የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 1/15 ገጽ 4-7
  • ‘ክርስቶስን ለመቀበል መነጠቅ’ — እንዴት?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘ክርስቶስን ለመቀበል መነጠቅ’ — እንዴት?
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የክርስቶስ “መገኘት”
  • “የአምላክ እሥራኤል”
  • የሚነጠቁት እንዴት ነው?
  • ከጥፋቱ ይተርፋሉ፤ ሆኖም በመነጠቅ አይደለም
  • በአካል መነጠቅ
    ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር
  • ‘የመጀመሪያው ትንሣኤ’ በመከናወን ላይ ነው!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • የክርስቶስ መመለስ
    ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር
  • ወደ ሰማይ ትነጠቃለህን?
    መጠበቂያ ግንብ—1993
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 1/15 ገጽ 4-7

‘ክርስቶስን ለመቀበል መነጠቅ’ — እንዴት?

የአሁኑ ክፉ ሥርዓት የሚጠፋበት ጊዜ በማያወላውል ሁኔታ በጣም እየቀረበ መጥቶአል። እያንዳንዱ ሰዓት፣ ደቂቃና ሴኮንድ ባለፈ ቁጥር ከረጅም ጊዜ በፊት የተነገሩ ትንቢቶች በአስደናቂ ሁኔታ ሲፈጸሙ እንመለከታለን። ከእነዚህ ትንቢቶች አንዱ መነጠቅ ነውን? ከሆነስ የሚከናወነው መቼና እንዴት ነው?

“ራፕቸር” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ይሁን እንጂ በራፕቸር የሚያምኑ ሰዎች ለእምነታቸው ድጋፍ እንዲሆናቸው በ1 ተሰሎንቄ 4:​17 ላይ የሚገኘውን የሐዋሪያው ጳውሎስን ቃላት ይጠቅሳሉ። ይህን ጥቅስ በዙሪያው ካሉት ሐሳቦች አንፃር እንመርምር። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጻፈ:-

“ነገር ግን፣ ወንድሞች ሆይ፣ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፣ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን። ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፣ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና። በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፣ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፣ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን። ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ።”​—⁠1 ተሰሎንቄ 4:​13-18

ሐዋሪያው ጳውሎስ የመጀመሪያ መልእክቱን በ50 እዘአ አካባቢ ለተሰሎንቄ ጉባኤ በጻፈ ጊዜ ይህ ጉባኤ ገና አዲስ ነበር። የጉባኤው አባሎች ከመሐከላቸው አንዳንዶቹ “በሞት በማንቀላፋታቸው” ምክንያት አዝነው ነበር። ይሁን እንጂ ጳውሎስ የጻፈላቸው ደብዳቤ በትንሣኤ ተስፋ አጽናንቶአቸው ነበር።

የክርስቶስ “መገኘት”

ጳውሎስ በዚያ ጊዜ የሞቱ ታማኝ ክርስቲያኖች እንደሚነሱ ቢያረጋግጥም:- “እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ [እስኪገኝ አዓት] ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም” ብሏል። (ቁጥር 15) እዚህ ላይ ሐዋሪያው የጌታን “መገኘት” እንደጠቀሰ ልብ ማለት ያስፈልጋል። የመጀመሪያው የግሪከኛ ጽሑፍ እዚህ ላይ የተጠቀመበት ቃል ፓሩሲያ የሚለውን ነው። ይህም ቃል በቀጥታ ሲተረጐም “ከ — ጋር መሆን” ማለት ነው።

አንድ የውጭ አገር መሪ አንድን ሌላ አገር በሚጎበኝበት ጊዜ ወደ አገሩ የሚደርስበት ቀንና ጊዜ ይነገራል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝበት ጊዜም እንዲሁ በቅድሚያ ተነግሯል። መጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት በቅንነት ለሚመረምሩ ሰዎች ኢየሱስ በሰማይ በንጉሣዊ ስልጣን የሚገኝበት ጊዜ በ1914 እንደጀመረ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ሳያሰልስ ሲያቀርብ ቆይቶአል። ከዚህ ዓመት ወዲህ የተፈጸሙት ሁኔታዎች በሙሉ ኢየሱስ በማይታይ ሁኔታ መገኘቱን መስክረዋል። (ማቴዎስ 24:​3-14) ስለዚህ ጳውሎስ ጌታ በሚገኝበት ጊዜ በሕይወት የሚኖሩ ክርስቲያኖች ጌታን በአየር ለመገናኘት እንደሚወሰዱ ሲናገር እነዚህ በሕይወት የቆዩ ክርስቲያኖች ክርስቶስን የሚገናኙት በምድር ከባቢ አየር ሳይሆን በማይታየው ሰማያዊ ግዛት ኢየሱስ በአምላክ ቀኝ በተቀመጠበት ስፍራ እንደሚሆን ማመልከቱ ነበር። (ዕብራውያን 1:​1-3) ይሁን እንጂ እነዚህ የሚነጠቁት ክርስቲያኖች እነማን ናቸው?

