የኢየሱስ ሰብዓዊ ሕይወት የመጨረሻ ዕለት
ዕለቱ ኒሳን 14, 33 እዘአ አርብ ከሰዓት በኋላ አመሻሹ ላይ ነው። ጥቂት ወንዶችና ሴቶች አንድ የቅርብ ወዳጃቸውን ለመቅበር ተሰባስበዋል። ከወንዶቹ መካከል አንዱ ማለትም ኒቆዲሞስ አስከሬኑን ለቀብር ለማዘጋጀት የሚያገለግሉ ሽቱዎችን አምጥቷል። ዮሴፍ የሚባለው ደግሞ ለቆሰለውና በድብደባ ለበለዘው አስከሬን መጠቅለያ የሚሆን ንጹሕ ጨርቅ ይዞ መጥቷል።
ሰዎቹ እነማን ናቸው? የሚቀብሩትስ ማንን ነው? ይህ ጉዳይ አንተን ይመለከታልን? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ይህን ታሪካዊ ቀን ከመጀመሪያው አንስተን እንመልከት።
ሐሙስ ምሽት፣ ኒሳን 14
በኢየሩሳሌም ደማቅ የሆነች ሙሉ ጨረቃ በዝግታ በመውጣት ላይ ነች። በሰዎች ተጨናንቃ የዋለችው ከተማ ረጭ እያለች ነው። የምሽቱ አየር የበግ ጥብስ የበግ ጥብስ ይሸታል። አዎን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ልዩ የሆነውን ዓመታዊ የማለፍ በዓል ለማክበር ሽርጉድ እያሉ ናቸው።
በአንድ ትልቅ ሳሎን ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስና 12 ሐዋርያቱ በተዘጋጀ ገበታ ዙሪያ ተቀምጠዋል። አሁን ኢየሱስ የሚናገረውን በትኩረት አዳምጡ! “ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር” አለ። (ሉቃስ 22:15) ኢየሱስ ሃይማኖታዊ ጠላቶቹ እርሱን የማስገደል ዓላማ እንዳላቸው ያውቃል። ሆኖም ያ ከመሆኑ በፊት በዚህ ምሽት ላይ አንድ ከፍተኛ ትርጉም ያለው ነገር ይከናወናል።
የማለፍ በዓል ተከብሮ ካበቃ በኋላ ኢየሱስ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል” ሲል ገለጸ። (ማቴዎስ 26:21) ይህ ነገር ሐዋርያቱን ረበሻቸው። ማን ሊሆን ይችላል? ጥቂት የሐሳብ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ ኢየሱስ ለአስቆሮቱ ይሁዳ “የምታደርገውን ቶሎ ብለህ አድርግ” አለው። (ዮሐንስ 13:27) ሌሎቹ ባይረዱትም እንኳ ይሁዳ ከሃዲ ሆኗል። ይሁዳ በኢየሱስ ላይ የሸረበውን ዕኩይ ተግባር ከግቡ ለማድረስ ክፍሉን ለቅቆ ወጣ።
በዓይነቱ ልዩ የሆነ በዓል
ኢየሱስ፣ የእርሱ ሞት የሚከበርበት በዓይነቱ አዲስ የሆነ አንድ በዓል አቋቋመ። ኢየሱስ ቂጣ አንስቶ የምስጋና ጸሎት ካቀረበ በኋላ “እንካችሁ፣ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው። ሁሉም ከቂጣው ከበሉ በኋላ ቀይ ወይን የያዘ ጽዋ አንስቶ ባረከው። “ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ” አላቸው። ከዚያም “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው” በማለት ገለጸላቸው። የቀሩትን 11 ታማኝ ሐዋርያት “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ሲል አዘዛቸው።—ማቴዎስ 26:26-28፤ ሉቃስ 22:19, 20፤ 1 ቆሮንቶስ 11:24, 25
በዚያ ምሽት ኢየሱስ ታማኝ ሐዋርያቱን ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ነገር በደግነት ያዘጋጃቸው ሲሆን ለእነርሱ ያለውን ጥልቅ ፍቅርም አረጋግጦላቸዋል። “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም። እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ” ሲል ገለጸ። (ዮሐንስ 15:13-15) አዎን፣ ኢየሱስ ፈተና በደረሰበት ወቅት 11ዱ ሐዋርያት እርሱን ፈጽሞ ባለመተው እውነተኛ ወዳጆች መሆናቸውን አስመስክረዋል።
