ለማንበብ ትጋ
“እስክመጣ ድረስ ለሕዝብ በማንበብ፣ በመስበክና በማስተማር ትጋ።”—1 ጢሞቴዎስ 4:13 የ1980 ትርጉም
1. መጽሐፍ ቅዱስ በማንበብ ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
ይሖዋ አምላክ ለሰው ልጅ ማንበብንና መጻፍን ለመማር የሚያስችል ድንቅ ችሎታ አጎናጽፎታል። አጥጋቢ ትምህርት ማግኘት እንድንችልም ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል። (ኢሳይያስ 30:20, 21) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሠፈሩት አገላለጾች እንደ አብርሃም፣ ይስሐቅ እና ያዕቆብ ካሉት አምላካዊ ፍርሃት ከነበራቸው የዕብራውያን አባቶች ጋር በስሜት ‘እንድንጓዝ’ ያስችሉናል። እንደ ሣራ፣ ርብቃና በታማኝነት ከኑኃሚን ጋር እንደተጣበቀችው ሞዓባዊቷ ሩት የመሳሰሉትን ለአምላክ አክብሮት የነበራቸው ሴቶች ‘ማየት’ እንችላለን። አዎን፣ የኢየሱስ ክርስቶስን የተራራ ስብከትም ‘መስማት’ እንችላለን። ጥሩ አንባቢዎች ከሆንን ከቅዱሳን ጽሑፎች የሚገኘውን ይህን ሁሉ ደስታና ታላቅ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን።
2. ኢየሱስና ሐዋርያቱ በደንብ ማንበብ ይችሉ እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው?
2 ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ ጥሩ የማንበብ ችሎታ እንደነበረውና የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠንቅቆ ያውቅ እንደነበር ጥርጥር የለውም። በመሆኑም ኢየሱስ በዲያብሎስ በተፈተነበት ወቅት ከእነዚሁ ጽሑፎች በተደጋጋሚ እየጠቀሰ “ተጽፏል” በማለት መልስ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 4:4, 7, 10) በአንድ ወቅት ናዝሬት ውስጥ በሚገኘው ምኩራብ ከኢሳይያስ ትንቢት ላይ የተወሰነውን ክፍል በሕዝብ ፊት ካነበበ በኋላ ትንቢቱ በእርሱ ላይ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ተናግሮ ነበር። (ሉቃስ 4:16-21) ስለ ኢየሱስ ሐዋርያትስ ምን ማለት ይቻላል? በጽሑፎቻቸው ውስጥ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን በርካታ ጊዜ ጠቅሰዋል። ጴጥሮስና ዮሐንስ በዕብራውያን ትምህርት ቤቶች ውስጥ ገብተው ከፍተኛ ትምህርት ባለመቅሰማቸው የአይሁዳውያን መሪዎች ያልተማሩና ተራ ሰዎች እንደሆኑ አድርገው ይቁጠሯቸው እንጂ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፏቸው ደብዳቤዎች በሚገባ መጻፍና ማንበብ ይችሉ እንደነበር የሚያረጋግጡ ሕያው ማስረጃዎች ናቸው። (ሥራ 4:13) ይሁን እንጂ የማንበብ ችሎታ በእርግጥ አስፈላጊ ነውን?
‘ድምፅ እያሰማ የሚያነበው ደስተኛ ነው’
3. ቅዱሳን ጽሑፎችንና ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን ማንበብ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
3 የቅዱሳን ጽሑፎችን ትክክለኛ እውቀት መቅሰምና በሥራ መተርጎም የዘላለም ሕይወት ሊያስገኝ ይችላል። (ዮሐንስ 17:3) በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ቅዱሳን ጽሑፎችን እንዲሁም አምላክ በቅቡዓን ክርስቲያኖች የታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል በኩል የሚያቀርበውን ክርስቲያናዊ ጽሑፎች ማንበብና ማጥናት የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ይገነዘባሉ። (ማቴዎስ 24:45-47) እንዲያውም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ንባብ ለማስተማር ተብለው በተዘጋጁ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች በመጠቀም ለማንበብ በመብቃታቸው በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ሕይወት ሰጪ እውቀት መቅሰም ችለዋል።
4. (ሀ) የአምላክን ቃል ማንበብ፣ ማጥናትና በሥራ መተርጎም ደስታ የሚያስገኘው እንዴት ነው? (ለ) ማንበብን በተመለከተ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ምን ብሎታል?
