የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 12/15 ገጽ 14-19
  • ፈጽሞ ወደ ጥፋት አናፈግፍግ!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ፈጽሞ ወደ ጥፋት አናፈግፍግ!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ወደ ጥፋት ማፈግፈግ ሲባል ምን ማለት ነው?
  • ክርስቲያኖች እንዲያፈገፍጉ የተደረገባቸው ተጽዕኖ
  • ፈጽሞ ወደ ጥፋት ማፈግፈግ የማይኖርባቸው ለምንድን ነው?
  • ፈጽሞ ወደ ጥፋት ማፈግፈግ የማይኖርብን ለምንድን ነው?
  • ከሚያምኑት ወገን እንሁን
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ለሕይወት የምታደርጉትን ሩጫ አታቋርጡ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • እምነት ከማጣት ተጠበቁ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • በይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ አምልኮ የማቅረብ መብትህን ከፍ አድርገህ ተመልከተው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 12/15 ገጽ 14-19

ፈጽሞ ወደ ጥፋት አናፈግፍግ!

“ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም።”—⁠ዕብራውያን 10:​39

1. ሐዋርያው ጴጥሮስ በፍርሃት እንዲርድ ያደረጉት ምን ሁኔታዎች ነበሩ?

ሐዋርያቱ የሚወዱት ጌታቸው ኢየሱስ ሁሉም እንደሚበተኑና እንደሚተዉት ሲነግራቸው በጣም ደንግጠው መሆን አለበት። በሕይወቱ ውስጥ ወሳኝ በሆነው በዚህ ወቅት እንዴት ትተውት ሊሄዱ ይችላሉ? ጴጥሮስ “ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም” ሲል በእርግጠኝነት ተናገረ። በእርግጥም ጴጥሮስ በደፋርነቱና በቆራጥነቱ የታወቀ ሰው ነበር። ሆኖም ኢየሱስ አልፎ ሲሰጥና ሲያዝ ጴጥሮስን ጨምሮ ሁሉም ሐዋርያት ተበተኑ። ኢየሱስን ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ቤት አስገብተው እየመረመሩት ሳለ ጴጥሮስ ግቢው ውስጥ በጭንቀት ተውጦ ይንቆራጠጥ ነበር። ቀዝቃዛው ሌሊት እየተገባደደ ሲሄድ ጴጥሮስ ኢየሱስም ሆነ ከኢየሱስ ጋር የተገኘ ማንኛውም ሰው ሊገደል ይችላል የሚል ፍርሃት ሳያድርበት አልቀረም። በዚያ አካባቢ የነበሩ ሰዎች ከኢየሱስ የቅርብ ጓደኞች አንዱ እንደሆነ ባወቁት ጊዜ ጴጥሮስ በፍርሃት ራደ። ከኢየሱስ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው በመናገር ሦስት ጊዜ አስተባበለ። እንዲያውም ጨርሶ አላውቀውም ሲል ካደ!​—⁠ማርቆስ 14:​27-31, 66-72

2. (ሀ) ኢየሱስ በተያዘበት ምሽት ጴጥሮስ በፍርሃት ተሸንፎ ያደረገው ነገር ‘ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ’ ሰዎች የማያስቆጥረው ለምንድን ነው? (ለ) ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይኖርበታል?

