ለደህንነት በሚያበቃ ንጹሕ ሃይማኖት መመላለስ
“ንጹሕና እውነተኛ የሆነ ሃይማኖት በእግዚአብሔር አብ ዘንድ . . . በዓለም ከሚገኝ እድፍ ሰውነትን እድፍ መጠበቅ ነው።”—ያዕቆብ 1:27 የፊሊፕስ ትርጉም
1. ለሃይማኖት ምን ዓይነት ፍች ተሰጥቷል? በሐሰት ሃይማኖትና በእውነተኛው ሃይማኖት መካከል ያለውን ልዩነት ለመወሰን መብት ያለው ማን ነው?
ሃይማኖት “የጽንፈ ዓለም ፈጣሪና ገዥ በመሆኑ ለሚታወቅ ከሰው በላይ የሆነ ኃይል የሚቀርብ የእምነትና የአክብሮት መግለጫ ነው” የሚል ፍች ተሰጥቶታል። ታዲያ ምክንያታዊ ሆነን ብንመለከተው በእውነተኛ ሃይማኖትን በሐሰተኛ ሃይማኖት መሃል ያለውን ልዩነት ለመወሰን መብት ያለው ማን ነው? በእርግጥ የሚታመንበትና የሚከበረው ፈጣሪ መሆን አለበት። ይሖዋ በእውነተኛ ሃይማኖትና በሐሰተኛ ሃይማኖት ረገድ ያለውን አቋም በቃሉ ውስጥ በግልጽ ዘርዝሯል።
“ሃይማኖት” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ
2. መዝገበ ቃላት “የአምልኮ መልክ” ወይም “ሃይማኖት” ተብሎ የተተረጎመውን ግሪክኛ ቃል የሚያብራሩት እንዴት ነው? ለምንስ ዓይነት አምልኮቶች ሊሠራበት ይችላል?
2 “የአምልኮ መልክ” ወይም “ሃይማኖት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ትሬስኬያ ነው። የአዲስ ኪዳን የግሪክኛ - እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ይህን ቃል “የአምላክ አምልኮ፣ ሃይማኖት በተለይም በሃይማኖታዊ አገልግሎት ወይም በአምልኮ ሥርዓት የሚገለጽ ሃይማኖት” በማለት ይፈታዋል። ዘ ቲዮሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት እንደሚከተለው በማለት ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣል፦ “የቃሉ አመጣጥ አከራካሪ ነው። . . . ዘመናዊ ምሁራን ቴራፕ (‘ማገልገል’) ከሚለው ቃል ጋር ማያያዝን ይመርጣሉ።. . . . የትርጉም ልዩነት ሊስተዋል ይችላል። ‘ሃይማኖታዊ ቅንዓት’፣ . . . ‘የአምላክ አምልኮ’፣ ‘ሃይማኖት’ የሚል ጥሩ ገጽታ ያለው ትርጉም ሲኖረው . . . መጥፎ ገጽታ ያለው ትርጉምም አለው። እሱም ‘ሃይማኖታዊ አክራሪነት’፣ ‘የተሳሳተ አምልኮ’ የሚል ነው።” ስለዚህ በበጎም ሆነ በመጥፎ ገጽታው ትሬስኬያ “ሃይማኖት” ወይም “የአምልኮ መልክ” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል።
3. “የአምልኮ መልክ” ተብሎ የተተረጎመውን ቃል ሐዋርያው ጳውሎስ የተጠቀመበት እንዴት ነው? በቆላስይስ 2:18 ትርጉም ላይስ ምን ትኩረታችንን የሚስብ አስተያየት ተሰጥቷል?
