የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 12/1 ገጽ 15-20
  • ‘እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ’
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሌሎችን ይቅር ማለት የሚገባን ለምንድን ነው?
  • ‘እርስ በርስ መቻቻላችሁን ቀጥሉ’
  • ቁስሉ ከባድ በሚሆንበት ጊዜ
  • ይቅር ልንለው የማንችለው ሆኖ ሲታየን
  • እርስ በርስ በነፃ ይቅር ተባባሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • ይቅር ማለትና መርሳት የሚቻለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—1995
  • ይቅር ባዮች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ይቅር ማለት ሲባል ምን ማለት ነው?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 12/1 ገጽ 15-20

‘እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ’

“እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።”​—⁠ቆላስይስ 3:​13 NW

1. (ሀ) ጴጥሮስ ሌሎችን “ሰባት ጊዜ” ይቅር እንድንል ሐሳብ ሲያቀርብ ራሱን እንደ ቸር ቆጥሮ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ “እስከ ሰባ ሰባት ጊዜ” ድረስ ይቅር ማለት እንደሚገባን ሲናገር ምን ማለቱ ነበር?

“ጌታ ሆይ፣ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜን?” (ማቴዎስ 18:​21) ጴጥሮስ ይህን ሐሳብ ሲያቀርብ ራሱን በጣም ቸር እንደሆነ አድርጎ አስቦ ሊሆን ይችላል። በወቅቱ የነበረው የረቢዎች ወግ አንድ ሰው ለተመሳሳይ በደል ከሦስት ጊዜ በላይ ይቅርታ ሊያደርግ አይገባም ይል ነበር።a ኢየሱስ “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት [“እስከ ሰባ ሰባት ጊዜ፣” NW] እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም” ብሎ ሲመልስለት ጴጥሮስ ምን ያህል እንደሚገረም አስቡት! (ማቴዎስ 18:​22) ሰባት ቁጥር ተደጋግሞ መጠቀሱ “በቁጥር ላልተወሰነ ጊዜ” የማለት ያክል ነበር። በኢየሱስ አመለካከት አንድ ክርስቲያን ሌሎችን ይቅር ማለት ያለበት በቁጥር ለተወሰኑ ጊዜያት አይደለም።

2, 3. (ሀ) ሌሎችን ይቅር ማለት አስቸጋሪ መስሎ የሚታየው በየትኞቹ ሁኔታዎች ነው? (ለ) ሌሎችን ይቅር ማለታችን ለራሳችን ጥቅም እንደሆነ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

2 ይሁን እንጂ ይህንን ምክር ሥራ ላይ ማዋል ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ከእኛ መካከል ያላግባብ በተፈጸመበት በደል ምክንያት ያልቆሰለ ማን ነው? ምናልባትም አንድ የምታምነው ሰው ምሥጢርህን አባክኖብህ ይሆናል። (ምሳሌ 11:​13) የአንድ የቅርብ ወዳጅህ አሳቢነት የጎደለው ንግግር ‘እንደ ሰይፍ ወግቶህ’ ይሆናል። (ምሳሌ 12:​18) ትወደው ወይም ትተማመንበት የነበረ አንድ ሰው የፈጸመብህ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት በኃይል አቁስሎህ ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ነገሮች ሲፈጸሙ የምንሰጠው የተለመደው ምላሽ መቆጣት ሊሆን ይችላል። የበደለንን ሰው ላለማነጋገር ከተቻለንም ጨርሶ ከእርሱ ለመራቅ እንሞክር ይሆናል። ይህን ሰው ይቅር ማለት ላደረሰብን በደል ቅጣቱን ሳያገኝ መተው እንደሆነ ሊሰማን ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ቂም ይዞ መኖር ትርፉ ራስን መጉዳት ነው።

