-
ፈጽሞ ወደ ጥፋት አናፈግፍግ!መጠበቂያ ግንብ—1999 | ታኅሣሥ 15
-
-
ፈጽሞ ወደ ጥፋት አናፈግፍግ!
“ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም።”—ዕብራውያን 10:39
1. ሐዋርያው ጴጥሮስ በፍርሃት እንዲርድ ያደረጉት ምን ሁኔታዎች ነበሩ?
ሐዋርያቱ የሚወዱት ጌታቸው ኢየሱስ ሁሉም እንደሚበተኑና እንደሚተዉት ሲነግራቸው በጣም ደንግጠው መሆን አለበት። በሕይወቱ ውስጥ ወሳኝ በሆነው በዚህ ወቅት እንዴት ትተውት ሊሄዱ ይችላሉ? ጴጥሮስ “ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም” ሲል በእርግጠኝነት ተናገረ። በእርግጥም ጴጥሮስ በደፋርነቱና በቆራጥነቱ የታወቀ ሰው ነበር። ሆኖም ኢየሱስ አልፎ ሲሰጥና ሲያዝ ጴጥሮስን ጨምሮ ሁሉም ሐዋርያት ተበተኑ። ኢየሱስን ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ቤት አስገብተው እየመረመሩት ሳለ ጴጥሮስ ግቢው ውስጥ በጭንቀት ተውጦ ይንቆራጠጥ ነበር። ቀዝቃዛው ሌሊት እየተገባደደ ሲሄድ ጴጥሮስ ኢየሱስም ሆነ ከኢየሱስ ጋር የተገኘ ማንኛውም ሰው ሊገደል ይችላል የሚል ፍርሃት ሳያድርበት አልቀረም። በዚያ አካባቢ የነበሩ ሰዎች ከኢየሱስ የቅርብ ጓደኞች አንዱ እንደሆነ ባወቁት ጊዜ ጴጥሮስ በፍርሃት ራደ። ከኢየሱስ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው በመናገር ሦስት ጊዜ አስተባበለ። እንዲያውም ጨርሶ አላውቀውም ሲል ካደ!—ማርቆስ 14:27-31, 66-72
2. (ሀ) ኢየሱስ በተያዘበት ምሽት ጴጥሮስ በፍርሃት ተሸንፎ ያደረገው ነገር ‘ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ’ ሰዎች የማያስቆጥረው ለምንድን ነው? (ለ) ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይኖርበታል?
2 ይህ በጴጥሮስ ሕይወት ውስጥ ጥቁር ነጥብ የጣለና በቀረው የሕይወት ዘመኑ ሁሉ ይጸጸትበት የነበረ ድርጊት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም ጴጥሮስ በዚያ ምሽት ያደረገው ነገር የመጨረሻ ፈሪ ያሰኘዋልን? ጳውሎስ “ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም” ብሎ በጻፈ ጊዜ ‘ወደ ጥፋት እንደሚያፈገፍጉ’ አድርጎ ከገለጻቸው ሰዎች መካከል ያስቆጥረዋልን? (ዕብራውያን 10:39) የጳውሎስ ቃላት በጴጥሮስ ላይ እንደማይሠሩ አብዛኞቻችን እንደምንስማማ የታወቀ ነው። ለምን? ምክንያቱም ድፍረትና እምነት በተሞላበት ሕይወቱ ውስጥ የተከሰተ ቅጽበታዊ ነገር በመሆኑ የጴጥሮስ ፍርሃት ጊዜያዊ ብቻ ነበር። በተመሳሳይም ብዙዎቻችን ድንገት በፍርሃት የተሸነፍንባቸውና የፈለግነውን ያህል ለእውነት በድፍረት ሳንቆም በመቅረታችን ትዝ ሲሉን የምናፍርባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ። (ከሮሜ 7:21-23 ጋር አወዳድር።) እንዲህ ያለው ቅጽበታዊ ሁኔታ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ ሰዎች መካከል እንደማያስቆጥረን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። አሁንም ቢሆን ከእነዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች መካከል ላለመሆን ቆራጥ መሆን ያስፈልገናል። ለምን? እንዲህ ዓይነት ሰው ከመሆን መራቅ የምንችለውስ እንዴት ነው?
ወደ ጥፋት ማፈግፈግ ሲባል ምን ማለት ነው?
3. ነቢዩ ኤልያስና ነቢዩ ዮናስ በፍርሃት የተሸነፉት እንዴት ነበር?
3 ጳውሎስ ‘የሚያፈገፍጉ’ ብሎ የጻፈው ለቅጽበት ድፍረት የሚያጡ ሰዎችን ለማመልከት አልነበረም። ጳውሎስ የጴጥሮስንም ሆነ ሌሎች ተመሳሳይ ሁኔታዎችን እንደሚያውቅ የተረጋገጠ ነው። ደፋርና በግልጽ ይናገር የነበረው ነቢዩ ኤልያስ ክፉ የነበረችው ንግሥት ኤልዛቤል እንደምትገድለው በዛተችበት ጊዜ በጣም ስለፈራ ሕይወቱን ለማዳን እግሬ አውጪኝ ብሎ ሸሽቷል። (1 ነገሥት 19:1-4) ነቢዩ ዮናስ ከዚያ የከፋ ፍርሃት አድሮበት ነበር። ይሖዋ በዓመፅና በክፋት ወደምትታወቀው ወደ ነነዌ ከተማ እንዲሄድ አዝዞት ነበር። ዮናስ ግን ወዲያው በጀልባ ተሳፍሮ ከነነዌ በተቃራኒ አቅጣጫ 3,500 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ወደ ተርሴስ አቀና! (ዮናስ 1:1-3) ሆኖም ሐዋርያው ጴጥሮስም ሆነ እነዚህ ታማኝ ነቢያት ወደኋላ የሚያፈገፍጉ ሊባሉ አይችሉም። ለምን?
4, 5. (ሀ) ጳውሎስ በዕብራውያን 10:39 ላይ “ጥፋት” ሲል ምን ማለቱ እንደነበር ለመወሰን በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ) ጳውሎስ “እኛ ግን . . . ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም” ሲል ምን ማለቱ ነበር?
4 ጳውሎስ የተጠቀመበት ሙሉ ሐረግ “ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም” እንደሚል ልብ በል። “ጥፋት” ሲል ምን ማለቱ ነው? ጳውሎስ የተጠቀመበት ግሪክኛ ቃል አንዳንድ ጊዜ ዘላለማዊ ጥፋትን ለማመልከት ይሠራበታል። ይህ የቃሉ ፍቺ ደግሞ በጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ ጋር ይስማማል። ጳውሎስ “የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና፣ የሚያስፈራ ግን የፍርድ መጠበቅ ተቃዋሚዎችንም ሊበላ ያለው የእሳት ብርታት አለ” ሲል አስጠንቅቆ ነበር።—ዕብራውያን 10:26, 27
5 ስለዚህ ጳውሎስ ለእምነት ባልደረቦቹ “እኛ ግን . . . ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም” ብሎ ሲናገር እሱም ሆነ ታማኝ ክርስቲያን አንባቢዎቹ ምን ጊዜም ቢሆን ከይሖዋ ላለመራቅና እሱን ማገልገላቸውን ላለማቆም እንደቆረጡ መግለጹ ነበር። ወደኋላ ማፈግፈግ የመጨረሻ ውጤቱ ዘላለማዊ ጥፋት ብቻ ነው። ሆነ ብለው የይሖዋን መንፈስ የሚቃረን ነገር እንደሠሩት እንደ ሌሎቹ የእውነት ጠላቶች ሁሉ የአስቆሮቱ ይሁዳም ወደ ዘላለማዊ ጥፋት ካፈገፈጉት ሰዎች መካከል ይገኝበታል። (ዮሐንስ 17:12፤ 2 ተሰሎንቄ 2:3) እንዲህ ዓይነቶቹ ግለሰቦች በምሳሌያዊው የእሳት ባሕር ውስጥ ዘላለማዊ ጥፋት ከሚደርስባቸው ‘ፈሪዎች’ መካከል የሚመደቡ ናቸው። (ራእይ 21:8) እኛ በፍጹም እንደዚያ ዓይነት ሰዎች መሆን አንፈልግም!
