የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 6/15 ገጽ 28-31
  • የነጠላነት ኑሮ የኢኮኖሚ ችግር ባለበት ጊዜ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የነጠላነት ኑሮ የኢኮኖሚ ችግር ባለበት ጊዜ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ያለህበትን ሁኔታ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት
  • የነገሮችን መልካም ጎን ተመልከት
  • አገልግሎትህን ልታሰፋው ትችላለህን?
  • የወደፊቱ አስተማማኝ ሁኔታ
  • ነጠላነትንና ትዳርን አስመልክቶ የተሰጠ ጥበብ ያዘለ ምክር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • ነጠላነት አሳብ ሳይከፋፈል ለማገልገል የሚያስችል አጋጣሚ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • በይሖዋ አገልግሎት ደስተኛ የሆኑ ያላገቡ ክርስቲያኖች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ጋብቻ​—አፍቃሪ ከሆነው አምላክ የተገኘ ስጦታ
    ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 6/15 ገጽ 28-31

የነጠላነት ኑሮ የኢኮኖሚ ችግር ባለበት ጊዜ

“25 ዓመት ሲሆነኝ ለማግባት ፈለግሁ” ይላል በምዕራብ አፍሪካ የሚኖር ቹክስ የተባለ አንድ ሰው። “ለትዳር የምትሆነኝ አንዲት ልጅ አስቤ ነበር፤ እርሷም የትዳር ጓደኛ እንድሆናት ተስማምታ ነበር። ችግሩ ገንዘብ ነበር። አባቴና ታላቅ ወንድሜ ከሥራ ተባረዋል፤ ታናናሽ ወንድሞቼና እህቶቼ ደግሞ ተማሪዎች ነበሩ። ቤተሰቡ ሁሉ የሚጠብቀው የእኔን እጅ ነበር። ይባስ ብሎ ደግሞ ወላጆቼ ታመሙ፤ ይህም ለሕክምና የሚከፈል ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘትን የሚጠይቅ ነበር።”

የይሖዋ ምሥክር የሆነው ቹክስ የሚያገባትን ሚስት ለማስተዳደር ሳይችል ትዳር ውስጥ መግባት አልፈለገም። በ1 ጢሞቴዎስ 5:8 ላይ ያሉትን የጳውሎስ ቃላት ልብ ብሎ ነበር፦ “ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፣ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።”

ቹክስ ሐሳቡን በመቀጠል “ጠንክሬ ብሠራም ገንዘቡ በፍጹም የሚበቃ አልነበረም። በዚህም ምክንያት የጋብቻችን እቅድ በተደጋጋሚ ለሌላ ጊዜ ይተላለፍ ነበር። በመጨረሻም አንድ ሰው እርሷን ለማግባት አባቷን እንደጠየቀ የሚገልጽ ደብዳቤ ከልጅቷ ደረሰኝ። አባቷም ተስማሙ። ደብዳቤዋ ከመጣ ከጥቂት ቀናት በኋላ ቀለበት አደረጉ” ሲል ተናግሯል።

ልክ እንደ ቹክስ ብዙ ክርስቲያን ወንዶች በከባድ የኢኮኖሚ ችግር የተነሳ የጋብቻ እቅዳቸው የመጨናገፍ ወይም የመዘግየት ሁኔታ ደርሶበታል። በብዙ አገሮች የገንዘብ ዋጋ አሽቆልቁሏል። ለምሳሌ በአንድ የመካከለኛው አፍሪካ አገር በአንድ ዓመት የዕቃ ዋጋ 8,319 በመቶ አሻቅቧል! በአንዳንድ አገሮች ሥራ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው። ብዙ ጊዜ ደግሞ የሚከፈለው ደሞዝ በጣም አነስተኛ ስለሆነ አንድን ሰው ለማስተዳደር በቂ አይደለም፤ በዚህ ላይ ሚስትና ልጆች ተጨምረውበትማ የባሰ ነው። አንድ በናይጄሪያ የሚኖር ወጣት ሙሉ ቀን በሚሠራበት በአንድ ፋብሪካ በወር የሚከፈለው 17 ዶላር ከሥራ ወደ ቤትና ከቤት ወደ ሥራ ከሚመላለስበት የትራንስፖርት ወጪ እንደማያልፍ በምሬት ተናግሯል!

