“ሁሉንም ዓይነት ጥሩነት” ማፍራት
“የብርሃንም ፍሬ ሁሉንም ዓይነት ጥሩነት ያካትታል።”—ኤፌሶን 5:9 አዓት
1, 2. ከጥንት ጊዜያት ጀምሮ ምን የተለያዩ ሁለት ቡድኖች ነበሩ? ዛሬስ ባለው ሁኔታ ምን ልዩነት ይታያል?
ከስድስት ሺህ ዓመታት በፊት በኤደን ከተሠራው አመጽ በኋላና እንደገናም በኖኅ ዘመን ከነበረው የጥፋት ውሃ በኋላ የሰው ዘር በአንድ በኩል ይሖዋን የሚያገለግሉ በሌላ በኩል ደግሞ ሰይጣንን የሚከተሉ ሰዎች ባሉባቸው ሁለት ቡድኖች ወይም ድርጅቶች ተከፍሎ ነበር። እነዚህ ድርጅቶች አሁንም ይኖራሉን? በእርግጥም አሉ። ነቢዩ ኢሳይያስ እነዚህን ሁለት ቡድኖች ጠቅሶ በጊዜያችን የሚኖራቸውን ሁኔታ ተንብዮአል፦ “እነሆ ጨለማ ምድርን፣ ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ [ይሖዋ (አዓት)] ይወጣል ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል።”—ኢሳይያስ 60:1, 2
2 አዎን በእነዚህ ሁለት ድርጅቶች መካከል ያለው ልዩነት የጨለማንና የብርሃንን ያህል ታላቅ ነው። በጨለማ ውስጥ የጠፋን አንድን ሰው ትንሽ የብርሃን ፍንጣቂ እንደሚስበው ሁሉ በዚህ በጨለማ ዓለም ውስጥ ከይሖዋ የፈነጠቀው ብርሃን በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ወደ አምላክ ድርጅት ስቦአቸዋል። ኢሳይያስ ቀጥሎ እንደተናገረው፦ “አሕዛብም [ሌሎች በጎች] ወደ ብርሃንሽ ነገሥታትም [ቅቡዓን የመንግሥት ወራሾች] ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ።”—ኢሳይያስ 60:3
3. ክርስቲያኖች የይሖዋን ክብር የሚያሳዩት በምን መንገዶች ነው?
3 የይሖዋ ሕዝቦች የይሖዋን ክብር የሚያሳዩት እንዴት ነው? በአንደኛ ደረጃ ስለተቋቋመችው የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ምሥራች ይሰብካሉ። (ማርቆስ 13:10) ይሁን እንጂ ከዚህም በላይ የጥሩነት ዋነኛ ምሳሌ የሆነውን ይሖዋን ይመስላሉ። በዚህም ጠባያቸው ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ወደ ብርሃን ይስባሉ። (ኤፌሶን 5:1) ጳውሎስ እንዲህ አለ፦ “ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፤ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፤ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ።” ቀጥሎም ‘የብርሃኑም ፍሬ በሁሉም ዓይነት በጎነትና (ጥሩነትና) በጽድቅ በእውነትም የሚገኝ ነውና። ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ . . . ፍሬም ከሌለው የጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ።’ (ኤፌሶን 5:8-11) ጳውሎስ “ሁሉም ዓይነት ጥሩነት” ሲል ምን ማለቱ ነው?
4. ጥሩነት ምንድን ነው? በአንድ ክርስቲያንስ ላይ የሚታየው እንዴት ነው?
