ራስን መወሰንና የመምረጥ ነፃነት
“በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን።”—ገላትያ 5:1
1. “ዴዲኬሽን፣” “ኢኖጉሬሽን” ወይም “ኮንሲክሬሽን” ተብለው ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት በዋነኛነት የሚያገለግሉት ምንን ለማመልከት ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ለአንድ ቅዱስ ዓላማ የተለዩ መሆንን ወይም መወሰንን ለመግለጽ የተለያዩ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት ተጠቅመዋል። እነዚህ ቃላት በእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዴዲኬሽን” [ለአምላክ የተወሰኑ መሆን]፣ “ኢኖጉሬሽን” [ምረቃ] ወይም “ኮንሲክሬሽን” [የተለዩ መሆን] እየተባሉ ተተርጉመዋል። እነዚሁ ቃላት ከሕንፃዎች ጋር በተያያዘ ሁኔታ የገቡባቸው አንዳንድ ቦታዎች ያሉ ሲሆን በአብዛኛው የተሠራባቸው በጥንቷ ኢየሩሳሌም የነበረውን የአምላክ ቤተ መቅደስና በዚያ ይካሄድ የነበረውን አምልኮ ለማመልከት ነው። እነዚህ ቃላት ከዚህ ውጭ ሰብዓዊ ነገሮችን ለማመልከት ያገለገሉበት ጊዜ እምብዛም ነው።
“ለእስራኤል አምላክ” የተወሰኑ መሆን
2. ይሖዋ “የእስራኤል አምላክ” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
2 አምላክ በ1513 ከዘአበ እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነፃ አውጥቷቸው ነበር። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከእርሱ ጋር በቃል ኪዳን እንዲተሳሰሩ በማድረግ ለእርሱ የተለዩ ሕዝብ እንዲሆኑ አደረጋቸው። “አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፣ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ዘጸአት 19:5፤ መዝሙር 135:4) እስራኤላውያን ለእርሱ የተመረጠ ርስት እንዲሆኑ በማድረጉ ይሖዋ ‘የእስራኤል አምላክ’ መባሉ ተገቢ ነበር።—ኢያሱ 24:23
3. ይሖዋ እስራኤልን ሕዝቡ አድርጎ በመምረጡ አድልዎ አላሳየም የምንለው ለምንድን ነው?
3 ይሖዋ እስራኤላዊ ላልሆኑትም ብሔራት ቢሆን ፍቅራዊ አሳቢነቱን ስላልነፈገ እስራኤላውያንን ለእርሱ የተወሰኑ ሕዝብ እንዲሆኑ ማድረጉ አድሏዊ አያሰኘውም። ለሕዝቦቹ እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጥቷል:- “በአገራችሁ ውስጥ ከእናንተ ጋር እንግዳ ቢቀመጥ ግፍ አታድርጉበት። እናንተ በግብጽ ምድር እንግዶች ነበራችሁና ከእናንተ ጋር የሚቀመጥ እንግዳ እንደ አገር ልጅ ይሁንላችሁ፣ እርሱንም እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።” (ዘሌዋውያን 19:33, 34) ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ የአምላክን አመለካከት ለመቀበል ተገድዶ ነበር፤ ከዚያ በኋላ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ።”—ሥራ 10:34, 35
4. በአምላክና በእስራኤል መካከል ለነበረው ግንኙነት ምን ነገሮች መሟላት ነበረባቸው? እስራኤላውያንስ የሚፈለግባቸውን አሟልተው ተገኝተዋልን?
4 ለአምላክ የተወሰኑ ሕዝቦች መሆናቸው በሁኔታዎች ላይ የተመካ እንደነበረም ልብ በል። ለአምላክ ‘የተመረጠ ርስት’ የሚሆኑት የእርሱን ቃል በጥብቅ እስከታዘዙና ቃል ኪዳኑን እስከጠበቁ ድረስ ብቻ ነበር። የሚያሳዝነው እስራኤላውያን ይህን ብቃት ሳያሟሉ ቀሩ። አምላክ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የላከውን መሲህ ለመቀበል አሻፈረን ካሉ በኋላ የነበራቸውን ልዩ መብት አጥተዋል። ይሖዋ “የእስራኤል አምላክ” መሆኑ ቀረ። ሥጋዊ እስራኤላውያንም ለአምላክ የተወሰኑ ሕዝቦች መሆናቸው አከተመ።—ከማቴዎስ 23:23 ጋር አወዳድር።
‘የአምላክ እስራኤል’ የተወሰነ መሆን
5, 6. (ሀ) ኢየሱስ በማቴዎስ 21:42, 43 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን ትንቢታዊ ቃላት ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? (ለ) ‘የአምላክ እስራኤል’ ወደ ሕልውና የመጣው መቼና እንዴት ነው?
