የጌታን ንብረት በአግባቡ መያዝ
1 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ አገልጋይ ከፍተኛ አመኔታ ይጣልበት ነበር። አብርሃም የንብረቱ ሁሉ ኃላፊ የነበረውን አገልጋዩን ለልጁ ለይስሐቅ ሚስት እንዲፈልግ ኃላፊነት ሰጥቶታል። (ዘፍ. 24:1-4 የ1980 ትርጉም) ይህ አገልጋይ የአብርሃምን የዘር ሐረግ በትክክል የመጠበቅ ኃላፊነት ተጥሎበት ነበር ለማለት ይቻላል። እንዴት ያለ ከፍተኛ ኃላፊነት ነው! ሐዋርያው ጳውሎስ “መጋቢዎች የታመኑ ሆነው መገኘት ይፈለግባቸዋል” ብሎ መናገሩ ምንም አያስደንቅም!—1 ቆሮ. 4:2 NW
ክርስቲያናዊ የመጋቢነት ሥራ
2 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንድ የክርስቲያናዊ አገልግሎት ገጽታዎች የመጋቢነት ሥራዎች እንደሆኑ ተገልጸዋል። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች ሲጽፍ:- “ለእናንተ ስለ ተሰጠኝ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት በእርግጥ ሰምታችኋል” ብሏቸዋል። (ኤፌ. 3:2፤ ቆላ. 1:25) ጳውሎስ ምሥራቹን ለአሕዛብ እንዲያዳርስ የተሰጠውን ተልዕኮ የተመለከተው በታማኝነት ሊወጣው እንደሚገባ የመጋቢነት ሥራ አድርጎ ነው። (ሥራ 9:15፤ 22:21) ሐዋርያው ጴጥሮስ ለቅቡዓን ወንድሞቹ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ያለ ማንጐራጐር እርስ በርሳችሁ እንግድነትን ተቀባበሉ፤ ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፣ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ።” (1 ጴጥ. 4:9, 10፤ ዕብ. 13:16) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች የነበራቸው ማንኛውም ቁሳዊ ንብረት፣ ይገባናል በማይሉት የይሖዋ ደግነት ያገኙት ነበር። በመሆኑም የዚህ ንብረት ባለ አደራዎች ከመሆናቸውም በላይ ያገኙዋቸውን ነገሮች ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድ መጠቀም ነበረባቸው።
3 በዛሬው ጊዜም የይሖዋ ምሥክሮች ተመሳሳይ የሆነ አመለካከት አላቸው። ራሳቸውን ለይሖዋ አምላክ የወሰኑ እንደመሆናቸው መጠን ሕይወታቸውን፣ ጉልበታቸውንም ሆነ ያላቸውን ማንኛውንም ቁሳዊ ንብረት የሚመለከቱት እንደ ‘ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ’ ውጤቶች አድርገው ነው። የታመኑ መጋቢዎች እንደመሆናቸው መጠን በእነዚህ ነገሮች አጠቃቀም ረገድ በይሖዋ አምላክ ፊት ተጠያቂዎች እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የምስራቹ እውቀት አላቸው። ይህም ቢሆን በአደራ የተሰጣቸው ስለሆነ የይሖዋን ስም ለማወደስና ሌሎች እውነትን እንዲያውቁ ለመርዳት ውጤታማ በሆነ መንገድ ሊጠቀሙበት ይፈልጋሉ።—ማቴ. 28:19, 20፤ 1 ጢሞ. 2:3, 4፤ 2 ጢሞ. 1:13, 14