4 የአምላክን ቃል ማንበብ፣ ማጥናትና በሥራ ላይ ማዋል ደስታ ያስገኛል። ምክንያቱም ይህን ማድረጋችን አምላክን የሚያስደስትና የሚያስከብር ከመሆኑም በላይ የእርሱን በረከት ያስገኝልናል፣ ደስታም እንድናጭድ ያደርገናል። ይሖዋ አገልጋዮቹ ደስተኞች እንዲሆኑ ይፈልጋል። በዚህም ምክንያት ካህናቱ ለጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ ሕጉን እንዲያነቡላቸው አዝዞ ነበር። (ዘዳግም 31:9-12) ጸሐፊው ዕዝራና ሌሎችም በኢየሩሳሌም ለተሰበሰቡት ሁሉ ሕጉን ባነበቡበት ወቅት ትርጉሙንም ጭምር ስላብራሩላቸው ‘እጅግ ደስ ብሏቸው’ ነበር። (ነህምያ 8:6-8, 12) ከጊዜ በኋላ ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ የአገልግሎት አጋሩን ጢሞቴዎስን “እስክመጣ ድረስ ለሕዝብ በማንበብ፣ በመስበክና በማስተማር ትጋ” ብሎት ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 4:13 የ1980 ትርጉም) አንድ ሌላ ትርጉም ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “ቅዱሳን ጽሑፎችን በሕዝብ ፊት ለማንበብ ትጋ።”—ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን
5. ራእይ 1:3 ደስታን ከንባብ ጋር የሚያዛምደው እንዴት ነው?
5 ደስታ ማግኘታችን የተመካው የአምላክን ቃል በማንበባችንና በሥራ በመተርጎማችን ላይ እንደሆነ በራእይ 1:3 ላይ ተገልጿል። ጥቅሱ እንዲህ ይለናል፦ “ዘመኑ ቀርቧል፣ የሚያነበው፣ [“ድምፁን እያሰማ የሚያነበው፣” አዓት] የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው።” አዎን፣ በራእይ መጽሐፍና በሌሎቹም ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያለውን የአምላክ ትንቢታዊ ቃል ድምፃችንን እያሰማን ማንበብ እንዲሁም መስማት ይኖርብናል። ‘በይሖዋ ሕግ ደስ የሚለው፣ ሕጉንም በቀንና በሌሊት በተመስጦ ከንፈሩን እያንቀሳቀሰ የሚያነብ’ ሰው እውነተኛ ደስታ ይኖረዋል። ውጤቱስ ምን ይሆናል? “የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።” (መዝሙር 1:1-3 አዓት) እንግዲያውስ የይሖዋ ድርጅት ቃሉን በየግላችን፣ በቤተሰብ መልክ እና ከጓደኞቻችን ጋር ሆነን እንድናነብና እንድናጠና እያንዳንዳችንን አጥብቆ የሚያሳስብበት ጥሩ ምክንያት አለው።
በተመስጦ አስብ እንዲሁም አሰላስል
6. ኢያሱ ምን እንዲያነብ ትእዛዝ ተሰጥቶት ነበር? ይህስ ጠቃሚ የነበረው እንዴት ነው?
