ኢየሱስ በአምላክ ላይ እምነት ነበረውን?
የሥላሴ አማኞችን ግራ የሚያጋባ ጥያቄ
“ኢየሱስ እንዴት እምነት ሊኖረው ይችላል? እሱ አምላክ ነው፤ የሌላ የማንንም እርዳታ ሳይፈልግ ማንኛውንም ነገር ማወቅም ሆነ ማየት ይችላል። እምነት ደግሞ በሌላ ላይ መደገፍንና የማይታየውን ነገር አምኖ መቀበልን የሚጠይቅ መሆኑ ግልጽ ነው። እንግዲያው ኢየሱስ ራሱ እግዚአብሔር ስለሆነ እምነት ሊኖረው ይችላል የሚለው አስተሳሰብ ከዚህ ውጭ ነው።”
ፈረንሳዊው የሃይማኖት ሊቅ ዣክ ጊል እንደሚሉት ይህ አባባል በጣም ቁልፍ የሆነ የካቶሊካውያን አመለካከት ነው። ይህ አነጋገር ያስገርምሃልን? ኢየሱስ በማንኛውም ነገር ለክርስቲያኖች ምሳሌ ስለሆነ በእምነትም ጭምር ምሳሌ መሆን ይኖርበታል ብለህ አስበህ ይሆናል። እንዲህ የሚል አስተሳሰብ ካለህ የሕዝበ ክርስትናን የሥላሴ ትምህርት አላጤንከው ይሆናል።
ሥላሴ “የክርስትና እምነትና ሕይወት ዋና ምሥጢር ነው” ብለው ለሚያምኑት ለካቶሊክ፣ ለፕሮቴስታንትና ለኦርቶዶክስ የሃይማኖት ሊቃውንት የኢየሱስን እምነት በተመለከተ የሚነሣው ጥያቄ ለማስረዳትም ሆነ ለመረዳት በጣም አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል።a ይሁን እንጂ ኢየሱስ እምነት አልነበረውም ብለው የሚክዱት ሁሉም አይደሉም። ምንም እንኳን ከሥላሴ ትምህርት አንፃር ሲታይ “እርስ በርሱ የሚቃረን” መሆኑን ቢያምኑም ዣክ ጊሌት “ኢየሱስ እምነት እንደነበረው አልቀበልም ማለት የማይቻል ነው” ሲሉ ሳይሸሽጉ ተናግረዋል።
ፈረንሳዊው ጀስዊት ዣን ጋሎ እና እንደ እርሳቸው ያሉ ሌሎች የሃይማኖት ሊቃውንት “ክርስቶስ እውነተኛ አምላክና እውነተኛ ሰው ስለሆነ . . . በራሱ ሊያምን አይችልም” ብለው በግልጽ ይናገራሉ። ላ ቺቪልታ ካቶሊካ የተባለው መጽሔት “እምነት በራስ ላይ ማመንን ሳይሆን በሌላ ላይ ማመንን የሚጠይቅ ነው” ይላል። ሁለቱ ሐሳቦች በቀጥታ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ስለሆኑ ኢየሱስ እምነት እንደነበረው ለመቀበል እንቅፋት የሆነው የሥላሴ ትምህርት ነው።
የሃይማኖት ሊቃውንት “ወንጌሎች ኢየሱስ እምነት እንደነበረው በፍጹም አይናገሩም” ይላሉ። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የገቡት ፒስቲቮ (ማመን፣ እምነት ማሳደር) እና ፒስቲስ (እምነት) የሚሉት ቃላት በአጠቃላይ የሚያመለክቱት ኢየሱስ በሰማያዊ አባቱ ላይ የነበረውን እምነት ሳይሆን ደቀ መዛሙርቱ በእግዚአብሔር ወይም በክርስቶስ ላይ የነበራቸውን እምነት ነው። ታዲያ የአምላክ ልጅ እምነት አልነበረውም ብለን መደምደም ይኖርብናልን? ኢየሱስ ካደረገውና ከተናገረው ነገር ምን መረዳት እንችላለን? በዚህ ጉዳይ ላይ ቅዱሳን ጽሑፎች ምን ይላሉ?
