የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • kr ምዕ. 20 ገጽ 209-219
  • የእርዳታ አገልግሎት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የእርዳታ አገልግሎት
  • የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የእርዳታ ሥራ “ቅዱስ አገልግሎት” የሆነው ለምንድን ነው?
  • ግልጽ ዓላማዎች ያሉት እርዳታ
  • የእርዳታ አገልግሎት ዘላቂ ጥቅሞች ያስገኛል
  • የበኩልህን ድርሻ ማበርከት ትችላለህ?
  • አደጋ ከደረሰ በኋላ እርዳታ ማበርከት የሚቻለው እንዴት ነው?
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
  • የይሖዋ ምሥክሮች በአደጋ ለተጎዱ ሰዎች እርዳታ ይሰጣሉ?
    ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች
  • የአደጋ ጊዜ እርዳታ ሥራ በ2023—“የይሖዋን ፍቅር በዓይናችን አይተናል”
    የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
  • የእርዳታ ሥራ በ2021—ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አልተተዉም
    የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
ለተጨማሪ መረጃ
የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!
kr ምዕ. 20 ገጽ 209-219

ምዕራፍ 20

የእርዳታ አገልግሎት

የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

በአስቸጋሪ ወቅቶች በተግባር የታየ ክርስቲያናዊ ፍቅር

1, 2. (ሀ) በይሁዳ ያሉ ክርስቲያኖች ምን አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጠማቸው? (ለ) በይሁዳ ያሉ ክርስቲያኖች የትኛውን የፍቅር ድርጊት ተመልክተዋል?

ወቅቱ 46 ዓ.ም. ገደማ ሲሆን ይሁዳ በረሃብ ተጠቅታለች። ከፍተኛ የእህል እጥረት ስላለ የምግብ ዋጋ የማይቀመስ ሆኗል፤ በመሆኑም በይሁዳ ያሉት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እህል ለመግዛት የሚያስችል አቅም አልነበራቸውም። የምግብ እጥረቱ እጅግ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል። ሆኖም እነዚህ ክርስቲያኖች፣ ማንኛውም የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ከዚያ በፊት ባላየው መንገድ የይሖዋን እጅ ሊያዩ ነው። እንዴት?

2 በሶርያ፣ አንጾኪያ የሚገኙ አይሁድና ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያሉ ክርስቲያኖች ባጋጠማቸው ችግር ስላዘኑ ለእምነት ባልንጀሮቻቸው የሚሆን ገንዘብ አሰባሰቡ። ከዚያም ከመካከላቸው ሁለት ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞችን ይኸውም በርናባስንና ሳኦልን መርጠው እርዳታውን በኢየሩሳሌም ላሉት የጉባኤ ሽማግሌዎች እንዲያደርሱ ላኳቸው። (የሐዋርያት ሥራ 11:27-30⁠ን እና 12:25⁠ን አንብብ።) በይሁዳ ያሉት የተቸገሩ ወንድሞች፣ በአንጾኪያ ያሉ ወንድሞቻቸው ባሳዩዋቸው ፍቅር ልባቸው በጥልቅ ተነክቶ እንደሚሆን አያጠራጥርም!

3. (ሀ) በዘመናችን ያሉ የአምላክ ሕዝቦች በአንጾኪያ የነበሩትን የጥንት ክርስቲያኖች አርዓያ የሚከተሉት እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ። (“በዘመናችን ያከናወንነው የመጀመሪያው መጠነ ሰፊ የእርዳታ ሥራ” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።) (ለ) በዚህ ምዕራፍ ላይ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተከሰተው ይህ ሁኔታ በአንድ ቦታ ያሉ ክርስቲያኖች በሌላ የዓለም ክፍል የሚኖሩ ወንድሞቻቸውን ለማገዝ ስለላኩት እርዳታ የሚገልጽ የመጀመሪያው በጽሑፍ የሰፈረ ዘገባ ነው። በዛሬው ጊዜ እኛም የአንጾኪያ ወንድሞቻችን የተዉትን ምሳሌ እንከተላለን። በሌላ አካባቢ ያሉ የእምነት ባልንጀሮቻችን በተፈጥሮ አደጋ ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ችግር ላይ እንደወደቁ ስናውቅ እርዳታ እናደርግላቸዋለን።a እርዳታ ለመስጠት የምናደርገው ጥረት ከሌሎች የአገልግሎት እንቅስቃሴዎቻችን ጋር እንዴት እንደሚያያዝ ለመረዳት እንድንችል የእርዳታ አገልግሎትን በተመለከተ የሚከተሉትን ሦስት ጥያቄዎች እንመረምራለን፦ እርዳታ መስጠትን እንደ አገልግሎት የምንቆጥረው ለምንድን ነው? የእርዳታ ሥራ የምናከናውንበት ዓላማ ምንድን ነው? ከእርዳታ አገልግሎት ምን ጥቅሞች እናገኛለን?

የእርዳታ ሥራ “ቅዱስ አገልግሎት” የሆነው ለምንድን ነው?

4. ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ወንድሞች ስለ ክርስቲያናዊው አገልግሎት ምን ብሏቸዋል?

4 ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ የክርስቲያኖች አገልግሎት ሁለት ገጽታዎች እንዳሉት ገልጿል። ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈው ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ቢሆንም የተናገረው ነገር በዛሬው ጊዜ ላሉ የክርስቶስ “ሌሎች በጎች” ጭምር ይሠራል። (ዮሐ. 10:16) የአገልግሎታችን አንዱ ገጽታ “የማስታረቅ አገልግሎት” ይኸውም የስብከቱና የማስተማሩ ሥራ ነው። (2 ቆሮ. 5:18-20፤ 1 ጢሞ. 2:3-6) ሌላው ገጽታ ደግሞ ለእምነት ባልንጀሮቻችን ስንል የምናከናውነው አገልግሎት ነው። ጳውሎስ ይህን አገልግሎት ‘የእርዳታ አገልግሎት’ በማለት ጠርቶታል። (2 ቆሮ. 8:4) “የማስታረቅ አገልግሎት” እና ‘የእርዳታ አገልግሎት’ በሚሉት በሁለቱም አገላለጾች ላይ “አገልግሎት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ዲያኮኒያ ነው። ታዲያ ይህ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?

