አባትና ሽማግሌ ሁለቱንም ኃላፊነቶች መወጣት
“አንድ ሰው የገዛ ቤተሰቡን እንዴት እንደሚያስተዳድር ካላወቀ የአምላክን ጉባኤ እንዴት ማስተዳደር ይችላል?”—1 ጢሞቴዎስ 3:5 አዓት
1, 2. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ነጠላ የሆኑ የበላይ ተመልካቾችና ልጆች የሌሏቸው ያገቡ የበላይ ተመልካቾች ወንድሞቻቸውን ለማገልገል የቻሉት እንዴት ነበር? (ለ) አቂላና ጵርስቅላ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ አያሌ ባለ ትዳር የበላይ ተመልካቾች ምሳሌ የሚሆኑት እንዴት ነው?
በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የነበሩ የበላይ ተመልካቾች ነጠላ ወንዶች ወይም ልጆች የሌሏቸው ወይም የልጆች አባት የሆኑ ባለ ትዳር ወንዶች ሊሆኑ ይችሉ ነበር። ከእነዚያ ክርስቲያኖች አንዳንዶቹ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ መልእክቱ በምዕራፍ 7 ላይ የሰጣቸውን ምክር ለመከተል በመቻላቸው ነጠላ ሆነው እንደኖሩ አያጠራጥርም። ኢየሱስ “ስለ መንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ” በማለት ገልጿል። (ማቴዎስ 19:12) እንደ ጳውሎስ፣ ምናልባት ደግሞ እንደ አንዳንዶቹ ተጓዥ ጓደኞቹ ያሉት ነጠላ ወንዶች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እየተዘዋወሩ ወንድሞቻቸውን ለመርዳት የሚያስችል ነፃነት ነበራቸው።
2 መጽሐፍ ቅዱስ በርናባስ፣ ማርቆስ፣ ሲላስ፣ ሉቃስ፣ ጢሞቴዎስና ቲቶ ነጠላ ስለ መሆናቸው ወይም ስለ አለመሆናቸው የሚገልጸው ነገር የለውም። ባለ ትዳሮች የነበሩ ከሆኑ የቤተሰብ ኃላፊነቶቻቸው ወደ ተለያዩ የሥራ ምድቦች ለመሄድ ነፃ እንዲሆኑ የሚያስችሉ እንደነበሩ ግልጽ ነው። (ሥራ 13:2፤ 15:39-41፤ 2 ቆሮንቶስ 8:16, 17፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:9-11፤ ቲቶ 1:5) ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሲጓዙ ሚስቶቻቸውን ይዘው ይሄዱ እንደነበሩት እንደ ጴጥሮስና “ሌሎች ሐዋርያት” ከሚስቶቻቸው ጋር አብረው ሊሄዱ ይችሉ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 9:5) ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመዘዋወር ፈቃደኞች የነበሩት አቂላና ጵርስቅላ ለባለ ትዳሮች ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው። ጳውሎስን ተከትለው ከቆሮንቶስ ወደ ኤፌሶን፣ ከዚያ ወደ ሮም ከተሻገሩ በኋላ እንደገና ወደ ኤፌሶን ተመልሰዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ልጆች የነበራቸው ስለ መሆኑ ወይም ስላለመሆኑ የሚገልጸው ነገር የለም። ለወንድሞቻቸው ያበረከቱት ከፍተኛ አገልግሎት ‘ከሁሉም የአሕዛብ ጉባኤዎች’ አድናቆት አትርፎላቸዋል። (ሮሜ 16:3-5፤ ሥራ 18:2, 18፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:19) በዛሬው ጊዜ እንደ አቂላና ጵርስቅላ ሌሎች ጉባኤዎችን መርዳት የሚችሉ ብዙ ባልና ሚስት እንደሚኖሩ አያጠራጥርም፤ ምናልባትም ይህን እርዳታ የሚያበረክቱት የምሥራቹ አገልጋዮች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ በመዛወር ሊሆን ይችላል።
አባትና ሽማግሌ
3. አብዛኞቹ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ሽማግሌዎች ቤተሰብ የነበራቸው ያገቡ ወንዶች እንደ ነበሩ የሚያሳየው ምንድን ነው?
