የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 12/15 ገጽ 9-13
  • ሁከት በነገሠባት ምድር እውነተኛ ሰላም ማግኘት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሁከት በነገሠባት ምድር እውነተኛ ሰላም ማግኘት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • “ትልቅ ስሆን የአይ አር ኤ አባል እሆናለሁ!”
  • ገለልተኛ መሆን እውነተኛ ጥበቃ ያስገኛል
  • “ብቸኛው መከላከያዬ መሣሪያዬ ነበር”
  • “ነገሮች ሁሉ ምንም ስሜት አይሰጡኝም ነበር”
  • “ምሥክሮቹ ሁልጊዜ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሩናል”
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 12/15 ገጽ 9-13

ሁከት በነገሠባት ምድር እውነተኛ ሰላም ማግኘት

በ1969 የወጣ አንድ ዘገባ “አስፈሪ የሃይማኖታዊ አንጃዎች አምባጓሮ ተቀሰቀሰ” በማለት ሪፖርት አድርጎ ነበር። ሰሜናዊ አየርላንድን እስከ አሁን ድረስ በማመስ ላይ የሚገኘው ሁከት የጀመረው በዚህ ወቅት ነበር።

የፕሮቴስታንትና የካቶሊክ ገዳዮች ማለትም ፖለቲካዊም ሃይማኖታዊም ጎራ የለዩ “በሁለቱም ወገን የተሰለፉ አረመኔ ሰዎች” በአየርላንድ የበላይነትን ለማስጠበቅ በሚያደርጉት ፍልሚያ ሃይማኖታዊ ዓመፅና ግድያ የአገሪቱ የዕለት ተዕለት ዕጣ እንዲሆን አድርገውታል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን በዘለቀው በዚህ “30 ዓመታት በፈጀ አምባጓሮ ከ3,600 የሚበልጡ ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወትና ለአካል ጉዳተኝነት መዳረጋቸውን” ዚ አይሪሽ ታይምስ ዘግቧል።

እርግጥ ነው፣ ይህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጀመረ ትግል አይደለም። አየርላንድን ለበርካታ መቶ ዘመናት ሲያምሳት የኖረ ነገር ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ብጥብጡ በሰሜናዊው አየርላንድ እጅግ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል። ሆኖም ብጥብጡ ያስከተለው አስከፊ መዘዝ በመላው አየርላንድ የሚኖሩ ሰዎችን ሕይወት በእጅጉ ነክቷል።

ይህ ሁሉ እያለ የይሖዋ ምሥክሮች በዚህች ሁከት በነገሠባት አገር ላለው ችግር እውነተኛ መፍትሔ ምን እንደሆነ ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ ሲናገሩ ቆይተዋል። ለችግሩ መፍትሔ ሊያመጣ የሚችለው በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት ነው። (ማቴዎስ 6:​9, 10) በ1969 ችግሩ በተቀሰቀሰበት ወቅት በአየርላንድ 876 የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። አሁን ከ100 በሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ ከ4,500 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። ለፖለቲካና ለውትድርና እንቅስቃሴ ጀርባቸውን ከሰጡት መካከል የጥቂቶቹ ተሞክሮ ከዚህ ቀጥሎ ሰፍሯል።

“ትልቅ ስሆን የአይ አር ኤ አባል እሆናለሁ!”

ማይክልa ያደገው በአየርላንድ ሪፑብሊክ በካቶሊክ ሃይማኖት ነው። ገና ተማሪ እያለ ስለ አየርላንድና አየርላንድ ከብሪታንያ ጋር ስለነበራት ዘመናት ያስቆጠረ ግጭት የሚገልጹ ታሪኮችን ተምሯል። ከልጅነቱ ጀምሮ “የአየርላንድን ሕዝብ እንደሚጨቁን” አድርጎ ለሚመለከተው የእንግሊዝ ሕዝብ ከፍተኛ ጥላቻ አዳብሯል። የአሥር ዓመት ልጅ በነበረ ጊዜ ለሴት አያቱ “ትልቅ ስሆን የአይ አር ኤ (የአይሪሽ ሪፑብሊክ ጦር ሠራዊት) አባል እሆናለሁ!” ብሎ ነገራቸው። “አያቴ ያቀመሰችኝን ጥፊ እስከ አሁን ድረስ አልረሳውም” በማለት ይናገራል። በኋላ ወንድ አያቱ የብሪታንያ ጦር ሠራዊት አባል እንደነበሩ አወቀ። በአንድ ወቅት ሴት አያቱ የአይ አር ኤ አባላት ወንድ አያቱን እንዳይገድሏቸው ሰብአዊ ጋሻ ሆነው አድነዋቸዋል።

