የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 53—2 ተሰሎንቄ
ጸሐፊው:- ጳውሎስ
የተጻፈበት ቦታ:- ቆሮንቶስ
ተጽፎ ያለቀው:- በ51 ከክ.ል.በኋላ ገደማ
ሐዋርያው ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች ሁለተኛ ደብዳቤውን የጻፈው የመጀመሪያውን ከጻፈ ብዙም ሳይቆይ ነው። ይህን ደብዳቤ የጻፈው የመጀመሪያውን ከጻፈ ብዙም ሳይቆይ፣ በዚያው በቆሮንቶስ ከተማ እያለ መሆኑን ለማወቅ የሚያስችለን በመጀመሪያው ደብዳቤ ላይ ስማቸው የተጠቀሰው ስልዋኖስና ጢሞቴዎስ ከጳውሎስ ጋር በመሆን በተሰሎንቄ ለሚገኘው ጉባኤ ሰላምታ መላካቸው ነው። ሁሉም በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከቦታ ቦታ እየተጓዙ ያገለግሉ ነበር፤ እነዚህ ሦስት ወንድሞች በቆሮንቶስ ከተገናኙ በኋላ እንደገና ስለመገናኘታቸው የሚገልጽ ዘገባ የለም። (2 ተሰ. 1:1፤ ሥራ 18:5, 18) ደብዳቤው የሚያወሳው ርዕሰ ጉዳይና ይዘቱ እንደሚያመለክተው ጳውሎስ፣ ጉባኤው የሠራውን ስህተት ለማረም አፋጣኝ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ተሰምቶት ነበር።
2 እንደ አንደኛ ተሰሎንቄ ሁሉ የዚህም ደብዳቤ ትክክለኛነት በሚገባ የተረጋገጠ ነው። ኢራኒየስም (በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ) ሆነ ሌሎች ቀደምት ጸሐፊዎች ከዚህ ደብዳቤ ጠቅሰዋል፤ ከዚህም በተጨማሪ ሰማዕቱ ጀስቲን (በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ) “የዐመፅ [የኃጢአት] ሰው” ብሎ ሲጽፍ 2 ተሰሎንቄ 2:3ን መጥቀሱ ሳይሆን አይቀርም። የሁለተኛ ተሰሎንቄ መጽሐፍ፣ አንደኛ ተሰሎንቄ በሚገኝባቸው ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝሮች ውስጥ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜ በቼስተር ቢቲ ፓፒረስ ቁጥር 2 (P46) ውስጥ ባይገኝም ከአንደኛ ተሰሎንቄ በኋላ ከነበሩት ሰባት የጠፉ ገጾች መካከል በመጀመሪያዎቹ ሁለት ገጾች ውስጥ እንደነበረ አያጠራጥርም።
3 የዚህ ደብዳቤ ዓላማ ምን ነበር? ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች ከሰጠው ምክር ለመረዳት እንደምንችለው በጉባኤው ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች የጌታ መገኘት በቅርቡ እንደሚሆን ይከራከሩ የነበረ ከመሆኑም በላይ ራሳቸው ያመነጩትን ይህን ግምታዊ ጽንሰ ሐሳብ በስፋት ይሰብኩ እንዲሁም በጉባኤው ውስጥ ከፍተኛ ብጥብጥ ይፈጥሩ ነበር። እንዲያውም አንዳንዶች ላለመሥራት ይህን እንደ ምክንያት አድርገው ያቀርቡ የነበረ ይመስላል። (2 ተሰ. 3:11) ጳውሎስ በመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ ስለ ጌታ መገኘት ጠቅሶ ነበር፤ እነዚህ በራሳቸው ግምት የሚመሩ ሰዎች ደብዳቤው ሲነበብ በሚሰሙበት ጊዜ የጳውሎስን ሐሳብ በማጣመም እሱ ከጻፈው የተለየ ትርጉም ሰጥተውት ነበር። እንዲሁም የጳውሎስ ደብዳቤ እንደሆነ በስህተት የተገመተ አንድ ሌላ ደብዳቤ የያዘው ሐሳብ ‘የይሖዋ ቀን እንደደረሰ’ የሚጠቁም እንደሆነ አድርገው ተረድተውት ሊሆን ይችላል።—2:1, 2
