-
ለሁሉ የሚሆን ተመጣጣኝ ቤዛመጠበቂያ ግንብ—1991 | የካቲት 15
-
-
ተመጣጣኝ ቤዛ
10. የእንስሳት መሥዋዕት የሰዎችን ኃጢአት ለመሸፈን በቂ ለመሆን የማይችለው ለምንድን ነው?
10 ከላይ የተመለከትነው ምሳሌ እንደሚያሳየው ቤዛ ለሚተካው ወይም ለሚሸፍነው ነገር በመጠኑ የሚተካከል መሆን አለበት። ከአቤል ጀምሮ የነበሩት የእምነት ሰዎች ያቀረቡአቸው የእንስሳት መሥዋዕቶች የሰዎችን ኃጢአት ሊሸፍኑ አልቻሉም። ምክንያቱም የሰው ልጆች ከእንስሳት የበለጡ ናቸው። (መዝሙር 8:4-8) በዚህም ምክንያት ጳውሎስ “የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና” ብሎ ለመጻፍ ችሎአል። እንደነዚህ ያሉት መሥዋዕቶች ለሚመጣው መሥዋዕት ሰዎችን የሚያዘጋጁ ጥላነት ወይም ምሳሌነት ያላቸው መሥዋዕቶች ብቻ ነበሩ።—ዕብራውያን 10:1-4
11, 12. (ሀ) የሰውን ኃጢአተኛነት ለመሸፈን በሺህ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መሥዋዕት ሆነው መሞት የማያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? (ለ) ‘ተመጣጣኝ ቤዛ’ ሊሆን የሚችለው ማን ብቻ ሆነ? የሞተውስ ለምን ዓላማ ነው?
11 አምላክ በአዳም ላይ የበየነው የሞት ፍርድ የሰውን ዘር በሙሉ የሚኮንን ስለሆነ ይህ ጥላ የተደረገለት ቤዛ ከአዳም ጋር የሚመጣጠን መሆን ይኖርበታል። 1 ቆሮንቶስ 15:22 “ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ” ይናገራል። ስለዚህ ለአዳም ግለሰብ ተወላጆች በሙሉ ምትክ የሚሆኑ በሺህ ሚልዮን የሚቆጠሩ ግለሰቦች መሥዋዕታዊ ሞት መሞት አያስፈልጋቸውም። “ኃጢአት በአንድ ሰው [በአዳም] ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት።” (ሮሜ 5:12) እንግዲህ “ሞት [በአንድ]ሰው በኩል ስለ መጣ” የሰው ዘርም በአንድ ሰው ሊቤዥ ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 15:21
12 ቤዛ ሊሆን የሚችለው ሰው ከአዳም ጋር ሙሉ በሙሉ የሚተካከል ሥጋና ደም የሆነ ፍጹም ሰው መሆን ይኖርበታል። (ሮሜ 5:14) መንፈሳዊ ፍጡር ወይም “ሰውም አምላክም” የሆነ አካል የፍትሕ ሚዛን የሚጠይቀውን ያዛባል። ከአዳም ጋር ሙሉ በሙሉ የሚተካከል “ተመጣጣኝ ቤዛ” ሊያቀርብ የሚችለው የአዳም የሞት ፍርድ የማይመለከተው ፍጹም የሆነ ሰው ብቻ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:6)a ይህ “ኋለኛ አዳም” ሕይወቱን በፈቃዱ በመሰዋት ‘የመጀመሪያውን ሰው የአዳምን’ የኃጢአት ደመወዝ ሊከፍል ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 15:45፤ ሮሜ 6:23
-
-
ለሁሉ የሚሆን ተመጣጣኝ ቤዛመጠበቂያ ግንብ—1991 | የካቲት 15
-
-
a እዚህ ላይ የተጠቀሰው አንቲሊትሮን የተባለው የግሪክኛ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሌላ ሥፍራ አይገኝም። ቃሉ ኢየሱስ በማርቆስ 10:45 ላይ ስለ ቤዛ ሲናገር ከተጠቀመበት ቃል ጋር (ከሊትሮን ጋር) ይዛመዳል። ይሁን እንጂ አዲሱ ኢንተርናሽናል የአዲስ ኪዳን መንፈሣዊ ትምህርት መዝገበ ቃላት ሊትሮን አንድን ነገር የሌላው ነገር ልዋጭ ማድረግን ያጎላል። ስለዚህ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም “ተመጣጣኝ ቤዛ” ብሎ መተርጎሙ ተገቢ ነው።
-