ያም ሆኖ ማይክል ትልቅ ከሆነ በኋላ በሰሜን አየርላንድ የሚኖሩ የካቶሊክ እምነት ባልደረቦቹን ለመርዳት አንድ ነገር ማድረግ ይፈልግ ነበር። “በዚያን ወቅት በሰሜን አየርላንድ የሚኖሩ ካቶሊኮችን ለመርዳት የሚንቀሳቀሰው አይ አር ኤ ብቻ እንደሆነ አድርጌ አስብ ነበር” በማለት ይናገራል። በመሆኑም የአይ አር ኤ አባል መሆን ትክክለኛ እርምጃ እንደሆነ አድርጎ በማሰብ ከቡድኑ ጋር ተቀላቀለና የጦር መሣሪያ ሥልጠና ተሰጠው። ሦስት ጓደኞቹ በሰሜናዊ አየርላንድ ከፕሮቴስታንት እንቅስቃሴ በተተኮሰ ጥይት ተገደሉ።

ከጊዜ በኋላ ማይክል ይህ ጦር የሚያካሂደው ትግል እንዳሰበው ሳይሆን ከመቅረቱም በላይ በወታደራዊ አንጃው የተለያዩ ቡድኖች መካከል በሚፈጠረው ግጭት በጣም ተረበሸ። በአይ አር ኤ እንቅስቃሴ በመካፈሉ ምክንያት ታስሮ በነበረበት ወቅት ዘላቂ ሰላምና ፍትሕ ሊያስገኝ የሚችለውን እውነተኛ መንገድ እንዲያመለክተው ወደ አምላክ ጸለየ። ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቱን አንኳኩ። ሆኖም እድሜ ልኩን አብሮት የኖረው ወገናዊ ጥላቻ ጋሬጣ ሆነበት። ምሥክሮቹ የእንግሊዝ ተወላጆች ነበሩ። በውስጡ የነበረው ስር የሰደደ ጥላቻ እንዳያዳምጥ እንቅፋት ሆነበት። “ፊት ብነሳቸውም” ይላል ማይክል “እኔን ለማነጋገር እቤት መምጣታቸውን አላቆሙም። እኔ ለማስወገድ እታገል የነበረውን ሁሉንም ዓይነት የፖለቲካና የማኅበራዊ የፍትሕ መጓደል የሚያስወግደው የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ቀስ በቀስ መገንዘብ ጀመርኩ።”​—⁠መዝሙር 37:​10, 11፤ 72:​12-14

አንድ ምሽት ማይክል ከአይ አር ኤ አዛዥ ሹም ጋር በተገናኘ ጊዜ የቁርጥ ቀን ሆነ። ሹሙም “የምትሠራው አንድ ሥራ አለ” አለው። “ወዲያው አንድ ውሳኔ ማድረግ እንዳለብኝ ተሰማኝ” በማለት ማይክል ይናገራል። “ስለዚህ ወደ ውስጥ አየር ሳብኩና በዚያን ወቅት ገና ያልተጠመቅኩ ብሆንም እንኳ ‘አሁን እኔ የይሖዋ ምሥክር ነኝ’ አልኩት። የይሖዋ አገልጋይ መሆን እፈልግ እንደነበር ያወኩት የዚያን ጊዜ ነበር።” አዛዥ መኮንኑም “ግድግዳ አስደግፈን እንረሽንሃለን” በማለት መለሰለት። ማይክል ይህ ዛቻ ቢሰነዘርበትም ከአይ አር ኤ ለቀቀ። የይሖዋ ቃል አእምሮውንና ልቡን እንዲነካው መፍቀዱ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ድፍረት አስገኝቶለታል። “ከጊዜ በኋላ ባለቤቴና ከልጆቼ መካከል አንዳንዶቹ ራሳቸውን ለይሖዋ ወሰኑ። አሁን በልባችን ውስጥ እውነተኛ ሰላም አለን። ይሖዋ እውነትን እንድንማርና ሁከት በተሞላበት አገር ሰላማዊ መልእክት በማሰራጨቱ ተግባር እንድንካፈል ስለ ፈቀደልን ሁልጊዜ እናመሰግነዋለን።”​—⁠መዝሙር 34:​14፤ 119:​165

