‘ለተረት ጆሮህን አትስጥ’
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰዎች በሚናገሩ ታሪኮችና ተሞክሮዎች የተሞላ ነው። እነዚህን ታሪኮች በማንበብ ከመደሰታችንም በላይ ጠቃሚ ትምህርቶችን እናገኝባቸዋለን። ሐዋርያው ጳውሎስ “በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና” በማለት በሮም ለነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ጽፏል።—ሮሜ 15:4
ጳውሎስ ራሱ ስላጋጠሙት ነገሮች ለሌሎች ሰዎች ተናግሯል። ጳውሎስና በርናባስ በመጀመሪያው የሚስዮናዊ ጉዟቸው መጨረሻ ላይ የሆነውን ነገር መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይናገራል፦ “በደረሱም ጊዜ [በሶርያ አንጾኪያ] ቤተ ክርስቲያኑን [ጉባኤውን አዓት] ሰብስበው እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ ለአሕዛብም የሃይማኖትን ደጅ እንደከፈተላቸው ተናገሩ።” (ሥራ 14:27) ወንድሞች በእነዚህ ተሞክሮዎች በጣም ተበረታትው እንደነበረ አያጠራጥርም።
ይሁን እንጂ ሁሉም ተሞክሮዎች የሚያንጹ አይደሉም። ጳውሎስ በመንፈስ አነሣሽነት “የአሮጊቶችን ሴቶች ጨዋታ ከሚመስለው ተረት ራቅ” ሲል ጢሞቴዎስን አስጠንቅቆት ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 4:7) ጳውሎስ ለቲቶ በጻፈው ደብዳቤ ላይም ታማኝ ክርስቲያኖች “የአይሁድን ተረትና ከእውነት ፈቀቅ የሚሉትን ሰዎች ትእዛዝ” ማዳመጥ የማይገባቸው መሆኑን ገልጿል።—ቲቶ 1:14
እውነትነት የሌላቸው እነዚህ ተረቶች ወይም አፈ ታሪኮች ምን ነበሩ? ተረት ወይም አፈ ታሪክ የሚሉትን የሁለቱንም ቃላት ትርጉም የያዘው “ሚት” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ሜቶስ ከሚለው የግሪክኛ ቃል የመጣ ነው። ዘ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ ይህን ቃል “ከእውነታ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለውን [ሃይማኖታዊ] ተረት” ያመለክታል በማለት ያትታል።
በጳውሎስ ዘመን የነበረው ዓለም እንዲህ ባሉት ተረቶች የተሞላ ነበር። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን ከጳውሎስ በፊት ከሁለት መቶ ከሚበልጡ ዓመታት አስቀድሞ እንደተጻፈ የሚገመተው የጦቢት አዋልድ መጽሐፍ ነው። ይህ አፈ ታሪክ የሚናገረው በሁለቱም ዓይኖቹ ላይ የወፍ ኩስ ጠብ ብሎበት ዓይነ ስውር ሆኖ ስለነበረ ጦቢት ስለተባለ ጻድቅ አይሁዳዊ ሰው ነው። እርሱም ከጊዜ በኋላ ተበድረውት ከነበሩ ሰዎች ገንዘብ እንዲሰበስብ ጦቢያስ የተባለውን ልጁን ይልከዋል። ጦቢያስ በመንገድ እየሄደ ሳለ አንድ መልአክ የነገረውን ተከትሎ የዓሣ ልብ፣ ጉበትና ሃሞት ይዞ ይሄዳል። ቀጥሎም ሰባት ጊዜ ብትዳርም ሁሉም ባሎቿ በሠርጉ ቀን ማታ በክፉ መንፈስ ስለተገደሉባት ድንግል ሆና የቆየች አንዲት መበለት ያገኛል። በመልአኩ አበረታችነት ጦቢያስ እርሷን ያገባና የዓሣውን ልብና ጉበት በእሳት በማቀጠል ጋኔኑን ያባርረዋል። በኋላም ጦቢያስ በዓሣው ሃሞት የአባቱን ዓይን ይፈውሳል።