5. ጳውሎስ የእርዳታ ሥራው፣ አገልግሎት እንደሆነ መናገሩ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?

5 ጳውሎስ በሁለቱም ቦታዎች ላይ አንድ ዓይነት የግሪክኛ ቃል መጠቀሙ የእርዳታውን ሥራ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከሚከናወኑ ሌሎች አገልግሎቶች ጋር እንደፈረጀው የሚያሳይ ነው። ቀደም ሲል እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር፦ “ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ፤ ሁሉም አገልግሎት የሚቀርበው ግን ለአንድ ጌታ ነው፤ በተጨማሪም ልዩ ልዩ ሥራዎች አሉ፤ ሆኖም . . . እነዚህን ሁሉ ነገሮች የሚያከናውነው ያው አንድ መንፈስ ነው።” (1 ቆሮ. 12:4-6, 11) እንዲያውም ጳውሎስ በጉባኤ ውስጥ የሚከናወኑትን የተለያዩ አገልግሎቶች ‘ከቅዱስ አገልግሎት’ ጋር አያይዞ ገልጿቸዋል።b (ሮም 12:1, 6-8) ከዚህ አንጻር፣ ሐዋርያው የተወሰነ ጊዜውን “ቅዱሳንን ለማገልገል” መመደቡ አስፈላጊ እንደሆነ የተሰማው መሆኑ አያስገርምም!—ሮም 15:25, 26

6. (ሀ) ጳውሎስ እንደተናገረው የእርዳታ ሥራ የአምልኳችን ክፍል የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ የእርዳታ ሥራ የምናከናውነው እንዴት እንደሆነ ግለጽ። (“አደጋ ሲከሰት!” የሚለውን በገጽ 214 ላይ የሚገኝ ሣጥን ተመልከት።)

6 ጳውሎስ የእርዳታ ሥራ፣ ክርስቲያኖች የሚያከናውኑት አገልግሎትና ለይሖዋ የሚያቀርቡት አምልኮ ክፍል የሆነበትን ምክንያት እንዲገነዘቡ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ረድቷቸዋል። ያቀረበውን ማስረጃ እንመልከት፦ እርዳታ የሚሰጡ ክርስቲያኖች ይህን የሚያደርጉት “ስለ ክርስቶስ ለሚገልጸው ምሥራች ተገዢዎች [ስለሆኑ]” እንደሆነ ተናግሯል። (2 ቆሮ. 9:13) ክርስቲያኖች የክርስቶስን ትምህርት በሥራ ማዋል ስለሚፈልጉ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ይረዳሉ። ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች ለወንድሞቻቸው ሲሉ የሚያከናውኑት የደግነት ተግባር “አምላክ [የሰጣቸው] የላቀ ጸጋ” መገለጫ እንደሆነ ተናግሯል። (2 ቆሮ. 9:14፤ 1 ጴጥ. 4:10) ከዚህ አንጻር፣ የታኅሣሥ 1, 1975 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) የተቸገሩ ወንድሞቻችንን ስለማገልገል (የእርዳታ ሥራን ይጨምራል) የሚከተለውን ሐሳብ መስጠቱ የተገባ ነው፦ “ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዚህ ዓይነቱ አገልግሎት ከፍ ያለ ቦታ እንደሚሰጡ ፈጽሞ ልንጠራጠር አይገባም።” በእርግጥም የእርዳታ ሥራ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ‘የቅዱስ አገልግሎት’ ክፍል ነው።—ሮም 12:1, 7፤ 2 ቆሮ. 8:7፤ ዕብ. 13:16

ግልጽ ዓላማዎች ያሉት እርዳታ

7, 8. የምናከናውነው የእርዳታ አገልግሎት የመጀመሪያ ዓላማ ምንድን ነው? አብራራ።

7 የእርዳታ አገልግሎት የምንሰጥበት ዓላማ ምንድን ነው? ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥቷል። (2 ቆሮንቶስ 9:11-15⁠ን አንብብ።) ጳውሎስ “ሕዝባዊ አገልግሎት” ይኸውም የእርዳታ ሥራ የምናከናውንባቸውን ሦስት ዋና ዋና ዓላማዎች በዚህ ጥቅስ ላይ ጎላ አድርጎ ገልጿል። እስቲ እነዚህን ዓላማዎች አንድ በአንድ እንመልከታቸው።

8 አንደኛ፣ የእርዳታ አገልግሎት መስጠታችን ለይሖዋ ክብር ያመጣል። ጳውሎስ ከላይ በተጠቀሱት አምስት ቁጥሮች ላይ ለወንድሞቹ ስለ ይሖዋ አምላክ ምን ያህል ደጋግሞ እንደተናገረ ልብ በል። ሐዋርያው ‘ለአምላክ ስለሚቀርብ ምስጋና’ እንዲሁም ‘ለአምላክ ስለሚቀርብ ብዙ ምስጋና’ ለወንድሞቹ ገልጾላቸዋል። (ቁጥር 11, 12) የእርዳታ ሥራ፣ ክርስቲያኖች “አምላክን እንዲያከብሩ” እንዲሁም ‘አምላክ የሰጣቸውን የላቀ ጸጋ’ እንዲያደንቁ እንደሚያደርግ ተናግሯል። (ቁጥር 13, 14) ጳውሎስ ስለ እርዳታ አገልግሎት የሰጠውን ሐሳብ የደመደመው “አምላክ የተመሰገነ ይሁን” በማለት ነው።—ቁጥር 15፤ 1 ጴጥ. 4:11

9. የእርዳታ ሥራ በሰዎች አመለካከት ላይ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል? ምሳሌ ስጥ።

