የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ጽናት ለክርስቲያኖች እጅግ አስፈላጊ ነው
    መጠበቂያ ግንብ—1993 | መስከረም 15
    • ጽናት ለክርስቲያኖች እጅግ አስፈላጊ ነው

      “በእምነታችሁ [ላይ] . . . መጽናትን . . . ጨምሩ። ” — 2 ጴጥሮስ 1:​5, 6

      1, 2. ሁላችንም እስከ መጨረሻው መጽናት ያለብን ለምንድን ነው?

      አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካችና ባለቤቱ በ90ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ አንድ ክርስቲያን ወንድማቸውን ለመጠየቅ ሄደው ነበር። ይህ ወንድም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ብዙ አሥርተ ዓመታት አሳልፏል። በሚጨዋወቱበት ጊዜ አረጋዊው ወንድም ባለፉት ዓመታት ካገኛቸው መብቶች አንዳንዶቹን እያስታወሰ ነገራቸው። እንባው በጉንጮቹ ላይ ኮለል ብሎ እየወረደ “አሁን ግን ብዙ መሥራት አልችልም” ሲል በሐዘን ተናገረ። ተጓዥ የበላይ ተመልካቹም መጽሐፍ ቅዱሱን ገለጠና ኢየሱስ “እስከ መጨረሻው የሚጸና . . . እርሱ ይድናል” ሲል የተናገረበትን ማቴዎስ 24:​13ን አውጥቶ አነበበለት። ከዚያም የበላይ ተመልካቹ ይህን ውድ ወንድማችንን እየተመለከተ “ምንም ያህል ብዙ ወይም ጥቂት ሥራ ብንሠራ ሁላችንም የተሰጠን ትልቁ ተልዕኰ እስከ መጨረሻው ጸንቶ መገኘት ነው” አለው።

      2 አዎን፤ እስከዚህ ሥርዓት መጨረሻ ድረስ ወይም እስከ ሕይወታችን ፍጻሜ ድረስ ሁላችንም መጽናት አለብን። ለመዳን የሚያስችለንን የይሖዋን ሞገስ የምናገኝበት ሌላ ምንም መንገድ የለም። የምንገኘው በሕይወት ሩጫ ውስጥ ነው። የሩጫውን የመጨረሻ መስመር እስክናልፍ ድረስም ‘በጽናት መሮጥ’ አለብን። (ዕብራውያን 12:​1 አዓት) ሐዋርያው ጴጥሮስ የዚህን ባሕርይ አስፈላጊነት አጥብቆ ሲገልጽ ክርስቲያኖችን “በእምነታችሁ [ላይ] . . . መጽናትን . . . ጨምሩ” ሲል መክሯል። (2 ጴጥሮስ 1:​5, 6) ግን መጽናት ማለት ምን ማለት ነው?

      መጽናት ማለት ምን ማለት ነው?

      3, 4. መጽናት ማለት ምን ማለት ነው?

      3 መጽናት ማለት ምን ማለት ነው? “መጽናት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል (ሃይፖሜኖ) ቃል በቃል ሲተረጎም “ባሉበት መቆየት ወይም መቀጠል” ማለት ነው። ይህ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 17 ጊዜ ተጠቅሷል። የመዝገበ ቃላት አዘጋጆች በሆኑት በደብልዩ ባወር፣ በኤፍ ደብልዩ ጊንግሪች እና በኤፍ ዳንከር መሠረት ቃሉ “ከመሸሽ ይልቅ በነበሩበት መቆየት . . .፣ ከአቋም ፍንክች አለማለት፣ ችግሩን መቋቋም” የሚል ትርጉም አለው። “ጽናት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ስም (ሃይፖሜኔ) ከ30 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ ይገኛል። በዊልያም ባርክሌይ የተዘጋጀው ኤ ኒው ቴስታመንት ወርድቡክ የተሰኘው መጽሐፍ ይህንን ቃል አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “ቃሉ አንድን ነገር በትዕግሥት ብቻ ሳይሆን ደስ የሚያሰኝ ተስፋ ይዞ የመቻልን መንፈስ ያመለክታል። . . . አንድ ሰው ፊቱን ነፋስ ወደሚመጣበት አቅጣጫ አዙሮ ሳይንገዳገድ እንዲቆም የሚያስችለው ባሕርይ ነው። ከባዱን መከራ ወደ ክብር ለመለወጥ የሚችል መልካም ባሕርይ ነው፤ ምክንያቱም ከስቃዩ በስተጀርባ ያለውን ግቡን አሻግሮ ይመለከታል።”

      4 እንግዲያው ጽናት ከአቋማችን ፍንክች ሳንል እንድንቆምና ዕንቅፋቶች ወይም ችግሮች ቢያጋጥሙንም ተስፋ እንዳንቆርጥ ያደርገናል። (ሮሜ 5:​3–5) በጊዜው ካለው ሥቃይ በስተጀርባ ያለውን ግብ ማለትም በሰማይም ሆነ በምድር ላይ ዘላለማዊ ሕይወት የማግኘትን ሽልማት ወይም ስጦታ አሻግሮ ይመለከታል። — ያዕቆብ 1:​12

      መጽናት ለምን አስፈለገ?

      5. (ሀ) ሁሉም ክርስቲያኖች ‘መጽናት የሚያስፈልጋቸው’ ለምንድን ነው? (ለ) የሚደርሱብን ፈተናዎች በምን ሁለት ክፍሎች ሊከፈሉ ይችላሉ?

      5 ክርስቲያኖች ስለሆንን ሁላችንም ‘መጽናት ያስፈልገናል።’ (ዕብራውያን 10:​36) ለምን? መሠረታዊው ምክንያት “ልዩ ልዩ ፈተና” ስለሚደርስብን ነው። ይህ በያዕቆብ 1:​2 ላይ የሚገኘው ጥቅስ በግሪክኛው ቋንቋ አንድ ሰው ዘራፊ ሲያጋጥመው ከሚሰማው ድንገተኛ ወይም የማያስደስት ገጠመኝ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ያመለክታል። (ከሉቃስ 10:​30 ጋር አወዳድር።) የሚደርሱብን ፈተናዎች በሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ፤ እነርሱም:- በወረስነው ኃጢአት ምክንያት በሰው ሁሉ ላይ የሚደርሱ መከራዎችና ለአምላክ ያደርን በመሆናችን ምክንያት የሚደርሱብን መከራዎች ናቸው። (1 ቆሮንቶስ 10:​13፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​12 አዓት) ከነዚህ ፈተናዎች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

      6. አንድ የይሖዋ ምስክር የደረሰበትን የሚያሰቃይ ሕመም በጽናት የተቋቋመው እንዴት ነበር?