3 ይህ ቃል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሰው አራት ጊዜ ብቻ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ የሐሰት ሃይማኖትን ለማመልከት ሁለት ጊዜ ተጠቅሞበታል። በሥራ 26:5 ላይ ክርስቲያን ከመሆኑ አስቀድሞ “በአምልኮታችን (“ሃይማኖታችን” የፊሊፕስ ትርጉም) ከሁሉ ይልቅ ሕግን በመጠንቀቅ እንደሚተጋ ወገን ፈሪሳዊ” እንደነበር መናገሩ ተመዝግቧል። ለቆላስይስ ሰዎች በጻፈላቸው ደብዳቤ ላይ “በአጉል ትሕትናና መላእክትንም በማምለክ የሚመካ ማንም ሰው ያለ ዋጋ እንዳያስቀራችሁ ተጠንቀቁ” በማለት አስጠንቅቋል። (ቆላስይስ 2:18 የ1980 ትርጉም) በግልጽ እንደሚታየው ይህ የመላእክት አምልኮ በዚያ ዘመን በፍርጊያ የተስፋፋ ነበር። ይሁንና ይህ አምልኮ የሐሰት ሃይማኖት አንዱ ገጽታ ነበር። በቆላስይስ 2:18 ላይ ያለውን ትሬስኪያ የሚለውን የግሪክኛ ቃል አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “ሃይማኖት” ብለው ሲተረጉሙት አብዛኞቹ ግን “አምልኮ” በማለት ተርጉመውታል። አዲሲቱ ዓለም ትርጉም ትሬስኪያን “የአምልኮ መልክ” የሚል አንድ ወጥ ትርጉም ሲሰጠው በባለማጣቀሻው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ትሬስኪያ ባለበት ቦታ ሁሉ በላቲን ትርጉሞች የተሠራበትን “ሃይማኖት” የሚለውን አማራጭ ቃል ይጠቅሳል።
በአምላክ አመለካከት “ንጹሕና ነውር የሌለበት” የሆነው ሃይማኖት
4, 5. (ሀ) ያዕቆብ በተናገረው መሠረት በሃይማኖት ረገድ ከሁሉ የበለጠ አስፈላጊ የሆነው የማን አቋም ነው? (ለ) የአንድን ሰው የአምልኮ መልክ ዋጋ ቢስ ሊያደርግ የሚችለው ምንድን ነው? “ከንቱ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ትርጉም ምንድን ነው?
4 ትሬስኪያ የሚለው ቃል የሚገኝባቸው ሁለት ሌሎች ቦታዎች የሚገኙት የመጀመሪያው መቶ ዘመን የአስተዳደር አካል አባል በሆነው በደቀመዝሙሩ በያዕቆብ በተጻፈው ደብዳቤ ላይ ነው። እንዲህ በማለት ጻፈ፦ “አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ (“ሃይማኖት” ፊልፕስ ትርጉም) ከንቱ ነው። ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ (“ሃይማኖት” ፊልፕስ ትርጉም) በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው። ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ በዓለምም ከሚገኘው እድፍ ሰውነትን መጠበቅ ነው።”—ያዕቆብ 1:26, 27
5 አዎን የይሖዋን ሞገስ ለማግኘትና ከጥፋት ተርፈን ተስፋ ወደተገባልን አዲስ ዓለም ለመግባት የምንፈልግ ከሆነ ይሖዋ በሃይማኖት ላይ ያለውን አቋም መጠበቅ ያስፈልገናል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ያዕቆብ አንድ ሰው ለራሱ እውነተኛ ሃይማኖታዊ የሆነ ሊመስለው እንደሚችልና ሆኖም ግን የአምልኮ መልኩ ወይም አምልኮቱ ከንቱ ሊሆንበት እንደሚችል ገልጿል። እዚህ ላይ “ከንቱ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “የማይረባ፣ ባዶ፣ ፍሬቢስ፣ ጥቅም የሌለው፣ አቅመቢስ፣ እውነትነት የጎደለው” በመባል ተተርጉሟል። አንድ ክርስቲያን ነኝ ባይ አንደበቱን ገትቶ አምላክን ለማወደስና ክርስቲያን መሰሎቹን ለማነጽ ካልተጠቀመበት አምልኮቱ ከንቱ ሊሆንበት ይችላል። “የራሱን ልብ እያታለለ” ሊሆን ይችላል። “በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕና እውነተኛ በሆነ ሃይማኖት” አልተመላለሰም። (የፊሊፕስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም) ዋጋ የሚኖረው የይሖዋ አመለካከት ነው።
6. (ሀ) የያዕቆብ ደብዳቤ ዋና መልእክት ምንድን ነው? (ለ) የያዕቆብ አጥብቆ የገለጸው ለንጹሕ አምልኮ የሚያስፈልግ ምን ነገር ነው? ዘመናዊው የአስተዳደር አካልስ በዚህ ረገድ ምን ተናግሯል?
