁም አገልጋዮቹ በአንፃራዊ ሁኔታ እንዲገዙላቸው ይፈልጋል። ታዲያ አምላክ የእሱ አምላኪዎች ቀረጥ እንዲከፍሉ የሚገፋፋው ለምንድን ነው? ጳውሎስ ሦስት መሠረታዊ የሆኑ ምክንያቶችን ጠቅሷል። እነሱም (1) ‘የበላይ ባለ ሥልጣኖች’ ሕግን የሚያፈርሱትን ለመቅጣት የሚያሳዩት ‘ቁጣ’፤ (2) በሚከፍለው ቀረጥ ረገድ የሚያጭበረብር ከሆነ ንጹሕ ሊሆን የማይችል የክርስቲያን ኅሊና፤ (3) የተለያዩ ግልጋሎቶችን ስለሚሰጡና በመጠኑም ቢሆን ሥርዓት ስለሚያስከብሩ ለእነዚህ “የሕዝብ አገልጋዮች [አዓት]” የመክፈል አስፈላጊነት ናቸው። (ሮሜ 13:1–7) ብዙዎች ቀረጥ መክፈልን አይወዱት ይሆናል። ይሁን እንጂ ፖሊስ ወይም የእሳት አደጋ መከላከያ በሌለበት፣ የመንገድ ጥገና በሌለበት፣ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች በሌሉበትና የፖስታ አገልግሎት በሌለበት አገር መኖርን ከዚያ የበለጠ እንደሚጠሉት የተረጋገጠ ነው። አንድ ጊዜ አሜሪካዊው የሕግ አዋቂ ኦሊቨር ዊንደል ሆልምስ “ቀረጦች የሠለጠነ ኅብረተሰብ ለማግኘት የምንከፍላቸው ነገሮች ናቸው” ሲሉ ገልጸውታል።

ለአምላክ አገልጋዮች ቀረጦችን መክፈል አዲስ ነገር አይደለም። የጥንቷ እስራኤል ነዋሪዎች ንጉሦቻቸውን ለመደጎም ቀረጦችን ይከፍሉ ነበር። ከእነዚህ ነገሥታት አንዳንዶቹም በሕዝቡ ላይ ከመጠን በላይ የሆነ ቀረጥ ይጭኑባቸው ነበር። አይሁዶችም ይገዟቸው ለነበሩት እንደ ግብፅ፣ ፋርስና ሮም ለመሳሰሉት የውጭ ኃይሎች ግብርና ቀረጥ ይከፍሉ ነበር። ስለዚህ በጳውሎስ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ጳውሎስ ቀረጥ ስለመክፈል በጠቀሰበት ጊዜ ስለ ምን እየተናገረ እንዳለ በሚገባ ያውቁ ነበር። ቀረጦቹ ምክንያታዊ ሆኑም አልሆኑም እንዲሁም መንግሥት ገንዘቡን ለምንም ያውለው ለምን የሚፈለግባቸውን ቀረጥ የመክፈል ግዴታ እንደነበረባቸው ያውቁ ነበር። ዛሬ ባሉ ክርስቲያኖችም ላይ ይኸው መሠረታዊ ሥርዓት ይሠራል። ሆኖም በዚህ በተወሳሰበ ዘመን የሚፈለግብንን ቀረጥ ስንከፍል የትኞቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመሪያ ሊሆኑን ይችላሉ?

