የገና በዓል ኢየሱስን በደስታ የምንቀበልበት መንገድ ነውን?
የአዳኛችንና ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየው መሲሕ ልደት በእርግጥ የመደሰቻ ጊዜ ነው። በቤተልሔም አቅራቢያ በጎቻቸውን ይጠብቁ ለነበሩ የበግ እረኞች አንድ መልአክ “እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ። ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና” በማለት አብስሯል። ከእርሱም ጋር ብዙ የመላእክት ሠራዊት አምላክን በማወደስ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን። ሰላምም በምድር ለበጐ ፈቃድ ሰዎች ይሁን” አለ።—ሉቃስ 2:10-14 አንዳንዶች ክርስቶስ ወደ ምድር በመጣበት በዚያ ጊዜ መላእክት ደስታቸውን እንደገለጹ ክርስቲያኖችም እንዲሁ ማድረግ አለባቸው ብለው ያስባሉ።
በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገብ ውስጥ መላእክት በደስታ በመፈንደቅ የውዳሴ መዝሙር የዘመሩት በዚህ ጊዜ ብቻ አልነበረም። የምድር መሠረት ሲጣል ‘አጥቢያ ኮከቦች በደስታ ዘምረዋል፤ የአምላክ ልጆች ሁሉ እልል ብለዋል።’ (ኢዮብ 38:4-7) ይህ እልልታ የተደረገበት ትክክለኛ ቀን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተመዘገበም። (ዘፍጥረት 1:1, 14-18) ወቅቱ ምንም ያህል አስደሳች ይሁን መላእክት እልል ስላሉ ክርስቲያኖች ምድር የተፈጠረችበትን ቀን እናከብራለን ብለው በመከራከር አረማውያን የምድርን መፈጠር ወይም የመሬትን ልደት የሚያከብሩበትን በዓል አልወረሱም።
ሆኖም ገናን የሚያከብሩ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ረገድ የሚያደርጉት ይህንኑ ነው። የትኛውንም የታመነ ኢንሳይክሎፒድያ “ገና” በሚለው ርዕስ ስር ብንመለከት የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ቀን እንደማይታወቅ ያረጋግጥልናል። ዕለቱን በሚመለከት መጽሐፍ ቅዱስ ምንም የሚናገረው ነገር የለም።
“መለከት ትርጉሙ የማይታወቅ ድምፅ ቢሰጥ”
ሐዋርያው ጳውሎስ በጥንቷ ቆሮንቶስ ጉባኤ የነበረውን ሥርዓት የለሽነት ለማረም “እግዚአብሔር የሥርዓት አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም” በማለት ጽፏል። ስለዚህ ጉዳይ በገለጸበት በዚያው ምዕራፍ ውስጥ “መለከት ትርጉሙ የማይታወቅ ድምፅ ቢሰጥ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል?” በማለት ጠይቋል። (1 ቆሮንቶስ 14:8, 33) ታዲያ የሥርዓት አምላክ በምድር የሚኖሩ ክርስቲያኖች የልጁን ልደት እንዲያከብሩ ካሰበ ፍጹማን ያልሆኑት ሰዎች ከአረማውያን በዓላት አንዱን ቀን እንዲመርጡና አምላካዊ ያልሆኑ ልማዶችን እንዲወርሱ ይተዋቸው ነበርን?