ምሽቱ ማብቂያ ላይ፣ ምናልባትም እኩለ ሌሊት ካለፈ በኋላ ኢየሱስ ከፍተኛ ትርጉም ያዘለ ጸሎት አቅርቦ ሲጨርስ ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙሮች ዘመሩ። ከዚያም ሙሉ ጨረቃ በምታበራው ብርሃን ከከተማዋ ወጥተው የኬድሮንን ሸለቆ አቋርጠው ሄዱ።—ዮሐንስ 17:1–18:1
በጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢየሱስና ሐዋርያቱ በጌቴሴማኒ ወደሚገኘው የአትክልት ሥፍራ ደረሱ። ኢየሱስ ስምንቱን ሐዋርያት በአትክልት ሥፍራው መግቢያ ላይ ትቷቸው ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ የወይራ ዛፎች ወዳሉበት ውስጠኛ ክፍል ገባ። ለሦስቱ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቆዩ ትጉም” አላቸው።—ማርቆስ 14:33, 34
ኢየሱስ ለመጸለይ ወደ አትክልት ሥፍራው ውስጠኛ ክፍል ሲገባ ሦስቱ ሐዋርያት እዚያው ቆዩት። በከፍተኛ ጩኸትና እንባ “አባት ሆይ፣ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ” ሲል ተማጸነ። በኢየሱስ ጫንቃ ላይ ከፍተኛ ኃላፊነት ወድቋል። ይሖዋ፣ አንድያ ልጁ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ በሚሰቀልበት ጊዜ ጠላቶቹ ምን እንደሚሉ ማሰብ ለኢየሱስ እንዴት የሚያስጨንቅ ነበር! ኢየሱስን ይበልጥ ያስጨነቀው ሐሳብ ይህን ወሳኝ ፈተና ከወደቀ በውድ ሰማያዊ አባቱ ላይ የሚከመረው ነቀፋ ነው። ኢየሱስ ልባዊ ጸሎት ከማቅረቡም በላይ ከፍተኛ ውጥረት ተሰምቶት ስለነበር ላቡ እንደ ደም ጠብታ መሬት ላይ ተንጠባጥቧል።—ሉቃስ 22:42, 44
ኢየሱስ ለሦስተኛ ጊዜ ጸልዮ ገና ከመጨረሱ ችቦና ፋና የያዙ ሰዎች መጡ። ፊት ፊት እየመራ በቀጥታ ወደ ኢየሱስ የመጣው ከአስቆሮቱ ይሁዳ ሌላ ማንም እንደማይሆን የታወቀ ነው። “መምህር ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን” ብሎ ኢየሱስን ሳመው። ኢየሱስ ደግሞ “ይሁዳ ሆይ፣ በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው።—ማቴዎስ 26:49፤ ሉቃስ 22:47, 48፤ ዮሐንስ 18:3
ሐዋርያቱ ምን እየተደረገ እንዳለ ወዲያው ገባቸው። ጌታቸውና የቅርብ ወዳጃቸው ሊያዝ ነው! በመሆኑም ጴጥሮስ በቅጽበት ሰይፍ መዝዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ ጆሮ ቆረጠ። ወዲያውኑ ኢየሱስ “ይህንስ ፍቀዱ” ሲል ነገራቸው። ኢየሱስ ወደፊት ጠጋ ብሎ የባሪያውን ጆሮ ከፈወሰ በኋላ ጴጥሮስን “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ” ሲል አዘዘው። (ሉቃስ 22:50, 51፤ ማቴዎስ 26:52) አዛዦቹና ወታደሮቹ ኢየሱስን ይዘው ሲያስሩት ሐዋርያቱ በፍርሃትና በግራ መጋባት ተውጠው በጭለማ ኢየሱስን ጥለው ሸሹ።—ማቴዎስ 26:56፤ ዮሐንስ 18:12
አርብ ጠዋት፣ ኒሳን 14
አሁን እኩለ ሌሊቱ ተገባድዶ አርብ ጎሕ ሊቀድ ተቃርቧል። በመጀመሪያ ኢየሱስ አሁንም ከፍተኛ ተደማጭነትና ሥልጣን ወዳለው የቀድሞው ሊቀ ካህን ወደ ሐና ቤት ተወሰደ። ሐና ጥያቄ ካቀረበለት በኋላ የሳንሄድሪን ሸንጎ ወደተሰበሰበበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ቤት እንዲወሰድ አደረገ።