6 ያዕቆብ ይሖዋ የሚያዛቸውን ከንጹሕ አምልኮ ጋር የተያያዙ ነገሮች በሙሉ አይዘረዝርም። ከአጠቃላዩ የደብዳቤው ዋና መልእክት ከሆነው በሥራ የተደገፈ እምነት ከመያዝና ከሰይጣን ዓለም ወዳጅነት ነፃ ከመሆን ጋር በመስማማት ሁለት ብቃቶችን ጎላ አድርጎ ገልጿል። አንዱ “ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ ነው” ይህም እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅርን ያጠቃልላል። ይሖዋ ሁልጊዜ ወላጆች ለሌላቸው ልጆችና ለመበለቶች ፍቅራዊ አሳቢነት ያሳያል። (ዘዳግም 10:17, 18፤ ሚልክያስ 3:5) የመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ አስተዳደር አካል ከፈጸማቸው የመጀምሪያው ተግባሮች አንዱ ለክርስቲያን መበለቶች የተደረገው ዝግጅት ነበር። (ሥራ 6:1-6) ሐዋርያው ጳውሎስ የሚረዳቸው ቤተሰብ ለሌላቸውና ለበርካታ ዓመታት ታማኝነታቸውን ላረጋገጡ በዕድሜ የሸመገሉ ችግረኛ መበለቶች ሊደረግ ስለሚገባው ፍቅራዊ እንክብካቤ ዝርዝር መመሪያዎችን ሰጥቷል። (1 ጢሞቴዎስ 5:3-16) ዘመናዊው የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካልም በተመሳሳይ “ለድሆች ስለመጠንቀቅ” እንዲህ በማለት ግልጽ መመሪያዎችን አውጥቷል፦ “እውነተኛ አምልኮ ሥጋዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ታማኞች እንክብካቤ ማድረግንም ይጨምራል።” (አገልግሎታችንን ለመፈጸም መደራጀት የሚለውን መጽሐፍ ገጽ 122-3 ተመልከቱ።) በዚህ ጉዳይ ላይ ቸልተኝነት የሚያሳዩ የሽማግሌዎች አካላት ወይም ግለሰብ ክርስቲያኖች በአምላካችንና በአባታችን ፊት ንጹሕና ነውር የሌለበት አምልኮ አንድ አስፈላጊ ክፍል የሆነውን ነገር እያስቀሩ ነው ማለት ነው።
“ከዓለም እድፍ ራስን መጠበቅ”
7, 8. (ሀ) የያዕቆብ ለእውነተኛ ሃይማኖት የሚያስፈልግ ምን ሁለተኛ ነገር ጠቅሷል? (ለ) ቀሳውስትና ካህናትስ ይህን ብቃት ያሟላሉን? (ሐ) ስለ ይሖዋ ምሥክሮችስ ምን ሊባል ይችላል?