5 ታዲያ ይህ ማለት ይሖዋ ለእርሱ የተወሰነ ሕዝብ አይኖረውም ማለት ነውን? እንደዚያ ማለት አይደለም። ኢየሱስ የመዝሙራዊውን ቃላት በመጥቀስ እንዲህ ብሏል:- “ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፣ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን? ስለዚህ እላችኋለሁ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች።”—ማቴዎስ 21:42, 43
6 ይህ ‘ፍሬዋን የሚያደርግ ሕዝብ’ የክርስቲያን ጉባኤ ሆኖ ተገኘ። ኢየሱስ ምድር ላይ በቆየበት ጊዜ የዚህን ሕዝብ የመጀመሪያ እጩ አባላት መርጧል። ይሁን እንጂ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በመጀመሪያዎቹ 120 አባላት ላይ ቅዱስ መንፈሱን በማፍሰስ የክርስቲያን ጉባኤ እንዲመሠረት ያደረገው ይሖዋ ራሱ ነው። (ሥራ 1:15፤ 2:1-4) ሐዋርያው ጴጥሮስ ከጊዜ በኋላ እንደጻፈው ይህ አዲስ ጉባኤ በዚህ ወቅት “የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን” ሆኗል። የተመረጡት ለምን ዓላማ ነበር? “ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራ[ቸውን] የእርሱን በጎነት” እንዲናገሩ ነበር። (1 ጴጥሮስ 2:9) ከዚህ በኋላ በአምላክ መንፈስ የተቀቡት የኢየሱስ ተከታዮች ለአምላክ የተወሰነ ብሔር ማለትም ‘የአምላክ እስራኤል’ ሆነዋል።—ገላትያ 6:16
7. የአምላክ እስራኤል አባላት ምን አግኝተው ነበር? ከምን ነገርስ እንዲርቁ ተነግሯቸዋል?
7 የዚህ ቅዱስ ሕዝብ አባላት ‘ለርስቱ የተለየ ወገን’ ቢሆኑም ባሪያ ናቸው ማለት አልነበረም። እንዲያውም ለአምላክ የተወሰነ የነበረው የሥጋዊ እስራኤላውያን ብሔር ካገኘው የሚበልጥ ነፃነት ያገኙ ነበር። ኢየሱስ ለዚህ አዲስ ብሔር እጩ አባላት “እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ሲል ቃል ገብቷል። (ዮሐንስ 8:32) ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች ከሕጉ ቃል ኪዳን ግዴታዎች ነፃ መውጣታቸውን ገልጿል። ይህን በሚመለከት በገላትያ የነበሩትን የእምነት አጋሮቹን እንዲህ ሲል አሳስቧቸዋል:- “በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ።”—ገላትያ 5:1
8. የክርስትና ዝግጅት ከሕጉ ቃል ኪዳን ይልቅ በሥሩ ላሉት ግለሰቦች የበለጠ ነፃነት የሚሰጠው በምን መንገድ ነው?
8 ከጥንቱ የሥጋዊ እስራኤላውያን ብሔር በተለየ መልኩ የአምላክ እስራኤል እስከ ዛሬም ድረስ ለአምላክ የተወሰነ ብሔር መሆኑ የሚጠይቅበትን ግዴታ በጥብቅ ሲፈጽም ቆይቷል። ይህ ሊያስገርመን አይገባም፤ ምክንያቱም የብሔሩ አባላት ለመታዘዝ የመረጡት በፈቃደኛነት ነው። የሥጋዊ እስራኤላውያን አባላት ለአምላክ የተወሰኑ የሆኑት በውልደት ሲሆን የአምላክ እስራኤል አባላት ግን በገዛ ምርጫቸው ነው። በዚህ መንገድ የክርስትና ዝግጅት የሰዎችን ነፃ ምርጫ ሳይጠብቅ ለአምላክ የተወሰኑ እንዲሆኑ ካደረጋቸው የአይሁዳውያን የሕግ ቃል ኪዳን ፈጽሞ የተለየ ነው።
9, 10. (ሀ) ኤርምያስ ራስን ለአምላክ መወሰንን በተመለከተ ለውጥ እንደሚኖር የጠቆመው እንዴት ነው? (ለ) ዛሬ ያሉት ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች በሙሉ የአምላክ እስራኤል አባላት አይደሉም የምትለው ለምንድን ነው?
