የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 5/15 ገጽ 15-20
  • የአምላክን ቃል አንብቡ በእውነትም አገልግሉት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአምላክን ቃል አንብቡ በእውነትም አገልግሉት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ዘላቂ ጥቅሞች
  • ለሁሉም የግድ አስፈላጊ ነው
  • የአምላክን ቃል ድምፃችሁን እያሰማችሁ አንብቡ
  • በአንድ ርዕስ ላይ በማተኮር የሚደረግ ጥናት
  • ዘወትር በእውነት ተመላለሱ
  • በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ መጠቀም
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ለማንበብ ትጋ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • የነገሥታትን ምሳሌ ተከተል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • የመጽሐፍ ቅዱስን ምንነት እንዳለ አምኖ መቀበል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 5/15 ገጽ 15-20

የአምላክን ቃል አንብቡ በእውነትም አገልግሉት

“አቤቱ ይሖዋ ሆይ፣ መንገድህን አስተምረኝ። በእውነትህም እመላለሳለሁ።”—መዝሙር 86:11 አዓት

1. የዚህ መጽሔት የመጀመሪያ እትም እውነትን በተመለከተ የሰጠው ሐሳብ ምን ነበር?

ይሖዋ ብርሃንና እውነትን ይልካል። (መዝሙር 43:3) ከዚህም በተጨማሪ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብና እውነትን የመማር ችሎታ ሰጥቶናል። በሐምሌ 1879 የወጣው የዚህ መጽሔት የመጀመሪያ እትም እንደሚከተለው ብሎ ነበር፦ “እውነት በጣም ተንሰራፍቶ በሚገኝ የሐሰት አረም መካከል ልትዋጥ ምንም ያህል እንዳልቀራት በሕይወት ደን ውስጥ እንደምትገኝ ትንሽ አበባ ናት። ካገኘሃት በንቃት ልትከታተላት ይገባሃል። ውብ መሆኗን ከተገነዘብክ የሐሰትን አረምና የግትርነትን እሾህ ጠራርገህ ማጽዳት ይኖርብሃል። ንብረትህ ልታደርጋት ከፈለግህ ራስህን ዝቅ ማድረግ አለብህ። አንድ የእውነት አበባ ስላገኘህ ብቻ አትርካ። አንድ ብቻ ቢበቃ ኖሮ ሌላ ባልኖረም ነበር። መሰብሰብህን አታቋርጥ፣ ፍለጋህን ቀጥል።” የአምላክን ቃል ማንበብና ማጥናት ትክክለኛ እውቀት ለመቅሰምና በእውነት ለመመላለስ ያስችለናል።—መዝሙር 86:11 አዓት

2. ዕዝራና ሌሎች ሰዎች በጥንቷ ኢየሩሳሌም ውስጥ ለነበሩት አይሁዶች የአምላክን ሕግ ባነበቡላቸው ጊዜ ምን ውጤት ተገኘ?

2 የኢየሩሳሌም ቅጥሮች በ455 ከዘአበ እንደገና ከተገነቡ በኋላ ካህኑ ዕዝራና ሌሎች ሰዎች የአምላክን ሕግ ለአይሁዳውያን አነበቡላቸው። ከዚያም አስደሳች የዳስ በዓል ካከበሩና ኃጢአታቸውንም ከተናዘዙ በኋላ “የታመነውን ቃል ኪዳን” በማድረግ ደመደሙ። (ነህምያ 8:1—9:38) እንዲህ የሚል እናነባለን፦ “የእውነተኛውን አምላክ የሕግ መጽሐፍ ጮክ ብለው ማንበባቸውን ቀጠሉ፣ ያብራሩላቸውና መልእክቱንም ያስረዷቸው ነበር፤ ሕዝቡም የሚነበበውን ያስተውሉ ነበር።” (ነህምያ 8:8 አዓት) አንዳንድ ምሁራን አይሁዳውያኑ የዕብራይስጥን ቋንቋ በደንብ መረዳት ይቸግራቸው ስለነበር በአረማይክ ቋንቋ ይብራራላቸው ነበር የሚል አስተያየት ይሰጣሉ። ይሁን እንጂ ጥቅሱ እንዲሁ ቋንቋውን የሚመለከት ማብራሪያ መስጠትን አያመለከትም። ዕዝራም ሆነ ሌሎቹ ሰዎች ሕጉን ያብራሩ የነበረው ሕዝቡ መሠረታዊ ሥርዓቶቹን እንዲያስተውሉና ተግባራዊ ማድረግ እንዲችሉ ነበር። ክርስቲያናዊ ጽሑፎችና ስብሰባዎች የአምላክ ቃል ‘የያዘውን መልእክት እንድናስተውል’ ይረዱናል። ‘የማስተማር ብቃት ያላቸው’ የተሾሙ ሽማግሌዎችም በዚህ ረገድ ጥሩ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።—1 ጢሞቴዎስ 3:1, 2፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:24