ብዙ ነጠላ ክርስቲያን ሴቶችም የኢኮኖሚ ችግሮች ለማግባት የነበራቸውን እቅድ እያከሸፈባቸው ነው። ብዙ ጊዜ ደግሞ የቤተሰባቸውን አባላት ለማስተዳደር የግድ መሥራት አለባቸው። አንዳንድ ነጠላ ወንዶች ሁኔታውን ሲያዩ ለማግባት ያመነታሉ፤ እንዲህ ባለው ሁኔታ ስር የሚያገባ ሰው ሚስቱን ብቻ ሳይሆን የእርሷን ቤተሰብ ጭምር ለመርዳት የሚችል መሆን እንዳለበት ይገነዘባሉ። የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ የሆነችው አዮ ራሷዋን፣ እናቷንና ታናናሽ ወንድሞቿንና እህቶቿን ለመርዳት ትፍጨረጨራለች። “ለማግባት ፈለኩ፤ ነገር ግን ሌሎች የምረዳቸውን ሰዎች ብዛት ሲመለከቱ ሊያገቡኝ አይፈልጉም” ስትል ብሶቷን ትናገራለች።

ምንም እንኳን የገንዘብ ችግር ቢኖርባቸውም ብዙ ያላገቡ ክርስቲያኖች እንዲያገቡና ልጆች እንዲወልዱ በዘመዶቻቸውና በሌሎች ሰዎች ግፊት ይደረግባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ይህ ግፊት የማሾፍ መልክ ይይዛል። ለምሳሌ ያህል በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ሰላምታ በሚለዋወጡበት ጊዜ ስለ ባል ወይም ስለ ሚስት እና ስለ ልጆች መጠየቅ የተለመደ ነው። አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነቶቹን ሰላምታዎች ባላገባው ሰው ላይ ለማላገጥ ይጠቀሙባቸዋል። በ40ዎቹ እድሜ ላይ የሚገኘው ጆን እንዲህ አለ፦ “ሰዎች በማሾፍ ‘ሚስትህ እንዴት ነች?’፣ ሲሉኝ እኔ ደግሞ መልሼ ‘እየመጣች ነው’ እላቸዋለሁ። እውነታው ግን ላስተዳድራት የማልችል ከሆነ እንዴት ሚስት ማግኘት እችላለሁ?”

የጆንና የሌሎች ብዙ እሱን መሰል ሰዎች ሁኔታ በአንድ የዮሩባውያን ምሳሌ ይጠቃለላል፦ “ቸኩሎ ማግባት አያኮራም፤ ዋናው ቤተሰብን ማስተዳደሩ ላይ ነው።”

ያለህበትን ሁኔታ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት

አንድ ሊሆን የማይችል ነገር ለማግኝት በጣም የምንጓጓ ከሆነ መጨነቃችን የማይቀር ነው። ምሳሌ 13:12 “የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች” ይላል። ምናልባት ለማግባት ጓጉተህ የገንዘብ አቅምህ ግን ሳይፈቅድልህ ሲቀር የሚሰማህ ስሜት ይህ ሊሆን ይችላል። በተለይ ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በምኞት የሚቃጠሉ’ ብሎ ከገለጻቸው ሰዎች መካከል ከሆንክ ይህ ይበልጥ እውነት ይሆናል።—1 ቆሮንቶስ 7:9

ችግሮችን ማሸነፍ ቀላል ላይሆን ይችላል፣ ነገር ግን ጸንተህ ለመቆም ሌላው ቀርቶ ባለህበት ሁኔታ ደስታ ለማግኘት ልታደርግ የምትችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ያላገባ ሰው የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ የጠበቁት ነገር ሳይሳካ በመቅረቱ ምክንያት የሚመጣን ሐዘን ለማሸነፍ የሚረዳህን ተግባራዊ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ሰጥቷል። እንዲህ አለ፦ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [ደስተኛ አዓት] ነው።”—ሥራ 20:35

ይህን ምክር ለቤተሰብህም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ላሉ ለሌሎች መልካም ነገሮች በማድረግ ተግባራዊ ልታደርገው ትችላለህ። ምናልባትም በክርስቲያናዊ አገልግሎት ያለህን ተሳትፎም ከፍ ልታደርገው ትችላለህ። ጊዜህን ሙሉ በሙሉ ራስ ወዳድነት በሌለበት የለጋስነት ተግባር እንዲያዝ ካደረከው ‘በልብህ የጸናህና ሥጋህን ለመቆጣጠር ሥልጣን ያለህ’ ልትሆን ትችላለህ።—1 ቆሮንቶስ 7:37