መመሪያ የሚሆኑ አምስት መሠረታዊ ሥርዓቶች

ሥርዓታማ ሁን። ‘የሰላም አምላክ እንጂ የሁከት አምላክ ያልሆነውን’ ይሖዋን እናገለግላለን፤ እንዲሁም እንመስለዋለን። (1 ቆሮንቶስ 14:33፤ ኤፌሶን 5:1) ቀረጥ መክፈልን በተመለከተ ሥርዓታማ መሆን በጣም አስፈላጊ ነው። ሰነዶቻችሁ የተሟሉ፣ ትክክለኛና በሥርዓት የተቀመጡ ናቸውን? ብዙውን ጊዜ በጣም ውድ የሆነ የፋይል ማስቀመጫ ካቢኔት አያስፈልግም። (እንደ ደረሰኞች ያሉ) ልዩ ልዩ ወጪዎችህን የሚገልጹ ወረቀቶችን የያዙ የእያንዳንዱ ሰነድ ስም የተለጠፈበት ማኅደር (ክርታስ) ሊኖርህ ይችላል። እነዚህን ሰነዶች ተለቅ ባሉ ማኅደሮች ውስጥ በእያንዳንዱ ዓመት ከፋፍሎ ማስቀመጥ በቂ ሊሆን ይችላል። ምናልባት መንግሥት የቆዩ ሰነዶችን ለመመርመር እፈልጋለሁ ሊል ስለሚችል በብዙ አገሮች እነዚህን ፋይሎች ለብዙ ዓመታት ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው። ስለዚህ የማያስፈልግ መሆኑን እስክታረጋግጥ ድረስ ምንም ነገር አትጣል።

ሐቀኛ ሁን። ጳውሎስ “ስለ እኛ መጸለያችሁን አታቁሙ፤ እኛ ሐቀኛ ሕሊና አለን ብለን እናምናለን፤ ምክንያቱም በሁሉም ነገር በሐቅ እየሠራን ለመኖር እንመኛለን” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 13:18 አዓት) የሚፈለግብንን ቀረጥ በምንከፍልበት ጊዜ ማንኛውንም ውሳኔ ስናደርግ ሐቀኛ ለመሆን ያለን ልባዊ ፍላጎት ሊመራን ይገባል። በመጀመሪያ ለመንግሥት ሪፖርት በሚደረገው ገቢ መሠረት የሚከፈለውን ቀረጥ አስብ። በብዙ አገሮች ከጉርሻ፣ ከታቀደው በላይ በመሠራቱ ከሚገኝ ትርፍ፣ ከሽያጭ የሚገኙ ተጨማሪ ገቢዎች ከተገለጸው በላይ ሲሆኑ ቀረጥ ይከፈልባቸዋል። “ሐቀኛ ሕሊና” ያለው አንድ ክርስቲያን በሚኖርበት አገር ለምን ዓይነት ገቢ ቀረጥ መክፈል እንዳለበት ጠይቆ በመረዳት ተገቢውን ቀረጥ ይከፍላል።

ሁለተኛው ጉዳይ የቀረጥ ቅናሽን የሚመለከት ነው። መንግሥታት ብዙውን ጊዜ ቀረጥ ከፋዮች ቀረጥ እንዲከፍሉ ከሚያደርጓቸው ገቢዎች ላይ አንዳንድ ወጪዎችን እንዲቀንሱ ይፈቅዱላቸዋል። በዚህ አጭበርባሪ በሆነ ዓለም ውስጥ እነዚህን የሚቀነሱ ወጪዎች በሚናገሩበት ጊዜ “ያልሆነውን ፈጥሮ ማቅረብ” ምንም ስሕተት የለውም ብለው ያስባሉ። አንድ በዮናይትድ ስቴትስ የሚኖር ሰው ለሚስቱ ዋጋው በጣም ውድ የሆነ ምርጥ ፀጉራም ኮት ገዛላት። ከዚያም የንግድ ቦታውን “ለማስጌጥ” እንደገዛው በማስመሰል የሚከፍለው ቀረጥ እንዲቀነስለት ለማድረግ በሱቁ ውስጥ ለአንድ ቀን ሰቀለው! አንድ ሌላ ሰው ደግሞ ለሴት ልጁ ሠርግ ያወጣውን ወጪ ለንግድ ያወጣሁት ወጪ ነው በማለት የሚከፍለው ቀረጥ እንዲቀነስለት ጠየቀ። አንድ ሌላ ሰው ደግሞ ምንም እንኳን ባለቤቱ ለብዙ ወራት አብራው ወደ ሩቅ ምሥራቅ የተጓዘችው ለራሷ የግል ጉዳይና ለመዝናናት ቢሆንም የእሷን ወጪ ከንግድ ወጪው ጋር በመደመር የሚከፍለው ቀረጥ እንዲቀነስለት ለማድረግ ሞክሯል። እንደዚህ ዓይነት የማጭበርበር ድርጊቶችን ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም። የንግድ ወጪ ሳይሆን የንግድ ወጪ እንደሆነ በማስመሰል ቀረጥ ማስቀነስ አምላካችን ይሖዋ ፈጽሞ የሚጠላው አንዱ የውሸት ዓይነት መሆኑ በግልጽ ተቀምጧል።—ምሳሌ 6:16–19