9 ነቢዩ ኤርምያስ እንደሚከተለው በመጻፍ ለአምላክ የተወሰኑ በመሆን ረገድ ለውጥ እንደሚኖር አስቀድሞ ተናግሯል:- “እነሆ፣ ከእስራኤልና ከይሁዳ ቤት ጋር ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ከግብጽ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፣ እኔም ቸል አልኋቸው፣ ይላል እግዚአብሔር። ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፣ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል።”—ኤርምያስ 31:31-33
10 የአምላክ እስራኤል አባላት የአምላክ ሕግ ‘በልባቸው የተጻፈ’ ያህል ‘በውስጣቸው’ ስለተተከለ ለአምላክ ራሳቸውን ሲወስኑ የገቡትን ቃል ጠብቀው እንዲመላለሱ ይገፋፋቸዋል። ለሥራ የሚያንቀሳቅሳቸው ውስጣዊ ግፊት በምርጫ ሳይሆን በውልደት ለአምላክ ከተወሰኑት ሥጋዊ እስራኤላውያን ይበልጥ ጠንካራ ነው። ዛሬ የአምላክ እስራኤል አባላት ያላቸው ዓይነት ጠንካራ ውስጣዊ ግፊት የሚያሳዩ ከአምስት ሚልዮን የሚበልጡ መሰል አምላኪዎች በምድር ዙሪያ ይገኛሉ። እነርሱም እንዲሁ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ሕይወታቸውን ለይሖዋ አምላክ ወስነዋል። እነዚህ ግለሰቦች እንደ አምላክ እስራኤል አባላት የሰማያዊ ሕይወት ተስፋ ባይኖራቸውም በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ግዛት ሥር በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ በማግኘታቸው ይደሰታሉ። የመንፈሳዊ እስራኤላውያን ጥቂት ቀሪዎች ‘ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን የጠራቸውን የእርሱን በጎነት የመናገር’ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ በትጋት በመደገፍ ለእነርሱ ያላቸውን አድናቆት ያሳያሉ።
ከአምላክ ያገኘነውን ነፃነት በጥበብ መጠቀም
11. የሰው ልጅ የተፈጠረው ምን ከማድረግ ችሎታ ጋር ነው? ይህስ ሊሠራበት የሚገባው እንዴት ነው?
11 አምላክ የሰው ልጆችን የፈጠረው ለነፃነት ልዩ ግምት እንዲኖራቸው አድርጎ ነው። የመምረጥ ነፃነት አላብሷቸዋል። የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት የመምረጥ ነፃነታቸውን ተጠቅመውበታል። ይሁን እንጂ ጥበብና ፍቅራዊነት የጎደለው ምርጫቸው ራሳቸውንም ሆነ ልጆቻቸውን የችግር አዘቅት ውስጥ የከተተ ነበር። ሆኖም ይህ ይሖዋ የማሰብ ችሎታ ያላቸውን ፍጡራኑን ከውስጣዊ ግፊታቸው ወይም ከምኞታቸው ተቃራኒ የሆነ ጎዳና እንዲከተሉ ፈጽሞ እንደማያስገድ በግልጽ የሚያሳይ ነው። አምላክ ‘በደስታ የሚሰጠውን ስለሚወድድ’ ራሳችንን መወሰናችን በፊቱ ተቀባይነት የሚኖረው በፍቅር የተመሠረተ፣ ደስ እያለን በፈቃደኛነትና በመምረጥ ነፃነታችን ተጠቅመን ያደረግነው ከሆነ ብቻ ነው። (2 ቆሮንቶስ 9:7) ከዚህ ውጭ የተደረገ ከሆነ ተቀባይነት አይኖረውም።
12, 13. ለልጆች ተገቢውን ሥልጠና በመስጠት ረገድ የጢሞቴዎስ ታሪክ ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው? ይህስ ብዙ ወጣቶችን ምን እንዲያደርጉ ገፋፍቷቸዋል?