6 የአምላክን ቃልና ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን በምታነብበት ጊዜ ከሁሉ በተሻለ መንገድ ለመጠቀም የምትችለው እንዴት ነው? ፈሪሃ አምላክ የነበረው የጥንቷ እስራኤል መሪ ኢያሱ ያደረገው ነገር ጠቃሚ ሆኖ ሳታገኘው አትቀርም። ኢያሱ የሚከተለው ትእዛዝ ተሰጥቶት ነበር፦ “የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፣ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው [“ከንፈርህን እያንቀሳቀስህ በተመስጦ አንብበው፣” አዓት]፤ የዚያን ጊዜ መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም።” (ኢያሱ 1:8) ‘ከንፈርን እያንቀሳቀሱ በተመስጦ ማንበብ’ ማለት ለአንተ በሚሰማ መጠን ድምፅህን ዝቅ አድርገህ ቃላቱን መጥራት ማለት ነው። ይህ ትምህርቱ በአእምሮህ ውስጥ እንዲቀረጽ ስለሚያደርግ ለማስታወስ ይረዳል። ኢያሱ የአምላክን ሕግ “በቀንም በሌሊትም” ወይም በሌላ አባባል ዘወትር ማንበብ ይጠበቅበት ነበር። ስኬታማ መሆንና አምላክ የሰጠውን ኃላፊነት በጥበብ መወጣት የሚችለው በዚህ መንገድ ነበር። በዚህ መንገድ የአምላክን ቃል አዘውትሮ የማንበብ ልማድ አንተንም በተመሳሳይ መንገድ ሊጠቅምህ ይችላል።
7. የአምላክን ቃል በምናነብበት ጊዜ መጣደፍ የሌለብን ለምንድን ነው?
7 የአምላክን ቃል በምታነብበት ጊዜ አትጣደፍ። መጽሐፍ ቅዱስን ወይም ሌሎች ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን ለማንበብ የተወሰነ ጊዜ መድበህ ከሆነ ረጋ ብለህ ማንበብ ይኖርብህ ይሆናል። በተለይ ዋና ዋና ነጥቦችን ለመጨበጥ ሥራዬ ብለህ በምታነብበት ጊዜ እንዲህ ማድረግህ በጣም አስፈላጊ ነው። ስታነብ በተመስጦ አስብ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊው ያሰፈረውን ሐሳብ በጥሞና መርምር። ‘ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት ምንድን ነው? ይህን ትምህርት ልሠራበት የምችለው እንዴት ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ።
8. ቅዱሳን ጽሑፎችን ስናነብ ማሰላሰል ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
8 ቅዱሳን ጽሑፎችን ስታነብ ጊዜ ወስደህ አሰላስል። ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ለማስታወስና ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ ለማዋል ይረዳሃል። በአምላክ ቃል ላይ ማሰላሰልህና ነጥቦቹ በአእምሮህ ውስጥ እንዲቀረጹ ማድረግህ በቅን ልቦና ተነሣስተው ለሚጠይቁ ሰዎች ከልብ የመነጨና የማያስቆጭ ትክክለኛ መልስ እንድትሰጥም ያስችልሃል። በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ አንድ ምሳሌ “የጻድቅ ልብ መልስ መስጠት እንዲችል ያሰላስላል” ይላል።—ምሳሌ 15:28 አዓት
አዲስ ያገኘሃቸውን ሐሳቦች በፊት ከምታውቃቸው ጋር አዛምድ
9, 10. አዲስ ያገኘሃቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች ቀደም ሲል ከምታውቃቸው ጋር በማዛመድ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ ሊጎለብት የሚችለው እንዴት ነው?
