አምላክ የሰጠውን ተስፋ በመፈጸም ረገድ አይዘገይም
“አቤቱ፣ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው?” እነዚህን ቃላት የተናገረው በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይኖር የነበረው ዕብራዊው ነቢይ ዕንባቆም ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ቃላት አንድ የተለመደ ሐሳብ ያስተላልፋሉ፣ አይደለም እንዴ? ሰዎች ስንባል በጣም የምንናፍቀውን ነገር ወዲያውኑ ወይም በቶሎ ማግኘት እንፈልጋለን። በተለይ ቅጽበታዊ ደስታ ለማግኘት የሚጥሩ ሰዎች በበዙበት በዚህ በእኛ ዘመን ይህ ነገር እውነት ነው።—ዕንባቆም 1:2
በመጀመሪያው መቶ ዘመን አምላክ የሰጠውን ተስፋ ቶሎ መፈጸም ነበረበት የሚል አስተሳሰብ የነበራቸው አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። ትዕግሥታቸው ከመሟጠጡ የተነሣ አምላክ ዳተኛ ነው ወይም ይዘገያል እስከ ማለት ደርሰው ነበር። በዚህ ምክንያት ሐዋርያው ጴጥሮስ አምላክ ስለ ጊዜ ያለው አመለካከት እኛ ካለን አመለካከት የተለየ መሆኑን ማሳሰብ አስፈልጎት ነበር። ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ወዳጆች ሆይ፣ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፣ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ።”—2 ጴጥሮስ 3:8
በዚህ የጊዜ አቆጣጠር መሠረት አንድ የ80 ዓመት ሰው የኖረው ወደ ሁለት ሰዓት ገደማ ብቻ ሲሆን ጠቅላላው የሰው ልጅ ታሪክ የፈጀው ጊዜ ደግሞ ስድስት ቀናት እንኳን አይሞላም። ነገሩን ከዚህ አንፃር ስንመለከተው አምላክ ከእኛ ጋር ግንኙነት የሚያደርግበትን መንገድ ለመረዳት ቀላል ይሆንልናል።
ይሁን እንጂ አምላክ ስለ ጊዜ ግድ የለሽ አይደለም። እንዲያውም ጊዜን በተመለከተ በጣም ጥንቁቅ ነው። (ሥራ 1:7) በመሆኑም ጴጥሮስ ቀጥሎ እንዲህ ብሏል:- “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።” (2 ጴጥሮስ 3:9) ከሰዎች በተለየ መልኩ አምላክ ጊዜው የተሟጠጠበት ይመስል ነገሮችን በጥድፊያ ስሜት ማከናወን እንዳለበት ሆኖ አይሰማውም። ‘ዘላለማዊ ንጉሥ’ እንደ መሆኑ መጠን ነገሮችን ከሁሉም አቅጣጫ የመመልከት ግሩም የሆነ ችሎታ ስላለው በጊዜ ሂደት ውስጥ ሁሉንም በሚጠቅም ወቅት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ሊወስን ይችላል።—1 ጢሞቴዎስ 1:17
አምላክ የዘገየ የሚመስልበትን ምክንያት ካብራራ በኋላ ጴጥሮስ እንደሚከተለው ሲል አስጠንቅቋል:- “የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል።” ይህም የፍርድ ቀን የሚመጣው ሰዎች ይመጣል ብለው በማይጠብቁበት ጊዜ ይሆናል ማለት ነው። ከዚያም በሚቀጥሉት ጥቅሶች ላይ ጴጥሮስ “በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል” የሚመላለሱ ሰዎች አስደናቂ ነገር እንደሚጠብቃቸው ይኸውም በሕይወት ተርፈው አምላክ ተስፋ ወደሰጠባቸው ‘አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር’ እንደሚገቡ አመልክቷል።—2 ጴጥሮስ 3:10-13