12 የይሖዋ ምሥክሮች ይህን መመዘኛ አሳምረው ስለሚያውቁ ሰዎች ራሳቸውን ለአምላክ መወሰን እንዳለባቸው አጥብቀው ቢያምኑም ልጆቻቸውን ጨምሮ ማንንም ሰው ራሱን እንዲወስን ፈጽሞ አያስገድዱም። የይሖዋ ምሥክሮች ከብዙዎቹ አብያተ ክርስቲያናት በተለየ መልኩ ልጆቻቸውን ሕፃናት እያሉ አያጠምቋቸውም፤ ይህ ልጆቻቸው ያለገዛ ምርጫቸው ራሳቸውን ለአምላክ እንዲወስኑ እንደማስገደድ የሚቆጠር ይሆናል። ወጣቱ ጢሞቴዎስ የተከተለው ጎዳና ጥሩ ቅዱስ ጽሑፋዊ አብነት ይሆነናል። ትልቅ ሰው ከሆነ በኋላ ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ነግሮታል:- “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፣ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፣ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል።”—2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15
13 ጢሞቴዎስ የቅዱሳን ጽሑፎችን እውቀት ሊያገኝ የቻለው ከሕፃንነቱ ጀምሮ ተምሮ ስለነበር መሆኑ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ነው። እናቱና ሴት አያቱ የክርስትናን ትምህርቶች እንዲያምን አስረድተውት ነበር እንጂ አላስገደዱትም። (2 ጢሞቴዎስ 1:5) ከዚህ የተነሣ ጢሞቴዎስ የክርስቶስ ተከታይ በመሆን በክርስትና ጎዳና ራሱን ለአምላክ ለመወሰን የግሉን ምርጫ ማድረጉ ጥበብ እንደሆነ አስተዋለ። ዛሬም ቢሆን ወላጆቻቸው የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ይህንኑ ምሳሌ ተከትለዋል። (መዝሙር 110:3 NW) ሌሎች ደግሞ እንደዚያ ሳያደርጉ ቀርተዋል። ይህ የእያንዳንዱ የግል ምርጫ ነው።
የማን ባሪያ ለመሆን ትመርጣላችሁ?
14. ሮሜ 6:16 ፍጹም ነፃ መሆንን አስመልክቶ የሚነግረን ነገር ምንድን ነው?
14 ፍጹም ነፃ የሆነ አንድም ሰው የለም። ሁሉም ሰው እንደ ስበት ሕግ ባሉት የተፈጥሮ ሕጎች ነፃነቱ የተገደበ ነው፤ እነዚህን ሕጎች ችላ ብልም ምንም አይደርስብኝም ሊል የሚችል አይኖርም። በመንፈሳዊ ሁኔታም ሲታይ ጨርሶ ነፃ የሆነ ሰው የለም። ጳውሎስ እንዲህ ሲል አስረድቷል:- “ለመታዘዝ ባሪያዎች እንድትሆኑ ራሳችሁን ለምታቀርቡለት፣ ለእርሱ ለምትታዘዙለት ባሪያዎች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን? ወይም ለሞት የኃጢአት ባሪያዎች ወይም ለጽድቅ የመታዘዝ ባሪያዎች ናችሁ።”—ሮሜ 6:16
15. (ሀ) ሰዎች ባሪያ ስለመሆን ምን ይሰማቸዋል? ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ምን ሲያደርጉ ይታያል? (ለ) ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች ብንጠይቅ ተገቢ ይሆናል?
15 ብዙዎች የሌላው ባሪያ ናችሁ የሚለው ሐሳብ ያስከፋቸዋል። ይሁንና ሐቁ ሲታይ ዛሬ ባለው ዓለም ውስጥ ሰዎች በአብዛኛው ብዙ የረቀቁ ነገሮች እንዲነዷቸው ወይም ተጽዕኖ እንዲያሳድሩባቸው ስለሚፈቅዱ ሳይወዱት ሌሎች እንዲያደርጉ የሚፈልጉባቸውን ነገር ለማድረግ ይገደዳሉ። ለምሳሌ ያህል የማስታወቂያው ኢንዱስትሪና የመዝናኛው ዓለም በሰዎች ላይ የፈለጉትን ዓይነት አስተሳሰብ ለመቅረጽና ሰዉ የሚከተለውን የአቋም ደረጃ ለማውጣት ይጥራሉ። ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ሰዎች የእነርሱን አመለካከትና ዓላማ እንዲደግፉ ያደርጋሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ደግሞ ሁልጊዜ አሳማኝ ምክንያቶችን በማቅረብ ሳይሆን አንድነትና ታማኝነት በሚል ስም ነው። ጳውሎስ ‘ለምትታዘዙለት ባሪያዎች ናችሁ’ ስላለ እያንዳንዳችን እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው:- ‘እኔ ባርያ የሆንኩት ለማን ነው? በማደርጋቸው ውሳኔዎችና በአኗኗሬ ላይ ከፍተኛውን ሚና የሚጫወተው ማን ነው? ሃይማኖታዊ ቀሳውስት፣ ፖለቲካዊ መሪዎች፣ ቱጃር ነጋዴዎች ወይም የመዝናኛው ዓለም ኮከቦች ናቸውን? የምታዘዘው ማንን ነው? አምላክን ወይስ ሰዎችን?’