ያለ እምነት መጸለይ ይቻላልን?
ኢየሱስ የጸሎት ሰው ነበር። በማንኛውም ወቅት ይጸልይ ነበር። ሲጠመቅ ጸልዮአል። (ሉቃስ 3:21) 12ቱን ሐዋርያት ከመምረጡ በፊት ሌሊቱን ሙሉ ጸልዮአል። (ሉቃስ 6:12, 13) ከሐዋርያቱ ማለትም ከጴጥሮስ፣ ከዮሐንስና ከያዕቆብ ጋር በተራራ ላይ ሳለ በተአምር ከመለወጡ በፊት ጸልዮአል። (ሉቃስ 9:28, 29) ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ቀርቦ ‘እንዴት እንደምንጸልይ አስተምረን’ ብሎ በጠየቀው ጊዜም እየጸለየ ነበር፤ በመሆኑም የጌታን ጸሎት (“አባታችን ሆይ” የተባለውን ጸሎት) አስተማራቸው። (ሉቃስ 11:1–4፤ ማቴዎስ 6:9–13) ማለዳ ተነሥቶ ለብቻው በመሄድ ረጅም ጸሎት ይጸልይ ነበር። (ማርቆስ 1:35–39) በአንድ ተራራ ላይ ሊመሽ ሲል ደቀ መዛሙርቱን ካሰናበተ በኋላ ብቻውን ይጸልይ ነበር። (ማርቆስ 6:45, 46) ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ ለደቀ ዛሙርቱ ይጸልይ ነበር። (ሉቃስ 22:32፤ ዮሐንስ 17:1–26) አዎን፣ ጸሎት የኢየሱስ ሕይወት የጎላ ክፍል ነበር።
ተአምር ከመፈጸሙ በፊትም ይጸልይ ነበር። ለምሳሌ ያህል ወዳጁን አልዓዛር ከሞት ከማስነሣቱ በፊት እንዲህ ሲል ጸልዮአል፦ “አባት ሆይ፣ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። ሁልጊዜም እንድትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ።” (ዮሐንስ 11:41, 42) አባቱ ጸሎቱን እንደሚመልስለት የነበረው እርግጠኝነት እምነቱ ምን ያህል ጠንካራ እንደነበረ ያመለክታል። ወደ አምላክ በመጸለይና በእሱ ላይ በማመን መካከል ያለው ግንኙነት ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ከተናገረው ቀጥሎ ካለው ሐሳብ ማየት ይቻላል፦ “የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፣ ይሆንላችሁማል።”—ማርቆስ 11:24
ኢየሱስ እምነት ካልነበረው ወደ እግዚአብሔር ለምን ጸለየ? ኢየሱስ ሰውም አምላክም ነበር የሚለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ የሕዝበ ክርስትና የሥላሴ ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት የሚያደበዝዝ ነው። የሥላሴ ትምህርት ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ቀላል ትምህርትና ያለውን ኃይል እንዳይረዱ እንቅፋት ይሆንባቸዋል። ሰው የሆነው ኢየሱስ ይለምን የነበረው ማንን ነበር? ራሱን ነበርን? እሱ ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ አያውቅም ነበርን? እሱ ራሱ እግዚአብሔር ከነበረና ይህንንም የሚያውቅ ከሆነ ለምን ጸለየ?
ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ቀን ያቀረበው ጸሎት በሰማያዊ አባቱ ላይ ስለነበረው ጽኑ እምነት ይበልጥ ጥልቀት ያለው ማስተዋል እንዲኖረን ይረዳናል። ኢየሱስ የነበረውን ተስፋና ልበ ሙሉነትን ሲያንፀባርቅ “አሁንም፣ አባት ሆይ፣ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ” ሲል ጠይቋል።—ዮሐንስ 17:5
በደብረ ዘይት ተራራ በጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ ውስጥ በነበረበት ምሽት በጣም አስቸጋሪ ፈተናዎችና ሞት ከፊቱ እንደተደቀኑ አውቆ “ሊያዝን ሊተክዝም ጀመር።” እንዲሁም “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች” አለ። (ማቴዎስ 26:36–38) ከዚያም ተንበርክኮ “አባት ሆይ፣ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር።” በዚህ ጊዜ “ከሰማይ መጥቶ የሚያበረታው መልአክ ታየው።” አምላክ ጸሎቱን ሰምቶለታል። ስሜቱ በጥልቅ ከመነካቱና የሚጠብቀው ፈተና በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሣ “ወዙም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ነበረ።”—ሉቃስ 22:42–44
በኢየሱስ ላይ የደረሱት መከራዎች፣ የሚያበረታታው መፈለጉና ያቀረበው ምልጃ ምን ያመለክታሉ? ዣክ ጊሌት “መቼም አንድ ነገር የተረጋገጠ ነው፤ ኢየሱስ ይጸልይ ነበር፤ ጸሎት የሕይወቱም ሆነ የእንቅስቃሴዎቹ አንዱ የጎላ ዘርፍ ነበር። እንደ ሰዎች ይጸልያል፤ እንዲሁም ስለ ሰዎች ይጸልይ ነበር። ሰዎች ያለ እምነት የሚያቀርቧቸው ጸሎቶች ተሰሚነት የላቸውም። ታዲያ ኢየሱስ ያለ እምነት የሚያቀርባቸው ጸሎቶች ተሰሚነት ይኖራቸዋልን?” ሲሉ ጽፈዋል።
ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ አንዱን የዳዊት መዝሙር በመጥቀስ ድምፁን ከፍ አድርጎ ጮኸ። ከዚያም በታላቅ ድምፅ “አባት ሆይ፣ ነፍሴን [መንፈሴን አዓት] በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” በማለት የመጨረሻውን የእምነት ምልጃ አቀረበ። (ሉቃስ 23:46፤ ማቴዎስ 27:46) ፓሮላ ዴል ሲኞሬ የተባለው አንድ የጣልያንኛ ሃይማኖታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኢየሱስ ‘ሕይወቱን ለአብ አደራ ሰጠ’ ይላል።
ዣክ ጊል “የወንጌል ጸሐፊዎች ክርስቶስ የእስራኤልን መዝሙሮች በመጥቀስ ወደ አባቱ እየጮኸ እንደተሰቀለ በመናገር ይህ አንድያ ልጅ ያሰማው ጩኸት፣ የጭንቀት ጩኸት፣ ሙሉ በሙሉ በአባቱ ላይ የመመካት ጩኸት፣ የእርግጠኝነት ጩኸት፣ እምነትን ጠብቆ የመሞት ጩኸት መሆኑን ያሳምኑናል” ሲሉ ጽፈዋል።
አንዳንድ የሃይማኖት ሊቃውንት ኢየሱስ እምነት እንደነበረው የሚያሳየው ይህ ግልጽና ተጨባጭ ማስረጃ ሲቀርብላቸው እምነትና “ትምክህት” በሚሉት ቃላት መካከል ልዩነት ለመፍጠር ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ ሁለቱን በመለያየት የሚያቀርቡት ገለጻ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ አይደለም።
ሆኖም በጽናት የተቋቋማቸው ከባድ ፈተናዎች ስለ ኢየሱስ እምነት የሚገልጹት ትክክለኛው ነገር ምንድን ነው?