ይህ ደግሞ አምላክ ፍርድ የሚሰጥበት ጊዜ መዘግየቱ ያለውን ጥቅም ይበልጥ እንድናደንቅ ሊያደርገን ይገባል። እስከ አሁን ድረስ መታገሡ ዓላማውን እንድናውቅና ቃል የገባቸውን በረከቶች ለማግኘት ሕይወታችንን እንድናስተካክል አስችሎናል። ጴጥሮስ እንደገለጸው ‘የጌታችንን ትዕግሥት መዳናችን እንደ ሆነ ልንቆጥር’ አይገባም? (2 ጴጥሮስ 3:15) ይሁን እንጂ በአምላክ ትዕግሥት ውስጥ የሚካተት ሌላም ጉዳይ አለ።
መሙላት ያለበት የኃጢአት ጽዋ
አምላክ በጥንት ጊዜ ከሰው ዘር ጋር የነበረውን ግንኙነት ስንመረምር አብዛኛውን ጊዜ ሰዎቹ ከእንግዲህ ወዲያ ምንም መሻሻል አያደርጉም የሚል መደምደሚያ ላይ እስከሚደርስ ድረስ ፍርዱን ያዘገይ እንደነበር እንመለከታለን። ለምሳሌ ያህል አምላክ በከነዓናውያን ላይ የቅጣት እርምጃ ከመውሰዱ ከረጅም ጊዜ በፊት ስለሠሩት ኃጢአት ለአብርሃም ነግሮት ነበር። ሆኖም ፍርዱን የሚያስፈጽምበት ጊዜ አልደረሰም ነበር። ለምን? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “የአሞራውያን [የከነዓናውያን] ኃጢአት ገና አልተፈጸመምና” ወይም የኖክስ ትርጉም እንደሚለው “የአሞራውያን ክፋት ጽዋ ገና አልሞላም ነበር።”—ዘፍጥረት 15:16a
ይሁን እንጂ ከ400 ዓመታት በኋላ የአምላክ ፍርድ መጣ፤ የአብርሃም ዘሮች የሆኑት እስራኤላውያንም ምድሪቱን ወረሱ። ረዓብንና ገባዖናውያንን የመሳሰሉ ጥቂት ከነዓናውያን በነበራቸው ዝንባሌና በወሰዱት እርምጃ ምክንያት የዳኑ ቢሆንም በዘመናዊ አርኪኦሎጂያዊ ቁፋሮዎች የተገኙ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት አብዛኛው ሕዝብ የረከሰ ተግባር በመፈጸም እጅግ ርቆ ሄዶ ነበር። የወንድ የፆታ ብልት አምልኮ ያካሂዱና በቤተ መቅደስ ውስጥ ግልሙትና ይፈጽሙ የነበረ ሲሆን ልጆቻቸውንም ይሠዉ ነበር። ሃሌይስ ባይብል ሃንድቡክ እንዲህ ይላል:- “የከነዓናውያንን ከተሞች ፍርስራሽ ቆፍረው ጥናት ያደረጉ አርኪኦሎጂስቶች አምላክ ለምን ከዚያ ቀደም ብሎ እንዳላጠፋቸው በጣም ይገርማቸዋል።” በመጨረሻ የከነዓናውያን ‘ኃጢአት ተፈጸመ፤’ የክፋታቸው ‘ጽዋ ሞላ።’ ስለሆነም አምላክ ጥሩ አቋም የነበራቸውን ሰዎች አድኖ ምድሪቱን ከክፋት ማጽዳቱ ፍትሕ የጎደለው እርምጃ ነው ብሎ አምላክን የሚከስ ሊኖር አይችልም።
በኖኅ ዘመንም ሁኔታው ተመሳሳይ ነበር። የጥፋት ውኃ ከመምጣቱ በፊት የነበሩት ሰዎች ክፉዎች መሆናቸው ግልጽ ቢሆንም እንኳ የሚኖሩበትን ዘመን በ120 ዓመት በማራዘም ምሕረቱን አሳይቷል። ከዚህ ጊዜ ውስጥ ከፊሉን ኖኅ የጽድቅ ሰባኪ ሆኖ አገልግሏል። (2 ጴጥሮስ 2:5) ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ክፋታቸውም የዚያኑ ያህል እየጨመረ ሄደ። “እግዚአብሔርም ምድርን አየ፣ እነሆም ተበላሸች፤ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ ነበርና።” (ዘፍጥረት 6:3, 12) የኃጢአታቸው ጽዋ ሞልቶ ነበር፤ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ደግሞ መጥፎ ዝንባሌያቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጓል። አምላክ እርምጃ መውሰዱ ተገቢ ነበር። በአምላክ ዓይን ጻድቅ ሆነው የተቆጠሩት ስምንት ሰዎች ብቻ የነበሩ ሲሆን እነሱንም አድኗቸዋል።