ሌላው ያላገባ ሰው የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ የሚከተለውን ጠቃሚ ምክር ጽፏል፦ “እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ።” (ኤፌሶን 5:15, 16) ብዙ ያላገቡ ክርስቲያኖች ጊዜያቸውን ወደ ይሖዋ በጸሎት ለመቅረብ፣ የአምላክን ቃል ለማጥናትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ተሳትፎ ለማድረግ በመጠቀም ‘ለነፍሳቸው እረፍት ለማግኝት’ ችለዋል። (ማቴዎስ 11:28–30) ይህን ካደረክ አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን በጣም በተሳካ ሁኔታ ልትቋቋም ትችላለህ። ወደፊት የምታገባም ከሆነ የተሻለ ባል ወይም ሚስት ለመሆን የሚያስችልህን የላቀ መንፈሳዊነት እንድታዳብር ይረ ዳሃል።

ይሖዋ እሱን ለሚያገለግሉት ሁሉ እንደሚያስብላቸው ፈጽሞ አትርሳ። ያሉብህን ችግሮችና አስጨናቂ ሁኔታዎች በሚገባ ያውቃል። በተጨማሪም አፍቃሪው ሰማያዊው አባታችን በመንፈሳዊም ሆነ በስሜታዊ ለአንተ በጣም የተሻለው ነገር ምን እንደሆነም አርቆ ይመለከታል። በርትተህ የቃሉን መመሪያዎች በእለታዊ ሕይወትህ በሥራ ላይ የምታውላቸው ከሆነ፤ እሱ በወሰነው ጊዜ እረፍትን እንደሚያመጣልህና ለዘላለማዊ ጥቅምህ በሚስማማ መንገድ የሚያስፈልጉህንና የምትፈልጋቸውን ነገሮች በማሟላት እንደሚያረካህ አትርሳ። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር በቅንነት የሚሄዱትን ከመልካም ነገር አያሳጣቸውም” በማለት ያረጋግጥልናል።—መዝሙር 84:11

የነገሮችን መልካም ጎን ተመልከት

ነጠላ መሆን የሚያመጣቸው ጥቅሞች እንዳሉት አስታውስ። ሐዋርያው ጳውሎስ “ድንግልን ያገባ መልካም አደረግ ያላገባም የተሻለ አደረገ” በማለት ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 7:38

ነጠላ መሆን ከማግባት “የተሻለ” የሆነው ለምንድን ነው? ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል፤ ያገባው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንደሚያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል፣ ልቡም ተከፍሎአል። ያልተጋባች ሴትና ድንግል በሥጋም በነፍስም እንዲቀደሱ የጌታን ነገር ያስባሉ፤ የተጋባች ግን ባልዋን እንዴት ደስ እንድታሰኘው የዓለምን ነገር ታስባለች።”—1 ቆሮንቶስ 7:32–34

በሌላ አባባል ያገቡ ክርስቲያኖች በጣም የሚያሳስባቸው የትዳር ጓደኞቻቸው የሚያስፈልጓቸው፣ የሚወዷቸውና የሚጠሏቸው ነገሮች ናቸው። ነጠላ ክርስቲያኖች ግን በበለጠ ማስተዋል በይሖዋ አገልግሎት ላይ ሊያተኩሩ ይችላሉ። ካገቡት ጋር ሲነጻጸር፣ ነጠላ ክርስቲያኖች ‘ሳይባክኑ በጌታ ለመጽናት’ በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።—1 ቆሮንቶስ 7:35

ጳውሎስ ነጠላ ክርስቲያኖች ሐሳብ የሚከፋፍል ምንም ነገር የለባቸውም ማለቱ አይደለም። የኢኮኖሚ ችግር ጫና ተጭኖህ ከሆነ ከአገልግሎትህ ለማዘናጋት የሚያሰጉ ብዙ ነገሮች እንዳሉ ይሰማህ ይሆናል። ይሁን እንጂ በግለሰብ ደረጃ ነፃ ሆኖ ይሖዋን የማገልገል መብት ካገቡት ይልቅ ላላገባ ወንድ ወይም ላላገባች ሴት የበዛ ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስ ነጠላነት የተሻለ ዘዴ መሆኑን ሲጠቁም ማግባት ስህተት ነው አላለም። እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም።” ሆኖም በመቀጠል “እንዲህ በሚያደርጉ [በሚያገቡ] በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል” ብሏል።—1 ቆሮንቶስ 7:28