7 ለእውነተኛ ሃይማኖት የሚያስፈልግ ያዕቆብ የጠቀሰው ሁለተኛው ነገር “ራስን ከዓለም እድፍ መጠበቅ ነው።” ኢየሱስ “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለችም” ብሏል። ከዚህ ጋር በመስማማት የእሱ እውነተኛ ተከታዮችም “የዚህ ዓለም ክፍል አይሆኑም።” (ዮሐንስ 15:19፤ 18:36) ስለዚህ ዓለም ሃይማኖቶች ቀሳውስትና ካህናት “የዚህ ዓለም ክፍል አይደሉም” ሊባል ይችላልን? የተባበሩት መንግሥታትን መደገፋቸውን ገልጸዋል። አብዛኞቹ ሃይማኖታዊ መሪዎች ጥቅምት 1986 የተባበሩት መንግሥታት የወሰነው “ዓለም አቀፍ የሰላም ዓመት” እንዲሳካ ጸሎት እንዲያቀርቡ የሮማው ሊቀ ጳጳስ ያቀረቡትን ጥሪ በመቀበል በኢጣልያ አገር በአሲሲ ተሰብስበዋል። ይሁን እንጂ በዚያው ዓመት የተደረጉት ጦርነቶችና ከዚያም ወዲህ የተገደሉት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሲታዩ ጥረታቸው ከንቱ ሆኗል። ቀሳውስቱ በሥልጣን ላይ የወጣ ማንኛውም ፓርቲ በወዳጅነት እንዲመለከታቸው ሲሉ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በስውር እየተዋዋሉ በሥልጣን ላይ ካለው ፓርቲ ጋር አብረው ይበላሉ፣ ይጠጣሉ። —ያዕቆብ 4:4
8 የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካዊ ጉዳዮችና በዚህ ዓለም ግጭቶች ረገድ ገለልተኞች ሆነው የሚኖሩ ክርስቲያኖች በመሆን ጥሩ ስም አትርፈዋል። በሁሉም የዓለም ክፍል በሚገኙ የጋዜጣ ዘገባዎችና በዘመናዊ የታሪክ መዝገቦች እንደተመሠከረላቸው ይህን አቋማቸውን የያዙት በሁሉም አህጉራትና በሁሉም መንግሥታት ሥር ነው። በእርግጥም “ከዓለም እድፍ ራሳቸውን ጠብቀዋል። ” “በአምላክ ፊት ንጹሕና እውነተኛ የሆን ሃይማኖት የእነሱ ብቻ ነው።”— ያዕቆብ 1:27 ፊሊፕስ ትርጉም
የእውነተኛ ሃይማኖት ሌሎች ምልክቶች
9. ለእውነተኛ ሃይማኖት የሚያስፈልገው ሦስተኛ መሥፈርት ምንድን ነው? ለምንስ?
9 ሃይማኖት “የጽንፈ ዓለም ፈጣሪና ገዥ በመሆኑ የሚታወቅ ከሰው በላይ የሆነ ኃይልን ማክበር” ከሆነ እውነተኛ ሃይማኖት አምልኮቱን ለእውነተኛው አምላክ ለይሖዋ ማቅረብ ያለበት መሆኑ አያጠራጥርም። እውነተኛ ሃይማኖት አብ ሁሉን ቻይነቱን፣ ክብሩንና ዘላለማዊነቱን ከሌሎች ሁለት አካላት ጋር ስለሚካፈልበት አንድነት በሦስትነት ያለው አምላክ በማስተማር ሰዎች ስለ አምላክ ያላቸውን እውቀት ማጨለም የለበትም። (ዘዳግም 6:4; 1 ቆሮንቶስ 8:6) ወደርየለሽ የአምላክ ስም የሆነውን ይሖዋን ያሳውቃል፤ ይህን ስም ያከብራል፤ የተደራጀ ሕዝብ በመሆንም የአምላክን ስም ይሸከማል። (መዝሙር 83:18፤ ሥራ 15:14) በዚህ ረገድ በዚህ በእውነተኛው ሃይማኖት የሚመላለሱ ሰዎች የክርስቶስ ኢየሱስን ምሳሌነት መከተል አለባቸው። (ዮሐንስ 17:6) በአሁኑ ጊዜ ከክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮች ሌላ ይህን መሥፈርት የሚያሟላ ማን ነው?