6. ሰይጣን ዲያብሎስ ምን ዓይነት ጎዳና እንድንከተል ይፈልጋል?
6 ሰይጣን ዲያብሎስ ወደ ጥፋት እንድናፈገፍግ ይፈልጋል። “በተንኮል ድርጊቶች” የተካነ ስለሆነ የጥፋት ጎዳና በጥቃቅን ነገሮች እንደሚጀመር ያውቃል። (ኤፌሶን 6:11 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ቀጥተኛ በሆነ ስደት ዓላማውን ማሳካት ካቃተው በረቀቁ ዘዴዎች ተጠቅሞ የእውነተኛ ክርስቲያኖችን እምነት መሸርሸር ይፈልጋል። ደፋርና ቀናተኛ የሆኑትን የይሖዋ ምሥክሮች አፋቸውን ለማዘጋት ይፈልጋል። ጳውሎስ ለጻፈላቸው ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ምን ዘዴ እንደተጠቀመ እስቲ እንመልከት።
ክርስቲያኖች እንዲያፈገፍጉ የተደረገባቸው ተጽዕኖ
7. (ሀ) በኢየሩሳሌም የነበረው ጉባኤ ያስመዘገበው ታሪክ ምን ይመስል ነበር? (ለ) ጳውሎስ የጻፈላቸው የአንዳንዶቹ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?
7 ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤውን የጻፈው በ61 እዘአ ገደማ መሆኑን ማስረጃዎች ይጠቁማሉ። በኢየሩሳሌም ያለው ጉባኤ ኃዘንና ደስታ የተፈራረቀበት ጉባኤ ነበር። ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ከባድ ስደት ተነሳና በከተማዋ የሚገኙ ክርስቲያኖች እንዲበታተኑ አደረገ። ሆኖም ከዚያ ተከትሎ የመጣው የሰላም ወቅት ክርስቲያኖች በቁጥር እንዲበዙ አድርጓል። (ሥራ 8:4፤ 9:31) ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ሌሎች ስደቶችና መከራዎች በተለያየ ወቅት ተከስተዋል። ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤውን በጻፈበት ወቅት ጉባኤው እንደገና አንጻራዊ ሰላም አግኝቶ የነበረ ይመስላል። ያም ሆኖ ግን ተጽዕኖዎች ነበሩ። ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌም መጥፋት ትንቢት ከተናገረ ወደ ሦስት የሚጠጉ አሥርተ ዓመታት አልፈዋል። አንዳንዶች መጨረሻው ከመጠን በላይ እንደዘገየና እነሱ በሕይወት ሳሉ እንደማይመጣ ሳይሰማቸው አልቀረም። ሌሎች ደግሞ በተለይም በእምነት አዲስ የሆኑት በከባድ ስደት ስላልተፈተኑ በመከራ ጊዜ መጽናት አስፈላጊ ስለመሆኑ ብዙ የሚያውቁት ነገር የለም። (ዕብራውያን 12:4) ሰይጣን እነዚህ ሁኔታዎች ሳያመልጡት እንደ ጥሩ አጋጣሚ አድርጎ ለመጠቀም ይፈልግ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ምን “የተንኮል ድርጊቶችን” ተጠቅሞ ይሆን?
8. ብዙዎቹ አይሁዶች ገና ጨቅላ ለነበረው ክርስቲያን ጉባኤ ምን አመለካከት ነበራቸው?
8 በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያለው የአይሁድ ኅብረተሰብ ገና ጨቅላ የነበረውን ክርስቲያን ጉባኤ በንቀት ይመለከተው ነበር። የጳውሎስን ደብዳቤ ይዘት በመመርመር ትዕቢተኛ የሆኑ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎችና ተከታዮቻቸው በክርስቲያኖች ላይ እንዴት ይሳለቁ እንደነበር አንዳንድ ሐሳብ ማግኘት እንችላለን። ‘በኢየሩሳሌም ለብዙ መቶ ዓመታት የኖረ ታላቅ ቤተ መቅደስ አለን! ከሌሎች የበታች ካህናት ጋር በመሆን የአምልኮ ሥርዓት የሚያከናውን የታወቀ ሊቀ ካህን አለን። መሥዋዕቶች በየዕለቱ ይቀርባሉ። በመላእክት አማካኝነት ለሙሴ የተሰጠውና በሲና ተራራ በታላላቅ ምልክቶች የጸናው ሕግ አለን። ከአይሁድ እምነት አፈንግጠው የወጡት እነዚህ ከሃዲ ክርስቲያን ኑፋቄዎች እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሏቸውም!’ እያሉ ተሳልቀውባቸው ሊሆን ይችላል። ይህ የንቀት ንግግር የታለመለትን ግብ መትቶ ይሆን? አንዳንድ ዕብራውያን ክርስቲያኖች በዚህ ተረብሸው እንደነበር ግልጽ ነው። የጳውሎስ ደብዳቤ የደረሳቸው ልክ በተገቢው ጊዜ ነበር።
ፈጽሞ ወደ ጥፋት ማፈግፈግ የማይኖርባቸው ለምንድን ነው?
9. (ሀ) ለዕብራውያን የተጻፈው ደብዳቤ ዋና ጭብጥ ምን ነበር? (ለ) ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ በተሻለ ቤተ መቅደስ ያገለግሉ የነበረው በምን ሁኔታ ነበር?
9 ጳውሎስ በይሁዳ የሚገኙ ወንድሞቹና እህቶቹ በፍጹም ወደ ጥፋት ማፈግፈግ የማይኖርባቸው ለምን እንደሆነ ለማስረዳት የተጠቀመባቸውን ሁለት ምክንያቶች እንመርምር። የመጀመሪያው የክርስትና እምነት የአምልኮ ሥርዓት የላቀ መሆኑን እንዲገነዘቡ መርዳት ሲሆን ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በተጻፈው ደብዳቤ ውስጥም ይህ ጉዳይ በብዛት ተንጸባርቋል። ጳውሎስ በደብዳቤው ውስጥ በጠቅላላ ይህን ጭብጥ አብራርቷል። በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ የላቀ ትርጉም ላለውና ‘በእጅ ላልተሠራው’ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምሳሌ ነበር። (ዕብራውያን 9:11) እነዚያ ክርስቲያኖች ለንጹህ አምልኮ በተደረገው መንፈሳዊ ዝግጅት ውስጥ የማገልገል መብት አግኝተው ነበር። ከሙሴ የላቀ ቦታ ያለው ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛ በሆነለትና ከረዥም ዘመን በፊት ቃል በተገባውና በተሻለው አዲስ ቃል ኪዳን ሥር ሆነው የማገልገል መብት አግኝተዋል።—ኤርምያስ 31:31-34
10, 11. (ሀ) የኢየሱስ የዘር ሐረግ በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ሊቀ ካህን ሆኖ የማገልገል መብት እንዳያገኝ ያላደረገው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ያገለግል ከነበረው ሊቀ ካህን የላቀ ሊቀ ካህን የሆነው በምን መንገድ ነው?
