የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 9/1 ገጽ 19-24
  • ለክርስቶስ ሕግ መገዛት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለክርስቶስ ሕግ መገዛት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በቤተሰብ ውስጥ
  • በጉባኤ ውስጥ
  • ሽማግሌዎች ሆይ፣ የክርስቶስን ሕግ በሥራ ተርጉሙ
  • ለክርስቶስ ሕግ እየተገዛችሁ ነውን?
  • የክርስቶስ ሕግ ተግባራዊ እየሆነ ነው!
  • የክርስቶስ ሕግ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ፍቅርና ፍትሕ—በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019
  • የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ልብ ብላችሁ አዳምጡ
    የ2017-2018 የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም—የቅርንጫፍ ቢሮ ተወካይ የሚገኝበት
  • ዛሬ ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 9/1 ገጽ 19-24

ለክርስቶስ ሕግ መገዛት

“ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ።”—ገላትያ 6:2

1. በዛሬው ጊዜ የክርስቶስ ሕግ በጎ ለማድረግ ብርቱ ግፊት ያሳድራል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

በሩዋንዳ የሚገኙ ሁቱና ቱትሲ የይሖዋ ምሥክሮች በቅርቡ አገሪቱን ካጥለቀለቀው የጎሳ እልቂት አንዳቸው ሌላውን ለማዳን ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ነበር። ጃፓን ውስጥ በኮቤ በደረሰው አውዳሚ የሆነ ርዕደ መሬት የቤተሰብ አባሎቻቸውን በሞት ያጡ የይሖዋ ምሥክሮች ከባድ ሐዘን ደርሶባቸዋል። ይሁንና የችግሩ ሰለባ የሆኑትን ሌሎች ሰዎች ለመርዳት ወዲያው ታጥቀው ተነሥተዋል። አዎን፣ ከመላው ዓለም የሚገኙት ልብ የሚነኩ ተሞክሮዎች በግልጽ እንደሚያሳዩት ዛሬም የክርስቶስ ሕግ ተግባራዊ እየሆነ ነው። ይህ ሕግ በጎ ለማድረግ የሚገፋፋ ብርቱ ኃይል ነው።

2. ሕዝበ ክርስትና የክርስቶስን ሕግ ትርጉም ሳትገነዘብ የቀረችው እንዴት ነው? የክርስቶስን ሕግ መፈጸም የምንችለው እንዴት ነው?

2 በአንጻሩ ደግሞ ስላለንባቸው አስጨናቂ ‘የመጨረሻ ቀናት’ የተነገረ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ ነው። ብዙዎች ‘ለአምላክ ያደሩ መስለው ይታያሉ ነገር ግን ኃይሉን ክደዋል።’ (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 5 አዓት) በተለይ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ሃይማኖት እንዲያው ለወጉ ያህል የሚደረግ ነገር እንጂ የልብ ጉዳይ አይደለም። እንዲህ የሆነው ለክርስቶስ ሕግ መገዛት አስቸጋሪ ስለሆነ ነውን? አይደለም፤ ኢየሱስ ልንፈጽመው የማንችለውን ሕግ አይሰጠንም። ሕዝበ ክርስትና የክርስቶስን ሕግ ትርጉም ሳትገነዘብ በመቅረቷ ነው። በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፉትን “ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ” የሚሉትን ቃላት ሳትታዘዝ ቀርታለች። (ገላትያ 6:2) ‘የክርስቶስን ሕግ የምንፈጽመው’ እንደ ፈሪሳውያን በወንድሞቻችን ላይ አላስፈላጊ ሸክም በመጫን ሳይሆን አንዳችን የሌላውን ሸክም በመሸከም ነው።

3. (ሀ) በክርስቶስ ሕግ ውስጥ የተካተቱ አንዳንድ ትእዛዞች የትኞቹ ናቸው? (ለ) የክርስቲያን ጉባኤ ክርስቶስ በቀጥታ ከሰጣቸው ትእዛዛት በስተቀር ሌላ ደንብ ሊኖረው አይገባም ብሎ መደምደም ስሕተት የሚሆነው ለምንድን ነው?

