የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g95 1/8 ገጽ 12-15
  • በሁሉም ዕለታዊ የኑሮ ክፍሎች ሴቶችን ማክበር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በሁሉም ዕለታዊ የኑሮ ክፍሎች ሴቶችን ማክበር
  • ንቁ!—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሴቶች እንዴት እንደሚታዩ
  • በቤት ውስጥ አክብሮት ማሳየት
  • በሥራ ቦታ አክብሮት ማሳየት
  • ለባለ ትዳሮች የሚሆን ጥበብ ያዘለ መመሪያ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ሴቶች፣ በቤታቸው ውስጥ ይከበራሉን?
    ንቁ!—1995
  • ወንድና ሴት—እያንዳንዳቸው ያላቸው የተከበረ ቦታ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • ትዳርን ዘላቂ ለማድረግ የሚረዱ ሁለት ቁልፍ ነገሮች
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1995
g95 1/8 ገጽ 12-15

በሁሉም ዕለታዊ የኑሮ ክፍሎች ሴቶችን ማክበር

ሴቶች በአሁኑ ጊዜ ከሚታየው በበለጠ መጠን እንዲከበሩ ከተፈለገ ለውጡ መጀመር ያለበት መቼና የት ነው? የተሳሳቱ አመለካከቶችና ምክንያተ ቢስ ጥላቻዎች የሚጀምሩት መቼና የት ነው? ገና በልጅነት ዕድሜ በቤትና በትምህርት ቤት አይደለምን? ዝንባሌዎቻችን በአብዛኛው የሚቀረጹት በወላጆቻችን ነው። ታዲያ ወጣት ወንዶች ስለ ሴቶች ባላቸው አመለካከትና ዝንባሌ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉት እነማን ናቸው? አባትና እናት እንደሆኑ ግልጽ ነው። ስለዚህ ለዚህ ችግር መፍቻ ቁልፎች አንዱ ወደ ቤቶች ጠልቆ የሚገባና በወላጆች ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር የሚችል ትምህርት ማስፋፋት ነው።

ሴቶች እንዴት እንደሚታዩ

አጉል አመለካከት የሚቀረጸው ከቤት ነው፤ ይህንንም ከአራት ሴት ልጆች የመጀመሪያ የሆነችውና በጸሐፊነት የምትሠራ ባለትዳር የሆነችው ጄኒ ከተናገረችው መረዳት ይቻላል። “ወጣት ሴቶች በነበርንበት ጊዜ ሁሉ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሴቶች ቁጥር ከወንዶች እንደሚበልጥ ዘወትር እናስብ ነበር። ስለዚህ ማግባት ከፈለጋችሁ ራሳችሁን ማራኪ አድርጋችሁ ማቅረብ ይኖርባችኋል።

“በተጨማሪም ሴቶች ራሳቸውን ከወንዶች ያነሱ ፍጡሮች እንደሆኑ አድርገው እንዲመለከቱ ይደረጋሉ። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ከወንድ ልጆች ያነሰ ዋጋ እንዳላችሁ አድርጋችሁ እንድታስቡ የሚያደርጓችሁ የገዛ ወላጆቻችሁ ናቸው። አንድ የሚጎዳኛችሁ ወንድ ሲያጋጥማችሁ ደግሞ ይህንኑ ከወንዶች ያነሳችሁ መሆናችሁን የሚያሳስባችሁ መልእክት ያስተላልፍላችኋል።

“ለራሳችን የምንሰጠውስ ዋጋና ግምት በአካላዊ ቅርጻችንና ውበታችን ላይ የሚመካው ለምንድን ነው? ወንዶች የሚለኩት በአካላዊ ቅርጻቸውና ውበታቸው ነውን?”

ካገባች 32 ዓመት የሆናትና የአንድ ትልቅ ሱቅ ሥራ አስኪያጅ የነበረችው ቤቲ ደግሞ ሌላ ነጥብ አስገንዝባለች። “ሴቶች በሥራ ልምዳቸው፣ በችሎታቸውና በብልህነታቸው ሳይሆን በጾታቸው የሚመዘኑት ለምንድን ነው? የምጠይቀው ወንዶች በአእምሮዬ ውስጥ ያለውን እንዲያዳምጡ ብቻ ነው። ሴት ስለሆንኩ ብቻ አይናቁኝ!