3 በመሆኑም ኢየሱስ ‘እስከ ሰባ ሰባት ጊዜ’ ድረስ ይቅር እንድንል አስተምሮናል። ትምህርቶቹ ፈጽሞ እንደማይጎዱን የተረጋገጠ ነው። ትምህርቱ ሁሉ ‘የሚረባንን ነገር ከሚያስተምረን’ ከይሖዋ የመነጨ ነው። (ኢሳይያስ 48:​17፤ ዮሐንስ 7:​16, 17) ሌሎችን ይቅር ማለታችን ለራሳችን ጥቅም እንደሆነ የታወቀ ነው። ለምን ይቅር ማለት እንደሚገባንና እንዴት ይቅር ማለት እንደምንችል ከመወያየታችን በፊት ይቅር ባይነት ምንድን ነው ምንስ አይደለም የሚለውን ጉዳይ ግልጽ ማድረግ ይጠቅመን ይሆናል። ስለ ይቅር ባይነት ያለን ግንዛቤ ሌሎች ሲበድሉን ይቅር ለማለት በሚኖረን ችሎታ ላይ የተወሰነ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

4. ሌሎችን ይቅር ማለት ምን ማለት አይደለም? ይሁን እንጂ ይቅር ባይነት ምን ፍቺ ተሰጥቶታል?

4 ሌሎች በግል የፈጸሙብንን በደል ይቅር ማለት የሠሩትን ነገር ቸል ብሎ ማለፍ ወይም አቃልሎ መመልከት ማለት አይደለም፤ ወይም ደግሞ ተላላ ሆነን ሌሎች መጠቀሚያ እንዲያደርጉን መፍቀድ ማለት አይደለም። ይሖዋም ቢሆን ይቅር ሲለን ኃጢአታችንን አቃልሎ ይመለከተዋል ማለት አይደለም፤ ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎች ምሕረቱን አላግባብ እንዲጠቀሙበት ፈጽሞ አይፈቅድም። (ዕብራውያን 10:​29) ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ይቅር ባይነት “የበደለንን ሰው መማር፤ በፈጸመብን በደል የተነሣ በእርሱ ላይ ቅሬታ አለመያዝና ብድር ለመመለስ ከማሰብ መቆጠብ” ነው። (ጥራዝ 1 ገጽ 861)b መጽሐፍ ቅዱስ ሌሎችን ይቅር ለማለት የሚያስችሉ አጥጋቢ ምክንያቶች ይሰጠናል።

ሌሎችን ይቅር ማለት የሚገባን ለምንድን ነው?

5. ሌሎችን ይቅር ለማለት ትልቅ ምክንያት የሚሆነው በኤፌሶን 5:​1 ላይ የተጠቀሰው ነገር ምንድን ነው?

5 ሌሎችን ይቅር የምንልበት አንዱ ትልቅ ምክንያት በኤፌሶን 5:​1 [NW] ላይ ተጠቅሷል:- “እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች አምላክን የምትመስሉ ሁኑ።” ‘አምላክን መምሰል’ የሚገባን በምን ረገድ ነው? “እንግዲህ” የሚለው ቃል ይህን ሐሳብ ከፊተኛው ቁጥር ጋር የሚያያይዝ ነው፤ እንዲህ ይነበባል:- “እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፣ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ [“በነጻ፣” NW] ይቅር ተባባሉ።” (ኤፌሶን 4:​32፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) አዎን፣ ይቅር በማለት ረገድ አምላክን ልንመስለው ይገባል። አንድ ትንሽ ልጅ ልክ እንደ አባቱ ለመሆን እንደሚጥር ሁሉ እኛም ይሖዋ ከልቡ የሚወደን ልጆቹ እንደመሆናችን መጠን ይቅር ባይ የሆነውን ሰማያዊውን አባታችንን ለመምሰል መጣር ይገባናል። ይሖዋ ከሰማይ ሆኖ ወደ ታች ሲመለከት ምድራዊ ልጆቹ እርስ በርሳቸው ይቅር በመባባል እርሱን ለመምሰል ሲጥሩ ማየቱ ምንኛ ልቡን ደስ ያሰኘው ይሆን!​—⁠ሉቃስ 6:​35, 36፤ ከማቴዎስ 5:​44-48 ጋር አወዳድር።

6. ይሖዋ በሚያሳየውና እኛ በምናሳየው ይቅር ባይነት መካከል ልዩነት ያለው በምን መንገድ ነው?

