የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 7/15 ገጽ 27-30
  • ትሕትናን መልበስ ያለብን ለምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ትሕትናን መልበስ ያለብን ለምንድን ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ትሕትና ምንድን ነው?
  • ልባዊ መሆን አለበት
  • የይሖዋ አመለካከት
  • አምላክና ክርስቶስ ትሕትናን አሳይተዋል
  • የትሕትና ጥቅሞች
  • ትሕትናና የአምላክ ድርጅት
  • ትሕትናና ተግሣጽ
  • ትሕትናን እንደተላበሳችሁ ኑሩ
  • እውነተኛ ትሕትናን አዳብሩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ይሖዋ ትሑት አገልጋዮቹን ከፍ አድርጎ ይመለከታል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019
  • ኢየሱስ በትሕትና ረገድ አርዓያ ትቷል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • ልንመስላቸው የሚገቡ የትሕትና ምሳሌዎች
    መጠበቂያ ግንብ—1993
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 7/15 ገጽ 27-30

ትሕትናን መልበስ ያለብን ለምንድን ነው?

አሜሪካዊው ደራሲ ኤድገር አላን ፖይ አዲስ የጻፈውን ትረካውን ለጓደኞቹ አንብቦ እንደጨረሰ ጓደኞቹ እየቀለዱ የገጸ ባሕርዩን ስም በጣም በማዘውተር እንደጠቀሰው ተናገሩ። የፖይ ምላሽ ምን ነበር? አንዱ ጓደኛው ታሪኩን ወደ ኋላ ተመልሶ ሲያስታውስ “ኩሩ መንፈሱ እንዲህ ዓይነቱን ግልጽ ግሣጼ መቋቋም ስላልቻለ ተናደደና ጓደኞቹ ሊከለክሉት እንኳ ጊዜ ከማግኘታቸው በፊት እያንዳንዱን ወረቀት በሚንበለበል እሳት ውስጥ ወረወረው።” “ከሱ የተለመደ ትካዜ ነፃ የሆነ በጣም አስቂኝ” ትረካው በዚህ መንገድ ጠፋ። ትሕትና ሊያድነው ይችል ነበር።

ኩራት ሰዎችን ጥበብ የጐደላቸው ነገሮች እንዲያደርጉ የሚያደርግ ቢሆንም ይህ ጠባይ በዓለም በጣም ተስፋፍቶ ይገኛል። ይሁን እንጂ የይሖዋ አገልጋዮች የተለዩ መሆን አለባቸው። ግሩም አሠራር ያለውን የትሕትናን መጐናጸፊያ መልበስ አለባቸው።

ትሕትና ምንድን ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ በጥንቷ የቆላስይስ ከተማ ለነበሩ መሰል አማኞች በጻፈላቸው ጊዜ ውብ የሆነውን የትሕትና ክርስቲያናዊ ልብስ ጠቅሷል። እንዲህ በማለት አሳሰባቸው፦ “እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን (ደግነትን)፣ ትሕትናን (“ራስን ዝቅ ማድረግን” አዓት)፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ።”​—ቆላስይስ 3:12

አዎን፣ ትሕትና “ራስን ዝቅ ማድረግ” ነው። “የአእምሮ ትሕትና፣ የኩራት አለመኖር፣ የዋህነት” ነው። ትሑት ሰው “በመንፈሱ ልከኛ ነው እንጂ ኩሩ አይደለም።” “ጥልቅ የሆነ አክብሮት ያሳያል።” (ዘ ወርልድ ቡክ ዲክሽነሪ ጥራዝ 1 ገጽ 1030) ትሕትና ፈሪነት ወይም ደካማነት አይደለም። እንደ እውነቱ ከሆነ ኩራት ደካማነትን ሲያንጸባርቅ ትሕትና ማሳየት ግን ድፍረትና ጥንካሬን ይጠይቃል።

በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ራስህን ዝቅ አድርግ” ተብሎ የሚተረጐመው ቃል ቀጥተኛ ፍቺው “ራስህን ዝቅ አድርገህ እርገጠው” የሚል ነው። ስለዚህ ጥበበኛው የምሳሌ መጽሐፍ ጸሐፊ እንዲህ በማለት መክሯል፦ “ልጄ ሆይ ለጐረቤትህ ዋስ ብትሆን (በአፍህ ቃል ብትያዝ) . . . ራስህን አድን፤ በጐረቤትህ እጅ ወድቀሃልና ፈጥነህ ሂድ [ራስህን ዝቅ አድርገህ እርገጠው] ጐረቤትህንም [በልመና] ነዝንዘው።” (ምሳሌ 6:1-3) ያም ማለት ኩራትን ወደጐን ጥለህ ስሕተትህን ተቀበልና ጉዳዩን አስተካክል ማለት ነው።