4 ያለፈው ርዕሰ ትምህርታችን እንዳሳየን ጥሩነት የላቀ የስነ ምግባር ደረጃ፣ ከፍተኛ የሆነ ባሕርይ ነው። በጥሩነት ረገድ ፍጹም የሆነው ይሖዋ ብቻ እንደሆነ ኢየሱስ ተናግሯል። (ማርቆስ 10:18 አዓት) ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን የመንፈስ ፍሬ የሆነውን ጥሩነትን በመኮትኮት ይሖዋን ሊመስለው ይችላል። (ገላትያ 5:22 አዓት) “ጥሩ” ተብሎ ስለተተረጎመው አጋቶስ ስለተባለው የግሪክኛ ቃል ማብራሪያ ሲሰጥ የቫይን የብሉይና የአዲስ ኪዳን ቃላት ገላጭ መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላል፦ “በባሕርዩ ወይም በሥነ ፍጥረቱ ጥሩ፣ በውጤቱም ጠቃሚ የሆነን ነገር ያመለክታል። ” የጥሩነትን ባሕርይ የሚኮተኩት ክርስቲያን ጥሩ ይሆናል ጥሩም ያደርጋል። (ከዘዳግም 12:28 ጋር አወዳድር።) በተጨማሪም የጥሩነት ተቃራኒ የሆኑትን ነገሮች ማለትም ‘ፍሬ ከሌላቸው የጨለማ ሥራዎች’ ይርቃል። አንድ ክርስቲያን በጠባዩ ጥሩነትን ሊያሳይ የሚችልባቸው የተለያዩ መንገዶች ጳውሎስ የጠቀሳቸው ‘የጥሩነት ዓይነቶች’ ናቸው። ከእነዚህ አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
“ጥሩ ማድረጋችሁን ቀጥሉ”
5. አንዱ የጥሩነት ባሕርይ ዓይነት ምንድን ነው? አንድ ክርስቲያን ኮትኩቶ ሊያሳድገው የሚገባውስ ለምንድን ነው?
5 ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤው ላይ ‘ከጥሩነት ዓይነቶች’ መካከል አንዱን ገልጿል። “ለበላይ ባለ ሥልጣኖች” ስለመገዛት ሲናገር እንዲህ አለ፦ “ባለሥልጣንን እንዳትፈራ ትወዳለህን? መልካሙን (ጥሩውን) አድርግ ከእርሱም ምስጋና ይሆንልሃል።” እዚህ ላይ ጳውሎስ ‘ጥሩ’ ብሎ የጠቀሰው ዓለማዊ ባለሥልጣኖች ላወጧቸው ሕጎችና ሥርዓቶች ታዛዥ መሆንን ነው። አንድ ክርስቲያን ለእነዚህ ሕጎች ታዛዥ መሆን የሚገባው ለምንድን ነው? ከባለሥልጣኖች ጋር አስፈላጊ ባልሆነ መንገድ ከመጋጨት ለመሸሽና ከቅጣት ለመዳን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአምላክ ፊት ንፁህ ሕሊና ይዞ ለመኖር ሲል ነው። (ሮሜ 13:1-7) አንድ ክርስቲያን በአንደኛ ደረጃ የሚታዘዘው ይሖዋን ቢሆንም ይሖዋ አምላክ እንዲኖሩ በፈቀደላቸው ባለሥልጣኖች ላይ ባለማመጽ ‘ንጉሥን ያከብራል።’ (1 ጴጥሮስ 2:13-17) በዚህም መንገድ ክርስቲያኖች ጥሩ ጎረቤቶች፣ ጥሩ ዜጎችና ጥሩ ምሳሌዎች ይሆናሉ።
ለሌሎች አሳቢ መሆን
6. (ሀ) ሌላው የጥሩነት ገጽታ ምንድን ነው? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሳቢነታችንን ልናሳያቸው የሚገቡ እነማን ተጠቅሰዋል