      6 ከባድ ሕመም። አንዳንድ ክርስቲያኖች እንደ ጢሞቴዎስ ‘በተደጋጋሚ የሚመላለስባቸውን በሽታ’ ችለው ለመኖር ተገደዋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:​23) በተለይም ሥር የሰደደ፣ ምናልባትም በጣም የሚያሰቃይ በሽታ ሲይዘን በአምላክ እርዳታ መጽናት፣ ከአቋማችን ፍንክች ሳንል መቆምና ክርስቲያናዊ ተስፋችን እንዳይደበዝዝብን መጠበቅ ያስፈልገናል። ፈጥኖ በሚሰራጭ የካንሰርነት ባሕርይ ያለው እጢ ምክንያት ከደረሰበት ሥቃይ ጋር ለረጅም ጊዜ ሲታገል የቆየውን በ50ዎቹ ዓመታት ዕድሜው መጀመሪያ ላይ የሚገኝ የአንድ ምስክር ምሳሌ ተመልከቱ። ሁለት ጊዜ ቀዶ ሕክምና ሲደረግለት ደም ላለመውሰድ ባለው አቋም ጸንቷል። (ሥራ 15:​28, 29) ሆኖም እጢው እንደገና በሆዱ ውስጥ ከመውጣቱም በላይ በአከርካሪው አጠገብ ማደግ ጀመረ። እብጠቱ እየጨመረ ሲሄድ ይህ ወንድም ምንም ዓይነት መድኃኒት ሊያስታግሰው የማይችል ከፍተኛ አካላዊ ሥቃይ ደረሰበት። ይሁን እንጂ በጊዜው ከነበረበት ሥቃይ ባሻገር በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚያገኘውን የሕይወት ሽልማት ይመለከት ነበር። ስለዚህም በውስጡ ይንቀለቀል የነበረውን ተስፋ ለዶክተሮች፣ ለነርሶችና ሊጠይቁት ለመጡት ሰዎች ማካፈሉን አላቆመም። ወንድም እስከ መጨረሻው ማለትም እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ጸና። ያለብህ የጤና ችግር ለሕይወትህ የማያሰጋ ሊሆን ወይም ይህ የተወደደ ወንድም የደረሰበትን ያህል የሚያሰቃይ ላይሆን ቢችልም ትልቅ የጽናት ፈተና ሊያመጣብህ ይችላል።

      7. ለአንዳንድ መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መጽናት ምን ዓይነት ሥቃይንም ጭምር መቋቋምን ይጨምራል?

      7 ስሜታዊ ሥቃይ። አልፎ አልፎ አንዳንድ የይሖዋ ምስክሮች ‘በልብ ሐዘን’ ምክንያት የሚመጣ ‘የመንፈስ መሰበር’ ያጋጥማቸዋል። (ምሳሌ 15:​13 አዓት) በዚህ ‘አስጨናቂ ዘመን’ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ማጋጠሙ እንግዳ ነገር አይደለም። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) ሳይንስ ኒውስ የተባለው መጽሔት በታኅሣሥ 5, 1992 እትሙ እንዲህ በማለት ሪፖርት አድርጓል:- “ከባድ፣ ብዙውን ጊዜም አካልን የሚያደክም የመንፈስ ጭንቀት ከ1915 ወዲህ ባለው ትውልድ ላይ በየዓመቱ እየጨመረ ሄዷል።” ለዚህ ዓይነቱ የመንፈስ ጭንቀት መንስኤ የሚሆኑት ነገሮች ከሥነ አእምሮአዊ ችግሮች አንስቶ አስከፊ እስከሆኑ ገጠመኞች ድረስ የተለያዩ ናቸው። አንዳንድ ክርስቲያኖች በየዕለቱ የሚደርስባቸውን ስሜታዊ ቀውስ ተቋቁመው ለመጽናት ተገደዋል። ሆኖም እጃቸውን አይሰጡም፤ እያነቡም ቢሆን ለይሖዋ ታማኝ ሆነው ይቆያሉ። — ከመዝሙር 126:​5, 6 ጋር አወዳድር።

      8. ምን ዓይነት የገንዘብ ችግር ሊያጋጥመን ይችላል?

      8 የሚያጋጥሙን የተለያዩ ፈተናዎች ከባድ የኢኮኖሚ ችግርንም የሚጨምሩ ሊሆኑ ይችላሉ። በኒው ጀርሲ ዩ ኤስ ኤ የሚኖር አንድ ወንድም በድንገት ከሥራ ሲወጣ ቤተሰቡን የመመገቡና መኖሪያ ቤቱን የማጣቱ ጉዳይ አሳሰበው። ነገሩ ለምን እንዳሳሰበው ሊገባን ይችላል። ይሁን እንጂ የመንግሥቱ ተስፋ እንዲጨልምበት አልፈቀደም። ሌላ ሥራ እያፈላለገ ይህንን አጋጣሚ ረዳት አቅኚ ሆኖ ለማገልገል ተጠቀመበት። በመጨረሻም ሥራ አገኘ። — ማቴዎስ 6:​25–34

      9. (ሀ) የምንወደው ሰው መሞት ጽናት ሊጠይቅብን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) የሐዘን እንባ ማንባት ስህተት እንዳልሆነ የሚያሳዩት የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው?

      9 የምትወደው ሰው በሞት ተለይቶህ ከሆነ ሊያጽናኑህ የመጡት ሰዎች ሁሉ ወደወትሮው ተግባራቸው ከተመለሱ በኋላ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ጽናት እንዲኖርህ ያስፈልጋል። በተለይ በየዓመቱ ያ የምትወደው ሰው የሞተበት ቀን ሲደርስ ሐዘኑ ይከብድብህ ይሆናል። ይህን ዓይነት ሐዘን ችሎ መጽናት ይገባል ሲባል ግን የሐዘን እንባ ማፍሰስ ስህተት ነው ማለት አይደለም። አንድ የምንወደው ሰው ሲሞት ማዘን ተፈጥሮአዊ ባሕርይ ነው። በትንሣኤ ተስፋ ላይ እምነት እንደሌለን በጭራሽ አያመለክትም። (ዘፍጥረት 23:​2፤ ከዕብራውያን 11:​19 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ አልዓዛር ከሞተ በኋላ ለማርታ “ወንድምሽ ይነሳል” ብሎ በእርግጠኛነት ቢነግራትም ‘እንባውን አፍስሷል።’ አልዓዛርም ኢየሱስ እንዳለው ተነስቷል! — ዮሐንስ 11:​23, 32–35, 41–44

      10. የይሖዋ ሕዝቦች ከሌሎች ሰዎች በተለየ መንገድ መጽናት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

      10 በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሱት መከራዎች በተጨማሪ የይሖዋ ሕዝቦች በተለየ መንገድ መጽናት ያስፈልጋቸዋል። ኢየሱስ “ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” ሲል አስጠንቅቋል። (ማቴዎስ 24:​9) እንዲሁም “እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል” ብሏል። (ዮሐንስ 15:​20) ይህ ሁሉ ጥላቻና ስደት የሚደርስብን ለምንድን ነው? የትም ቦታ እንኑር የአምላክ አገልጋዮች በመሆናችን ሰይጣን ለይሖዋ ያለንን የታማኝነት አቋም ሊያበላሽብን ስለሚጥር ነው። (1 ጴጥሮስ 5:​8፤ ከራእይ 12:​17 ጋር አወዳድር።) ሰይጣን ይህን ዓላማውን ለማሳካት ሲል የስደቱን እሳት እያራገበ ጽናታችን ከባድ ፈተና እንዲደርስበት ያደርጋል።

      11, 12. (ሀ) የይሖዋ ምስክሮችና ልጆቻቸው በ1930ዎቹና በ1940ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ምን የጽናት ፈተና አጋጥሟቸው ነበር? (ለ) የይሖዋ ምስክሮች ለብሔራዊ አርማ ሰላምታ የማይሰጡት ለምንድን ነው?