“ብዙ ጊዜ ወንዶች ትክክለኛ ውሳኔ ለመወሰን እንደማንችል ደደብ ፍጡሮች ይቆጥሩናል። ምን ማለቴ እንደሆነ ይገባችኋል? ለእነርሱ እንዲደረግላቸው የሚፈልጉትን ለእኛም ያድርጉልን። ይህን ቢያደርጉ አመለካከታቸው ብዙ ሳይቆይ ይቀየራል!” የጠየቀችው ወንዶች ‘ሌሎች እንዲያደርጉልህ የምትፈልገውን አንተም ለሌሎች አድርግላቸው’ በሚለው ወርቃማ ሕግ እንዲመሩ ብቻ ነው።— ማቴዎስ 7:12

እነዚህ ሴቶች ያነሷቸው ነጥቦች አግባብነት ያላቸው ናቸው። የአንዲት ሴት ትክክለኛ ዋጋ በውጭያዊና አካላዊ ቁመናዋ ወይም መልኳ ወይም በባሕላዊ አመለካከቶች መለካት አይኖርበትም። ይህን ቁም ነገር አንድ የስፓንኛ ተረት እንደሚከተለው በማለት ገልጾታል:- “ቆንጆ ሴት ደስ የምታሰኘው ዓይንን ሲሆን ጥሩ ሴት ግን ደስ የምታሰኘው ልብን ነው። የመጀመሪያይቱ ሴት ዕንቁ ብትሆን ሁለተኛዋ ውድ ሀብት ነች።”

መጽሐፍ ቅዱስም ለየት ባለ አነጋገር ተመሳሳይ የሆነ ቁም ነገር እንዲህ ሲል ያስገነዝባል:- “የእናንተ ውበት ጠጉርን በመሠራት፣ የወርቅ ጉትቻን በማንጠልጠል፣ የከበረ ልብስ በመልበስ በውጭ ከተገኘ ጌጥ አይሁን። ነገር ግን ውበታችሁ በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ በሆነና በማይጠፋው ጌጥ በገርነትና በጭምትነት መንፈስ ያጌጠው፣ በልብ ተሰውሮ የሚገኘው ውስጣዊ ሰውነት ይሁን።” የአንድን መጽሐፍ ጥራት ጥራዙን በመመልከት ብቻ ማወቅ እንደማይቻል ሁሉ የሰዎችንም ብቃት በወንድነታቸው ወይም በሴትነታቸው መወሰን የለበትም።— 1 ጴጥሮስ 3:3, 4 የ1980 ትርጉም

በቤት ውስጥ አክብሮት ማሳየት

ብዙ ሴቶች በተለይም ሥራ የሚውሉና የልጆች እናቶች የሆኑ ሴቶች የሚያሰሙት አግባብነት ያለው ስሞታ ባሎች የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንደተጨማሪ ኃላፊነት አድርገው የማይመለከቱና በእነዚህም ሥራዎች የማይካፈሉ መሆናቸው ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ሱዛን ፋሉዲ “ሴቶች 70 በመቶ የሚሆነውን ኃላፊነት በሚሸከሙበት በገዛ ቤታቸውም ቢሆን እኩልነት አያገኙም” ብለዋል። ለዚህ ፍትሕ የጎደለው ሁኔታ መፍትሔው ምንድን ነው?