4 የይሖዋ ምሥክሮች አደራ የተሰጣቸው መጋቢዎች መሆናቸውን ያስመሰከሩት እንዴት ነው? ዓመታዊው ሪፖርት የይሖዋ ምሥክሮች የተጣለባቸውን አደራ በታማኝነት እየተወጡ እንዳሉ ያሳያል። ባለፈው ዓመት ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ በመስበክ ከአንድ ቢልዮን ሰዓት በላይ ያሳለፉ ሲሆን ከ4,500,000 በላይ ለሚሆኑ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መርተዋል። (ማቴ. 24:14) ለዓለም አቀፉ ሥራና በአካባቢያቸው የሚገነቡትን የመንግሥት አዳራሾች ለመደገፍ በሚሰጡት ልግስና የተሞላበት አስተዋጽዖ፣ ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾችም ሆነ ለሌሎች በሚያሳዩት እንግዳ ተቀባይነትና በጦርነት ሳቢያ ለተፈናቀሉና ተመሳሳይ በሆነ ችግር ውስጥ ለሚገኙ በሚያከናውኑት ከፍተኛ የደግነት ተግባር ይሖዋ አደራ የሰጣቸው የታመኑ መጋቢዎች መሆናቸውን አሳይተዋል። በቡድን ደረጃ እውነተኛ ክርስቲያኖች የጌታን ንብረት በአግባቡ ይዘዋል።
“ታማኝና ልባም መጋቢ”
5 የመጋቢነት ሥራ የሚከናወነው በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በድርጅት ደረጃም ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ ያለውን የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ “ታማኝና ልባም መጋቢ” በማለት ጠርቶታል። (ሉቃስ 12:42) የዚህ “ታማኝ መጋቢ” ኃላፊነት ‘ምግብ’ ማቅረብና በዓለም አቀፉ የምስራች ስብከት ሥራ ግንባር ቀደም መሆን ነው። (ራእይ 12:17) በአስተዳደር አካሉ የተወከለው የታማኙ መጋቢ ቡድን አምላክ በአደራ የሰውን ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ “መክሊት” በአግባብ የመያዝ ኃላፊነት ተጥሎበታል። (ማቴ. 25:15) እያንዳንዱ ቅርንጫፍ ቢሮም ‘የታማኙን መጋቢ’ ምሳሌ በመከተል ማንኛውም የገንዘብ መዋጮ ለታለመለት ዓላማ ማለትም የመንግሥቱን ፍላጎት ለማራመድ እንዲውል ለማድረግ ይጥራል። ስለሆነም “ታማኝና ልባም ባሪያ” መዋጮው ለታቀደለት ዓላማ መዋሉን ብቻ ሳይሆን በጥንቃቄ፣ በቁጠባና ውጤታማ በሆነ መንገድ ሥራ ላይ መዋሉንም ጭምር የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት።
6 የይሖዋ ምሥክሮች በ20ኛው መቶ ዘመን በኅትመት ሥራ ረገድ ያደረጉት እድገት የሚደረገውን የገንዘብ መዋጮ ምን ያህል በአግባብ እንደሚጠቀሙ የሚያሳይ ምሳሌ ነው። በዚህ “በመጨረሻው ቀን” የመጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑ ጽሑፎች ማለትም የመጽሔቶች፣ የመጻሕፍት፣ የብሮሹሮች፣ የቡክሌቶች፣ የትራክቶችና የመንግሥት ዜናዎች ስርጭት ‘ወንጌሉን’ ለማዳረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። (ማር. 13:10፤ 2 ጢሞ. 3:1) ከዚህም በተጨማሪ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ‘ለእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች’ እና የሥራ ባልደረቦቻቸው ለሆኑት ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል ማለትም ‘ለእጅግ ብዙ ሰዎች’ ‘በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን’ ለመስጠት የሚያስችል ዋነኛ መሣሪያ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል።—ማቴ. 24:45፤ ኤፌ. 2:19፤ ራእይ 7:9፤ ዮሐ. 10:16