3 የክርስቶስ ሕግ ክርስቶስ ኢየሱስ የሰጣቸውን ትእዛዛት ሁሉ ይኸውም ማስተማርንና መስበክን፣ ምኞታችንን ንጹሕና ቀላል ማድረግን፣ ­ከጎረቤቶቻችን ጋር በሰላም ለመኖር መጣርን ወይም ከጉባኤው ውስጥ ርኩሰትን ማስወገድን ሁሉ ያጠቃልላል። (ማቴዎስ 5:27-30፤ 18:15-17፤ 28:19, 20፤ ራእይ 2:14-16) በእርግጥ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ለክርስቶስ ተከታዮች የተሰጡ ትእዛዛት በሙሉ የማክበር ግዴታ አለባቸው። በዚህ ብቻ አያበቃም። የይሖዋ ድርጅትም ሆነ እያንዳንዱ ጉባኤ ሥርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ አንዳንድ ደንቦችን ማውጣታቸውና የአሠራር መንገዶችን መቀየሳቸው ግድ ነው። (1 ቆሮንቶስ 14:33, 40) እንዲያውም የጉባኤ ስብሰባዎች መቼ፣ የትና እንዴት እንደሚካሄዱ አንዳንድ ደንቦች ባይወጡ ኖሮ ክርስቲያኖች አንድ ላይ መሰብሰብ ባልቻሉም ነበር። (ዕብራውያን 10:24, 25) በድርጅቱ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ያላቸው ወንድሞች ከሚያወጧቸው ምክንያታዊ መመሪያዎች ጋር ተስማምቶ መሥራትም የክርስቶስን ሕግ የምንፈጽምበት አንዱ መንገድ ነው።—ዕብራውያን 13:17

4. ከንጹሕ አምልኮ በስተጀርባ ያለው የሚገፋፋ ኃይል ምንድን ነው?

4 ሆኖም እውነተኛ ክርስቲያኖች አምልኳቸው ትርጉም የለሽ የሕግ ጋጋታ እንዲሆን አይፈቅዱም። ይሖዋን የሚያገለግሉት እንዲሁ አንድ ግለሰብ ወይም ድርጅት እንዲህ አድርጉ ብሎ ስለሚነግራቸው አይደለም። ከዚያ ይልቅ ከአምልኳቸው በስተጀርባ ያለው የሚገፋፋ ኃይል ፍቅር ነው። ጳውሎስ “የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናል” ሲል ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 5:14 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ኢየሱስ ተከታዮቹ እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ አዟል። (ዮሐንስ 15:12, 13) የክርስቶስ ሕግ መሠረት የራሱን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር ሲሆን ይህም ፍቅር በየትም ቦታ የሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያኖችን በቤተሰብም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ግድ ይላቸዋል ወይም ለተግባር ያንቀሳቅሳቸዋል። ይህ እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

በቤተሰብ ውስጥ

5. (ሀ) ወላጆች በቤታቸው ውስጥ የክርስቶስን ሕግ መፈጸም የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ልጆች ከወላጆቻቸው ምን ይፈልጋሉ? አንዳንድ ወላጆች ይህን ለማሟላት ምን ነገር ማሸነፍ ይኖርባቸዋል?

5 ሐዋርያው ጳውሎስ “ባሎች ሆይ! ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደወደደና ራሱን ስለ እርስዋ አሳልፎ እንደ ሰጠ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ” ሲል ጽፏል። (ኤፌሶን 5:25 የ1980 ትርጉም) አንድ ባል የክርስቶስን ምሳሌ በመኮረጅ ሚስቱን በፍቅርና በማስተዋል ሲይዛት የክርስቶስን ሕግ ዐቢይ ዘርፍ ይፈጽማል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ሕፃናትን በማቀፍና እጁን ጭኖ በመባረክ ፍቅሩን በግልጽ አሳይቷል። (ማርቆስ 10:16) የክርስቶስን ሕግ የሚፈጽሙ ወላጆችም ለልጆቻቸው ፍቅር ያሳያሉ። በዚህ ረገድ የክርስቶስን ምሳሌ መከተል አስቸጋሪ የሚሆንባቸው ወላጆች እንዳሉ አይካድም። አንዳንዶቹ በተፈጥሯቸው ስሜታቸውን መግለጽ አይችሉም። ወላጆች ሆይ፣ እንዲህ ያለው ሁኔታ ለልጆቻችሁ ያላችሁን ፍቅር ከመግለጽ እንዲያግዳችሁ አትፍቀዱለት! ልጆቻችሁን እንደምትወዷቸው እናንተ ማወቃችሁ ብቻ አይበቃም። እነሱም ይህን ማወቅ ይኖርባቸዋል። ፍቅራችሁን የምትገልጹበት መንገድ ከሌለ ደግሞ እንደምትወዷቸው ፈጽሞ ሊያውቁ አይችሉም።—ከማርቆስ 1:11 ጋር አወዳድር።