6 የይሖዋ ጥሩነት ለሁሉም የምድር ነዋሪዎች “ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት” በመስጠቱ ተገልጾአል። ይህም ‘የተሟላ ምግብና ጥሩ ደስታ’ እንዲገኝ አስችሏል። በእውነት አሳቢ አምላክ መሆኑንም አሳይቷል። (ሥራ 14:17) በዚህ ረገድ እኛም በትንንሽም ሆነ በትልልቅ መንገዶች ለሌሎች አሳቢነትን በማሳየት አምላክን ልንመስለው እንችላለን። በተለይ ለእነማን አሳቢነት ልናሳይ እንችላለን? ጳውሎስ “በመካከላችሁ የሚደክሙትን በጌታም የሚገዙአችሁን የሚገሥጹአችሁንም” በማለት በተለይ ለሽማግሌዎች አሳቢነት ማሳየት እንደሚገባን አመልክቷል። (1 ተሰሎንቄ 5:12, 13) ይህን ለማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ከሽማግሌዎች ጋር ሙሉ በሙሉ በመስማማት፣ ለምሳሌ ያህል በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ በሚሠራው አስፈላጊ ሥራ ተካፋይ በመሆን ነው። አስፈላጊ በሚሆንበት በማንኛውም ጊዜ እርዳታ ለማግኘት ወደ ሽማግሌዎች ለመቅረብ ነፃ እንደሆንን ቢሰማንም ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ሁሉ ነገር እንዲደረግልን የምንጠይቅ መሆን አይገባንም። ከዚህ ይልቅ በምንችለው መንገድ ሁሉ የእነዚህን ትጉህ እረኞች ሸክም ለማቅለል እንሞክራለን። ብዙዎቹ ሽማግሌዎች ከጉባኤ ኃላፊነቶች በተጨማሪ የቤተሰብ ኃላፊነቶችም አሉባቸው።
7. ለአረጋውያን አሳቢነታችንን በምን መንገዶች ልናሳይ እንችላለን?
7 በአካል ለሸመገሉትም ቢሆን አሳቢነታችንን ልናሳይ ይገባናል። በሙሴ ሕግ ውስጥ በተለይ ይህን በተመለከተ የተሰጠው አንዱ ትዕዛዝ “በሽበታሙ ፊት ተነሣ፣ ሽማግሌውንም አክብር፣ አምላክንም ፍራ፤ እኔ [ይሖዋ (አዓት)] ነኝ” ይላል። (ዘሌዋውያን 19:32) ይህ አሳቢነት ሊገለጥ የሚችለው እንዴት ነው? ወጣቶች ገበያ ለመገብየት ወይም በቤት ውስጥ ሥራዎች ለመርዳት ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ሽማግሌዎቹም በአሳቢነት በመነሳሳት ማንኛውም አረጋዊ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት እርዳታ ያስፈልገው እንደሆነ ይከታተላሉ። በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ብርቱ የሆኑ ወጣት ግለሰቦች በዝግታ የሚጓዙትን አረጋውያን በችኩልነት ጎሽመዋቸው ወይም ገፍትረዋቸው ለማለፍ ከመሞከር ይጠበቃሉ። አንድ አረጋዊ ለመቀመጥ ወይም ምግብ ለማግኘት ትንሽ ቢዘገይ ይታገሣሉ።
8. በመጽሐፍ ቅዱስ ተለይቶ ለተጠቀሰ ለሌላ ቡድን አሳቢነታችንን እንዴት ልናሳይ እንችላለን?
8 መዝሙራዊው አሳቢነት ልናሳየው ስለሚገባ አንድ ሌላ የሰዎች ክፍል እንደሚከተለው ሲል ገልጿል፦ “ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው።” (መዝሙር 41:1) ታዋቂ ለሆኑና ለሃብታም ሰዎች አሳቢነት ማሳየት ቀላል ሊሆን ይችላል። ችግረኛና ድሃ ለሆኑትስ? የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ እንደነዚህ ላሉት ሰዎች እኩል የሆነ አሳቢነት ማሳየታችን የጽድቃችንና የክርስቲያን ፍቅራችን መፈተኛ እንደሆነ አመልክቷል። ሁኔታቸው ምንም ይሁን ምን ለሰው ሁሉ አሳቢ መሆናችንን በማሳየት ይህን ፈተና የምናልፍ እንሁን።—ፊልጵስዩስ 2:3, 4፤ ያዕቆብ 2:2-4, 8, 9
“መሐሪዎች ሁኑ”
9, 10. ክርስቲያኖች መሐሪ መሆን የሚገባቸው ለምንድን ነው? የዚህ ዓይነቱ የጥሩነት ባሕርይ ሊታይ የሚችለውስ እንዴት ነው?