2 ይህ በጴጥሮስ ሕይወት ውስጥ ጥቁር ነጥብ የጣለና በቀረው የሕይወት ዘመኑ ሁሉ ይጸጸትበት የነበረ ድርጊት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም ጴጥሮስ በዚያ ምሽት ያደረገው ነገር የመጨረሻ ፈሪ ያሰኘዋልን? ጳውሎስ “ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም” ብሎ በጻፈ ጊዜ ‘ወደ ጥፋት እንደሚያፈገፍጉ’ አድርጎ ከገለጻቸው ሰዎች መካከል ያስቆጥረዋልን? (ዕብራውያን 10:​39) የጳውሎስ ቃላት በጴጥሮስ ላይ እንደማይሠሩ አብዛኞቻችን እንደምንስማማ የታወቀ ነው። ለምን? ምክንያቱም ድፍረትና እምነት በተሞላበት ሕይወቱ ውስጥ የተከሰተ ቅጽበታዊ ነገር በመሆኑ የጴጥሮስ ፍርሃት ጊዜያዊ ብቻ ነበር። በተመሳሳይም ብዙዎቻችን ድንገት በፍርሃት የተሸነፍንባቸውና የፈለግነውን ያህል ለእውነት በድፍረት ሳንቆም በመቅረታችን ትዝ ሲሉን የምናፍርባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ። (ከሮሜ 7:​21-23 ጋር አወዳድር።) እንዲህ ያለው ቅጽበታዊ ሁኔታ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ ሰዎች መካከል እንደማያስቆጥረን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። አሁንም ቢሆን ከእነዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች መካከል ላለመሆን ቆራጥ መሆን ያስፈልገናል። ለምን? እንዲህ ዓይነት ሰው ከመሆን መራቅ የምንችለውስ እንዴት ነው?

ወደ ጥፋት ማፈግፈግ ሲባል ምን ማለት ነው?

3. ነቢዩ ኤልያስና ነቢዩ ዮናስ በፍርሃት የተሸነፉት እንዴት ነበር?

3 ጳውሎስ ‘የሚያፈገፍጉ’ ብሎ የጻፈው ለቅጽበት ድፍረት የሚያጡ ሰዎችን ለማመልከት አልነበረም። ጳውሎስ የጴጥሮስንም ሆነ ሌሎች ተመሳሳይ ሁኔታዎችን እንደሚያውቅ የተረጋገጠ ነው። ደፋርና በግልጽ ይናገር የነበረው ነቢዩ ኤልያስ ክፉ የነበረችው ንግሥት ኤልዛቤል እንደምትገድለው በዛተችበት ጊዜ በጣም ስለፈራ ሕይወቱን ለማዳን እግሬ አውጪኝ ብሎ ሸሽቷል። (1 ነገሥት 19:​1-4) ነቢዩ ዮናስ ከዚያ የከፋ ፍርሃት አድሮበት ነበር። ይሖዋ በዓመፅና በክፋት ወደምትታወቀው ወደ ነነዌ ከተማ እንዲሄድ አዝዞት ነበር። ዮናስ ግን ወዲያው በጀልባ ተሳፍሮ ከነነዌ በተቃራኒ አቅጣጫ 3,500 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ወደ ተርሴስ አቀና! (ዮናስ 1:​1-3) ሆኖም ሐዋርያው ጴጥሮስም ሆነ እነዚህ ታማኝ ነቢያት ወደኋላ የሚያፈገፍጉ ሊባሉ አይችሉም። ለምን?

4, 5. (ሀ) ጳውሎስ በዕብራውያን 10:​39 ላይ “ጥፋት” ሲል ምን ማለቱ እንደነበር ለመወሰን በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ) ጳውሎስ “እኛ ግን . . . ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም” ሲል ምን ማለቱ ነበር?

4 ጳውሎስ የተጠቀመበት ሙሉ ሐረግ “ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም” እንደሚል ልብ በል። “ጥፋት” ሲል ምን ማለቱ ነው? ጳውሎስ የተጠቀመበት ግሪክኛ ቃል አንዳንድ ጊዜ ዘላለማዊ ጥፋትን ለማመልከት ይሠራበታል። ይህ የቃሉ ፍቺ ደግሞ በጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ ጋር ይስማማል። ጳውሎስ “የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና፣ የሚያስፈራ ግን የፍርድ መጠበቅ ተቃዋሚዎችንም ሊበላ ያለው የእሳት ብርታት አለ” ሲል አስጠንቅቆ ነበር።​—⁠ዕብራውያን 10:​26, 27