በአንዳንድ ባሕሎች ላደጉ ባሎች የማይዋጥላቸው ቢሆንም በተለይ ሚስቲቱ ለሥራ ከቤት ውጭ የምትውል ከሆነ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መከፋፈል ይገባል። እርግጥ የኃላፊነትና የሥራ ክፍፍል በሚደረግበት ጊዜ ለመኪና እንክብካቤ እንደ ማድረግ፣ ግቢ እንደ ማጽዳት፣ አትክልት እንደ መኮትኮት፣ እንደ ቧንቧና ኤሌክትሪክ ሥራ ያሉት በወንዶች የሚሠሩ ሥራዎች አብዛኛውን ጊዜ ሚስት በቤት ውስጥ ሥራዎች ከምታሳልፈው ያነሰ ጊዜ የሚያስፈልጋቸው ቢሆኑም ግምት ውስጥ መግባት ይኖርባቸዋል። በአንዳንድ አገሮች ባሎች መኪናቸው የመኖሪያ ቤታቸው ክፍል የሆነ ይመስል ሚስቶቻቸው እንዲያጸዱላቸው ይጠብቃሉ።

ይህ ባሎች ከሚስቶቻቸው ጋር የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንዲካፈሉ የቀረበው ሐሳብ ሐዋርያው ጴጥሮስ ባሎች ከሚስቶቻቸው ጋር “በማስተዋል” አብረዋቸው እንዲኖሩ ከሰጠው ምክር ጋር የሚስማማበት መንገድ አለው። (1 ጴጥሮስ 3:7) ይህም ማለት ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ ባሎች ስሜትና አዘኔታ የሌላቸው ደባሎች ወይም የቤት ተጋሪዎች መሆን የለባቸውም ማለት ነው። ለሚስቶቻቸው ብልህነትና ተሞክሮ አክብሮት ማሳየት ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም የሴትነት፣ የሚስትነትና የእናትነት ስሜቶቻቸውን ማስተዋልና መረዳት ይገባቸዋል። ይህም ሥራ ውሎ ደመወዝ ከማምጣት የበለጠ ነገር ያጠቃልላል። ምክንያቱም ውጭ ሠርተው ደመወዝ የሚያመጡ ብዙ ሴቶች አሉ። አካላዊ፣ ስሜታዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ወሲባዊና ከሁሉም በላይ ደግሞ መንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸውን መገንዘብና ማስተዋል ይኖርባቸዋል።

ክርስቲያናዊ ሥርዓቶችን እከተላለሁ የሚል ባል ደግሞ ከዚህ የበለጠ ኃላፊነት አለው። የክርስቶስን አርዓያ መከተል ይኖርበታል። ኢየሱስ ‘ለደከሙና ሸክማቸው ለከበደባቸው ሁሉ’ “ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። . . . እኔ የዋህ፣ በልቤም ትሁት ነኝና ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ” የሚል ማራኪ ግብዣ አቅርቧል። (ማቴዎስ 11:28, 29) ክርስቲያን ባሎችንና አባቶችን በእጅጉ ሊያሳስባቸው የሚገባ ነገር ነው! ራሳቸውን ‘ለሚስቴ እረፍት እሰጣለሁ ወይስ እጨቁናታለሁ? ደግና በቀላሉ የምቀረብ ነኝ ወይስ ጨቋኝ፣ ፈላጭ ቆራጭና አምባ ገነን ነኝ? በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ “የወንድማማችነት ፍቅር” እያሳየሁ በቤት ግን በጣም አስቸጋሪ የሆነ ጠባይ አሳያለሁን?’ ብለው መጠየቅ ይኖርባቸዋል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የቤት ቀጋ የውጭ አልጋ የሆኑ ባሎች መኖር የለባቸውም።— 1 ጴጥሮስ 3:8, 9

ስለዚህ አንዲት በደል የደረሰባት ክርስቲያን ሴት ስለባልዋ የሰጠችው የሚከተለው መግለጫ ትክክል ሊሆን የሚችልበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም። “በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በጣም ጥሩ ሰው ሆኖ የሚታይና ለሌሎች ስጦታ ገዝቶ የሚሰጥ ሚስቱን ግን እንደ ጥራጊ ቆሻሻ የሚመለከት በወንድነቱ የሚኩራራ ክርስቲያን ራስ ነው” ብላለች። ሚስቱን የሚያከብር ባል ሊጨቁናት ወይም ሊያዋርዳት አይችልም። እርግጥ ይህ አክብሮት የማሳየት ጉዳይ ሁለት ገጽ እንዳለው ሳንቲም ነው፤ ሚስትም በበኩልዋ ባልዋን ማክበር ይኖርባታል።— ኤፌሶን 5:33፤ 1 ጴጥሮስ 3:1, 2