ዘላቂ ጥቅሞች

3. መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ የሚገኙ አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

3 ክርስቲያን ቤተሰቦች መጽሐፍ ቅዱስን አንድ ላይ ሆነው ሲያነቡ ዘላቂ ጥቅሞችን እንደሚያገኙ እሙን ነው። ከአምላክ ሕግጋት ጋር ከመተዋወቃቸውም በተጨማሪ ስለ መሠረተ ትምህርቶች፣ ትንቢቶችና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች እውነቱን ይማራሉ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከተነበበ በኋላ የቤተሰቡ ራስ እንደሚከተለው በማለት ሊጠይቅ ይችላል፦ ይህ ትምህርት ምን እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል? ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር እንዴት ይዛመዳል? እነዚህን ነጥቦች ምሥራቹን ለመስበክ እንዴት ልንጠቀምባቸው እንችላለን? አንድ ቤተሰብ መጽሐፍ ቅዱስ በሚያነብበት ጊዜ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ ወይም የማኅበሩ ጽሑፎች ላይ በሚገኙ ሌሎች ማውጫዎች በመጠቀም ምርምር የሚያደርግ ከሆነ የበለጠ ጥልቅ ማስተዋል ያገኛል። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (በእንግሊዝኛ የሚገኝ) የተባለውን መጽሐፍ ሁለት ጥራዞች መመልከትም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

4. በኢያሱ 1:8 ላይ የሚገኘውን ምክር ኢያሱ በምን መንገድ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበት ነበር?

4 ከቅዱሳን ጽሑፎች የምናገኛቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታችን ውስጥ መመሪያ ሆነው ሊያገለግሉን ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ ‘ቅዱሳን ጽሑፎችን’ ማንበብና ማጥናት ‘መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ይሰጡናል።’ (2 ጢሞቴዎስ 3:15) የአምላክ ቃል እንዲመራን ካደረግን በአምላክ እውነት መመላለሳችንን ከመቀጠላችንም በላይ የጽድቅ ፍላጎቶቻችን ይሟሉልናል። (መዝሙር 26:3፤ 119:130 አዓት) ይሁን እንጂ በሙሴ እግር የተተካው ኢያሱ እንዳደረገው ማስተዋል ለማግኘት መጣጣር ይኖርብናል። ኢያሱ ‘የሕጉ መጽሐፍ’ ከአፉ መለየት አልነበረበትም፤ በቀንና በሌሊትም ሊያነበው ይገባ ነበር። (ኢያሱ 1:8) ‘የሕጉ መጽሐፍ’ ከአፉ መለየት አልነበረበትም ማለት ኢያሱ በሕጉ ውስጥ የሚገኙትን እውቀት ሰጪ ነገሮች ለሌሎች ከመናገር መቦዘን አልነበረበትም ማለት ነው። ሕጉን በቀንና በሌሊት ማንበብ ነበረበት ማለት ደግሞ በሕጉ ላይ ማሰላሰልና ሕጉን ማጥናት ነበረበት ማለት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስም በተመሳሳይ ጢሞቴዎስ ስለ አኗኗሩ፣ አገልግሎቱና ትምህርቱ ‘እንዲያስብ’ ማለትም እንዲያሰላስል አጥብቆ መክሮታል። ጢሞቴዎስ ክርስቲያን ሽማግሌ እንደመሆኑ መጠን በኑሮው ምሳሌ በመሆንና የቅዱሳን ጽሑፎችን እውነት በማስተማር ረገድ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈልጎት ነበር።—1 ጢሞቴዎስ 4:15

5. የአምላክን እውነት ለማግኘት ምን ነገር ያስፈልገናል?