      11 ለምሳሌ ያህል በ1930ዎቹና በ1940ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ በዩናይትድ ስቴትስና በካናዳ ይኖሩ የነበሩ የይሖዋ ምስክሮችና ልጆቻቸው በኅሊናቸው ምክንያት ለብሔራዊው አርማ ሰላምታ አንሰጥም ስላሉ ስደት ደርሶባቸው ነበር። ምስክሮቹ የሚኖሩበትን አገር ብሔራዊ አርማ የሚያከብሩ ቢሆንም በአምላክ ሕግ ውስጥ በዘጸአት 20:​4, 5 ላይ የተሰጠውን እንዲህ የሚል መሠረታዊ ሥርዓት ይፈጽማሉ:- “በላይ በሰማይ ካለው፣ በታችም በምድር ካለው፣ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፣ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፣ አታምልካቸውምም፤ . . . እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና።” በትምህርት ላይ የሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች የሆኑ አንዳንድ ልጆች ይሖዋ አምላክን ብቻ ለማምለክ በመፈለጋቸው ምክንያት ከትምህርት ቤት ተባረዋል። በዚህም ምክንያት ምስክሮቹ ልጆቹን ለማስተማር የመንግሥቱን ትምህርት ቤቶች አቋቁመዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬው ጊዜ ያሉ ስለ ጉዳዩ የተረዱ መንግሥታት እንደሚያደርጉት የምስክሮቹን ሃይማኖታዊ አቋም ካወቀላቸው በኋላ እነዚህ ተማሪዎች ወደ ሕዝብ ትምህርት ቤቶች ተመልሰዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ወጣቶች በድፍረት ያሳዩት ጽናት በመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች መሠረት ለመኖር ጥረት በማድረጋቸው የተነሳ መሳቂያና መሳለቂያ ለሆኑት የዘመናችን ክርስቲያን ወጣቶች አብነት ሆኖ ያገለግላል። — 1 ዮሐንስ 5:​21

      12 በሰው ሁሉ የሚደርሱትም ይሁኑ በክርስቲያናዊ እምነታችን የተነሳ የሚመጡብን የተለያዩ ፈተናዎች መጽናት አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ያሳያሉ። ይሁን እንጂ መጽናት የምንችለው እንዴት ነው?

      እስከ መጨረሻው መጽናት የሚቻለው እንዴት ነው?

      13. ይሖዋ ጽናትን የሚጨምርልን እንዴት ነው?

      13 የአምላክ ሕዝቦች ይሖዋን ከማያመልኩት ሰዎች ይልቅ ለመጽናት በሚያስችል የተሻለ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የተረጋገጠ ነው። እርዳታ ለማግኘት “ጽናት የሚሰጠውን አምላክ” መጠየቅ እንችላለን። (ሮሜ 15:​5 አዓት) ይሁን እንጂ ይሖዋ ጽናት የሚሰጠን እንዴት ነው? አንዱ መንገድ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው በሚገኙት የጽናት ምሳሌዎች አማካኝነት ነው። (ሮሜ 15:​4) ለጽናት አርዓያ ስለሚሆኑ ስለነዚህ ሰዎች ስናሰላስል ለመጽናት ከመበረታታታችንም በላይ እንዴት መጽናት እንደሚቻልም የበለጠ እንማራለን። በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት የጽናት አርዓያዎች ውስጥ ሁለቱን ማለትም ኢዮብ በድፍረት ያሳየውን ጽናትና የኢየሱስ ክርስቶስን እንከን የለሽ ጽናት እንመልከት። — ዕብራውያን 12:​1–3፤ ያዕቆብ 5:​11

      14, 15. (ሀ) ኢዮብ በጽናት የተቋቋመው ምን ዓይነት መከራዎችን ነው? (ለ) ኢዮብ ያጋጠሙትን ፈተናዎች በጽናት ሊቋቋማቸው የቻለው እንዴት ነው?

      14 የኢዮብ ጽናት እንዲፈተን ያደረጉት ሁኔታዎች ምን ነበሩ? ኢዮብ አብዛኛውን ንብረቱን በማጣቱ ምክንያት የኢኮኖሚ ችግር ደረሰበት። (ኢዮብ 1:​14–17፤ ከኢዮብ 1:​3 ጋር አወዳድር።) አሥሩም ልጆቹ በዐውሎ ንፋስ ሲሞቱበት ከፍተኛ ሐዘን ተሰምቶታል። (ኢዮብ 1:​18–21) ከባድና በጣም የሚያሰቃይ በሽታ ይዞት ነበር። (ኢዮብ 2:​7, 8፤ 7:​4, 5) የገዛ ሚስቱ አምላክን እንዲክድ ትገፋፋው ነበር። (ኢዮብ 2:​9) የቅርብ ወዳጆቹ የሚጎዱ፣ ደግነት የጎደላቸውና እውነት ያልሆኑ ነገሮችን ተናገሩት። (ኢዮብ 16:​1–3 እና ኢዮብ 42:​7ን አወዳድር።) ይህ ሁሉ ቢደርስበትም ኢዮብ ከአቋሙ ፍንክች ሳይል ንጹሕ አቋሙን ጠብቋል። (ኢዮብ 27:​5) ኢየሱስ በጽናት የተቋቋማቸው ችግሮች በዛሬው ጊዜ የሚገኙት የይሖዋ ሕዝቦች ከሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች ጋር ተመሳሳይ ናቸው።

      15 ኢዮብ በእነዚያ ሁሉ ፈተናዎች ችሎ ሊጸና የቻለው እንዴት ነው? ኢዮብን የረዳው አንዱና ዋነኛው ነገር ተስፋ ነው። “ዛፍ ቢቆረጥ ደግሞ ያቆጠቁጥ ዘንድ፣ ቅርንጫፉም እንዳያልቅ ተስፋ አለው” ሲል ገለጸ። (ኢዮብ 14:​7) ኢዮብስ ምን ተስፋ ነበረው? ከጥቂት ቁጥሮች በኋላ እንዲህ ሲል እንደተናገረ እንመለከታለን:- “በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን? . . . በጠራኸኝና በመለስሁልህ ነበር፣ የእጅህንም ሥራ በተመኘኸው ነበር።” (ኢዮብ 14:​14, 15) አዎን፤ ኢዮብ በጊዜው ከደረሰበት ሥቃይ ባሻገር የሚኖረውን ሁኔታ ተመልክቷል። መከራው ለዘላለም እንደማይቆይ ያውቅ ነበር። ግፋ ቢል መጽናት የሚኖርበት እስከ ሞት ድረስ ብቻ ነው። ሙታንን ለማስነሳት ፍቅራዊ ምኞት ያለው ይሖዋ ወደ ሕይወት እንደሚመልሰው በተስፋ ይጠባበቅ ነበር። — ሥራ 24:15

      16. (ሀ) ከኢዮብ ምሳሌ ስለ ጽናት ምን እንማራለን? (ለ) የመንግሥቱ ተስፋ የቱን ያህል እውን ሊሆንልን ይገባል? ለምንስ?

      16 ከኢዮብ ጽናት ምን እንማራለን? እስከ መጨረሻው ለመጽናት ከፈለግን ተስፋችን በፍጹም ሊጨልምብን አይገባም። የመንግሥቱ ተስፋ የተረጋገጠ በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ የሚደርስብን ማንኛውም መከራ ከተስፋችን ጋር ሲነፃፀር ‘በጣም አጭር’ መሆኑንም አስታውስ። (2 ቆሮንቶስ 4:​16–18) ውድ ተስፋችን በጽኑ የተመሠረተው ይሖዋ ‘እንባዎችንም ሁሉ [ከዓይኖቻችን] የሚያብስበት፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ የማይሆንበት ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ የማይሆንበት’ ጊዜ በቅርቡ ይመጣል ሲል በገባልን ቃል ላይ ነው። (ራእይ 21:​3, 4) ‘የማያሳፍረን’ ይህ ተስፋ አስተሳሰባችንን መጠበቅ ይኖርበታል። (ሮሜ 5:​4, 5፤ 1 ተሰሎንቄ 5:​8) ይህ ተስፋ አዲሱ ዓለም ውስጥ ገብተን ከበሽታና ከጭንቀት ጋር መታገላችን ቀርቶ በየቀኑ ጠዋት ጠዋት ጥሩ ጤናና ንጹሕ አእምሮ ይዘን ስንነሳ፣ ስለ ከባድ የኢኮኖሚ ችግር መጨነቃችን ቀርቶ የተረጋጋ ኑሮ ስንኖር፣ ለሞቱ ወዳጆቻችን ማልቀስ ቀርቶ ከሞት ሲነሱ እያየን ስንደሰት በእምነት ዓይናችን እስኪታየን ድረስ እውን ሊሆንልን ይገባል። (ዕብራውያን 11:​1) ይህ ተስፋ ከሌለን በአሁኑ ጊዜ በሚደርሱብን ፈተናዎች ልንሸነፍና ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። እንዲህ ያለ ተስፋ ስላለን በትግላችን እንድንገፋና እስከ መጨረሻው ድረስ እንድንጸና የሚያስችለን ከፍተኛ ምክንያት አለን።