7 ቀደም ባሉት ጊዜያት የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጁዋቸውን ጽሑፎች በሙሉ የሚያሳትሙት በንግድ ማተሚያ ቤቶች ነበር። ሆኖም ይበልጥ ውጤታማና በመንፈሳዊም ጠቃሚ ስለሆነ በ1920ዎቹ ውስጥ የይሖዋ አገልጋዮች የራሳቸው ማተሚያ እንዲኖራቸው ተወሰነ። በ1920 በብሩክሊን ኒው ዮርክ በትንሹ የተጀመረው የኅትመት ሥራ ቀስ በቀስ አድጎ በከፍተኛ ስፋት ይካሄድ ጀመር። በ1967 የኅትመት ሥራው በከተማው ውስጥ በአንድ አካባቢ ያሉ አራት ሕንፃዎች ጠቀለለ። በሌሎች አገሮችም የኅትመት ሥራ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት በአብዛኞቹ አገሮች ሥራው ተቋረጠ።
8 ምንም እንኳ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የኅትመት ሥራው ከፍተኛ እድገት ቢያሳይም መላውን ዓለም ለማዳረስ ግን በቂ አልነበረም። በዚህ ምክንያት ከጦርነቱ በኋላ በነበሩት ዓመታት ካናዳን፣ ዴንማርክን፣ እንግሊዝን፣ ግሪክን፣ ደቡብ አፍሪካን፣ ስዊዘርላንድንና ምዕራብ ጀርመንን ጨምሮ በሌሎች በርካታ አገሮች የኅትመት ሥራ እንዲካሄድ የተደረገ ሲሆን በአንዳንዶቹ ደግሞ በፊቱንም ተጀምሮ ነበር። በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ በአውስትራሊያ፣ በብራዚል፣ በፊንላንድ፣ በጋና፣ በጃፓን፣ በናይጄሪያና በፊሊፒንስም የኅትመት ሥራ ተጀመረ። ከእነዚህ አገሮች ውስጥ አንዳንዶቹ ጠንካራ ሽፋን ያላቸው መጻሕፍት ያዘጋጁ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ በጊልያድ ትምህርት ቤት የነበሩ ሚስዮናውያን በኅትመት ሥራ ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ የአገሩ ተወላጅ የሆኑ ወንድሞችን በሥራው ለመርዳት ከእነዚህ አገሮች ወደ አንዳንዶቹ ተልከዋል።
9 በ1980ዎቹ ውስጥ መጽሔቶች የሚታተሙባቸው አገሮች ብዛት 51 ደርሶ ነበር።a እንዲህ መደረጉ የጌታ ንብረት በአግባቡ መያዙን አሳይቷል! የመንግሥቱ ሥራ ላሳየው እድገት ምንኛ ጠንካራ ማስረጃ ነው! ‘ይሖዋን ከሃብታቸው የሚያከብሩ’ በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በግለሰብ ደረጃ በልግስና ለሰጡት ድጋፍ ትልቅ ምክር ነው! (ምሳሌ 3:9) በዚህ መንገድ መልካም መጋቢዎች መሆናቸውን አስመስክረዋል፤ ይሖዋም በተለያዩ መንገዶች ባርኳቸዋል።
የትኩረት አቅጣጫ ለውጥ