5 የአምላክ እውነት በዋጋ ሊተመን የማይችል ውድ ሀብት ነው። ይህን እውነት ማግኘት የሚቻለው በመቆፈር ማለትም ሳይታክቱ ቅዱሳን ጽሑፎችን በመመርመር ነው። ጥበብ ማግኘትና ለይሖዋ አክብሮታዊ ፍርሃት ማሳየት ምን ማለት እንደሆነ መረዳት የምንችለው ልክ በልጅነት ዕድሜ ላይ እንደሚገኙ ተማሪዎች ልባችንን ክፍት አድርገን ከታላቁ አስተማሪ ስንማር ብቻ ነው። (ምሳሌ 1:7፤ ኢሳይያስ 30:20, 21) እርግጥ ነው የተማርነውን ነገር ከቅዱሳን ጽሑፎች ማረጋገጥ ይኖርብናል። (1 ጴጥሮስ 2:1, 2) በቤርያ ይኖሩ የነበሩት አይሁዳውያን “በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና፦ ነገሩ [ጳውሎስ የተናገረው ነገር] እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ።” የቤርያ ሰዎች ይህን ማድረጋቸው አስመሰገናቸው እንጂ አላስኮነናቸውም።—ሥራ 17:10, 11

6. ኢየሱስ አንዳንድ አይሁዳውያን ቅዱሳን ጽሑፎችን መመርመራቸው ምንም እንዳልፈየደላቸው ሊናገር የቻለው ለምን ነበር?

6 ኢየሱስ አንዳንድ አይሁዳውያንን እንደሚከተለው ብሏቸው ነበር፦ “እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና መጻሕፍትን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሠክሩ ናቸው፤ ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም።” (ዮሐንስ 5:39, 40) ቅዱሳን ጽሑፎች ወደ ሕይወት ሊመሩን ይችላሉ የሚል ትክክለኛ ዓላማ ይዘው ይመረምሩ ነበር። በእርግጥም ቅዱሳን ጽሑፎቹ ሕይወት የሚገኘው በኢየሱስ እንደሆነ የሚጠቁሙ መሲሐዊ ትንቢቶችን ያቀፉ ነበሩ። ይሁን እንጂ አይሁዳውያን እርሱን ለመቀበል አሻፈረኝ አሉ። ስለዚህ ቅዱሳን ጽሑፎችን መመርመራቸው ምንም አልፈየደላቸውም።

7. ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለንን ማስተዋል ለማሳደግ ምን ያስፈልጋል? ለምንስ?

7 ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለን ማስተዋል እንዲያድግ ከአምላክ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል የሚገኘው መመሪያ ያስፈልገናል። ‘መንፈስ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንኳ ሳይቀር ሁሉን በመመርመር’ ትርጉማቸውን ግልጽ ያደርግልናል። (1 ቆሮንቶስ 2:10) በተሰሎንቄ የነበሩት ክርስቲያኖች የሰሟቸውን ትንቢቶች ‘ሁሉ መፈተን’ ነበረባቸው። (1 ተሰሎንቄ 5:20, 21) ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች ሲጽፍ (በ50 እዘአ ገደማ) ከግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች መካከል በወቅቱ ተጽፎ የነበረው የማቴዎስ ወንጌል ብቻ ነበር። በመሆኑም በተሰሎንቄና በቤርያ የነበሩት ሰዎች ሁሉን መፈተን ይችሉ የነበረው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን የግሪክ ሴፕቱጀንት ትርጉም በመመርመር ነበር ማለት ነው። እነርሱ ቅዱሳን ጽሑፎችን ማንበብና ማጥናት አስፈልጓቸው እንደነበር ሁሉ እኛም እንዲሁ ማድረግ ይኖርብናል።

ለሁሉም የግድ አስፈላጊ ነው

8. የተሾሙ ሽማግሌዎች የላቀ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ሊኖራቸው የሚገባው ለምንድን ነው?