9 አብዛኞቹ ክርስቲያኖች በአንድ ወቅት ስለ አምላክ፣ ስለ ቃሉና ስለ ዓላማው የነበራቸው እውቀት በጣም አነስተኛ እንደነበር አይካድም። ይሁን እንጂ ዛሬ እነዚህ ክርስቲያን አገልጋዮች ከፍጥረት ሥራዎችና የሰው ልጅ ኃጢአት ከፈጸመበት ሁኔታ አንስቶ የክርስቶስ መሥዋዕት ዓላማ ምን እንደሆነ አንድ በአንድ ማብራራት ይችላሉ፤ በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ላይ ስለሚመጣው ጥፋትም ሆነ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ገነት በሆነች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት በማግኘት የሚባረኩት እንዴት እንደሆነ ማስረዳት ይችላሉ። ለዚህ ውጤት ከፍተኛ ድርሻ ያበረከተው ነገር እነዚህ የይሖዋ አገልጋዮች መጽሐፍ ቅዱስንና ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን በማጥናት ‘አምላክ የሚሰጠውን እውቀት’ መቅሰማቸው ነው። (ምሳሌ 2:1-5) የተማሯቸውን አዳዲስ ነገሮች ቀደም ሲል ከሚያውቋቸው ጋር ቀስ በቀስ አዛምደዋል።
10 ያገኘሃቸውን አዳዲስ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች ቀደም ሲል ከምታውቃቸው ጋር ማዛመድህ ጠቃሚ ነው። (ኢሳይያስ 48:17) የመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎች፣ መሠረታዊ ሥርዓቶች ወይም አንዳንድ ረቂቅ የሚመስሉ ሐሳቦች ሲያጋጥሙህ በፊት ከምታውቃቸው ነገሮች ጋር አዛምዳቸው። ያገኘኸውን ሐሳብ ‘ስለ ጤናማ ቃላት ሥርዓት’ ከተማርከው ነገር ጋር አስማማ። (2 ጢሞቴዎስ 1:13 አዓት) ከአምላክ ጋር ያለህን ዝምድና ለማጠናከር፣ ክርስቲያናዊ ባሕርይህን ለማሻሻል ወይም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ለማካፈል የሚረዳህ ነጥብ ፈልግ።
11. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ምግባር የሚናገረውን ሐሳብ በምታነብበት ጊዜ ምን ማድረጋችን ጠቃሚ ሊሆን ይችላል? በምሳሌ አስረዳ።
11 መጽሐፍ ቅዱስ ምግባርን በተመለከተ የሚሰጠውን ሐሳብ ስታነብ በዚያ ውስጥ የተንጸባረቀውን መሠረታዊ ሥርዓት ለማስተዋል ሞክር። በዚያ ላይ አሰላስል፤ ተመሳሳይ ሁኔታ ሲገጥምህ ምን እንደምታደርግ ወስን። የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ “እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአት እሠራለሁ?” በማለት ከጶጢፋር ሚስት ጋር የጾታ ብልግና ለመፈጸም በተደጋጋሚ ጊዜ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። (ዘፍጥረት 39:7-9) ከዚህ ስሜት ከሚነካ ታሪክ በስተጀርባ የጾታ ብልግና በአምላክ ላይ የሚፈጸም ኃጢአት መሆኑን የሚገልጽ አንድ መሠረታዊ ሥርዓት ታገኛለህ። ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኙት ሌሎች ሐሳቦች ጋር በአእምሮህ ልታዛምደው ትችላለህ። ምናልባት እንዲህ ዓይነት ኃጢአት እንድትፈጽም ብትፈተን ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በማስታወስ ልትጠቀም ትችላለህ።—1 ቆሮንቶስ 6:9-11
ቅዱስ ጽሑፋዊ ክንውኖችን በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት
12. የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ስታነብ የምታነበውን ታሪክ በዓይነ ሕሊናህ መሳል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
12 በምታነብበት ጊዜ ነጥቦቹን በአእምሮህ ውስጥ ለመቅረጽ እንድትችል እየተከናወነ ያለውን ነገር በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ጋራ ሸንተረሩን፣ ቤቶቹንና ሰዎቹን በአእምሮህ ሳላቸው። ሲናገሩ ይሰማህ። በምጣድ ላይ ያለው ዳቦ ይሽተትህ። ትዕይንቱን ወደ አእምሮህ አምጣው። ጥንታዊ ከተማ ልትመለከት፣ ትልቅ ተራራ ልትወጣ፣ ተዓምራዊውን የፍጥረት ሥራ ልታደንቅ ወይም ደግሞ ጽኑ እምነት ከነበራቸው ወንዶችና ሴቶች ጋር አብረህ ጊዜ ልታሳልፍ ስለምትችል ንባብህ ስሜት ቀስቃሽ ይሆናል።
13. በመሳፍንት 7:19-22 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ታሪክ እንዴት ትገልጸዋለህ?