6. (ሀ) ልጆች ወላጆች የሚያወጡት መመሪያ ያስፈልጋቸዋልን? እንደዚህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው? (ለ) ልጆች እንዲገነዘቡት የሚያስፈልገው በቤተሰብ ውስጥ ከሚወጡት መመሪያዎች በስተጀርባ ያለው ነገር ምንድን ነው? (ሐ) በቤተሰብ ውስጥ የክርስቶስ ሕግ ሲሰፍን የትኞቹ አደጋዎች ይወገዳሉ?

6 በሌላ በኩል ደግሞ ልጆች ወሰን ያስፈልጋቸዋል፤ ይህም ወላጆቻቸው አንዳንድ መመሪያዎችን ማውጣትና አልፎ አልፎም እነዚህን መመሪያዎች ተግሣጽ በመስጠት ማስፈጸም ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው። (ዕብራውያን 12:7, 9, 11) ወላጆች እነዚህን መመሪያዎች እንዲያወጡ የገፋፋቸው ነገር ለእነርሱ ያላቸው ፍቅር መሆኑን ልጆች እንዲገነዘቡ መርዳት የግድ ያስፈልጋል። እንዲሁም ወላጆቻቸውን ለመታዘዝ ሊገፋፋቸው የሚገባው ከሁሉ የተሻለ ምክንያት ፍቅር መሆኑን መማር ይኖርባቸዋል። (ኤፌሶን 6:1፤ ቆላስይስ 3:20፤ 1 ዮሐንስ 5:3) የአንድ አስተዋይ ወላጅ ግብ ልጆቹ የኋላ ኋላ በራሳቸው ጥሩ ውሳኔዎችን ማድረግ ይችሉ ዘንድ ዛሬ ‘በማመዛዘን ችሎታቸው’ እንዲጠቀሙ ማስተማር ነው። (ሮሜ 12:1 አዓት፤ ከ1 ቆሮንቶስ 13:11 ጋር አወዳድር።) በሌላ በኩል መመሪያዎቹ ከልክ በላይ መብዛት የለባቸውም፤ ተግሣጹም በጣም ከባድ መሆን አይኖርበትም። ጳውሎስ “አባቶች ሆይ፣ ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው” ብሏል። (ቆላስይስ 3:21፤ ኤፌሶን 6:4) በቤተሰብ ውስጥ የክርስቶስ ሕግ ሲሰፍን ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ቁጣ ወይም ጎጂ በሆኑ የአሽሙር ቃላት የሚሰጥ ተግሣጽ ቦታ አይኖረውም። በእንዲህ ዓይነቱ ቤት ውስጥ ልጆች ከአደጋ እንደተጠበቁና እንደሚታነጹ ይሰማቸዋል እንጂ ሸክም እንደተጫነባቸው ወይም እንደተጣሉ ሆኖ አይሰማቸውም።—ከመዝሙር 36:7 ጋር አወዳድር።

7. በቤተሰብ ውስጥ መመሪያ ማውጣትን በተመለከተ የቤቴል ቤቶች ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉት በምን መንገዶች ነው?