3 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ አብዛኞቹ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ልጆች ያሏቸው ባለ ትዳሮች የነበሩ ይመስላል። ጳውሎስ ‘ለበላይ ተመልካችነት ኃላፊነት ከሚጣጣር ሰው’ የሚፈለጉትን ብቃቶች በሚዘረዝርበት ወቅት እንዲህ ዓይነቱ ክርስቲያን ‘ቤተሰቡን በመልካም ሁኔታ የሚያስተዳድር፣ ልጆቹ በጭምትነት ሁሉ የሚገዙለት’ መሆን ይኖርበታል በማለት ገልጿል።—1 ጢሞቴዎስ 3:1, 4
4. ልጆች ካላቸው ያገቡ ሽማግሌዎች ምን ይፈለጋል?
4 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው አንድ የበላይ ተመልካች ልጆችን መውለድ ይቅርና የማግባት ግዴታ እንኳ የለበትም። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን ያገባ ከሆነ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን እንዲችል በሚስቱ ላይ ያለውን የራስነት ሥልጣን በአግባቡና ፍቅራዊ በሆነ መንገድ መጠቀም አለበት። ከዚህም በተጨማሪ ልጆቹን በትክክል የማስተዳደር ብቃት እንዳለው በተግባር ማሳየት ይኖርበታል። (1 ቆሮንቶስ 11:3፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:12, 13) አንድ ወንድም ቤተሰቡን በማስተዳደር ረገድ አንድ ዓይነት ከባድ ድክመት ካለበት በጉባኤው ውስጥ ልዩ መብቶችን ለማግኘት ብቃት አይኖረውም። ለምን? ጳውሎስ “አንድ ሰው የገዛ ቤተሰቡን እንዴት እንደሚያስተዳድር ካላወቀ የአምላክን ጉባኤ እንዴት ማስተዳደር ይችላል?” በማለት ገልጿል። (1 ጢሞቴዎስ 3:5 አዓት) የገዛ ቤተሰቦቹ ለእሱ የበላይ ጥበቃ ለመገዛት ፈቃደኛ ካልሆኑ ሌሎች ምን ምላሽ ይሰጣሉ?
“አማኝ ልጆች ያሉት”
5, 6. (ሀ) ጳውሎስ ልጆችን በተመለከተ ለቲቶ የጠቀሰው ብቃት ምንድን ነው? (ለ) ልጆች ያሏቸው ሽማግሌዎች ምን ይጠበቅባቸዋል?
5 ጳውሎስ በቀርጤስ በሚገኙ ጉባኤዎች ውስጥ የበላይ ተመልካቾችን እንዲሾም ለቲቶ መመሪያ ሲሰጥ የሚከተሉትን ብቃቶች ጠቅሶ ነበር፦ “ከክስ ነፃ የሆነ፣ የአንዲት ሚስት ባል የሆነ፣ በብልግናም ሆነ በሥርዓት አልበኛነት የማይከሰሱ አማኝ ልጆች ያሉት ሰው ካለ ሹመው። አንድ የበላይ ተመልካች እንደ አምላክ መጋቢ ከክስ ነፃ የሆነ መሆን አለበት።” “አማኝ ልጆች ያሉት” የሚለው የብቃት መመዘኛ ምን ትርጉም አለው?—ቲቶ 1:6, 7 አዓት
6 “አማኝ ልጆች” የሚለው አነጋገር ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው የተጠመቁ ወጣቶችን ወይም ራስን ለአምላክ ለመወሰንና ለመጠመቅ ወደሚያስችል ደረጃ እድገት በማድረግ ላይ የሚገኙ ልጆችን ያመለክታል። የጉባኤ አባላት የሽማግሌዎች ልጆች አብዛኛውን ጊዜ ጥሩ ጠባይ እንደሚኖራቸውና ታዛዦች እንደሚሆኑ ይጠብቃሉ። አንድ ሽማግሌ የልጆቹን እምነት ለማጠንከር የሚችለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርበታል። ንጉሥ ሰሎሞን “ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፣ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም” ብሎ ጽፏል። (ምሳሌ 22:6) ሆኖም እንዲህ ዓይነቱን ሥልጠና ያገኘው ወጣት ይሖዋን ለማገልገል ባይፈልግ ወይም ከባድ ኃጢአት ቢሠራስ?