9 እንደ ጳውሎስ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮችም የእርዳታ ሥራዎችን የሚመለከቷቸው ለይሖዋ ክብር ለማምጣት እንዲሁም ትምህርቶቹ ውበት እንዲጎናጸፉ ለማድረግ እንደሚያስችሉ አጋጣሚዎች አድርገው ነው። (1 ቆሮ. 10:31፤ ቲቶ 2:10) ደግሞም የእርዳታ ሥራ አንዳንዶች ስለ ይሖዋና ስለ ምሥክሮቹ ያላቸውን አሉታዊ አመለካከት ለመቀየር ብዙውን ጊዜ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ በአውሎ ነፋስ ከባድ ጉዳት በደረሰበት አካባቢ የምትኖር አንዲት ሴት በሯ ላይ “የይሖዋ ምሥክሮች፣ በሬን እንዳታንኳኩ” የሚል ምልክት ለጥፋ ነበር። ከዚያም አንድ ቀን ፈቃደኛ ሠራተኞች ከቤቷ ፊት ለፊት የሚገኘውን በአውሎ ነፋስ ጉዳት የደረሰበት ቤት ሲጠግኑ ተመለከተች። በሠራተኞቹ መካከል ወዳጃዊ መንፈስ እንዳለ በየዕለቱ ታስተውል ስለነበር እነዚህ ሰዎች እነማን እንደሆኑ ለማወቅ ወደ ቦታው ሄደች። እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ስትገነዘብ በጣም ተገረመች። “አሁን እንዳስተዋልኩት ስለ እናንተ የነበረኝ አመለካከት የተሳሳተ ነው” በማለት ተናገረች። ይህች ሴት ምን አድርጋ ይሆን? በሯ ላይ የለጠፈችውን ምልክት አንስታለች።

10, 11. (ሀ) የእርዳታ ሥራችን ሁለተኛ ዓላማ ግቡን እየመታ እንዳለ የሚያሳዩ ምን ምሳሌዎች አሉ? (ለ) የእርዳታ ሠራተኞችን የሚያግዝ ምን ጽሑፍ ተዘጋጅቷል? (“የእርዳታ ሠራተኞችን የሚጠቅም ተጨማሪ መሣሪያ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

10 ሁለተኛ፣ የእምነት ባልንጀሮቻችን “የሚያስፈልጓቸው ነገሮች በሚገባ እንዲሟሉላቸው” እናደርጋለን። (2 ቆሮ. 9:12ሀ) ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በአፋጣኝ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላትና ሥቃያቸውን ለማስታገስ እንፈልጋለን። ለምን? ምክንያቱም የክርስቲያን ጉባኤ አባላት በሙሉ ‘አንድ አካል’ ስለሆኑ “አንድ የአካል ክፍል ቢሠቃይ ሌሎቹ የአካል ክፍሎች በሙሉ አብረውት ይሠቃያሉ።” (1 ቆሮ. 12:20, 26) በመሆኑም በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ወንድሞችና እህቶች፣ የእምነት ባልንጀሮቻቸው ችግር እንዳጋጠማቸው ሲያውቁ ወዲያውኑ ሁሉን ነገር ትተው የሚያስፈልጋቸውን መሣሪያ ብቻ በመያዝ እርዳታ ለመስጠት በአደጋ ወደተጠቁ ቦታዎች እንዲሄዱ የሚያነሳሳቸው ለወንድሞቻቸው ያላቸው ፍቅርና ርኅራኄ ነው። (ያዕ. 2:15, 16) ለምሳሌ ያህል፣ ጃፓን በ2011 በሱናሚ በተመታች ጊዜ የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ለሚገኙ የአካባቢ የግንባታ ኮሚቴዎች ደብዳቤ በመጻፍ ጃፓን ሄደው የመንግሥት አዳራሾችን እንደገና መገንባት የሚችሉ “ብቃት ያላቸው ጥቂት ወንድሞች” ማግኘት ይቻል እንደሆነ ጠየቀ። ታዲያ ምን ምላሽ ተገኘ? በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወደ 600 ገደማ ፈቃደኛ ሠራተኞች በራሳቸው ወጪ ወደ ጃፓን ተጉዘው እርዳታ ለመስጠት ራሳቸውን አቀረቡ! የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ “ያገኘነው ምላሽ ከጠበቅነው በላይ ሆኖብናል” ብሏል። በጃፓን የሚኖር አንድ ወንድም፣ እርዳታ ለመስጠት ከሌላ አገር የመጣን ወንድም ይህን ያደረገው ለምን እንደሆነ ሲጠይቀው “በጃፓን ካሉ ወንድሞቻችን ጋር ‘አንድ አካል’ ነን። በመሆኑም ሥቃያቸውና ችግራቸው እኛንም ይሰማናል” የሚል ምላሽ ሰጥቶታል። ፈቃደኛ ሠራተኞቹ፣ ሕይወታቸውን እንኳ አደጋ ላይ ጥለው የእምነት ባልንጀሮቻቸውን የረዱባቸው ጊዜያትም አሉ፤ ይህም የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር እንዳላቸው ያሳያል።c—1 ዮሐ. 3:16

በስዊዘርላንድ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ለእምነት ባልንጀሮቿ የእርዳታ ቁሳቁስ ስታዘጋጅ፣ 1946

ስዊዘርላንድ፣ 1946

በዘመናችን ያከናወንነው የመጀመሪያው መጠነ ሰፊ የእርዳታ ሥራ

መስከረም 1945 ይኸውም በአውሮፓ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ከጥቂት ወራት በኋላ ወንድም ኖር “በመካከለኛው አውሮፓ ላሉ ችግር ላይ የወደቁ ወንድሞቻችን ቁሳዊ እርዳታ” ለመላክ መጠነ ሰፊ ዘመቻ እንደሚጀመር አስታወቀ።

ይህ ማስታወቂያ በተነገረ በሳምንታት ውስጥ በካናዳ፣ በዩናይትድ ስቴትስና በሌሎች አገሮች የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች አልባሳትን በዓይነት በዓይነቱ እየለዩ ማዘጋጀት እንዲሁም ምግብ ማሰባሰብ ጀመሩ። ከጥር 1946 ጀምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶች ወደ ሃንጋሪ፣ ሩማንያ፣ ቡልጋሪያ፣ ቤልጅየም፣ ቻይና፣ ቼኮዝሎቫኪያ፣ ኔዘርላንድ፣ ኖርዌይ፣ እንግሊዝ፣ ኦስትሪያ፣ ዴንማርክ፣ ጀርመን፣ ግሪክ፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ፊሊፒንስ፣ ፊንላንድና ፖላንድ ተላኩ።