7 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የቤቴል ቤቶችን የጎበኙ አንዳንድ ሰዎች እነዚህ ቦታዎች ለቤተሰብ ሚዛናዊ መመሪያ በማውጣት ረገድ ጥሩ ምሳሌ እንደሚሆኑ ተናግረዋል። ምንም እንኳ የቤቴል ቤቶች አዋቂዎችን ብቻ ያቀፉ ቢሆንም በአመዛኙ የሚንቀሳቀሱት በቤተሰብ መልክ ነው።a በቤቴል ውስጥ የሚከናወኑት ነገሮች በርካታ በመሆናቸው አንድ ቤተሰብ ከሚያስፈልገው የበለጡ ብዙ መመሪያዎችን ይጠይቃሉ። የሆነ ሆኖ በቤቴል መኖሪያዎች፣ ቢሮዎችና ፋብሪካ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ሽማግሌዎች የክርስቶስን ሕግ ተግባራዊ ለማድረግ ይጥራሉ። ኃላፊነታቸው ሥራውን ማደራጀት ብቻ ሳይሆን አብረዋቸው በሚያገለግሉት ወንድሞች መካከል መንፈሳዊ እድገትና “የይሖዋ ደስታ” እንዲሰፍን ማድረግ ጭምር እንደሆነ ይሰማቸዋል። (ነህምያ 8:10 አዓት) በመሆኑም ነገሮችን አዎንታዊ በሆነና በሚያበረታታ መንገድ ለማከናወንና ምክንያታዊ ሆነው ለመገኘት ይጥራሉ። (ኤፌሶን 4:31, 32) የቤቴል ቤተሰቦች ባላቸው ደስተኛ መንፈስ የሚታወቁ መሆናቸው አያስገርምም!

በጉባኤ ውስጥ

8. (ሀ) በጉባኤ ውስጥ ምን ጊዜም ግባችን ምን መሆን ይኖርበታል? (ለ) አንዳንዶች ደንብ እንዲወጣ የጠየቁባቸው ወይም ደንብ ለማውጣት የሞከሩባቸው አንዳንድ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?

8 በጉባኤ ውስጥም ግባችን እርስ በርስ በፍቅር መተናነጽ ነው። (1 ተሰሎንቄ 5:11) ስለዚህ ሁሉም ክርስቲያኖች በሌሎች የግል ምርጫ ውስጥ ገብተው እነርሱ የሚሉት እንዲደረግ በመጫን የሌሎችን ሸክም ላለማክበድ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። አንዳንዶች የተወሰኑ ፊልሞችን፣ መጻሕፍትንና አሻንጉሊቶችን ሳይቀር በስም ጠቅሰው ስለ እነዚህ ነገሮች ሊኖራቸው ስለሚገባው አመለካከት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ደንቦችን እንዲያወጣ በደብዳቤ የሚጠይቁበት ጊዜ አለ። ሆኖም ማኅበሩ እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች ሁሉ እየመረመረ እንዲህ መደረግ አለበት ለማለት መብት የለውም። በአብዛኛው እነዚህ ነገሮች እያንዳንዱ ግለሰብ ወይም የቤተሰብ ራስ ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ባለው ፍቅር ላይ ተመርኩዞ ውሳኔ የሚሰጥባቸው ነገሮች ናቸው። ሌሎች ደግሞ ማኅበሩ የሚያቀርባቸውን ሐሳቦችና መመሪያዎች ድርቅ ያለ ደንብ አድርገው መውሰድ ይቀናቸዋል። ለምሳሌ ያህል የመጋቢት 15, 1996 መጠበቂያ ግንብ ሽማግሌዎች ለጉባኤው አባላት ዘወትር የእረኝነት ጉብኝት እንዲያደርጉ የሚያበረታታ ጥሩ ትምህርት ይዞ ወጥቷል። የትምህርቱ ዓላማ ደንብ ማውጣት ነውን? አይደለም። የቀረቡትን ሐሳቦች በገቢር ሊተረጉሟቸው የሚችሉ ካሉ ብዙ ጥቅሞችን የሚያገኙ ቢሆንም አንዳንድ ሽማግሌዎች እንደዚያ ለማድረግ ሁኔታቸው አይፈቅድላቸውም። በተመሳሳይም በሚያዝያ 1, 1995 የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ የወጣው “የአንባብያን ጥያቄዎች” አምድ ድግስ እንደ ማዘጋጀትን፣ የድል አድራጊነት መንፈስ የሚያንጸባርቅ ፈንጠዝያ ማሳየትን ከመሳሰሉት የጥምቀት ሥርዓቱ ክብር እንዳይኖረው የሚያደርጉ ነገሮች እንድንጠበቅ አስጠንቅቆ ነበር። አንዳንዶች ይህን ምክር በማክረር በዚህ ወቅት የማበረታቻ ካርድ መላክ እንኳ ስህተት ነው የሚል ድርቅ ያለ ደንብ እስከማውጣት ደርሰዋል!