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌዎችን ብንመረምር ይሖዋ አምላክ ለሕዝቡ ይህን የመሰለ ነገር እንደማያደርግ ለመረዳት እንችላለን። እስራኤላውያንን በሙሴ ሕግ አማካኝነት ዓመታዊ በዓሎችን እንዲያከብሩ ሲያዛቸው የተወሰኑ ቀኖችን ለይቶ በመናገር እነዚያን የበዓል ወቅቶች እንዲጠብቁ ነግሯቸዋል። (ዘጸአት 23:14-17፤ ዘሌዋውያን 23:34-43) ኢየሱስ ክርስቶስም ልደቱ እንዲከበር ፈጽሞ ያላዘዘ ቢሆንም አንድ የተወሰነ ቀን እንዲያከብሩ ተከታዮቹን አዟቸዋል። “ኢየሱስ አልፎ በተሰጠባት በዚያች ሌሊት” ኒሳን 14, 33 እዘአ ያልቦካ ቂጣና ወይንን በመጠቀም የጌታ ራትን በዓል ጀምሯል። “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” በማለት አዟል። (1 ቆሮንቶስ 11:23, 24) የጌታ ራት መቼና እንዴት መከበር እንዳለበት የሚገልጸው የመለከት ድምፅ ግልጽና የማያሻማ ነው። ታዲያ ገናስ? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የክርስቶስ ልደት እንዲከበር የታዘዘበት ቦታ አናገኝም። መቼና እንዴት መከበር እንዳለበት የሚገልጽ ነገር አናገኝም።
ሰዎችን ለመማረክ
በቶኪዮ ከተማ በሚገኘው የጽዮን ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉ አንድ ቄስ “በእርግጥ ገና ከአረማውያን የመጣ መሆኑን አውቃለሁ። ነገር ግን በክርስትና ውስጥ ያሉ ሰዎች ለታህሣሥ 25 ልዩ ስሜት እስከኖራቸውና የተከበረውን የኢየሱስን ትምህርት ለመማር እስከመጡ ድረስ ገና በክርስትና ውስጥ ቦታ አለው” በማለት ተናግረዋል። ብዙዎች ከዚህ አስተሳሰብ ጋር ይስማማሉ። ይህ ዓይነቱ አቋምን የማላላት ተግባር ተገቢ ነው ብለህ ታምናለህን?
አንዳንዶች ጳውሎስም እንኳ አማኞችን ለማግኘት ብሎ አቋሙን አላልቶ ነበር በማለት ይከራከራሉ። “የሚበልጡትን እንድጠቅም እንደ ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛለሁ። . . . ከሕግ በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንሁ። በወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 9:19-23) እነዚህ ቃላት አሕዛብን ወደ ክርስትና ለመሳብ ሲባል አረማዊ በዓላትን ማክበር ተገቢ እንደሆነ ያሳያሉን?
በጳውሎስ አባባል ዙሪያ ያሉትን ሐሳቦች በጥንቃቄ መርምራቸው። በቁጥር 21 ላይ “ይህ ማለት ያለ እግዚአብሔር ሕግ እኖራለሁ ማለት አይደለም። በእርግጥ በክርስቶስ ሕግ ስር ነኝ” ብሏል። (እንደ ቱዳይስ ኢንግሊሽ ትርጉም) ስለዚህ ጳውሎስ የክርስቶስን ሕግ በመተላለፍ ጉዳይ ላይ ያለውን አቋም አላላላም። ይሁን እንጂ ከክርስትና ትእዛዞች ጋር የሚጋጩ እስካልሆኑ ድረስ የአካባቢውን ልማዶች በማክበር “እንደ አሕዛብ ሆኗል” ማለት ነው።a