9 ሌላው ዓይነት የጥሩነት ባሕርይ ኢየሱስ በተናገራቸው አንዳንድ ምሳሌዎች ውስጥ ተገልጾአል። ከእነዚህ ምሳሌዎች ውስጥ በአንዱ ላይ ኢየሱስ አንድ ተዘርፎና ክፉኛ ተደብድቦ በመንገድ ላይ የተጣለን ሰው በአጋጣሚ ስላገኘ ሳምራዊ ተናግሮአል። ሌዋዊውና ካህኑ የተጎዳውን ሰው ለመርዳት ፈቃደኛ ሳይሆኑ አይተውት አልፈው ሄዱ። ሆኖም ሳምራዊው ቆም ብሎ ከአንድ ሣምራዊ ሊጠበቅ የማይችል እርዳታ አደረገለት። ይህ ታሪክ ብዙ ጊዜ የጥሩው ሳምራዊ ምሳሌ ተብሎ ይጠራል። ሳምራዊው ያሳየው ምን ዓይነት የጥሩነት ባሕርይ ነበር? ምሕረት አሳይቶአል። ኢየሱስ ያዳምጠው የነበረውን ሰው ለተጎዳው ሰው ወዳጅ የሆነው ማን እንደሆነ እንዲነግረው ሲጠይቀው የተሰጠው ትክክለኛ መልስ “ምሕረት ያደረገለት” የሚል ነበር።—ሉቃስ 10:37
10 መሐሪ የሆኑ ክርስቲያኖች ሙሴ ለእስራኤላውያን “አምላክህ [ይሖዋ (አዓት)] መሐሪ አምላክ ነውና አይተውህም፣ አያጠፋህምም፣ ለአባቶችህም የማለላቸውን ቃል ኪዳኑን አይረሳም” ሲል የተናገረለትን ይሖዋን ይመስላሉ። (ዘዳግም 4:31) ኢየሱስ “አባታችሁ መሐሪ እንደሆነ ሁሉ መሐሪዎች ሁኑ” በማለት የአምላክ መሐሪነት እንዴት ሊነካን እንደሚገባ አሳይቷል። (ሉቃስ 6:36 አዓት) ምሕረትን ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው? የኢየሱስ ምሳሌ እንዳሳየን አንዱ መንገድ አደጋ ወይም ችግር ሊያስከትልብን የሚችል ቢሆንም እንኳ ጎረቤታችንን ለመርዳት ዝግጁ በመሆን ነው። አንድ ጥሩ ሰው አንድ ነገር ለማድረግ በሚችልበት ደረጃ ላይ ከሆነ ወንድሙ ሲሰቃይ እያየ ዝም አይልም።—ያዕቆብ 2:15, 16
11, 12. ኢየሱስ ስለ ባሪያዎቹ በተናገረው ምሳሌ መሠረት መሐሪ መሆን ምንን ይጨምራል? ይህንንስ ዛሬ እንዴት ልናሳይ እንችላለን?