“የአምላክ እሥራኤል”

ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ ሥጋዊ እስራኤልም ሆነ ስለ መንፈሳዊ “የአምላክ እስራኤል” ብዙ ነገር ይናገራሉ። እነዚህ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል የተቀቡት ሰዎች ከአይሁዳውንና ከአሕዛብ አማኞች የተውጣጡ ናቸው። (ገላትያ 6:16፤ ሮሜ 11:​25, 26፤ 1 ዮሐንስ 2:​20, 27) የራእይ መጽሐፍ የመንፈሳዊው እሥራኤል አባላት ቁጥር 144,000 እንደሚሆንና ሁሉም ከበጉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰማያዊትዋ ጽዮን ተራራ እንደሚሆኑ ያመለክታል። ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ካህናትና ነገሥታት ይሆናሉ። (ራእይ 7:​1-8፤ 14:​1-4፤ 20:⁠6) ከእነዚህ መካከል በጥንቷ የተሰሎንቄ ጉባኤና በሌሎች ስፍራዎችም የነበሩ ከተለያዩ ነገድና ብሔር የተውጣጡ ግለሰቦች ይኖራሉ።​—⁠ሥራ 10:​34, 35

ማንኛውም ታማኝ የመንፈሳዊ እስራኤል አባል ሰማያዊውን ሽልማቱን ከመቀበሉ በፊት ማየት የሚኖርበት አንድ ነገር አለ። ኢየሱስ ወደ ሰማያዊ ሕይወት ከመነሳቱ በፊት በመከራ እንጨት እንደሞተ ሁሉ፣ ሰማያዊ ሽልማት የሚያገኙ ክርስቲያን ሁሉ መሞት ያስፈልጋቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:​35, 36) ይህም እዘአ በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ሆነ በዘመናቸን በሚገኙት የመንፈሳዊ እስራኤል ግለሰብ አባሎች ላይ ተፈጻሚነት ይኖረዋል።

ጳውሎስ ስለ ጌታ መገኘት ከጠቀሰ በኋላ ሞተው የነበሩ ታማኝ መንፈሳዊ እስራኤላውያን ሰማያዊ ሽልማታቸውን ስለሚያገኙበት ጊዜ ተናግሯል። እንዲህ ሲል ጻፈ:- “ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፣ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ።” (ቁጥር 16) ስለዚህ ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ ከተገኘበት ጊዜ ጀምሮ ሰማያዊው ትንሣኤ ፍጹም አቋማቸውን ጠብቀው በሞቱት መንፈሳዊ እስራኤላውያን እንደሚጀምር ልንጠብቅ እንችላለን። (1 ቆሮንቶስ 15:23) እነርሱም በአሁኑ ጊዜ በሰማይ ከኢየሱስ ጎን ሆነው ያገለግላሉ። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ በምድር የሚኖሩ በቁጥር አነስተኛ የሆኑት ቅቡዓንስ ምን ይሆናሉ? የሚነጠቁበትን ጊዜ ይጠብቃሉን?

የሚነጠቁት እንዴት ነው?

ጳውሎስ ስለሞቱ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከተናገረ በኋላ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፣ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፣ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።” (ቁጥር 17) “ሕያዋን” የተባሉት ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ በሕይወት የሚገኙት ናቸው። ከጌታ ኢየሱስ ጋር እንዲሆኑ ይነጠቃሉ። እንደ ጥንቶቹ ታማኝ ክርስቲያኖች ሁሉ እነርሱም በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ለመሆን እንደ ሰው ሆነው መሞት ያስፈልጋቸዋል።​—⁠ሮሜ 8:​17, 35-39

ጳውሎስ በቆሮንቶስ ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “ነገር ግን፣ ወንድሞች ሆይ፣ ይህን እላለሁ:- ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፣ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም። እነሆ፣ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና፤ ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን።” (1 ቆሮንቶስ 15:​50-52) እያንዳንዱ የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪ በጌታ መገኘት ዘመን በታማኝነት እንደሞተ ወዲያው ሰማያዊ ሽልማቱን ያገኛል። “በቅጽበት ዓይን” መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ በመነሳት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመሆንና በሰማያት መንግሥት ተባባሪ ወራሽ ሆኖ እንዲያገለግል ይወሰዳል። ይሁን እንጂ ይሖዋን ስለሚያመልኩት ሌሎች ሰዎችስ ምን ሊባል ይቻላል? የዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ ሲመጣ እነርሱም ወደ ሰማይ ይወሰዳሉን?