ይህ የእርዳታ ዝግጅት የተካሄደው ለአንድ ጊዜ ብቻ አልነበረም። ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል እርዳታ ይላክ ነበር! በዚህ ጊዜ ውስጥ 85,000 የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች በጦርነት በተጎዱ አገሮች ውስጥ ለሚኖሩ የእምነት ባልንጀሮቻቸው 300,000 ኪሎ ግራም የሚሆን ምግብ፣ 450,000 ኪሎ ግራም የሚሆኑ አልባሳት እንዲሁም ከ124,000 በላይ ጥንድ ጫማዎች ልከዋል። ይህ መጠነ ሰፊ የእርዳታ ዝግጅት ነሐሴ 1948 አበቃ። የ1949 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) “ይህ አንዳችን ለሌላው ፍቅር ያሳየንበት መንገድ እንደሆነ ጥርጥር የለውም” ብሏል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉም ወንድሞች ይህን ያደረጉት ጌታን ለማክበር እንዲሁም ይህ ቁሳዊ እርዳታ አንዳንዶች እውነተኛውን አምልኮ ማከናወናቸውን እንዲቀጥሉ እንደሚረዳቸው በማሰብ እንደሆነ እናውቃለን፤ በመሆኑም ወንድሞቻቸውን በዚህ መንገድ ማገልገል መቻላቸውን እንደ ትልቅ መብት ይቆጥሩታል።” ይህ የእርዳታ ዝግጅት ለይሖዋ ክብር አምጥቷል፣ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ለመርዳት አስችሏል፤ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ባሉት ወንድሞቻችን መካከል ያለው አንድነት እንዲጠናከር አድርጓል።

11 የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችም የምናከናውነውን የእርዳታ ሥራ እንደሚያደንቁ ገልጸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ2013 በአርከንሶ፣ ዩናይትድ ስቴትስ አደጋ በተከሰተ ጊዜ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች የሰጡትን ፈጣን ምላሽ በተመለከተ አንድ ጋዜጣ እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ፈቃደኛ ሠራተኞቻቸውን በሚገባ ስላደራጇቸው አደጋ ለደረሰባቸው ሰዎች እርዳታ የሚሰጡት በተቀላጠፈና ውጤታማ በሆነ መንገድ ነው።” በእርግጥም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው ችግር ላይ የወደቁ ወንድሞቻችን “የሚያስፈልጓቸው ነገሮች በሚገባ እንዲሟሉላቸው” እናደርጋለን።

12-14. (ሀ) የእርዳታ ሥራችንን ሦስተኛ ዓላማ ማሳካታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ወንድሞች ወደ ቀድሞ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻቸው መመለሳቸው ያለውን ጠቀሜታ የሚያሳዩት የትኞቹ አስተያየቶች ናቸው?

12 ሦስተኛ፣ አደጋ የደረሰባቸው ወንድሞቻችን ወደ ቀድሞው መንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ እንረዳቸዋለን። ይህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ጳውሎስ እርዳታ የሚደረግላቸው ሰዎች ‘ለአምላክ ብዙ ምስጋና ለማቅረብ’ እንደሚነሳሱ ገልጿል። (2 ቆሮ. 9:12ለ) ችግር ላይ የወደቁ ወንድሞች በተቻለ ፍጥነት ወደ መንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸው ከመመለስ በላይ ለይሖዋ ያላቸውን አድናቆት የሚገልጹበት ምን የተሻለ መንገድ ሊኖር ይችላል? (ፊልጵ. 1:10) የ1945 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ጳውሎስ መዋጮ እንዲሰበሰብ የተስማማው . . . መዋጮው ችግር ላይ የወደቁ . . . ወንድሞች በቁሳዊ ረገድ የተወሰነ እርዳታ እንዲያገኙና በዚህም ምክንያት ስለ ሥጋዊ ነገር ሳይጨነቁ ሙሉ ኃይላቸውን ስለ ይሖዋ በመመሥከሩ ሥራ ላይ እንዲያደርጉ ስለሚረዳቸው ነው።” ዛሬም ዓላማችን ይኸው ነው። ወንድሞቻችን ወደ ስብከቱ ሥራ መመለሳቸው የተጨነቁ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ራሳቸውንም ያበረታታቸዋል።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4⁠ን አንብብ።

13 በጣም ያስፈልጋቸው የነበረውን እርዳታ ካገኙ በኋላ በአገልግሎት መካፈላቸውን የቀጠሉ አንዳንዶች እንዲህ ማድረጋቸው እንዴት እንዳበረታታቸው የሰጡትን አስተያየት እንመልከት። አንድ ወንድም “ቤተሰባችን በአገልግሎት መካፈሉ በረከት ሆኖለታል” ብሏል። አክሎም “ሌሎችን ለማጽናናት ጥረት ማድረጋችን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ስለ ራሳችን ጉዳዮች በማሰብ እንዳንጨነቅ ረድቶናል” በማለት ተናግሯል። አንዲት እህት ደግሞ “በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ማተኮሬ በአካባቢዬ ስለደረሰው ውድመት እንዳላስብ አድርጎኛል። የደኅንነት ስሜት እንዲሰማኝ ረድቶኛል” ብላለች። አንዲት ሌላ እህትም እንዲህ ብላለች፦ “ብዙ ነገሮች ከእኛ አቅም በላይ ቢሆኑም አገልግሎት፣ ቤተሰባችን በተስፋችን ላይ እንዲያተኩር ረድቶታል። አዲሱን ዓለም በተመለከተ ስላለን ተስፋ ለሌሎች መናገራችን ሁሉም ነገር አዲስ እንደሚሆን ያለንን እምነት አጠናክሮልናል።”