10 በ1970ዎቹ ውስጥና በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ የኅትመት ሥራ ቴክኖሎጂ ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል፤ የይሖዋ ምሥክሮችም አዳዲስ በሆኑት የኅትመት ዘዴዎች መጠቀም ጀመሩ። ቀደም ባሉት ጊዜያት የሚጠቀሙት ኋላ ቀር በሆነ የኅትመት መሣሪያ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች እጅግ ዘመናዊ በሆነ የኅትመት መሣሪያ መጠቀም ሲጀምሩ የበፊቶቹን መሣሪያዎች ቀስ በቀስ በአዳዲሶቹ መተካት ጀመሩ። ይህም በመሆኑ ባለ ሙሉ ቀለም ስዕሎች የያዙ ማራኪ ጽሑፎች ማዘጋጀት ተቻለ። ይህ ደግሞ በድሮዎቹ መሣሪያዎች ይታተሙ የነበሩት ባለ ሁለት ቀለም ስዕሎች (ጥቁርና አንድ ሌላ ቀለም) እንዲቀየሩ አስችሏል። ከዚህም በተጨማሪ የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ከኅትመት በፊት ያለው ሥራ (ለኅትመት የሚደረገው ቅድመ ዝግጅት) ባጠቃላይ እንዲቀየር አስችሏል። የይሖዋ ምሥክሮች መልቲላንጉዌጅ ኤሌትሮኒክ ፎቶታይፕሴቲንግ ሲስተም (ሜፕስ) የተባለ የተራቀቀ የኮምፒዩተር ፕሮግራም ስላዘጋጁ በ370 ቋንቋዎች ጽሑፎች ማዘጋጀት ችለዋል። የትኛውም በገበያ ላይ ያለ ፕሮግራም የሜፕስን ያህል እነዚህን በሚያህሉ በርካታ ቋንቋዎች የመሥራት አቅም የለውም።
11 ሜፕስ የተባለው የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂና በኮምፒዩተር አማካኝነት የሚደረግ የመልእክት ልውውጥን የመሳሰሉ አዳዲስ ግኝቶች መንፈሳዊ ምግብ በወቅቱ በማቅረብ ረገድ ሌላ ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ላይ እንዲደረስ አስችለዋል። ኋላ ቀር በሆነ ቴክኖሎጂ ይሠራ በነበረበት ቀደም ባለው ጊዜ በእንግሊዝኛ ሳይሆን በሌላ ቋንቋ በሚዘጋጁ መጽሔቶች ላይ የሚወጣው ትምህርት በእንግሊዝኛው መጽሔት ላይ ከወጣ ወራት አንዳንዴም አንድ ዓመት ያለፈው ነበር። በአሁኑ ጊዜ መጠበቂያ ግንብ በ115 ቋንቋዎች ንቁ! ደግሞ በ62 ቋንቋዎች እኩል ይታተማሉ። ይህ ማለት የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ በሚያደርጉት ሳምንታዊ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ከሚገኙት ውስጥ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑ ተሰብሳቢዎች በተመሳሳይ ጊዜ አንድ ዓይነት ትምህርት ያገኛሉ። እንዴት ያለ በረከት ነው! ለእነዚህ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ወጪ መደረጉ የጌታን ንብረት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም!
ድርጅታዊ የአሠራር ለውጦች
12 እነዚህ አዳዲስ የማተሚያ ዘዴዎች የይሖዋ ምሥክሮች በሚያካሂዱት ዓለም አቀፋዊ የኅትመት ሥራ ላይ ድርጅታዊ የአሠራር ለውጦች አስከትለዋል። አዳዲሶቹ የማተሚያ መሣሪያዎች ከድሮዎቹ ይልቅ እጅግ ፈጣን ናቸው። ሆኖም የዚያኑ ያክል ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ናቸው። የጽሑፍ፣ የትርጉም፣ የስዕልና የግራፊክስ ሥራዎችን የሚደግፉት የኮምፒዩተር መዋቅሮች ከበፊተኞቹ ይልቅ ላቅ ያለ የሥራ ቅልጥፍና ያስገኙ ቢሆንም በጣም ውድ ናቸው። በዚህ ሁኔታ በ51 አገሮች ውስጥ መጽሔቶች ማተም የሚያዋጣ እንደማይሆን ወዲያውኑ ግልጽ ሆነ። ይህም በመሆኑ በ1990ዎቹ ውስጥ ‘ታማኙ መጋቢ’ ጉዳዩን እንደገና ገመገመ። ምን ውሳኔ ላይ ተደረሰ?