ይህን ሲል ምን ማለቱ ነው? ጋብቻ አንዳንድ ጭንቀቶችን ያመጣል። እነዚህ ጭንቀቶች ምናልባት በአስቸጋሪ የኢኮኖሚ ወቅቶች አባት ለሚስቱና ለልጆቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ስለ ማቅረብ መጨነቅንም ይጨምር ይሆናል። ሕመምም በቤተሰቡ ላይ ተጨማሪ የገንዘብም ሆነ ስሜታዊ ጫናዎችን ሊያመጣ ይችላል።

ስለዚህ ያለህበት ሁኔታ ምንም እንኳን አንተ የምትመርጠው ዓይነት ባይሆንም ብታገባና ለልጆችህ የሚያስፈልጋቸውን ነገር የማቅረብ ኃላፊነት ያለብህ ብትሆን ኖሮ ከሚኖርህ ሁኔታ በተሻለ ደረጃ ላይ ልትሆን ትችላለህ። አሁን የተጋፈጥካቸው ችግሮች ጊዜያዊ ናቸው፤ በአምላክ አዲስ ሥርዓት ይወገዳሉ፤ አንዳንዶቹ ችግሮችህ እንዲያውም እስከዚያም ላይቆዩ ይችላሉ።—ከመዝሙር 145:16 ጋር አወዳድር።

አገልግሎትህን ልታሰፋው ትችላለህን?

ሁሉም ሰው ማድረግ ባይችልም አንዳንዶች ምንም እንኳ የገንዘብ ችግር ቢኖርባቸውም ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መግባት ችለዋል። አስቀድሞ የተጠቀሰው ቹክስ ቤተሰቡን ለመርዳት የጽሕፈት መሣርያዎችን እየገዛ ይሸጥ ነበር። የጋብቻ እቅዱ በተበላሸበት በዚያው ጊዜ ገደማ በአገሩ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በጊዜያዊነት በግንባታ ሥራ እንዲያገለግል የሚጋብዝ ደብዳቤ ደረሰው። ታላቅ ወንድሙ ስለ ገንዘቡ በማሰብ እንዳይሄድ ተስፋ ሊያስቆርጠው ሞከረ። ይሁን እንጂ ቹክስ ይሖዋ የጽሕፈት መሣሪያ ንግዱን እንዲያቋቁም ረድቶት እንደነበረ አሰበ፤ ስለዚህ ከሁሉ በፊት የመንግሥቱን ጉዳዮች ማስቀደምና አምላክ ለመስጠት ባለው ችሎታ ላይ መታመን ነበረበት። (ማቴዎስ 6:25–34) በተጨማሪም ለሦስት ወር ብቻ እንደሚሄድ አሰበ።

ቹክስ ግብዣውን ተቀበለና ንግዱን ለታላቅ ወንድሙ አስተላለፈ። ከስድስት ዓመታት በኋላ ቹክስ አሁንም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጸንቷል፤ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም ሽማግሌ ሲሆን በገንዘብ ረገድም ለማግባት በሚችልበት ደረጃ ላይ ነው። በሕይወቱ ውስጥ ነገሮች በዚህ መልክ በመለዋወጣቸው ይጸጸታልን? ቹክስ እንዲህ ይላል፦ “ለማግባት በፈለግሁበት ጊዜ ባለማግባቴ ሐዘን ተሰምቶኝ ነበር፤ ነገሮች ግን የተለወጡት ለእኔ በሚጠቅም መልኩ ነበር። ብዙ ደስታና የአገልግሎት መብቶች አግኝቻለሁ፤ ምናልባት አስቀድሜ አግብቼና ቤተሰብ ኖሮኝ ቢሆን ኖሮ እነዚህን መብቶች ላገኝና ልደሰት አልችልም ነበር።”

