የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • lr ምዕ. 7 ገጽ 42-46
  • ታዛዥነት ይጠብቅሃል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ታዛዥነት ይጠብቅሃል
  • ከታላቁ አስተማሪ ተማር
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ‘ልጆች ሆይ፣ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • “ለመታዘዝ ዝግጁ” ነህ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
  • “መታዘዝን ተማረ”
    “ተከታዬ ሁን”
  • የአምላክ ፍቅር ለዘላለም ይኖራል
    ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ
ለተጨማሪ መረጃ
ከታላቁ አስተማሪ ተማር
lr ምዕ. 7 ገጽ 42-46

ምዕራፍ 7

ታዛዥነት ይጠብቅሃል

የምትፈልገውን ነገር ሁሉ ማድረግ ብትችል ደስ ይልህ ነበር? ‘ማንም ሰው እንዲህ አድርግ፣ እንዲህ አታድርግ ብሎ ባያዘኝ ጥሩ ነበር’ ብለህ የተመኘህበት ጊዜ አለ? እስቲ ሳትደብቅ እውነቱን ንገረኝ።—

አንድ ልጅ አንድ ትልቅ ሰው የሚነግረውን ሲያዳምጥ

ትልልቅ ሰዎችን መስማት የሚኖርብህ ለምንድን ነው?

ይሁን እንጂ ለአንተ የሚሻልህ የትኛው ነው? በእርግጥ የሚጠቅምህ የፈለከውን ነገር ሁሉ ማድረግ ነው ወይስ አባትህንና እናትህን መታዘዝ?— ወላጆችህን መታዘዝ እንዳለብህ የተናገረው አምላክ ስለሆነ ይህን ትእዛዝ የሰጠበት ጥሩ ምክንያት መኖር አለበት። እስቲ ምክንያቱን ለመረዳት እንሞክር።

ዕድሜህ ስንት ነው?— የአባትህ ዕድሜ ስንት እንደሆነ ታውቃለህ?— የእናትህ ወይም የአያቶችህ ዕድሜስ ስንት ነው?— እነሱ አንተ ከመወለድህ በፊት ብዙ ዓመታት ኖረዋል። አንድ ሰው ረጅም ዕድሜ በኖረ መጠን ደግሞ ብዙ ነገሮች ለመማር ሰፊ ጊዜ ይኖረዋል። በየዓመቱ ብዙ ነገሮችን ለመስማት፣ ብዙ ነገሮችን ለማየት እና ብዙ ነገሮችን ለመሥራት ተጨማሪ ጊዜ ያገኛል። ስለዚህ ልጆች ከትልልቅ ሰዎች ብዙ ነገር ሊማሩ ይችላሉ።

በዕድሜ ከአንተ የሚያንስ ልጅ ታውቃለህ?— ታዲያ አንተ እሱ ወይም እሷ ከሚያውቁት የበለጠ ነገር አታውቅም?— አንተ ከእሱ ወይም ከእሷ የበለጠ ነገር ልታውቅ የቻልከው ከእነሱ የበለጠ ዕድሜ ስለኖርክ ነው። በዕድሜ ከአንተ ከሚያንሱት ይበልጥ ብዙ ነገሮችን ለመማር ጊዜ አግኝተሃል።

ከአንተ፣ ከእኔም ሆነ ከማንኛውም ሰው ይበልጥ ረጅም ዘመን የኖረው ማን ነው?— ይሖዋ አምላክ ነው። ይሖዋ አንተም ሆንክ እኔ ከምናውቀው የበለጠ ብዙ ነገር ያውቃል። እሱ የሚያዘን ነገር ከባድ በሚሆንበት ጊዜም እንኳን አድርጉ ያለንን ነገር ማድረግ ተገቢ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ታላቁ አስተማሪም እንኳን በአንድ ወቅት አምላክ ያለውን መታዘዝ ከባድ ሆኖበት እንደነበር ታውቃለህ?—

አንድ ጊዜ አምላክ ኢየሱስን አንድ በጣም አስቸጋሪ ነገር እንዲያደርግ ጠይቆት ነበር። በሥዕሉ ላይ እንደምናየው ኢየሱስ ስለዚህ ጉዳይ ጸልዮ ነበር። ‘ፈቃድህ ከሆነ ይህን ከባድ ነገር አስቀርልኝ’ ብሎ ጸለየ። ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መጸለዩ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ቀላል የማይሆንበት ጊዜ እንዳለ ያሳያል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በጸሎቱ መደምደሚያ ላይ ምን ብሎ እንደነበር ታውቃለህ?—

ኢየሱስ ሲጸልይ

ከኢየሱስ ጸሎት ምን እንማራለን?