9. እንከን የምንፈላልግና እርስ በርሳችን የምንነቃቀፍ አለመሆናችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

9 በተጨማሪም “ነፃ የሚያወጣው ፍጹሙ ሕግ” በመካከላችን ከሰፈነ የሁሉም ሰው ክርስቲያናዊ ሕሊና አንድ ዓይነት እንዳልሆነ አምነን መቀበል እንዳለብን ልብ በል። (ያዕቆብ 1:25) ሌሎች ሰዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የማያስጥሱ የግል ምርጫዎች ቢያደርጉ ለምን እንዲህ ሆነ ብለን ልናዝን ይገባልን? አይገባም። እንዲህ ማድረጋችን መለያየትን ይፈጥራል። (1 ቆሮንቶስ 1:10) ጳውሎስ በመሰል ክርስቲያን ላይ ከመፍረድ እንድንቆጠብ ሲያስጠነቅቀን እንዲህ ብሏል፦ “እርሱ ቢቆም ወይም ቢወድቅ ለገዛ ጌታው ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሊያቆመው ይችላልና ይቆማል።” (ሮሜ 14:4) ለግለሰቡ ሕሊና በሚተዉ ጉዳዮች ውስጥ እየገባን እርስ በርስ የምንወቃቀስ ከሆነ አምላክን ልናሳዝን እንችላለን።—ያዕቆብ 4:10-12

10. ጉባኤውን ለመጠበቅ የተሾሙት እነማን ናቸው? እነርሱንስ ልንደግፋቸው የምንችለው እንዴት ነው?

10 በተጨማሪም ሽማግሌዎች የተሾሙት የአምላክን መንጋ ለመጠበቅ እንደሆነ አንዘንጋ። (ሥራ 20:28) ይህ ቦታ የተሰጣቸው ሌሎችን እንዲረዱ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከመሆናቸውም በላይ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ላይ ከወጡት ሐሳቦች ጋር በሚገባ ስለሚተዋወቁ ወደ እነርሱ ቀረብ ብለን ምክር ለመጠየቅ ማመንታት አይገባንም። ሽማግሌዎቹ ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ወደ መጣስ የሚመራ አድራጎት ሲመለከቱ አስፈላጊውን ምክር በድፍረት ይሰጣሉ። (ገላትያ 6:1) የጉባኤ አባላት በመካከላቸው ቀዳሚ በመሆን ከሚመላለሱት ከእነዚህ ውድ እረኞች ጋር በመተባበር የክርስቶስን ሕግ ያከብራሉ።—ዕብራውያን 13:7

ሽማግሌዎች ሆይ፣ የክርስቶስን ሕግ በሥራ ተርጉሙ

11. ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ የክርስቶስን ሕግ በሥራ ሊተረጉሙ የሚችሉት እንዴት ነው?

11 ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ የክርስቶስን ሕግ ለመፈጸም ዝግጁ ናቸው። ምሥራቹን በመስበክ፣ ልብ በሚነካ መንገድ ከመጽሐፍ ቅዱስ በማስተማር ቀዳሚ ሆነው ከመገኘታቸውም በላይ አፍቃሪና ደግ እረኞች እንደ መሆናቸው መጠን “የተጨነቁትን ነፍሳት” ያጽናናሉ። (1 ተሰሎንቄ 5:14 አዓት) ዛሬ በብዙ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከሚንጸባረቀው ክርስቲያናዊ ያልሆነ አስተሳሰብ ይርቃሉ። ይህ ዓለም በፍጥነት እየተፍረከረከ መሄዱ አይካድም፤ ሽማግሌዎችም እንደ ጳውሎስ ስለ መንጋው ይጨነቁ ይሆናል፤ ሆኖም ግን ስለ ጉባኤው የሚያሳስቧቸውን ነገሮች ለመፍታት ሲጥሩ ሚዛናቸውን ይጠብቃሉ።—2 ቆሮንቶስ 11:28

12. አንድ ክርስቲያን ምክር ለመጠየቅ ወደ አንድ ሽማግሌ ሲቀርብ ሽማግሌው ምን ምላሽ ሊሰጥ ይችላል?