የወደፊቱ አስተማማኝ ሁኔታ

በአስቸጋሪ ጊዜያት ብዙዎች ወደፊት ከሚመጣባቸው የገንዘብ ችግር ለመከላከል የትዳራቸው ደህንነት የሚጠበቅበትን ዘዴ ወይም መንገድ ይፈልጋሉ። አንዳንድ አገሮች ከፍተኛ የዕዳ ጫና ስላለባቸው ለአረጋውያን ምንም ዓይነት እርዳታ አይሰጡም። ስለዚህ ወላጆች አብዛኛውን ጊዜ ቤተሰቦቻቸው በተለይም ደግሞ ልጆቻቸው ሲያረጁ እንደሚጦሯቸው ይተማመናሉ። ስለዚህ ነጠላ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ያላቸው የገንዘብ አቅም የማያስተማምን ቢሆንም እንኳ ለማግባትና ልጆች ለመውለድ ይገፋፋሉ።

ነገር ግን ጋብቻም ሆነ ልጆች መውለድ ጧሪ ለማግኘት ዋስትና ሊሆን አይችልም። አንዳንድ ዓለማዊ ልጆች ያረጁ ወላጆቻቸውን ለመጦር ፈቃደኞች አይደሉም፣ አንዳንዶቹ ደግሞ አቅሙ የላቸውም፤ ሌሎቹ ደግሞ ወላጆቻቸው ከመሞታቸው በፊት ይሞታሉ። ክርስቲያኖች ግን አስተዋይ በመሆን ዋስትና ለማግኘት ወደ የትም ሳይሆን በቅድሚያ አምላክ “አልለቅህም ከቶም አልተውህም” በማለት ወደ ሰጠው ተስፋ ይመለከታሉ።—ዕብራውያን 13:5

ይሖዋን በሙሉ ጊዜ ለማገልገል ሲሉ ሳያገቡ የሚቆዩ ሁሉ ፈጽሞ አይጣሉም። ክሪስቲና ነጠላና የ32 ዓመት እድሜ ያላት እህት ናት። ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በናይጄሪያ ውስጥ የዘወትር አቅኚ ሆና አገልግላለች። እንዲህ ትላለች፦ “አገልጋዮቹን ፈጽሞ እንደማይተው ባረጋገጠልን በይሖዋ ላይ እምነቴን እጥላለሁ። የሰጠው ተስፋ መታመኛዬ ነው። ይሖዋ በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ ይንከባከበኛል። ደግ አባት መሆኑን አሳይቶኛል። ለምሳሌ ያህል፣ ምሥክሮቹ ይበልጥ ወደ ሚያስፈልጉበት ቦታ በአቅኚነት ለማገልገል ተዛወርኩ። ምንም እንኳ ያሉት ጥቂት የምግብ መሸጫ መደብሮች ብቻ ቢሆኑም ባለው ነገር መተዳደርን ተምሬያለሁ። የተስቦ በሽታ ይዞኝ ሆስፒታል በገባሁበት ጊዜ ቀድሞ በነበርኩበት ጉባኤ የነበሩ ወንድሞች ይጠይቁኝና ይንከባከቡኝ ነበር።

“በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በጣም ረክቻለሁ። ከአጽናፈ ዓለም ፈጣሪና በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ብዙ ወንድሞችና እህቶች ጋር አብሮ መሥራትን እንደ ታላቅ መብት እመለከተዋለሁ። በዙሪያቸው እየተፈጸመ ባለው ነገር የሚበሳጩና ተስፋቢስ የሆኑ ብዙ ወጣቶችን አያለሁ። ለእኔ ግን ሕይወቴ ትርጉም ያለው ነው፤ የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነትና በናፍቆት እጠባበቃለሁ። ወደ ይሖዋ መቅረብ አሁን ለተጋፈጥናቸው ችግሮች ከሁሉ የሚበልጥ መፍትሔ እንደሆነ አውቃለሁ።”

ለማግባት የምትጓጓ ብትሆንም በአስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሁኔታ የተነሳ ማግባት ሳትችል ብትቀር ተስፋ አትቁረጥ! ይህ ዓይነት ሁኔታ የሚያጋጥመው አንተን ብቻ አይደለም። በይሖዋ እርዳታ ይህን በሚመስል ፈተና የጸኑ ብዙዎች አሉ። ለሌሎች ሰዎች መልካም በማድረግና መንፈሳዊነትህን በማሳደግ ያለህበትን ሁኔታ ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት። ወደ አምላክ ቅረብ፤ እርሱም ይረዳሃል ምክንያቱም እርሱ ስለ አንተ ያስባል።—1 ጴጥሮስ 5:7

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