“የእምነታችን ፍጹም አድራጊ” ፍጹም ተደረገ
ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ሰዎች በጻፈው ደብዳቤው በ11ኛው ምዕራፍ ላይ በቅድመ ክርስትና ዘመን ይኖሩ የነበሩትን እንደ ታላቅ ደመና የሆኑ ታማኝ ወንዶችንና ሴቶችን ገልጿል። ከዚያም ወደ ታላቁና ፍጹሙ የእምነት ምሳሌ በማመልከት እንደሚከተለው በማለት ይደመድማል፦ “እኛ ደግሞ የእምነታችን ዋነኛ መገኛና የእምነታችን ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን በትኩረት እንመለከታለን። እርሱ ወደፊት የሚያገኘውን ደስታ በማሰብ በመከራ እንጨት ላይና በውርደት ታገሠ። . . . በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፣ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ።”—ዕብራውያን 12:1–3 አዓት
አብዛኞቹ የሃይማኖት ሊቃውንት ይህ ጥቅስ “ስለ ኢየሱስ የግል እምነት” አይናገርም፤ ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ “የእምነት አመንጪ ወይም መሥራች” በመሆን ስለተጫወተው ሚና ነው ይላሉ። በዚህ ሐረግ ውስጥ የሚገኘው ቴሊዮቲስ የሚለው የግሪክኛ ቃል ትርጉሙ አንድን ነገር ፍጹም የሚያደርግ፣ ወደ ሕልውና የሚያመጣ ወይም የተሟላ የሚያደርግን ሰው የሚያመለክት ነው። ኢየሱስ “ፍጹም አድራጊ” እንደመሆኑ መጠን እሱ ወደ ምድር መጥቶ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙና በዚህ መንገድ ለእምነት የበለጠ ጠንካራ መሠረት እንዲጣል በማድረጉ እምነት የተሟላ እንዲሆን አድርጓል። ታዲያ እንዲህ ሲባል እሱ እምነት አልነበረውም ማለት ነውን?
በገጽ 15 ላይ በሚገኘው ሣጥን ውስጥ ያሉት ለዕብራውያን ሰዎች ከተጻፈው ደብዳቤ የተወሰዱት ምንባቦች ይህን በተመለከተ ያለውን ማንኛውንም ጥርጣሬ ያስወግዳሉ። ኢየሱስ በደረሱበት መከራዎችና ባሳየው ታዛዥነት ፍጹም ተደርጓል። ምንም እንኳን ኢየሱስ ቀድሞውንም ፍጹም ሰው ቢሆንም የደረሱበት ነገሮች እምነትን ጨምሮ በሁሉም ነገር ፍጹምና የተሟላ በመሆን ለእውነተኛ ክርስቲያኖች መዳን የሚያገለግል ሊቀ ካህን ለመሆን ሙሉ በሙሉ ብቁ እንዲሆን አስችለውታል። ኢየሱስ “ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር” አባቱን ለምኗል። ለአምላክ “ታማኝ” ነበር። “አምላካዊ ፍርሃትም” ነበረው። (ዕብራውያን 3:1, 2፤ 5:7–9) ዕብራውያን 4:15 “በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው” ይላል። ይህም አንድ ታማኝ ክርስቲያን በእምነቱ ላይ ‘ልዩ ልዩ ፈተና’ እንደሚደርስበት ሁሉ በእሱም ላይ የእምነት ፈተና ደርሶ ነበር ማለት ነው። (ያዕቆብ 1:2, 3) ታዲያ ኢየሱስ በእምነቱ ሳይፈተን በነገር ሁሉ “እንደ” ተከታዮቹ ተፈትኗል ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነውን?
ምልጃ፣ ታዛዥነት፣ መከራ፣ ፈተና፣ የታመነ ሆኖ መገኘትና አምላካዊ ፍርሃት የኢየሱስን የተሟላ እምነት የሚያረጋግጡ ናቸው። ኢየሱስ “የእምነታችን ፍጹም አድራጊ” የሆነው በመጀመሪያ በራሱ እምነት ፍጹም ከተደረገ በኋላ መሆኑን ያመለክታሉ። የሥላሴ ትምህርት እንደሚለው ኢየሱስ እግዚአብሔር ወልድ እንዳልነበረ ግልጽ ነው።—1 ዮሐንስ 5:5
የአምላክን ቃል አያምንም ነበርን?