10. አንድ ሃይማኖት ከጥፋት በማትረፍ ወደ አምላክ አዲስ ዓለም ያስገባ ዘንድ ምን ማድረግ አለበት? ለምንስ?
10 ሐዋርያው ጴጥሮስ “መዳንም በሌላ በማንም የለም። እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና ” በማለት ተናግሯል። (ሥራ 4:8-12) ስለዚህ ከጥፋት በማትረፍ ወደ አምላክ አዲስ ዓለም የሚያስገባ ንጹሕ ሃይማኖት ሰዎች በክርስቶስና በቤዛው መሥዋዕት ዋጋ ላይ እምነት እንዲያደርጉ ይቀሰቅሳል። (ዮሐንስ 3:16, 36፤ 17:3፤ ኤፌሶን 1:7) ከዚህም በላይ እውነተኛ አምላኪዎች ክርስቶስ በመግዛት ላይ ያለ የይሖዋ ንጉሥና ቅቡዕ ሊቀ ካህናት እንደመሆኑ እንዲታዘዙለት መርዳት ይኖርበታል።—መዝሙር 2:6-8፤ ፊልጵስዮስ 2:9-11፤ ዕብራውያን 4:14, 15
11. እውነተኛ ሃይማኖት መመሥረት ያለበት በምን ላይ ነው? በዚህ ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው አቋም ምንድን ነው?
11 ንጹሕ ሃይማኖት መመሥረት ያለበት በተገለጠው የአንዱ እውነተኛ አምላክ ፈቃድ ላይ እንጂ በሰው ሠራሽ ወጎች ወይም ፍልስፍናዎች ላይ አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይገለጥልን ኖሮ ስለ ይሖዋና ስለ አስደናቂ ዓላማዎቹም ይሁን ስለ ኢየሱስና ስለ ቤዛዊ መሥዋዕቱ ምንም ነገር አናውቅም ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የማይናወጥ እምነት እንዲያሳድሩ ይረዳሉ። በዕለታዊ አኗኗራቸውም ሐዋርያው ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሳጽ ልብንም ለማቅናት . . . ይጠቅማል” ብሎ ከተናገረው ጋር እንደሚስማሙ ያረጋግጣሉ።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
እውነተኛው ሃይማኖት—የሕይወት መንገድ ነው
12. አምልኮ እውነት እንዲሆን ከተፈለገ ከእምነት በተጨማሪ ምን ያስፈልጋል? እውነተኛ ሃይማኖት የሕይወት መንገድ የሆነው በምን ረገድ ነው?
12 ኢየሱስ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 4:24) ስለዚህ እውነተኛው ሃይማኖት ወይም የአምልኮ መልክ የታይታ ሥርዓት፣ ልማዳዊ ወይም አምላካዊነትን የሚያሳይ ውጫዊ ትርኢት አይደለም። ንጹሕ አምልኮ መንፈሳዊና በእምነት ላይ የተመሠረተ ነው። (ዕብራውያን 11:6) ይሁን እንጂ ይህ እምነት በሥራ መደገፍ አለበት። (ያዕቆብ 2:17) እውነተኛ ሃይማኖት ዘመናዊ ዝንባሌዎችን አይቀበልም። የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባርና የንጹሕ አነጋገር ሥርዓት አጥብቆ ይይዛል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ኤፌሶን 5:3-5) በእውነተኛው ሃይማኖት የሚመላለሱ ሰዎች በቤተሰብ ኑሮአቸው፣ በመተዳደሪያ ሥራቸው፣ በትምህርት ቤትና በመዝናኛዎቻቸውም ሳይቀር የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች ለማፍራት ከልብ ይጥራሉ። (ገላትያ 5:22, 23) የይሖዋ ምሥክሮች “እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውንም ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን ምክር ችላ እንዳይሉ ይጥራሉ። (1 ቆሮንቶስ 10:31) ሃይማኖታቸው አምልኮታዊ ሥርዓቶችን በመፈጸም ላይ ብቻ የተመካ አይደለም። የሕይወት መንገድ ነው።