10 በተጨማሪም እነዚህ ክርስቲያኖች የተሻለ ሊቀ ካህን ኢየሱስ ክርስቶስ ነበራቸው። ኢየሱስ ከአሮን የዘር ሐረግ የተገኘ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሊቀ ካህን የሆነው “እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት” ነው። (መዝሙር 110:4) የዘር ሐረጉ የማይታወቀው መልከ ጼዴቅ የጥንቷ ሳሌም ንጉሥ ከመሆኑም በላይ ሊቀ ካህኗ ነበር። በዚህ መንገድ ፍጽምና በሌለው ሰብዓዊ የዘር ሐረግ ላይ ሳይሆን በሚበልጠው ማለትም በራሱ በይሖዋ አምላክ መሐላ ካህን ለሆነው ለኢየሱስ መልከ ጼዴቅ ተስማሚ ትንቢታዊ ጥላ ሆኗል። እንደ መልከ ጼዴቅ ሁሉ ኢየሱስም ሊቀ ካህን ብቻ ሳይሆን ንጉሥም ሆኖ የሚያገለግል ከመሆኑም በላይ ለዘላለም ይኖራል።—ዕብራውያን 7:11-21
11 ከዚህም በተጨማሪ በኢየሩሳሌም ያለው ሊቀ ካህን ያቀርብ እንደነበረው ኢየሱስ ከዓመት ዓመት መሥዋዕቶችን ማቅረብ አያስፈልገውም። የእሱ መሥዋዕት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያቀረበው የራሱ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ነው። (ዕብራውያን 7:27) በቤተ መቅደሱ ይቀርቡ የነበሩት መሥዋዕቶች በጠቅላላ ኢየሱስ ያቀረበውን መሥዋዕት የሚያመለክቱ ጥላ ብቻ ነበሩ። እሱ ያቀረበው መሥዋዕት ለሚያምኑበት ሰዎች ሁሉ እውነተኛ የኃጢአት ይቅርታ ያስገኛል። በተጨማሪም ይህ ሊቀ ካህን በኢየሩሳሌም ያሉ ክርስቲያኖች ያውቁት የነበረው ያው ኢየሱስ መሆኑን በተመለከተ ጳውሎስ የሰጠው አስተያየት ልብ የሚነካ ነው። እሱም ትሁት፣ ደግ እንዲሁም ‘በድካማችን የሚራራልን’ ነው። (ዕብራውያን 4:15፤ 13:8) እነዚያ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የክርስቶስ የበታች ካህናት ሆነው የማገልገል ተስፋ ከፊታቸው ተዘርግቶላቸው ነበር! እንደገና “ወደ ደካማ ወደሚናቅም” ብልሹ የአይሁድ እምነት ማፈግፈግን እንዴት ሊያስቡት ይችላሉ?—ገላትያ 4:9
12, 13. (ሀ) ጳውሎስ ወደ ኋላ ማፈግፈግ እንደማይገባ ለማስረዳት የተጠቀመበት ሁለተኛ ምክንያት ምንድን ነው? (ለ) ዕብራውያን ክርስቲያኖች ከዚህ ቀደም ያሳዩት ጽናት በፍጹም ወደ ጥፋት እንዳያፈገፍጉ የሚያበረታታቸው ለምንድን ነው?
12 ጳውሎስ በዚህ ብቻ ሳይወሰን የዕብራውያን ክርስቲያኖች ወደ ጥፋት ማፈግፈግ የማይኖርባቸው ለምን እንደሆነ የሚያሳይ ሁለተኛ ማስረጃ ጠቅሷል። ይኸውም ቀደም ሲል ያሳዩት ጽናት ነው። “ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ መከራ በሆነበት በትልቅ ተጋድሎ የጸናችሁበትን የቀደመውን ዘመን አስቡ” ሲል ጽፏል። በነቀፋና በጭንቅ “እንደ መጫወቻ” ሆነው እንደነበር እንዲያስታውሱ አደረጋቸው። አንዳንዶች በእስር ተንገላተዋል፤ ሌሎች ደግሞ እስር ቤት ያሉትን በመርዳት የጭንቀታቸው ተካፋይ ሆነዋል። አዎን፣ ምሳሌ የሚሆን እምነትና ጽናት አሳይተዋል። (ዕብራውያን 10:32-34) ሆኖም ጳውሎስ እንዲህ ዓይነቱን መጥፎ ተሞክሮ ‘ዘወትር እንዲያስቡ’ የጠየቃቸው ለምንድን ነው? ይህ ተስፋ አስቆራጭ አይሆንምን?
13 ከዚህ ይልቅ ‘የቀደመውን ዘመን ማሰባቸው’ በፈተና ወቅት ይሖዋ እንዴት አድርጎ እንደደገፋቸው እንዲያስታውሱ ያደርጋቸዋል። በይሖዋ እርዳታ ብዙዎቹን የሰይጣን ጥቃቶች ተቋቁመዋል። ጳውሎስ “እግዚአብሔር፣ . . . ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 6:10) ይሖዋ ዳርቻ በሌለው መታሰቢያው ውስጥ የታማኝነት ሥራቸውን ሁሉ መዝግቦ ስለያዘው ያደረጉትን ነገር አይረሳም። ይህም ኢየሱስ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ ሲል የሰጠውን ምክር ያስታውሰናል። ይህ መዝገብ ሌባ ሊሰርቀው፣ ብልና ዝገት ሊያጠፉት አይችሉም። (ማቴዎስ 6:19-21) ይህ መዝገብ ሊጠፋ የሚችለው አንድ ክርስቲያን ወደ ጥፋት ካፈገፈገ ብቻ ነው። እንዲህ ማድረግ በሰማይ የተሰበሰበው መዝገብ በከንቱ እንዲጠፋ ያደርጋል። ጳውሎስ ዕብራውያን ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት ጎዳና ፈጽሞ መከተል እንደማይኖርባቸው ያቀረበው ይህ ማስረጃ ምንኛ ጠንካራ ነው! በታማኝነት ያገለገሉባቸው ዓመታት ለምን ከንቱ ሆነው ይቀራሉ? በታማኝነት መጽናቱ ተገቢ ብቻ ሳይሆን የተሻለም ነው።
ፈጽሞ ወደ ጥፋት ማፈግፈግ የማይኖርብን ለምንድን ነው?
14. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን ካጋጠሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች ጋር የሚመሳሰሉ ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል?
14 ዛሬ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም ወደ ጥፋት የማያፈገፍጉበት ተመሳሳይ የሆነ ጠንካራ ምክንያት አላቸው። በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ በሰጠን ንጹህ አምልኮ ውስጥ ያገኘነውን በረከት እናስብ። እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም የምንኖረው ባሏቸው ማራኪ ሃይማኖታዊ ሕንፃዎችና ቅርሳ ቅርሶች በመኩራራት በእኛ ላይ የሚሳለቁ ሰዎች በሞሉበት ጊዜ ውስጥ ነው። ሆኖም ይሖዋ የሚቀበለው የእኛን አምልኮ መሆኑን ዋስትና ሰጥቶናል። እንዲያውም እኛ ዛሬ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ያላገኟቸውን በረከቶች አግኝተናል። ‘ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። እነሱ ይኖሩ የነበሩት መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ገና ሥራውን በጀመረበት ወቅት ላይ ነበር። ክርስቶስ በ29 እዘአ በተጠመቀበት ጊዜ የዚህ ቤተ መቅደስ ሊቀ ካህን ሆነ። አንዳንዶች ተአምር ይፈጽም የነበረውን የአምላክን ልጅ አይተዋል። እሱ ከሞተ በኋላም ተጨማሪ ተአምራት ተፈጽመዋል። ይሁን እንጂ አስቀድሞ በተነገረው መሠረት እነዚህ ስጦታዎች አከተሙ።—1 ቆሮንቶስ 13:8
15. ዛሬ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚገኙት የትኛው ትንቢት በሚፈጸምበት ወቅት ነው? ይህስ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?