6 ይሖዋ እንደሚያደርገው ፍጹም በሆነ መንገድ ይቅር ማለት እንደማንችል አይካድም። ይሁን እንጂ እርስ በርሳችን ይቅር እንድንባባል የሚያስገድደንም ከሁሉ የላቀው ምክንያት ይህ ነው። እስቲ አስበው፣ ይሖዋ በሚያሳየውና እኛ በምናሳየው ይቅር ባይነት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። (ኢሳይያስ 55:​7-9) ብዙውን ጊዜ እኛ የበደሉንን ይቅር ስንል አንድ ወቅት ላይ እነርሱም ይቅር በማለት ብድሩን ሊመልሱልን እንደሚችሉ በማሰብ ነው። በሰዎች መካከል የሆነ እንደሆነ ሁልጊዜ አንዱን ኃጢአተኛ ይቅር የሚለው ሌላ ኃጢአተኛ የሆነ ሰው ነው። ከይሖዋ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ግን ይቅር የሚለው አንድ ወገን ብቻ ነው። እርሱ ይቅር ይለናል እኛ ግን እርሱን ይቅር የምንለው ነገር የለም። ምንም የማይበድለው ይሖዋ አንዳች በማይጎድለው ፍቅራዊ መንገድ እንዲህ ይቅር ሊለን ከቻለ ኃጢአተኛ የሆንነው ሰዎች እርስ በርሳችን ይቅር ለመባባል መጣር አይገባንምን?​—⁠ማቴዎስ 6:​12

7. ምሕረት ለማሳየት የሚያስችል መሠረት እያለ ሌሎችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ አለመሆናችን ከይሖዋ ጋር ያለንን ግንኙነት ሊያበላሸው የሚችለው እንዴት ነው?

7 ከሁሉ በላይ ደግሞ ምሕረት ለማሳየት የሚያስችል መሠረት እያለ ሌሎችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ሳንሆን ብንቀር ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ሊያበላሽብን ይችላል። ይሖዋ እርስ በርስ ይቅር ተባባሉ ብሎ ሲናገር እንዲሁ ሐሳብ መለገሱ አይደለም፤ ተግባራዊ እንድናደርገው ይፈልጋል። ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚሉት ይቅር ባዮች እንድንሆን ከሚያነሳሱን ምክንያቶች አንዱ ይሖዋ ይቅር እንዲለን የምንፈልግ መሆናችን ወይም ቀደም ሲል ይቅር ያለን መሆኑ ነው። (ማቴዎስ 6:​14፤ ማርቆስ 11:​25፤ ኤፌሶን 4:​32፤ 1 ዮሐንስ 4:​11) እንግዲያው ይቅር ለማለት የሚያስችል ጥሩ ምክንያት እያለ ሌሎችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ሳንሆን ቀርተን ይሖዋ ተመሳሳይ ይቅርታ እንዲያሳየን ልንጠብቅ እንችላለንን?​—⁠ማቴዎስ 18:​21-35

8. ይቅር ባይ መሆን ለእኛው ጥቅም የሚያስገኘው እንዴት ነው?

8 ይሖዋ ሕዝቦቹ ‘ሊሄዱበት የሚገባውን መልካም መንገድ’ ያስተምራቸዋል። (1 ነገሥት 8:​36) እርስ በርሳችን ይቅር እንድንባባል ሲያስተምረን የምናገኘውን የላቀ ጥቅም በማሰብ እንደሆነ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ለቁጣው ፈንታ ስጡ” የሚለን ያለ ምክንያት አይደለም። (ሮሜ 12:​19) ቅሬታ በሕይወታችን ውስጥ ከባድ ሸክም ነው። በውስጣችን ቅሬታ የምንይዝ ከሆነ ሐሳባችን ሁሉ በዚያ ላይ ያተኩራል፣ ሰላማችንን ይነጥቀናል እንዲሁም ደስታ ያሳጣናል። ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ቁጣ ልክ እንደ ቅንዓት በአካላዊ ጤንነታችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። (ምሳሌ 14:​30) እኛ ውስጥ ውስጡን እንዲህ ስንብከነከን የበደለን ሰው ግን ስለ እኛ ሥቃይ ምንም የሚያውቀው ነገር አይኖር ይሆናል! አፍቃሪው ፈጣሪያችን ሌሎችን ሙሉ በሙሉ ይቅር ማለት የሚኖርብን ለበደሉን ሰዎች ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለራሳችንም ብለን እንደሆነ ያውቃል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ይቅር እንድንል የሚሰጠን ምክር ‘ልንሄድበት የሚገባ መልካም መንገድ’ ነው።