13 በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ማተሚያዎች ቢታጠፉ የይሖዋ ምሥክሮችና ባልንጀሮቻቸው የሚያዋጡት “ሃብት” ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ሥራ ላይ ሊውል እንደሚችል ጥናቶች አሳይተዋል። ስለሆነም ኅትመት የሚካሄድባቸው ቅርንጫፍ ቢሮዎች ቁጥር ቀስ በቀስ ተቀነሰ። ጀርመን፣ ከዚህ በፊት የራሳቸውን ኅትመት ያካሂዱ የነበሩ አገሮችን ጨምሮ በምስራቅና በምዕራብ አውሮፓ ለሚገኙ በርካታ አገሮች መጽሔቶችና ጽሑፎች ማተም ጀመረች። ኢጣሊያ፣ ለአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች እንዲሁም ግሪክና አልባኒያን ጨምሮ ለደቡብ ምስራቅ አውሮፓ አገሮች ታትማለች። በአፍሪካ ውስጥ ኅትመት የሚካሄደው በናይጄሪያና በደቡብ አፍሪካ ብቻ ሆኗል። በዓለም ዙሪያ ተመሳሳይ የሆነ ውህደት ተደርጓል።
ሊጤኑ የሚገባቸው ጉዳዮች
14 ከሐምሌ 1998 ጀምሮ የሚከተሉት የአውሮፓ አገሮች መጽሔቶችን ማተም ያቆማሉ:- ኦስትሪያ፣ ቼኮዝላቫኪያ፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ግሪክ፣ ሀንጋሪ፣ ኔዘርላንድ፣ ሩማኒያ፣ ስዊዘርላንድና የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ። በአውሮፓ ውስጥ የኅትመት ሥራ የሚካሄደው በብሪታንያ፣ በፊንላንድ፣ በጀርመን፣ በኢጣሊያ፣ በስፔይንና በስዊድን ብቻ ይሆናል። በዚህ መንገድ አላስፈላጊ ወጪዎች እንዲቀነሱና መዋጮዎች በተሻለ መንገድ ለዓለም አቀፉ ሥራ እንዲውሉ ይደረጋል። የትኞቹ አገሮች የኅትመት ሥራ መቀጠል እንዳለባቸውና የትኞቹ ደግሞ ማቆም እንደሚኖርባቸው የተወሰነው እንዴት ነው? ‘ታማኙ መጋቢ’ የጌታን ንብረት በአግባቡ በመያዝ ረገድ የተጣለበትን አደራ ለመወጣት በእያንዳንዱ ቦታ የኅትመት ሥራውን ለማካሄድና ጽሑፎቹን በተፈላጊው ቦታ ለማድረስ ያለውን ወጪ በጥንቃቄ አስልቷል።
15 በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ለተወሰነ ጊዜ የዘለቀ ስም የማጥፋት ዘመቻ ተካሂዶባቸዋል። (ማቴ. 5:11) ሥርዓት አልበኛ የሆኑ አንዳንድ ግለሰቦች ምሥክሮቹ “አደገኛ ኑፋቄ” የሚል ስያሜ እንዲሰጣቸው ለማድረግ ሞክረዋል። ይህ ጥቃት አንዳንዶች በእነዚህ አገሮች ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸውን ሕጋዊ መብት እስከመዳፈር አድርሷቸዋል። ውሸቱ እንዲጋለጥና እውነቱ እንዲታወቅ ለማድረግ አንዳንድ እርምጃዎች በመወሰድ ላይ ናቸው። ውጤቱን በተመለከተ ይሖዋ ምን እንደሚያደርግ በትዕግሥት እንጠብቃለን። (መዝ. 62:7-9) በዓለም ዙሪያ በብዙ አገሮች ባለሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ ከአድልዎ ነፃ የሆኑ ውሳኔዎችን አድርገዋል። በእነዚህ አገሮች ያሉ ባለሥልጣናትም ጉዳዩን ያለ አድልዎ ተመልክተው የይሖዋ ምሥክሮችን ሕጋዊ መብት የሚያስከብር ትክክለኛ ውሳኔ ያደርጋሉ የሚል ትምክህት አለን።