ገለልተኛ መሆን እውነተኛ ጥበቃ ያስገኛል

“ያደግኩት በሰሜናዊ አየርላንድ በሚገኘው በካውንቲ ዴሪ ገጠራማ አካባቢ ነው” በማለት ፓትሪክ ይናገራል። “ከልጅነቴ ጀምሮ ከሁከት በቀር የማውቀው ነገር የለም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ማደጌ በአመለካከቴና በአስተሳሰቤ ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረብኝ ግልጽ ነው።” ፓትሪክ ብሔራዊ ስሜት ባሳደረበት ተጽዕኖ የጽንፈኝነት አመለካከትና ሥር የሰደደ ጸረ-ብሪታንያ አቋም እንዲይዝ አደረገው። በሁለቱም ጎራ ተሰልፈው ፖለቲካዊ ትግል የሚያካሂዱ ሃይማኖታዊ ሰዎች አስፈላጊ የሆኑ የክርስትና መሠረታዊ ሥርዓቶችንም ሆነ የሰውን ልጅ መሠረታዊ መልካም ምግባር ሲጥሱ ተመልክቷል። በዚህም የተነሳ ከሃይማኖት ራቀ፤ ውሎ አድሮም አምላክ የለም ባይና አክራሪ ማርክሲስት ሆነ።​—⁠ከማቴዎስ 15:​7-9፤ 23:​27, 28 ጋር አወዳድር።

“በሰሜን የሚኖሩ ሪፑብሊካን እስረኞች ያደረጉት የረሃብ አድማ ፈጽሞ የማልረሳው ትዝታ ቀርጾብኛል” በማለት ፓትሪክ ይናገራል። “ከሚገመተው በላይ ተጽዕኖ አሳድረውብኛል። በሄድኩበት ቦታ ሁሉ የአይሪሽን ሰንደቅ ዓላማ እየሰቀልኩ ጸረ-ብሪታንያ መፈክሮችን እጽፍ እንደነበረ ትዝ ይለኛል። ገና የ15 ዓመት ልጅ ሳለሁ ከረሃብ አድመኞቹ መካከል አንዱ እስር ቤት እንዳለ በሞተ ጊዜ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ዋና አስተባባሪ ነበርኩ።” በጊዜው በነበረው ሁከትና ውዥንብር ተስበው እንደገቡት እንደ ሌሎቹ ሁሉ ፓትሪክም ለኅብረተሰቡ ፍትሕና እኩልነት ለማስፈን ሲል በረብሻዎችና በተቃውሞ ስብሰባዎች ውስጥ ተካፍሎ ነበር። የብሪታንያ ባለ ሥልጣናት እስር ቤት ከከተቷቸው በርካታ ብሔራዊ ጽንፈኞች ጋር ወዳጅነት መሠረተ።

“ከዚያም” ይላል ፓትሪክ “ለኢኮኖሚው ስል ለተወሰነ ጊዜ በዚያ ለመኖር ወደ እንግሊዝ ሄድኩ። እዚያ እያለሁ ቦምብ የማፈንዳት ተልእኮ የነበረውን አንዱን ጓደኛዬን የብሪታንያ ፖሊሶች ይዘው አሠሩት።” ምንም እንኳ ፓትሪክ ብሔራዊ ስሜቱ ያልጠፋለት ቢሆንም የአመለካከት ለውጥ ማድረግ ጀመረ። ጠቅላላውን የእንግሊዝ ሕዝብ የሚጠላበት ምንም ምክንያት እንደሌለው መገንዘብ ጀመረ። “እንዲሁም አንጃዎች ምንም ያህል ከፍተኛ እንቅስቃሴ ቢያደርጉ ለችግሮች ፈጽሞ መፍትሔ ሊያመጡ እንደማይችሉና እኔን በጣም የሚረብሸኝ የፍትሕ መጓደል ሊያስቀሩ እንደማይችሉ መገንዘብ ጀመርኩ። አንጃዎቹን የሚመሩት ሰዎች ሙስናና ሌሎች እንከኖች ነበሩባቸው።”​—⁠መክብብ 4:​1፤ ኤርምያስ 10:​23