ጥንቁቅ ሁን። ኢየሱስ ተከታዮቹ “እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች” እንዲሆኑ አጥብቆ መክሯቸዋል። (ማቴዎስ 10:16) ይህ ምክር የቀረጥ አከፋፈላችንንም በተመለከተ በሚገባ ሊሠራ ይችላል። በተለይ በበለጸጉት አገሮች በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ምን ያህል ቀረጥ መክፈል እንዳለባቸው እንዲያሰላላቸው የሒሳብ ሥራ ለሚያካሂድ ድርጅት ወይም ለአንዳንድ የሒሳብ አዋቂዎች ገንዘብ ይከፍላሉ። ከዚያም ፈርመው ቼኩን ይልካሉ። “የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል” የሚለውን በምሳሌ 14:15 ላይ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ ማለት የሚያስፈልገው በዚህ ጊዜ ነው።

ብዙ ቀረጥ ከፋዮች ከመንግሥት ጋር ይጋጫሉ ምክንያቱም አንዳንድ አታላይ የሆኑ የሒሳብ ሠራተኞች ወይም ልምድ የሌላቸው የቀረጥ አዘጋጂዎች ‘የሚነግሯቸውን ሁሉ ስለሚያምኑ’ ነው። እንግዲያው ብልህ መሆን ምንኛ የተሻለ ነው! ማንኛውንም ሰነድ ከመፈረምህ በፊት በጥንቃቄ በማንበብ ረገድ ጠንቃቃ ሁን። አንድ ሒሳብ፣ ሳይሞላ የቀረ ነገር ወይም ከጠቅላላ ገቢው ላይ የሚቀነሰው ወጪ ግር የሚል ሆኖ ካገኘኸው እንዲብራራልህ አድርግ። እንዲያውም አስፈላጊ ከሆነ ነገሩ ትክክለኛና ሕጋዊ መሆኑ በደንብ እስኪገባህ ድረስ በተደጋጋሚ እንዲብራራልህ አድርግ። እውነት ነው፣ በብዙ አገሮች የቀረጥ ሕጎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ የተወሳሰቡ እየሆኑ ነው፤ ይሁን እንጂ በተቻለ መጠን የምትፈርምበትን ማንኛውንም ነገር ማስተዋል የጥበብ መንገድ ነው። አንዳንድ ጊዜ ስለ ቀረጥ ሕግ የሚያውቅ መሰል ክርስቲያን አንዳንድ ጥልቀት ያላቸውን ሐሳቦች እንዲነግርህ ማድረግ ትችል ይሆናል። ቀረጥን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በጠበቃነት የሚከታተል አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ “ሒሳብ ያዥህ ከጠበቅከው በላይ ጥሩ የሆነ አንድ እውነት የሚመስል ሐሳብ ቢያቀርብልህ ማጭበርበር የታከለበት ሊሆን ይችላል ብሎ መጠርጠሩ አይከፋም!” ሲል እጥር ምጥን ባለ አነጋገር ገልጿል።

ኃላፊነቱን የምትሸከም ሁን። ሐዋርያው ጳውሎስ “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና” ሲል ጽፏል። (ገላትያ 6:5) ቀረጥ መክፈልን በተመለከተ እያንዳንዱ ክርስቲያን ሐቀኛና ሕግ አክባሪ የመሆንን ኃላፊነት መሸከም አለበት። ይህ የጉባኤ ሽማግሌዎች በእነሱ ጥበቃ ሥር ያለውን መንጋ የሚቆጣጠሩበት ጉዳይ አይደለም። (ከ2 ቆሮንቶስ 1:24 ጋር አወዳድር።) አንድን ከባድ ኃጢአት ምናልባትም በማኅበረሰቡ ውስጥ ነቀፋ የሚያስከትል የማጭበርበር ድርጊት መፈጸሙን እስካላወቁ ድረስ በቀረጥ ጉዳዮች ውስጥ ራሳቸውን ጣልቃ አያስገቡም። በአጠቃላይ ይህ ጉዳይ ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥዓቶችን በሥራ ላይ በማዋል ረገድ ግለሰቡ ክርስቲያን በሚገባ የሠለጠነ ሕሊናውን የመጠቀም ኃላፊነት የሚያስከትልበት ነው። (ዕብራውያን 5:14) ይህም አንድን የቀረጥ ሰነድ ማንም አዘጋጀው ማን በዚያ ላይ መፈረምህ ሰነዱን እንዳነበብከውና በላዩ ላይ የሰፈረውን ነገር እውነት ነው ብለህ እንደምታምን የሚያሳይ በመሆኑ በሕግ ፊት ሊያስጠይቅህ እንደሚችል ማወቅንም ይጨምራል።a