16 ‘ታማኙ መጋቢ’ ይህን ስም የማጥፋት ዘመቻ በቸልታ የማይመለከተው ቢሆንም እንኳ በአንዳንድ አገሮች የኅትመት ሥራው እንዲቋረጥና በሌሎቹ ደግሞ በስፋት እንዲቀጥል የተወሰነበት ዐበይት ምክንያት ከተግባራዊነቱ አንፃር ታይቶ ነው። አንድ አገር ለሌሎች በርካታ አገሮች ጽሑፍ እንዲያትም መደረጉ ይበልጥ አመቺ ከመሆኑም በላይ ውድ የሆኑትን መሣሪያዎች በተሻለ መንገድ ለመጠቀም ያስችላል። በአሁኑ ጊዜ የኅትመት ሥራ የሚካሄደው ዝቅተኛ ወጪ በሚጠይቁ፣ ጥሬ ዕቃዎች በሚገኙባቸውና ጥሩ የማጓጓዣ አቅርቦት ባላቸው አገሮች ውስጥ ነው። እንዲህ በመደረጉም የጌታ ንብረት አግባብ ባለው መንገድ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። በአንድ አገር ውስጥ የኅትመት ሥራ መቋረጡ የስብከቱ ሥራ ያቆማል ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። አሁንም ቢሆን የተትረፈረፈ የጽሑፎች አቅርቦት ይኖራል። ከዚህም በተጨማሪ ኅትመት በማይካሄድባቸው አገሮች ውስጥ የሚገኙት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ለጎረቤቶቻቸው ‘የሰላምን ምስራች’ በቅንዓት መናገራቸውን ይቀጥላሉ። (ኤፌ. 2:17) ከዚህም በላይ ይህ አዲስ አደረጃጀት ሌሎች ጥቅሞችንም አስገኝቷል።
17 በዴንማርክ፣ በግሪክ፣ በኔዘርላንድና በስዊዘርላንድ የነበሩት አብዛኛዎቹ ዘመናዊ የማተሚያ መሣሪያዎች ወደ ናይጄሪያና ፊሊፒንስ መላካቸው ካስገኛቸው ጥቅሞች መካከል አንዱ ነው። በአውሮፓ የሚገኙት የማተሚያ መሣሪያዎቹን የሚያንቀሳቅሱት ልምድ ያላቸው ወንድሞች መሣሪያዎቹ ወደ ተላኩባቸው አገሮች በመሄድ በዚያ ለሚገኙት ወንድሞች አጠቃቀማቸውን በተመለከተ ስልጠና እንዲሰጡ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለዋል። ይህም በመሆኑ እነዚህ አገሮች ሌሎቹ የነበራቸው ዓይነት ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸው መጽሔቶች ሊያገኙ ነው።
18 መጽሔቶች ለማተም የሚወጣው ወጪ የኅትመት ሥራው በቀጠለባቸው ጥቂት አገሮች ላይ ብቻ መወሰኑም ጥቅም አስገኝቷል። ከዚህም የተነሳ የኅትመት ሥራው ካቆመባቸው አገሮች የሚገኘው ገንዘብ የመንግሥት አዳራሾችን ለመገንባት፣ ድሀ በሆኑ አገሮች የሚኖሩ ወንድሞቻችንን ለመርዳትና ለመሳሰሉት ሌሎች ዓላማዎች ሊውል ይችላል። በዚህ መንገድ የጌታን ንብረት በጥንቃቄ ጥቅም ላይ ማዋሉ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የጻፋቸው ቀጥሎ ያሉት ቃላት በዓለም አቀፍ ደረጃ ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ተፈጻሚነት እንዲያገኙ አስችሏል:- “ሁላችሁም እኩል እንድትሆኑ እንጂ እናንተ በመስጠት ስትቸገሩ ሌሎች እንዲያርፉ ብዬ አይደለም። . . . አሁን የእናንተ ሀብት ለእነርሱ ችግር ይዋል፤ በዚህ ዐይነት በመካከላችሁ እኩልነት ይኖራል።”—2 ቆሮ. 8:13, 14 የ1980 ትርጉም
19 በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ማተሚያዎች በመታጠፋቸው በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እርስ በርሳቸው በጥብቅ ተሳስረዋል። በዴንማርክ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ምንም እንኳ ቀደም ሲል የራሳቸውን መጽሔቶች ያትሙ የነበረ ቢሆንም አሁን መጽሔቶቻቸው በጀርመን መታተማቸው ምንም ችግር አይፈጥርባቸውም። በጀርመን ያሉ ወንድሞቻቸው ለሚሰጡዋቸው አገልግሎት አመስጋኞች ናቸው። በጀርመን የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ያዋጡት መዋጮ ለዴንማርክ ወይም ለሩሲያ፣ ለዩክሬይንና ለሌሎች አገሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ለማቅረብ መዋሉ ቅር ያሰኛቸዋልን? በጭራሽ! አሁን በእነዚህ አገሮች ያሉ ወንድሞቻቸው የሚሰጡት መዋጮ ለሌሎች አስፈላጊ ዓላማዎች ሊውል እንደሚችል በማወቃቸው ይደሰታሉ።