ኢየሱስ ጸሎቱን ያበቃው “ይሁንና የእኔ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም” በማለት ነበር። (ሉቃስ 22:41, 42) አዎ፣ ኢየሱስ የራሱ ፈቃድ ሳይሆን የአባቱ ፈቃድ እንዲፈጸም ፈልጓል። በመሆኑም ኢየሱስ እሱ ራሱ ይሻላል ብሎ ያሰበውን ሳይሆን አምላክ የፈለገውን ነገር አድርጓል።

ታዲያ እኛ ከዚህ የምንማረው ምንድን ነው?— አምላክ አድርጉ የሚለንን ነገር ማድረግ ቀላል የማይሆንበት ጊዜ ቢኖርም እንኳን እሱ የሚያዘንን ነገር ማድረግ ምንጊዜም ትክክል እንደሆነ እንማራለን። ሌላም የምንማረው ነገር አለ። ምን እንደሆነ ታውቃለህ?— አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት አምላክና ኢየሱስ አንድ እንዳልሆኑ እንማራለን። ይሖዋ አምላክ በዕድሜ ከልጁ ከኢየሱስ ስለሚበልጥ ይሖዋ፣ ኢየሱስ ከሚያውቀው የበለጠ ብዙ ነገር ያውቃል።

አምላክን ስንታዘዝ እንደምንወደው እያሳየን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነው” ይላል። (1 ዮሐንስ 5:3) ስለዚህ አየህ፣ ሁላችንም አምላክን መታዘዝ ያስፈልገናል። አንተም ቢሆን እሱን መታዘዝ ትፈልጋለህ፣ አይደል?—

እስቲ መጽሐፍ ቅዱሳችንን እንግለጥና አምላክ ለልጆች ምን ትእዛዝ እንደሰጠ እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ በ⁠ኤፌሶን ምዕራፍ 6 ቁጥር 1, 2 እና  3 ላይ ምን እንደሚል እናንብብ። እንዲህ ይላል:- “ልጆች ሆይ፣ ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ፤ ምክንያቱም ይህ በአምላክ ዓይን ትክክለኛ ነገር ነው:- ‘አባትህንና እናትህን አክብር’፤ ይህ የተስፋ ቃል ያለው የመጀመሪያ ትእዛዝ ነው:- ‘ይህም መልካም እንዲሆንልህና ዕድሜህ በምድር ላይ እንዲረዝም ያደርጋል።’”

ስለዚህ አየህ፣ ለአባትህና ለእናትህ ታዛዥ እንድትሆን የሚነግርህ ይሖዋ አምላክ ራሱ ነው። አባትህንና እናትህን “አክብር” ሲባል ምን ማለት ነው? ወላጆችህን ከፍ አድርገህ መመልከትና ለሚሉህ ነገር ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባሃል ማለት ነው። ወላጆችህን የምትታዘዝ ከሆነ ‘መልካም እንደሚሆንልህ’ አምላክ ቃል ገብቷል።

ታዛዦች በመሆናቸው ምክንያት ከጥፋት የተረፉ ሰዎችን ታሪክ ልንገርህ። እነዚህ ሰዎች ከብዙ ጊዜ በፊት ትልቅ ከተማ በነበረችው በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር። በከተማዋ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች አምላክን የማይሰሙ ስለነበሩ አምላክ ከተማቸውን ሊያጠፋ እንደሆነ ኢየሱስ አስጠነቀቃቸው። በተጨማሪም ኢየሱስ ሰዎቹ ትክክል የሆነውን ነገር የሚወዱ ከሆነ እንዴት ከጥፋት መትረፍ እንደሚችሉ ነገራቸው። እንዲህ አላቸው:- ‘ኢየሩሳሌም በጦር ሠራዊት ተከባ በምታዩበት ጊዜ ጥፋቷ እንደተቃረበ ታውቃላችሁ። በዚያን ጊዜ ከኢየሩሳሌም ወጥታችሁ ወደ ተራሮች መሸሽ ይኖርባችኋል።’—ሉቃስ 21:20-22

ሰዎች ኢየሱስን በመታዘዝ ከኢየሩሳሌም ሲወጡ

እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ የሰጣቸውን ትእዛዝ መታዘዛቸው ሕይወታቸውን ያተረፈላቸው እንዴት ነው?