5 ስለዚህ ጳውሎስ ለእምነት ባልደረቦቹ “እኛ ግን . . . ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም” ብሎ ሲናገር እሱም ሆነ ታማኝ ክርስቲያን አንባቢዎቹ ምን ጊዜም ቢሆን ከይሖዋ ላለመራቅና እሱን ማገልገላቸውን ላለማቆም እንደቆረጡ መግለጹ ነበር። ወደኋላ ማፈግፈግ የመጨረሻ ውጤቱ ዘላለማዊ ጥፋት ብቻ ነው። ሆነ ብለው የይሖዋን መንፈስ የሚቃረን ነገር እንደሠሩት እንደ ሌሎቹ የእውነት ጠላቶች ሁሉ የአስቆሮቱ ይሁዳም ወደ ዘላለማዊ ጥፋት ካፈገፈጉት ሰዎች መካከል ይገኝበታል። (ዮሐንስ 17:​12፤ 2 ተሰሎንቄ 2:​3) እንዲህ ዓይነቶቹ ግለሰቦች በምሳሌያዊው የእሳት ባሕር ውስጥ ዘላለማዊ ጥፋት ከሚደርስባቸው ‘ፈሪዎች’ መካከል የሚመደቡ ናቸው። (ራእይ 21:​8) እኛ በፍጹም እንደዚያ ዓይነት ሰዎች መሆን አንፈልግም!

6. ሰይጣን ዲያብሎስ ምን ዓይነት ጎዳና እንድንከተል ይፈልጋል?

6 ሰይጣን ዲያብሎስ ወደ ጥፋት እንድናፈገፍግ ይፈልጋል። “በተንኮል ድርጊቶች” የተካነ ስለሆነ የጥፋት ጎዳና በጥቃቅን ነገሮች እንደሚጀመር ያውቃል። (ኤፌሶን 6:​11 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ቀጥተኛ በሆነ ስደት ዓላማውን ማሳካት ካቃተው በረቀቁ ዘዴዎች ተጠቅሞ የእውነተኛ ክርስቲያኖችን እምነት መሸርሸር ይፈልጋል። ደፋርና ቀናተኛ የሆኑትን የይሖዋ ምሥክሮች አፋቸውን ለማዘጋት ይፈልጋል። ጳውሎስ ለጻፈላቸው ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ምን ዘዴ እንደተጠቀመ እስቲ እንመልከት።

ክርስቲያኖች እንዲያፈገፍጉ የተደረገባቸው ተጽዕኖ

7. (ሀ) በኢየሩሳሌም የነበረው ጉባኤ ያስመዘገበው ታሪክ ምን ይመስል ነበር? (ለ) ጳውሎስ የጻፈላቸው የአንዳንዶቹ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

7 ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤውን የጻፈው በ61 እዘአ ገደማ መሆኑን ማስረጃዎች ይጠቁማሉ። በኢየሩሳሌም ያለው ጉባኤ ኃዘንና ደስታ የተፈራረቀበት ጉባኤ ነበር። ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ከባድ ስደት ተነሳና በከተማዋ የሚገኙ ክርስቲያኖች እንዲበታተኑ አደረገ። ሆኖም ከዚያ ተከትሎ የመጣው የሰላም ወቅት ክርስቲያኖች በቁጥር እንዲበዙ አድርጓል። (ሥራ 8:​4፤ 9:​31) ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ሌሎች ስደቶችና መከራዎች በተለያየ ወቅት ተከስተዋል። ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤውን በጻፈበት ወቅት ጉባኤው እንደገና አንጻራዊ ሰላም አግኝቶ የነበረ ይመስላል። ያም ሆኖ ግን ተጽዕኖዎች ነበሩ። ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌም መጥፋት ትንቢት ከተናገረ ወደ ሦስት የሚጠጉ አሥርተ ዓመታት አልፈዋል። አንዳንዶች መጨረሻው ከመጠን በላይ እንደዘገየና እነሱ በሕይወት ሳሉ እንደማይመጣ ሳይሰማቸው አልቀረም። ሌሎች ደግሞ በተለይም በእምነት አዲስ የሆኑት በከባድ ስደት ስላልተፈተኑ በመከራ ጊዜ መጽናት አስፈላጊ ስለመሆኑ ብዙ የሚያውቁት ነገር የለም። (ዕብራውያን 12:​4) ሰይጣን እነዚህ ሁኔታዎች ሳያመልጡት እንደ ጥሩ አጋጣሚ አድርጎ ለመጠቀም ይፈልግ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ምን “የተንኮል ድርጊቶችን” ተጠቅሞ ይሆን?