14 አደጋ የደረሰባቸው የእምነት ባልንጀሮቻችን በተቻለ ፍጥነት ሊቀጥሉት የሚገባው ሌላው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ነው። ኪዮኮ የተባሉ እህት ምን እንዳጋጠማቸው እንመልከት። የሚኖሩበት አካባቢ በሱናሚ በተመታበት ወቅት በ50ዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ የነበሩት እህት ኪዮኮ ከለበሱት ልብስና ካደረጉት ጫማ በቀር ሁሉን ነገር አጡ፤ በመሆኑም ምን እንደሚያደርጉ ግራ ገብቷቸው ነበር። ከዚያም አንድ ሽማግሌ፣ መደበኛ ክርስቲያናዊ ስብሰባቸውን በእሱ መኪና ውስጥ እንደሚያደርጉ ነገራቸው። እህት ኪዮኮ እንዲህ ብለዋል፦ “መኪናው ውስጥ አንድ የጉባኤ ሽማግሌና ሚስቱ እንዲሁም እኔና አንዲት ሌላ እህት ነበርን። ስብሰባው አጠር ያለ ቢሆንም የሱናሚው ሐሳብ ከአእምሮዬ በንኖ ጠፋ፤ ይህ ተአምር ነበር። የአእምሮ ሰላም አገኘሁ። ይህ ስብሰባ፣ ክርስቲያኖች አንድ ላይ መሰብሰባቸው ምን ያህል ጥቅም እንዳለው አስገንዝቦኛል።” አንዲት ሌላ እህት አደጋ ከደረሰ በኋላ ስለተገኘችባቸው የጉባኤ ስብሰባዎች ስትናገር “በጽናት እንድቀጥል ረድተውኛል” ብላለች።—ሮም 1:11, 12፤ 12:12

የእርዳታ አገልግሎት ዘላቂ ጥቅሞች ያስገኛል

15, 16. (ሀ) በቆሮንቶስም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ያሉ ክርስቲያኖች ከእርዳታ ሥራ ምን ጥቅም አግኝተዋል? (ለ) እኛስ በዛሬው ጊዜ ከሚከናወነው የእርዳታ ሥራ ተመሳሳይ ጥቅም የምናገኘው እንዴት ነው?

15 ጳውሎስ የእርዳታ አገልግሎትን በተመለከተ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በሰጠው ሐሳብ ላይ እነሱም ሆኑ ሌሎች ክርስቲያኖች ከዚህ ሥራ ስለሚያገኙት ጥቅምም ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ከሰጣችሁ የላቀ ጸጋ የተነሳ ስለ እናንተ ምልጃ እያቀረቡ [እርዳታ የተደረገላቸው በኢየሩሳሌም ያሉ አይሁዳዊ ክርስቲያኖች] ለእናንተ ያላቸውን ፍቅር ይገልጻሉ።” (2 ቆሮ. 9:14) በእርግጥም የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ያሳዩት ልግስና፣ በይሁዳ ያሉ ክርስቲያኖች በቆሮንቶስ ላሉ ወንድሞቻቸው (ከአሕዛብ የመጡትንም ይጨምራል) እንዲጸልዩ አነሳስቷቸዋል፤ እንዲሁም ለእነሱ ያላቸው ፍቅር እንዲጨምር አድርጓል።

16 የታኅሣሥ 1, 1945 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ጳውሎስ የእርዳታ ሥራ ያለውን ጥቅም አስመልክቶ የተናገረው ሐሳብ በዘመናችን እንዴት እንደሚሠራ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በአንድ አካባቢ ያሉ ራሳቸውን የወሰኑ የአምላክ ሕዝቦች በሌላ አካባቢ ያሉ የተቸገሩ ወንድሞቻቸውን መርዳታቸው ምን ያህል አንድነት ሊፈጥር እንደሚችል አስቡ!” በዛሬው ጊዜ ያሉ የእርዳታ ሥራ የሚያከናውኑ ወንድሞችም የሚሰማቸው እንዲሁ ነው። በጎርፍ ለተጠቁ ወንድሞች እርዳታ ያደረገ አንድ ሽማግሌ “በእርዳታ ሥራው መካፈሌ ከመቼውም የበለጠ ከወንድሞቼ ጋር እንደተቀራረብኩ እንዲሰማኝ አድርጓል” ብሏል። እርዳታ የተደረገላት አንዲት እህት አመስጋኝነቷን ስትገልጽ “የወንድማማች ፍቅራችን ምድር ገነት በምትሆንበት ወቅት ምን ሁኔታ እንደሚኖር የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ነው” ብላለች።—ምሳሌ 17:17⁠ን አንብብ።

17. (ሀ) ኢሳይያስ 41:13 ከእርዳታ ሥራ ጋር በተያያዘ ፍጻሜ የሚያገኘው እንዴት ነው? (ለ) የእርዳታ ሥራ ይሖዋን የሚያስከብረውና ከወንድሞቻችን ጋር ያለንን አንድነት የሚያጠናክረው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ። (“በዓለም ዙሪያ ያሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች እፎይታ ያስገኛሉ” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

17 እርዳታ የሚሰጡ ወንድሞች በአደጋ ለተጠቁት ወንድሞች ሲደርሱላቸው በአካባቢው ያሉት ክርስቲያኖች አምላክ “‘አትፍራ። እረዳሃለሁ’ የምልህ እኔ፣ አምላክህ ይሖዋ ቀኝ እጅህን ይዣለሁ” በማለት የገባውን ቃል እውነተኝነት ለየት ባለ መንገድ ማየት ችለዋል። (ኢሳ. 41:13) ከአደጋ የተረፈች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “የደረሰውን ውድመት ስመለከት ተስፋ ቆርጬ ነበር፤ ይሖዋ ግን እጁን ዘረጋልኝ። ከወንድሞች ያገኘሁት እርዳታ በቃላት ሊገለጽ አይችልም።” ሁለት ሽማግሌዎች፣ የሚኖሩበት አካባቢ በአደጋ ከተጠቃ በኋላ ጉባኤዎቻቸውን ወክለው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የምድር መናወጡ ከፍተኛ ሥቃይ ቢያስከትልም በወንድሞቻችን አማካኝነት የይሖዋን እጅ ማየት ችለናል። ስለ እርዳታ ሥራ አንብበን እናውቃለን፤ አሁን ግን እንዲህ ዓይነት እርዳታ ሲደረግ በገዛ ዓይናችን መመልከት ችለናል።”

ፒተር ጆንሰን በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክት ላይ ሲሠራ

ሕይወቱን አቅጣጫ አስይዞለታል

ወጣቶች በእርዳታ ሥራ መካፈላቸው ምን በጎ ተጽዕኖ ያሳድርባቸዋል? በ18 ዓመቱ በእርዳታ ሥራ መካፈል የጀመረውን ፒተር ጆንሰንን እንደ ምሳሌ እንመልከት። እንዲህ ይላል፦ “ወንድሞች ምን ያህል አመስጋኝ እንደሆኑ እንዲሁም መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ መመልከቴ ልቤን ነካው። ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ በይሖዋ አገልግሎት ለማሳለፍ የነበረኝን ፍላጎት አጠናክሮልኛል።” ከዚያ በኋላ ፒተር አቅኚነት ጀመረ። ከዚያም በቤቴል አገልግሏል፤ ከጊዜ በኋላ ደግሞ የአካባቢ የግንባታ ኮሚቴ አባል ሆኖ መሥራት ጀመረ። ፒተር “በ1974 ለመጀመሪያ ጊዜ በእርዳታ ሥራ መካፈሌ ሕይወቴን አቅጣጫ አስይዞታል” በማለት ተናግሯል። አንተስ፣ ወጣት ነህ? ከሆነ የፒተርን ምሳሌ መከተል ትችላለህ? የእርዳታ ሥራ፣ ለይሖዋ ከምታቀርበው አገልግሎት ጋር በተያያዘ ሕይወትህን በየትኛው አቅጣጫ እንደሚመራው ማን ያውቃል?

