እድገት አድርግ
በፊት የነበረህን አስተሳሰብ፣ ንግግርና ጠባይ ቀስ በቀስ መለወጥ የጀመርከው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወትህ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግን ስትማር ነበር። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከመመዝገብህ በፊት ብዙ ለውጥ አድርገሃል። ከዚያ በኋላም ቢሆን ሕይወትህን ለይሖዋ እስከ መወሰን ድረስ ተጨማሪ ለውጥ አድርገህ መሆን አለበት። ታዲያ ከዚህ በላይ እድገት ማድረግ አያስፈልግህም ማለት ነው? በፍጹም። መጠመቅህ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ እርምጃ አይደለም።
ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ፣ ይህንም አዘውትር” በማለት መክሮታል። ጳውሎስ ይህን ሲል ጢሞቴዎስ ስላገኘው ምክርም ሆነ ስለ አገልግሎት መብቱ አጥብቆ እንዲያስብ ማሳሰቡ ነው። በዚህ ወቅት ጢሞቴዎስ ክርስቲያን ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግል ሰው ነበር። (1 ጢሞ. 4:12-15) በእውነት መንገድ መመላለስ የጀመርከው በቅርቡ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ በክርስቲያናዊ አኗኗር ስትመላለስ የቆየህ ልትሆን ትችላለህ። ያም ሆነ ይህ እድገት ለማድረግ መጣጣር ይኖርብሃል።
እውቀት መቅሰምና ለውጥ ማድረግ
ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹ የእውነትን ‘ስፋትና ርዝመት እንዲሁም ከፍታና ጥልቀት ለማወቅ ይበረቱ ዘንድ’ እንደጸለየ በኤፌሶን 3:14-19 ላይ እናነባለን። ኢየሱስ ይህን በማሰብ ጉባኤውን የሚያስተምሩ፣ የሚያስተካክሉና የሚያንጹ ስጦታ የሆኑ ወንዶችን ሾሟል። በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ላይ አዘውትሮ ማሰላሰል ተሞክሮ ካላቸው አስተማሪዎች ከሚገኘው መመሪያ ጋር ተዳምሮ በመንፈሳዊ ‘እንድናድግ’ ሊረዳን ይችላል።—ኤፌ. 4:11-15
ይህ እድገት ‘አእምሮአችንን ለተግባር በሚያነሳሳው ኃይል መታደስን ይጨምራል።’ ይህም ከአምላክና ከክርስቶስ ጋር የሚስማማ አስተሳሰብ ማዳበርን የሚጠይቅ ነው። ‘አዲሱን ሰውነት ለመልበስ’ ከይሖዋና ከክርስቶስ አስተሳሰብ ጋር በሚገባ መተዋወቅ ያስፈልጋል። (ኤፌ. 4:23, 24) ስለ ክርስቶስ ሕይወት የሚገልጸውን የወንጌል ዘገባ ስታጠና የእርሱን ምሳሌ መኮረጅ ስለምትችልበት መንገድ ታስባለህ? ኢየሱስ ካሳያቸው ባሕርያት በአንዳንዶቹ ላይ ለማሰላሰልና በሕይወትህ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ትጥራለህ?—1 ጴጥ. 2:21
ከሰዎች ጋር ስትወያይ የምታወራው ነገር ምን ያህል እድገት እንዳደረግህ የሚጠቁም ምልክት ሊሆን ይችላል። አዲሱን ሰውነት ከለበሱ ሰዎች አፍ ሐቀኝነት የጎደለው ንግግር፣ ስድብ፣ ጸያፍ አነጋገር ወይም የማያንጽ ወሬ አይወጣም። ይልቁንም ንግግራቸው “ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ . . . ለማነጽ የሚጠቅም” ነው። (ኤፌ. 4:25, 26, 29, 31፤ 5:3, 4፤ ይሁዳ 16) ከሰዎች ጋር ሲነጋገሩም ሆነ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ሲሰጡ ከአንደበታቸው የሚወጣው ቃል እውነት ሕይወታቸውን እየለወጠው እንዳለ የሚያሳይ ነው።
‘በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምህ ወዲያና ወዲህ የማትንሳፈፍ’ ከሆነ እድገት አድርገሃል ማለት ነው። (ኤፌ. 4:14) ለምሳሌ ያህል ዓለም በየጊዜው የሚያፈልቃቸውን አዳዲስ ሐሳቦች ወይም የሚያቀርባቸውን መዝናኛዎች በተመለከተ ያለህ አቋም ምንድን ነው? እነዚህን ነገሮች ለመከታተል ስትል ለክርስቲያናዊ ግዴታዎችህ የምታውለውን ጊዜ ትቀንሳለህ? እንዲህ የምታደርግ ከሆነ መንፈሳዊ እድገትህ ይገታል። ከዚህ ይልቅ ለመንፈሳዊ ነገሮች ጊዜ መዋጀቱ እጅግ አስፈላጊ ነው!—ኤፌ. 5:15, 16
ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለህ ግንኙነትም መንፈሳዊ እድገትህን የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። ወንድሞችህንና እህቶችህን ‘በርኅራኄ የምትይዝና በነፃ ይቅር የምትል ነህን?’—ኤፌ. 4:32
በጉባኤም ይሁን በቤት ውስጥ የምትሠራቸውን ነገሮች ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ በማከናወን ረገድም ዕድገትህ ግልጽ ሆኖ መታየት ይኖርበታል። ይህም በትምህርት ቤት፣ በገበያ፣ በሥራና በሌላ በማንኛውም ቦታ ጭምር ሊንጸባረቅ ይገባል። (ኤፌ. 5:21–6:9) በእነዚህ ሁሉ አጋጣሚዎች አምላክ የሚወድዳቸውን ባሕርያት በተሟላ መልኩ የምታንጸባርቅ ከሆነ እድገትህ ግልጽ ሆኖ ይታያል።
ተሰጥዎህን ተጠቀምበት
ሁላችንም ይሖዋ የሰጠን ችሎታና ተሰጥዎ አለን። እነዚህን ችሎታዎችና ተሰጥኦዎች ሌሎችን ለማገልገል እንድንጠቀምባቸው ይፈልጋል። እንዲህ ካደረግን በእኛ አማካኝነት ፍቅራዊ ደግነቱን ለሌሎች ሊገልጽ ይችላል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህንን በሚመለከት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፣ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ።” (1 ጴጥ. 4:10) ታዲያ የተጣለብህን የመጋቢነት ኃላፊነት እንዴት እየተወጣህ ነው?
ጴጥሮስ በመቀጠል “ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን፣ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር” ብሏል። (1 ጴጥ. 4:11) ይህ ጥቅስ የምንናገረው ነገር ሙሉ በሙሉ ከአምላክ ቃል ጋር የሚስማማ መሆን እንዳለበት ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል። ይህን ማድረጋችን አምላክን ያስከብራል። ይሁን እንጂ የምንናገረው ነገር ብቻ ሳይሆን የምንናገርበት መንገድ ጭምር አምላክን የሚያስከብር ሊሆን ይገባል። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት አማካኝነት የሚሰጠው ሥልጠና ተሰጥዎህን ለአምላክ ክብር በሚያመጣ መንገድ ሌሎችን ለመርዳት እንድትጠቀምበት ያስችልሃል። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ከጊዜ ወደ ጊዜ የምታደርገውን መሻሻል መገምገም የምትችለው እንዴት ነው?
በምክር መስጫ ቅጽህ ላይ ከሰፈሩት ነጥቦች መካከል ምን ያህሉን ሸፍኛለሁ እያልክ ከማሰብ ወይም የተሰጡህን የክፍል ዓይነቶች ከመቁጠር ይልቅ ሥልጠናው የማቀርበውን የምሥጋና መሥዋዕት ጥራት በማሻሻል ረገድ ምን ያህል ረድቶኛል እያልክ አስብ። ትምህርት ቤቱ በአገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ እንድንሆን ያሰለጥነናል። እንግዲያው ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘አገልግሎት ስሄድ የምናገረውን ነገር አስቀድሜ እዘጋጃለሁ? ለምመሠክርላቸው ሰዎች ልባዊ አሳቢነት የማሳየት ባሕርይ አዳብሬያለሁ? በሚቀጥለው ጊዜ የምንወያይበት አንድ ጥያቄ በማንሳት ለተመላልሶ መጠየቅ ሁኔታዎችን አመቻቻለሁ? መጽሐፍ ቅዱስ የማስጠናው ሰው ካለ ልቡን ለመንካት የሚረዳ የማስተማር ችሎታ ለማዳበር ጥረት እያደረግሁ ነው?’
እድገትህን መመዘን ያለብህ ከምታገኛቸው የአገልግሎት መብቶች አንጻር ብቻ መሆን የለበትም። እድገትህን ለመለካት የሚረዳው ትልቁ ነገር መብት ማግኘትህ ሳይሆን ያገኘኸውን መብት ምን ያህል ትሠራበታለህ የሚለው ጉዳይ ነው። የማስተማር አጋጣሚ ከተሰጠህ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ጥሩ የማስተማር ጥበብ ተጠቅሜያለሁን? ትምህርቱን ያቀረብኩት አድማጮች በሕይወታቸው እንዲሠሩበት በሚያነሳሳ መንገድ ነው?’