ይህን በአእምሮህ በመያዝ በሚቀጥለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ መሠረት አረማዊ ስነ በዓሎችን በገና ስም ወደ ክርስትና ማስገባት ምን መስሎ እንደሚታይ አስብ። “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ። ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? . . . ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? . . . ስለዚህ ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኩስንም አትንኩ ይላል ይሖዋ እኔም እቀበላችኋለሁ።” (2 ቆሮንቶስ 6:14-17) ምንም ዓይነት ማመካኛ ይቅረብ ክርስትናን ከአረማዊ ስነ በዓሎች ጋር መቀላቀል የኢየሱስን አዳኝነት የምንቀበልበት መንገድ አይደለም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስ በሥጋ በመጣ ጊዜ እንዲህ ያለ ድርጊት ቢፈጸም ተገቢ አይሆንም ነበር። ክርስቶስ የአምላክን ፍርድ ለማስፈጸም ንጉሥ ሆኖ በሚመጣበት ባሁኑ ጊዜም ሆነ ለወደፊቱም ቢሆን የማይገባ ድርጊት ነው። (ራእይ 19:11-16) እንዲያውም “ክርስቲያን” በሚል መሸፈኛ አረማዊ በዓልን ለማክበር የሚመርጡ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስን እየካዱት ነው።
“የተደበቁት ክርስቲያኖች” አልተመለሱም
በሾገን ዘመን (በ1867-68 እስከተደረገው አብዮት ድረስ ጃፓንን ከመሩት ወታደራዊ ገዥዎች አንዱ) በጃፓን አገር በካቶሊኮች ላይ ከደረሰው ነገር ትምህርት ውሰዱ። በ1614 ካቶሊኮችን መጨቆን በተጀመረ ጊዜ 300,000 የሚሆኑ ጃፓናውያን ካቶሊኮች ሦስት ምርጫዎች ተደቀኑባቸው፦ ሰማዕት መሆን፣ እምነታቸውን መተው ወይም መደበቅ። የተደበቁት ክርስቲያኖች ድብቅ ክርስቲያኖች ተብለው ተጠሩ። የእምነታቸውን ምንነት ለመደበቅ የተለያዩ የቡዲስትና የሺንቶ ልማዶችን ተከተሉ። በአምልኮታቸው ማርያምን መስላ የምትሳለውን ሕፃን ያቀፈች የቡዲስት ቦድሂሳትቫ ማሪያ ካኖን ተጠቀሙ። በዓሎቻቸው ቡዲሂዝምን፣ ካቶሊሲዝምንና ባሕላዊ ሃይማኖቶችን አቀላቀሉ። ይሁን እንጂ የቡዲስት የቀብር ስነ ሥርዓት ላይ እንዲገኙ ሲገደዱ የክርስቲያን ጸሎቶችን ይዘምሩና የቡዲስትን ቅዳሴ ለመሻር ሞዶሺ የሚባለውን ስነ ሥርዓት ይፈጽሙ ነበር። እነዚህ “ክርስቲያኖች” ምን ደረሰባቸው?
የተደበቁት ክርስቲያኖች የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚገልጸው “አብዛኞቹን ክርስቲያኖች የሺንቶና የቡዲስት አማልክትን አምልኮ መተው አስቸጋሪ የሚያደርግባቸው ሃይማኖታዊ መተሳሰር ተፈጠረ” ይላል። እገዳው ተነስቶ የካቶሊክ ሚስዮናውያን ወደ ጃፓን በተመለሱ ጊዜ “ከተደበቁት ክርስቲያኖች” አብዛኞቹ ቅይጥ ሃይማኖታቸውን አጥብቀው ያዙ።
ይሁን እንጂ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እነዚያን ወደ ሮማ ካቶሊክ ሃይማኖት ለመመለስ እምቢ ያሉትን “ድብቅ ክርስቲያኖች” ልትነቅፋቸው ትችላለችን? የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ራሷም ገናን ጨምሮ ብዙ አረማዊ ትምህርቶችንና በዓሎችን ወርሳለች። ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች እንደሆኑ ቢናገሩም “ክርስትናቸውን” ከአረማዊ በዓላትና ከአረማዊነት ጋር ከቀላቀሉ ኢየሱስ ክርስቶስን መናቃቸው ሊሆን አይችልምን?