የበኩልህን ድርሻ ማበርከት ትችላለህ?

18. በእርዳታ ሥራ መካፈል ከፈለግህ ምን ማድረግ ትችላለህ? (“ሕይወቱን አቅጣጫ አስይዞለታል” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

18 በእርዳታ ሥራ መካፈል የሚያስገኘውን ደስታ መቅመስ ትፈልጋለህ? ከሆነ የእርዳታ ሠራተኞች በአብዛኛው የሚመረጡት በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ከሚካፈሉት መካከል እንደሆነ አስታውስ። ስለዚህ በዚህ ሥራ ለመካፈል ማመልከት እንደምትፈልግ ለጉባኤህ ሽማግሌዎች ንገራቸው። በእርዳታ ሥራ የረጅም ጊዜ ተሞክሮ ያለው አንድ ሽማግሌ እንዲህ የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል፦ “አደጋ ወደደረሰበት ቦታ መጓዝ ያለብህ የእርዳታ ሰጪ ኮሚቴው እንዲህ እንድታደርግ ግብዣ ካቀረበልህ ብቻ ነው።” እንዲህ ካደረግን የእርዳታውን ሥራ ሥርዓት ባለው መንገድ ማከናወን እንችላለን።

19. የእርዳታ ሠራተኞች እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን በግልጽ የሚያሳዩት እንዴት ነው?

19 በእርግጥም የእርዳታ ሥራ ክርስቶስ “እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” በማለት የሰጠንን ትእዛዝ የምንፈጽምበት አንዱ መንገድ ነው። እንዲህ ዓይነት ፍቅር በማሳየት የክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን እናስመሠክራለን። (ዮሐ. 13:34, 35) በዛሬው ጊዜ፣ የአምላክ መንግሥት ታማኝ ደጋፊዎች አደጋ በሚያጋጥማቸው ወቅት የእርዳታ አገልግሎት በመስጠት ለይሖዋ ክብር የሚያመጡ በርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞች በመካከላችን መኖራቸው እንዴት ያለ በረከት ነው!

a በዚህ ምዕራፍ ላይ የምንመረምረው ለእምነት ባልንጀሮቻችን ስለምንሰጠው የእርዳታ አገልግሎት ነው። ሆኖም በምንሰጠው እርዳታ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችም የተጠቀሙባቸው ብዙ ጊዜያት አሉ።—ገላ. 6:10

b ጳውሎስ ስለ ‘ጉባኤ አገልጋዮች’ ሲናገር የተጠቀመው ዲያኮኖስ (አገልጋይ) የሚለውን ቃል ብዙ ቁጥር ነው።—1 ጢሞ. 3:12

c በኅዳር 1, 1994 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 23-27 ላይ የወጣውን “በቦስኒያ የሚኖሩትን የእምነት ቤተሰቦቻችን መርዳት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

የአምላክ መንግሥት ለአንተ ምን ያህል እውን ነው?

  • የእርዳታ ሥራ ለይሖዋ የምናቀርበው ቅዱስ አገልግሎት ክፍል መሆኑን እንዴት እናውቃለን?

  • የምናከናውነው የእርዳታ ሥራ ሦስት ዋና ዋና ዓላማዎች ምንድን ናቸው?

  • የእርዳታ ሥራ ምን ዘላቂ ጥቅሞች ያስገኛል?

  • የእርዳታ ሥራ ኢየሱስ በዮሐንስ 13:34 ላይ ከሰጠው መመሪያ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

በዓለም ዙሪያ ያሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች እፎይታ ያስገኛሉ

መካከለኛውና ምዕራብ አፍሪካ

በ1994 በሩዋንዳ ባሉ ጎሳዎች መካከል በተካሄደው የዘር ማጥፋት ዘመቻ 800,000 ወይም ከዚያ የሚበልጡ ሰዎች ተገድለዋል። ይህ እልቂት በሌሎች የመካከለኛው አፍሪካ አገሮች አለመረጋጋት አስከተለ፤ በዚህም የተነሳ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች በሕዝብ ተጨናነቁ። በስዊዘርላንድ፣ በቤልጂየምና በፈረንሳይ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ችግር ላይ የወደቁትን እነዚህን የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለመርዳት ወደ 300 ቶን የሚመዝኑ አልባሳት፣ መድኃኒቶች፣ ድንኳኖች፣ ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶች በአውሮፕላን ላኩ። እነዚህ ቁሳቁሶች ለተቸገሩት ወንድሞቻችን በሳምንታት ውስጥ ደርሰዋል።

ከዚህም ሌላ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ አሥር ሐኪሞችንና ነርሶችን ያቀፈ አንድ የፈረንሳይ የሕክምና ቡድን አፍሪካ ውስጥ በእርስ በርስ ጦርነት፣ በረሃብና በበሽታ ጉዳት ለደረሰባቸው ወንድሞቻችን የሕክምና እርዳታ ሲሰጥ ቆይቷል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ቡድኑ ከ10,000 ለሚበልጡ ጊዜያት ለተለያዩ ሰዎች የሕክምና እርዳታ ሰጥቷል። የእነዚህ ወንድሞች ሥራ ለይሖዋም ሆነ ለድርጅቱ ክብር አምጥቷል። ከነርሶቹ አንዷ እንዲህ ብላለች፦ “ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ለመርዳት ወደ አንድ አካባቢ ስንሄድ ሰዎች ‘እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። የመጡት ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ነው’ በማለት በአክብሮት ይናገራሉ።” አንዲት እህት፣ ከነርሶቹ አንዷ ከረዳቻት በኋላ “እህቴ ሆይ፣ አመሰግንሻለሁ። ይሖዋ አመሰግንሃለሁ!” በማለት ተናግራለች።