የሃይማኖት ሊቃውንት ኢየሱስ “በአምላክ ቃልና በያዘው መልእክት ሊያምን አይችልም” ምክንያቱም “እሱ ራሱ የአምላክ ቃል ስለሆነ ያንን ቃል ማወጅ ብቻ ነው የሚችለው” ብለው እስኪያምኑ ድረስ የሥላሴ ትምህርት በአመለካከታቸው ላይ ተጽእኖ አሳድሯል።—አንጄሎ አማቶ ዠዛ ኢል ሲኞሬ የቤተ ክርስቲያን ሕጎችን የያዘው መጽሐፍ
ይሁን እንጂ ኢየሱስ በተደጋጋሚ ከቅዱሳን ጽሑፎች መጥቀሱ ምን ያሳያል? ኢየሱስ በተፈተነበት ወቅት ሦስት ጊዜ ከቅዱሳን ጽሑፎች ጠቅሷል። ሦስተኛው መልሱ ኢየሱስ እግዚአብሔርን ብቻ እንደሚያመልክ ለሰይጣን አስገንዝቦታል። (ማቴዎስ 4:4, 7, 10) ኢየሱስ በእሱ ላይ የተፈጸሙትን ትንቢቶች ብዙ ጊዜ ጠቅሷል። በዚህም ትንቢቶቹ እንደሚፈጸሙ ያለውን እምነት አሳይቷል። (ማርቆስ 14:21, 27፤ ሉቃስ 18:31–33፤ 22:37፤ ከሉቃስ 9:22 እና ከ24:44–46 ጋር አወዳድር።) ከዚህ ካደረግነው ምርመራ ኢየሱስ ቅዱሳን ጽሑፎች ከአባቱ የመነጩ መሆናቸውን ያውቅ እንደነበረ፣ በእምነት እንደጠበቃቸው እንዲሁም በእሱ ላይ ስለሚደርሰው ፈተና፣ መከራ፣ ሞትና ስለሚያገኘው ትንሣኤ የሚናገሩት ትንቢቶች እንደሚፈጸሙ ሙሉ እምነት ነበረው ብለን መደምደም ይኖርብናል።
ኢየሱስ ልንመስለው የሚገባ የእምነት አብነት ነው
ኢየሱስ ከአባቱ ጎን በታማኝነት ለመቆምና ‘ዓለምን ለማሸነፍ’ ሲል እስከ መጨረሻው ድረስ በእምነት መጋደል ነበረበት። (ዮሐንስ 16:33) ያለ እምነት እንዲህ ዓይነቱን ድል መቀዳጀት አይቻልም። (ዕብራውያን 11:6፤ 1 ዮሐንስ 5:4) ኢየሱስ በነበረው በዚህ ድል አድራጊ እምነቱ ለታማኝ ተከታዩቹ ምሳሌ ሆኖላቸዋል። በእርግጥም በእውነተኛው አምላክ ላይ እምነት ነበረው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የሥላሴን ትምህርት መሠረተቢስነት በተመለከተ በኒው ዮርክ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በተዘጋጀው በሥላሴ ማመን ይገባሃልን? በተባለው ብሮሹር ውስጥ ይበልጥ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ማግኘት ይቻላል።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ፍጹም አድራጊው” ኢየሱስ ፍጹም ተደረገ
ዕብራውያን 2:10 አዓት፦ “ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ የመዳናቸው ዋና መገኛ በመከራ ፍጹም ይደረግ ዘንድ፤ ከእርሱ የተነሣ ሁሉ በእርሱም ሁሉ ለሆነ፣ ለእርሱ ተገብቶታልና።”
ዕብራውያን 2:17, 18፦ “ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፣ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፣ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው። እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና።”
ዕብራውያን 3:2፦ “ሙሴ ደግሞ በቤቱ ሁሉ የታመነ እንደ ሆነ፣ እርሱ ለሾመው የታመነ ነበረ።”
ዕብራውያን 4:15፦ “ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፣ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም።”
ዕብራውያን 5:7–9፦ “እርሱም በሥጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትና ምልጃን አቀረበ፣ እግዚአብሔርንም ስለመፍራቱ ተሰማለት፤ ምንም ልጅ ቢሆን፣ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ ከተፈጸመም [ፍጹም ከተደረገም አዓት] በኋላ . . . ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው።”