8 የተሾሙ ሽማግሌዎች የላቀ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ሊኖራቸው ይገባል። ‘የማስተማር ብቃት ያላቸውና’ ‘በታመነው ቃል የሚጸኑ’ መሆን ይኖርባቸዋል። የበላይ ተመልካች የነበረው ጢሞቴዎስ ‘የእውነትን ቃል በትክክል መጠቀም’ ይጠበቅበት ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 3:2፤ ቲቶ 1:9፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:15 አዓት) አባቱ አማኝ የነበረ ባይሆንም እንኳ እናቱ ኤውንቄና አያቱ ሎይድ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ቅዱሳን ጽሑፎችን በማስተማር በውስጡ ‘ግብዝነት የሌለበት’ እምነት ተክለውለታል። (2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:15) አማኝ የሆኑ አባቶች ልጆቻቸውን ‘በጌታ ምክርና ተግሣጽ’ ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል፤ በተለይ ደግሞ ሽማግሌ የሆኑ አባቶች “ስድ በመሆንና ባለመታዘዝ ምክንያት የማይወቀሱ አማኞች ልጆች” ሊኖሯቸው ይገባል። (ኤፌሶን 6:4፤ ቲቶ 1:6 1980 ትርጉም) ሁኔታችን ምንም ይሁን ምን የአምላክን ቃል የማንበብ፣ የማጥናትና በሥራ የመተርጎሙን አስፈላጊነት በጣም አክብደን ልንመለከተው ይገባል።

9. ከመሰል ክርስቲያኖች ጋር አንድ ላይ ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

9 መጽሐፍ ቅዱስን ከመሰል አማኞችም ጋር አንድ ላይ ሆነን ማጥናት ይኖርብናል። ጳውሎስ በተሰሎንቄ የሚገኙት ክርስቲያኖች የሰጣቸውን ምክር እርስ በርስ እንዲወያዩበት ፈልጎ ነበር። (1 ተሰሎንቄ 4:18) ስለ እውነት ያለንን ግንዛቤ ለማስፋት ለቃሉ ከፍተኛ ፍቅር ካላቸው ሌሎች ተማሪዎች ጋር ሆነን ቅዱሳን ጽሑፎችን ከመመርመር የተሻለ መንገድ የለም። “ብረት ብረትን ይስለዋል፣ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል” የሚለው ምሳሌ እውነት ነው። (ምሳሌ 27:17) ከብረት የተሠራ መገልገያ በየጊዜው የማንጠቀምበት ከሆነና ካልተሳለ ሊዝግ ይችላል። በተመሳሳይም አዘውትረን መሰብሰብና በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት በማንበብ፣ በማጥናትና በማሰላሰል ያገኘነውን እውቀት አንዳችን ለሌላው በማካፈል እርስ በርስ መሳሳል ይኖርብናል። (ዕብራውያን 10:24, 25) ከዚህም በላይ ከመንፈሳዊ ብርሃን ብልጭታዎች ጥቅም ማግኘት የምንችልበት አንዱ መንገድ ይህ ነው።—መዝሙር 97:11፤ ምሳሌ 4:18

10. በእውነት መመላለስ ምን ማለት ነው?

10 ቅዱሳን ጽሑፎችን በምናጠናበት ጊዜ እንደ መዝሙራዊው “ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ” ብለን መጸለያችን ተገቢ ነው። (መዝሙር 43:3) የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የምንፈልግ ከሆነ በእርሱ እውነት መመላለስ ይኖርብናል። (3 ዮሐንስ 3, 4) ይህም እርሱ ከሚፈልግብን ብቃት ጋር ተስማምቶ መሄድን እንዲሁም የታመኑ ሆኖ መገኘትንና ከልብ ማገልገልን ይጨምራል። (መዝሙር 25:4, 5፤ ዮሐንስ 4:23, 24) ይሖዋን በቃሉ ላይ በተገለጸውና ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ ጽሑፎች ላይ በተብራራው እውነት መሠረት ማገልገል ይኖርብናል። (ማቴዎስ 24:45-47) ይህን ለማድረግ ደግሞ የግድ ትክክለኛ የቅዱሳን ጽሑፎች እውቀት ሊኖረን ይገባል። እንዲህ ከሆነ ታዲያ የአምላክን ቃል ማንበብና ማጥናት የሚኖርብን እንዴት ነው? ከዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ቁጥር 1 ጀምረን 66ቱንም መጻሕፍት በቅደም ተከተል ማንበብ ይኖርብናልን? አዎን፣ በቋንቋው የተዘጋጀ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ያለው እያንዳንዱ ክርስቲያን ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ድረስ ማንበብ ይኖርበታል። መጽሐፍ ቅዱስንና ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን ስናነብ ዓላማችን አምላክ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በኩል የሚዘጋጅልንን የተትረፈረፈ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነት ይበልጥ መረዳት መሆን ይገባዋል።

የአምላክን ቃል ድምፃችሁን እያሰማችሁ አንብቡ

11, 12. መጽሐፍ ቅዱስ በስብሰባዎች ላይ ጮክ ተብሎ መነበቡ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?