16. ክርስቲያኖች ለአምላክ ባሪያ የሆኑት ከምን አንጻር ነው? እንዲህ ስላለውስ ባርነት ሊኖረን የሚገባው ተገቢ አመለካከት ምንድን ነው?
16 ክርስቲያኖች ለአምላክ መታዘዝን የግል ነፃነታቸውን እንደሚነፍግ አፈና አድርገው አይቆጥሩትም። የግል ፍላጎቶቻቸውንና ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ነገሮች ከአምላክ ፈቃድ ጋር በማስማማት እንደ ምሳሌያቸው እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ነፃነታቸውን በፈቃደኛነት ይጠቀሙበታል። (ዮሐንስ 5:30፤ 6:38) ክርስቶስ የጉባኤው ራስ እንደመሆኑ መጠን ለእርሱ በመገዛት ‘የእርሱን አስተሳሰብ’ ያዳብራሉ። (1 ቆሮንቶስ 2:14-16፤ ቆላስይስ 1:15-18) ሁኔታው የምትወደውን ሰው አግብታ በፈቃደኛነት ከእርሱ ጋር እየተባበረች ከምትኖር ሴት ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል። እንዲያውም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለክርስቶስ እንደታጨች ድንግል ሆነው ተገልጸዋል።—2 ቆሮንቶስ 11:2፤ ኤፌሶን 5:23, 24፤ ራእይ 19:7, 8
17. ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ምን ለመሆን መርጠዋል?
17 እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር ተስፋው ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸምና እርሱን እንደ ገዥው አድርጎ ለመቀበል በግሉ ከአምላክ ጋር ቃል ገብቷል። እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር ራሱን ለአምላክ የወሰነው የሰዎች ባርያ ሆኖ ከመኖር ለአምላክ ባሪያ ለመሆን የግሉን ምርጫ በማድረግ ነው። ይህም “በዋጋ ተገዝታችኋል፤ የሰው ባሪያዎች አትሁኑ” ከሚለው የሐዋርያው ጳውሎስ ምክር ጋር ይስማማል።—1 ቆሮንቶስ 7:23
ራሳችንን መጥቀምን መማር
18. የይሖዋ ምሥክር ለመሆን የሚያስብ ሰው ለመጠመቅ ብቁ የሚሆነው መቼ ነው?
18 አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ብቁ ከመሆኑ በፊት አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን ማሟላት ይጠበቅበታል። ሽማግሌዎች ወደፊት የይሖዋ ምሥክር የሚሆነው ይህ ሰው በክርስትና ጎዳና ራስን ለአምላክ መወሰን ማለት ምን ማለት እንደሆነ በእርግጥ ገብቶት እንደሆነና እንዳልሆነ ለማረጋገጥ ጥንቃቄ ያደርጋሉ። በእርግጥ ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ለመሆን ይፈልጋልን? ይህ ውሳኔው የሚያስከትለውንስ ኃላፊነት ለመቀበል ፈቃደኛ ነውን? ካልሆነ ለጥምቀት ብቁ አይሆንም።
19. አንድ ሰው ራሱን የወሰነ የአምላክ አገልጋይ ለመሆን ቢወስን የሚተችበት ምክንያት አይኖርም የምንለው ለምንድን ነው?