13 ለምሳሌ ያህል መሳፍንት 7:19-22ን እያነበብክ ነው እንበል። ምን እየተከናወነ እንዳለ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። መስፍኑ ጌዴዎንና ሦስት መቶ ጀግና እስራኤላውያን ወንዶች በምድያማውያን ጦር ሠፈር ዳርቻ መጥተው ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል። ከምሽቱ አራት ሰዓት ገደማ ማለትም “ከእኩለ ሌሊት ትንሽ ቀደም ብሎ፣ ዘብ ጠባቂዎች ከተቀያየሩ በኋላ” [የ1980 ትርጉም] ነበር። የምድያማውያን ዘብ ጠባቂዎች በቦታቸው ቆመዋል፣ ያንቀላፉትን የእስራኤላውያን ጠላቶች ጦር ሠፈር ጨለማ ውጦታል። ተመልከት! ጌዴዎንና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች መለከት ይዘዋል። በግራ እጆቻቸው የያዙትን ችቦ የሚከልል ትልቅ የውኃ ማሠሮም ይዘዋል። መቶ መቶ ሰው ያሉባቸው ሦስቱ ጭፍሮች በድንገት መለከታቸውን ነፉ፣ ማሠሮዎቻቸውን ሰባበሩና ችቦዎቻቸውን ከፍ አድርገው በማብራት “የእግዚአብሔርና የጌዴዎን ሰይፍ!” ብለው ጮኹ። የጦር ሠፈሩን ተመልከት። ምድያማውያን ሸሹ፤ ጩኸታቸውንም ያቀልጡት ጀመር! ሦስት መቶዎቹ ሰዎች መለከታቸውን መንፋት ሲቀጥሉ አምላክ ምድያማውያን እርስ በርሳቸው በሰይፍ እንዲተላለቁ አደረገ። ምድያማውያን ሸሽተው ሄዱ፤ ይሖዋ ድሉ የእስራኤል እንዲሆን አደረገ።
ጠቃሚ ትምህርቶችን መቅሰም
14. አንድ ልጅ ትሑት የመሆንን አስፈላጊነት እንዲገነዘብ ለመርዳት መሳፍንት ምዕራፍ 9ን እንዴት ልንጠቀምበት እንችላለን?
14 የአምላክን ቃል በማንበብ ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ለምሳሌ ያህል ለልጆቻችሁ ትሑት የመሆንን አስፈላጊነት ለማስገንዘብ ፈለጋችሁ እንበል። እንደዚያ ከሆነ የጌዴዎን ልጅ ኢዮአታም በተናገረው ትንቢት ውስጥ የተገለጹትን ነገሮች በአእምሮ ውስጥ መሳልና ቁም ነገሩን መጨበጥ ከባድ አይሆንም። ከመሳፍንት 9:8 ጀምራችሁ አንብቡ። “አንድ ጊዜ” አለ ኢዮአታም “ዛፎች በላያቸው ንጉሥ ሊያነግሡ ሄዱ።” የወይራ ዛፍ፣ በለስና ወይን ለመግዛት ፈቃደኞች አልሆኑም። ይሁን እንጂ ተራው የእሾህ ቁጥቋጦ ንጉሥ ለመሆን ፈለገ። ለልጆቻችሁ ይህን ታሪክ ድምፃችሁን እያሰማችሁ ካነበባችሁላቸው በኋላ ጠቃሚ የሆኑት ዛፎች በእስራኤላውያን ወንድሞቻቸው ላይ ንጉሥ ለመሆን ያልፈለጉትን ብቃት ያላቸው ሰዎች እንደሚያመለክቱ ልታስረዷቸው ትችላላችሁ። ለማገዶ ብቻ የሚያገለግለው እሾህ የሚያመለክተው በሌሎች ላይ ለመግዛት ቢፈልግም ኢዮአታም በተናገረው ትንቢት መሠረት የጠፋውን የኩራተኛውንና የነፍሰ ገዳዩን አቤሜሌክ ንግሥና ነበር። (መሳፍንት ምዕራፍ 9) ሲያድግ እንደ እሾህ መሆን የሚፈልግ የትኛው ልጅ ነው?