ልክ ኢየሱስ እንደተናገረው የጦር ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ለመውጋት መጣ። የሮም የጦር ሠራዊት ከተማዋን ዙሪያዋን ከበባት። ከዚያም ወታደሮቹ ባልታወቀ ምክንያት አካባቢውን ጥለው ሄዱ። በዚህ ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች አደጋው የቀረ መሰላቸው። ስለዚህ በከተማዋ መኖር ቀጠሉ። ሆኖም ኢየሱስ ምን እንዲያደርጉ ነግሯቸው ነበር?— አንተ በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም ብትኖር ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?— ኢየሱስ የተናገረውን ነገር ያመኑ ሰዎች ቤታቸውን ጥለው ከኢየሩሳሌም ርቀው ወደሚገኙ ተራሮች ሸሹ።

ዓመቱን በሙሉ በኢየሩሳሌም ላይ ምንም ነገር አልደረሰም። በሁለተኛውም ዓመት ምንም ነገር አልሆነም። በሦስተኛውም ዓመት ምንም ነገር አልደረሰም። በዚህ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች ከተማዋን ትተው የሸሹት ሰዎች ሞኞች እንደሆኑ አድርገው አስበው ይሆናል። በአራተኛው ዓመት ግን የሮም ጦር ሠራዊት ተመልሶ መጣ። እንደገና ኢየሩሳሌምን ዙሪያዋን ከበባት። በዚህ ጊዜ ከከተማዋ ወጥቶ ለማምለጥ ጊዜው አልፎ ነበር። የጦር ሠራዊቱ ከተማዋን አጠፋት። በከተማዋ ውስጥ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች ሞቱ፤ የቀሩትም ተማርከው ተወሰዱ።

ኢየሱስን የታዘዙት ሰዎችስ ምን ሆኑ?— እነሱ ዳኑ። ከኢየሩሳሌም ርቆ በሚገኝ ቦታ ስለነበሩ ምንም ጉዳት አልደረሰባቸውም። ታዛዥ መሆናቸው ሕይወታቸውን አትርፎላቸዋል።

አንተም ታዛዥ ከሆንክ ታዛዥነት ሕይወትህን ሊያተርፍልህ ይችላል?— ወላጆችህ በመኪና መንገድ ላይ ወይም ወንዝ ውስጥ እንዳትጫወት ሊነግሩህ ይችላሉ። ወላጆችህ እንዲህ የሚሉህ ለምንድን ነው?— መኪና ሊገጭህ ወይም ወንዝ ውስጥ ሰምጠህ ልትሞት ስለምትችል ነው። ይሁን እንጂ አንድ ቀን እንዲህ ብለህ ታስብ ይሆናል:- ‘አሁን መንገዱ ላይ መኪና የለም። ምንም ጉዳት አይደርስብኝም። ሌሎች ልጆች መንገዱ ላይ ወይም ወንዙ ውስጥ ይጫወታሉ፤ ሆኖም ምንም ጉዳት ሲደርስባቸው አላየሁም።’

ሁለት ልጆች አስፋልት ላይ እየተጫወቱ ሳለ መኪና ሲመጣ

አደጋ የሚፈጥር ነገር እንደሌለ በሚሰማህ ጊዜም እንኳን መታዘዝ የሚኖርብህ ለምንድን ነው?

በኢየሩሳሌም የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎችም እንዲህ ብለው አስበው ነበር። የሮም የጦር ሠራዊት ከተማዋን ትቶ ሲሄድ ሁሉም ነገር ደህና የሆነ መስሏቸው ነበር። ሌሎች ሰዎች በከተማዋ መኖር ስለቀጠሉ እነሱም በኢየሩሳሌም መኖር ቀጠሉ። ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም አልታዘዙም። በዚህ ምክንያት ሞቱ።

አንድ ልጅ በክብሪት እየተጫወተ ሳለ እሳት ሲነሳ

ሌላ ምሳሌ ደግሞ እንመልከት። በክብሪት ተጫውተህ ታውቃለህ?— ክብሪቱን ጭረህ ሲቀጣጠል ማየቱ ያስደስትህ ይሆናል። በክብሪት መጫወት ግን አደገኛ ሊሆን ይችላል። ቤቱ በሙሉ ሊቃጠልና አንተም ልትሞት ትችላለህ!

አንዳንድ ጊዜ ብቻ መታዘዝ በቂ እንዳልሆነ አስታውስ። ሁልጊዜ የምትታዘዝ ከሆነ ግን ሕይወትህ ከአደጋ ይጠበቃል። ‘ልጆች ሆይ፣ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ’ ብሎ ያዘዘው ማን ነው?— አምላክ ነው። አምላክ ይህን ትእዛዝ የሰጠህ ደግሞ ስለሚወድህ መሆኑን አስታውስ።

አሁን ደግሞ ታዛዥነት አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳዩትን የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብቡ:- ምሳሌ 23:22፤ መክብብ 12:13፤ ኢሳይያስ 48:17, 18፤ ቆላስይስ 3:20

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