13. እውነተኛ አምልኮ ምን ነገሮችን ያጠቃልላል? የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛ ሃይማኖታዊ ሕዝብ ናቸው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
13 እርግጥ፣ እውነተኛ ሃይማኖት መንፈሳዊ ሥራዎችንም ያጠቃልላል። እነዚህ ሥራዎች የግልና የቤተሰብ ጸሎትን፣ የአምላክን ቃልና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎችን አዘውትሮ ማጥናትን፣ በእውነተኛ ክርስቲያናዊ የጉባኤ ስብሰባዎች መገኘትን ይጨምራሉ። የጉባኤ ስብሰባዎች የሚከፈቱትና የሚዘጉት ይሖዋን በሚያወድሱ መዝሙሮችና በጸሎቶች ነው። (ማቴዎስ 26:30፤ ኤፌሶን 5:19) በንግግሮችና በሁሉም እጅ በሚገኝ የታተመ ጽሑፍ ላይ በሚደረግ የጥያቄና መልስ ውይይት አማካኝነት የሚያንጹ መንፈሳዊ ርዕሰ ትምህርቶች ይጠናሉ። እንዲህ ዓይነቶቹ ስብሰባዎች የሚደረጉት አብዛኛውን ጊዜ ንጹሕ በሆኑና በጌጣ ጌጥ ባላሸበረቁ የመንግሥት አዳራሾች ነው። የመንግሥት አዳራሾች የሚያገለግሉት ለሃይማኖታዊ ጉዳዮች ብቻ ማለትም ለስብሰባዎች፣ ለጋብቻ ሥርዓትና የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር ነው። የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሾቻቸውና የታላላቅ ስብሰባ አዳራሾቻቸው ለይሖዋ አምልኮ የተወሰኑ ስለሆኑ በአክብሮት ይይዟቸዋል። የመንግሥት አዳራሾች እንደ ብዙዎቹ ቤተክርስቲያኖች ማኅበራዊ ክበቦች አይደሉም።
14.ለዕብራይስጥ ተናጋሪ ሕዝቦች አምልኮ ማለት ምን ትርጉም ነበረው? በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ ለይቶ የሚያሳውቀው ምንድን ነው?
14 ቀደም ሲል ምሁራን “የአምልኮ መልክ” ወይም “ሃይማኖት” ተብሎ የተተረጎመውን የግሪክኛ ቃል “ማገልገል” ከሚለው ግሥ ጋር እንደሚያዛምዱት ተመልክተናል። የዕብራይስጡ ተመሳሳይ ቃል ‛አቮድነህʹ ሲሆን “አገልግሎት” ወይም “አምልኮ” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ለዕብራውያን አምልኮ ማለት አገልግሎት ማለት ነበር። ዛሬም ለእውነተኛ አምላኪዎች ተመሳሳይ ትርጉም አለው። የእውነተኛው ሃይማኖት በጣም አስፈላጊና ጉልህ መለያ ምልክት የሚመላለሱበት ሁሉ “ለአሕዛብም ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህን የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ” በመስበኩ አምላካዊ አገልግሎት መካፈላቸው ነው። (ማቴዎስ 24:14፤ ሥራ 1:8፤ 5:42) የአምላክ መንግሥት የሰው ልጅ ብቸኛ ተስፋ መሆኗን ለሕዝብ በመመስከር የታወቀው የትኛው ሃይማኖት ነው?
አዎንታዊ ውጤትና አንድነት የሚያስገኝ ኃይል
15. የእውነተኛ ሃይማኖት ዓይነተኛ መለያ ምንድን ነው?