12 ለምሳሌ ያህል አንድ ክርስቲያን በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በቀጥታ ስላልተጠቀሰና የተለያዩ የክርስትና መሠረታዊ ሥርዓቶችን ማመዛዘን ስለሚጠይቅ አንድ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ጉዳይ አንድን ሽማግሌ ማማከር ይፈልግ ይሆናል። ምናልባት የደሞዝ ጭማሪ የሚያስገኝ ሆኖም ተጨማሪ ኃላፊነቶችን የሚያስከትል የሥራ ዕድገት አግኝቶ ይሆናል። ወይም ደግሞ የአንድ ወጣት ክርስቲያን የማያምን አባት የልጁን አገልግሎት ሊያስተጓጉልበት የሚችል ነገር እንዲያደርግ ጠይቆት ሊሆን ይችላል። እነዚህን በመሰሉ ጉዳዮች ረገድ ሽማግሌው የግል አስተያየት ከመስጠት ይቆጠባል። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን ገልጦ ግለሰቡ ከጉዳዩ ጋር በሚዛመዱ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ እንዲያስብ ያደርጋል። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ በቅርብ የሚያገኝ ከሆነም “ታማኝና ልባም ባሪያ” ስለዚያ ርዕሰ ጉዳይ በመጠበቂያ ግንብ እና በሌሎች ጽሑፎች ላይ ያወጣውን ሐሳብ መመልከት ይችላል። (ማቴዎስ 24:45) ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ ይህ ክርስቲያን በሽማግሌው ዓይን ጥበብ መስሎ የማይታይ ውሳኔ ቢያደርግስ? ያደረገው ውሳኔ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ወይም ሕጎች በቀጥታ የማይተላለፍ እስከሆነ ድረስ ሽማግሌው ‘እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም እንደሚሸከም’ በመገንዘብ ግለሰቡ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ለማድረግ ያለውን መብት ያከብርለታል። ይሁን እንጂ ይህ ክርስቲያን ‘ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ እንደሚያጭድ’ ማስታወስ ይኖርበታል።—ገላትያ 6:5, 7

13. ሽማግሌዎች ለቀረቡት ጥያቄዎች ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ወይም የራሳቸውን አስተያየት ከመስጠት ይልቅ ሌሎች በጉዳዩ ላይ እንዲያስቡበት የሚያደርጉት ለምንድን ነው?

13 ተሞክሮ ያለው ሽማግሌ እንደዚህ የሚያደርገው ለምንድን ነው? ቢያንስ በሁለት ምክንያቶች የተነሣ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ጳውሎስ ለአንድ ጉባኤ ‘በእምነታቸው ላይ የሚገዛ እንዳልሆነ’ ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 1:24) ወንድሙ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ እንዲያስብና በእውቀት ላይ ተመሥርቶ የራሱን ውሳኔ እንዲያደርግ የሚረዳው ሽማግሌ የጳውሎስን አስተሳሰብ ይዟል። ኢየሱስ ሥልጣኑ ገደብ እንዳለው እንደተገነዘበ ሁሉ ይህም ሽማግሌ ሥልጣኑ ገደብ እንዳለው ይገነዘባል። (ሉቃስ 12:13, 14፤ ይሁዳ 9) በአንጻሩ ደግሞ ሽማግሌዎች ጠቃሚ አልፎ ተርፎም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ጠንከር ያለ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ይሰጣሉ። በሁለተኛ ደረጃ ክርስቲያን ወንድሙን እያሠለጠነው ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በሥራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን [“ለጎለመሱ፣” አዓት] ሰዎች ነው” ብሏል። (ዕብራውያን 5:14) ወደ ጉልምስና ለማደግ ደግሞ ሁልጊዜ ሌላ ሰው እንዲወስንልን ከመጠበቅ ይልቅ የማስተዋል ችሎታችንን መጠቀም ይኖርብናል። ሽማግሌው ክርስቲያን ወንድሙ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ በጥልቀት ማሰብ የሚችለው እንዴት እንደሆነ በማሳየት እድገት እንዲያደርግ ይረዳዋል።