ከባድ አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜም የእርዳታ ሥራ ማከናወን አስፈላጊ ይሆናል። በ2012 በናይጄሪያ በተከሰተ የመኪና አደጋ የአንድ ትንሽ ጉባኤ አባላት የሆኑ 13 የይሖዋ ምሥክሮች የሞቱ ሲሆን 54ቱ ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል። የእርዳታ ኮሚቴው፣ አደጋ የደረሰበት እያንዳንዱ ግለሰብ ሌት ተቀን ክትትል እንዲደረግለት ዝግጅት አደረገ። ሆስፒታል የተኛች አንዲት ሕመምተኛ አደጋ ለደረሰባቸው ወንድሞችና እህቶች ምን ያህል እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው ስትመለከት ለቤተ ክርስቲያኗ ፓስተር ስልክ ደውላ እንዲህ ብላዋለች፦ “ከቤተ ክርስቲያናችን ማንም መጥቶ አልጠየቀኝም። ወደ ሆስፒታሉ መጥተህ የይሖዋ ምሥክሮች ፍቅራቸውን በተግባር ሲገልጹ ተመልከት!”

በዚያ ትንሽ ጉባኤ የሚገኙት ውድ ወንድሞቻችን ባጋጠማቸው ነገር እጅግ ቢያዝኑም የእምነት ባልንጀሮቻቸው ባሳዩዋቸው ፍቅር በጣም ተጽናንተዋል። በተጨማሪም የእርዳታ ሠራተኞች ጉዳት ለደረሰባቸው ወንድሞች ባደረጉት ፍቅራዊ እንክብካቤ ልባቸው የተነካ በርካታ የጉባኤው አባላት አገልግሎታቸውን ይበልጥ ለማቀጣጠል ተነሳስተዋል። ከአደጋው በፊት ይህ ጉባኤ 35 አስፋፊዎች ነበሩት። በአንድ ዓመት ውስጥ ይህ ቁጥር ወደ 60 አድጓል።

አውስትራሊያ

በ2013 ከኩዊንስላንድ የባሕር ዳርቻ የተወሰነው ክፍል በጎርፍ የተጥለቀለቀ ሲሆን 70 የይሖዋ ምሥክሮች ቤታቸውን አጥተዋል። ማርክና ራንዳ፣ ቤታቸው በጎርፍ በመጥለቅለቁ ሴት ልጃቸውን ይዘው ወደ መጠለያ ተቋም ሄዱ። ቦታው በሰው ተጨናንቆ ነበር። ራንዳ “ያገኘነው መቆሚያ ቦታ ብቻ ነበር” በማለት ተናግራለች። በአቅራቢያው የሚያርፉትና የሚነሱት ሄሊኮፕተሮች የሚያሰሙት ጆሮ የሚያደነቁር ድምፅ ይበልጥ ውጥረት ይፈጥር ነበር። በጭንቀት የተዋጠችው ራንዳ “ምን ማድረግ ይሻለናል?” በማለት ባሏን ጠየቀችው። ማርክ፣ ይሖዋ እንዲረዳቸው አጥብቆ ጸለየ። ራንዳ እንዲህ ብላለች፦ “ከ30 ደቂቃ ገደማ በኋላ አንድ መኪና ወደ መጠለያ ጣቢያው መጣና ሦስት ወንድሞች ወረዱ። እኛን ሲያገኙን ‘አብራችሁን ሄዳችሁ አንድ ወንድም ቤት ታርፋላችሁ’ አሉን።” ራንዳ አክላም “የይሖዋ ድርጅት የሚያደርግልንን ፍቅራዊ እንክብካቤ በተመለከተ በወቅቱ የተሰማንን ስሜት በቃላት መግለጽ ይከብዳል” ብላለች።

ከ250 በላይ ፈቃደኛ ሠራተኞች ወንድሞቻቸውን ለመርዳት በአደጋ ወደተጠቃው ወደዚያ አካባቢ በፍጥነት ሄዱ። አንድ በዕድሜ የገፉ ወንድም እንዲህ ብለዋል፦ “በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በአንድ ጊዜ መጥተው በደለል የተሸፈነውን ቤቴን እንደ ጉንዳን በመውረር ማጽዳት ጀመሩ። እኔና ባለቤቴ ያደረጉልንን እርዳታ መቼም አንረሳውም።”

ብራዚል

በ2008 በሳንታ ካታሪና ግዛት በተከሰተው የጭቃ ናዳ እና የጎርፍ መጥለቅለቅ ሳቢያ 80,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ቤታቸውን ጥለው ለመሸሽ ተገድደዋል። አንድ የአካባቢው ነዋሪ ሁኔታው “የሸክላ፣ የጭቃ እና የዛፎች ሱናሚ” የመጣ ያህል እንደነበር ተናግሯል። አንዳንድ ወንድሞች በአንድ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ተጠልለው ነበር። አዳራሹን የሚንከባከበው ማርስዩ “ከአደጋው ያመለጡት ወንድሞች ከለበሱት ልብስ ሌላ ምንም ነገር አልያዙም፤ ልብሳቸውም ቢሆን በጭቃ ተበላሽቶ ነበር” ብሏል። አንዲት እህት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ቤታችን ተደረመሰ። በጥቂት ሴኮንዶች ውስጥ ቤታችን እንዳልነበረ ሲሆን ማየት በጣም ያሳዝናል፤ ይሁንና ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዴት እንዳጽናኑን መቼም ቢሆን አልረሳውም። ብዙዎች ለእኛ ያላቸውን ፍቅር አሳይተውናል! ይህ አጋጣሚ ለመንፈሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ መስጠት የጥበብ እርምጃ መሆኑን አስተምሮኛል።”

በብራዚል ከደረሰው አደጋ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች የእርዳታ ቁሳቁሶችን ሲያደራጁና ሲያከፋፍሉ

