እንዴት ዓይነት ሰዎች ልትሆኑ ይገባችኋል?
1 የሰው ልጆች በጠቅላላ ላደረጉት ነገር መልስ የሚሰጡበት ጊዜ ቀርቧል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ጊዜ ‘የእግዚአብሔር ቀን’ በማለት ይጠራዋል። ይህ ቀን በክፉዎች ላይ መለኮታዊ ፍርድ የሚሰጥበትና ጻድቃን ነፃ የሚወጡበት ጊዜ ነው። በዚያን ጊዜ በሕይወት የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይከተሉት ስለነበረው የሕይወት ጎዳና መልስ ይሰጣሉ። ጴጥሮስ ይህንን በአእምሮው በመያዝ “እንዴት ዓይነት ሰዎች ልትሆኑ ይገባችኋል?” በማለት ራሳችንን እንድንመረምር የሚያደርግ አንድ ጥያቄ አቅርቧል። ‘ቅዱስ የሆነ አኗኗርን፣ ለአምላክ ማደርን የሚያሳዩ ተግባራትንና የይሖዋን ቀን አቅርቦ የመመልከትን’ ጠቀሜታም ሆነ ‘ነውርና ነቀፋ የሌለብን የመሆንንና በሰላም የመገኘትን’ አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ገልጿል።— 2 ጴጥ. 3:11–14
2 ቅዱስ አኗኗርና ለአምላክ ማደርን የሚያሳዩ ተግባራት፦ ቅዱስ አኗኗር ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አክብሮት እንዳለን የሚያሳዩ ለሌሎች አርዓያ የሚሆኑ ሥራዎችን ያጠቃልላል። (ቲቶ 2:7, 8) አንድ ክርስቲያን ራስ ወዳድነት በሚንጸባረቅባቸው የሥጋ ምኞቶች ገፋፊነት ከሚደረገው ዓለማዊ ተግባር መራቅ አለበት።— ሮሜ 13:11, 14
3 ለአምላክ ያደሩ መሆን “ማራኪ ለሆኑት የአምላክ ጠባዮች ጥልቅ አድናቆት ካደረበት ልብ የመነጨ ከአምላክ ጋር የሚፈጠር የጠበቀ የግል ዝምድና” ነው ተብሎ ተገልጿል። በአገልግሎት የምናሳየው ቅንዓት ይህንን ባሕርይ የምናንጸባርቅበት ዋነኛው መንገድ ነው። በስብከቱ ሥራ የምንካፈለው ግዴታ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ለይሖዋ ካለን ጥልቅ ፍቅር የተነሳ ነው። (ማር. 12:29, 30) በእንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ስለምንገፋፋ አገልግሎታችንን ለአምላክ ያደርን መሆናችንን የምናሳይበት ትርጉም ያለው መግለጫ አድርገን እንመለከተዋለን። ሁልጊዜ ለአምላክ ያደርን መሆን ስላለብን በስብከቱ ሥራ የምናደርገው ተሳትፎ ያዝ ለቀቅ መሆን የለበትም። የሳምንታዊ እንቅስቃሴዎቻችን ፕሮግራም ዋነኛ ክፍል መሆን አለበት።— ዕብ. 13:15
4 የይሖዋን ቀን “አቅርቦ መመልከት” ማለት በዕለታዊ ሐሳባችን ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ መስጠትና ዋጋ እንደሌለው ነገር ገሸሽ አለማድረግ ማለት ነው። ይህም በሕይወታችን ውስጥ ለመንግሥቱ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት ማለት ነው።— ማቴ. 6:33
5 ያለ ነውር፣ ያለ ነቀፋ መሆንና በሰላም መገኘት፦ ከእጅግ ብዙ ሰዎች መካከል እንደመሆናችን መጠን ‘ልብሳችንን አጥበን በበጉ ደም አንጽተናል።’ (ራእይ 7:14) ስለዚህ “ያለ ነውር” መሆን ማለት ለአምላክ በወሰንነው ንጹሕ ሕይወት ላይ የዓለም ቆሻሻዎች እንዳይፈናጠቁበት አጥብቀን መከላከል አለብን ማለት ነው። አምላካዊ ያልሆኑ ቁሳዊ ነገሮችን ማሳደድ ክርስቲያናዊ ጠባያችንን እንዳያጎድፈው በመከላከል “ያለ ነቀፋ” ሆነን መገኘት አንችላለን። (ያዕ. 1:27፤ 1 ዮሐ. 2:15–17) ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ሁሉ ‘የአምላክን ሰላም’ በማንፀባረቅ “በሰላም” እንደምንኖር እናሳያለን።— ፊልጵ. 4:7፤ ሮሜ 12:18፤ 14:19
6 ከዓለም እድፈት ራሳችንን ከጠበቅን ይሖዋ ያወገዘውን ‘ይህንን የነገሮች ሥርዓት’ በምንም መንገድ ‘አንመስልም።’ ከዚህ ይልቅ መልካም ሥራዎቻችን ሌሎች “ለእግዚአብሔር በሚገዛውና በማይገዛው መካከል” ያለውን ልዩነት እንዲመለከቱ ይረዷቸዋል። (ሮሜ 12:2፤ ሚል. 3:18) ቅንዓት የተሞላበት የስብከት ሥራችንም እንደዚሁ ነው። ብዙ አዳዲስ ሰዎች አብረውን ለመሥራት ብቃቱን አሟልተው ይሆናል። በነሐሴ ወር በመስክ አገልግሎት እንዲካፈሉ በመርዳት በረከት ልንሆንላቸው እንችላለን።
7 ‘መልካም ሥራዎችን’ በትጋት ማከናወናችንን ስንቀጥል የይሖዋ ስም ከፍ ከፍ ይላል፣ ጉባኤው ይበረታታል እንዲሁም ሌሎች ይጠቀማሉ። (1 ጴጥ. 2:12) ምንጊዜም እንዲህ ዓይነት ሰዎች እንሁን።