15 እኛ ግን የምንኖረው በሕዝቅኤል 40 እስከ 48 ላይ የሚገኘው ስለ ቤተ መቅደስ የሚናገረው ሰፊ ትንቢት ታላቅ ፍጻሜውን እያገኘ ባለበት ወቅት ነው።a አምላክ ለንጹህ አምልኮ ያደረገው ዝግጅት ተመልሶ ሲቋቋም ተመልክተናል። ይህ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ከማንኛውም ዓይነት ሃይማኖታዊ ብክለትና የጣዖት አምልኮ ጸድቷል። (ሕዝቅኤል 43:9፤ ሚልክያስ 3:1-5) ይህ የማጽዳት ሥራ መከናወኑ ለእኛ ያስገኘውን ጥቅም አስብ።
16. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ተስፋ የሚያስቆርጥ ምን ሁኔታ ገጥሟቸው ነበር?
16 በአንደኛው መቶ ዘመን ለነበረው ክርስቲያን ጉባኤ የወደፊቱ ሁኔታ የጨለመ ነበር። ኢየሱስ አዲስ በተዘራ የስንዴ ማሳ ላይ በአናቱ እንክርዳድ ሲዘራ ስንዴውን ከእንክርዳዱ ለመለየት አስቸጋሪ የሚሆነውን ያህል የጨለመ ሁኔታ እንደሚኖር አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 13:24-30) የሆነውም ይኸው ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ማብቂያ ገደማ ላይ በዕድሜ ገፍቶ የነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ የክርስትናን እምነት ከብክለት ለመከላከል የመጨረሻውን ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም ክህደት በእጅጉ በመስፋፋት ላይ ነበር። (2 ተሰሎንቄ 2:6፤ 1 ዮሐንስ 2:18) ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ መንጋውን የሚጨቁንና የተለየ ልብስ የሚለብስ አንድ የቀሳውስት ቡድን ተነሳ። ክህደቱ ልክ እንደ ጋንግሪን እየተስፋፋ ሄደ። ይህ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ምንኛ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነበር! ለንጹህ አምልኮ የተደረገው አዲስ ዝግጅት ብልሹ በሆነ አምልኮ ሲበረዝ ተመልክተዋል። ይህ የሆነው ደግሞ ክርስቶስ ጉባኤውን ካቋቋመ መቶ ዓመት እንኳ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው።
17. ዛሬ ያለው ክርስቲያን ጉባኤ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበረው ክርስቲያን ጉባኤ ይበልጥ ረጅም ዕድሜ አስቆጥሯል የምንለው ከምን አንጻር ነው?
17 አሁን ንጽጽሩን ተመልከት። ንጹህ አምልኮ ሐዋርያት ሞተው እስኪያልቁ ድረስ ከቆየበት ጊዜ ይልቅ ዛሬ ረጅም ዕድሜ አስቆጥሯል! የዚህ መጽሔት የመጀመሪያ እትም ከወጣበት ከ1879 ጀምሮ ይሖዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠራ በሚሄድ አምልኮ ባርኮናል። በ1918 ይሖዋና ኢየሱስ ክርስቶስ ለማጽዳት ወደ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ገብተው ነበር። (ሚልክያስ 3:1-5) ከ1919 ጀምሮ ይሖዋ አምላክን ለማምለክ የተደረገው ዝግጅት ደረጃ በደረጃ እየጠራ መጥቷል። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ያለን እውቀትም ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። (ምሳሌ 4:18) ለዚህ ሁሉ መመስገን ያለበት ማን ነው? ፍጽምና የሌላቸው ሰብዓዊ ሰዎች ሊሆኑ አይችሉም። የጉባኤ ራስ ከሆነው ከልጁ ጋር በመሆን በዚህ በተበከለ ጊዜ ሕዝቡን ከብክለት መጠበቅ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። ስለዚህ ዛሬ ባለው ንጹህ አምልኮ ውስጥ እንድንሳተፍ ስለፈቀደልን ይሖዋን ልናመሰግነው ይገባናል። እንዲሁም ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ ሰዎች መካከል ላለመሆን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ!
18. ፈጽሞ ወደ ጥፋት እንዳናፈገፍግ የሚያደርገን ምን ምክንያት አለን?
18 እንደ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም በፍርሃት ወደ ኋላ ከማፈግፈግ የምንርቅበት ሁለተኛ ምክንያት ያለን ሲሆን ይህም ከዚህ ቀደም ያሳየነው ጽናት ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይሖዋን ማገልገል የጀመርንም እንሁን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በታማኝነት ስናገለግል የቆየን በክርስቲያናዊ ሥራ ያስመዘገብነው መዝገብ አለን። መታሰርም ይሁን፣ እገዳ፣ የጭካኔ ድርጊትም ሆነ ንብረትን ማጣት ብቻ ምንም ይሁን ምን አብዛኞቻችን ስደት ደርሶብናል። ብዙዎች ደግሞ የቤተሰብን ተቃውሞ፣ የሌሎችን ማንቋሸሽ፣ ፌዝና ግዴለሽነት ተቋቁመዋል። የተለያዩ የሕይወት ውጣ ውረዶችና ፈተናዎች ቢኖሩም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችንን በመቀጠል ሁላችንም ጽናት አሳይተናል። እንዲህ በማድረጋችንም ይሖዋ የማይረሳው የጽናት መዝገብ በሰማይ አከማችተናል። ስለዚህ ይህ ጊዜ ትተነው ወደመጣነው ብልሹ አሮጌ ሥርዓት የምናፈገፍግበት ጊዜ አይደለም! ድካማችን ሁሉ መና ሆኖ እንዲቀር ለምን እናደርጋለን? በተለይ መጨረሻው ሊመጣ “በጣም ጥቂት ጊዜ” ብቻ ቀርቶት ባለበት በአሁኑ ወቅት ወደ ጥፋት ማፈግፈግ እንዴት ያለ ትልቅ ኪሳራ ነው።—ዕብራውያን 10:37
19. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?