ዶክተር ሱዛን ፎርዋርድ የዚህን ትክክለኛነት ሲያረጋግጡ “ጥሩ ዝምድና የሚመሠረተው እርስ በርስ በመከባበር ላይ ነው።” ለጥምረቱ መሳካት ሁለቱም ኃላፊነት አለባቸው ማለት ነው። በመቀጠልም እንዲህ ብለዋል:- “አንዳቸው ስለሌላው ስሜትና ፍላጎት ማሰብ ይኖርባቸዋል። እያንዳንዱን የትዳር ጓደኛ ልዩ ለሚያደርጉት ባሕርያትም አድናቆት ማሳየት ያስፈልጋል። . . . እርስ በርሳቸው የሚፋቀሩ ባለ ትዳሮች በመካከላቸው የሚነሱትን ልዩነቶች የሚያስወግዱባቸው ጥሩ መንገዶች አሏቸው። እያንዳንዱን አለመግባባት እንደ ጦር ሜዳ ቆጥረው ለድል ወይም ለሽንፈት አይሟሟቱም።”— ሜን ሁ ሄት ዉሜን ኤንድ ዘ ዉሜን ሁ ላቭ ዘም

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በኤፌሶን 5:28 ላይ ለባሎች ጥሩ ምክር ይሰጣል። “ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል።” ይህ አባባል ትክክል የሚሆነው ለምንድን ነው? ጋብቻ ባልና ሚስት እኩል ገንዘብ አዋጥተው እንዳስቀመጡት የባንክ ሂሣብ ስለሚቆጠር ነው። ባልዬው ይህን ገንዘብ ቢያባክን የሁለቱንም ሀብት ማባከን ይሆንበታል። በተመሳሳይም አንድ ባል በማንኛውም መንገድ ሚስቱን ቢጎዳ ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ በራሱ ላይ ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም። ለምን ቢባል ጋብቻ የጋራ ሀብት ነው። አንደኛው ወገን በዚህ ሀብት ላይ ጉዳት ቢያደርስ የሚጎዱት ሁለቱም ይሆናሉ።

አክብሮት በመስጠት ረገድ ሊታወስ የሚገባው አንድ አስፈላጊ ነገር አለ። አክብሮት አክብሩኝ በማለት የሚገኝ ነገር አይደለም። እያንዳንዱ የትዳር ጓደኛ ሌላውን የማክበር ግዴታ ቢኖርበትም አክብሮት የሚገባው ሰው ሆኖ መገኘት አስፈላጊ ነው። ክርስቶስ የበላይነት ሥልጣኑን ወይም ኃይሉን በማሳየት አክብሮት ለማግኘት ሞክሮ አያውቅም።a በትዳር ውስጥም ቢሆን ባሎችና ሚስቶች አንዳቸው ለሌላው በሚያደርጉት የአሳቢነት ተግባር አክብሮት ያገኛሉ እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እንደ አርጩሜ በመጠቀም አይደለም።

በሥራ ቦታ አክብሮት ማሳየት

ወንዶች ሴቶችን የወንድነት ቦታቸውንና ሥልጣናቸውን እንደሚጋፉ አድርገው መመልከት ይኖርባቸዋልን? ኤልዛቤት ፎክስ ጀኖቬዝ ፌሚኒዝም ዊዝአውት ኢሉዥንስ በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “እንደ እውነቱ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ የብዙ ሴቶች ፍላጎት ከወንዶች የተለየ አይደለም። ጥሩ ኑሮ ለመኖር፣ ፍሬያማና የሚያስደስት የግል ሕይወት ለመምራትና በዓለም ውስጥ ብዙ የኑሮ ውጣ ውረድ ሳያጋጥማቸው ለመኖር ይፈልጋሉ።” ታዲያ ይህ ፍላጎታቸው ወይም ምኞታቸው በወንዶች ላይ እንደተቃጣ ጥቃት መቆጠር ይኖርበታልን? በተጨማሪም “በዓለማችን ላይ በጣም ብዙ ለውጥ የታየና ወደፊትም ቢሆን ለውጥ መኖሩ የማይቀር ቢሆን ልዩነቶች መኖራቸው እንደማይቀርና እነዚህም ልዩነቶች አስደሳች ሊሆኑልን እንደሚችሉ መገንዘብ የሚያቅተን ለምን ይሆን?” ብለዋል።