8. ብዙዎቹ አይሁዶች ገና ጨቅላ ለነበረው ክርስቲያን ጉባኤ ምን አመለካከት ነበራቸው?

8 በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያለው የአይሁድ ኅብረተሰብ ገና ጨቅላ የነበረውን ክርስቲያን ጉባኤ በንቀት ይመለከተው ነበር። የጳውሎስን ደብዳቤ ይዘት በመመርመር ትዕቢተኛ የሆኑ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎችና ተከታዮቻቸው በክርስቲያኖች ላይ እንዴት ይሳለቁ እንደነበር አንዳንድ ሐሳብ ማግኘት እንችላለን። ‘በኢየሩሳሌም ለብዙ መቶ ዓመታት የኖረ ታላቅ ቤተ መቅደስ አለን! ከሌሎች የበታች ካህናት ጋር በመሆን የአምልኮ ሥርዓት የሚያከናውን የታወቀ ሊቀ ካህን አለን። መሥዋዕቶች በየዕለቱ ይቀርባሉ። በመላእክት አማካኝነት ለሙሴ የተሰጠውና በሲና ተራራ በታላላቅ ምልክቶች የጸናው ሕግ አለን። ከአይሁድ እምነት አፈንግጠው የወጡት እነዚህ ከሃዲ ክርስቲያን ኑፋቄዎች እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሏቸውም!’ እያሉ ተሳልቀውባቸው ሊሆን ይችላል። ይህ የንቀት ንግግር የታለመለትን ግብ መትቶ ይሆን? አንዳንድ ዕብራውያን ክርስቲያኖች በዚህ ተረብሸው እንደነበር ግልጽ ነው። የጳውሎስ ደብዳቤ የደረሳቸው ልክ በተገቢው ጊዜ ነበር።

ፈጽሞ ወደ ጥፋት ማፈግፈግ የማይኖርባቸው ለምንድን ነው?

9. (ሀ) ለዕብራውያን የተጻፈው ደብዳቤ ዋና ጭብጥ ምን ነበር? (ለ) ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ በተሻለ ቤተ መቅደስ ያገለግሉ የነበረው በምን ሁኔታ ነበር?

9 ጳውሎስ በይሁዳ የሚገኙ ወንድሞቹና እህቶቹ በፍጹም ወደ ጥፋት ማፈግፈግ የማይኖርባቸው ለምን እንደሆነ ለማስረዳት የተጠቀመባቸውን ሁለት ምክንያቶች እንመርምር። የመጀመሪያው የክርስትና እምነት የአምልኮ ሥርዓት የላቀ መሆኑን እንዲገነዘቡ መርዳት ሲሆን ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በተጻፈው ደብዳቤ ውስጥም ይህ ጉዳይ በብዛት ተንጸባርቋል። ጳውሎስ በደብዳቤው ውስጥ በጠቅላላ ይህን ጭብጥ አብራርቷል። በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ የላቀ ትርጉም ላለውና ‘በእጅ ላልተሠራው’ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምሳሌ ነበር። (ዕብራውያን 9:​11) እነዚያ ክርስቲያኖች ለንጹህ አምልኮ በተደረገው መንፈሳዊ ዝግጅት ውስጥ የማገልገል መብት አግኝተው ነበር። ከሙሴ የላቀ ቦታ ያለው ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛ በሆነለትና ከረዥም ዘመን በፊት ቃል በተገባውና በተሻለው አዲስ ቃል ኪዳን ሥር ሆነው የማገልገል መብት አግኝተዋል።​—⁠ኤርምያስ 31:​31-34

10, 11. (ሀ) የኢየሱስ የዘር ሐረግ በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ሊቀ ካህን ሆኖ የማገልገል መብት እንዳያገኝ ያላደረገው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ያገለግል ከነበረው ሊቀ ካህን የላቀ ሊቀ ካህን የሆነው በምን መንገድ ነው?