15 የሐሰት ሃይማኖት ይከፋፍላል። ጥላቻና ደም መፋሰስን አስከትሏል። እስከ አሁንም እያስከተለ ነው። በተቃራኒው ደግሞ እውነተኛ ሃይማኖት አንድ ያደርጋል። ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ደቀመዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:35) የይሖዋ ምሥክሮችን አንድ የሚያደርግ ፍቅር የተቀረውን የሰው ዘር የሚከፋፍለውን ብሔራዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ጎሣዊ ድንበሮችን ንቆና ልቆ የሚሄድ ነው። ምሥክሮቹ “በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብረው እየተጋደሉ፣ በአንድ መንፈስ ጸንተው ቆመዋል። ”—ፊልጵስዩስ 1:27
16. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች ምን “የምሥራች” ይሰብካሉ? (ለ) በይሖዋ ሕዝቦች ላይ እየተፈጸሙ ያሉት ምን ትንቢቶች ናቸው? ምን በረከቶችስ ተገኝተዋል?
16 የይሖዋ ምስክሮች የሚሰብኩት “የምሥራች” የአምላክ የማይለወጥ ዓላማ በቅርቡ የሚፈጸም መሆኑን የሚገልጽ ነው። ፈቃዱ “በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ላይ” ልትፈጸም ነው። (ማቴዎስ 6:10) የይሖዋ ክብራማ ስም ይቀደሳል፤ ምድርም እውነተኛ አምላኪዎች ለዘላለም የሚኖሩባት ገነት ትሆናለች። (መዝሙር 37:29) በሁሉም አገሮች ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቃል በቃል “ይሖዋ ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ” እያሉ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እየተባበሩ ነው። (ዘካርያስ 8:23) ይሖዋ ሕዝቡን እየባረከ ነው። በእርግጥም “ታናሹ” በማንኛውም ረገድ ማለትም በሐሳብ፣ በሥራና በአምልኮ ሙሉ በሙሉ አንድነት ያለው ዓለም አቀፍ ጉባኤ “ብርቱ ሕዝብ” ሆኗል። (ኢሳይያስ 60:22) ይህ የሐሰት ሃይማኖት ሊያደርገው ያልቻለ ነገር ነው።
የንጹሕ አምልኮ አሸናፊነት
17. ታላቂቱ ባቢሎንን የሚጠብቃት ምንድን ነው? ይህስ የሚመጣው እንዴት ነው?
17 የአምላክ ቃል በምሳሌያዊ አጠራር “ታላቂቱ ባቢሎን” የተባለችው የዓለም የሐሰት ሃይማኖቶች ግዛት እንደምትጠፋ ተንብዮአል። መጽሐፍ ቅዱስ የምድር “ነገሥታትን” ወይም ፖለቲካዊ መሪዎችን ቀንዶች ባሉት የዱር አውሬ ይመስላቸዋል። አምላክ ይህችን አመንዝራ መሰል የሰይጣን ዲያብሎስ ድርጅት ለመገልበጥና ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ያለውን ዓላማ በእነዚህ መሪዎች ልብ ውስጥ እንደሚያደርግ ይነግረናል።—ራእይ 17:1, 2, 5, 6, 12, 13, 15-18ን ተመልከቱa
18. መጽሐፍ ቅዱስ ታላቂቱ ባቢሎን መጥፋት ያለባት በምን አስፈላጊ ምክንያት እንደሆነ ይናገራል? የሐሰት ሃይማኖት ይህን አሰቃቂ አካሄድ የጀመረው መቼ ነው?