      17. (ሀ) ኢየሱስ በጽናት የተቋቋመው ምን ዓይነት መከራዎችን ነው? (ለ) ኢየሱስ በጽናት የቻለው መከራ ምን ያህል ከባድ እንደነበረ ከምን መረዳት ይቻላል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

      17 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን ‘ትኩር ብለን እንድንመለከትና’ ስለ እርሱም ‘እንድናስብ’ አጥብቆ ይመክረናል። ኢየሱስ የጸናባቸው መከራዎች ምንድን ናቸው? ከፈተናዎቹ አንዳንዶቹ በሌሎች ኃጢአትና አለፍጽምና ምክንያት የመጡ ናቸው። ኢየሱስ ችሎ የጸናው ‘ከኀጢአተኞች የደረሰበትን መቃወም’ ብቻ ሳይሆን በደቀ መዛሙርቱ መካከል ማን ታላቅ እንደሚሆን የተነሳውን ተደጋጋሚ ጭቅጭቅና በመካከላቸው የተነሱ ሌሎች ችግሮችን ጭምር ነበር። ከዚህም በላይ በማንም ላይ ደርሶ የማያውቅ የእምነት ፈተናም አጋጥሞታል። ‘በመከራ እንጨት ላይ እስከመሞት ጸንቷል።’ (ዕብራውያን 12:​1–3 አዓት፤ ሉቃስ 9:​46፤ 22:​24) መሰቀሉና የአምላክን ስም እንደተሳደበ ተቆጥሮ በውርደት መገደሉ ያስከተለበትን የአእምሮና የአካል ሥቃይ መገመት እንኳን ያስቸግራል።a

      18. ሐዋርያው ጳውሎስ በተናገረው መሠረት ኢየሱስን የረዱት ምን ሁለት ነገሮች ናቸው?

      18 ኢየሱስን እስከ መጨረሻው እንዲጸና ያስቻለው ነገር ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስን የረዱትን ሁለት ነገሮች ጠቅሷል። እነርሱም:- ‘ጸሎትና ምልጃ’ እንዲሁም ‘በፊቱ ያለው ደስታ’ ናቸው። ፍጹሙ የአምላክ ልጅ ኢየሱስ እርዳታ ለመጠየቅ አላፈረም። “በብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር” ወደ አምላክ ጸለየ። (ዕብራውያን 5:​7፤ 12:​2) በተለይ የመጨረሻው ከፍተኛ መከራ የሚደርስበት ጊዜ እየተቃረበ ሲሄድ ጥንካሬ እንዲሰጠው በተደጋጋሚና በጥብቅ መጸለይ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል። (ሉቃስ 22:​39–44) ይሖዋ ኢየሱስ ላቀረበው ምልጃ መልስ የሰጠው መከራውን በማስወገድ ሳይሆን መከራውን ለመቋቋም የሚያስችለውን ብርታት በመስጠት ነበር። ኢየሱስ የጸናው ከመከራው እንጨት በስተጀርባ የሚያገኘውን ሽልማት ማለትም ለይሖዋ ስም መቀደስና የሰውን ልጆች ቤተሰብ ከሞት ለመቤዠት አስተዋጽዖ በማድረጉ የሚያገኘውን ደስታ አሻግሮ ስለተመለከተ ነው። — ማቴዎስ 6:​9፤ 20:⁠28

      19, 20. ጽናት ስለሚያጠቃልላቸው ነገሮች ከእውነታው ያልራቀ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን የኢየሱስ ምሳሌ የረዳን እንዴት ነው?

      19 ከኢየሱስ ምሳሌ ጽናት ስለሚያጠቃልላቸው ነገሮች ከእውነታው ያልራቀ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን የሚረዱንን ብዙ ነገሮች እንማራለን። የጽናት ጎዳና ቀላል አይደለም። አንድን ፈተና መቋቋም ከከበደን ኢየሱስም እንዲሁ ተሰምቶት እንደነበረ ማወቃችን ያጽናናናል። እስከ መጨረሻው ለመጽናት ከፈለግን ኃይል እንዲሰጠን ደጋግመን መጸለይ አለብን። ፈተና ሲደርስብን አንዳንድ ጊዜ ለመጸለይ እንኳን የማንበቃ እንደሆንን ሊሰማን ይችላል። ይሖዋ ግን ‘ስለሚያስብልን’ ልባችንን እንድናፈስስለት ይጋብዘናል። (1 ጴጥሮስ 5:​7) በተጨማሪም በቃሉ ውስጥ በሰጠን ተስፋ መሠረት በእምነት ለሚለምኑት ‘ከተለመደው በላይ የሆነውን ኃይሉን’ ይሰጣቸዋል። — 2 ቆሮንቶስ 4:​7–9 አዓት

      20 አንዳንድ ጊዜ እያነባን ለመጽናት እንገደድ ይሆናል። ኢየሱስን ያስደሰተው በመከራ እንጨት ላይ የደረሰበት ሥቃይ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እርሱን ያስደሰተው በፊቱ ያለው ሽልማት ነበር። እኛም ፈተና ሲደርስብን ሁልጊዜ በደስታ እንፈነድቃለን ብለን ካሰብን የማይቻለውን ነገር መጠበቅ ይሆንብናል። (ከዕብራውያን 12:​11 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ ሽልማታችንን አሻግረን በመመልከት የሚያጋጥመንን በጣም አስቸጋሪ የሆነ ሁኔታ እንኳን ‘እንደ ሙሉ ደስታ’ ልንቆጥር እንችላለን። (ያዕቆብ 1:​2–4፤ ሥራ 5:​41) ዋናው ነገር እያነባንም ቢሆን ጸንተን መቆየታችን ነው። ኢየሱስ ያለው ‘ከሁሉ ያነሰ እንባ ያፈሰሰ ይድናል’ ሳይሆን “እስከ መጨረሻው የሚጸና . . . እርሱ ይድናል” ነው። — ማቴዎስ 24:⁠13

      21. (ሀ) በ2 ጴጥሮስ 1:​5, 6 ላይ በጽናታችን ላይ ምን እንድንጨምር በጥብቅ ተመክረናል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ምን ጥያቄዎች ይመረመራሉ?