10 በተጨማሪም እነዚህ ክርስቲያኖች የተሻለ ሊቀ ካህን ኢየሱስ ክርስቶስ ነበራቸው። ኢየሱስ ከአሮን የዘር ሐረግ የተገኘ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሊቀ ካህን የሆነው “እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት” ነው። (መዝሙር 110:​4) የዘር ሐረጉ የማይታወቀው መልከ ጼዴቅ የጥንቷ ሳሌም ንጉሥ ከመሆኑም በላይ ሊቀ ካህኗ ነበር። በዚህ መንገድ ፍጽምና በሌለው ሰብዓዊ የዘር ሐረግ ላይ ሳይሆን በሚበልጠው ማለትም በራሱ በይሖዋ አምላክ መሐላ ካህን ለሆነው ለኢየሱስ መልከ ጼዴቅ ተስማሚ ትንቢታዊ ጥላ ሆኗል። እንደ መልከ ጼዴቅ ሁሉ ኢየሱስም ሊቀ ካህን ብቻ ሳይሆን ንጉሥም ሆኖ የሚያገለግል ከመሆኑም በላይ ለዘላለም ይኖራል።​—⁠ዕብራውያን 7:​11-21

11 ከዚህም በተጨማሪ በኢየሩሳሌም ያለው ሊቀ ካህን ያቀርብ እንደነበረው ኢየሱስ ከዓመት ዓመት መሥዋዕቶችን ማቅረብ አያስፈልገውም። የእሱ መሥዋዕት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያቀረበው የራሱ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ነው። (ዕብራውያን 7:​27) በቤተ መቅደሱ ይቀርቡ የነበሩት መሥዋዕቶች በጠቅላላ ኢየሱስ ያቀረበውን መሥዋዕት የሚያመለክቱ ጥላ ብቻ ነበሩ። እሱ ያቀረበው መሥዋዕት ለሚያምኑበት ሰዎች ሁሉ እውነተኛ የኃጢአት ይቅርታ ያስገኛል። በተጨማሪም ይህ ሊቀ ካህን በኢየሩሳሌም ያሉ ክርስቲያኖች ያውቁት የነበረው ያው ኢየሱስ መሆኑን በተመለከተ ጳውሎስ የሰጠው አስተያየት ልብ የሚነካ ነው። እሱም ትሁት፣ ደግ እንዲሁም ‘በድካማችን የሚራራልን’ ነው። (ዕብራውያን 4:​15፤ 13:​8) እነዚያ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የክርስቶስ የበታች ካህናት ሆነው የማገልገል ተስፋ ከፊታቸው ተዘርግቶላቸው ነበር! እንደገና “ወደ ደካማ ወደሚናቅም” ብልሹ የአይሁድ እምነት ማፈግፈግን እንዴት ሊያስቡት ይችላሉ?​—⁠ገላትያ 4:​9

12, 13. (ሀ) ጳውሎስ ወደ ኋላ ማፈግፈግ እንደማይገባ ለማስረዳት የተጠቀመበት ሁለተኛ ምክንያት ምንድን ነው? (ለ) ዕብራውያን ክርስቲያኖች ከዚህ ቀደም ያሳዩት ጽናት በፍጹም ወደ ጥፋት እንዳያፈገፍጉ የሚያበረታታቸው ለምንድን ነው?