ግንባር ቀደም ሠራተኞች ወይም የበላይ ተመልካቾች ሆነው የሚያገለግሉ ክርስቲያን ወንዶች ለሴቶች የሥራ ባልደረቦቻቸው አክብሮት ማሳየት ይኖርባቸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት አንዲት ያገባች ሴት አንድ “ራስ” ብቻ እንዳላትና እርሱም ባልዋ እንደሆነ ዘወትር ማስታወስ ይኖርባቸዋል። ሌሎች በኃላፊነት ቦታ ላይ ሊሆኑና ለዚህም አክብሮት ሊሰጣቸው ይችላል፤ ይሁን እንጂ በትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ አባባል መሠረት ለአንዲት ሴት “ራስ” ባልዋ እንጂ ሌላ ወንድ አይደለም።— ኤፌሶን 5:22–24

በሥራ ቦታ የሚሰሙ ጭውውቶች ሁልጊዜ የሚገነቡ መሆን ይኖርባቸዋል። ወንዶች ሌላ ትርጉም ያለው ከግብረ ሥጋ ጋር ግንኙነት ያለው የብልግና ጨዋታ ቢያመጡ ለሴቶች አክብሮት አለማሳየት ከመሆኑም በላይ ለራሳቸው በሚሰጠው አክብሮትና ዝና ላይ ጥቁር ነጥብ ይጥላሉ። ጳውሎስ ለክርስቲያኖች እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኩሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ። የሚያሳፍር ነገርም የስንፍና ንግግርም ወይም ዋዛ የማይገቡ ናቸውና አይሁኑ፣ ይልቁን ምስጋና እንጂ።”— ኤፌሶን 5:3, 4

የአንዲትን ሴት ስሜት ግንዛቤ ውስጥ ሳያስገቡ ከምድብ ሥራዋ መቀየርም ለሴቶች አክብሮት ያለማሳየት ባሕርይ ከሚገለጥባቸው መንገዶች አንዱ ነው። ጄን የተባለችው ነርስ እንዲህ ብላለች:- “የሥራ ዝውውር ከመደረጉ በፊት ሐሳባችን ቢጠየቅ ጥሩ ይሆን ነበር። በሥነ ልቦናችን ላይ ጥሩ ውጤት ይኖረዋል። ሴቶች ርኅራሄ ያስፈልጋቸዋል። ዋጋ ያላቸውና የሚከበሩ መሆናቸው እንዲሰማቸው ይፈልጋሉ።”

ሌላው ሴቶች በሥራ ቦታቸው ከበሬታ እንዳያገኙ እንቅፋት የሚሆንባቸው አንዳንድ ሴቶች “የመስተዋት ጣሪያ” ብለው የሚጠሩት ነገር ነው። “ሴቶች በግል ኢንዱስትሪ መስኮች የሥራ አስኪያጅነት ቦታ እንዳይሰጣቸው የሚያግደውን የድርጅቶች የተሳሳተ አመለካከት” መጠቆማቸው ነው። (ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ጥር 3, 1992) በዚህ ምክንያት በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ የተደረገ ጥናት በሴቶች የተያዙ ከፍተኛ የሥራ አመራር ቦታዎች በጣም አነስተኛ እንደሆኑ ያመለክታል። በሐዋይ 14 በመቶ፣ በዩታ 18 በመቶ፣ በሉዊዝያና ደግሞ 39 በመቶ እንደሆነ ጥናቱ ያመለክታል። ለሴቶች ተገቢ አክብሮት ቢሰጥ ኖሮ በሥራ ቦታዎች እድገት የሚሰጠው በችሎታና በሥራ ልምድ እንጂ በወንድነት ወይም በሴትነት አይሆንም ነበር። የምርምር ዲሬክተር የሆኑት ሻሮን ሃርላን እንዲህ ብለዋል:- “ሁኔታቸው እየተሻሻለ መጥቷል። ቢሆንም . . . በሴቶች ፊት የሚጋረጡ መዋቅራዊ እንቅፋቶች አሁንም ብዙ ናቸው።”