‘እርስ በርስ መቻቻላችሁን ቀጥሉ’

9, 10. (ሀ) የግድ ምሕረት የማይጠይቁ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ‘እርስ በርስ መቻቻላችሁን ቀጥሉ’ የሚለው አነጋገር ምን ያመለክታል?

9 በአካል ላይ የሚደርሰው ጉዳት ከትንሽ ጭረት አንስቶ እስከ ከባድ ቁስል ድረስ የሚለያይ እንደመሆኑ መጠን ሁሉም እኩል ትኩረት አይሻም። በስሜት ላይ የሚደርሰውም ጉዳት ቢሆን ተመሳሳይ ነው፤ አንዳንዱ ቁስል ከሌላው ይበልጥ ከበድ ይላል። ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት የሚደርሱብንን ጥቃቅን በደሎች ሁሉ አጋንነን ልንመለከታቸው ይገባልን? የሚያናድዱ፣ የሚያበሳጩ ወይም የሚያስቆጡ ጥቃቅን ነገሮች የሕይወታችን ክፍል በመሆናቸው ሁልጊዜ ምሕረትን የሚጠይቁ አይሆኑም። እያንዳንዷን ጥቃቅን ስህተት ምክንያት በማድረግ ሌሎችን የምንሸሽ ከሆነና ግንኙነታችን እንዲስተካከል ከፈለጉ መጥተው ይቅርታ ሊጠይቁኝ ይገባል ብለን ድርቅ የምንል ከሆነ ከእኛ ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ በጣም እንዲጨነቁ ወይም ከእኛ ጋር ያላቸውን ቅርርብ እንዲገድቡ ልናደርጋቸው እንችላለን!

10 ከዚህ ይልቅ ‘ምክንያታዊ ናቸው የሚል ስም ማትረፍ’ እጅግ የተሻለ ነው። (ፊልጵስዩስ 4:​5 የፊሊፕስ ትርጉም) እጅ ለእጅ ተያይዘን የምናገለግል ፍጽምና የሌለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን አንዳንድ ጊዜ ወንድሞቻችን ሊያስከፉንና እኛም እንዲሁ ልናስከፋቸው እንደምንችል መጠበቃችን ምክንያታዊ ይሆናል። ቆላስይስ 3:​13 [NW] “እርስ በርስ መቻቻላችሁን . . . ቀጥሉ” በማለት ይመክረናል። ይህ አገላለጽ ሌሎችን መታገሥ፣ በእነርሱ ላይ የተመለከትነውን የምንጠላውን ነገር ወይም የሚያስከፋንን ባሕርያቸውን መቻል የሚል መልእክት ያስተላልፋል። እንዲህ ያለው ትዕግሥት ወይም ቻይነት ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ትንሽ ብንጫር ወይም ብንላጥ የጉባኤውን ሰላም ሳናደፈርስ ችግሮቹን ለመወጣት ያስችለናል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 16:​14

ቁስሉ ከባድ በሚሆንበት ጊዜ

11. ሌሎች ሲበድሉን ይቅር እንድንላቸው ሊረዳን የሚችለው ነገር ምንድን ነው?