ይህ ተረት ሐሰት መሆኑ ግልጽ ነው። የፈጠራ ታሪክና በአጉል እምነት ላይ የተመሠረተ ከመሆኑም በላይ ትክክል ያልሆነ ዘገባ ይዟል። ለምሳሌ በእስራኤል ታሪክ ውስጥ በ257 ዓመታት ልዩነት የተፈጸሙትን ማለትም የሰሜኑ ነገዶችን ማመፅና እስራኤላውያን በግዞት ወደ ነነዌ መወሰዳቸውን ጦቢት አይቶ እንደነበር ይናገራል። ይሁን እንጂ ጦቢት የሞተው በ112 ዓመቱ እንደነበረ ታሪኩ ይገልጻል።—ጦቢት 1:4, 11፤ 14:1 ዘ ጀሩሳሌም ባይብል
እንዲህ ያሉት አፈ ታሪኮች በአምላክ ታማኝ አገልጋዮች የተገለጸው “ጤናማ ቃል” ከያዘው እውነት ጋር ምንም ዝምድና የላቸውም። (2 ጢሞቴዎስ 1:13) እነዚህ አፈ ታሪኮች ለአምላክ አክብሮት በሌላቸው ሴቶች የሚነገሩትን ተረቶች የሚመስሉና ከእውነተኛው ታሪካዊ ሐቅ ጋር የሚቃረኑ የግምታዊ አስተሳሰብ ውጤት ናቸው። ክርስቲያኖች ሽሿቸው የተባሉት እነዚህን ተረቶች ነበር።
የእውነትን ቃላት ለይቶ ማወቅ
ዛሬም ተመሳሳይ ተረቶች ሞልተዋል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “[ሰዎች] ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን . . . እውነትንም ከመስማት ጆሮአቸውን ይመልሳሉ፣ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4) በአንዳንድ የምድር ክፍሎች ከሰው ባሕርይ ውጭ ስለሆኑ ድርጊቶች የሚነገሩ ተረቶች በስፋት የተሰራጩና በአብዛኛው የሚታወቁ ናቸው። ስለዚህ ሃይማኖታዊ አፈ ታሪኮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መስማማት አለመስማማታቸውን ለማወቅ ክርስቲያኖች ጥበብ በተሞላ መንገድ ‘ቃልን የሚለዩ’ መሆን አለባቸው።—ኢዮብ 12:11
ብዙዎቹ አፈ ታሪኮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይስማሙ መሆናቸው ግልጽ ነው። ለምሳሌ ያህል በአብዛኛው የዓለም ክፍል የሰው ነፍስ አትሞትም የሚለውን አስተሳሰብ የሚደግፉ ተረቶችን መስማት የተለመደ ነው። እነዚህ ተረቶች አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ሕፃን ሆኖ ይወለዳል፤ ወይም መንፈስ ወይም እንስሳ ሆኖ ይለወጣል ወይም በሌላ ቦታ ሄዶ ሰው ሆኖ ይወለዳል በማለት ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ ሰብአዊ ነፍሳት ሊሞቱ የማይችሉ ሳይሆኑ ሟቾች መሆናቸውን የአምላክ ቃል ያሳያል። (ሕዝቅኤል 18:4) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ማሰብ፣ መናገር ወይም አንዳች ነገር ማድረግ በማያስችል ሕይወት አልባነት ሁኔታ ላይ በመቃብር ውስጥ ያሉ መሆናቸውን ይናገራል። (መክብብ 9:5, 10፤ ሮሜ 6:23) ስለዚህ ነፍስ አትሞትም የሚለውን ትክክል ያልሆነ አስተሰሳብ በሚያራምዱ ተረቶች የተታለሉት ሰዎች ጳውሎስ እንዳለው ከመጽሐፍ ቅዱስ “ጤናማ ቃል” “ፈቀቅ” ብለዋል።
ከሰው ባሕርይ ውጭ የሆኑ አፈ ታሪኮች
ሌሎች ተረቶች በአስማተኞችና በጠንቋዮች ሥራ ላይ ያተኮሩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች አስማተኞችና ጠንቋዮች ከፍተኛ ኃይል እንዳላቸውና በሆዳቸው የሚሳቡ እንስሳት፣ ዝንጀሮ ወይም ወፍ ለመሆን፤ ተልእኳቸውን ለመፈጸም ሲሉ በአየር ላይ ለመብረር፤ ለመታየትና ለመሰወር፤ እንዲሁም በግንብ ውስጥ ለማለፍና የተቀበሩ ነገሮችን ለማየት እንደሚችሉ ተደርጎ ይነገርላቸዋል።