15. በታማኝነት የመጣበቅ አስፈላጊነት በሩት መጽሐፍ ውስጥ ጎላ ብሎ የተገለጸው እንዴት ነው?
15 በታማኝነት የመጣበቁ አስፈላጊነት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በሩት መጽሐፍ ውስጥ በግልጽ ተቀምጧል። ለምሳሌ ያህል በቤተሰባችሁ ውስጥ ይህን ታሪክ ድምፃችሁን እያሰማችሁ ተራ በተራ በማንበብ የሚያስተላልፈውን መልእክት ለመረዳት እየሞከራችሁ ነው እንበል። ሞዓባዊቷ ሩት ከመበለቲቱ አማቷ ከኑኃሚን ጋር ወደ ቤተ ልሔም ስትጓዝ ታያላችሁ፤ “ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል” ስትልም ትሰማላችሁ። (ሩት 1:16) ታታሪዋ ሩት በቦዔዝ እርሻ ላይ ስትቃርም ከአጫጆቹ ኋላ ሆና ትታያለች። ቦዔዝ “በአገሬ ያሉ ሕዝብ ሁሉ ምግባረ መልካም ሴት እንደሆንሽ ያውቃሉ” በማለት ሲያሞግሳት ትሰማላችሁ። (ሩት 3:11) ብዙም ሳይቆይ ቦዔዝ ሩትን ያገባታል። በጊዜው በነበረው ከባል የቅርብ ዘመድ ጋር የሚደረግ የጋብቻ ሥርዓት መሠረት ሩት “ለኑኃሚን” ከቦዔዝ ወንድ ልጅ ወለደችላት። ሩት የዳዊት በኋላም የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ዓያት ሆናለች። በዚህ መንገድ ‘ፍጹም ደመወዝ’ አገኘች። ከዚህም በላይ ይህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ታሪክ የሚያነቡ ሁሉ ከይሖዋ ጋር በታማኝነት ከተጣበቅን አብዝቶ እንደሚባርከን የሚያሳይ ጠቃሚ ትምህርት ያገኛሉ።—ሩት 2:12፤ 4:17-22፤ ምሳሌ 10:22፤ ማቴዎስ 1:1, 5, 6
16. ሦስቱ ዕብራውያን የገጠማቸው ፈታኝ ሁኔታ ምን ነበር? ይህ ታሪክ እኛን እንዴት ሊጠቅመን ይችላል?