      21 እንግዲያው ለመዳን መጽናት እጅግ ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ በ2 ጴጥሮስ 1:​5, 6 ላይ በጽናታችን ላይ ለአምላክ ያደሩ መሆንን እንድንጨምር በጥብቅ ተመክረናል። ለአምላክ ያደሩ መሆን ምን ማለት ነው? ከጽናት ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው? ለአምላክ ያደሩ የመሆንን ባሕርይ ልታገኝ የምትችለውስ እንዴት ነው? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ይመረመራሉ።

      [የግርጌ ማስታወሻ]

      a ኢየሱስ ፍጹም አካሉ በእንጨት ላይ ከተሰቀለ ብዙም ሳይቆይ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ መሞቱ ችሎ የጸናው መከራ የቱን ያህል ከባድ እንደነበረ ያሳያል። ከጎኑ የተሰቀሉትን ክፉ አድራጊዎች ሞት ለማፋጠን ግን እግራቸውን መስበር አስፈልጎ ነበር። (ዮሐንስ 19:​31–33) ኢየሱስ ከመሰቀሉ በፊት እንቅልፍ ባይኑ ሳይዞር ባሳለፈው ሌሊት የደረሰበትን ዓይነት አእምሮአዊና አካላዊ ሥቃይ በእነርሱ ላይ አልደረሰም። የደረሰበት ሥቃይ በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ የሚሰቀልበትን የመከራ እንጨት እንኳን መሸከም እስከሚያቅተው ድረስ አድክሞት የነበረ ይመስላል። — ማርቆስ 15:​15, 21

  • በጽናት ላይ ለአምላክ ያደሩ መሆንን ጨምሩ
    መጠበቂያ ግንብ—1993 | መስከረም 15
    • በጽናት ላይ ለአምላክ ያደሩ መሆንን ጨምሩ

      “በእምነታችሁ [ላይ] . . . መጽናትን፣ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል [ለአምላክ ያደሩ መሆንን አዓት] . . . ጨምሩ። ” — 2 ጴጥሮስ 1:​5, 6

      1, 2. (ሀ) ከ1930ዎቹ ዓመታት ጀምሮ በናዚ ቁጥጥር ሥር ባሉ አገሮች በሚኖሩ የይሖዋ ምስክሮች ላይ ምን ደረሰ? ለምንስ? (ለ) ያደረሱባቸው ይህ ሁሉ ሥቃይ በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ምን ውጤት አመጣ?

      ጊዜው በ20ኛው መቶ ዘመን ታሪክ ውስጥ ከነበሩት ጊዜያት ሁሉ የከፋ ጊዜ ነበር። ከ1930ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ አንስቶ በናዚ ቁጥጥር ሥር በነበሩ አገሮች ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ይታሰሩና ወደ እስረኞች ማጎሪያ ካምፖች ይጣሉ ነበር። ለምን? በቆራጥነት ገለልተኛ በመሆናቸውና ‘አዳኛችን ሂትለር ነው’ የሚል መፈክር ለማሰማት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ነበር። በእስር ቤት ውስጥስ ምን ደረሰባቸው? “የኤስ ኤስ ወታደሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን [የይሖዋ ምስክሮችን] ያህል . . . በጭካኔ ያሰቃዩት ሌላ የእስረኞች ቡድን አልነበረም። በዓለም ላይ ያለ የትኛውም ቋንቋ ሊገልጸው የማይችል የማያቋርጥ የአካልና የአእምሮ ሥቃይ ያደርሱባቸው ነበር።” — የቀድሞ የጀርመን መንግሥት ባለ ሥልጣን የነበሩት ካርል ዊቲግ።

      2 ታዲያ የይሖዋ ምስክሮች አቋም ምን ነበር? ዘ ናዚ ስቴት ኤንድ ዘ ኒው ሪሊጅንስ:- ፋይቭ ኬዝ ስተዲስ ኢን ነን ኮንፈርሚቲ በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ ዶክተር ክርቲን ኢ ኪንግ እንዲህ ብለዋል:- “[ከሌሎቹ የሃይማኖት ቡድኖች ጋር ሲነፃፀር] የመንግሥት ጥረት ያልተሳካው በምስክሮቹ ላይ ብቻ ነበር።” አዎን፤ ምንም እንኳን የደረሰባቸው መከራ በመቶ ለሚቆጠሩት እስከ ሞት ድረስ መጽናትን የጠየቀባቸው ቢሆንም በቡድን ደረጃ ስንመለከታቸው የይሖዋ ምስክሮች ከአቋማቸው ፍንክች ሳይሉ ቆመ⁠ዋል።

      3. የይሖዋ ምስክሮች ከባድ መከራዎችን ችለው እንዲጸኑ ያስቻላቸው ምንድን ነው?

      3 የይሖዋ ምስክሮች በናዚ ጀርመን ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሌሎች አገሮችም ጭምር እንዲህ ያሉ ፈተናዎችን በጽናት እንዲቋቋሙ ያስቻላቸው ምንድን ነው? ለአምላክ ያደሩ በመሆናቸው ምክንያት የሰማዩ አባታቸው እንዲጸኑ ረድቷቸዋል። ‘ይሖዋ ለእርሱ ያደሩትን ሰዎች ከፈተና እንዴት እንደሚያድን ያውቃል’ ሲል ሐዋርያው ጴጥሮስ ገልጿል። (2 ጴጥሮስ 2:​9 አዓት) በዚያው ደብዳቤ ላይ ከፍ ብሎ ክርስቲያኖችን “በእምነታችሁ [ላይ] . . . መጽናትን፣ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል [ለአምላክ ያደሩ መሆንን አዓት] . . . ጨምሩ” በማለት መክሯቸዋል። (2 ጴጥሮስ 1:​5, 6) ስለዚህ ጽናት ለአምላክ ያደሩ ከመሆን ጋር በጣም የተያያዘ ነው። እንዲያውም እስከ መጨረሻው ለመጽናት ‘ለአምላክ ማደርን መከታተል’ እንዲሁም ማሳየት ይኖርብናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:​11 አዓት) ግን ለአምላክ ያደሩ መሆን ምንድን ነው?

      ለአምላክ ያደሩ መሆን ምንድን ነው?

      4, 5. ለአምላክ ያደሩ መሆን ምን ማለት ነው?

      4 “ለአምላክ ያደሩ መሆን” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ስም (ዩሴብያ) “ተገቢ የሆነ ከፍተኛ አክብሮት” ተብሎ ቃል በቃል ሊተረጎም ይችላል።a (2 ጴጥሮስ 1:​6 ኪንግደም ኢንተርሊንየር) ቃሉ ለአምላክ የምናሳየውን ሞቅ ያለና ከልብ የመነጨ ስሜት ያንጸባርቃል። በደብልዩ ኢ ቫይን አባባል ቃል በቃል ሲተረጎም “ተገቢና አክብሮታዊ” የሚል ፍቺ ያለው ዩሴበስ የተባለው ቅጽል “አምላክን በቅድስና በማክበር የሚመራውንና በሙሉ ልብ በሚደረግ እንቅስቃሴ የሚገለጸውን ኃይል ያመለክታል።” — 2 ጴጥሮስ 2:​ 9

      5 ስለዚህ “ለአምላክ ያደሩ መሆን” የሚለው ቃል ይሖዋን የሚያስደስተውን ነገር እንድናደርግ የሚያነሳሳን ከፍተኛ አክብሮት ወይም ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ያመለክታል። አምላክን ከልባችን ስለምንወደው ይህን የምናደርገው ከባድ መከራዎች በሚደርሱብን ጊዜም ጭምር ነው። በአኗኗራችን የሚገለጽ ይሖዋን የሙጥኝ የማለትና በታማኝነት ከይሖዋ ጎን የመቆም ባሕርይ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘ለአምላክ በማደር . . . ጸጥና ዝግ ብለው’ ለመኖር ይችሉ ዘንድ እንዲጸልዩ በጥብቅ ተመክረዋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:​1, 2) የመዝገበ ቃላት አዘጋጅ በሆኑት ጄ ፒ ሎ እና ኢ ኤ ኒዳ እንደገለጹት “በ1 ጢ⁠ሞ 2.​2 ላይ የተጠቀሰው [ዩሴብያ] በብዙ ቋንቋዎች ‘አምላክ የሚፈልገውን ዓይነት ኑሮ መኖር’ ወይም ‘አምላክ በነገረን መንገድ መኖር’ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል።”

      6. በጽናትና ለአምላክ ያደሩ በመሆን መካከል ምን ዝምድና አለ?