11 ሌላው የኢየሱስ ምሳሌ ደግሞ በምህረት ላይ የተመሠረተ ጥሩነት ሌሎችን ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆንን እንደሚጨምር ያመለክታል። ከጌታው አሥር ሺህ መክሊት ስለተበደረ ባሪያ ተናገረ። ባሪያው ለመክፈል ስላልቻለ ጌታው ምሕረት እንዲያደርግለት ለመነው። ጌታውም በደግነት 60,000,000 ዲናር የሚያክለውን ከፍተኛ ዕዳ ማረው። ሆኖም ባሪያው ከዚያ ሄዶ ከእርሱ አንድ መቶ ዲናር ብቻ የተበደረ ሌላ ባሪያ አገኘ። ዕዳው የተማረለት ባሪያ ምሕረት በጎደለው መንገድ ይህን ተበዳሪ ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ በወህኒ እንዲጣል አደረገው። እዚህ ላይ በግልጽ እንደሚታየው ምሕረት ያላደረገው ባሪያ ጥሩ ሰው አልነበረም። በዚህም ምክንያት ጌታው የተፈጸመውን ነገር ሲሰማ ዕዳውን እንዲከፍል አስገደደው።—ማቴዎስ 18:23-35
12 እኛም ከዚህ ይቅርታ ከተደረገለት ባሪያ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን። ይሖዋ የእኛን ከባድ የሆነ የኃጢአት ዕዳ በኢየሱስ መስዋዕት አማካኝነት ይቅር ብሎልናል። እንግዲያው ሌሎችን ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆን ይኖርብናል። ኢየሱስ ያለ ምንም ገደብ “እስከ ሰባ ሰባት ጊዜ” ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆን እንዳለብን ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:7፤ 6:12, 14, 15፤ 18:21, 22) እንደዚህ ከሆነ አንድ መሐሪ የሆነ ክርስቲያን ቂም አይዝም። ቅሬታ በአእምሮው አይይዝም ወይም ተቀይሞ ክርስቲያን ጓደኞቹን ለማነጋገር እምቢ አይልም። እንደዚህ ያለው የምሕረት ጉድለት የክርስቲያን ጥሩነት ባሕርይ ምልክት አይደለም።
ለጋስና እንግዳ ተቀባይ
13. የጥሩነት ባሕርይ ምን ሌላ ነገር ይጨምራል?
13 የጥሩነት ባሕርይ በለጋስነትና በእንግዳ ተቀባይነትም ይገለጻል። በአንድ አጋጣሚ ጊዜ አንድ ወጣት ሰው ከኢየሱስ ምክር ለመጠየቅ መጣ። እርሱም “መምህር ሆይ፣ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም (ጥሩ) ነገር ላድርግ?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም የአምላክን ትዕዛዛት በቅደም ተከተል መጠበቅ እንዳለበት ነገረው። አዎን፣ የይሖዋን ትዕዛዛት ማክበር አንዱ የጥሩነት ባሕርይ ገጽታ ነው። ወጣቱ ሰው በሚችለው ሁሉ ይህን እያደረገ እንዳለ ተሰምቶት ነበር። እርግጥ በጎረቤቶቹም ጥሩ ሰው እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ሆኖም አንድ ነገር እንደጎደለው ሆኖ ተሰማው። ስለዚህ ኢየሱስ “ፍጹም ልትሆን ብትወድ፣ ሂድና ያለህን ሽጠህ ለድሆች ስጥ፣ መዝገብንም በሰማያት ታገኛለህ፣ መጥተህም ተከተለኝ አለው።” (ማቴዎስ 19:16-22) ወጣቱ ሰው እያዘነ ሄደ። በጣም ሃብታም ነበር። የኢየሱስን ምክር ተከትሎ ቢሆን ኖሮ የሐብት አሳዳጅ አለመሆኑን ለማሳየት ይችል ነበር። ስስት የሌለበትን የእውነተኛ ለጋስነት ጥሩ ሥራ ሊፈጽም ይችል ነበር።
14. ይሖዋና ኢየሱስ ልግስናን በተመለከተ ምን ጥሩ ምክር ሰጥተዋል?