12 ጳውሎስ በዚህ ብቻ ሳይወሰን የዕብራውያን ክርስቲያኖች ወደ ጥፋት ማፈግፈግ የማይኖርባቸው ለምን እንደሆነ የሚያሳይ ሁለተኛ ማስረጃ ጠቅሷል። ይኸውም ቀደም ሲል ያሳዩት ጽናት ነው። “ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ መከራ በሆነበት በትልቅ ተጋድሎ የጸናችሁበትን የቀደመውን ዘመን አስቡ” ሲል ጽፏል። በነቀፋና በጭንቅ “እንደ መጫወቻ” ሆነው እንደነበር እንዲያስታውሱ አደረጋቸው። አንዳንዶች በእስር ተንገላተዋል፤ ሌሎች ደግሞ እስር ቤት ያሉትን በመርዳት የጭንቀታቸው ተካፋይ ሆነዋል። አዎን፣ ምሳሌ የሚሆን እምነትና ጽናት አሳይተዋል። (ዕብራውያን 10:​32-34) ሆኖም ጳውሎስ እንዲህ ዓይነቱን መጥፎ ተሞክሮ ‘ዘወትር እንዲያስቡ’ የጠየቃቸው ለምንድን ነው? ይህ ተስፋ አስቆራጭ አይሆንምን?

13 ከዚህ ይልቅ ‘የቀደመውን ዘመን ማሰባቸው’ በፈተና ወቅት ይሖዋ እንዴት አድርጎ እንደደገፋቸው እንዲያስታውሱ ያደርጋቸዋል። በይሖዋ እርዳታ ብዙዎቹን የሰይጣን ጥቃቶች ተቋቁመዋል። ጳውሎስ “እግዚአብሔር፣ . . . ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 6:​10) ይሖዋ ዳርቻ በሌለው መታሰቢያው ውስጥ የታማኝነት ሥራቸውን ሁሉ መዝግቦ ስለያዘው ያደረጉትን ነገር አይረሳም። ይህም ኢየሱስ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ ሲል የሰጠውን ምክር ያስታውሰናል። ይህ መዝገብ ሌባ ሊሰርቀው፣ ብልና ዝገት ሊያጠፉት አይችሉም። (ማቴዎስ 6:​19-21) ይህ መዝገብ ሊጠፋ የሚችለው አንድ ክርስቲያን ወደ ጥፋት ካፈገፈገ ብቻ ነው። እንዲህ ማድረግ በሰማይ የተሰበሰበው መዝገብ በከንቱ እንዲጠፋ ያደርጋል። ጳውሎስ ዕብራውያን ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት ጎዳና ፈጽሞ መከተል እንደማይኖርባቸው ያቀረበው ይህ ማስረጃ ምንኛ ጠንካራ ነው! በታማኝነት ያገለገሉባቸው ዓመታት ለምን ከንቱ ሆነው ይቀራሉ? በታማኝነት መጽናቱ ተገቢ ብቻ ሳይሆን የተሻለም ነው።

ፈጽሞ ወደ ጥፋት ማፈግፈግ የማይኖርብን ለምንድን ነው?

14. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን ካጋጠሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች ጋር የሚመሳሰሉ ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል?

14 ዛሬ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም ወደ ጥፋት የማያፈገፍጉበት ተመሳሳይ የሆነ ጠንካራ ምክንያት አላቸው። በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ በሰጠን ንጹህ አምልኮ ውስጥ ያገኘነውን በረከት እናስብ። እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም የምንኖረው ባሏቸው ማራኪ ሃይማኖታዊ ሕንፃዎችና ቅርሳ ቅርሶች በመኩራራት በእኛ ላይ የሚሳለቁ ሰዎች በሞሉበት ጊዜ ውስጥ ነው። ሆኖም ይሖዋ የሚቀበለው የእኛን አምልኮ መሆኑን ዋስትና ሰጥቶናል። እንዲያውም እኛ ዛሬ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ያላገኟቸውን በረከቶች አግኝተናል። ‘ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። እነሱ ይኖሩ የነበሩት መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ገና ሥራውን በጀመረበት ወቅት ላይ ነበር። ክርስቶስ በ29 እዘአ በተጠመቀበት ጊዜ የዚህ ቤተ መቅደስ ሊቀ ካህን ሆነ። አንዳንዶች ተአምር ይፈጽም የነበረውን የአምላክን ልጅ አይተዋል። እሱ ከሞተ በኋላም ተጨማሪ ተአምራት ተፈጽመዋል። ይሁን እንጂ አስቀድሞ በተነገረው መሠረት እነዚህ ስጦታዎች አከተሙ።​—⁠1 ቆሮንቶስ 13:​8

15. ዛሬ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚገኙት የትኛው ትንቢት በሚፈጸምበት ወቅት ነው? ይህስ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?