እንዲህ ያሉት ተረቶች በብዛት መኖራቸውና በስፋት የሚታመንባቸው መሆኑ በክርስቲያን ጉባኤ ያሉት አንዳንዶች ጭምር ተረቶቹ እውነት ናቸው ብለው ወደ ማመኑ እንዲያዘነብሉ ተጽዕኖ አድርጎባቸው ይሆናል። እነርሱም እንዲህ የመሰሉትን ነገሮች ሰዎች ማድረግ ባይችሉም ከሰው በላይ የሆነ ኃይል ካለቸው መንፈሳዊ ፍጡራን ይኸውም ከአጋንንት ኃይል ያገኙ ሰዎች ሊያደርጉ ይችላሉ ብለው ያስቡ ይሆናል። እንዲህ ብለው ለመደምደም መሠረት አድርገው የወሰዱት በ2 ተሰሎንቄ 2:9, 10 ላይ [በ1980 ትርጉም] እንዲህ የሚለውን ሐሳብ ይመስላል፦ “የዓመፅ ሰው የሚመጣው በሰይጣን ኀይል አሳሳች ተአምራትንና ምልክቶችን፣ አስደናቂ ነገሮችንም በማድረግ ነው፤ እንዲሁም በሚጠፉት ሰዎች ላይ ልዩ ልዩ ክፋ ማታለል በማድረግ ነው፤ እነዚህ ሰዎች የሚጠፉትም ለመዳን የሚያበቃቸውን እውነት ስላልወደዱ ነው።”
ይህ ጥቅስ ሰይጣን ከሰው ችሎታ በላይ የሆነ ሥራ ማከናወን የሚችል መሆኑን የሚገልጽ ቢሆንም ‘የሐሰተኛ ምልክቶችና ድንቆች’ እንዲሁም ‘በዓመፃ የመታለል’ ምንጭ መሆኑንም ይጠቅሳል። መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለሙን ሁሉ የሚያስተው” ዋናው አታላይ ሰይጣን መሆኑን ብዙ ጊዜ ይገልጻል። (ራእይ 12:9) ሰይጣን ሰዎች እውነት ያልሆኑ ነገሮችን እንዲያምኑ በማድረግ የተዋጣለት ነው።
በዚህ ምክንያት በመናፍስታዊ ሥራ ወይም በጥንቆላ የሚካፈሉ ሰዎች የሚናገሯቸው ነገሮችም ቢሆኑ ብዙ ጊዜ ሊታመኑ የማይችሉ ናቸው። እንዲህ ያሉት ሰዎች አንዳንድ ነገሮችን እንዳዩ፣ እንደሰሙ ወይም አንዳንድ ሁኔታዎች እንዳጋጠሟቸው ከልብ ያምኑ ይሆናል፤ ሆኖም እንደሚሉት አላጋጠማቸውም። ለምሳሌ ከሞቱ ሰዎች መናፍስት ጋር እንደተነጋገሩ አድርገው የሚያስቡ ሰዎች አሉ፤ ሆኖም የሰይጣናዊ ተንኮል ሰለባዎች በመሆናቸው ተሳስተዋል፣ ተታለዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን “ወደ ዝምታ ዓለም” የወረዱ መሆናቸውን ይናገራል።—መዝሙር 115:17 የ1980 ትርጉም
ዲያብሎስ በታሪኩ የቱን ያህል አታላይ እንደነበረ ሲታይ በማንኛውም መንገድ የሚነገሩት ከሰው ባሕርይ ውጭ የሆኑትን ታሪኮች በጥርጣሬ ልናያቸው ይገባል። አብዛኞቹ ዘወትር ተደጋግመው በመነገር የተጋነኑና በአጉል እምነቶች ላይ የተመሠረቱ ግምታዊ የፈጠራ ታሪኮች ናቸው።
እንዲህ ያሉትን ተረቶች ማሰራጨት የሐሰት አባት የሆነውን የሰይጣን ዲያብሎስን ፍላጎት ያራምዳል። (ዮሐንስ 8:44) እነዚህ ተረቶች ወይም አፈ ታሪኮች በይሖዋ ፊት አጸያፊ ለሆነው ለጥንቆላ ሥራ ፍላጎትን የሚቀሰቅሱ ናቸው። (ዘዳግም 18:10–12) ሰዎችን በፍርሃትና በአጉል እምነት ተብትበው ያጠምዳሉ። እንግዲያው ጳውሎስ እነዚህን የውሸት ‘ተረቶች ወይም አፈ ታሪኮች እንዳያደምጡ’ ክርስቲያኖችን መምከሩ አያስደንቅም።—1 ጢሞቴዎስ 1:3, 4
የአጋንንትን ምስክርነት አለመቀበል
የሚነገሩት ታሪኮች እውነተኛ መስለው ቢታዩስ? አንዳንድ ጊዜ መናፍስት ወይም መናፍስት ያሉባቸው ሰዎች የይሖዋን የበላይነትና የምስክሮቹን እውነተኝነት አምነው መቀበላቸውን የሚገልጹ ተሞክሮዎች አሉ። ክርስቲያኖች እንዲህ ያሉ ታሪኮችን ለሌሎች ማውራት ይገባቸዋልን?