19 አዎን፣ ‘ከሚያምኑቱ እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉት’ ላለመሆን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ! (ዕብራውያን 10:39) ከዚህ መግለጫ ጋር የምንስማማ ሰዎች መሆናችንን ማረጋገጥ የምንችለው እንዴት ነው? ሌሎች ክርስቲያኖችም እንዲህ እንዲያደርጉ ልንረዳቸው የምንችለውስ እንዴት ነው? ይህ ጉዳይ በሚቀጥለው ርዕስ ይብራራል።
-
-
ከሚያምኑት ወገን እንሁንመጠበቂያ ግንብ—1999 | ታኅሣሥ 15
-
-
ከሚያምኑት ወገን እንሁን
“እኛ . . . ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ ነን።”—ዕብራውያን 10:39
1. የእያንዳንዱ ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ እምነት ውድ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
በሚቀጥለው ጊዜ የይሖዋ አምላኪዎች በተሰበሰቡበት የመንግሥት አዳራሽ ስትገኝ ትንሽ ቆም በልና በዙሪያህ ያሉትን ወንድሞችና እኅቶች ተመልከት። እምነት ያሳዩባቸውን በርካታ ሁኔታዎች አስብ። ለብዙ አሥርተ ዓመታት አምላክን ያገለገሉ አረጋውያንን፣ በየዕለቱ የሚደርስባቸውን የእኩዮች ተጽዕኖ እየተቋቋሙ ያሉ ወጣቶችንና ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ልጆች ለማሳደግ ከፍተኛ ትግል እያደረጉ ያሉ ወላጆችን ልትመለከት ትችላለህ። ብዙ ኃላፊነቶችን የተሸከሙ የጉባኤ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮችም አሉ። አዎን፣ ይሖዋን ለማገልገል ሲሉ ብዙ ዓይነት መሰናክሎችን ያለፉ በተለያየ የዕድሜ ክልል የሚገኙ መንፈሳዊ ወንድሞችንና እህቶችን ትመለከታለህ። የእያንዳንዳቸው እምነት እንዴት ውድ ነው!—1 ጴጥሮስ 1:7
2. በዕብራውያን ምዕራፍ 10 እና 11 ላይ የሚገኘው የጳውሎስ ምክር ዛሬ ለእኛ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
2 ፍጹማን ካልሆኑ ሰዎች መካከል የጳውሎስን ያክል የእምነትን አስፈላጊነት የተገነዘበ ሰው ይኖራል ለማለት ያዳግታል። እንዲያውም ጳውሎስ እውነተኛ እምነት ‘ነፍስን ሊያድን’ እንደሚችል ተናግሯል። (ዕብራውያን 10:39) ሆኖም ጳውሎስ በዚህ እምነት የለሽ ዓለም ውስጥ እምነት ጥቃት ሊደርስበትና ሊሸረሸር እንደሚችል ያውቅ ነበር። እምነታቸውን ለመጠበቅ ይታገሉ የነበሩት በኢየሩሳሌምና በይሁዳ የሚገኙ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ሁኔታ ጳውሎስን በእጅጉ አሳስቦት ነበር። ዕብራውያን ምዕራፍ 10 እና 11ን በከፊል በምንመረምርበት ጊዜ ጳውሎስ እምነታቸውን ለመገንባት የተጠቀመበትን ዘዴ ልብ እንበል። እግረ መንገዳችንንም የራሳችንንም ሆነ የሌሎችን እምነት እንዴት መገንባት እንደምንችል እንማራለን።
በሌሎች ላይ ትምክህት እንዳላችሁ ግለጹላቸው
3. በዕብራውያን 10:39 ላይ የሚገኙት የጳውሎስ ቃላት ጳውሎስ በወንድሞቹና በእህቶቹ እምነት ላይ ትምክህት እንደነበረው የሚያሳዩት እንዴት ነው?
3 በመጀመሪያ የምናስተውለው ጳውሎስ ለአድማጮቹ የነበረውን አዎንታዊ አመለካከት ነው። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም።” (ዕብራውያን 10:39) ጳውሎስ የታማኝ ክርስቲያን ወንድሞቹን ደካማ ጎን ሳይሆን ጠንካራ ጎን ተመልክቶ ነበር። በተጨማሪም “እኛ” የሚል መግለጫ እንደተጠቀመ ልብ በሉ። ጳውሎስ ጻድቅ ሰው ነበር። ይሁን እንጂ ራሱን ያለ ልክ ጻድቅ አድርጎ በማቅረብ አድማጮቹን ዝቅ ዝቅ አላደረገም። (ከመክብብ 7:16 ጋር አወዳድር።) ከዚህ ይልቅ ራሱንም ከእነሱ ጋር ደምሮ ገልጿል። እሱም ሆነ ታማኝ ክርስቲያን አንባቢዎቹ ተስፋ አስቆራጭ የሆኑ እንቅፋቶች ቢገጥሟቸውም ወደ ጥፋት ላለማፈግፈግ ቆራጦች በመሆን እምነት ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን እንደሚያስመሰክሩ ገልጿል።
4. ጳውሎስ በእምነት አጋሮቹ ላይ ትምክህት ሊኖረው የቻለው ለምንድን ነው?
4 ጳውሎስ እንዲህ ዓይነት ትምክህት ሊኖረው የቻለው ለምንድን ነው? የዕብራውያን ክርስቲያኖችን ድክመት ማየት ተስኖት ነበር ማለት ነውን? በፍጹም። እንዲያውም መንፈሳዊ ድክመቶቻቸውን እንዲያሸንፉ ለመርዳት ቀጥተኛ የሆነ ምክር ሰጥቷቸዋል። (ዕብራውያን 3:12፤ 5:12-14፤ 6:4-6፤ 10:26, 27፤ 12:5) ያም ሆኖ ግን ጳውሎስ በወንድሞቹ ላይ ትምክህት እንዲኖረው ያደረጉት ቢያንስ ሁለት ጥሩ ምክንያቶች ነበሩት። (1) ጳውሎስ የይሖዋን ምሳሌ በመኮረጅ የአምላክን አገልጋዮች በይሖዋ ዓይን ለመመልከት ጥረት አድርጓል። ይህም ማለት ድክመቶቻቸውን ብቻ ከመመልከት ይልቅ መልካም ባሕርያቶቻቸውንና ወደፊት መልካም ለማድረግ ሊመርጡ የሚችሉ መሆናቸውን ተመልክቷል። (መዝሙር 130:3፤ ኤፌሶን 5:1) (2) ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ ባለው ኃይል ላይ ጠንካራ እምነት ነበረው። ይሖዋ እሱን በታማኝነት ለማገልገል ለሚጥር ማንኛውም ክርስቲያን “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” እንዳይሰጥ ሊያግደው የሚችል እንቅፋት ወይም ሰብዓዊ ድክመት እንደማይኖር ያውቅ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 4:7 NW፤ ፊልጵስዩስ 4:13) ስለዚህ ጳውሎስ በወንድሞቹና በእህቶቹ ላይ የነበረው ትምክህት የተሳሳተ፣ ከእውነታው የራቀ ወይም ጭፍን አልነበረም። ጽኑ መሠረትና ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ያለው ነበር።
5. በወንድሞቻችን ላይ ትምክህት በማሳደር ረገድ የጳውሎስን ምሳሌ ልንኮርጅ የምንችለው እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?
5 ጳውሎስ ያሳየው ትምክህት ወደ ሌሎችም ተጋብቶ ተመሳሳይ ባሕርይ እንዲያሳዩ እንዳነሳሳቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ጳውሎስ እንዲህ በሚያበረታታ መንገድ መናገሩ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ለነበሩት ጉባኤዎች ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቶ መሆን አለበት። ከአይሁድ ተቃዋሚዎቻቸው የሚሰነዘርባቸውን ቅስም የሚሰብር ፌዝና ንቀት ለመቋቋም እየታገሉ ባሉበት ወቅት የተሰጣቸው ይህ ማበረታቻ ዕብራውያን ክርስቲያኖች እምነት ያላቸው ሰዎች ሆነው ለመገኘት ከልብ ቆርጠው እንዲነሱ ረድቷቸዋል። እኛስ እርስ በርሳችን እንዲህ መበረታታት እንችል ይሆን? የሌሎችን ስህተትና የባሕርይ ጉድለት መዘርዘር በጣም ቀላል ነው። (ማቴዎስ 7:1-5) ሆኖም እያንዳንዱ ሰው ያለውን በዓይነቱ ልዩ የሆነ እምነት ብንመለከትና ብናደንቅ እርስ በርሳችን ይበልጥ ልንበረታታ እንችላለን። እንዲህ ያለው ማበረታቻ እምነትን ይበልጥ እንደሚያጎለብት የታወቀ ነው።—ሮሜ 1:11, 12
በአምላክ ቃል በጥሩ ሁኔታ መጠቀም
6. ጳውሎስ በዕብራውያን 10:38 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን ቃላት የጠቀሰው ከየት ነው?