ልባዊ መሆን አለበት

ትሑት የሚመስሉ ሰዎች ሁሉ እውነተኛ ትሕትና አላቸው ማለት አይደለም። ትሑት የሚመስሉ አንዳንድ ግለሰቦች እንዲያውም ኩሩዎች ሊሆኑና እኔ ያልኩት ካልሆነ ብለው የሚደርቁ ሊሆኑ ይችላሉ። በሌላም በኩል በሌሎች ለመደነቅ ብለው የውሸት ትሕትና ካባ የሚለብሱ አሉ። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ “የቀልድ ትሕትና” የሚያሳዩ አንዳንድ ሰዎች አጋጥመውት ነበርና ይህን የሚያደርግ ማንኛውም ሰው “በሥጋዊ አእምሮ በከንቱ የታበየ” መሆኑን አመልክቷል። እንዲህ ዓይነቱ ግለሰብ የአምላክን ሞገስ ማግኘት በመብላት ወይም ባለመብላት፣ በመጠጣት ወይም ባለመጠጣት ወይም አንዳንድ ነገሮችን ባለመንካት ወይም አንዳንድ ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ቀኖችን በመጠበቅ ላይ የተመካ ነው ብሎ በተሳሳተ መንገድ ያስባል። እውነት ነው፣ ሃይማኖተኛና ትሑት መስሎ ታይቶ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የውሸት ትሕትናው ዋጋ ቢስ ነበር። (ቆላስይስ 2:18, 23) እንዲያውም ኩራቱ የሕይወት ሽልማት የሚሰጠው ቁሳዊ ነገሮችን ለካዱ ሰዎች ነው ብሎ ወደማሰብ መርቶታል። ከዚህም ሌላ ይህ የሐሰት ትሕትና በረቀቀ መንገድ ሌላ ዓይነት ፍቅረ ንዋይ ይዞታል ምክንያቱም የብሕትውና ክልክል ነገሮች የሚያተኩሩት እሱ (ባሕታዊው) ንቋቸዋል በተባሉት ነገሮች ላይ ስለሆነ ነው።

በሌላው በኩል እውነተኛው ትሕትና አንድን ሰው በልብሱ፣ በጸጉር አያያዙና በአኗኗሩ ከሌሎች በልጦ ለመታየት ከመሞከር ይገታዋል። (1 ዮሐንስ 2:15-17) ትሕትናን የለበሰ ሰው ወደራሱ ወይም ወደ ችሎታዎቹ አላስፈላጊ የሆነ ትኩረትን አይስብም። ከዚህ ይልቅ ትሕትና ሌሎችን በአሳቢነት እንዲይዛቸውና አምላክ እንደሚያየው አድርጐ ራሱን እንዲያይ ይረዳዋል። ታዲያ አምላክ የሚያየው እንዴት ነው?

የይሖዋ አመለካከት

ነቢዩ ሳሙኤል ለእስራኤል ሕዝብ አዲስ ንጉሥ ሊሾምላቸው በሄደ ጊዜ ይሖዋ የመረጠው የእሴይን ልጅ ኤልያብን ነው ብሎ አስቦ ነበር። አምላክ ግን ሳሙኤልን “ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ። ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት። ሰው ፊትን ያያል ይሖዋ ግን ልብን ያያል” አለው። ሰባቱም የእሴይ ልጆች ውድቅ ተደረጉ። አምላክ የመረጠው የታማኝነትና የትሕትና ባለቤት የሆነው ዳዊት ሆኖ ተገኘ።​—1 ሳሙኤል 13:14፤ 16:4-13

የትሕትና መጐናጸፊያ ኩሩዎችና ትምክህተኞች በመሆን የአምላክን ሞገስ እንዳናጣ ይጠብቅብናል። እሱ “ትዕቢተኞችን ይቃወማልና። ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።” (ያዕቆብ 4:6) የሱ አመለካከት “ይሖዋ ከፍ ያለ ነውና ወደ ችግረኞች (ትሑታንም) ይመለከታል። ትዕቢተኞችንም ከሩቅ (ብቻ) ያውቃል” በሚሉት የመዝሙራዊው ቃላት ተገልጿል። (መዝሙር 138:6፤ 1 ጴጥሮስ 5:5, 6) አምላክ ከአገልጋዮቹ የሚጠብቀው ነገር በሚክያስ 6:8 ላይ በቀረበው ጥያቄ ተገልጿል፦ “እግዚአብሔር ከአንተ ዘንድ የሚሻው . . . ፍርድን ታደርግ ዘንድ ምሕረትንም (ደግነትንም) ትወድድ ዘንድ ከአምላክህም ጋር በትሕትና [ቦታህን ጠብቀህ] ትሄድ ዘንድ አይደለምን?”