ወደ እውነተኛ ክርስትና ተመለሰች
ለ36 ዓመታት ለሃይማኖቷ ያደረች አክራሪ ካቶሊክ የነበረችው ሴሱኮ በመጨረሻ ወደዚህ ግንዛቤ ደርሳለች። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ መንፈሳዊ ጥማቷን ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር በመተባበር ለማርካት ሞከረች። በገና የቅዳሴ ሥርዓት ስትካፈልና በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥና ውጭ የሚያማምሩ የገና ዛፎችን ስትመለከት “እንዴት ደስ ይላል!” ትል ነበር። “በአቅራቢያው ካሉ ቤተ ክርስቲያኖች ሁሉ በሚበልጠው የቤተ ክርስቲያናችን አሸላለም ወይም አጋጌጥ ኩራት ይሰማኝ ነበር” አለች። የሆነ ሆኖ ሴሱኮ ለጥቂት ጊዜ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ብታስተምርም እንኳ የካቶሊክ ትምህርቶች አይገቧትም ነበር። በቤተ ክርስቲያን ሥራ ይበልጥ እንድትካፈል በመፈለግ ቄሷን ጥቂት ጥያቄዎችን ጠየቀቻቸው። ጥያቄዋን በመመለስ ፈንታ ቄሱ እሷኑ አንቋሸሿት። ተስፋ በመቁረጥም መጽሐፍ ቅዱሷን ራሷ ለማጥናት ወሰነች። ከሁለት ሳምንታት በኋላ የይሖዋ ምስክሮች ጎበኟትና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላት ተስማማች።
“የቀድሞ እምነቶቼን የሚያፈራርሱ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ፊት ለፊት መጋፈጥ የሚያሳምም ነገር ነበር። በመበሳጨቴ ምክንያት ኦሎፔሽያ ኒውሮቲካ የሚባል የራስ ጠጉር መርገፍ በሽታ ደርሶብኛል። ይሁን እንጂ ቀስ በቀስ የእውነት ብርሃን በልቤ ውስጥ አበራ። ኢየሱስ እረኞች የበግ መንጋቸውን በሌሊት ሊጠብቁና በሜዳ ሊያድሩ በማይችሉበት በብርዳማውና በዝናባማው ታህሣሥ ሊወለድ እንደማይችል ስማር በጣም ተገረምኩ። (ሉቃስ 2:8-12) የበጎችና የበግ እረኞችን ትዕይንት ለማስጌጥ አመዳይን በሚያመለክት የጥጥ ባዘቶ እንጠቀም ስለነበር ስለልደት የነበረኝን እምነት ብትንትኑን አወጣው።”
ሴሱኮ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያስተምረው ትክክለኛ ነገር ራሷን ካሳመነች በኋላ ገናን ማክበሯን ለማቆም ወሰነች። ከዚያ ወዲያ በየቀኑ የሚገኘውን ደስታ የተሞላበትን የክርስቲያናዊ መስጠት መንፈስ ታሳያለች እንጂ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚታየው “የገና መንፈስ” የላትም።
በክርስቶስ ከልብ የምታምን ከሆነ አረማውያን ገናን ሲያበላሹት ብትመለከት አትበሳጭ። ከመጀመሪያውም ቢሆን አረማዊ በዓል መሆኑን ማረጋገጣቸው ነው። ገና ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖ በማይታይ ሁኔታ የተመለሰውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲቀበል ማንንም አይመራም። (ማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25፤ ማርቆስ ምዕራፍ 13፤ ሉቃስ ምዕራፍ 21) ከዚህ ይልቅ እውነተኛ ክርስቲያኖች በዓመቱ በሙሉ ክርስቶስን መሰል መንፈስ በማሳየት ኢየሱስ ንጉሥዋ የሆነላትን መንግሥት ምሥራች ያውጃሉ። አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን እንድንቀበለው የሚፈልገው እንደ አዳኛችንና እንደ መንግሥቱ ንጉሥ አድርገን ነው።—መዝሙር 2:6-12
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ጳውሎስ በግዝረት ጉዳይ ላይ ምላሽ የሰጠባቸውን ሁለት መንገዶች አወዳድር። መገረዝ ከንቱ መሆኑን ቢያውቅም በእናቱ በኩል አይሁዳዊ የነበረውን ጢሞቴዎስን ገርዞታል። (1 ቆሮንቶስ 7:19፤ ሥራ 16:3) ቲቶን ግን ከይሁዲነት ጠበቆች ጋር በነበረው ክርክር ምክንያት ሕግ ግዴታ ያለመሆኑን ለማሳየት እንዳይገረዝ አድርጐታል። (ገላትያ 2:3) ቲቶ ግሪካዊ ነበር። ስለዚህ እንደ ጢሞቴዎስ እንዲገረዝ የሚያደርገው ምክንያት አልነበረውም። ከአሕዛብ የነበረ እንደመሆኑ ቢገረዝ ኖሮ “ክርስቶስ ምንም አይጠቅመውም” ነበር።—ገላትያ 5:2-4
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነተኛ ክርስቲያኖች ኢየሱስን በዓመቱ በሙሉ ያከብሩታል