አይገባቸውም። ርኩሳን መናፍስት ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ እየጮሁ በተናገሩ ጊዜ “እንዳይገልጡትም በጣም አዘዛቸው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ይናገራል። (ማርቆስ 3:12) በተመሳሳይም የሟርት ጋኔን ያደረባት አንዲት ልጃገረድ ጳውሎስንና በርናባስን “የልዑል አምላክ ባሪያዎች” እንደሆኑና “የመዳንን መንገድ” የሚሰብኩ መሆናቸውን እንድትናገር ርኩስ መንፈሱ ገፋፍቷታል። (ሥራ 16:16–18) ኢየሱስም ሆነ ጳውሎስ ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ከጻፉት ሰዎች አንዳቸውም አጋንንት ስለ አምላክ ዓላማ ወይም ስለ ምርጥ አገልጋዮቹ ምስክርነት እንዲሰጡ አልፈቀዱላቸውም።
ኢየሱስ ክርስቶስም ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በመንፈሳዊ ዓለም ይኖር እንደነበረ ማስታወስ ያስፈልጋል። ሰይጣንን በግል ያውቀው ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ስለ ሰይጣን ሥራዎች የሚገልጹ ታሪኮችን በመንገር ደቀ መዛሙርቱ እንዲስቁ አላደረገም ወይም ዲያብሎስ ማድረግ ስለሚችላቸውና ስለማይችላቸው ነገሮች ዝርዝር ጉዳዮችን አላወራላቸውም። ሰይጣንና አጋንንቱ የክርስቶስ ወዳጆች አልነበሩም። እነርሱ ከአምላክ ቤተሰብ የተባረሩ፣ ዓመፀኞች፣ ቅዱስ የሆነውን ነገር የሚጠሉና የአምላክ ጠላቶች ናቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ ማወቅ የሚገባንን ነገር ይነግረናል። አጋንንት እነማን መሆናቸውን፣ ሰዎችን እንዴት እንደሚያስቱና ከአጋንንት መራቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስረዳል። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋና ኢየሱስ ከአጋንንት የበለጡ ኃያላን እንደሆኑ ያሳያል። በተጨማሪም ይሖዋን በታማኝነት ካገለገልነው ክፉ መናፍስት ጉዳት ሊያደርሱብን እንደማይችሉ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል።—ያዕቆብ 4:7
እንግዲያው ክርስቲያኖች የአምላክ ተቃዋሚዎችን ፍላጎት ከማራመድ በስተቀር ምንም ጥቅም ለሌላቸውና ከእውነት ለራቁት ተረቶች ጆሯቸውን የማይሰጡበት ጥሩ ምክንያት አላቸው። ኢየሱስ ‘ለእውነት እንደመሰከረ’ ሁሉ ዛሬ ያሉት ተከታዮቹም እንዲሁ ያደርጋሉ። (ዮሐንስ 18:37) “እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ . . . እነዚህን አስቡ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መከተላቸው ጥሩ ነው።—ፊልጵስዩስ 4:8
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነተኛ ክርስቲያኖች ማንኛውንም ስውርና ምሥጢራዊ የጥንቆላ ሥራ አጥብቀው መሸሽ አለባቸው