የማትነቀፍ ሁን። ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ለተሰጣቸው ኃላፊነት ብቁ ለመሆን ‘የማይነቀፉ’ መሆን አለባቸው። በተመሳሳይም መላው ጉባኤ በአምላክ ፊት የማይነቀፍ መሆን ይኖርበታል። (1 ጢሞቴዎስ 3:2፤ ከኤፌሶን 5:27 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ ቀረጥ በመክፈልም ጭምር ቢሆን በኅብረተሰቡ ዘንድ መልካም ስም እንዲኖራቸው ለማድረግ ይጥራሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በዚህ ረገድ ምሳሌ ትቷል። የእሱ ደቀ መዝሙር የሆነው ጴጥሮስ ኢየሱስ የቤተ መቅደስ ቀረጥ ማለትም ሁለቱን ዲናር አይከፍል እንደሆነ ተጠይቆ ነበር። ቤተ መቅደሱ የአባቱ ቤት ስለሆነና ማንም ንጉሥ ደግሞ ከገዛ ልጁ ቀረጥ ስለማይጠይቅ በእርግጥ ኢየሱስ ከዚህ ቀረጥ ነፃ ነበር። ኢየሱስ ይህን ቢናገርም ቀረጡን ከፍሏል። እንዲያውም የሚፈለገውን ገንዘብ ለማግኘት ተአምር ተጠቅሟል! በትክክል ከቀረጥ ነፃ ሆኖ ሳለ የከፈለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ራሱ “እንዳናሰናክላቸው” ብሏል።—ማቴዎስ 17:24–27b

አምላክን የሚያስከብር ስም አትርፍ

ዛሬ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም በተመሳሳይ ሌሎችን እንዳያሰናክሉ ይጠነቀቃሉ። እንግዲያው በዓለም ዙሪያ በቡድን ደረጃ ሐቀኞችና ቀረጥ የሚከፍሉ ዜጎች ናቸው የሚል መልካም ስም ማግኘታቸው አያስደንቅም። ለምሳሌ ያክል ኤል ዲያሪዮ ቫስኮ የተባለው የስፔይን ጋዜጣ በአገሪቱ ውስጥ በጣም ስለተስፋፋው ቀረጥን ያለመክፈል ድርጊት አስተያየቱን ሰጥቶ ነበር። ነገር ግን “በዚህ የማይወቀሱት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው። በሚገዙበትም ሆነ በሚሸጡበት ጊዜ ቀረጥ ለመክፈል የሚያስታውቁት [የዕቃው] ዋጋ ፍጹም ትክክለኛ የሆነውን ነው” ሲል ገልጾ ነበር። በተመሳሳይም ሳን ፍራንሲስኮ ኤግዛማይነር የተባለው የዩናይትስ ስቴትስ ጋዜጣ ከጥቂት ዓመታት በፊት የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቶ ነበር፦ “[የይሖዋ ምሥክሮችን] ምሳሌ የሚሆኑ ዜጎች አድርጋችሁ ልትመለከቷቸው ትችላላችሁ። ቀረጥ በወቅቱ ይከፍላሉ፣ በሽተኞችን ያስታምማሉ፣ መሃይምነትን ይዋጋሉ።”