አምላክ ከእስራኤል ጋር የነበረውም ግንኙነት ተመሳሳይ ሁኔታ ይታይበታል። ታማኝነት የጎደለው ነውረኛ አካሄድ ቢከተሉም አምላክ በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት ታግሷቸዋል። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ለሕዝቡ . . . ስላዘነ . . . በመልእክተኞቹ እጅ ወደ እነርሱ ይልክ ነበር። እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በሕዝቡ ላይ እስኪወጣ ድረስ፣ ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ፣ . . . ቃሉንም ያቃልሉ፣ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር።” (2 ዜና መዋዕል 36:15, 16) ሕዝቡ ምንም መሻሻል ማድረግ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰው ነበር። ሊድኑ የሚችሉት ኤርምያስና ሌሎች ጥቂት ሰዎች ብቻ ነበሩ። በመጨረሻ አምላክ በተቀሩት ሰዎች ላይ የቅጣት እርምጃ መውሰዱ ፈጽሞ ፍትሕ አልባ አያሰኘውም።
አምላክ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ ደርሷል
አምላክ በዚህ የነገሮች ሥርዓት ላይ የሚያመጣውን ጥፋት ያዘገየው የቀጠረው ጊዜ እስከሚደርስ ብቻ መሆኑን ከእነዚህ ምሳሌዎች ለመመልከት እንችላለን። ይህ ሁኔታ አምላክ ለምሳሌያዊው ፍርድ አስፈጻሚ በሰጠው ትእዛዝ ላይ ተገልጿል:- “ዘለላዎቹ ፈጽመው በስለዋልና ስለታሙን ማጭድህን ስደድና በምድር ያለውን የወይን ዛፍ ዘለላዎች ቊረጥ ብሎ በታላቅ ድምፅ ጠራ። መልአኩም ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው፣ በምድርም ካለው ከወይን ዛፍ ቈርጦ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር ቊጣ መጥመቂያ ጣለ።” የሰው ልጆች ክፋት እንደ ‘በሰለ’ ማለትም ሊሻሻል ወደማይችልበት ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ ልብ በል። አምላክ ጣልቃ በመግባት የሚወስደው የቅጣት እርምጃ ፍትሐዊ እንደሚሆን ምንም አያጠራጥርም።—ራእይ 14:18, 19
ከላይ ያለውን ስንመረምር አምላክ በዚህ ዓለም ላይ የሚወስደው የቅጣት እርምጃ ቅርብ እንደሚሆን በግልጽ እንመለከታለን፤ ምክንያቱም ዓለም እየተጓዘ ያለው ቀደም ሲል አምላክ የቅጣት እርምጃ እንዲወስድ ባደረገው መንገድ ነው። ከኖኅ የጥፋት ውኃ በፊት እንደነበረው ሁሉ ዛሬም በማንኛውም ቦታ ብንመለከት ምድር በክፋት ተሞልታለች። የሰዎች ሁኔታ በዘፍጥረት 6:5 ላይ ከተገለጸው ጋር የሚመሳሰል እየሆነ ነው:- “[የሰው ልብ] አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ [ነው]።” ሌላው ቀርቶ በከነዓናውያን ላይ የአምላክ ፍርድ እንዲመጣ ያደረጉት ከባድ ኃጢአቶች በዛሬው ጊዜ ተራ ነገሮች ሆነዋል።
በተለይ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በሰው ልጅ ላይ አሳዛኝ የሆኑ ለውጦች ተከስተዋል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደም ምድርን ሲያጨቀያት ተመልክቷል። ጦርነት፣ ዘር ማጥፋት፣ ሽብርተኝነት፣ ወንጀልና ሕገ ወጥነት በዓለም ዙሪያ ተስፋፍቷል። ረሃብ፣ በሽታና የሥነ ምግባር ውድቀት ዓለማችንን አጥለቅልቀዋታል። ማስረጃዎቹ በሙሉ ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት በተናገረለት ክፉ ትውልድ መካከል እንደምንኖር ያሳያሉ:- “እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።” (ማቴዎስ 24:34) በአሁኑ ጊዜ የዓለም ‘ኃጢአት እየተፈጸመ’ ነው። ‘በምድር ያሉት የወይን ዛፍ ዘለላዎች’ ለመታጨድ በመብሰል ላይ ናቸው።