አምላክና ክርስቶስ ትሕትናን አሳይተዋል

ይሖዋ ትሕትና እንድናሳይ ቢጠብቅብን አያስደንቅም! ከራሱ ባሕርያት አንዱ ትሕትና ነው። አምላክ ከጠላቶቹ ካዳነው በኋላ ዳዊት እንዲህ በማለት ዘመረ፦ “ለደህንነቴም መታመኛን ሰጠኸኝ። . . . የራስህ ትሕትና ታላቅ ያደርገኛል።” (መዝሙር 18:35፤ 2 ሳሙኤል 22:1, 36) ይሖዋ ያለው በመጨረሻዎቹ ከፍተኛ ሰማያት ላይ ቢሆንም “የተዋረዱትን ለማንሣት በሰማይና በምድር ራሱን ዝቅ አድርጐ ይመለከታል። ችግረኛውን ከሕዝብ አለቆች ጋር ያስቀምጠው ዘንድ ከመሬት ያነሣል።” (መዝሙር 113:5-8) አምላክ ለኃጢአተኛው የሰው ዘር ምሕረት በማድረግ ትሕትና አሳይቷል። ኃጢአተኞችን የያዘበት መንገድና ልጁን ለኃጢአት መሥዋዕት አድርጐ መስጠቱ የትሕትናው፣ የፍቅሩና የሌሎች ባሕርያቱ መግለጫ ነው።​—ሮሜ 5:8፤ 8:20, 21

“የዋህና በልቡ ትሑት የነበረው” ኢየሱስ ክርስቶስም ከማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር የበለጠ የትሕትና ምሳሌ ነው። (ማቴዎስ 11:29) ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሎ ነገራቸው፦ “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል። ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል።” (ማቴዎስ 23:12) ይህ እንዲሁ ንግግር ለማሳመር ብቻ የተነገረ አይደለም። ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ኢየሱስ በባሪያዎች ይደረግ የነበረ አገልግሎት በመፈጸም የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቧል። (ዮሐንስ 13:2-5, 12-17) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት አምላክን በትሕትና አገልግሏል። ትንሣኤ አግኝቶ በሰማይ ከፍ ያለ ከተሰጠውም በኋላ ቢሆን ትሕትና ማሳየቱን ቀጥሏል። ስለዚህ ጳውሎስ መሰል አማኞችን ‘ሌሎች ከነሱ ይልቅ እንደሚሻሉ በትሕትና እንዲቆጥሩና’ የኢየሱስ ክርስቶስን ራስን ዝቅ የማድረግ ዝንባሌ እንዲይዙ መክሯቸዋል።​—ፊልጵስዩስ 2:3, 5-11

አምላክና ኢየሱስ ትሕትና ስለሚያሳዩ መለኮታዊ ድጋፍ ማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ይህን ባሕርይ ማሳየት አለባቸው። አንዳንዴ ትዕቢተኛነት አሳይተን ከሆነ ራሳችንን ዝቅ ማድረግና አምላክ ይቅርታ እንዲያደርግልን መጠየቅ ጥበብ ይሆናል። (ከ2 ዜና መዋዕል 32:24-26 ጋር አወዳድር) በተጨማሪም ስለራሳችን ታላቅ ግምት ከማሳደር ይልቅ “የትዕቢትን ነገር አታስቡ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ” ያለውን የጳውሎስን ምክር በተግባር ላይ ማዋል ያስፈልገናል። (ሮሜ 12:16) ይሁን እንጂ ትሕትና ራሳችንንና ሌሎችን ሊጠቅም የሚችለው እንዴት ነው?