14. የጎለመሱ ሰዎች በይሖዋ ላይ እንደሚታመኑ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

14 ይሖዋ አምላክ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት የእውነተኛ አምላኪዎቹን ልብ እንደሚለውጥ እምነት ሊኖረን ይችላል። በመሆኑም የጎለመሱ ክርስቲያኖች ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳደረገው በርኅራኄ በማነጋገር የወንድሞቻቸውን ልብ ለመንካት ይጥራሉ። (2 ቆሮንቶስ 8:8፤ 10:1፤ ፊልሞና 8, 9) አብዛኛውን ጊዜ በአግባቡ እንዲመላለሱ ዝርዝር ሕግ የሚያስፈልጋቸው ኃጢአተኛ ሰዎች እንጂ ጻድቃን እንዳልሆኑ ጳውሎስ ያውቅ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 1:9) በወንድሞቹ ላይ ጥርጣሬ እንዳደረበት ወይም በእነርሱ ላይ ያለውን እምነት እንዳጣ ሳይሆን የገለጸላቸው በእነርሱ ላይ እምነት እንዳለው ነው። ለአንድ ጉባኤ “ስለ እናንተ በጌታ ታምነናል” ሲል ጽፏል። (2 ተሰሎንቄ 3:4) በእርግጥም ጳውሎስ የነበረው እምነት፣ ትምክህትና እርግጠኝነት እነዚያን ክርስቲያኖች ለተግባር ለማንቀሳቀስ ትልቅ ድርሻ እንደነበረው ምንም ጥርጥር የለውም። ዛሬም ሽማግሌዎችና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ከዚህ የተለየ ዓላማ የላቸውም። እነዚህ እምነት የሚጣልባቸው ሰዎች የአምላክን መንጋ በፍቅር የሚንከባከቡ በመሆናቸው ምንኛ መንፈስን የሚያድሱ ናቸው!—ኢሳይያስ 32:1, 2፤ 1 ጴጥሮስ 5:1-3

ለክርስቶስ ሕግ እየተገዛችሁ ነውን?

15. ከወንድሞቻችን ጋር ባለን ግንኙነት የክርስቶስን ሕግ በሥራ ላይ ማዋልና አለማዋላችንን ለማረጋገጥ ራሳችንን ልንጠይቅ የምንችላቸው አንዳንድ ጥያቄዎች ምንድን ናቸው?

15 ሁላችንም ለክርስቶስ ሕግ የምንገዛ መሆናችንን ለማረጋገጥ ዘወትር ራሳችንን መመርመር ያስፈልገናል። (2 ቆሮንቶስ 13:5) በእርግጥም ሁላችንም የሚከተሉትን ጥያቄዎች ብንጠይቅ ልንጠቀም እንችላለን፦ ‘ሌሎችን የማንጽ ሰው ነኝ ወይስ ተቺ? ሚዛናዊ ሰው ነኝ ወይስ አክራሪ? ለሌሎች አሳቢ ነኝ ወይስ የራሴን መብት ለማስጠበቅ ብቻ የቆምኩ? አንድ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ባልተቀመጡ ጉዳዮች ላይ ወንድሙን እንዲህ ማድረግ አለብህ ወይም እንዲህ ማድረግ የለብህም ብሎ ሊያስገድደው አይሞክርም።—ሮሜ 12:1 አዓት፤ 1 ቆሮንቶስ 4:6

16. ስለ ራሳቸው አሉታዊ አመለካከት ያላቸውን በመርዳት የክርስቶስን ሕግ ዐቢይ ገጽታ መፈጸም የምንችለው እንዴት ነው?