ተሰጥዎህን እንድትጠቀምበት የቀረበልህን ማበረታቻ ተግባራዊ ማድረግ ቀዳሚ ሆኖ መገኘት ይጠይቅብሃል። ሌሎች አብረውህ እንዲያገለግሉ ትጠይቃለህ? ጉባኤህ ውስጥ ያሉትን አዲሶች፣ ወጣቶች እንዲሁም አቅመ ደካማ የሆኑትን ወንድሞችና እህቶች ለመርዳት ጥረት ታደርጋለህ? የመንግሥት አዳራሹን በማጽዳት ወይም በአውራጃ ስብሰባና በሌሎች ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ በተለያየ ሥራ ትሳተፋለህ? አልፎ አልፎ ረዳት አቅኚ ሆነህ ማገልገል ትችላለህ? የዘወትር አቅኚ ሆነህ ማገልገል ወይም ይበልጥ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ጉባኤ ተዛውረህ መርዳት ትችላለህ? የተጠመቅህ ወንድ ከሆንክ የጉባኤ አገልጋይና ሽማግሌ ለመሆን የሚያስፈልጉትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች ለማሟላት እየተጣጣርህ ነው? በሥራ ለማገዝና ኃላፊነት ለመቀበል ፈቃደኛ ሆኖ መገኘት የእድገት ምልክት ነው።—መዝ. 110:3 አ.መ.ት
ተሞክሮ የሚያበረክተው ድርሻ
በክርስቲያናዊ አኗኗር ብዙም ተሞክሮ የሌለህ በመሆንህ አቅምህ ውስን እንደሆነ ቢሰማህ ተስፋ አትቁረጥ። የአምላክ ቃል ‘ተሞክሮ የሌላቸውን ጠቢባን’ ሊያደርግ ይችላል። (መዝ. 19:7 NW፤ 119:130፤ ምሳሌ 1:1-4) በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር መከተል ፍጹም ከሆነው የይሖዋ ጥበብ እንድንጠቀም ያስችለናል። ይህ ጥበብ በራሳችን ተሞክሮ ብቻ ከምናገኘው ከማንኛውም እውቀት እጅግ የላቀ ነው። ይሁንና በይሖዋ አገልግሎት እድገት ስናደርግ ጠቃሚ ተሞክሮዎችን እያካበትን እንሄዳለን። ታዲያ ያገኘነውን ተሞክሮ ጥሩ አድርገን ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
አንድ ሰው በሕይወቱ ብዙ ነገር ስላየ ‘ይህ ነገር ከአሁን ቀደም አጋጥሞኛል። ስለዚህ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አውቃለሁ’ ሊል ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ጥበብ ይሆናልን? ምሳሌ 3:7 “በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን” በማለት ያስጠነቅቃል። እርግጥ በሕይወታችን ያካበትነው ተሞክሮ አንዳንድ ነገሮች ሲገጥሙን ጉዳዩን አእምሮአችንን ሰፋ አድርገን እንድንመለከተው እንደሚረዳን የታወቀ ነው። ሆኖም መንፈሳዊ እድገት የምናደርግ ሰዎች ከሆንን ያገኘነው ተሞክሮ በይሖዋ የመታመንን አስፈላጊነት ከልብ እንድንገነዘብ ይረዳናል። እንዲህ ከሆነ መንፈሳዊ እድገት ማድረጋችን የሚታየው የሚያጋጥሙንን ነገሮች በራሳችን ታምነን በመጋፈጣችን ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ ከይሖዋ መመሪያ ለማግኘት በመጣራችን ነው። ያለ ይሖዋ ፈቃድ ምንም ነገር ሊፈጸም እንደማይችል ያለን እምነት እንዲሁም ከሰማያዊ አባታችን ጋር የመሠረትነውን በፍቅርና በመተማመን ላይ የተገነባ ወዳጅነት መጠበቃችን እድገታችንን የሚያንጸባርቅ ይሆናል።
እድገት ማድረግህን ቀጥል
ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈሳዊ የጎለመሰ ቅቡዕ ቢሆንም የሕይወት ሽልማቱን ለማግኘት ‘ወደፊት መዘርጋት’ እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር። (ፊልጵ. 3:13-16) አንተስ የእርሱ ዓይነት አመለካከት አለህን?
ምን ያህል እድገት አድርገሃል? እንደሚከተሉት ያሉትን ጥያቄዎች በመጠየቅ ያደረግኸውን እድገት ገምግም:- ‘አዲሱን ሰውነት ምን ያህል በተሟላ መንገድ ለብሻለሁ? ራሴን ለይሖዋ ሉዓላዊነት የማስገዛው እስከምን ድረስ ነው? ተሰጥዎዬን ይሖዋን ለማክበር ምን ያህል በትጋት እየተጠቀምሁበት ነው?’ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ሥልጠና እያገኘህ ስትሄድ በአምላክ ቃል ውስጥ ጉልህ ስፍራ የተሰጣቸው ባሕርያት በንግግርህና በትምህርትህ በግልጽ መንጸባረቅ ይጀምራሉ። በእነዚህ አቅጣጫዎች እድገት ስለማድረግ ዘወትር ልታስብ ይገባል። በምታደርገው እድገት ደስ ይበልህ። እድገትህ ግልጽ ሆኖ መታየቱ አይቀርም።