11 ይሁን እንጂ ሌሎች በጣም ከባድ በደል ቢፈጽሙብንስ? በጣም ከባድ የሆነ በደል ካልሆነ ‘እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ሥራ ላይ ለማዋል እምብዛም አይከብደን ይሆናል። (ኤፌሶን 4:​32) በዚህ መንገድ ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆን ጴጥሮስ በመንፈስ አነሳሽነት ከተናገራቸው ከሚከተሉት ቃላት ጋር ይስማማል:- “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።” (1 ጴጥሮስ 4:​8) እኛም ራሳችን ኃጢአተኞች እንደሆንን ማስታወስ የሌሎችን በደል ችለን ለማለፍ ይረዳናል። በመሆኑም ይቅር ስንል ቅሬታውን አምቀን ከመያዝ ይልቅ እንተወዋለን ማለት ነው። ከዚህም የተነሣ ከበደለን ሰው ጋር ያለን ግንኙነት ምንም ዓይነት ዘለቄታዊ ችግር የማይገጥመው ከመሆኑም ሌላ የጉባኤውን ውድ ሰላም ለመጠበቅም እገዛ እናደርጋለን። (ሮሜ 14:​19) ከጊዜ በኋላ ሰውዬው የፈጸመብንንም በደል እንረሳው ይሆናል።

12. (ሀ) ስሜታችንን በጣም የጎዳንን ሰው ይቅር ለማለት በራሳችን ተነሳስተን ምን ማድረግ ያስፈልገን ይሆናል? (ለ) በኤፌሶን 4:​26 ላይ የሚገኙት ቃላት ጉዳዩን ሳይውል ሳያድር መፍታት እንዳለብን የሚጠቁሙት እንዴት ነው?

12 ይሁን እንጂ አንድ ሰው በጣም ከባድ በደል ቢፈጽምብንና ስሜታችን በጥልቅ ቢጎዳስ? ለምሳሌ ያህል አንድ የምታምነው ወዳጅህ በምሥጢር የነገርከውንና ፈጽሞ ሌላ ሰው ሊያውቀው የማይገባ የግል ጉዳይ አወጣብህ እንበል። ስሜትህን በጣም ይጎዳዋል፣ ታፍራለህ እንዲሁም እንዳሳጣህ ይሰማሃል። ጉዳዩን ልትረሳው ትሞክራለህ ግን የሚረሳ አልሆነም። እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ ችግሩን ለመፍታት ቀዳሚ ሆነህ መገኘት ያስፈልግህ ይሆናል። ምናልባትም ቅድሚያውን ወስደህ የበደለህን ሰው ቀርበህ ማነጋገር ትችል ይሆናል። ጉዳዩ ሥር እየሰደደ ከመሄዱ በፊት እንዲህ ማድረጉ ጥበብ ነው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል አጥብቆ አሳስቦናል:- “ተቈጡ ኃጢአትንም አታድርጉ [ቁጣውን አምቆ በመያዝ ወይም በዚያ ተነሳስቶ እርምጃ በመውሰድ ማለት ነው]፤ በቊጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ።” (ኤፌሶን 4:​26) በአይሁዳውያን ዘንድ አንዱ ቀን አብቅቶ ሌላ አዲስ ቀን የሚጀምረው ፀሐይ ስትጠልቅ መሆኑ እነዚህን የጳውሎስ ቃላት ይበልጥ ትርጉም ያዘሉ ያደርጋቸዋል። በመሆኑም ምክሩ ጉዳዩን ሳይውል ሳያድር ፍቱት የሚል ነው!​—⁠ማቴዎስ 5:​23, 24

13. የበደለንን ሰው ቀርበን ስናነጋግር ዓላማችን ምን መሆን አለበት? ይህንንስ ለማድረግ የትኞቹ ሐሳቦች ሊረዱን ይችላሉ?