7. (ሀ) ምሳሌ 22:6 ሁልጊዜ ሊሠራ የሚችል ደንብ እንዳልሆነ ግልጽ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የአንድ ሽማግሌ ልጅ ይሖዋን ለማገልገል ባይፈልግ ሽማግሌው ወዲያውኑ መብቶቹን የማያጣው ለምንድን ነው?
7 ከላይ የተገለጸው ምሳሌ ሁልጊዜ ሊሠራ የሚችል ደንብ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ይህ ደንብ የነፃ ምርጫን ሥርዓት አይጻረርም። (ዘዳግም 30:15, 16, 19) አንድ ወንድ ልጅ ወይም ሴት ልጅ በግላቸው በኃላፊነት በሚጠየቁበት ዕድሜ ላይ ሲደርሱ ራስን መወሰንንና ጥምቀትን በተመለከተ ውሳኔ ማድረግ ያለባቸው እሱ ወይም እሷ ናቸው። አንድ ሽማግሌ አስፈላጊውን መንፈሳዊ እርዳታ፣ መመሪያና ተግሣጽ በተገቢ ሁኔታ ቢሰጥም እንኳ ልጁ ይሖዋን ለማገልገል ባይመርጥ አባትየው ከበላይ ተመልካችነት ወዲያውኑ እንዲወርድ አይደረግም። በሌላ በኩል ደግም አንድ ሽማግሌ በቤት ውስጥ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ቢኖሩትና እነዚህ ልጆች አንድ በአንድ በመንፈሳዊ እየታመሙ ችግር ውስጥ ቢገቡ “የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር” ተደርጎ ላይታይ ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 3:4) ዋናው ነገር አንድ የበላይ ተመልካች ‘በብልግናም ሆነ በሥርዓት አልበኛነት የማይከሰሱ አማኝ ልጆች’ እንዲኖሩት የሚችለውን ሁሉ እያደረገ እንዳለ በግልጽ መታየት ይኖርበታል።a
“ያላመነች ሚስት ያለችው”
8. አንድ ሽማግሌ የማታምን ሚስቱን እንዴት መያዝ ይኖርበታል?
8 ጳውሎስ የማያምኑ ሴቶችን ያገቡ ክርስቲያኖችን በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከወንድሞች ወገን ያላመነች ሚስት ያለችው ቢኖር እርስዋም ከእርሱ ጋር ልትቀመጥ ብትስማማ፣ አይተዋት፤ . . . ያላመነችም ሚስት በባልዋ ተቀድሳለች፤ አለዚያ ልጆቻችሁ ርኵሳን ናቸው፤ አሁን ግን የተቀደሱ ናቸው። . . . አንተ ሰው፣ ሚስትህን ታድን እንደ ሆንህ ምን ታውቃለህ?” (1 ቆሮንቶስ 7:12-14, 16) እዚህ ላይ የገባው “ያላመነች” የሚለው ቃል የሚያመለክተው ምንም ሃይማኖታዊ እምነት የሌላትን ሚስት ሳይሆን ራሷን ለይሖዋ ያልወሰነች ሴትን ነው። አይሁዳዊ ወይም ደግሞ አረማዊ አማልክት የምታመልክ ልትሆን ትችል ነበር። በዛሬው ጊዜ አንድ ሽማግሌ የተለየ ሃይማኖት ያላት፣ ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልም የምትል ወይም አምላክ የለም ባይ የሆነች የማታምን ሚስት ትኖረው ይሆናል። እሷ ከእሱ ጋር ለመኖር ፈቃደኛ ከሆነች በእምነት ከእሱ የተለየች በመሆኗ ብቻ ሊተዋት አይገባም። እሷን ለማዳን ተስፋ በማድረግ ‘ለተሰባሪ ዕቃ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ለሴትነቷ አክብሮት በማሳየት ከእሷ ጋር በእውቀት መኖር’ አለበት።—1 ጴጥሮስ 3:7 አዓት፤ ቆላስይስ 3:19
9. ባልም ሆነ ሚስት ልጆቻቸውን የየራሳቸውን ሃይማኖት እንዲያስተምሩ ሕጉ መብት በሚሰጥባቸው አገሮች ውስጥ አንድ ሽማግሌ ምን ማድረግ አለበት? ይህስ መብቶቹን የሚነካበት እንዴት ነው?
