-
“ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ ጥበብ ትገኛለች”መጠበቂያ ግንብ—2000 | ነሐሴ 1
-
-
‘ሎሌና’ ‘መጋቢ’ የነበረው ጳውሎስ
4. ጳውሎስ ምን ልዩ መብቶች ነበሩት?
4 ጳውሎስ በጥንቶቹ ክርስቲያኖች ዘንድ ጉልህ ቦታ ነበረው፤ ደግሞም እንደዚያ መሆኑ አያስገርምም። በአገልግሎት በተካፈለባቸው ጊዜያት በባሕር፣ በየብስ ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዟል፤ በርካታ ጉባኤዎችንም አቋቁሟል። በተጨማሪም ራእይ እንዲያይና በልሳን እንዲናገር በማድረግ ይሖዋ ባርኮታል። (1 ቆሮንቶስ 14:18፤ 2 ቆሮንቶስ 12:1-5) እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል የሆኑትን 14 ደብዳቤዎች እንዲጽፍ በመንፈሱ አነሳስቶታል። ከዚህ ለማየት እንደምንችለው ጳውሎስ ከሌሎቹ ሐዋርያት ይበልጥ ደክሟል ተብሎ ሊነገርለት ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 15:10
5. ጳውሎስ ስለ ራሱ የነበረው አመለካከት ልክን የማወቅ ባሕርይ የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው?
5 ጳውሎስ በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ግንባር ቀደም ስለነበር አንዳንዶች የሰዎችን ትኩረት ለማግኘት እንዲያውም ሥልጣኑን ለማሳወቅ የሚፈልግ ሰው እንደሆነ አድርገው ሊመለከቱት ይችሉ ይሆናል። ሆኖም ጳውሎስ ልኩን የሚያውቅ ሰው ስለሆነ እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ አልነበረውም። “ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ” በማለት ራሱን ከመጥራቱም በላይ “የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ” ነኝ በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 15:9) ጳውሎስ ቀደም ሲል ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረ እንደመሆኑ ልዩ የአገልግሎት መብት ማግኘት ይቅርና ወደ አምላክ መቅረብ የቻለው ይገባኛል በማይለው ደግነቱ እንደሆነ ፈጽሞ አልረሳም። (ዮሐንስ 6:44፤ ኤፌሶን 2:8) በመሆኑም ጳውሎስ በአገልግሎቱ ብዙ ማከናወን መቻሉ ከሌሎች የላቀ ሆኖ እንዲሰማው አላደረገውም።—1 ቆሮንቶስ 9:16
6. ጳውሎስ ከቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጋር በነበረው ግንኙነት ልክን የማወቅ ባሕርይ ያሳየው እንዴት ነው?
6 ጳውሎስ ከቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጋር የነበረው ግንኙነት ልኩን የሚያውቅ ሰው መሆኑን ይበልጥ ግልጽ አድርጎ ያሳያል። አንዳንዶች አጵሎስን፣ ኬፋንና ራሱን ጳውሎስን ጨምሮ ዋነኛ ብለው ላሰቧቸው አንዳንድ የበላይ ተመልካቾች ከፍተኛ ግምት ሰጥተው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 1:11-15) ሆኖም ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን በማግባባት የእነርሱን ውዳሴም ሆነ አድናቆት ለማግኘት አልሞከረም። በሚጎበኛቸው ጊዜ “በቃልና በጥበብ ብልጫ” ራሱን አላቀረበም። ከዚያ ይልቅ ጳውሎስ ስለ ራሱም ሆነ ስለ ባልንጀሮቹ ሲናገር “እንዲሁ ሰው እኛን እንደ ክርስቶስ ሎሌዎችና እንደ እግዚአብሔር ምሥጢር መጋቢዎች ይቍጠረን” በማለት ተናግሯል።a—1 ቆሮንቶስ 2:1-5፤ 4:1
7. ጳውሎስ ምክር በሚሰጥበት ጊዜም እንኳ ሳይቀር ልክን የማወቅ ባሕርይ ያንጸባረቀው እንዴት ነው?
7 ጳውሎስ ሌላው ቀርቶ ጠንካራ ምክርና መመሪያ እንዲሰጥ በተገደደበት ጊዜ እንኳን ሳይቀር ልክን የማወቅ ባሕርይ አሳይቷል። ክርስቲያን ባልንጀሮቹን በሐዋርያዊ ሥልጣኑ ሳይሆን “በእግዚአብሔር ርኅራኄ” እና “ስለ ፍቅር” ለምኗቸዋል። (ሮሜ 12:1, 2፤ ፊልሞና 8, 9) ጳውሎስ እንደዚህ ያደረገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ‘በእምነታቸው ላይ እንደሚገዛ’ ሳይሆን የእነርሱ ‘የሥራ ባልደረባ’ እንደሆነ አድርጎ ራሱን ይቆጥር ስለነበር ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:24) ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጉባኤዎች ዘንድ እንዲወደድ ያደረገው ይኸው ልክን የማወቅ ባሕርይ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።—ሥራ 20:36-38
-
-
“ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ ጥበብ ትገኛለች”መጠበቂያ ግንብ—2000 | ነሐሴ 1
-
-
a “ሎሌ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በአንድ ትልቅ መርከብ ላይ ለመቅዘፍ የተመደበን ባሪያ ሊያመለክት ይችላል። በተቃራኒው ደግሞ አንድ “መጋቢ” ርስትን እስከ ማስተዳደር ድረስ ብዙ ኃላፊነት ሊሰጠው ይችላል። የሆነ ሆኖ፣ መጋቢም ሆነ መርከብ የሚቀዝፍ ባሪያ በአብዛኞቹ ጌቶች ዓይን ልዩነት የላቸውም።
-