-
‘ከወትሮው የበለጠ ትኩረት ስጡ’መጠበቂያ ግንብ—2002 | መስከረም 15
-
-
‘ከወትሮው የበለጠ ትኩረት ስጡ’
“ከሰማናቸው ነገሮች ምናልባት እንዳንወሰድ ከወትሮው የበለጠ ትኩረት መስጠት ይገባናል።”—ዕብራውያን 2:1 NW
1. የሐሳብ መከፋፈል እንዴት ለአደጋ ሊዳርግ እንደሚችል ግለጽ።
ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ በየዓመቱ 37,000 የሚሆኑ ሰዎች በመኪና አደጋ ይሞታሉ። አሽከርካሪዎች ይበልጥ በጥንቃቄ ቢያሽከረክሩ ኖሮ አብዛኞቹ ሰዎች ለሞት ባልተዳረጉ ነበር ሲሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። አንዳንድ አሽከርካሪዎች መንገድ ላይ የተለጠፉ ምልክቶችና የንግድ ማስታወቂያዎች ሲመለከቱ ወይም በተንቀሳቃሽ ስልክ ሲያወሩ ትኩረታቸው ይሰረቃል። መኪና እያሽከረከሩ ምግብ የሚበሉም አሉ። እነዚህ ሁኔታዎች ትኩረትን የሚሰርቁ በመሆናቸው ለአደጋ ሊዳርጉ ይችላሉ።
2, 3. ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ምን ምክር ሰጠ? ምክሩስ ተገቢ የነበረው ለምንድን ነው?
2 መኪና ከመፈልሰፉ ከ2, 000 ዓመታት ገደማ በፊት ሐዋርያው ጳውሎስ አንዳንድ የዕብራውያን ክርስቲያኖችን አደጋ ላይ የጣለ ትኩረት የሚሰርቅ ሁኔታ እንዳለ ተናግሮ ነበር። ጳውሎስ ከሞት የተነሣው ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክ ቀኝ የተቀመጠ በመሆኑ ከመላእክት ሁሉ የላቀ ቦታ እንደተሰጠው ጎላ አድርጎ ገልጿል። ከዚያ በመቀጠል ሐዋርያው “ስለዚህ ከሰማናቸው ነገሮች ምናልባት እንዳንወሰድ ከወትሮው የበለጠ ትኩረት መስጠት ይገባናል” ሲል ተናገረ።—ዕብራውያን 2:1 NW
3 ዕብራውያን ክርስቲያኖች ኢየሱስን በተመለከተ ‘ለሰሙት ነገር ከወትሮው የበለጠ ትኩረት መስጠት’ ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ኢየሱስ ምድርን ለቅቆ ከሄደ 30 የሚጠጉ ዓመታት አልፈውታል። አንዳንድ ዕብራውያን ክርስቲያኖች መሪያቸው ምድር ባልነበረበት በእነዚህ ጊዜያት ከእውነተኛው አምልኮ ወደ ኋላ ማለት ጀምረው ነበር። ቀድሞ ይከተሉት የነበረው የአይሁድ እምነት ትኩረታቸውን ስቦት ነበር።
የበለጠ ትኩረት መስጠት አስፈልጓቸው ነበር
4. አንዳንድ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ወደ አይሁድ እምነት ለመመለስ የተፈተኑት ለምን ሊሆን ይችላል?
4 አንድ ክርስቲያን ወደ አይሁድ እምነት እንዲመለስ የሚፈተነው ለምን ሊሆን ይችላል? በሕጉ መሠረት የሚከናወነው የአምልኮ ሥርዓት በዓይን የሚታዩ ነገሮችን አካትቶ የያዘ ነበር። ሰዎች ቤተ መቅደሱ ውስጥ ካህናት ሲያገለግሉና የሚቃጠል መሥዋዕት ሲቀርብ መመልከት ይችሉ ነበር። ይሁን እንጂ በአንዳንድ ጉዳዮች ረገድ የክርስትና እምነት ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነበር። ክርስቲያኖችም ሊቀ ካህን ያላቸው ሲሆን እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሆኖም ሊቀ ካህናቸው ለመጨረሻ ጊዜ ምድር ላይ ከታየ ሦስት አሥርተ ዓመታት አልፈዋል። (ዕብራውያን 4:14) ቤተ መቅደስም ያላቸው ቢሆንም ቅዱሱ ሥፍራ የሚገኘው በሰማይ ነው። (ዕብራውያን 9:24) በሕጉ ሥር ከሰፈረው ሥጋዊ ግርዘት በተለየ የክርስቲያኖች ግርዘት “በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ” ነው። (ሮሜ 2:29) በመሆኑም ዕብራውያን ክርስቲያኖች የክርስትና እምነት ተጨባጭ ነገር የሌለው እንደሆነ አድርገው ማሰብ ጀምረው ሊሆን ይችላል።
5. ኢየሱስ ያቋቋመው የአምልኮ ሥርዓት በሕጉ ሥር ከነበረው የላቀ መሆኑን ጳውሎስ ያሳየው እንዴት ነው?