6 በተጨማሪም ጳውሎስ ቅዱሳን ጽሑፎችን በጥበብ በመጠቀም የእምነት አጋሮቹን እምነት ገንብቷል። ለምሳሌ ያህል “ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ፣ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 10:38) እዚህ ላይ ጳውሎስ ነቢዩ ዕንባቆም የተናገረውን መጥቀሱ ነበር።a እነዚህ ቃላት የትንቢት መጻሕፍትን ጠንቅቀው ለሚያውቁት የጳውሎስ አንባቢዎች ማለትም ለዕብራውያን ክርስቲያኖች እንግዳ እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። በ61 እዘአ በኢየሩሳሌምና በአቅራቢያዋ የሚገኙ ክርስቲያኖችን እምነት ለማጠንከር ከነበረው ግብ አንጻር ጳውሎስ የዕንባቆምን ምሳሌ ለመጠቀም መምረጡ የተገባ ነበር። ለምን?
7. ዕንባቆም ትንቢቱን የመዘገበው መቼ ነው? በዚያን ወቅት በይሁዳ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?
7 ከሁኔታዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ዕንባቆም መጽሐፉን የጻፈው ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ ከመጥፋቷ ከሁለት አሥርተ ዓመታት በፊት ነበር። ‘መራርና ፈጣን’ ሕዝብ የሆኑት ከለዳውያን (ወይም ባቢሎናውያን) ድንገት በይሁዳ ላይ እንደሚነሱና ኢየሩሳሌምን እንደሚያጠፉ እንዲሁም ሕዝቡንም ሆነ ነገሥታቶቻቸውን እንደሚውጡ ነቢዩ በራእይ ተመልክቶ ነበር። (ዕንባቆም 1:5-11) ሆኖም እንዲህ ዓይነት ጥፋት እንደሚመጣ ትንቢት የተነገረው ከአንድ መቶ ዓመት ከሚበልጥ ጊዜ በፊት ማለትም ከኢሳይያስ ዘመን ጀምሮ ነበር። በዕንባቆም ዘመን ጥሩ ንጉሥ በነበረው በኢዮስያስ ምትክ ኢዮአቄም ነግሦ የነበረ ሲሆን ይህም በይሁዳ ክፋት እንደገና እንዲስፋፋ አደረገ። ኢዮአቄም በይሖዋ ስም የሚናገሩ ሰዎችን ያሳድድ አልፎ ተርፎም ይገድል ነበር። (2 ዜና መዋዕል 36:5፤ ኤርምያስ 22:17፤ 26:20-24) በጭንቀት የተዋጠው ነቢዩ ዕንባቆም “አቤቱ፣ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው?” በማለት ሮሮ ማሰማቱ አያስገርምም።—ዕንባቆም 1:2
8. የዕንባቆም ምሳሌ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩትም ሆነ ዛሬ ላሉት ክርስቲያኖች ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
8 ዕንባቆም የኢየሩሳሌም ጥፋት ምን ያህል እንደቀረበ አያውቅም ነበር። በተመሳሳይም የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የአይሁድ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ መቼ እንደሚሆን አያውቁም ነበር። እኛም ብንሆን በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ላይ የይሖዋ ፍርድ የሚጀምርበትን ‘ቀንና ሰዓት’ አናውቅም። (ማቴዎስ 24:36) እንግዲያው ይሖዋ ለዕንባቆም የሰጠውን ድርብ መልስ ልብ እንበል። በመጀመሪያ ደረጃ ፍጻሜው ከተቀጠረለት ጊዜ ዝንፍ እንደማይል ለነቢዩ አረጋገጠለት። በሰብዓዊ አመለካከት የዘገየ ቢመስልም እንኳ አምላክ “አይዘገይም” ሲል ተናግሯል። (ዕንባቆም 2:3) በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ይሖዋ “ጻድቅ በእምነቱ በሕይወት ይኖራል” በማለት ለዕንባቆም ነገረው። (ዕንባቆም 2:4) ይህ እንዴት ያለ ግሩምና ለመረዳት የማይከብድ እውነት ነው! ትልቅ ለውጥ የሚያመጣው መጨረሻው የሚመጣበት ጊዜ ሳይሆን የእኛ በእምነት መቀጠል አለመቀጠል ነው።
9. ታዛዥ የሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች ታማኝ ሆነው በመገኘታቸው (ሀ) በ607 ከዘአበ (ለ) ከ66 እዘአ በኋላ በሕይወት ሊተርፉ የቻሉት እንዴት ነው? (ሐ) እምነታችንን ማጎልበታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
9 ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ በጠፋችበት ወቅት ኤርምያስ፣ የእሱ ጸሐፊ የነበረው ባሮክ፣ አቤሜሌክና ታማኞቹ ሬካባውያን ይሖዋ ለዕንባቆም የሰጠው ተስፋ ሲፈጸም ተመልክተዋል። በኢየሩሳሌም ላይ ከደረሰው አሰቃቂ ጥፋት ተርፈው ‘በሕይወት መኖራቸውን ቀጥለዋል።’ ለምን? ይሖዋ ለታማኝነታቸው ወሮታ ስለከፈላቸው ነው። (ኤርምያስ 35:1-19፤ 39:15-18፤ 43:4-7፤ 45:1-5) በተመሳሳይም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ዕብራውያን ክርስቲያኖች ለጳውሎስ ምክር አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተው መሆን አለበት። ምክንያቱም በ66 እዘአ የሮማ ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት መሰንዘር ከጀመረ በኋላ ባልታወቀ ምክንያት ወደ ኋላ ሲያፈገፍግ በወቅቱ የነበሩት ክርስቲያኖች ኢየሱስ ወደ ተራራ ስለመሸሽ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ በታማኝነት ተግባራዊ አድርገዋል። (ሉቃስ 21:20, 21) በሕይወት መኖራቸውን መቀጠል የቻሉት ታማኝ ሆነው በመገኘታቸው ነው። እኛም በተመሳሳይ መጨረሻው በሚመጣበት ጊዜ ታማኝ ሆነን ከተገኘን በሕይወት መኖራችንን እንቀጥላለን። ከአሁኑ እምነታችንን እንድናጠነክር የሚያበረታታ እንዴት ያለ ግሩም ሐሳብ ነው!
የእምነት ምሳሌዎችን ሕያው አድርጎ መግለጽ
10. ጳውሎስ የሙሴን እምነት የገለጸው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ሙሴን ልንመስለው የምንችለው እንዴት ነው?