ንብረቱን በጥንቃቄ መያዝ
20 በመላው ዓለም በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሾች ውስጥ “ማኅበሩ ለሚያካሂደው ዓለም አቀፋዊ ሥራ የሚውል መዋጮ—ማቴዎስ 24:14” የሚል ጽሑፍ የተለጠፈባቸው የመዋጮ ሣጥኖች ይቀመጣሉ። ከእነዚህ ሣጥኖች ውስጥ የሚሰበሰበው በፈቃደኝነት የተሰጠ መዋጮ አስፈላጊ በሆነበት ቦታ ሁሉ ሥራ ላይ ይውላል። መዋጮዎቹ ጥቅም ላይ የሚውሉበትን መንገድ የሚወስነው ‘ታማኙ መጋቢ’ ነው። ይህም በመሆኑ በአንድ አገር ውስጥ የተሰጠ መዋጮ በብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሚገኝ ሌላ አገር ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች የሚሠሩትን ሥራ ለመደገፍ ሊውል ይችላል። መዋጮዎች በዓውሎ ነፋስ፣ በመሬት መንቀጥቀጥና በእርስ በርስ ጦርነቶች ለተጎዱ የእምነት ጎደኞቻችን አስቸኳይ እርዳታ ለመለገስ ውለዋል። ከዚህም በተጨማሪ መዋጮዎች ከ200 በላይ በሚሆኑ አገሮች ውስጥ የሚያገለግሉ ሚስዮናውያንን ለመደገፍ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው።
21 እንደሚታወቀው በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ገንዘብ ነክ ጉዳዮች የሚጠቀሱት በወር አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን ያውም ለጥቂት ደቂቃዎች ነው። በመንግሥት አዳራሾችም ሆነ በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ሙዳየ ምጽዋት አይዞርም። ግለሰቦች የገንዘብ እርዳታ እንዲሰጡ ለመገፋፋት ተብሎ የሚደረግ የተለየ ነገር የለም። ተቀጥረው ገንዘብ የሚያሰባስቡ ሰዎች የሉም። የመጠበቂያ ግንብ፣ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የሚያካሂደውን ዓለም አቀፋዊ ሥራ ለመደገፍ የሚፈልጉ ሰዎች በምን መልኩ መዋጮዎች መስጠት እንደሚችሉ የሚገልጽ ጽሑፍ በዓመት አንድ ጊዜ መጠበቂያ ግንብ ላይ ይወጣል። የማኅበሩን የገንዘብ እንቅስቃሴ አስመልክቶ በንቁ! መጽሔት ላይ በቋሚነት የሚጠቀስ ነገር የለም። ታዲያ ሰፊ ለሆነው ዓለም አቀፋዊ የምሥራቹ ስብከት ሥራ፣ አስፈላጊ ለሆኑ የመንግሥት አዳራሾች ግንባታ፣ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሰማሩትን ለመደገፍና በችግር ላይ ላሉ ክርስቲያኖች እርዳታ መስጠት የተቻለው እንዴት ነው? ይሖዋ ለሕዝቦቹ የለጋስነት መንፈስ በመስጠት አስደናቂ በሆነ መንገድ ባርኳቸዋል። (2 ቆሮ. 8:2) በዚህ አጋጣሚ ‘ይሖዋን ከሀብታቸው በማክበር’ ድርሻቸውን ያበረከቱትን በሙሉ ለማመስገን እንወዳለን። ‘ታማኙ መጋቢ’ የጌታን ንብረት መቆጣጠሩን እንደሚቀጥል እርግጠኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሖዋ ዓለም አቀፋዊውን ሥራ ለማስፋፋት የተደረጉትን ዝግጅቶች በሙሉ መባረኩን እንዲቀጥል እንጸልያለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ከእነዚህ አገሮች ውስጥ በሰባቱ የኅትመት ሥራው ይከናወን የነበረው በንግድ ማተሚያ ቤቶች ነበር።