16 ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የተባሉት ዕብራውያን ያስመዘገቡት ታሪክ ፈታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን በአምላክ ዘንድ የታመንን ትእዛዝ አክባሪዎች እንድንሆን ሊረዳን ይችላል። ዳንኤል ምዕራፍ 3 ሲነበብ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናችሁ ተመልከቱ። ባቢሎናውያን ባለ ሥልጣኖች በተሰበሰቡበት በዱራ ሜዳ አንድ በጣም ግዙፍ የወርቅ ምስል ቆሟል። የሙዚቃ መሣሪያዎች ድምፅ ሲሰማ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ወድቀው ይሰግዳሉ። ከሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ በቀር ሁሉም ለምስሉ ሰግደዋል። የእርሱን አማልክት እንደማያገለግሉና ለወርቁ ምስል እንደማይሰግዱ አክብሮት በተሞላበት መንገድ ፈርጠም ብለው ለንጉሡ ተናገሩ። እነዚህ ወጣት ዕብራውያን በኃይል የሚንቀለቀል እሳት በሚነድበት እቶን ውስጥ ተጣሉ። ይሁን እንጂ የተፈጸመው ሁኔታ ምን ነበር? ንጉሡ ወደ እሳቱ ውስጥ ሲመለከት አራት ሰዎች አየ፤ አንደኛው “የአማልክት ልጅ” ይመስል ነበር። (ዳንኤል 3:25) ሦስቱ ዕብራውያን ከእቶኑ ውስጥ እንዲወጡ ተደረገ፤ ናቡከደነፆርም አምላካቸውን ባረከ። ይህን ታሪክ በዓይነ ሕሊና መመልከት የሚያስደስት ነው። በፈተና ወቅት ለይሖዋ የታመኑ ትእዛዝ አክባሪ ሆኖ በመገኘት ረገድ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ታሪክ ነው!
መጽሐፍ ቅዱስን በቤተሰብ መልክ በማንበብ ጥቅም ማግኘት
17. ቤተሰባችሁ መጽሐፍ ቅዱስን አንድ ላይ በማንበብ ሊማራቸው ከሚችላቸው ጠቃሚ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን በአጭሩ ጥቀስ።
17 ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን አብራችሁ የምታነቡ ከሆነ ቤተሰባችሁ ብዙ ጥቅም ሊያገኝ ይችላል። ከዘፍጥረት ጀምራችሁ ስታነቡ የፍጥረት ሥራዎችን በዓይነ ሕሊናችሁ መዳሰስና በሰው ልጅ የመጀመሪያ መኖሪያ በገነት የነበረውን ሁኔታ በጥልቀት መመልከት ትችላላችሁ። የታመኑ የዕብራውያን አባቶችና ቤተሰቦቻቸው ያሳለፉትን ተሞክሮ መካፈልና እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን በደረቅ ምድር ሲሻገሩ መመልከት ትችላላችሁ። እረኛ የነበረው ብላቴናው ዳዊት ግዙፉን ፍልስጤማዊ ጎልያድን ሲጥለው ታያላችሁ። ቤተሰባችሁ የይሖዋ ቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም ሲገነባ፣ በባቢሎናውያን ጭፍራ ሲደመሰስና በገዥው በዘሩባቤል መሪነት ተመልሶ ሲገነባ ሁኔታው ምን ይመስል እንደነበር መመልከት ይችላል። መላእክት የኢየሱስን መወለድ ሲያበስሩ በቤተ ልሔም አቅራቢያ ከነበሩት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ከነበራቸው እረኞች ጋር አብራችሁ መስማት ትችላላችሁ። ስለ ጥምቀቱና አገልግሎቱ ዝርዝር ታሪኮችን ማግኘት ትችላላችሁ፤ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ሲሰጥ መመልከትና በትንሣኤ መነሣቱ ባስገኘው ደስታ መካፈል ትችላላችሁ። በመቀጠልም ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር በመጓዝ ክርስትና እየተስፋፋ ሲሄድ የተቋቋሙትን ጉባኤዎች ማስተዋል ትችላላችሁ። ቤተሰባችሁ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸውንና የክርስቶስን የሺህ ዓመት ግዛት የሚያካትተውን የሐዋርያው ዮሐንስ ታላቅ ራእይም መመልከት ይችላል።
18, 19. በቤተሰብ መልክ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብን በተመለከተ ምን ሐሳቦች ቀርበዋል?