14 ይሖዋ እስራኤላውያንን ለጋሶች እንዲሆኑ አሳስቧቸው ነበር። ለምሳሌ እንዲህ እናነባለን፦ “እጅህን በምትጥልበት ሁሉ አምላክህ [ይሖዋ (አዓት)] ስለዚህ በሥራህ ሁሉ ይባርክሃልና [በችግር ለተጠቃው ወንድምህ] ስጠው፣ በሰጠኸውም ጊዜ በልብህ አትፀፀት።” (ዘዳግም 15:10፤ ምሳሌ 11:25) ኢየሱስ ክርስቶስም ሰዎች ለጋሶች እንዲሆኑ መክሮአል። “ስጡ ይሰጣችሁማል፤ የተጨቆነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል።” (ሉቃስ 6:38) ከዚህም በላይ ኢየሱስ ራሱ በጣም ለጋስ ነበር። በአንድ አጋጣሚ ጊዜ ለትንሽ ጊዜ እረፍት ለማድረግ አስቦ ነበር። ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ያለበትን ቦታ ፈልገው ወደ እርሱ መጡ። ኢየሱስም ለማረፍ የነበረውን ፍላጎት ትቶ በለጋስነት መንፈስ ሕዝቡን ማገልገል ጀመረ። በኋላም ይህን ለሚያክል እጅግ ብዙ ሕዝብ ምግብ በማቅረብ ከፍተኛ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳይቷል።—ማርቆስ 6:30-44
15. ልግስናን በማሳየት በኩል የኢየሱስ ደቀመዛሙርት እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ ምሳሌ የተዉት እንዴት ነው?
15 ብዙዎቹ የኢየሱስ ደቀመዛሙርት ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰጡት ምክር ታማኝ በመሆን ለጋሶችና እንግዳ ተቀባዮች ሆነዋል። የክርስቲያን ጉባኤ ሥራውን በጀመረባቸው በመጀመሪያዎቹ ቀናት በ33 እዘአ የተከበረውን የጴንጠቆስጤ በዓል ለማክበር የመጡ ብዛት ያላቸው ሰዎች የሐዋርያትን ስብከት ሰምተው አማኞች ሆነዋል። ከበዓሉ በኋላ የበለጠ ለመማር በመፈለግ እዚያው በመቆየታቸው የያዙትን ስንቅ ጨረሱ። ስለዚህ የአገሩ ተወላጆች የነበሩት አማኞች እነዚህ ከውጭ አገሮች የመጡ ሰዎች በይበልጥ እንዲጠነክሩ ለማስቻል ሲሉ ያላቸውን ንብረት ሸጠው ለእነዚህ አዳዲስ ወንድሞቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ለማቅረብ የገንዘብ መዋጮ አደረጉ። እንዴት ያለ ቸርነት ነው!—ሥራ 4:32-35፤ በተጨማሪም ሥራ 16:15፤ ሮሜ 15:26 ተመልከት
16. ዛሬ እና እንግዳ ተቀባይና ለጋስ ልንሆን የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች ጥቀስ።
16 ዛሬም ክርስቲያኖች በአካባቢያቸው ለሚገኙት ጉባኤዎችና ለዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ስለሚሰጡ ተመሳሳይ የሆነ የክርስቶስን መሰል ልግሳ ይታያል። በተጨማሪም በተፈጥሮ አደጋ ወይም በጦርነት የሚሰቃዩ ወንድሞቻቸውን በሚረዱበት ጊዜ በግልጽ ታይቶአል። የክልል የበላይ ተመልካቹ ጉባኤዎችን በሚጎበኝበት ጊዜ በሚደረግለት እንክብካቤም ይገለጻል። አባት የሌላቸው ልጆች ከሌሎች ክርስቲያን ቤተሰቦች ጋር አብረው እንዲዝናኑና በቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እንዲካፈሉ በልግስና ሲጋበዙም የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየት ነው። የክርስቲያን የጥሩነት ባሕርይ ከሚገለጥባቸው መንገዶች አንዱ ነው።—መዝሙር 68:5
እውነትን መናገር
17. ዛሬ እውነተኛ መሆን ፈታኝ ሁኔታ የሆነው ለምንድን ነው?