ከጊዜ በኋላ ፓትሪክ ወደ ሰሜን አየርላንድ ተመለሰ። “ከተመለስኩ በኋላ አንድ ጓደኛዬ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አስተዋወቀኝ።” ፓትሪክ ከምሥክሮቹ ጋር ያደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በሰው ልጆች መካከል ላለው ግጭትና ብጥብጥ ትክክለኛው መፍትሔ ምን እንደሆነ መገንዘብ ጀመረ። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አእምሮውንና ልቡን እየነኩት በሄዱ መጠን ፈጣን መንፈሳዊ እድገት ማድረጉን ቀጠለ። (ኤፌሶን 4:​20-24) “አሁን” ይላል ፓትሪክ “ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሥርዓት ከሥሩ መንግሎ ለመጣል ከማደም ይልቅ ከዚህ በፊት ዝር በማልልበት አክራሪ ፖለቲከኞች በሚኖሩበት አካባቢ እንኳ ሳይቀር የሰላምን መልእክት ከመጽሐፍ ቅዱስ መስበክ ጀመርኩ። እንዲያውም በቤልፋስት በሃይማኖታውያን መካከል ከፍተኛ ግድያ በነበረበት ጊዜ እንኳን አክራርያንና ብሔራዊ ስሜት የተጠናወታቸው ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ የጦር መሣሪያ ሳይዙ በነፃነት ይንቀሳቀሱ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ነበሩ።” በዚህ ወቅት በሰሜን አየርላንድ ይኖሩ እንደነበሩት እንደ ሌሎቹ ምሥክሮችና እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እውነተኛ ጥበቃ የሚያስገኘው የገለልተኝነት አቋም መያዝ እንደሆነ በሚገባ ተረድቷል። (ዮሐንስ 17:​16፤ 18:​36) እንዲህ በማለት ይደመድማል:- “ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ለመላው የሰው ልጅ እውነተኛ ፍትሕና ነፃነት እንደሚሰጥ ማወቁ ትልቅ እፎይታ ነው።”​—⁠ኢሳይያስ 32:​1, 16-18

“ብቸኛው መከላከያዬ መሣሪያዬ ነበር”

“ያደኩት በሌላኛው ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ጎራ ነበር” በማለት ዊሊያም ይናገራል። “ፕሮቴስታንቶች የነበራቸው ዓይነት ጥላቻ አደረብኝና ካቶሊክ የተባለ ሁሉ በጣም እጠላ ጀመር። በተቻለኝ መጠን የካቶሊክ ሰው ሱቅ ውስጥ ገብቼ ዕቃ ላለመግዛት እጠነቀቅ ነበር። እንዲሁም አየርላንድ ሪፑብሊክ የሄድኩት አንድ ጊዜ ብቻ ነው። እንደ ኦሬንጅ ኦርደር ያሉ የፕሮቴስታንት ሃይማኖትንና የአኗኗር መንገዱን ጠብቆ ለማቆየት የሚታገሉ ድርጅቶችን በመሰሉ በተለያዩ የፕሮቴስታንት ቡድኖችና ተቋሞች ውስጥ ገባሁ።” ዊልያም 22 ዓመት እንደሞላው የብሪታንያ ጦር ክፍል በሆነው በአልስተር ዲፌንስ ሬጂመንት ውስጥ ለማገልገል ተመለመለ። አብዛኞቹ የጦር ሠራዊቱ አባላት ፕሮቴስታንቶች ነበሩ። ቅርሱን ለማስጠበቅ ሲል ከመግደል ፈጽሞ ወደኋላ አይልም ነበር። “በርካታ የጦር መሣሪያ የነበረኝ ሲሆን አስፈላጊም ሆኖ ከተገኘ ለመጠቀም ወደኋላ አልልም ነበር። ሁልጊዜ ማታ ማታ አንዱን ትራሴ ሥር ሸጉጬ አስቀምጥ ነበር።”