በሳንታ ካታሪና፣ ብራዚል የሚገኝ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ወንድሞች በለገሷቸው ቁሳቁሶች ተሞልቶ፣ 2009

በሪዮ ዴ ጄኔሮ ከተማ አቅራቢያ የተከሰተው የጭቃ ናዳ በተራራው ግርጌ በነበሩት አካባቢዎች ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል። ወንድሞች በተደጋጋሚ ለሚከሰቱት እንዲህ ያሉ አደጋዎች ዝግጁ ለመሆን ሲሉ ቋሚ የእርዳታ ሰጪ ኮሚቴ አቋቁመዋል። የጭቃ ናዳ ሊከሰት እንደሚችል የሚጠቁም ሁኔታ ሲፈጠር ተቆጣጣሪዎች (ለዚህ ሥራ የተመደቡ በአካባቢው የሚኖሩ ወንድሞች) ሁኔታውን ለኮሚቴው ያሳውቃሉ። ወዲያውኑ “የይሖዋ ምሥክሮች—ሰብዓዊ እርዳታ” የሚል ምልክት የተለጠፈባቸው ከባድ መኪኖች የያዙ ፈቃደኛ ሠራተኞች ይመጣሉ። በሚገባ የተደራጁት ሁሉም የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አስቀድሞ የተመደበላቸው ሥራ አላቸው። ሠራተኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን በግልጽ የሚጠቁም ልብስ ይለብሳሉ። እነዚህ ወንድሞች፣ በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ውስጥ ከሚሠሩ ወንድሞች ጋር በመተባበር የተጎዱ ወንድሞችንና እህቶችን ይረዳሉ። የእርዳታ ሠራተኞች ምግብ፣ ውኃ፣ የሕክምና ቁሳቁሶች፣ አልባሳት እና የጽዳት መሣሪያዎችን ያመጣሉ። ጭቃውን ከቤቶች ላይ ማጽዳት በጣም ከባድ ሥራ ነው። በቅርቡ ከተከሰተ የጭቃ ናዳ በኋላ 60 ፈቃደኛ ሠራተኞች ከአንድ ቤት ብቻ አራት የጭነት መኪና የሚሆን ጭቃ አንስተዋል።

ለአደጋ ጊዜ አስቀድሞ መዘጋጀት

የበላይ አካሉ፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ለአደጋ እንዴት አስቀድመው መዘጋጀት እንደሚችሉ እንዲሁም አደጋ ሲያጋጥም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለጉባኤ ሽማግሌዎችና ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾች መመሪያ እንዲሰጡ አዝዟል። ለምሳሌ ያህል፣ አደጋ ከመከሰቱ በፊት ሽማግሌዎች የእያንዳንዱ የጉባኤ አባል ወቅታዊ አድራሻ እንዳላቸው ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።

አደጋ ሲከሰት!

  1. አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ አንድን የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ ሲጠይቅ

    በአካባቢው ያሉ ሽማግሌዎች ሁሉንም አስፋፊዎች ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ

  2. ሽማግሌዎች፣ ለሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ ሪፖርት ያደርጋሉ

  3. የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪዎች፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ ኃላፊነት ያላቸው ወንድምችና ቅርንጫፍ ቢሮው ተባብረው ሲሠሩ

    አስተባባሪዎች ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ከቅርንጫፍ ቢሮው ጋር ግንኙነት ላላቸው ሌሎች ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ሪፖርት ያደርጋሉ

  4. ምግብና ውኃ

    ምግብ፣ ውኃ፣ መጠለያ፣ የሕክምና እርዳታ እንዲሁም የሚያስፈልገው ስሜታዊና መንፈሳዊ እርዳታ በተቻለ ፍጥነት ይሰጣል

  5. ስለ እርዳታ በቀረበው ሪፖርት ላይ ውይይት ሲካሄድ

    ቅርንጫፍ ቢሮው፣ ስለ ሁኔታው እንዲሁም ስለሚያስፈልጉት ነገሮች ለበላይ አካሉ የአስተባባሪዎች ኮሚቴ ሪፖርት ያቀርባል

  6. የእርዳታ ቁሳቁስ ማከፋፈል

    የእርዳታ ሰጪ ኮሚቴው የእርዳታውን ሥራ ያደራጃል፤ እንዲሁም ወንድሞችና እህቶች መልሰው እንዲቋቋሙ የሚያስችል እርዳታ ያቀርባል

  7. አየር ላይ ያለ አውሮፕላን

    የአስተባባሪዎች ኮሚቴ ምን ዓይነት እርዳታ እንደሚያስፈልግ ያጠናል፤ እንዲሁም አስፈላጊ ከሆነ በሌሎች አገሮች ያሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች ወደ ቦታው እንዲሄዱ ፈቃድ ይሰጣል

የእርዳታ ሠራተኞችን የሚጠቅም ተጨማሪ መሣሪያ

የይሖዋ ምሥክሮች በአደጋ ጊዜ የሚሰጡት እርዳታ የተሰኘው ብሮሹር ሽፋን

የይሖዋ ምሥክሮች በአደጋ ጊዜ የሚሰጡት እርዳታ (እንግሊዝኛ) የተባለ ብሮሹር ሰኔ 2013 ወጣ። ይህ ብሮሹር የተዘጋጀው በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ በአደጋ ጊዜ የሚሰጠውን እርዳታ የሚከታተሉ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ታሳቢ በማድረግ ነው። ብሮሹሩ ከ1940ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ጀምሮ ስላከናወንናቸው አንዳንድ የእርዳታ ሥራዎች ይገልጻል። በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ የእርዳታ ሥራ ያካሄድንባቸውን አገሮች የሚያሳይ ካርታ አለው። የእርዳታ ሥራ በማደራጀቱ ተግባር የሚካፈል አንድ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “በእርዳታ ሰጪ ኮሚቴዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ወንድሞች፣ ለአደጋ በተጋለጡ ቦታዎች ከሚሠሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር አደጋ ከመከሰቱ በፊት ለመገናኘት በዚህ ብሮሹር ይጠቀማሉ። እነዚህ ባለሥልጣናት የምናከናውነውን የእርዳታ ሥራ በደንብ ካወቁት አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜ ወደዚያ አካባቢ ለመግባት የሚያስፈልገንን ፈቃድ ማግኘት ቀላል ይሆንልናል።”

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