የትሕትና ጥቅሞች

አንዱ የትሕትና ጥቅም ስለራሳችን ጉራ ከመንዛት የሚገታን መሆኑ ነው። በዚህ መንገድ ሌሎችን ከማበሳጨት እንቆጠባለን፤ በሥራ ክንውናችን ሌሎች ሳይደነቁ በመቅረታቸውም መልሰን ከማፈር ያድነናል። በራሳችን ሳይሆን በይሖዋ መመካት ይኖርብናል።​—1 ቆሮንቶስ 1:31

ትሕትና መለኮታዊ አመራር እንድናገኝ ይረዳናል። ይሖዋ ለዳንኤል ራእይ አስይዞ መልአክ ሰደደለት፤ ምክንያቱም ያ ነቢይ አመራርና ማስተዋል ለማግኘት በአምላክ ፊት ራሱን ዝቅ አድርጐ ስለነበረ ነው። (ዳንኤል 10:12) ዕዝራ በኢየሩሳሌም የነበረውን የይሖዋን ቤተ መቅደስ ለማስጌጥ ከብዙ ወርቅና ብር ጋር የአምላክን ሕዝቦች ከባቢሎን አውጥቶ ሊወስዳቸው ሲል ራሳቸውን በአምላክ ፊት ለማዋረድ ይችሉ ዘንድ ጾም አወጁ። ውጤቱስ ምን ሆነ? በአደገኛው ጉዞ ወቅት ይሖዋ ከጠላት አደጋና ጥቃት ጠበቃቸው። (ዕዝራ 8:1-14, 21-32) እኛም ከአምላክ የተሰጡንን ኃላፊነቶች በራሳችን ጥበብና ብርታት ለመፈጸም ከመሞከር ይልቅ እንደ ዳንኤልና እንደ ዕዝራ ትሕትናን እናሳይና የይሖዋን አመራር እንሻ።

የትሕትናን መጐናጸፊያ ከለበስን ሌሎችን እናከብራለን። ለምሳሌ ትሕትና ያላቸው ልጆች ወላጆቻቸውን ያከብራሉ፣ ይታዘዛሉም። ትሕትና የማናዳላ ስለሚያደርገን ትሑት ክርስቲያኖች ከሌላ ብሔረሰብ፣ ዘርና አስተዳደግ የሆኑ መሰል አማኞችን ያከብራሉ።​—ሥራ 10:34, 35፤ 17:26

ትሕትና ፍቅርንና ሰላምን ያዳብራል። ትሑት የሆነ ሰው መብቴ ነው የሚለውን ነገር ለማስጠበቅ በመሞከር ከመሰል አማኞች ጋር አይጣላም። ጳውሎስ የሚያንጹና የአንድን ወንድም ሕሊና የማይረብሹ ነገሮችን ብቻ ያደርግ ነበር። (ሮሜ 14:19-21፤ 1 ቆሮንቶስ 8:9-13፤ 10:23-33) ትሕትና ሌሎች የበደሉንን ይቅር በማለት ፍቅርና ሰላምን እንድናስፋፋ ይረዳናል። (ማቴዎስ 6:12-15፤ 18:21, 22) ቅር ወደተሰኘው ሰው እንድንሄድ፣ ጥፋታችንን እንድናምን፣ ይቅርታ እንድንጠይቅና የሠራነውን በደል ለማስተካከል የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ ይገፋፋናል። (ማቴዎስ 5:23, 24፤ ሉቃስ 19:8) የተጐዳብን ሰው ቀርቦ ካነጋገረንም ትሕትና ነገሮችን በፍቅር መንፈስ በሰላም እንድናቃና ይገፋፋናል።​—ማቴዎስ 18:15፤ ሉቃስ 17:3

መዳን ትሕትና በማሳየት ላይ የተመካ ነው። ለምሳሌ አምላክን በሚመለከት እንዲህ ተብሏል፦ “አንተ የተጠቃውን (የተዋረደውን) ሕዝብ ታድናለህና። የትዕቢተኞችን ዓይን ግን ታዋርዳለህ።” (2 ሳሙኤል 22:28) ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ስለ እውነት፣ ስለ ትሕትናና ስለ ጽድቅ በሚነሣበት ጊዜ’ በሱና ባባቱ ፊት ራሳቸውን የሚያዋርዱትን ያድናል። (መዝሙር 45:4 አዓት) ትሕትና የሚያሳዩ ሁሉ “እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ ይሖዋን ፈልጉ፤ ጽድቅንም ፈልጉ፤ ትሕትናንም ፈልጉ። ምናልባት በይሖዋ ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል” በሚሉት ቃላት መጽናናት ይችላሉ።​—ሶፎንያስ 2:3