11 ብቻችንን በምንሆንበት ጊዜ ድምፃችንን ሳናሰማ እናነብ ይሆናል። ይሁን እንጂ በጥንት ጊዜ ብቻቸውን ሆነው ሲያነቡ ድምፃቸውን ያሰሙ ነበር። ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በሠረገላው ላይ ተቀምጦ የኢሳይያስን ትንቢት ሲያነብ ወንጌላዊው ፊልጶስ ሰምቶታል። (ሥራ 8:27-30) “ማንበብ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል መሠረታዊ ትርጉሙ “መጥራት” ማለት ነው። እንግዲያውስ ድምፃቸውን ሳያሰሙ በማንበብ መልእክቱን ማስተዋል የማይችሉ ቢኖሩ ድምፃቸውን አውጥተው እያንዳንዱን ቃል ስለሚያነቡ ብቻ ተስፋ ሊቆርጡ አይገባም። ዋናው ነገር የተጻፈውን የአምላክ ቃል በማንበብ እውነትን መማሩ ነው።

12 በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ጮክ ተብሎ እንዲነበብ ማድረጉ ጠቃሚ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ የአገልግሎት አጋሩ የነበረው ጢሞቴዎስን “ለሕዝብ በማንበብ፣ በመስበክና በማስተማርም ትጋ” ሲል አጥብቆ መክሮታል። (1 ጢሞቴዎስ 4:13 የ1980 ትርጉም፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎች እንደሚከተለው ሲል ነግሯቸው ነበር፦ “ይህችም መልእክት በእናንተ ዘንድ ከተነበበች በኋላ፣ በሎዶቅያ ሰዎች ማኅበር ደግሞ እንድትነበብ አድርጉ፤ ከሎዶቅያም የምትገኘውን መልእክት እናንተ ደግሞ አንብቡ።” (ቆላስይስ 4:16) ራእይ 1:3 ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው [“ድምፁን እያሰማ የሚያነበው፣” አዓት] የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው።” በመሆኑም አንድ የሕዝብ ተናጋሪ ለጉባኤው የሚናገረውን ሐሳብ የሚደግፍ ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ይኖርበታል።

በአንድ ርዕስ ላይ በማተኮር የሚደረግ ጥናት

13. የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትን በመማር ረገድ ፈጣን እድገት ለማድረግ የሚያስችለን የትኛው ዘዴ ነው? ጥቅሶችንስ ለማውጣት ምን ሊረዳን ይችላል?

13 የቅዱሳን ጽሑፎችን እውነት በመማር ረገድ ፈጣን እድገት ለማድረግ የሚያስችለው የተሻለ መንገድ በአንድ ርዕስ ላይ በማተኮር ማጥናት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን ቃላት በፊደል ተራ በየመጽሐፉ ስም፣ ምዕራፍና ቁጥር በቅደም ተከተል እንደ አገባባቸው የሚያስቀምጡ ኮንኮርዳንሶች ከአንድ የተወሰነ ርዕስ ጋር የተያያዙ ጥቅሶችን በቀላሉ ለማግኘት ያስችላሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ ሐሳብ እርስ በርሱ ስለማይቃረን እነዚህን ጥቅሶች አንዱን ከሌላው ጋር ማዛመድ ይቻላል። በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት 40 የሚያክሉ ሰዎች ከ16 መቶ ዘመናት በላይ በፈጀ ጊዜ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲጽፉ አድርጓል፤ በተወሰነ ርዕስ ላይ በማተኮር ይህን መጽሐፍ ማጥናት እውነትን ለመማር የሚያስችል ውጤታማ መንገድ መሆኑ ከተሞክሮ ታይቷል።

14. የዕብራይስጥና የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን እያስተያዩ ማጥናት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

14 ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያለን አድናቆት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ጋር እያስተያየን እንድናነብና እንድናጠና ሊያነሳሳን ይገባል። ይህም የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ከአምላክ ዓላማ ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሚገኙት ትንቢቶች ላይ ብርሃን ይፈነጥቅልናል። (ሮሜ 16:25-27፤ ኤፌሶን 3:4-6፤ ቆላስይስ 1:26) በዚህ ረገድ የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ጠቃሚ ሆኖ እናገኘዋለን። አዘጋጆቹ ስለ መጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ፣ ስለ መጽሐፉ ታሪክና በውስጡ ስለያዛቸው ፈሊጣዊ አነጋገሮች የተገኘውን ተጨማሪ እውቀት የቀሰሙና ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ አገልጋዮች ናቸው። ይሖዋ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት ያዘጋጀልን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱት ጽሑፎችም በጣም አስፈላጊ ናቸው።

15. ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዚህም ከዚያም መጥቀሱ ተገቢ መሆኑን እንዴት ማስረዳት ትችላለህ?