9 አንድ የበላይ ተመልካች ልጆች ካሉት እነሱን “በጌታ ምክርና በተግሣጽ” በማሳደግ በባልነቱና በአባትነቱ ያለውን የራስነት ሥልጣን በአግባቡ ይሠራበታል። (ኤፌሶን 6:4) በብዙ አገሮች ሕጉ ለሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች ለልጆቻቸው የራሳቸውን ሃይማኖታዊ ትምህርት የመስጠት መብት ይፈቅድላቸዋል። በዚህ ረገድ ሚስትየዋ መብቷን ተጠቅማ ለልጆቿ የራሷን ሃይማኖታዊ ትምህርቶችና ልማዶች ለማሳወቅ ልትጠይቅ ትችላለች፤ ይህም እነሱን ወደ ቤተ ክርስቲያኗ መውሰድን ሊጨምር ይችላል።b እርግጥ ልጆቹ በሐሰት ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ አለመሳተፍን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነ ሕሊናቸው መመራት ይኖርባቸዋል። አባትየው የቤተሰብ ራስ እንደ መሆኑ መጠን መብቱን ተጠቅሞ ልጆቹን ሊያስጠናና በሚቻልበት ወቅት በመንግሥት አዳራሽ ወደሚደረጉት ስብሰባዎች ሊወስዳቸው ይገባል። ልጆቹ የራሳቸውን ውሳኔ ማድረግ የሚችሉበት ዕድሜ ላይ ሲደርሱ የትኛውን መንገድ እንደሚመርጡ ራሳቸው ይወስናሉ። (ኢያሱ 24:15) ሽማግሌው የቄሣር ሕግ በሚፈቅድለት መጠን ለልጆቹ በአግባቡ የእውነትን መንገድ እንዳስተማረ ሌሎች ሽማግሌዎችና የጉባኤው አባላት ከተመለከቱ ከበላይ ተመልካችነት እንዲወርድ አይደረግም።
“የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር”
10. አንድ የቤተሰብ ኃላፊ ሽማግሌ ከሆነ ተቀዳሚ ኃላፊነቱ ምንድን ነው?
10 ሌላው ቀርቶ ሚስቱ ክርስቲያን የእምነት ጓደኛው የሆነች ልጆች ያሉት ሽማግሌም እንኳ ጊዜውንና ትኩረቱን ለሚስቱ፣ ለልጆቹና ለጉባኤ ኃላፊነቶቹ በተገቢው መንገድ ማከፋፈል ቀላል አይሆንለትም። ቅዱሳን ጽሑፎች አንድ ክርስቲያን አባት ሚስቱንና ልጆቹን የመንከባከብ ግዴታ እንዳለበት በግልጽ ይናገራሉ። ጳውሎስ “ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ [“የሚያስፈልጋቸውን ነገር የማያቀርብ፣” አዓት] ማንም ቢሆን፣ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው” በማለት ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ጳውሎስ በዚሁ መልእክት ላይ ለበላይ ተመልካችነት የሚታጩ ያገቡ ወንዶች ቀደም ሲል ጥሩ ባሎችና አባቶች መሆናቸውን ያሳዩ መሆን እንዳለባቸው ገልጿል።—1 ጢሞቴዎስ 3:1-5
11. (ሀ) አንድ ሽማግሌ ‘ለእርሱ ለሆኑት የሚያስፈልገውን የሚያቀርበው’ በምን መንገዶች ነው? (ለ) አንድ ሽማግሌ የጉባኤ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ይህ ሊረዳው የሚችለው እንዴት ነው?