ከጥፋቱ ይተርፋሉ፤ ሆኖም በመነጠቅ አይደለም

የኢየሱስ ንጉሣዊ መገኘት የጀመረው በ1914 ስለሆነ በአሁኑ ጊዜ ወደዚህ ዓለም “የፍጻሜ ዘመን” በጣም ተቃርበናል። (ዳንኤል 12:⁠4) ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት አስጠንቅቋል:- “ወንድሞች ሆይ፣ ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤ የጌታ ቀን፣ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፣ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋል። ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ፣ ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም።” (1 ተሰሎንቄ 5:​1-3) ንቁ የሆኑ ክርስቲያኖች ግን ከጥፋቱ ያመልጣሉ። እንዴት?

“ሰላምና ደኅንነት” የሚለው ጩኸት ኢየሱስ ታላቁ መከራ ሲል ለጠራው ጊዜ መቅድም ይሆናል። የራእይ መጽሐፍ በምድራዊ ገነት ለዘላለም የመኖር ተስፋ ስላላቸው ታማኞች ስለሆኑ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ሲገልጽ:- “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፣ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ” ብሏል። (ራእይ 7:​9, 14፤ ሉቃስ 23:43) እነዚህ ሰዎች የሚጠብቁት ነገር መነጠቅን አይደለም። ከዚህ ይልቅ በዚችው ምድር ላይ ከጥፋት ተርፈው የመኖር ተስፋ አላቸው። ለዚህ ዝግጁ ሆነው እንዲኖሩ በመንፈሳዊ ዘወትር ንቁዎች ሆነው መገኘት ይገባቸዋል። በመንፈሳዊ ንቁ ሆነህ ለመኖርና ከዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ለመዳን የምትችለው እንዴት ነው?

ስሜቶችህን መጠበቅና ንቁ መሆን ‘የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር መልበስ’ እንዲሁም ‘የመዳንን ተስፋ ራስ ቁር ማድረግ’ ይኖርብሃል። (1 ተሰሎንቄ 5:​6-8) የአምላክን ትንቢታዊ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ በጥሞና የምንከታተልበት ጊዜ አሁን ነው። ከዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በፊት ያለው የእያንዳንዱ ሴኮንድ ባለፈ ቁጥር ጳውሎስ:- “ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ” ሲል የሰጠውን ምክር ልብ ማለት ይኖርብናል። (1 ተሰሎንቄ 5:​20, 21) እንግዲያው የይሖዋ ምስክሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችንና ሌሎቹን የአምላክ ቃል ገጽታዎች አብረሃቸው እንድትመረምር ወደ መንግሥት አዳራሻቸው ብትመጣ በደስታ ይቀበሉሃል።

ትክክለኛ እውቀት በማግኘትና በእምነት እያደግህ ስትሄድ ይሖዋ አምላክ ጠላቶቹን ከጽንፈ ዓለሙ ለማስወገድና ምድርን ወደ ገነትነት ለመመለስ ያለውን ዓላማ ለመፈጸም እንዴት ሁኔታዎችን በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ታስተውላለህ። አንተም እምነት ካለህ ከታላቁ መከራ በሕይወት ከሚተርፉት መካከል በመሆን ከሞት የሚነሱትን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለመቀበል ትችላለህ። በኢየሱስ ክርስቶስ እና በሰማያዊው ዓለም ለመኖር ከጌታ ጋር እንዲሆኑ በሕይወት ትንሣኤ ከተነጠቁት ተባባሪ ገዢዎች በሚተዳደረው የአምላክ መንግሥት ሥር መኖር ምንኛ የሚያስደስት ነገር ይሆናል!

እንግዲያው ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች የሚኖራቸው እውነተኛ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ተስፋ ምንድን ነው? መነጠቅ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ በአምላክ መንግሥት ግዛት ውስጥ በምድር ላይ የዘላለም ሕይወትን ማግኘት ነው።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከታላቁ መከራ የሚተርፉ ሰዎች በኢየሱስ እና ወደ ሰማይ በተወሰዱት ሰዎች ግዛት ስር በምትተዳደረው ምድራዊ ገነት ሙታንን ይቀበላሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