ትሕትናና የአምላክ ድርጅት

ትሕትና የአምላክን ሕዝቦች ድርጅቱን እንዲያደንቁና ጽኑ አቋም ጠባቂዎች ሆነው እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል። (ከዮሐንስ 6:66-69 ጋር አወዳድር) ተስፋ ያደረግነውን የአገልግሎት መብት ሳናገኝ ከቀረን ትሕትና በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ካላቸው ጋር እንድንተባበር ይረዳናል። የትሕትና ትብብራችንም ጥሩ አርዓያ ይሆናል።

በሌላ በኩል ትሕትና በይሖዋ ሕዝብ መካከል ባለን የአገልግሎት መብት ከንቱ ኩራት እንዳናሳይ ይጠብቀናል። በአምላክ ድርጅት ውስጥ ለማከናወን መብት ላገኘንበት ሥራ ምስጋና ፈላጊዎች ከመሆን ያግደናል። ከዚህም በላይ ሽማግሌዎች ሆነን በማገልገል ላይ ካለን ትሕትና የአምላክን መንጋ በርኅራኄ እንድንይዝ ይረዳናል።​—ሥራ 20:28, 29፤ 1 ጴጥሮስ 3:8

ትሕትናና ተግሣጽ

ትሕትናን መልበስ ተግሣጽን እንድንቀበል ይረዳናል። ትሑታን የሆኑ ሰዎች የክህነትን ሥራ ያለአግባብ እስከመንጠቅ ድረስ ልቡ እንደታበየው የይሁዳ ንጉሥ እንደ ዖዝያን አይደሉም። ዖዝያን በመሠዊያው ላይ ዕጣን ለማጨስ ወደ ቤተ መቅደስ በመግባት በይሖዋ ፊት የሚታመን ሳይሆን ቀርቷል። ዖዝያን ካህናቱን ለምን ታርሙኛላችሁ ብሎ በንዴት በተናገራቸው ጊዜ በለምፅ በሽታ ተመታ። ትሕትና በማጣቱ የከፈለው ዋጋ እንዴት ከፍተኛ ነበር! (2 ዜና መዋዕል 26:16-21፤ ምሳሌ 16:18) እንደ ዖዝያን ፈጽሞ አትሁን፤ ይሖዋ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጥህን ተግሣጽ እንዳትቀበል ኩራት አይከልክልህ።

ይህን በሚመለከት ጳውሎስ ለዕብራውያን ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንዲህ በማለት ነገራቸው፦ “እንደ ልጆችም ከእናንተ ጋር ‘ልጄ ሆይ [የይሖዋን አዓት] ቅጣት አታቃልል፤ በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም፤ [ይሖዋ አዓት] የሚወደውን ይቀጣዋልና የሚቀበለውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል’ ብሎ የሚነጋገረውን ምክር ረስታችኋል። . . . ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም። ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል።” (ዕብራውያን 12:5-11) እንዲሁም “የተግሣጽም ዘለፋ የሕይወት መንገድ” መሆኑንም አስታውሱ።​—ምሳሌ 6:23

ትሕትናን እንደተላበሳችሁ ኑሩ

ክርስቲያኖች የትሕትናን ልብስ ሁልጊዜ መልበሳቸው እንዴት አስፈላጊ ነው! ‘ለዘላለም ሕይወት ያዘነበለ ልብ ያላቸውን’ ሰዎች ለመፈለግ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በመሆን በትሕትና ከቤት ወደ ቤት በመመስከር እንድንጸና ይገፋፋናል። (ሥራ 13:48፤ 20:20) በእርግጥ ምንም እንኳ ትዕቢተኛ ተቃዋሚዎች የጽድቅ መንገዳችንን ቢጠሉም ትሕትና አምላክን በማንኛውም ረገድ በመታዘዝ እንድንቀጥል ይረዳናል።​—መዝሙር 34:21

ትሕትና “በሙሉ ልባችን በይሖዋ እንድንታመን” ስለሚገፋፋን ይሖዋም መንገዳችንን ያቀናልናል። (ምሳሌ 3:5, 6) እንዲያውም ይህን ጥሩ ባሕርይ ከተላበስን ብቻ ነው በእውነት ከአምላክ ጋር እየተመላለስን ሊሆን የሚችለውና የሱን ሞገስና በረከትም ልናገኝ የምንችለው። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንደጻፈው “[በይሖዋ አዓት] ፊት ራሳችሁን አዋርዱ። ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል።” (ያዕቆብ 4:10) ስለዚህ በይሖዋ መልክ የተዘጋጀውን ያንን ውብ ልብስ ትሕትናን እንልበስ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