15 አንዳንድ ሰዎች ‘በጽሑፎቻችሁ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጊዜ ይጠቀሳል፤ ይሁን እንጂ ከዚህም ከዚያም የምትጠቅሱት ለምንድን ነው?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። ጽሑፎቹ ከ66ቱም የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፎች ውስጥ ከዚህም ከዚያም በመጥቀስ የአንድን ትምህርት እውነተኝነት የሚያረጋግጡ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ በርካታ ማስረጃዎችን ያቀርባሉ። ይህን የማስተማሪያ ዘዴ ኢየሱስም ተጠቅሞበታል። የተራራ ስብከቱን በሰጠበት ወቅት ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ 21 ጊዜ ጠቅሷል። በዚህ ንግግሩ ላይ ከዘጸአት ሦስት ጊዜ፣ ከዘሌዋውያን ሁለት ጊዜ፣ ከዘኁልቁ አንድ ጊዜ፣ ከዘዳግም ስድስት ጊዜ፣ ከሁለተኛ ነገሥት አንድ ጊዜ፣ ከመዝሙር አራት ጊዜ፣ ከኢሳይያስ ሦስት ጊዜና ከኤርምያስ አንድ ጊዜ ጠቅሷል። ኢየሱስ እንዲህ በማድረጉ ለማስጨበጥ የሞከረው ነገር አልነበረም ማለት ነውን? አይደለም፤ ምክንያቱም ያስተማራቸው ‘እንደ ጻፎች ሳይሆን እንደ ባለ ሥልጣን ነበር።’ ይህ ሊሆን የቻለው ትምህርቱ ሁሉ በጽሑፍ በሠፈረው በአምላክ ቃል ላይ የተደገፈ ስለነበር ነው። (ማቴዎስ 7:29) ሐዋርያው ጳውሎስም እንደዚሁ አድርጓል።

16. ጳውሎስ በሮሜ 15:7-13 ላይ የትኞቹን የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል ጠቅሷል?

16 በሮሜ 15:7-13 ላይ በሚገኘው የቅዱስ ጽሑፉ ክፍል ውስጥ ጳውሎስ ከሦስት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ክፍሎች ማለትም ከሕግ፣ ከነቢያትና ከመዝሙራት ጠቅሷል። አይሁዳውያንና አሕዛብ አምላክን እንደሚያወድሱ ከገለጸ በኋላ ክርስቲያኖች ከየትኛውም ሕዝብ የመጡት ሰዎችን መቀበል እንደሚገባቸው ተናግሯል። እንዲህ አለ፦ “ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እንደ ተቀበላችሁ እንዲሁ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ። ለአባቶች የተሰጠውን የተስፋ ቃል ያጸና ዘንድ ደግሞም፦ [በመዝሙር 18:49 ላይ] ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ ለስምህም እዘምራለሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ አሕዛብም ስለ ምሕረቱ እግዚአብሔርን ያከብሩ ዘንድ፣ ክርስቶስ ስለ እግዚአብሔር እውነት የመገረዝ አገልጋይ ሆነ እላለሁ። ደግሞም [በዘዳግም 32:43 ላይ]፦ አሕዛብ ሆይ፣ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላል። ደግሞም [በመዝሙር 117:1 ላይ]፦ እናንተ አሕዛብ ሁላችሁ፣ ጌታን አመስግኑ ሕዝቦቹም ሁሉ ይወድሱት ይላል። ደግሞም ኢሳይያስ [11:1, 10]፦ የእሴይ ሥር አሕዛብንም ሊገዛ የሚነሣው ይሆናል፤ በእርሱ አሕዛብ ተስፋ ያደርጋሉ ይላል። የተስፋ አምላክም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተስፋ እንድትበዙ በማመናችሁ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ።” ጳውሎስ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ማብራሪያ መስጠት በሚቻልበት በዚህ ዘዴ በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚያስረዱ ጥቅሶችን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል አሳይቷል።

17. ክርስቲያኖች ከመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዚህም ከዚያም የሚጠቅሱት የትኛውን ምሳሌ በመከተል ነው?