ሆኖም ነገሮች ሁሉ በድንገት አዲስ መልክ መያዝ ጀመሩ። “ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ሆኜ አንድ ያረጀ ቤት በምናድስበት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ልዩ የሆነ ነገር እንዳላቸው ተገነዘብኩ። ይህ የሥራ ባልደረባዬ በእኔ ላይ ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል። ቤቱን አብረን በምንሠራበት ወቅት ችግሮችን፣ ሃይማኖትንና አምላክን በሚመለከት ይከነክኑኝ የነበሩ በርካታ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ችዬ ነበር። የሰጠኝ ቀላልና ግልጽ የሆነ መልስ የይሖዋ ምሥክሮችን ማንነት ማለትም የተባበሩ፣ ከዓመፃ ሁሉ የራቁና ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆኑ ሰዎች፣ ለአምላክና ለሰዎች በሚያሳዩት ፍቅር ተለይተው የሚታወቁ እንደሆኑ በትክክል እንድገነዘብ ረዳኝ።”​—⁠ዮሐንስ 13:​34, 35

ዊሊያም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት በጀመረ በአራት ወር ጊዜ ውስጥ ቀደም ሲል ከነበረበት ከማንኛውም ዓይነት ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ተቋም ወጣ። “ለረዥም ጊዜያት የቆዩ ልማዶችን እርግፍ አድርጌ መተው ስለነበረብኝ ይህ በሕይወቴ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የሚይዝ እርምጃ ነበር” በማለት ዊሊያም ያስታውሳል። ሆኖም ከሁሉ የሚከፋ ፈተና ገና ከፊቱ ይጠብቀው ነበር። “በሰሜን አየርላንድ በነበረው ሁኔታ ምክንያት ብቸኛ መከላከያዎቼ መሣሪያዎቼ እንደሆኑ አድርጌ አስብ ነበር። በአይ አር ኤ አንጃዎች ‘ዓይን’ ውስጥ ገብቼ ነበር። ስለዚህ እነዚህን የጦር መሣሪያዎች ማስወገድ በጣም አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነበር።” ሆኖም በኢሳይያስ 2:​2-4 ላይ ተመዝግበው የሚገኙ የመሰሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ቀስ በቀስ አመለካከቱን ለወጡት። በመጨረሻም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ክርስቲያኖች እንደሆነላቸው ሁሉ ለእርሱም እውነተኛ ጥበቃ የሚያስገኝለት ይሖዋ ብቻ እንደሆነ ተገነዘበ። በመጨረሻም ዊልያም መሣሪያዎቹን አስረከበ።

“በጣም ከሚያስደስቱኝ በርካታ ነገሮች መካከል አንዱ” ይላል ዊልያም “ቀደም ሲል እንደ ጠላት አድርጌ እመለከታቸው ከነበሩ ሰዎች ጋር አሁን የጠለቀና ቀጣይነት ያለው ወዳጅነት መመሥረቴ ነው። በተጨማሪም ቀደም ሲል ለእኔ ‘የተከለከሉ’ ቦታዎች እንደሆኑ አድርጌ እመለከታቸው ወደነበሩ አካባቢዎች የመጽሐፍ ቅዱስን የተስፋ መልእክት ይዤ ለመሄድ በመቻሌ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል። እውነት ለእኔና ለቤተሰቦቼ ያደረገልንን ነገር ሳስብ ይሖዋንና የእርሱን ድርጅት ለዘላለም እንዳመሰግን እገፋፋለሁ።”

“ነገሮች ሁሉ ምንም ስሜት አይሰጡኝም ነበር”