11 አንድ ሽማግሌ ለራሱ ቤተሰብ በቁሳዊ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊና በስሜት ረገድም ጭምር ‘የሚያስፈልጋቸውን ማቅረብ’ ይኖርበታል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “በስተ ሜዳ ሥራህን አሰናዳ፣ ስለ አንተ በእርሻ አዘጋጃት፤ ከዚያም በኋላ ቤትህን ሥራ” ሲል ጽፏል። (ምሳሌ 24:27) ስለዚህ አንድ የበላይ ተመልካች የሚስቱንና የልጆቹን ቁሳዊ፣ ስሜታዊና የመዝናኛ ፍላጎት ከማሟላቱ በተጨማሪ በመንፈሳዊም ሊያንጻቸው ይገባል። ይህም ጊዜ መመደብን ይጠይቃል፤ ለጉባኤ ጉዳዮች ሊያውል የማይችለውን ጊዜ መጠቀም ያስፈልገዋል። ይሁን እንጂ ይህ ለቤተሰብ ደስታና መንፈሳዊነት መጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። ቤተሰቡ በመንፈሳዊ ሲጠነክር ሽማግሌው የቤተሰብ ችግሮችን ለመፍታት ብዙ ጊዜ ማጥፋት ላያስፈልገው ይችላል። ይህም የጉባኤ ጉዳዮችን ለማከናወን ተጨማሪ አጋጣሚዎችን እንዲያገኝ ያስችለዋል። ጥሩ ባልና ጥሩ አባት በመሆን ያሳየው ምሳሌነት ለጉባኤው መንፈሳዊ ጠቀሜታ ያበረክታል።—1 ጴጥሮስ 5:1-3
12. ልጆች ያሏቸው ሽማግሌዎች ጥሩ ምሳሌ መሆን ያለባቸው በየትኛው የቤተሰብ ጉዳይ ረገድ ነው?
12 አንድን ቤተሰብ በመልካም ሁኔታ ማስተዳደር የቤተሰብ ጥናት ለመምራት ፕሮግራም ማውጣትን ይጨምራል። ጠንካራ ቤተሰቦች ጠንካራ ጉባኤ ስለሚያስገኙ ሽማግሌዎች በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ መሆናቸው እጅግ አስፈላጊ ነው። አንድ የበላይ ተመልካች ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር የሚያጠናበት ጊዜ እስኪያጣ ድረስ ጊዜው ሁሉ በሌሎች የአገልግሎት መብቶች መያዝ የለበትም። እንዲህ ከሆነ ፕሮግራሙን እንደገና መመርመር ይኖርበታል። ለሌሎች ጉዳዮች የሚያውለውን ጊዜ እንደገና ማጤን ወይም መቀነስ አልፎ ተርፎም አንዳንድ ጊዜ የተወሰኑ መብቶቹን መተው ሊያስፈልገው ይችላል።
ሚዛናዊ የበላይ ጥበቃ
13, 14. “ታማኝና ልባም ባሪያ” የቤተሰብ ራስ ለሆኑ ሽማግሌዎች ምን ምክር ሰጥቷል?
13 የቤተሰብና የጉባኤ ኃላፊነቶችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ስለ መወጣት ምክር ሲሰጥ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። “ታማኝና ልባም ባሪያ” ለብዙ ዓመታት ስለዚህ ጉዳይ ለሽማግሌዎች ምክር ሲሰጥ ቆይቷል። (ማቴዎስ 24:45) ከ37 ዓመታት በፊት የመስከረም 15, 1959 (የእንግሊዝኛ) መጠበቂያ ግንብ በገጽ 553 እና 554 ላይ የሚከተለውን ምክር ለግሶ ነበር፦ “ይህ ሁሉ በጊዜ አጠቃቀማችን ረገድ ሚዛናዊ የመሆን ጉዳይ አይደለምን? ይህን ሚዛን ለመጠበቅ ለገዛ ቤተሰባችሁ ጥቅሞች ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይገባችኋል። ይሖዋ አምላክ አንድ ሰው የገዛ ቤተሰቡን መዳን ሳይከታተል ወንድሞቹና ሌሎች ሰዎች እንዲድኑ ለመርዳት ጊዜውን ሁሉ ለጉባኤ ሥራ እንዲያውል እንደማይጠብቅበት የታወቀ ነው። የአንድ ሰው ተቀዳሚ ኃላፊነት ሚስቱና ልጆቹ ናቸው።”
14 መጠበቂያ ግንብ 11-107 በገጽ 4 ላይ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቶ ነበር፦ “ከቤተሰብ ጋር በመስክ አገልግሎት መሳተፍ ያቀራርባል። ይሁን እንጂ ልጆች ልዩ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ጊዜህንና ስሜትህን መሥዋዕት ማድረግ ይኖርብሃል። ስለዚህ ‘የራስህ ለሆኑት’ መንፈሳዊ፣ ስሜታዊና ሥጋዊ እንክብካቤ እያደረግህ ለ . . . ጉባኤ ኃላፊነቶች ምን ያህል ጊዜ ልታጠፋ እንደምትችል ለመወሰን ሚዛናዊ መሆን አለብህ። [አንድ ክርስቲያን] ‘ለአምላክ ያደሩ መሆንን በመጀመሪያ [በቤቱ] ውስጥ መማር’ ይኖርበታል። (1 ጢሞቴዎስ 5:4, 8)”
15. አንዲት ሚስትና ልጆች ያሉት ሽማግሌ ጥበብና ማስተዋል የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?