4 ጳውሎስ ስለዚህ ሁኔታ የሚገልጽ ሪፖርት የደረሰው ይመስላል፤ ሁኔታውን የነገረው የመጀመሪያውን ደብዳቤ ለጉባኤው ያደረሰለት ሰው ይሆናል። በመሆኑም እጅግ የሚወዳቸውን ወንድሞቹን አስተሳሰብ ለማስተካከል በጣም ተጨንቆ መሆን አለበት። በዚህም ምክንያት በ51 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ጳውሎስ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር በመሆን በተሰሎንቄ ለሚገኘው ጉባኤ ከቆሮንቶስ ደብዳቤ ላከ። ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ መገኘት የነበራቸውን የተሳሳተ አመለካከት ከማረሙም በተጨማሪ በእምነት ጸንተው እንዲቆሙ ሞቅ ያለ ማበረታቻ ሰጥቷቸዋል።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
10 በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት ለተሰሎንቄ ሰዎች የተጻፈው ይህ አጭር ደብዳቤ የክርስትና እውነትን በርካታ ገጽታዎች የሚዳስስ ሲሆን መልእክቱ በሙሉ ጠቃሚ ነው። በደብዳቤው ውስጥ ከተካተቱት መሠረታዊ ትምህርቶችና መመሪያዎች አንዳንዶቹን ተመልከት:- ይሖዋ የመዳን አምላክ ነው፤ በመንፈስ ይቀድሳል እንዲሁም በእውነት ላይ እምነት የሚያሳድሩትን መዳን እንዲያገኙ ይመርጣል (2:13)፤ ክርስቲያኖች ለአምላክ መንግሥት ብቁ ሆነው ለመቆጠር እንዲችሉ መከራ ሲደርስባቸው መጽናት አለባቸው (1:4, 5)፤ ክርስቲያኖች በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መገኘት ጊዜ በአንድ ላይ ይሰባሰባሉ (2:1)፤ ይሖዋ ለወንጌሉ በማይታዘዙት ላይ የጽድቅ ፍርድ ያመጣል (1:5-8)፤ የተጠሩት፣ እንደ አምላክ ጸጋ መጠን በክርስቶስ ኢየሱስ ይከበራሉ (1:12)፤ እነዚህ ሰዎች የተጠሩት በወንጌሉ ስብከት አማካኝነት ነው (2:14)፤ እምነት በጣም አስፈላጊ ብቃት ነው (1:3, 4, 10, 11፤ 2:13፤ 3:2)፤ አንድ ሰው በአገልግሎት በሚካፈልበት ጊዜ የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት መሥራቱ ተገቢ ነው፤ አንድ ሰው የማይሠራ ከሆነ ስንፍና ሊጠናወተውና በሌሎች ጉዳይ ጣልቃ መግባት ሊጀምር ይችላል (3:8-12)፤ የአምላክ ፍቅር ከጽናት ጋር ተያይዞ ተገልጿል (3:5)። በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው በዚህ አጭር ደብዳቤ ውስጥ በጣም የሚያንጽ ትምህርት ይገኛል!
11 ጳውሎስ በዚህ ደብዳቤ ላይ በተሰሎንቄ ስለሚገኙት ወንድሞቹ መንፈሳዊ ደኅንነት እንዲሁም ስለ ጉባኤው አንድነትና ብልጽግና በጥልቅ እንደሚያስብ አሳይቷል። የይሖዋ ቀን የሚመጣበትን ጊዜ በተመለከተ የነበራቸውን አመለካከት እንዲያስተካክሉ ለመርዳት ሲል በመጀመሪያ “የዐመፅ ሰው” መገለጥ እንዳለበትና “እርሱም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተቀምጦ፣ ‘እኔ አምላክ ነኝ’ እያለ ዐዋጅ” እንደሚያስነግር ገልጾላቸዋል። በሌላ በኩል ግን ‘ለአምላክ መንግሥት የበቁ ሆነው የተቆጠሩት’ ሰዎች፣ ጌታ ኢየሱስ በተወሰነው ጊዜ በሰማይ እንደሚገለጥና “በቅዱሳኑ ዘንድ ሊከብርና በሚያምኑበትም ሁሉ ዘንድ ሊገረም በሚመጣበት በዚያን ቀን” በሚንበለበል እሳት የበቀል እርምጃ እንደሚወስድ ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ።—2:3, 4፤ 1:5, 10