10 በተጨማሪም ጳውሎስ ጥሩ የእምነት ምሳሌዎችን በመጥቀስ የአንባቢዎቹን እምነት ገንብቷል። ዕብራውያን ምዕራፍ 11ን በምታነብበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለ ታሪኮችን እንዴት ሕያው በሆነ መንገድ እንደጠቀሰ ልብ በል። ለምሳሌ ያህል ስለ ሙሴ ሲናገር “የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና” ብሏል። (ዕብራውያን 11:27 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) በሌላ አነጋገር ይሖዋ ለሙሴ እውን ሆኖለት ስለነበር ሙሴ የማይታየውን አምላክ ያየው ያክል ነበር። ለእኛስ እንዲህ ሊባልልን ይችላልን? ከይሖዋ ጋር ስለሚኖር ዝምድና መናገር ቀላል ነው፤ ይህን ዝምድና መገንባትና ማጠንከር ግን ሥራ የሚጠይቅ ነገር ነው። ይህ ልንደክምለት የሚገባ ሥራ ነው! ይሖዋ ለእኛ እውን ነውን? ጥቃቅን የሚመስሉ ውሳኔዎችን በምናደርግበት ጊዜ ጭምር እሱን ግምት ውስጥ እናስገባለንን? እንዲህ ዓይነት እምነት ኃይለኛ ተቃውሞ ቢደርስብን እንኳ እንድንጸና ይረዳናል።
11, 12. (ሀ) የሄኖክ እምነት የተፈተነው በምን ዓይነት ሁኔታዎች ስር ሊሆን ይችላል? (ለ) ሄኖክ ምን የሚያበረታታ ሽልማት ተቀብሏል?
11 በተጨማሪም የሄኖክን እምነት ተመልከት። የገጠመው ተቃውሞ ልንገምተው ከምንችለው በላይ ነው። ሄኖክ በወቅቱ የነበሩትን ክፉ ሰዎች የሚያሰቃይ የፍርድ መልእክት መናገር ነበረበት። (ይሁዳ 14, 15) በዚህ ታማኝ ሰው ላይ አረመኔያዊ የጭካኔ ተግባር እንዲፈጸምበት የሚያደርግ ስደት አንዣቦ ስለነበር በጠላቶቹ እጅ እንዳይወድቅ ሲል ይሖዋ “ወስዶታል”፤ ማለትም በሞት እንዲያንቀላፋ አድርጎታል። ስለዚህ ሄኖክ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን ሲያገኝ የመመልከት አጋጣሚ አላገኘም። ያም ሆኖ ግን በአንዳንድ ሁኔታዎች ሲታይ የተሻለ ሽልማት ተቀብሏል።—ዕብራውያን 11:5፤ ዘፍጥረት 5:22-24
12 “[ሄኖክ] ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና” ሲል ጳውሎስ ተናግሯል። (ዕብራውያን 11:5) ይህ ምን ማለት ነው? ሄኖክ በሞት ከማንቀላፋቱ በፊት ምናልባትም ወደፊት ከሞት ሲነሳ የሚያገኛትን ምድራዊት ገነት የሚያሳይ አንድ ራእይ አይቶ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ይሖዋ፣ ባሳየው ታማኝነት መደሰቱን ሄኖክ እንዲያውቅ አድርጎታል። ሄኖክ የይሖዋን ልብ ደስ አሰኝቷል። (ከምሳሌ 27:11 ጋር አወዳድር።) የሄኖክን የሕይወት ተሞክሮ ማሰብ ልብን የሚነካ አይደለም? እንዲህ ዓይነት በእምነት ላይ የተመሠረተ ሕይወት እንዲኖርህ ትፈልጋለህ? እንግዲያው እንዲህ ባሉ የእምነት ምሳሌዎች ላይ አሰላስል። አሁን በእውን እንዳሉ አድርገህ ተመልከታቸው። ከዕለት ወደ ዕለት በእምነት ለመመላለስ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። በተጨማሪም እምነት ያላቸው ሰዎች ይሖዋን ለማገልገል የሚነሱት አምላክ የገባቸውን ተስፋዎች ሁሉ የሚፈጽምበትን ጊዜ በአእምሮ በመያዝ ወይም የጊዜ ገደብ በማበጀት እንዳልሆነ ማሰብ ያስፈልጋል። ከዚህ ይልቅ ይሖዋን ለዘላለም ማገልገል ቁርጥ ውሳኔያችን ሊሆን ይገባል! እንዲህ ማድረጋችን በዚህ የነገሮች ሥርዓትም ሆነ በመጪው ጊዜ በተሻለ የሕይወት ጎዳና ላይ እንድንመላለስ ያስችለናል።
በእምነት እየጎለበቱ መሄድ የሚቻለው እንዴት ነው?
13, 14. (ሀ) በዕብራውያን 10:24, 25 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት የጳውሎስ ቃላት ስብሰባዎቻችንን አስደሳች ለማድረግ ሊረዱን የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) የክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ዋነኛ ዓላማ ምንድን ነው?
13 ጳውሎስ ዕብራውያን ክርስቲያኖች እምነታቸውን ማጎልበት የሚችሉባቸውን በርካታ ተግባራዊ መንገዶች ጠቅሶላቸዋል። እስቲ ሁለቱን ብቻ እንመርምር። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ ዘወትር እንድንገኝ ለማሳሰብ በዕብራውያን 10:24, 25 ላይ የሰጠው ምክር ትዝ እንደሚለን የታወቀ ነው። ሆኖም በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት እነዚህ የጳውሎስ ቃላት በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ በታዛቢነት እንድንገኝ ብቻ የሚያበረታቱ እንዳልሆኑ አስታውሱ። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ እነዚህን ስብሰባዎች የገለጻቸው እርስ በርስ ለመተዋወቅ፣ አምላክን በተሻለ መንገድ ለማገልገል አንዱ ሌላውን ለማነቃቃትና እርስ በርስ ለመበረታታት የሚያስችሉ ጥሩ አጋጣሚዎች እንደሆኑ አድርጎ ነው። በዚያ የምንገኘው ለመቀበል ብቻ ሳይሆን ለመስጠትም ጭምር ነው። ይህ ደግሞ ስብሰባዎቻችን አስደሳች እንዲሆኑ አስተዋጽዖ ያደርጋል።—ሥራ 20:35
14 ሆኖም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የምንገኝበት ዋነኛ ዓላማ ይሖዋን ለማምለክ ነው። አብረን በመጸለይና በመዘመር፣ በጥሞና በማዳመጥ እንዲሁም በምንሰጠው ሐሳብና በስብሰባ ላይ በምናቀርባቸው ክፍሎች አማካኝነት ለይሖዋ በምናሰማው ውዳሴ “የከንፈሮችን ፍሬ” በማቅረብ አምልኮታችንን እናከናውናለን። (ዕብራውያን 13:15) እነዚህን ግቦች በአእምሮአችን የምንይዝና በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የምንጥር ከሆነ ያለ ምንም ጥርጥር እምነታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ ይሄዳል።
15. ጳውሎስ ዕብራውያን ክርስቲያኖች አገልግሎታቸውን አጥብቀው እንዲይዙ ያሳሰባቸው ለምንድን ነው? ዛሬም ይህ ዓይነት ምክር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
15 ሌላው እምነታችንን የምንገነባበት መንገድ የስብከቱ ሥራ ነው። ጳውሎስ “የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 10:23) ሰዎች አንድ ነገር ከእጃቸው ሊያመልጣቸው እንደሆነ ብታይ ጠበቅ አድርገው እንዲይዙት ማሳሰቢያ ትሰጧቸው ይሆናል። ሰይጣን ዕብራውያን ክርስቲያኖች አገልግሎታቸውን እንዲተዉ ለማድረግ ተጽእኖ ሲያደርግ ነበር፤ ዛሬ ባሉ የአምላክ ሕዝቦችም ላይ ተጽእኖ ያደርጋል። እንዲህ ዓይነት ተጽእኖ ሲያጋጥመን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ጳውሎስ ምን እንዳደረገ ተመልከት።
16, 17. (ሀ) ጳውሎስ ለአገልግሎቱ ድፍረት ያገኘው እንዴት ነው? (ለ) በአንዱ የክርስቲያናዊ አገልግሎት ዘርፍ መካፈል የሚያስፈራን ከሆነ ምን እርምጃዎች መውሰድ ይኖርብናል?