      6 አሁን በመጽናትና ለአምላክ ያደሩ በመሆን መካከል ያለውን ግንኙነት በተሻለ ሁኔታ ለመገንዘብ እንችላለን። አምላክ በሚፈልገው መንገድ ማለትም ለአምላክ ያደርን ሆነን ስለምንኖር ዓለም ይጠላናል። ይህ ደግሞ የእምነት ፈተና ማስከተሉ አይቀርም። (2 ጢሞቴዎስ 3:​12) ከሰማያዊ አባታችን ጋር ኃይለኛ ቅርርብ ባይኖረን ኖሮ እነዚህን የመሳሰሉትን ፈተናዎች በጽናት እንድንቋቋማቸው አንገፋፋም ነበር። ከዚህም በላይ ይሖዋ እንዲህ ያለውን ለአምላክ የማደር ባሕርይ ዝም ብሎ አይመለከትም። ለይሖዋ በማደራቸው ምክንያት ምንም ዓይነት ተቃውሞ ቢመጣባቸው እርሱን ለማስደሰት ጥረት የሚያደርጉትን ሰዎች ሰማይ ሆኖ ሲመለከት ምን እንደሚሰማው አስብ። ‘ለአምላክ ያደሩትን ሰዎች ከፈተና ለማዳን’ እንደሚፈልግ አያጠራጥርም!

      7. ለአምላክ የማደርን ባሕርይ መኮትኮት ያለብን ለምንድን ነው?

      7 ይሁን እንጂ ለአምላክ ያደርን ሆነን አልተወለድንም፤ ወይም ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ፈሪሃ አምላክ ካላቸው ወላጆች ልንወርስ አንችልም። (ዘፍጥረት 8:​21) ከዚህ ይልቅ መኮትኮትና ማደግ ያለበት ባሕሪይ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 4:​7, 10) በጽናታችንና በእምነታችን ላይ ለአምላክ ያደሩ መሆንን ለመጨመር መጣር አለብን። ጴጥሮስ ይህን ማድረግ “ትጋት” እንደሚጠይቅ ተናግሯል። (2 ጴጥሮስ 1:​5) ታዲያ ለአምላክ ያደሩ የመሆንን ባሕርይ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

      ለአምላክ ያደሩ የመሆንን ባሕርይ እንዴት ልናገኝ እንችላለን?

      8. ሐዋርያው ጴጥሮስ በተናገረው መሠረት ለአምላክ ያደሩ የመሆንን ባሕርይ ለማግኘት ቁልፉ ምንድን ነው?

      8 ሐዋርያው ጴጥሮስ ለአምላክ ያደሩ የመሆንን ባሕርይ ልናገኝ የምንችልበትን ቁልፍ ተናግሯል። እንዲህ አለ:- “የመለኮቱ ኃይል፣ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፣ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል [ለአምላክ ያደሩ ለመሆን አዓት] የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፣ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።” (2 ጴጥሮስ 1:​2, 3) ስለዚህ በእምነታችንና በጽናታችን ላይ ለአምላክ ያደሩ የመሆንን ባሕርይ ለመጨመር ትክክለኛ እውቀት ማለትም ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሟላ እውቀት ማግኘትና ማሳደግ ይገባናል።

      9. ስለ አምላክና ስለ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት መያዝ ማንነታቸውን ከማወቅ የበለጠ ነገርን እንደሚያጠቃልል በምሳሌ ማሳየት የሚቻለው እንዴት ነው?

      9 ስለ አምላክና ስለ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ማለት ምን ማለት ነው? ማንነታቸውን ከማወቅ የበለጠ ነገር እንደሚያጠቃልል ግልጽ ነው። በምሳሌ ለማስረዳት:- ጎረቤትህ ማን እንደሆነ ታውቃለህ፤ እንዲያውም ስሙን እየጠራህ ሰላም ትለው ይሆናል። ይሁን እንጂ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ታበድረዋለህን? ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ በደንብ ካላወቅህ በስተቀር አታበድረውም። (ከምሳሌ 11:​15 ጋር አወዳድር።) በተመሳሳይም ይሖዋንና ኢየሱስን በትክክል ወይም ሙሉ በሙሉ ማወቅ ሕልውናቸውን ከማመንና ስማቸውን ከማወቅ የበለጠ ነገርን ይጨምራል። ለእነርሱ ብለን እስከ ሞት ድረስ ለመጽናት ከፈለግን ከእነርሱ ጋር የቅርብ ትውውቅ ሊኖረን ይገባል። (ዮሐንስ 17:​3) ይህ ምንን ይጨምራል?

      10. ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ትክክለኛ እውቀት መያዝ ምን ሁለት ነገሮችን ያጠቃልላል? ለምንስ?

      10 ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ትክክለኛ ወይም የተሟላ እውቀት ማግኘት ሁለት ነገሮችን ያጠቃልላል። እነርሱም:- (1) የይሖዋንና የኢየሱስን ስብዕና ማለትም ባሕርያቸውን፣ ስሜታቸውንና መንገዳቸውን ማወቅና (2) እነርሱን መምሰል ናቸው። ለአምላክ ያደሩ መሆን ይሖዋን በግል ከልባችን መውደድንና ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረትን ይጨምራል። ይህ ደግሞ የሚገለጸው በአኗኗራችን ነው። እንግዲያው ይህንን ባሕርይ ለማግኘት የሰው አቅም እስከሚችለው ድረስ ይሖዋን በግል ማወቅና ከፈቃዱና ከመንገዶቹ ጋር በደንብ መተዋወቅ አለብን። በእውነትም በአምሳሉ የፈጠረንን ይሖዋን ለማወቅ እንደዚህ ባለው እውቀት መጠቀምና እርሱን ለመምሰል መጣር አለብን። (ዘፍጥረት 1:​26–28፤ ቆላስይስ 3:​10) ኢየሱስ በተናገራቸውና ባደረጋቸው ነገሮች ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ስለመሰለው ኢየሱስን ማወቃችን ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ለማዳበር ጠቃሚ እገዛ ያደርግልናል። — ዕብራውያን 1:​3

      11. (ሀ) ስለ አምላክና ስለ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      11 ታዲያ ስለ አምላክና ስለ ክርስቶስ እንዲህ ያለውን እውቀት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በማጥናት ነው።b ይሁን እንጂ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ለአምላክ የማደር ባሕርይ የሚያስገኝልን ጊዜ ወስደን ያነበብነውን ነገር ስናሰላስል ማለትም በነገሩ ላይ ስናስብበት ወይም ስናወጣና ስናወርደው ነው። (ከኢያሱ 1:​8 ጋር አወዳድር።) እንዲህ ማድረግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ለአምላክ ያደሩ መሆን ለአምላክ ሞቅ ያለና ከልብ የመነጨ ስሜት ማሳደር ማለት መሆኑን አስታውስ። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ማሰላሰል ከምሳሌያዊው ልብ ማለትም ከውስጣዊው ሰውነት ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ተገልጿል። (መዝሙር 19:​14፤ 49:​3፤ ምሳሌ 15:​28) ያነበብነውን ነገር በአድናቆት ብናሰላስለው ውስጣዊ ሰውነታችን ውስጥ ጠልቆ ስለሚገባ አስተሳሰባችንን በመቆጣጠር ስሜታችንን ይቀሰቅሰዋል። ጥናታችን ከይሖዋ ጋር ያለንን የግል ግንኙነት ሊያጠናክርልን የሚችለውና ፈታኝ ሁኔታዎች ወይም ከባድ መከራዎች ቢደርሱብንም እንኳን አምላክን በሚያስደስት መንገድ እንድንኖር የምንገፋፋው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው።

      በቤት ውስጥ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ማሳየት

      12. (ሀ) ጳውሎስ በተናገረው መሠረት አንድ ክርስቲያን ለአምላክ ያደረ መሆኑን በቤት ውስጥ ለማሳየት የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) እውነተኛ ክርስቲያኖች ያረጁ ወላጆቻቸውን መጦር ያለባቸው ለምንድን ነው?