18 ታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት ሊደርስባት የሚገባው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “በእርሷም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም በምድርም የታረዱ ደም ሁሉ ተገኘባት”በማለት መልስ ይሰጠናል። (ራእይ 18:24) ኢየሱስ ይህ የሐሰት ሃይማኖት ደም አፍሳሽነት ባቢሎን ከመመሥረቷም አስቀድሞ እንደጀመረ ሲገልጽ ራሱን ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር ያቆራኘውን የአይሁዳውያን ሃይማኖት መሪዎች አውግዟል። እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ እባቦች የእፉኝት ልጆች ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላቸሁ። . . . ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተመቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ እውነት እላችኋለሁ።” (ማቴዎስ 23:33-35) አዎን በኤደን ገነት ዓመፅ በተነሣ ጊዜ በምድር ላይ የተጀመረው ሐሰት ሃይማኖት ለፈጸመው አሰቃቂ ደም አፍሳሽነት ሁሉ መልስ መስጠት ይኖርበታል።
19, 20. (ሀ) እውነተኛ አምላኪዎች በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ፍርድ ከተፈጸመባት በኋላ ምን ያደርጋሉ? (ለ) ከዚያ በኋላስ ምን ነገር ይደርሳል? በእውነተኛ አምላኪዎች ፊት የሚከፈተው አጋጣሚ ምን ይሆናል
19 ታላቂቱ ባቢሎን ከጠፋች በኋላ በምድር ላይ የሚኖሩ እውነተኛ አምላኪዎች እንደሚከተለው ብሎ ከዘመረው ሰማያዊ የመዘምራን ቡድን ጋር ድምጻቸውን ያስተባብራሉ፦ “ሃሌ ሉያ . . . ታላቂቱ ጋለሞታ ስለፈረደባት፣ የባሪያዎቹንም ደም ከእጅዋ ስለተቀበለ . . . ጢስዋም ለዘላለም እስከ ዘላለም ይወጣል።”—ራእይ 19:1-3
20 ከዚያም ሌሎቹ የሰይጣን የሚታይ ድርጅት ክፍሎች ይጠፋሉ። (ራእይ 19:17-21) ከዚህ በኋላ የሐሰት ሃይማኖት መሥራች የሆነው ሰይጣንና አጋንንቱ ወደ ጥልቁ ይጣላሉ። ከዚያ ወዲያ የይሖዋን እውነተኛ አምላኪዎች ለማሳደድ ነፃ አይሆኑም። (ራእይ 20:1-3) ንጹሕ ሃይማኖት በሐሰተኛው ላይ ድል ይቀዳጃል። አሁን ከታላቂቱ ባቢሎን እንዲሸሹ የተሰጣቸውን መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ የሚቀበሉ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ከጥፋቱ ተርፈው ወደ አምላክ አዲስ ዓለም የመግባት አጋጣሚ ያገኛሉ። እዚያም ለዘላለም በእውነተኛው ሃይማኖት ለመመላለስና ይሖዋን በማምለክ ሊያገለግሉት ይችላሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስለዚህ ትንቢት ሙሉ ማብራሪያ ለማግኘት በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትናንሽ ጽሑሮች ማህበር የታተመውን ራእይ ታላቁ መደምደሚያ ቀርቧል የተሰኘውን መጽሐፍ ገጽ 33-36 ተመልከት።
ምን ያህል ታስታውሳላችሁ
◻ በሃይማኖት ረገድ ከሁሉ የበለጠ አስፈላጊ የሆነው የማን አቋም ነው? ለምንስ?
◻ ያዕቆብ ለእውነተኛ ሃይማኖት የሚያስፈልጉ ምን ሁለት ነገሮች አጥብቆ ገልጿል?
◻ ሌሎች የንጹሕ አምልኮ መሥፈርቶች ምንድን ናቸው?
◻ የይሖዋ ምሥክሮች እየሰበኩ ያሉት ምን “የምሥራች” ነው?
◻ እውነተኛ ሃይማኖት በሐሰተኛው ላይ ድል የሚቀዳጀው እንዴት ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥቅምት 1986 በአሲሲ ኢጣልያ የተሰበሰቡ ሃይማኖታዊ መሪዎች
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነተኛ ሃይማኖት ለአምልኮ አንድ ላይ መሰብሰብን ያጠቃልላል