ሮበርት እና ተሪሳ ፈጽሞ የተለያየ አስተዳደግ ነበራቸው። ሮበርት “እኔ የተወለድኩት በጣም አጥባቂ ፕሮቴስታንት ከሆነ ቤተሰብ ነው” በማለት ይናገራል። “አንዳንድ ዘመዶቼ በአንጃ እንቅስቃሴ ውስጥ ተካፍለዋል። እኔም በ19 ዓመት ዕድሜዬ በብሪታንያ ጦር በአልስተር ዲፌንስ ሬጂመንት ተቀጠርኩ። በዚያን ወቅት አብዛኛው ሥራዬ ያተኮረው ተሪሳ የምትኖርበትን አካባቢ እየተዘዋወርኩ መጠበቅ ነበር። አንድ ቀን ሌሊት እየተዘዋወርኩ ከምጠብቀው ከመደበኛ ሥራዬ የተለየ ሥራ ተሰጠኝ። በዚያች ምሽት እጓዝበት የነበረው ላንድ ሮቨር መኪና በፈንጂ ብትንትኑ ወጣ። ሁለት ወታደሮች ሲሞቱ ሌሎች ሁለት ደግሞ ቆሰሉ።”

ሮበርት የሕይወት ትርጉም ያሳስበው ጀመር። “በአምላክ የማምን ብሆንም በሰሜን አየርላንድ ያሉትን ሁኔታዎች ስመለከት ነገሮች ሁሉ ምንም ስሜት አይሰጡኝም ነበር። አሁን ግን ወደ አምላክ መጸለይ ጀምሬ ነበር። አምላክ በእርግጥ ካለህ ሕይወቴን የምመራበት ትክክለኛውን መንገድ አሳየኝ ብዬ ጸለይኩ። በአንድ ወቅት አንድ እውነተኛ ሃይማኖት የሆነ ቦታ መኖር አለበት ብዬ ለአምላክ እንደተናገርኩ ትዝ ይለኛል!” ከዚያም ጥቂት ቀናት እንዳለፉ አንድ የይሖዋ ምሥክር ሮበርትን አነጋገረና ጽሑፍ ሰጥቶት ሄደ። ሮበርት በዚያ ምሽት ከጥበቃ ሥራው ከተመለሰ በኋላ ጽሑፉን ማንበብ ጀምሮ ጠዋት በአሥራ አንድ ሰዓት ላይ ጨረሰ። “ወዲያው የእውነት ደወል በጭንቅላቴ ውስጥ አቃጨለ” ይላል ሮበርት፣ “እንዲሁም ሁሉም ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው ነገር ጋር አንድ እንደሆነ አስተዋልኩ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:​16) ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረና በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሱን ለአምላክ ወሰነ።

“ምሥክሮቹ ሁልጊዜ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሩናል”

በሌላው በኩል ደግሞ ተሪሳ ያደገችው ብሔራዊ ስሜት በከፍተኛ ሁኔታ በተጠናወተው በአንድ ካቶሊክ ቤተሰብ ውስጥ ነበር። “ገና ልጅ ሳለሁ የሺን ፌን አባል ሆንኩ።”b ተሪሳ ሳትሸሽግ እንዲህ ብላለች:- “ይህም ለአንጃ ተዋጊዎች ድጋፍ እንድሰጥ አደረገኝ። ለወታደራዊ ትግሉ ገንዘብ በማሰባሰብ ድጋፍ አድርጌያለሁ። በአካባቢዬ ምን ነገር እየተካሄደ እንዳለ ለአይ አር ኤ ያለማቋረጥ መረጃ አቀብል ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በብጥብጥ ውስጥ በመካፈል በፖሊሶችና እየተዘዋወሩ በሚጠብቁ ወታደሮች ላይ ድንጋይ እወረውር ነበር።”