13 የበደለህን ሰው ቀርበህ ማነጋገር ያለብህ እንዴት ነው? 1 ጴጥሮስ 3:​11 ‘ሰላምን እሻ ተከተለውም’ ይላል። በመሆኑም ዓላማህ ቁጣህን መግለጽ ሳይሆን ከወንድምህ ጋር ሰላም መፍጠር ነው። ይህን ለማድረግ እንድትችል ደግሞ ሸካራ ቃላት ከመናገርና አሳቢነት የጎደለው አካላዊ መግለጫዎች ከማሳየት መቆጠብ የተሻለ ይሆናል፤ እነዚህ ነገሮች የምታነጋግረውም ሰው ተመሳሳይ ምላሽ እንዲሰጥ ሊያነሳሱት ይችላሉ። (ምሳሌ 15:​18፤ 29:​11) ከዚህም በተጨማሪ “አንተ ሁልጊዜ . . . !” ወይም “አንተ በፍጹም . . . !” የሚሉትን የመሳሰሉ የተጋነኑ አገላለጾች አትጠቀም። እንዲህ ያሉት የተጋነኑ አስተያየቶች ግለሰቡ ጥፋቱን ወደመከላከል እንዲያደላ ሊያደርጉት ይችላሉ። ከዚህ ይልቅ ግን የድምፅህ ቃናና ፊትህ ላይ የሚነበበው ሁኔታ ስሜትህን በጥልቅ የጎዳውን ጉዳይ ለመፍታት እንደምትፈልግ የሚያሳይ ይሁን። ስለተፈጸመው ነገር የሚሰማህን ስሜት በምትገልጽበት ጊዜ ዙሪያ ጥምጥም አትሂድ። ግለሰቡ የፈጸመውን ነገር በተመለከተ ያለውን ሐሳብ እንዲገልጽ ዕድል ስጠው። የሚናገረውን ነገር አዳምጥ። (ያዕቆብ 1:​19) ይህ ምን መልካም ውጤት ይኖረዋል? ምሳሌ 19:​11 እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “ሰውን ጠቢብ አእምሮው ከቁጣ ያዘገየዋል፣ ለበደለኛው ይቅር ይል ዘንድ ክብር ይሆንለታል።” የዚያን ሰው ስሜትና እንደዚያ ያደረገበትን ምክንያት መረዳት ለእርሱ ያደረብንን አሉታዊ አስተሳሰብና ስሜት ያስወግድልን ይሆናል። ይህን የምናደርገው ሰላም ለመፍጠርና ይህን ሰላም የመፍጠር ዝንባሌ ጠብቀን ለመቀጠል በማሰብ ከሆነ ማንኛውም ዓይነት አለመግባባት ተወግዶ ግለሰቡ ተገቢውን ይቅርታ ሊጠይቅና ምሕረት ሊያገኝ የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው።

14. ሌሎችን ይቅር ስንል በደሉን መርሳትም የሚገባን በምን መንገድ ነው?

14 ሌሎችን ይቅር ስንል የተፈጸመውን ነገር ቃል በቃል መርሳት አለብን ማለት ነውን? ይሖዋ ራሱ በዚህ ረገድ የተወውን ምሳሌ በሚመለከት በፊተኛው ርዕስ ውስጥ የተሰጠውን ማብራሪያ አስታውስ። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ኃጢአታችንን ይረሳል ሲል ጨርሶ ሊያስታውሰው አይችልም ማለቱ አይደለም። (ኢሳይያስ 43:​25) ከዚህ ይልቅ አንድ ጊዜ ይቅር ካለን በኋላ ወደፊት ያንኑ ኃጢአት አንስቶ አይፈርድብንም ማለት ነው። (ሕዝቅኤል 33:​14-16) በተመሳሳይም ሌሎች ሰዎችን ይቅር ስንል የግድ ያደረጉትን ነገር ልናስታውሰው አንችልም ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ በበደለን ሰው ላይ ቂም ባለመያዝ ወይም ወደፊት ጉዳዩን እንደገና ባለማንሳት እንደረሳነው ማሳየት እንችላለን። ጉዳዩ በዚህ መልክ ከተፈታ በኋላ ስለዚያ ጉዳይ እያነሱ ማማት ወይም ደግሞ የበደለንን ግለሰብ እንደተወገደ ሰው ጭራሽ ማግለል ተገቢ አይሆንም። (ምሳሌ 17:​9) ከእርሱ ጋር የነበረን ግንኙነት ተመልሶ እስኪጠገን ድረስ የተወሰነ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል አይካድም፤ እንደ በፊቱ ዓይነት የቀረበ ግንኙነት አይኖረን ይሆናል። ይሁን እንጂ ክርስቲያን ወንድማችን እንደመሆኑ መጠን በዚህም ጊዜ ቢሆን እንወደዋለን፤ እንዲሁም ሰላማዊ ዝምድናችንን ለመጠበቅ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን።​—⁠ከሉቃስ 17:​3 ጋር አወዳድር።

ይቅር ልንለው የማንችለው ሆኖ ሲታየን

15, 16. (ሀ) ክርስቲያኖች ንስሐ የማይገባን ኃጢአተኛ ይቅር ማለት ይጠበቅባቸዋልን? (ለ) በመዝሙር 37:​8 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ልንሠራበት የምንችለው እንዴት ነው?