17 በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የመጀመሪያው የሐዋርያው ጴጥሮስ ደብዳቤ በሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙራት ውስጥ ከሚገኙ አሥር መጻሕፍት ውስጥ 34 ጊዜ ይጠቅሳል። ጴጥሮስ በሁለተኛ ደብዳቤው ውስጥ ከሦስት መጻሕፍት ስድስት ጊዜ ጠቅሷል። የማቴዎስ ወንጌል ከዘፍጥረት እስከ ሚልክያስ ካሉት መጻሕፍት ውስጥ 122 ጊዜ ይጠቅሳል። በ27ቱ የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከዘፍጥረት እስከ ሚልክያስ ካሉት መጻሕፍት በቀጥታ የተወሰዱ 320 ጥቅሶች ከመኖራቸውም በላይ ሌሎች በመቶ የሚቆጠሩ ሐሳቦች ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ተጠቅሰዋል። በዚህ ዘመን ያሉ ክርስቲያኖችም ኢየሱስ ከተወላቸውና ሐዋርያቱም ከተከተሉት ከዚህ ምሳሌ ጋር በመስማማት በአንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ጥናት ሲያደርጉ ከመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዚህም ከዚያም ይጠቅሳሉ። በተለይ አብዛኛዎቹ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ፍጻሜያቸውን እያገኙ ባሉባቸው በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀናት’ ውስጥ ይህ ይበልጥ ተስማሚ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ‘ታማኝና ልባም ባሪያ’ በሚያወጣቸው ጽሑፎች ላይ መጽሐፍ ቅዱስን በዚህ መልኩ ይጠቀማል፤ ይሁን እንጂ በአምላክ ቃል ላይ አንዳች አይጨምርም ወይም አይቀንስም።—ምሳሌ 30:5, 6፤ ራእይ 22:18, 19

ዘወትር በእውነት ተመላለሱ

18. ‘በእውነት መመላለስ’ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

18 በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ክርስቲያናዊ ትምህርት በሙሉ “እውነት” ወይም “የምሥራቹ እውነት” ስለሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳች ነገር መቀነስ አይገባንም። ይህን እውነት የሙጥኝ ማለታችን ማለትም ‘በእርሱ መመላለሳችን’ ለመዳን የግድ አስፈላጊ ነው። (ገላትያ 2:5፤ 2 ዮሐንስ 4፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) ክርስትና “የእውነት መንገድ” እንደመሆኑ ሌሎችን በመርዳት የክርስትናን ዓላማ ስናራምድ “የእውነት ሥራ ተካፋዮች” እንሆናለን።—2 ጴጥሮስ 2:2፤ 3 ዮሐንስ 8 የ1980 ትርጉም

19. ‘በእውነት መመላለሳችንን’ መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?

19 ‘በእውነት መመላለሳችንን መቀጠል’ የምንችለው መጽሐፍ ቅዱስ የምናነብና አምላክ ‘በታማኙ ባሪያ’ አማካኝነት በሚሰጠን መንፈሳዊ እርዳታ የምንጠቀም ከሆነ ብቻ ነው። (3 ዮሐንስ 4) ራሳችንንም ጠቅመን ሌሎችንም ስለ ይሖዋ አምላክ፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም ስለ መለኮታዊው ዓላማ ለማስተማር እንድንችል ይህን እናድርግ። የይሖዋ መንፈስ ቃሉን እንድረዳና በተሳካ ሁኔታ በእውነት እንድናገለግለው ለሚሰጠን እርዳታ አመስጋኞች እንሁን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ መጽሐፍ ቅዱስ በማንበብ የሚገኙ አንዳንድ ዘላቂ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

◻ መጽሐፍ ቅዱስን ከመሰል አማኞች ጋር አንድ ላይ ሆኖ ማጥናት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

◻ ከመላው መጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ ክፍሎች መጥቀሱ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

◻ ‘በእውነት መመላለስ’ ማለት ምን ማለት ነው? ይህንንስ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች ሆይ፣ ልጆቻችሁን ቅዱሳን ጽሑፎችን አስተምሯቸው

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ወቅት ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የተለያዩ ክፍሎችን ጠቅሷል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