18 መጽሐፍ ቅዱስን በቤተሰብ መልክ ድምፃችሁን እያሰማችሁ የምታነቡ ከሆነ ንባባችሁ ጥራትና ግለት ያለው ይሁን። አንዳንዶቹን የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል በምታነቡበት ጊዜ አንዱ የቤተሰብ አባል (ምናልባትም አባትየው ሊሆን ይችላል) እንደ ተራኪ ሆኖ አጠቃላይ ታሪኩን የሚዘግበውን ክፍል ሊያነብ ይችል ይሆናል። ሌሎቻችሁ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን ባለ ታሪኮች በመወከል ትክክለኛውን ስሜት በሚያንጸባርቅ መንገድ ልታነቡ ትችላላችሁ።
19 በቤተሰብ መልክ ሆናችሁ መጽሐፍ ቅዱስን ስታነቡ የንባብ ችሎታችሁ ሊሻሻል ይችላል። ስለ አምላክ ያላችሁ እውቀትም ሊጨምር ስለሚችል ይበልጥ ከእርሱ ጋር ያቀራርባችኋል። አሳፍ እንደሚከተለው ብሎ ዘምሯል፦ “ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረቤ መልካም ነው፤ የእርሱን ሥራ ለማብሠር እንድችል እግዚአብሔር አምላክን መጠጊያዬ አድርጌአለሁ።” (መዝሙር 73:28 የ1980 ትርጉም) ይህም ቤተሰባችሁ ‘የማይታየውን [ይሖዋን] እንደሚታየው አድርጎ እንደጸናው’ እንደ ሙሴ እንዲሆን ይረዳዋል።—ዕብራውያን 11:27
ንባብና ክርስቲያናዊ አገልግሎት
20, 21. የመስበክ ተልእኮአችን ከማንበብ ችሎታ ጋር የተያያዘው እንዴት ነው?
20 “የማይታየውን” አምላክ ለማምለክ ያለን ፍላጎት ጥሩ አንባቢዎች ለመሆን እንድንጣጣር ሊያነሳሳን ይገባል። ጥሩ የማንበብ ችሎታ ከአምላክ ቃል ለመመሥከር ይረዳናል። ኢየሱስ “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ባለ ጊዜ ለተከታዮቹ የሰጣቸውን የመንግሥቱን የስብከት ሥራ የማከናወን ተልእኮ ለመፈጸም እንደሚረዳን እሙን ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ሥራ 1:8) የይሖዋ አገልጋዮች ዋነኛ ሥራ ምሥክርነት መስጠት ነው፤ የማንበብ ችሎታ ደግሞ ይህን ለማከናወን ይረዳናል።
21 ጥሩ አንባቢዎችና የተዋጣልን የአምላክ ቃል አስተማሪዎች ለመሆን ጥረት ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው። (ኤፌሶን 6:17) እንግዲያውስ ‘የእውነትን ቃል በትክክል የምትጠቀም ሆነህ የተፈተነውን ራስህን ለአምላክ ለማቅረብ ትጋ።’ (2 ጢሞቴዎስ 2:15) ለማንበብ ትጉዎች በመሆን ስለ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነት ያለህን እውቀትና የይሖዋ ምሥክር ሆነህ የማገልገል ብቃትህን አሳድግ።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ደስታ የአምላክን ቃል በማንበብ ላይ የተመካ የሆነው እንዴት ነው?
◻ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባነበባችሁት ነገር ላይ ማሰላሰል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ቅዱሳን ጽሑፎችን ስናነብ ነገሮችን ማዛመድና በዓይነ ሕሊናችን መመልከት ያስፈለገው ለምንድን ነው?
◻ ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የምንማራቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
◻ መጽሐፍ ቅዱስን በቤተሰብ መልክ አንድ ላይ ሆኖ ድምፅ እያሰሙ ማንበብ ያስፈለገው ለምንድን ነው? ንባብ ከክርስቲያናዊ አገልግሎት ጋር ያለው ግንኙነትስ ምንድን ነው?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስን በቤተሰብ መልክ በምታነቡበት ጊዜ ታሪኩን በዓይነ ሕሊናችሁ ተመልከቱ፣ በሚያስተላልፈው መልእክትም ላይ አሰላስሉ