17 ጳውሎስ የብርሃንን ፍሬ ሲያብራራ ጥሩነትን ከጽድቅና ከእውነት ጋር አዛምዶአል። ስለዚህ እውነተኛነት ሌላው የጥሩነት ባሕርይ መግለጫ ነው ቢባል ትክክል ነው። ጥሩ ሰዎች ውሸት አይናገሩም። ይሁን እንጂ ውሸት በጣም በተስፋፋበት በአሁኑ ጊዜ እውነት መናገሩ ከባድ ፈተና ሆኖአል። ብዙ ሰዎች ግብር ለመክፈል የገቢ መግለጫ ፎርሞችን ሲሞሉ ይዋሻሉ። ተቀጥረው የሚሠሩ ሰዎች ስለሚሠሩት ሥራ ውሸት ይናገራሉ። ተማሪዎች በትምህርታቸውና በፈተናቸው በመዋሸት ያታልላሉ። ነጋዴዎችም በሚዋዋሉበት ጊዜ ይዋሻሉ። ልጆችም ከቅጣት ለማምለጥ ይዋሻሉ። በጥላቻ ስሜት የተነሳሱ ሐሜተኞች በውሸት የሌሎችን ስም ያጠፋሉ።
18. ይሖዋ ውሸታሞችን እንዴት ይመለከታቸዋል?
18 ውሸት በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ነው። ይሖዋ ከሚጠላቸው ‘ሰባት ነገሮች’ ውስጥ “ሐሰተኛ ምላስ” እና “በሐሰት የሚመሰክር ሐሰተኛ ምስክር” ይገኙበታል። (ምሳሌ 6:16-19)‘ሐሰተኞች በሙሉ’ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ቦታ ከማይኖራቸው ከሚፈሩ፣ ከነፍሰ ገዳዮችና ከአመንዝሮች ዝርዝር ውስጥ ገብተዋል። (ራእይ 21:8) ከዚህም በተጨማሪ አንድ ምሳሌ እንዲህ በማለት ይነግረናል፦ “በቅን የሚሄድ ሰው [ይሖዋን (አዓት)] ይፈራል፤ መንገዱን የሚያጣምም ግን ይንቀዋል።” (ምሳሌ 14:2) ውሸታም ሰው በመንገዱ ሁሉ ጠማማ ነው። በዚህም ምክንያት ውሸታም ሰው ይሖዋን እንደሚንቅ ያሳያል። እንዴት ያለ መጥፎ አስተሳሰብ ነው! ተግሣጽን የሚያስከትል ወይም የገንዘብ ኪሳራ የሚያመጣብን ቢሆንም እንኳ ምንጊዜም እውነትን እንናገር። (ምሳሌ 16:6፤ ኤፌሶን 4:25) እውነትን የሚናገሩ ሰዎች “የእውነት አምላክ የሆነውን ይሖዋን ይመስሉታል።”—መዝሙር 31:5
የጥሩነትን ባሕርይ ኮትኩቱ
19. አንዳንድ ጊዜ በዓለም ውስጥ የሚታይ ምን ሁኔታ ነው ፈጣሪን የሚያስመሰግነው?