16 በእነዚህ አስጨናቂ ቀናት እርስ በርሳችን የምንበረታታበትን መንገድ ለመፈለግ መጣራችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ዕብራውያን 10:24, 25፤ ከማቴዎስ 7:1-5 ጋር አወዳድር።) ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ስንመለከታቸው ከድክመቶቻቸው ይልቅ መልካም ባሕርያቶቻቸው ጎልተው ሊታዩን አይገባምን? እያንዳንዱ ሰው በይሖዋ ፊት ውድ ነው። የሚያሳዝነው ግን ስለራሳቸው እንኳ ሳይቀር እንደዚህ የማይሰማቸው አሉ። ብዙዎች የራሳቸውን ጉድለቶችና አለፍጽምና ብቻ መመልከት ይቀናቸዋል። እንደነዚህ ያሉትንም ሆነ ሌሎችን ለማበረታታት በእያንዳንዱ ስብሰባ ወቅት በስብሰባ ላይ መገኘታቸውን እንደምናደንቅ እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ የሚያበረክቱትን ድርሻ በመጥቀስ ከአንድ ወይም ሁለት ሰዎች ጋር ለመነጋገር መሞከር እንችላለንን? በዚህ መንገድ ሸክማቸውን ማቃለላችንና በዚያውም የክርስቶስን ሕግ መፈጸማችን ምንኛ የሚያስደስት ነው!—ገላትያ 6:2

የክርስቶስ ሕግ ተግባራዊ እየሆነ ነው!

17. በጉባኤህ ውስጥ የክርስቶስ ሕግ በምን በምን የተለያዩ መንገዶች በሥራ ላይ ሲውል ትመለከታለህ?

17 የክርስቶስ ሕግ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ተግባራዊ እየሆነ ነው። ይህም መሰል ምሥክሮች ምሥራቹን በጉጉት ለሌሎች ሲያካፍሉ፣ እርስ በርሳቸው ሲጽናኑና ሲበረታቱ፣ በጣም ከባድ ችግሮች እያሉባቸውም ይሖዋን ለማገልገል ሲታገሉ፣ ወላጆች ልጆቻቸው በደስተኛ ልብ ለይሖዋ ፍቅር አድሮባቸው እንዲያድጉ ለማድረግ ሲጥሩ እንዲሁም የበላይ ተመልካቾች የአምላክን ቃል በፍቅርና በግለት በማስተማር መንጋው ይሖዋን ለዘላለም የማገልገል ቅንዓት እንዲያድርበት ሲያነቃቁ በየዕለቱ የምናየው ነገር ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ 1 ተሰሎንቄ 5:11, 14) በግለሰብ ደረጃ የክርስቶስን ሕግ በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ስናደርግ የይሖዋ ልብ ይደሰታል! (ምሳሌ 23:15) የእርሱን ፍጹም ሕግ የሚያፈቅሩ ሁሉ ለዘላለም እንዲኖሩ ይፈልጋል። በመጪው ገነት ውስጥ የሰው ልጅ ፍጹም የሚሆንበት ጊዜ፣ ሕግ ተላላፊዎች የማይኖሩበት ጊዜና የልባችንን ዝንባሌ ሁሉ የምንቆጣጠርበት ጊዜ ሲመጣ እናያለን። ይህ ለክርስቶስ ሕግ መገዛት የሚያስገኘው እንዴት ያለ ክብራማ ሽልማት ነው!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a እነዚህ የቤቴል ቤቶች ከሕዝበ ክርስትና ገዳማት የተለዩ ናቸው። “አባዎች” ወይም “አባቶች” የሉም። (ማቴዎስ 23:9) በኃላፊነት ላይ ያሉ ወንድሞች አክብሮት የሚሰጣቸው ቢሆንም እነርሱም አገልግሎታቸውን የሚያከናውኑት ሁሉም ሽማግሌዎች በሚመሩበት መሠረታዊ ሥርዓት ነው።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ ሕዝበ ክርስትና የክርስቶስን ሕግ ትርጉም ሳትገነዘብ የቀረችው ለምንድን ነው?

◻ የክርስቶስን ሕግ በቤተሰብ ውስጥ በሥራ ላይ ልናውለው የምንችለው እንዴት ነው?

◻ የክርስቶስን ሕግ በጉባኤ ውስጥ በሥራ ለመተርጎም ከምን መቆጠብ ይኖርብናል? ምንስ ማድረግ ይኖርብናል?

◻ ሽማግሌዎች ከጉባኤው ጋር ባላቸው ግንኙነት የክርስቶስን ሕግ መታዘዝ የሚችሉት እንዴት ነው?

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጃችሁ ፍቅር በጣም ያስፈልገዋል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አፍቃሪ እረኞቻችን ምንኛ መንፈስን የሚያድሱ ናቸው!

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