15 ይሁንና አንዳንዶች ስሜታችንን እጅግ የሚያቆስል ከፍተኛ በደል ፈጽመውብን ጥፋታቸውን ባያምኑ፣ ንስሐ ባይገቡና ይቅርታ ባይጠይቁንስ? (ምሳሌ 28:​13) ይሖዋ ንስሐ የማይገቡ ልበ ደን⁠ዳና ኃጢአተኞችን ይቅር እንደማይል ቅዱሳን ጽሑፎች በግልጽ ያሳያሉ። (ዕብራውያን 6:​4-6፤ 10:​26, 27) እኛስ? ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ክርስቲያኖች ንስሐ ሳይገቡ ሆነ ብለው የክፋት ድርጊት የሚፈጽሙትን ሰዎች ይቅር እንዲሉ አይጠበቅባቸውም። እንዲህ ያሉት ሰዎች የአምላክ ጠላቶች ሆነዋል።” (ጥራዝ 1 ገጽ 862) እጅግ የከፋ ግፍ፣ አጸያፊ ወይም ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት የተፈጸመበት ክርስቲያን ንስሐ የማይገባን ኃጢአተኛ ይቅር የማለት ወይም በደሉን የመተው ግዴታ የለበትም።​—⁠መዝሙር 139:​21, 22

16 የጭካኔ ድርጊት የተፈጸመባቸው ሰዎች ስሜታቸው እንደሚጎዳ ወይም እንደሚበሳጩ ለማንም ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ቁጣንና ቅሬታን አምቆ መያዝ በጣም ሊጎዳን እንደሚችል አትዘንጋ። ግለሰቡ ላያደርገው ነገር፣ ጥፋቱን ማመን አለበት ወይም ይቅርታ ሊጠይቀኝ ይገባል ብለን የምንጠብቅ ከሆነ ትርፉ የከፋ ብስጭት ብቻ ሊሆን ይችላል። የተፈጸመብንን ግፍ ማብሰልሰል ንዴቱ ከውስጣችን እንዳይጠፋ የሚያደርግ በመሆኑ በመንፈሳዊ፣ ስሜታዊና አካላዊ ጤንነታችን ላይ አስከፊ ውጤት ይኖረዋል። ይህም መጀመሪያ ስሜታችንን የጎዳው ሰው አሁንም እየጎዳን እንዲቀጥል ከመፍቀድ ተለይቶ አይታይም። መጽሐፍ ቅዱስ “ከቁጣ ራቅ መዓትንም ተው” በማለት ጥበብ ያዘለ ምክር ይሰጠናል። (መዝሙር 37:​8) በመሆኑም አንዳንድ ክርስቲያኖች ከጊዜ በኋላ ይቅር ለማለት በሌላ አባባል ቅሬታን በውስጣቸው አምቀው ከመያዝ ተቆጥበዋል። ይህን ያደረጉት ጥፋቱን አቃልለው ስላዩት ሳይሆን በንዴት እየተብሰለሰሉ መኖር ስላልፈለጉ ነው። ጉዳዩን የፍትሕ አምላክ ለሆነው ፈጣሪ ሙሉ በሙሉ በመተዋቸው ትልቅ እፎይታ አግኝተው ሕይወታቸውን መምራት ችለዋል።​—⁠መዝሙር 37:​28

17. በራእይ 21:​4 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ይሖዋ የሰጠን ተስፋ ምን የሚያጽናና ማረጋገጫ ይዞልናል?