19 ይሁን እንጂ አንድ ሰው ብቃቶቹን ሁሉ ካሟላ በአምላክና በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃሉ ለመመራት በፈቃደኛነት የራሱን ውሳኔ በማድረጉ የሚነቀፍበት ምን ምክንያት ይኖራል? በሰዎች ከመመራት ይልቅ በአምላክ ለመመራት ራስን ማቅረብ የሚጠላ ነገር ነው? ወይስ የማይጠቅም? የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ብለው አያስቡም። “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ” ከሚሉት ኢሳይያስ ካሠፈራቸው የአምላክ ቃላት ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማሉ።—ኢሳይያስ 48:17
20. ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አማካኝነት ነፃ የሚወጡባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው?
20 የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በእሳታማ ሲኦል ውስጥ ለዘላለም መሰቃየት አለ የሚሉትን የመሰሉ የሐሰት ሃይማኖት መሠረተ ትምህርቶችን ከማመን ነፃ ያወጣል። (መክብብ 9:5, 10) ሰዎች በዚያ ፋንታ ሙታን ስላላቸው እውነተኛ ተስፋ ይኸውም በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ስለተገኘው የትንሣኤ ተስፋ በማወቅ ልባቸው በአመስጋኝነት ስሜት እንዲሞላ ያደርጋል። (ማቴዎስ 20:28፤ ሥራ 24:15፤ ሮሜ 6:23) የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሕልም እንጀራ እየሆኑ በሚቀሩት ፖለቲካዊ ተስፋዎች ላይ መታመን ከሚያመጣው ተስፋ መቁረጥ ይጠብቃቸዋል። ይልቁንም የይሖዋ መንግሥት በሰማይ መግዛት መጀመሯንና በቅርቡም ሙሉ በሙሉ ምድርን ማስተዳደር እንደምትጀምር በማወቃቸው ልባቸው በደስታ እንዲሞላ ያደርጋል። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለውዳቂው ሥጋ ማራኪ መስለው ከሚታዩ ነገር ግን አምላክን ከሚያዋርዱና ሰዎች ከእርሱ ጋር ያላቸው ዝምድና እንዲበላሽ፣ በበሽታ እንዲጠቁና ሕይወታቸው በአጭር እንዲቀጭ ከሚያደርጉ ልማዶች ነፃ ያወጣቸዋል። በአጭር አነጋገር የአምላክ ባሪያ መሆን የሰው ባሪያ ከመሆን እጅግ የላቀ ጠቀሜታ አለው። እንዲያውም ራስን ለአምላክ መወሰን “በዚህ ዘመን” የሚጠቅመን ከመሆኑም ሌላ “በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት” እንድናገኝ ዋስትና ይሆነናል።—ማርቆስ 10:29, 30
21. የይሖዋ ምሥክሮች ራስን ለአምላክ ስለመወሰን ምን ይሰማቸዋል? ምኞታቸውስ ምንድን ነው?
21 ዛሬ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ራሱን ለአምላክ የወሰነ ብሔር አባላት የሆኑት እንደ ጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ በውልደት አይደለም። ምሥክሮቹ ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች ያሉበት ጉባኤ አባላት ናቸው። እያንዳንዱ የተጠመቀ የይሖዋ ምሥክር ወደዚህ ደረጃ የደረሰው በግለሰብ ደረጃ የመምረጥ ነፃነቱን ተጠቅሞ ራሱን በመወሰን ነው። በእርግጥ የይሖዋ ምሥክሮች ራሳቸውን መወሰናቸው አምላክን በፈቃደኛነት ለማገልገልና ከእርሱ ጋር ሞቅ ያለ ወዳጅነት ለመመሥረት አስችሏቸዋል። በኢየሱስ አማካኝነት ነፃ የወጡበትን ነፃነት ለዘላለም አጥብቀው በመያዝ ይህን አስደሳች ዝምድና ለመጠበቅ ከልባቸው ይመኛሉ።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ አምላክ እስራኤልን ‘ለርስቱ የተለየ ወገን’ አድርጎ መምረጡ አድሏዊነት አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?
◻ በክርስትና ጎዳና ራስን ለአምላክ መወሰን ነፃነትን እንደሚነፍግ ተደርጎ ሊታይ አይገባም የምትለው ለምንድን ነው?
◻ ራስን ለይሖዋ አምላክ መወሰን ጥቅሙ ምንድን ነው?
◻ ለሰው ባርያ ከመሆን የይሖዋ አገልጋይ መሆን የተሻለ የሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ለአምላክ ራስን መወሰን በውልደት የሚገኝ ነገር ነበር
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በክርስትና ጎዳና ራስን መወሰን በምርጫ የሚደረግ ነገር ነው