15 እኛ ግን የምንኖረው በሕዝቅኤል 40 እስከ 48 ላይ የሚገኘው ስለ ቤተ መቅደስ የሚናገረው ሰፊ ትንቢት ታላቅ ፍጻሜውን እያገኘ ባለበት ወቅት ነው።a አምላክ ለንጹህ አምልኮ ያደረገው ዝግጅት ተመልሶ ሲቋቋም ተመልክተናል። ይህ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ከማንኛውም ዓይነት ሃይማኖታዊ ብክለትና የጣዖት አምልኮ ጸድቷል። (ሕዝቅኤል 43:​9፤ ሚልክያስ 3:​1-5) ይህ የማጽዳት ሥራ መከናወኑ ለእኛ ያስገኘውን ጥቅም አስብ።

16. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ተስፋ የሚያስቆርጥ ምን ሁኔታ ገጥሟቸው ነበር?

16 በአንደኛው መቶ ዘመን ለነበረው ክርስቲያን ጉባኤ የወደፊቱ ሁኔታ የጨለመ ነበር። ኢየሱስ አዲስ በተዘራ የስንዴ ማሳ ላይ በአናቱ እንክርዳድ ሲዘራ ስንዴውን ከእንክርዳዱ ለመለየት አስቸጋሪ የሚሆነውን ያህል የጨለመ ሁኔታ እንደሚኖር አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 13:​24-30) የሆነውም ይኸው ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ማብቂያ ገደማ ላይ በዕድሜ ገፍቶ የነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ የክርስትናን እምነት ከብክለት ለመከላከል የመጨረሻውን ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም ክህደት በእጅጉ በመስፋፋት ላይ ነበር። (2 ተሰሎንቄ 2:​6፤ 1 ዮሐንስ 2:​18) ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ መንጋውን የሚጨቁንና የተለየ ልብስ የሚለብስ አንድ የቀሳውስት ቡድን ተነሳ። ክህደቱ ልክ እንደ ጋንግሪን እየተስፋፋ ሄደ። ይህ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ምንኛ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነበር! ለንጹህ አምልኮ የተደረገው አዲስ ዝግጅት ብልሹ በሆነ አምልኮ ሲበረዝ ተመልክተዋል። ይህ የሆነው ደግሞ ክርስቶስ ጉባኤውን ካቋቋመ መቶ ዓመት እንኳ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው።

17. ዛሬ ያለው ክርስቲያን ጉባኤ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበረው ክርስቲያን ጉባኤ ይበልጥ ረጅም ዕድሜ አስቆጥሯል የምንለው ከምን አንጻር ነው?

17 አሁን ንጽጽሩን ተመልከት። ንጹህ አምልኮ ሐዋርያት ሞተው እስኪያልቁ ድረስ ከቆየበት ጊዜ ይልቅ ዛሬ ረጅም ዕድሜ አስቆጥሯል! የዚህ መጽሔት የመጀመሪያ እትም ከወጣበት ከ1879 ጀምሮ ይሖዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠራ በሚሄድ አምልኮ ባርኮናል። በ1918 ይሖዋና ኢየሱስ ክርስቶስ ለማጽዳት ወደ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ገብተው ነበር። (ሚልክያስ 3:​1-5) ከ1919 ጀምሮ ይሖዋ አምላክን ለማምለክ የተደረገው ዝግጅት ደረጃ በደረጃ እየጠራ መጥቷል። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ያለን እውቀትም ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። (ምሳሌ 4:​18) ለዚህ ሁሉ መመስገን ያለበት ማን ነው? ፍጽምና የሌላቸው ሰብዓዊ ሰዎች ሊሆኑ አይችሉም። የጉባኤ ራስ ከሆነው ከልጁ ጋር በመሆን በዚህ በተበከለ ጊዜ ሕዝቡን ከብክለት መጠበቅ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። ስለዚህ ዛሬ ባለው ንጹህ አምልኮ ውስጥ እንድንሳተፍ ስለፈቀደልን ይሖዋን ልናመሰግነው ይገባናል። እንዲሁም ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ ሰዎች መካከል ላለመሆን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ!