17 ቁስሉ በጣም ከባድ በሚሆንበት ጊዜ ቢያንስ ይህ ሥርዓት እስካለ ድረስ ትዝታው ሙሉ በሙሉ ከአእምሮአችን እንዲጠፋ ለማድረግ አይሳካልን ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ አንድ አዲስ ሥርዓት እንደሚመጣ ቃል ገብቷል፤ በዚህ ሥርዓት ውስጥ “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።” (ራእይ 21:​4) ዛሬ ለልባችን ሸክም የሚሆኑትን ማንኛቸውንም ነገሮች በዚያን ጊዜ ብናስብ ከባድ የስሜት ጉዳት ወይም ሥቃይ አያደርሱብንም።​—⁠ኢሳይያስ 65:​17, 18

18. (ሀ) ከሌሎች ወንድሞችና እህቶች ጋር ባለን ግንኙነት ይቅር ባይ መሆን ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ሌሎች ሲበድሉን ይቅር ማለትና መርሳት የምንችለው በምን መንገድ ነው? (ሐ) ይህ እኛን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

18 እስከዚያው ድረስ ግን ፍጽምና የሌለን ኃጢአተኛ ሰዎች መሆናችንን ሳንዘነጋ እንደ ወንድማማቾችና እህትማማቾች ሆነን በአንድነት ልንሠራና ልንኖር ይገባናል። ሁላችንም ስህተት እንሠራለን። አልፎ አልፎ አንዳችን ሌላውን የሚያስቆጣ ብሎም ስሜቱን የሚጎዳ ነገር እናደርጋለን። ኢየሱስ ሌሎችን ይቅር ማለት የሚያስፈልገን ‘እስከ ሰባ ሰባት ጊዜ እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ’ ብቻ እንዳልሆነ መገንዘቡ ትክክል ነበር! (ማቴዎስ 18:​22) የይሖዋን ያክል ፍጹም በሆነ መንገድ ይቅር ማለት እንደማንችል አይካድም። ይሁንና በአብዛኛው ወንድሞቻችን ሲበድሉን ቅሬታውን በማስወገድ ይቅር ልንላቸውና ዳግመኛ ጉዳዩን አንስተን ባለመውቀስ ልንረሳው እንችላለን። በዚህ መንገድ ይቅር ስንልና ስንረሳ የጉባኤውን ሰላም ብቻ ሳይሆን የልባችንንና የአእምሮአችንንም ሰላም መጠበቅ እንችላለን። ከሁሉ በላይ ደግሞ አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ይሖዋ ብቻ ሊሰጠው የሚችለውን ሰላም እናገኛለን።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​7

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የባቢሎናውያን ታልሙድ እንደሚገልጸው ከሆነ አንድ የረቢዎች ወግ እንዲህ ይላል:- “አንድ ሰው ቢበድል በመጀመሪያው፣ በሁለተኛውና በሦስተኛው ጊዜ ይቅር ይባላል፤ በአራተኛው ጊዜ ግን ይቅርታ አይደረግለትም።” (ዮማ 86ቢ) ለዚህ ሐሳብ በከፊል መሠረት የሆነው እንደ አሞጽ 1:​3፤ 2:​6 እንዲሁም ኢዮብ 33:​29 ያሉትን ጥቅሶች በሚመለከት ያላቸው የተሳሳተ ግንዛቤ ነው።

b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀ።

የክለሳ ጥያቄዎች

◻ ሌሎችን ይቅር ለማለት ፈቃደኞች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

◻ ‘እርስ በርስ መቻቻላችንን እንድንቀጥል’ የሚጠይቁት ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?

◻ ሌሎች የፈጸሙት በደል ስሜታችንን በጥልቅ ሲጎዳው ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ምን ማድረግ እንችላለን?

◻ ሌሎችን ይቅር ስንል መርሳት የሚገባን በምን መንገድ ነው?

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እኛ ቅሬታችንን አምቀን ስንይዝ የበደለን ሰው ስለ እኛ መብሰልሰል የሚያውቀው ነገር አይኖር ይሆናል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰላም ለመፍጠር በማሰብ ሌሎችን ቀርባችሁ ስታነጋግሩ አለመግባባቶች በቀላሉ ሊፈቱ ይችላሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