[የግርጌ ማስታወሻ]

a መጠበቂያ ግንብ 10–110 ገጽ 10–20 “ባል ፍቅርንና አክብሮት ሲያሳይ” እና “ሚስት ፍቅርንና አክብሮት ስታሳይ” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሴቶች አክብሮት ለማግኘት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

● ለራሳችሁ ተገቢ አክብሮት ይኑራችሁ

● በእናንተ ፊት ምን ቢነገርና ምን ቢደረግ እንደምትፈልጉ ግልጽ አድርጉ

● ተቀባይነት ባላቸውና በሌላቸው ጠባዮችና ንግግሮች ረገድ ተገቢ የሆነ ድንበር አብጁ

● በብልግና ንግግሮችና ተገቢ ባልሆኑ ቀልዶች ከወንዶች ጋር ለመወዳደር አትሞክሩ፣ የራሳችሁን ጨዋነት ዝቅ ከማድረጉም በላይ ወንዶቹም የጨዋነት ጠባያቸውን እንዲተው ያደርጋቸዋል

● በጊዜው የተስፋፋው ፋሽን ምንም ዓይነት ቢሆን የወሲብ ስሜት የሚቀሰቅስ ልብስ አትልበሱ። አለባበሳችሁ ለራሳችሁ ያላችሁን ግምትና አክብሮት ያንጸባርቃል

● በአካሄዳችሁና በጠባያችሁ አክብሮት ለማግኘት ሞክሩ። ወንዶች ሊያሳዩአችሁ የምትፈልጉትን አክብሮት እናንተም ለወንዶች አሳዩ

● የመሽኮርመም ጠባይ አታሳዩ

ወንዶች ለሴቶች አክብሮት ለማሳየት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

● ሁሉንም ሴቶች በአክብሮት ተመልከቱ። ጠንካራ ሴት ሲያጋጥማችሁ ቦታችሁን ወይም ሥልጣናችሁን እንደምታጡ ሆኖ አይሰማችሁ

● ሚስታችሁ ላልሆነች ሴት ከመጠን በላይ የመቀራረብ ስሜት አታሳዩ፣ ተገቢ ባልሆነ የቁልምጫ ወይም ተወዳጅነትን በሚያሳይ አጠራር አትጥሩ

● ተገቢ ካልሆኑ ቀልዶችና የጥቅሻ አስተያየቶች ራቁ

● ከመጠን በላይ አታወድሷቸው፣ ተገቢ ባልሆነም መንገድ አትነካኳቸው

● ሥራዋንም ሆነ ቁመናዋን አታቃልሉ

● በሚዛናዊነትና አድልዎ በሌለበት ሁኔታ አዳምጧት፣ አነጋግሯት፣ አማክሯት

● ለሴትዬዋ ሥራ ያላችሁን አድናቆት ግለጹ

● በቤት ውስጥ ሥራ እርዷት። የቤት ውስጥ ሥራ መሥራት ክብራችሁን የሚነካባችሁ መስሎ ከታያችሁ የእርሷንስ ክብር አይነካምን?

● ወላጆቻችሁ አብረዋችሁ የሚኖሩ ከሆነ ሚስታችሁ ብዙ ተጽእኖ እንደሚደርስባት ተገንዘቡ። ዋነኛ ኃላፊነታችሁ ለሚስታችሁ ስለሆነ ድጋፍ ልትሰጧት ይገባል (ማቴዎስ 19:5)

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