19 እነዚህ አንድ ክርስቲያን ሊኮተኩታቸው ከሚገቡት ‘የጥሩነት’ ዓይነቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። በዓለም ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የጥሩነትን ባሕርይ በመጠኑ ማሳየታቸው እውነት ነው። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶች እንግዳ ተቀባይ ናቸው፣ ሌሎችም ምሕረት የሚያሳዩ ናቸው። በእርግጥም ስለ ጥሩው ሳምራዊ የተነገረውን ምሳሌ አስደናቂ የሚያደርገው ነገር ኢየሱስ እንደተናገረው በአይሁድ ጉባኤ ውስጥ የሚገኙት ሽማግሌዎች ያላሳዩትን ምሕረት ይህ አይሁዳዊ ያልሆነ ሰው ማሳየቱ ነው። ከስድስት ሺህ የአለፍጽምና ዓመታት በኋላም እንኳ ቢሆን እንደነዚህ ዓይነቶቹ ጠባዮች አሁንም የሚታዩ መሆናቸው በእርግጥም የሰውን ፈጣሪ የሚያስመሰግነው ነው።
20, 21. (ሀ) የክርስቲያን የጥሩነት ባሕርይ በዓለም ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ላይ ከምናየው ከማንኛውም ዓይነት ጥሩነት የሚለየው ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ክርስቲያን የጥሩነትን ባሕርይ ሊኮተኩት የሚችለው እንዴት ነው? ይህን ለማድረግ መትጋት የሚያስፈልገንስ ለምንድን ነው?
20 ይሁን እንጂ ለክርስቲያኖች ጥሩነት ቢኖራቸውም ባይኖራቸውም ትልቅ ለውጥ የማያመጣ ተራ ባሕርይ አይደለም። ክርስቲያኖች አምላክን መምሰል ስለሚኖርባቸው ጥሩነት በሁሉም ገጽታዎቹ ሊኮተኩቱት የሚገባ ጠባይ ነው። ይሁን እንጂ ይህን ለማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩነትን ለመማር እንደምንችል ይነግረናል። መዝሙራዊው “ጥሩነትን አስተምረኝ፤ በትዕዛዝህ ታምኛለሁና” ብሎ ጸልዮአል። ጨምሮም “አንተ ጥሩ ነህ ጥሩም ታደርጋለህ። ሕጎችህን አስተምረኝ” አለ።—መዝሙር 119:66, 68
21 አዎን፣ የይሖዋን ትዕዛዛት ከተማርንና ከታዘዝን የጥሩነትን ባሕርይ እንኮተኩታለን። ምንጊዜም ጥሩነት የመንፈስ ፍሬ መሆኑን አትርሳ። በጸሎት፣ በስብሰባና በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የይሖዋን መንፈስ የምንፈልግ ከሆነ ይህንን ባሕርይ ኮትኩቶ ለማሳደግ በእርግጥም እርዳታ እናገኛለን። ከዚህም በላይ ጥሩነት ኃይል አለው። ክፉውንም ለማሸነፍ ይችላል። (ሮሜ 12:21) እንግዲያው ለሁሉም በተለይም ለክርስቲያን ወንድሞቻችን ጥሩ ማድረጋችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! (ገላትያ 6:10) ይህን ካደረግን ‘ጥሩ የሆነውን ለሚያደርግ ለማንኛውም ሰው’ ቃል የተገባለትን “ምስጋናና ክብር ሰላምም” ከሚያገኙት መካከል እንሆናለን።—ሮሜ 2:6-11
ልትመልሳቸው ትችላለህ?
◻ ከበላይ ባለ ሥልጣኖች ጋር በተያያዘ ጥሩ ማድረጋችንን ልንቀጥል የምንችለው እንዴት ነው?
◻ አሳቢነታችንን ልናሳያቸው ከሚገቡ ሰዎች ሌሎቹ እነማን ናቸው?
◻ ምሕረት ሊገለጥ የሚችለው በምን መንገዶች ነው?
◻ በዛሬው ጊዜ ያሉትን ክርስቲያኖች ለይተው የሚያሳውቋቸው ምን የልግስናና የእንግዳ ተቀባይነት ድርጊቶች ናቸው?
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለሌሎች አሳቢነትን ማሳየት አንዱ የጥሩነት ባሕርይ ገጽታ ነው
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ታላቅ አስተማሪ እንደመሆኑ ራሱን በልግስና ሰጥቷል