15 አንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌ “ቤት በጥበብ ይሠራል፣ በማስተዋልም ይጸናል” በማለት ይገልጻል። (ምሳሌ 24:3) አዎን፣ አንድ የበላይ ተመልካች ቤተሰቡን እያጠናከረ ቲኦክራሲያዊ ግዴታዎቹን ለመፈጸም እንዲችል ጥበብና ማስተዋል ያስፈልገዋል። ቅዱስ ጽሑፉ ቤተሰቡንና የጉባኤ ኃላፊነቶቹን የሚመለከቱ ከአንድ በላይ የሆኑ የበላይ ጥበቃ መስኮች እንዳሉት ይናገራል። በእነዚህ ሁለት መስኮች ረገድ ሚዛኑን ለመጠበቅ ማስተዋል ያስፈልገዋል። (ፊልጵስዩስ 1:9, 10) ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች ለመወሰን ጥበብ ያስፈልገዋል። (ምሳሌ 2:10, 11) ሆኖም የጉባኤ ኃላፊነቶቹን ለማከናወን የቱንም ያህል ኃላፊነት የሚሰማው ቢሆንም ባልና አባት እንደ መሆኑ መጠን አምላክ የሰጠው ተቀዳሚ ኃላፊነት ቤተሰቡን መንከባከብና ማዳን እንደሆነ መገንዘብ ይኖርበታል።
ጥሩ አባቶችና ጥሩ ሽማግሌዎች
16. አንድ ሽማግሌ የአባትነት ኃላፊነት ጭምር ካለው ምን ጥቅም ያገኛል?
16 ጥሩ ጠባይ ያላቸው ልጆች ያሉት ሽማግሌ እሴት ነው። ቤተሰቡን በጥሩ ሁኔታ መንከባከብ ከተማረ በጉባኤ ውስጥ ያሉትን ሌሎች ቤተሰቦች ለመርዳት ችሎታ ይኖረዋል። ችግሮቻቸውን በተሻለ መንገድ ከመረዳቱም በላይ የራሱን ተሞክሮ የሚያንጸባርቅ ምክር ሊሰጥ ይችላል። ደስ የሚለው በመላው ዓለም በሺህ የሚቆጠሩ ሽማግሌዎች የባልነት፣ የአባትነትና የበላይ ተመልካችነት ኃላፊነቶቻቸውን በጥሩ ሁኔታ በማከናወን ላይ ናቸው።
17. (ሀ)አባትና ሽማግሌ የሆነ ሰው ፈጽሞ መርሳት የማይኖርበት ነገር ምንድን ነው? (ለ) ሌሎች የጉባኤ አባላት ችግሩን እንደተረዱለት ማሳየት የሚኖርባቸው እንዴት ነው?