      12 ለአምላክ ያደሩ የመሆን ባሕርይ በመጀመሪያ ደረጃ መታየት የሚኖርበት በቤት ውስጥ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ማንም ባልቴት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት፣ እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤተ ሰዎቻቸው እግዚአብሔርን መምሰል [ለአምላክ የማደርን ባሕርይ አዓት] ያሳዩ ዘንድ፣ ለወላጆቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ ነውና።” (1 ጢሞቴዎስ 5:​4) ጳውሎስ እንዳስገነዘበው ያረጁ ወላጆችን መጦር ለአምላክ ያደርን ሰዎች መሆናችን ከሚገለጥባቸው መንገዶች አንዱ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች ወላጆቻቸውን የሚጦሩት ግዴታቸው እንደሆነ ስለሚሰማቸው ብቻ ሳይሆን ለወላጆቻቸው ባላቸው ፍቅር የተነሳ ነው። ከዚህም በላይ ይሖዋ ቤተሰብን መንከባከብን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ነገር አድርጎ እንደሚመለከተው ያውቃሉ። ወላጆች እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ጀርባቸውን መስጠት ‘ሃይማኖትን ከመካድ’ ጋር እንደሚመጣጠን በሚገባ ይገነዘባሉ። — 1 ጢሞቴዎስ 5:⁠8

      13. በቤት ውስጥ ለአምላክ ያደሩ የመሆንን ባሕርይ ማሳየት የሚያስቸግረው በምን ምክንያት ሊሆን ይችላል? ይሁን እንጂ ወላጆችን በመጦር ምን እርካታ ይገኛል?

      13 በቤት ውስጥ ለአምላክ ያደሩ የመሆንን ባሕርይ ማሳየት ሁልጊዜ ቀላል እንደማይሆን እሙን ነው። የቤተሰቡ አባሎች የሚኖሩት በጣም በተራራቁ ቦታዎች ሊሆን ይችላል። ራሳቸውን የቻሉት ልጆች የሚንከባከቡት የራሳቸው ቤተሰብ ሊኖራቸው ወይም የኢኮኖሚ ችግር ሊኖርባቸው ይችላል። ወላጆች የሚፈልጉት የእንክብካቤ ዓይነት ወይም መጠኑ የተንከባካቢውን የአካል፣ የአእምሮና የስሜት ጤንነት የሚያደክም ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ ግን አንድ ሰው ወላጆቹን በመጦሩ ‘ብድሩን ከመመለሱም’ በላይ ‘በሰማይና በምድር ያለ ቤተሰብ ሁሉ የሚሰየምበትን’ አምላክ ያስደስታል። — ኤፌሶን 3:​14, 15 አዓት

      14, 15. ልጆች ለወላጃቸው ያደረጉትን አምላካዊ ባሕርይ የሚታይበት እንክብካቤ የሚገልጽ ምሳሌ ተናገር።

      14 ቀጥሎ ያለውን ልብ የሚነካ ምሳሌ ተመልከት። ኤለስና አምስት ወንድሞቹና እህቶቹ አባታቸውን በቤት የማስታመም ከባድ ሥራ አለባቸው። “በ1986 አባቴ በደም ግፊት መብዛት ምክንያት ደሙ አንጎሉ ውስጥ በመፍሰሱ ሙሉ በሙሉ ሽባ ሆነ” ይላል ኤለስ። ስድስቱም ልጆች አባታቸውን በማስታመሙ ሥራ ይካፈላሉ። ይህም ገላውን ከማጠብ አንስቶ የአልጋ ቁራኛ በመሆኑ ምክንያት ጎኑ እንዳይቆስል በየጊዜው ማገላበጥን ይጨምራል። “እናነብለታለን፣ እናወራለታለን ሙዚቃም እንጫወትለታለን። በአካባቢው እየተደረገ ያለውን ነገር ይወቅ አይወቅ እርግጠኞች አይደለንም፤ ቢሆንም ልክ ሁሉን ነገር እንደሚያውቅ አድርገን እንይዘዋለን።”

      15 ልጆቹ አባታቸውን ይህን ያህል የሚንከባከቡት ለምንድን ነው? ኤለስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “በ1964 እናታችን ከሞተች በኋላ አባባ ያሳደገን ብቻውን ሆኖ ነበር። በጊዜው ዕድሜያችን ከ5 እስከ 14 ይደርስ ነበር። በዚያን ጊዜ የደረሰልን እርሱ ነበር፤ አሁን ደግሞ እኛ ደረስንለት።” እንዲህ ዓይነት እንክብካቤ ማድረግ ቀላል እንዳልሆነና ልጆቹም አንዳንድ ጊዜ ተስፋ እንደሚቆርጡ ግልጽ ነው። “ነገር ግን አባታችን በዚህ ሁኔታ የሚቆየው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ እንደሆነ እናውቃለን” ይላል ኤለስ። “አባታችን ጤናው የሚመለስለትንና ከእናታችን ጋር እንደገና የምንገናኝበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን።” (ኢሳይያስ 33:​24፤ ዮሐንስ 5:​28, 29) ለወላጆች በሙሉ ልብ የሚደረግ እንዲህ ያለ እንክብካቤ ልጆች ወላጆቻቸውን እንዲያከብሩ ያዘዘውን አምላክ ልብ ደስ እንደሚያሰኝ የተረጋገጠ ነው!c — ኤፌሶን 6:⁠1, 2

      ለአምላክ ያደሩ መሆንና አገልግሎት

      16. የምናገለግልበት ዋነኛው ምክንያት ምን መሆን ይኖርበ⁠ታል?

      16 ኢየሱስ ‘ያለማቋረጥ እንድንከተለው’ ያቀረበልንን ግብዣ ስንቀበል የመንግሥቱን ምሥራች እንድንሰብክና ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ በሚያዝዝ መለኮታዊ ግዴታ ሥር ገብተናል ማለት ነው። (ማቴዎስ 16:​24 አዓት፤ 24:​14፤ 28:​19, 20) በዚህ ‘የመጨረሻ ቀን’ በአገልግሎት መካፈል ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) ይሁን እንጂ ለመስበክና ለማስተማር የምንነሳሳው ግዴታችን ስለሆነ ብቻ መሆን የለበትም። በአገልግሎቱ እንድንሳተፍና በዚያ መጠን ያህል እንድናገለግል የሚገፋፋን ዋነኛው ምክንያት ለይሖዋ ያለን ጥልቅ ፍቅር መሆን አለበት። ኢየሱስ “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና” ብሏል። (ማቴዎስ 12:​34) አዎን፤ ልባችን ለይሖዋ ባለን ፍቅር የተትረፈረፈ ከሆነ ስለ እርሱ ለሌሎች ለመመስከር እንገፋፋለን። የሚገፋፋን ኃይል ለአምላክ ያለን ፍቅር ከሆነ አገልግሎታችን ለአምላክ ያደርን መሆናችን የሚገለጥበት ጥሩ መንገድ ይሆናል።

      17. ለአገልግሎት የሚገፋፋንን ትክክለኛ ኃይል ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

