ምዕራፍ 48
አምላክ በሚያመጣው ሰላማዊ አዲስ ዓለም ውስጥ መኖር ትችላለህ
አምላክ አዳምንና ሔዋንን በኤደን ገነት ውስጥ አስቀምጧቸው ነበር። አዳምና ሔዋን ባለመታዘዛቸው ምክንያት ቢሞቱም አምላክ፣ እኛን ጨምሮ ዘሮቻቸው በገነት ለዘላለም መኖር እንዲችሉ ዝግጅት አድርጓል። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት ተስፋ ይሰጣል።—መዝሙር 37:29
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ “አዲስ ሰማያት” እና “አዲስ ምድር” ይናገራል። (ኢሳይያስ 65:17፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) አሁን ያሉት “ሰማያት” በዛሬው ጊዜ ያሉትን ሰብዓዊ መንግሥታት በጠቅላላ የሚያመለክቱ ሲሆን “አዲስ ሰማያት” የተባሉት ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስና ከእሱ ጋር በሰማይ የሚገዙት ናቸው። ሰላም የሚያመጣውን የአምላክ ጻድቅ መስተዳድር የሚወክሉት እነዚህ አዲስ ሰማያት መላውን ምድር በሚገዙበት ጊዜ የሚኖረው ሁኔታ በጣም አስደሳች ይሆናል!
“አዲስ ምድር” የተባለው ደግሞ ምንድን ነው?— አዲስ ምድር የተባሉት ይሖዋን የሚወዱ ጥሩ ሰዎች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጊዜ “ምድር” ብሎ የሚጠራው መሬትን ሳይሆን በምድር ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ነው። (ዘፍጥረት 11:1 የ1954 ትርጉም፤ መዝሙር 66:4፤ 96:1) ስለዚህ አዲስ ምድር የሚሆኑት ሰዎች እዚሁ ምድር ላይ ይኖራሉ።
አሁን ያለው የክፉ ሰዎች ዓለም በዚያን ጊዜ አይኖርም። በኖኅ ዘመን የመጣው የጥፋት ውኃ በዚያን ጊዜ የነበረውን የክፉ ሰዎች ዓለም እንዳጠፋ አስታውስ። በተጨማሪም ቀደም ሲል እንደተማርነው በአሁኑ ጊዜ ያለው ክፉ ዓለም በአርማጌዶን ይጠፋል። ከአርማጌዶን በኋላ አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖረው ሕይወት ምን እንደሚመስል እስቲ እንመልከት።
አምላክ በሚያመጣው ሰላም በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ በገነት ለዘላለም መኖር ትፈልጋለህ?— ለዘላለም እንድንኖር ሊያደርገን የሚችል ሐኪም የለም። ከሞት ሊያድነን የሚችል መድኃኒትም የለም። ለዘላለም መኖር የምንችለው ወደ አምላክ ከቀረብን ብቻ ነው። ታላቁ አስተማሪም ወደ አምላክ እንዴት መቅረብ እንደምንችል ገልጾልናል።
መጽሐፍ ቅዱሳችንን እናውጣና ዮሐንስ ምዕራፍ 17 ቁጥር 3ን እናንብብ። እዚህ ጥቅስ ላይ ታላቁ አስተማሪ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ስለሆንከው ስለ አንተና ስለላክኸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠል አለባቸው።”
ስለዚህ ኢየሱስ ለዘላለም ለመኖር ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገን ተናግሯል?— በመጀመሪያ የሰማዩ አባታችንን ይሖዋንና ሕይወቱን ለእኛ የሰጠውን ልጁን በሚመለከት እውቀት መቅሰም አለብን። ይህም ማለት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ያስፈልገናል ማለት ነው። ከታላቁ አስተማሪ ተማር የተሰኘው ይህ መጽሐፍ እንዲህ ማድረግ እንድንችል እየረዳን ነው።
ይሁን እንጂ ስለ ይሖዋ መማር ለዘላለም መኖር እንድንችል የሚረዳን እንዴት ነው?— በየቀኑ ምግብ መብላት እንደሚያስፈልገን ሁሉ ስለ ይሖዋም በየቀኑ መማር ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ ሊኖር አይችልም” ይላል።—ማቴዎስ 4:4
በተጨማሪም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት መቅሰም ያስፈልገናል፤ ምክንያቱም አምላክ ልጁን የላከው ኃጢአታችንን እንዲያስወግድልን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “መዳን በሌላ በማንም አይገኝም” ይላል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “በወልድ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ የዘላለም ሕይወት አለው” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 4:12፤ ዮሐንስ 3:36) በኢየሱስ ‘ማመን’ ሲባል ምን ማለት ነው?— በኢየሱስ በእርግጥ የምናምን ከሆነ ያለ እሱ ለዘላለም መኖር እንደማንችል እንገነዘባለን ማለት ነው። ታዲያ እኛ በኢየሱስ እናምናለን?— የምናምን ከሆነ ታላቁ አስተማሪ ያስተማረውን ትምህርት በየቀኑ መማራችንን እንቀጥላለን፤ እንዲሁም የተናገረውን በተግባር እናውላለን።
ከታላቁ አስተማሪ መማር የምንችልበት አንዱ ጥሩ መንገድ ይህን መጽሐፍ ደጋግሞ ማንበብና ሁሉንም ሥዕሎች እያዩ በሥዕሎቹ ላይ ማሰላሰል ነው። ሥዕሎቹን በምትመለከትበት ጊዜ ከሥዕሎቹ ጋር ተያይዘው ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ሞክር። በተጨማሪም መጽሐፉን ከእናትህ ወይም ከአባትህ ጋር አንብበው። ወላጆችህ አብረውህ ካልሆኑ ከሌላ ትልቅ ሰው ጋር እንዲሁም ከሌሎች ልጆች ጋር አንብበው። ሌሎች ሰዎችም አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም ለመኖር ምን ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው እንዲያውቁ ከታላቁ አስተማሪ እንዲማሩ ልትረዳቸው ብትችል ጥሩ አይደለም?—
መጽሐፍ ቅዱስ ‘ዓለም በማለፍ ላይ ነው’ በማለት ይነግረናል። ከዚያም አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም መኖር የምንችለው እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ “የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” ይላል። (1 ዮሐንስ 2:17) ታዲያ አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም መኖር የምንችለው እንዴት ነው?— አዎ፣ ስለ ይሖዋና ውድ ልጁ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ እውቀት በመቅሰም ነው። ይሁን እንጂ የተማርነውን ነገር በሥራ ላይ ማዋልም ያስፈልገናል። ይህን መጽሐፍ ማጥናትህ ይህን እንድታደርግ እንዲረዳህ ምኞታችን ነው።