16 ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለሚገኙ ክርስቲያኖች እንደሚከተለው ሲል ጽፎላቸዋል:- “እንደምታውቁት በፊልጵስዩስ አስቀድመን መከራ ተቀብለን ተንገላትተንም፣ በብዙ ገድል የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንናገር ዘንድ በአምላካችን ደፈርን።” (1 ተሰሎንቄ 2:2) ጳውሎስና ጓደኞቹ በፊልጵስዩስ ‘የተንገላቱት’ እንዴት ነበር? አንዳንድ ሃይማኖታዊ ምሁራን እንደሚሉት ጳውሎስ የተጠቀመበት ግሪክኛ ቃል መሰደብን፣ መዋረድን ወይም ለሥቃይ መዳረግን ያመለክታል። በፊልጵስዩስ የሚገኙ ባለሥልጣናት በዱላ ደብድበዋቸዋል፣ ወኅኒ ቤት ጨምረዋቸዋል እንዲሁም በእግር ግንድ ውስጥ አስገብተው አስረዋቸዋል። (ሥራ 16:16-24) ጳውሎስ ይህ ሁሉ ስቃይ ሲደርስበት ምን ተሰማው? ፍርሃት፣ በሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞው ቀጥሎ ከሚጎበኛቸው ከተማዎች አንዷ ወደሆነችው ወደ ተሰሎንቄ እንዳይሄድ አድርጎታልን? በፍጹም፣ እንዲያውም ይበልጥ ‘ደፋር’ ሆኗል። ፍርሃትን በማሸነፍ በድፍረት መስበኩን ቀጥሏል።
17 ጳውሎስ ይህን ድፍረት ያገኘው ከየት ነው? ከራሱ? በፍጹም፤ “በአምላካችን” ደፈርን ሲል ተናግሯል። ለመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የተዘጋጀ አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ይህ አባባል “አምላክ ፍርሃትን ከልባችን ውስጥ አውጥቶ ጣለልን” ተብሎም ሊተረጎም እንደሚችል ይገልጻል። በተለይ አገልግሎት ሲባል የሚያስፈራህ ከሆነ ወይም ደግሞ በተወሰኑ የአገልግሎቱ ዘርፎች ለመካፈል ድፍረቱ ከሌለህ ተመሳሳይ እርዳታ ለማግኘት ለምን ይሖዋን አትማጸነውም? ፍርሃትን ከልብህ ውስጥ አውጥቶ እንዲጥልልህ ጠይቀው። ለሥራው ድፍረትን እንዲሰጥህ ጠይቀው። በተጨማሪም አንዳንድ ሌሎች እርምጃዎችን ውሰድ። አንተን በሚያስፈራህ የአገልግሎቱ ዘርፍ በመካፈል ልምድ ካለው ሰው ጋር ለመሥራት ዝግጅት አድርግ። ይህም በንግድ አካባቢዎች ማገልገልን፣ መንገድ ላይ መመሥከርን፣ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መስበክን ወይም በስልክ መመሥከርን የሚመለከት ሊሆን ይችላል። መጀመሪያ ላይ ምናልባት የአገልግሎት ጓደኛህ ቀዳሚ ለመሆን ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል። ከሆነ እሱን በማየት መማር ትችላለህ። ሆኖም ከዚያ በኋላ ራስህ ለመሞከር አንድትችል ድፍረት ማግኘት አለብህ።
18. በአገልግሎታችን ደፋሮች ከሆንን ምን በረከቶችን እናገኛለን?
18 ድፍረት ካገኘህ ምን ውጤት ሊገኝ እንደሚችል አስብ። ተስፋ ሳትቆርጥ ከጸናህ እውነትን ለሌሎች በማካፈል ረገድ ከዚህ በፊት ያላገኘሃቸውን ጥሩ ጥሩ ተሞክሮዎች ልታገኝ እንደምትችል የታወቀ ነው። (ገጽ 25ን ተመልከት።) ለአንተ አስቸጋሪ የሆነ ነገር በመሥራት ይሖዋን እያስደሰትከው እንዳለህ በማወቅ እርካታ ልታገኝ ትችላላችሁ። ፍርሃትህን በማሸነፍ ረገድ የይሖዋ በረከትና ድጋፍ አይለይህም። እምነትህ ጠንካራ ይሆናል። የራስህን እምነት ሳትገነባ የሌሎችን እምነት እገነባለሁ ማለት ዘበት ነው።—ይሁዳ 20, 21
19. ‘እምነት እንዳላቸው የሚያሳዩ’ ምን ውድ ሽልማት ይጠብቃቸዋል?
19 የራስህንም ሆነ የሌሎችን እምነት ለማጎልበት መጣርህን ቀጥል። የአምላክን ቃል በጥበብ በመጠቀም፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቅሳቸውን የእምነት ምሳሌዎች የሕይወት ታሪክ በማጥናትና ሕያው አድርጎ በመመልከት፣ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በመዘጋጀትና ተሳትፎ በማድረግ እንዲሁም ውድ መብት የሆነውን አገልግሎት አጥብቆ በመያዝ ይህን ማድረግ ትችላለህ። እንዲህ ካደረግህ በእርግጥ ‘ከሚያምኑት ወገን’ ነኝ ብለህ በእርግጠኝነት ልትናገር ትችላለህ። በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች ውድ የሆነ ሽልማት እንደሚጠብቃቸው አስታውስ። “ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ” ናቸው።b እምነትህ እየጎለበተ እንዲሄድና ይሖዋ አምላክ ለዘላለም በሕይወት እንዲጠብቅህ እንመኛለን!—ዕብራውያን 10:39
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ጳውሎስ የጠቀሰው በሰፕቱጀንት መሠረት “ማንም ወደ ኋላ ቢያፈገፍግ ነፍሴ በእሱ ደስ አይላትም” የሚል ሐረግ የሚጨምረውን ዕንባቆም 2:4ን ነበር። ይህ አገላለጽ አሁን በእጅ ባሉ የብራና ዕብራይስጥ ጽሑፎች ውስጥ በአንዳቸውም ላይ አይገኝም። አንዳንዶች ሰፕቱጀንት የተገለበጠው አሁን በእጅ በማይገኙ በጣም ጥንታዊ የብራና ጽሑፎች ላይ ነው የሚል አስተያየት ይሰጣሉ። ያም ሆነ ይህ ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ይህን ጥቅስ በመልእክቱ ውስጥ ጨምሮታል። ስለዚህ ይህ ሐሳብ መለኮታዊ ድጋፍ አለው ማለት ነው።
b በ2000 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት ጥቅስ “እኛ ግን . . . ከሚያምኑቱ ነን እንጂ . . . ከሚያፈገፍጉ አይደለንም” የሚለው ይሆናል።—ዕብራውያን 10:39
-