እርምጃ የምትወስድበት ጊዜ አሁን ነው
ሐዋርያው ዮሐንስ የፍርድ ጊዜ ሲቃረብ ሁለት ዓይነት መብሰል እንደሚኖር ተነግሮት ነበር። በአንድ በኩል “ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፣ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ።” በሌላ በኩል ደግሞ “ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፣ ቅዱሱም ወደ ፊት ይቀደስ።” (ራእይ 22:10, 11) በኋላ ላይ የተጠቀሰው ሐሳብ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚያከናውኑት መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ ጋር በተያያዘ መንገድ ተግባራዊ እየሆነ ነው። የዚህ ሥራ ዋነኛ ዓላማ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ብቃት ያላቸው ሆነው እንዲቆጠሩ አምላክ የሚፈልግባቸውን ነገር ማስተማር ነው። ይህ ሥራ በአሁኑ ጊዜ 87,000 በሚደርሱ ጉባኤዎች አማካኝነት 233 በሚያክሉ አገሮች ተዳርሷል።
አምላክ የሰጠውን ተስፋ ለመፈጸም አይዘገይም። ግለሰቦች ለሰጣቸው ተስፋዎች ብቁ እንዲሆኑ ለማድረግ ሲል ‘አዲሱን ሰው ለመልበስ’ የሚያስፈልጋቸውን ጊዜ በመስጠት ይታገሣል። (ኤፌሶን 4:24) በዛሬው ጊዜ በዓለም ያለው ሁኔታ እየተባባሰ ቢሄድም አምላክ አሁንም በትዕግሥት በመጠባበቅ ላይ ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን እውቀት ለጎረቤቶቻቸው በማካፈል አቅማቸው የሚፈቅደውን ሁሉ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። (ዮሐንስ 17:3, 17) ደስ የሚለው ነገር በየዓመቱ ከ300,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ለጥሪው ምላሽ በመስጠት ይጠመቃሉ።
ይህ ጊዜ በዘላለም ሕይወት ተስፋ ላይ በማትኮር እርምጃ የምንወስድበት እንጂ እጃችንን አጣጥፈን የምንቀመጥበት ጊዜ አይደለም። በቅርብ ጊዜ ውስጥ “ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም” የሚለው የኢየሱስ ትንቢት ፍጻሜውን ሲያገኝ እንመለከታለን።—ዮሐንስ 11:26
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ዘ ሶንሲኖ ሹሜሽ በተባለው መጽሐፍ ላይ የዚህ ጥቅስ የግርጌ ማስታወሻ እንዲህ ይላል:- “አምላክ የአንድ ብሔር የኃጢአት ጽዋ እስኪሞላ ድረስ ቅጣቱን ስለማያስፈጽም ሕዝቡ ከምድሪቱ አይባረሩም ነበር።”
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ ፍርድ አስፈጻሚ በምድር ያሉት የወይን ዛፍ ዘለላዎች በሚበስሉበት ጊዜ ማጭዱን እንዲሰድድ ተነግሮታል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ለአምላክ ዘላለማዊ በረከቶች ብቁ እንዲሆኑ ሰዎችን በመርዳት ላይ ናቸው