ይህንን ትጋት በተሞላበት ጥረት የተገኘ መልካም ስም ሊያጎድፍ የሚችል ማንኛውንም ነገር መሥራት የሚፈልግ እውነተኛ ክርስቲያን አይኖርም። ቀረጥ ለማጭበርበር የምትችልበት አጋጣሚ ቢፈጠር የተወሰነ ገንዘብ ለማዳን ስትል ለማጭበርበር ትመርጣለህን? በፍጹም። መልካም ስምህ ከሚጎድፍና በሥነ ምግባር አቋምህ አልፎ ተርፎም ለይሖዋ ባለህ አምልኮ ላይ ነቀፋ ከምታመጣ ገንዘብ ብታጣ እንደሚሻልህ የተረጋገጠ ነው።

እውነት ነው፣ ንጹሕ የሥነ ምግባር አቋም ያለው ሐቀኛ ሰው በመሆን መልካም ስም ማትረፍ አንዳንድ ጊዜ ብዙ ገንዘብ እንድታጣ ሊያደርግህ ይችላል። ይህም የጥንቷ ግሪክ ፈላስፋ ፕላቶ ከ24 መቶ ዓመታት በፊት እንደተናገረው ነው፦ “የገቢ ቀረጥ በሚኖርበት ጊዜ ለተመሳሳይ ገቢ ሐቀኛ ሰው ብዙ ሲከፍል አታላይ ደግሞ ያነሰ ይከፍላል።” ሐቀኛው ሰው ለሐቀኝነት ሲል ይህን ገንዘብ በመክፈሉ በፍጹም አይጸጸትም በማለት ሊያክልበት ይችል ነበር። ይህን ዓይነቱን መልካም ስም ለማትረፍ ሲባል እንኳ የተከፈለውም ቢከፈል ምንም አይደለም። ይህ ሁኔታ በእርግጥ ለክርስቲያኖች ይሠራል። ያላቸው መልካም ስም ለእነሱ በጣም ውድ ነገር ነው፤ ምክንያቱም መልካም ስማቸው ሰማያዊ አባታቸውን ያስከብራል፤ እንዲሁም ሌሎች ሰዎችን ወደ እነሱ የአኗኗር መንገድና ወደ አምላካቸው ወደ ይሖዋ ይስባል።—ምሳሌ 11:30፤ 1 ጴጥሮስ 3:1

ይሁን እንጂ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሁሉም በላይ ከይሖዋ ጋር ያላቸውን የግል ዝምድና ከፍ አድርገው ይመለከታሉ። አምላክ የሚያደርጉትን ማንኛውን ነገር ይመለከታል፤ እነሱም እሱን ማስደሰት ይፈልጋሉ። (ዕብራውያን 4:13) ስለዚህ መንግሥትን ለማታለል እንዲሞክሩ የሚመጣባቸውን ፈተና ይቃወማሉ። አምላክ ሐቀኛና ትክክለኛ በሆነ አኗኗር እንደሚደሰት ያውቃሉ። (መዝሙር 15:1–3) የይሖዋ አምላክን ልብ ለማስደሰት ስለሚፈልጉ የሚፈለግባቸውን ቀረጥ ሁሉ ይከፍላሉ።—ምሳሌ 27:11፤ ሮሜ 13:7

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ከማያምን የትዳር ጓደኛ ጋር በመሆን ገቢያቸውን በቅጽ ለሚሞሉ ክርስቲያኖች ይህ ሁኔታ ፈታኝ ሊሆን ይችላል። አንዲት ክርስቲያን ሚስት የራስነትን መሠረታዊ ሥርዓት ለቄሣር የቀረጥ ሕግ ከመታዘዝ አስፈላጊነት ጋር ሚዛናዊ ለማድረግ ጥንቃቄ የተሞላበት ጥረት ማድረግ አለባት። ይሁን እንጂ እያወቁ የተጭበረበረ ሰነድ መፈረም ሊያስከትል የሚችለውን ሕጋዊ ተጠያቂነት ማሰብ ይኖርባታል።—ከሮሜ 13:1 እና ከ1 ቆሮንቶስ 11:3 ጋር አወዳድር።

b የሚገርመው ነገር ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ ያጋጠመውን ይህን ሁኔታ የመዘገበው የማቴዎስ ወንጌል ብቻ ነው። ከዚህ በፊት ማቴዎስ ራሱ ቀረጥ ሰብሳቢ ስለነበረ በዚህ ጉዳይ ላይ ኢየሱስ ያሳየው ዝንባሌ እንዳስገረመው ምንም ጥርጥር የለውም።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