ከተሪሳ ቤተሰቦች መካከል አንዳንዶቹ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት በጀመሩ ጊዜ የእርሷም የማወቅ ፍላጎቷ ተቀሰቀሰ። የአምላክ ቃል ያለው ኃይል በእርሷ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳደረ። “ለጥያቄዎቻችን መልስ እንድናገኝ ምሥክሮቹ ሁልጊዜ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሩን ነበር” በማለት ትናገራለች። “ዳንኤል 2:​44 ላይ ሠፍሮ የሚገኘው ተስፋ በእርግጥም ዓይን የሚገልጥ ነበር። እኔ እታገልለት ለነበረው ለሁሉም ዓይነት የፍትሕ መጓደል መፍትሔው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ተገነዘብኩ።” አንጃዎች በሚፈጽሙት አንዳንድ የግፍ ሥራ በውስጧ የጥላቻ ስሜት እንዲያድርባት አድርጓል። ለምሳሌ ያህል የርኅራኄ ስሜትና መልካም ምግባር ያለው ሰው አሸባሪዎች በፈጸሙት ድርጊት ወታደሮች ወይም ሌሎች ሰዎች እንደተገደሉ ወይም የአካል ጉዳተኞች እንደሆኑና ቤተሰቦች ሐዘንና ሰቆቃ እንደደረሰባቸው የሚገልጽ ዜና ሲሰማ ለምን ደስ እንደሚለው ተሪሳ ሊገባት አይችልም ነበር። እርሷም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሰፈረው እውነት ጥሩ ምላሽ በመስጠት የአምላክ መሠረታዊ ሥርዓቶች አስተሳሰቧን እንዲያስተካክልላት ፈቀደች። ራሷን ለአምላክ ወሰነችና ወዲያው ተጠመቀች።​—⁠ምሳሌ 2:​1-5, 10-14

በሰሜን አየርላንድ በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ተሪሳና ሮበርት ተገናኙ። ተሪሳ እንዲህ ስትል ገልጻለች:- “ከሮበርት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ስንገናኝ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የብሪታንያ ፖለቲካዊና ወታደራዊ መጠቀሚያ እንደሆነ አድርጌ እቆጥረው የነበረውን ሰው በእርጋታና ሰላማዊ በሆነ መንገድ እያነጋገርኩ እንዳለሁ ለማመን ቸግሮኝ ነበር። የአምላክ ቃል በውስጤ ሥር ሰድዶ የነበረውን ጥላቻ እንዳስወግድ እንደረዳኝ ምንም ጥርጥር የለውም።” የተለያዩ ባሕሎችና ልማዶች ያመነጩት ጥላቻ እንዲከፋፍላቸው ከመፍቀድ ይልቅ አሁን የጋራ የሆኑ ብዙ ነገሮች አሏቸው። ከእነዚህ መካከል ከሁሉም የሚበልጠው ኃይል ደግሞ ለይሖዋ አምላክ ያላቸው ፍቅር ነው። እነዚህ ሁለት ሰዎች ተጋቡ። አሁን እውነተኛ ሰላም የሚያስገኘውን የአምላክን መልእክት የተለያየ ዓይነት አስተዳደግና እምነት ላላቸው በዚች ሁከት በነገሠባት አገር ለሚኖሩ ሰዎች ለማዳረስ አንድ ላይ ሆነው ይሠራሉ።

በአየርላንድ የሚኖሩ ሌሎችም ተመሳሳይ የሆኑ ተሞክሮዎች አሏቸው። በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል የሚያስተምራቸውን ትምህርቶች በማዳመጥና በመቀበል ‘ከሰዎች ፍልስፍናና ከንቱ ማታለል’ አምልጠዋል። (ቆላስይስ 2:​8) አሁን ጠቅላላ ትምክህታቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው በሚገኙት አምላክ በገባቸው ተስፋዎች ላይ ጥለዋል። ሙሉ በሙሉ ከሃይማኖታዊም ሆነ ከሌላ ከማንኛውም ዓይነት ዓመፅ ነፃ የሆነ ሰላም የሰፈነበት ዓለም ወደፊት እንደሚመጣ ያላቸውን ተስፋ ሊያዳምጣቸው ፈቃደኛ ለሆነ ሁሉ ለማካፈል ደስተኞች ናቸው።​—⁠ኢሳይያስ 11:​6-9

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ስሞቹ ተለውጠዋል።

b ከጊዜያዊ አይ አር ኤ ጋር የቅርብ ተዛማጅነት ያለው አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ነው።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በሰሜን አየርላንድ በየግድግዳዎች ላይ የተጻፉ መፈክሮች በአንጃዎች መካከል የሚደረገውን ትግል የሚያበረታቱ ናቸው

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