      17 ለአገልግሎት የሚገፋፋንን ትክክለኛ ዓላማ ልናዳብር የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ እርሱን እንድንወድደው የሰጠንን ሦስት ምክንያቶች በአድናቆት በማሰላሰል ነው። (1) እስካሁን ባደረገልን ነገሮች የተነሳ ይሖዋን እንወድደዋለን። ቤዛውን በመስጠት ካሳየን ፍቅር የሚበልጥ ፍቅር ሊያሳየን አይችልም። (ማቴዎስ 20:​28፤ ዮሐንስ 15:​13) (2) በአሁኑ ጊዜ እያደረገልን ባሉት ነገሮች የተነሳ ይሖዋን እንወድደዋለን። ከይሖዋ ጋር በነፃነት ልንነጋገር እንችላለን። እርሱም ጸሎታችንን ይመልስልናል። (መዝሙር 65:​2፤ ዕብራውያን 4:​14–16) ለመንግሥቱ ጥቅሞች ቅድሚያ በሰጠን መጠን ለሕይወት የሚያስፈልጉንን ነገሮች እናገኛለን። (ማቴዎስ 6:​25–33) የሚያጋጥሙንን ችግሮች እንድንቋቋም የሚረዳ የማያቋርጥ መንፈሳዊ ምግብ ይቀርብልናል። (ማቴዎስ 24:​45) ከቀረው ዓለም ሙሉ በሙሉ የሚለየን የዓለም አቀፉ ክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበር አባላት በመሆናችን ተባርከናል። (1 ጴጥሮስ 2:​17) (3) ገና ወደፊት በሚያደርግልን ነገሮች ምክንያትም ይሖዋን እንወድደዋለን። ከፍቅሩ የተነሳ ‘እውነተኛውን ሕይወት አጥብቀን ይዘናል፤’ እርሱም ወደፊት የምናገኘው የዘላለም ሕይወት ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:​12, 19) ይሖዋ ያሳየንን ፍቅር ስንመለከት ስለ እርሱና ስለ ክቡር ዓላማው ለሌሎች በመንገሩ ሥራ ሙሉ በሙሉ ለመካፈል ልባችን እንደሚገፋፋ አያጠራጥርም! ማድረግ ስላለብን ነገር ወይም በአገልግሎቱ ምን ያህል መሥራት እንዳለብን ሌሎች እንዲነግሩን አያስፈልግም። የምንችለውን ያህል እንድናደርግ ልባችን ይገፋፋናል።

      18, 19. አንዲት እህት በአገልግሎት ለመካፈል ስትል የተወጣችው ዕንቅፋት ምን ነበር?

      18 ለአምላክ በማደር ባሕርይ የተገፋፋ ልብ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙት እንኳን ለመናገር ይገፋፋል። (ከኤርምያስ 20:​9 ጋር አወዳድር።) ይህም ስቴላ በተባለች እጅግ ዓይናፋር በሆነች ክርስቲያን እህት ተሞክሮ ታይቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ገና እንደጀመረች ‘ከቤት ወደ ቤት መሄድ በጭራሽ አልችልም!’ ስትል አሰበች። “ሁልጊዜ ዝምተኛ ነበርኩ። ሰዎችን ቀርቤ አነጋግሬ ውይይት መጀመር ፈጽሞ አይሆንልኝም” ትላለች። ጥናቷን እየቀጠለች ስትሄድ ለይሖዋ ያላት ፍቅር እየጨመረ በመምጣቱ ስለ እርሱ ለሌሎች ለመናገር ከፍተኛ ፍላጎት አደረባት። “የመጽሐፍ ቅዱስ አስጠኚዬን ‘ለመናገር በጣም እፈልጋለሁ፤ ግን መናገር አልችልም፤ አለመቻሌ ደግሞ ያናድደኛል’ ብዬ እንደነገርኳት አስታውሳለሁ። እሷም ‘ስቴላ፣ ለመናገር ፍላጎቱ ስላለሽ አመስጋኝ ሁኚ’ ብላ የነገረችን እስከመቼም አልረሳውም።”

      19 ብዙም ሳትቆይ ስቴላ ለጎረቤቷ መመስከር ጀመረች። ከዚያም ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት በመካፈል ትልቅ እርምጃ ወሰደች። (ሥራ 20:​20, 21) እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “የምናገረውን መልእክት ጽፌው ነበር፤ ግን በጣም ፈርቼና ተደናግጬ ስለነበር ማስታወሻዬ ከፊት ለፊቴ እያለ እንኳን ጎንበስ ብዬ ማንበብ አልቻልኩም!” አሁን ይህ ከሆነ 35 ዓመት ያለፈው ቢሆንም አሁንም ስቴላ በተፈጥሮዋ በጣም ዓይን አፋር ነች። ሆኖም የመስክ አገልግሎቱን ትወድደዋለች፤ እንዲሁም በመስክ አገልግሎት በሚገባ ትካፈላለች።

      20. ስደትም ሆነ እስራት ለይሖዋ ያደሩ ምስክሮችን አፍ ሊዘጋ እንደማይችል ምን ምሳሌ ያሳያል?

      20 ስደትም ሆነ እስራት ለይሖዋ ያደሩ ምስክሮችን አፍ ሊዘጋ አይችልም። የጀርመናዊዎቹን የኧርንስትንና የሂልዴጋርት ዛሊገርን ምሳሌ ተመልከት። በእምነታቸው ምክንያት ሁለቱም በናዚ የእስረኞች ማጎሪያ ካምፖችና በኮሚዩኒስት እስር ቤቶች ውስጥ በድምሩ ከ40 ዓመታት በላይ አሳልፈዋል። በእስር ቤት ውስጥ እያሉም እንኳን ለሌሎች እስረኞች መመስከራቸውን አላቋረጡም። ሂልዴጋርት የሆነውን ነገር በማስታወስ እንዲህ ብላ ነበር:- “የእስር ቤቱ ባለ ሥልጣኖች እኔን በጣም አደገኛ እንደሆንኩ አድርገው ይመለከቱኝ ነበር። ምክንያቱም አንዲት ሴት ጠባቂ እንደተናገረችው ቀኑን ሙሉ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ስናገር እውላለሁ። በዚህም ምክንያት በእስር ቤቱ ምድር ቤት የሚገኝ ክፍል ውስጥ ታሰርኩ።” በመጨረሻ ከእስር ቤት ከተለቀቁ በኋላ ወንድምና እህት ዛሊገር ሙሉ ጊዜያቸውን ለክርስቲያናዊው አገልግሎት አዋሉት። ወንድም ዛሊገር በ1985 ሚስቱ ደግሞ በ1992 እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ ሁለቱም በታማኝነት አገልግለዋል።

      21. በጽናታችን ላይ ለአምላክ ማደርን ለመጨመር ምን ማድረግ አለብን?

      21 የአምላክን ቃል በትጋት በማጥናትና የተማርነውን ነገር ጊዜ ወስደን በአድናቆት በማሰላሰል ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ባለን እውቀት እያደግን እንሄዳለን። ይህም ውድ የሆነውን ለአምላክ የማደር ባሕርይ ሙሉ በሙሉ እንድናገኝ ያስችለናል። ለአምላክ የማደር ባሕርይ ካልኖረን ክርስቲያኖች በመሆናችን ምክንያት የሚመጡብንን መከራዎች በጽናት የምንቋቋምበት ምንም መንገድ አይኖርም። ስለዚህ የሐዋርያው ጴጥሮስን ምክር ተከትለን ‘በእምነታችን ላይ መጽናትን በመጽናትም ለአምላክ ያደሩ መሆንን መጨመራችንን’ እንቀጥል። — 2 ጴጥሮስ 1:​5, 6 አዓት

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