18. ፈጽሞ ወደ ጥፋት እንዳናፈገፍግ የሚያደርገን ምን ምክንያት አለን?

18 እንደ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም በፍርሃት ወደ ኋላ ከማፈግፈግ የምንርቅበት ሁለተኛ ምክንያት ያለን ሲሆን ይህም ከዚህ ቀደም ያሳየነው ጽናት ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይሖዋን ማገልገል የጀመርንም እንሁን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በታማኝነት ስናገለግል የቆየን በክርስቲያናዊ ሥራ ያስመዘገብነው መዝገብ አለን። መታሰርም ይሁን፣ እገዳ፣ የጭካኔ ድርጊትም ሆነ ንብረትን ማጣት ብቻ ምንም ይሁን ምን አብዛኞቻችን ስደት ደርሶብናል። ብዙዎች ደግሞ የቤተሰብን ተቃውሞ፣ የሌሎችን ማንቋሸሽ፣ ፌዝና ግዴለሽነት ተቋቁመዋል። የተለያዩ የሕይወት ውጣ ውረዶችና ፈተናዎች ቢኖሩም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችንን በመቀጠል ሁላችንም ጽናት አሳይተናል። እንዲህ በማድረጋችንም ይሖዋ የማይረሳው የጽናት መዝገብ በሰማይ አከማችተናል። ስለዚህ ይህ ጊዜ ትተነው ወደመጣነው ብልሹ አሮጌ ሥርዓት የምናፈገፍግበት ጊዜ አይደለም! ድካማችን ሁሉ መና ሆኖ እንዲቀር ለምን እናደርጋለን? በተለይ መጨረሻው ሊመጣ “በጣም ጥቂት ጊዜ” ብቻ ቀርቶት ባለበት በአሁኑ ወቅት ወደ ጥፋት ማፈግፈግ እንዴት ያለ ትልቅ ኪሳራ ነው።​—⁠ዕብራውያን 10:​37

19. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?

19 አዎን፣ ‘ከሚያምኑቱ እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉት’ ላለመሆን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ! (ዕብራውያን 10:​39) ከዚህ መግለጫ ጋር የምንስማማ ሰዎች መሆናችንን ማረጋገጥ የምንችለው እንዴት ነው? ሌሎች ክርስቲያኖችም እንዲህ እንዲያደርጉ ልንረዳቸው የምንችለውስ እንዴት ነው? ይህ ጉዳይ በሚቀጥለው ርዕስ ይብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a መጋቢት 1, 1999 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 8-23 ተመልከት።

ታስታውሳለህን?

◻ ወደ ጥፋት ማፈግፈግ ምን ማለት ነው?

◻ ጳውሎስ የጻፈላቸው ዕብራውያን ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ተጽዕኖዎች ነበሩባቸው?

◻ ጳውሎስ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ወደ ጥፋት ማፈግፈግ እንደማይኖርባቸው ለማስረዳት የተጠቀመበት ምክንያት ምንድን ነው?

◻ ፈጽሞ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ ሰዎች መካከል ላለመሆን እንድንቆርጥ የሚያበረታቱን ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ጴጥሮስ ለተወሰነ ቅጽበት በፍርሃት መሸነፉ ‘ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ’ ሰዎች መካከል አያስመድበውም

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