17 አንድ የቤተሰብ ኃላፊነት ያለበት ሰው ሽማግሌ እንዲሆን ከተፈለገ ሚስቱንና ልጆቹን ችላ ሳይል በጉባኤ ውስጥ ያሉትን ሌሎች ሰዎች ለመርዳት እንዲችል ሥራዎቹን በሚገባ ማደራጀት የሚችል የጎለመሰ ክርስቲያን መሆን ይኖርበታል። የእረኝነት ሥራው ከቤት እንደሚጀምር በጭራሽ መርሳት የለበትም። አንዲት ሚስትና ልጆች ያሏቸው ሽማግሌዎች የቤተሰብና የጉባኤ ኃላፊነት እንዳለባቸው በመገንዘብ የጉባኤው አባላት አለአግባብ ጊዜያቸውን ላለማጥፋት ይጥራሉ። ለምሳሌ ያህል በሚቀጥለው ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት የሚወስደው ልጅ ያለው ሽማግሌ ከምሽት ስብሰባዎች በኋላ አዘውትሮ ጥቂት ለመቆየት አይችል ይሆናል። ሌሎች የጉባኤው አባሎች ይህን ተረድተው አሳቢነት ሊያሳዩት ይገባል።—ፊልጵስዩስ 4:5
ሽማግሌዎቻችንን ልንወዳቸው ይገባል
18, 19. (ሀ) በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 7 ላይ ያደረግነው ምርምር ምን እንድንገነዘብ አስችሎናል? (ለ) እንደነዚህ ያሉትን ክርስቲያን ወንዶች እንዴት መመልከት ይኖርብናል?
18 ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈላቸው የመጀመሪያ መልእክት በምዕራፍ 7 ላይ ያደረግነው ምርምር ብዙ ነጠላ ወንዶች የጳውሎስን ምክር ተከትለው የመንግሥቱን ጥቅሞች ለማራመድ ነፃነታቸውን እየተጠቀሙበት እንደሆነ ለመረዳት አስችሎናል። በተጨማሪም ለሚስቶቻቸው ተገቢውን ትኩረት በማድረግ በአውራጃዎች፣ በወረዳዎች፣ በጉባኤዎችና በመጠበቂያ ግንብ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ ጥሩ የበላይ ተመልካቾች ሆነው የሚያገለግሉ ልጆች የሌሏቸው ብዙ ባለ ትዳር ወንድሞች አሉ። ሚስቶቻቸው ያሳዩት ትብብርም የሚያስመሰግን ነው። በመጨረሻም ለሚስቶቻቸውና ለልጆቻቸው ፍቅራዊ እንክብካቤ ከማድረጋቸውም በላይ አሳቢ ሽማግሌዎች ሆነው ወንድሞቻቸውን የሚያገለግሉ ብዙ አባቶች ወደ 80,000 በሚጠጉት የይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤዎች ውስጥ እንደሚገኙ ሳንጠቅስ አናልፍም።—ሥራ 20:28
19 ሐዋርያው ጳውሎስ “በመልካም የሚያስተዳድሩ ሽማግሌዎች፣ ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙት፣ እጥፍ ክብር ይገባቸዋል” ሲል ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 5:17) አዎን፣ በቤታቸውና በጉባኤያቸው በጥሩ ሁኔታ የሚያስተዳድሩ ሽማግሌዎች የእኛ ፍቅርና አክብሮት ሊቸራቸው ይገባል። በእርግጥም ‘እነሱን የሚመስሉትን ማክበር’ ይኖርብናል።—ፊልጵስዩስ 2:29
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
ለክለሳ ያህል
◻ በመጀሪያው መቶ ዘመን እዘአ የነበሩት አብዛኞቹ ሽማግሌዎች ልጆች እንደነበሯቸው እንዴት እናውቃለን?
◻ ልጆች ያሏቸው ያገቡ ሽማግሌዎች ምን ይፈለግባቸዋል?
◻ “አማኝ ልጆች ያሉት” ማለት ምን ማለት ነው? ሆኖም የአንድ ሽማግሌ ልጆች ይሖዋን ለማገልገል ባይፈልጉ ምን ይደረጋል?
◻ አንድ ሽማግሌ ‘ለእሱ ለሆኑት የሚስፈልጋቸውን ነገሮች ማቅረብ’ የሚኖርበት በምን በምን መንገዶች ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጠንካራ ቤተሰቦች ጠንካራ ጉባኤዎች ያስገኛሉ