5 ዕብራውያን ክርስቲያኖች ክርስቶስ ያቋቋመውን የአምልኮ ሥርዓት በተመለከተ መገንዘብ የሚያስፈልጋቸው አንድ ከፍተኛ ትርጉም ያዘለ ጉዳይ ነበር። አምልኮው የተመሠረተው በሚታይ ነገር ላይ ሳይሆን በእምነት ላይ ቢሆንም በነቢዩ ሙሴ አማካኝነት ከተላለፈው ሕግ የሚልቅ ነበር። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የኮርማዎችና የፍየሎች ደም በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ፣ ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን?” (ዕብራውያን 9:13, 14) አዎን፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ማመን የሚያስገኘው የኃጢአት ይቅርታ በሕጉ ሥር የሚቀርቡት መሥዋዕቶች ከሚያስገኙት የኃጢአት ይቅርታ በብዙ መንገዶች እጅግ የላቀ ነው።—ዕብራውያን 7:26-28
6, 7. (ሀ) ዕብራውያን ክርስቲያኖች ሳይዘገዩ ‘ለሰሙት ነገር ከወትሮው የበለጠ ትኩረት መስጠት’ የሚያስፈልጋቸው ለምን ነበር? (ለ) ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤውን በጻፈበት ወቅት በኢየሩሳሌም ላይ የሚደርሰው ጥፋት ምን ያህል ተቃርቦ ነበር? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
6 ዕብራውያን ክርስቲያኖች ኢየሱስን በተመለከተ ለተማሩት ትምህርት ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጡ የሚያደርጋቸው ሌላም ምክንያት ነበራቸው። ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ ትንቢት ተናግሮ ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ወራት ይመጣብሻልና፣ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፣ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፣ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።”—ሉቃስ 19:43, 44
7 ይህ የሚፈጸመው መቼ ነው? ኢየሱስ ቀኑንና ሰዓቱን አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ ይህን መመሪያ ሰጠ:- “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ። የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፣ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ፣ በገጠር ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ።” (ሉቃስ 21:20, 21) ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ በነበሩት 30 ዓመታት ውስጥ በኢየሩሳሌም የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች የጥድፊያ ስሜታቸውን ከማጣታቸውም በላይ ትኩረታቸው ተከፋፍሎ ነበር። መኪና እያሽከረከረ ትኩረቱ ወደ ሌላ ቦታ እንደተሰረቀ አሽከርካሪ ሆነው ነበር ለማለት ይቻላል። አስተሳሰባቸውን ካላስተካከሉ በስተቀር አደጋ ላይ መውደቃቸው አይቀርም። ይህን አመኑም አላመኑ በኢየሩሳሌም ላይ ጥፋት አጥልቶ ነበር!a ጳውሎስ የሰጠው ምክር በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ በመንፈሳዊ ላንቀላፉ ክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ እንደሚያሰማ ደወል ሆኖላቸው ነበር።
በዛሬው ጊዜ “ከወትሮው የበለጠ ትኩረት መስጠት”
8. ለአምላክ ቃል እውነት “ከወትሮው የበለጠ ትኩረት መስጠት” ያለብን ለምንድን ነው?
8 እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም ለአምላክ ቃል እውነት “ከወትሮው የበለጠ ትኩረት መስጠት” ያስፈልገናል። ለምን? እኛም ብንሆን ከፊታችን ጥፋት ተጋርጦብናል። ይህ ጥፋት በአንድ ብሔር ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው ሥርዓት ላይ የሚመጣ ነው። (ራእይ 11:18፤ 16:14, 16) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ይህን እርምጃ የሚወስድበትን ትክክለኛውን ቀንና ሰዓት አናውቅም። (ማቴዎስ 24:36) ሆኖም “በመጨረሻው ቀን” እንደምንኖር በግልጽ የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሲፈጸሙ እየተመለከትን ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ስለዚህ ትኩረታችን በምንም ነገር እንዳይከፋፈል መጠንቀቅ አለብን። የአምላክን ቃል በትኩረት መከታተልና የጥድፊያ ስሜታችንን መጠበቅ ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን “ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ” እንችላለን።—ሉቃስ 21:36
-
-
‘ከወትሮው የበለጠ ትኩረት ስጡ’መጠበቂያ ግንብ—2002 | መስከረም 15
-
-
a ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የተላከው ደብዳቤ የተጻፈው በ61 እዘአ ሳይሆን አይቀርም። ይህ ከሆነ ኢየሩሳሌም በሴስትየስ ጋለስ በሚመራው ሠራዊት የተከበበችው ከአምስት ዓመታት በኋላ ነበር ማለት ነው። ብዙም ሳይቆይ ሠራዊቱ ወደኋላ ማፈግፈጉ ንቁ የሆኑ ክርስቲያኖች አካባቢውን ለቅቀው እንዲሸሹ አስችሏቸዋል። ከአራት ዓመታት በኋላ ከተማዋ በጄኔራል ቲቶ በሚመራው ጦር ተደመሰሰች።
-