ሃይማኖታዊ መሪዎች በኢየሱስ ላይ የውሸት ክስ የሚያቀርቡ ምሥክሮች ለማግኘት ሞከሩ። ይሁን እንጂ የሐሰት ምሥክሮቹ በሚሰጡት ምሥክርነት ሊስማሙ አልቻሉም። ይህ ሁሉ ሲሆን ኢየሱስ አንድም ቃል አልተነፈሰም። ቀያፋ ዘዴውን በመቀየር “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደ ሆነ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ” ሲል አጥብቆ ጠየቀው። ይህ ሊታበል የማይችል ሐቅ ስለሆነ ኢየሱስ በድፍረት “እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ” ሲል መለሰ።—ማቴዎስ 26:63፤ ማርቆስ 14:60-62
ቀያፋ “ተሳድቦአል” ሲል ጮኸ። “ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮች ስለ ምን ያስፈልገናል?” በዚህ ጊዜ አንዳንዶቹ ኢየሱስን በጥፊ መቱት እንዲሁም ተፉበት። ሌሎቹ ደግሞ ጎሰሙት እንዲሁም አፌዙበት። (ማቴዎስ 26:65-68፤ ማርቆስ 14:63-65) በጭለማ የተካሄደውን ሕገ ወጥ ችሎት ሕጋዊ ለማስመሰል ሳይሆን አይቀርም አርብ ጠዋት የሳንሄድሪን ሸንጎ በድጋሚ ተሰበሰበ። ኢየሱስ የአምላክ ልጅ የሆነው ክርስቶስ መሆኑን እንደገና በድፍረት ተናገረ።—ሉቃስ 22:66-71
ከዚያም የካህናት አለቆቹና ሽማግሌዎቹ ኢየሱስን የይሁዳ አስተዳዳሪ ወደሆነው ሮማዊ ገዥ ጴንጤናዊው ጲላጦስ ፊት ለፍርድ አቀረቡት። ሕዝቡን በማጣመም፣ ለቄሣር ቀረጥ እንዳይከፈል በመከልከል እንዲሁም “እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ ሲል አገኘነው” ሲሉ ኢየሱስን ከሰሱት። (ሉቃስ 23:2፤ ከማርቆስ 12:17 ጋር አወዳድር።) ጲላጦስ ለኢየሱስ ጥያቄ ካቀረበለት በኋላ “በዚህ ሰው አንድ በደል እንኳ አላገኘሁበትም” ሲል ገለጸ። (ሉቃስ 23:4) ኢየሱስ የገሊላ ሰው መሆኑን ጲላጦስ ሲሰማ የማለፍ በዓልን ለማክበር በኢየሩሳሌም ይገኝ ወደነበረው የገሊላ ገዥ ሄሮድስ አንጢፓስ ላከው። ሄሮድስ ፍትሕ ተጠብቋል አልተጠበቀም ለሚለው ጉዳይ ትኩረት አልሰጠም። የእርሱ ፍላጎት ኢየሱስ ተአምር ሲሠራ ማየት ብቻ ነው። ኢየሱስ ጉጉቱን ስላላረካለትና ምንም ስላልተናገረ ሄሮድስም ሆነ ወታደሮቹ ከተሳለቁበት በኋላ መልሶ ወደ ጲላጦስ ላከው።
ጲላጦስ “ያደረገው ክፋት ምንድን ነው?” ሲል በድጋሚ ጠየቀ። “ለሞት የሚያደርሰው በደል አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ።” (ሉቃስ 23:22) ስለዚህ ብዙ ምላስ ባለው የቆዳ ጅራፍ ጀርባው ክፉኛ እስኪተለተል ድረስ አስገረፈው። ከዚያም ወታደሮቹ ራሱ ላይ የእሾህ አክሊል ደፍተው አፌዙበት እንዲሁም ጭንቅላቱን በደረቅ መቃ እየመቱ እሾኹ ጭንቅላቱን እንዲወጋው አደረጉ። ኢየሱስ ይህ ሁሉ በቃላት ሊገለጽ የማይችል ስቃይና ነቀፋ ቢደርስበትም አስገራሚ የሆነ የመረጋጋትና የጽናት መንፈስ አሳይቷል።
ጲላጦስ ምናልባት የኢየሱስን የተጎሳቆለ ሁኔታ ማየታቸው እንዲራሩለት ያነሳሳቸዋል በሚል ተስፋ ሳይሆን አይቀርም ኢየሱስን በድጋሚ ወደ ሕዝቡ አወጣው። ጲላጦስ “እነሆ፣ አንዲት በደል እንኳ እንዳላገኘሁበት ታውቁ ዘንድ እርሱን ወደ ውጭ አወጣላችኋለሁ” ሲል ገለጸ። ሆኖም የካህናት አለቆቹ “ስቀለው ስቀለው” እያሉ ጮኹ። (ዮሐንስ 19:4-6) ጲላጦስ የሕዝቡ ውትወታ ይበልጥ እየጨመረ ሲሄድ ለእነርሱ ፈቃድ በመሸነፍ ኢየሱስን እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጠው።
የሥቃይ ሞት
አሁን ጊዜው ረፋዱ ላይ ሲሆን ምናልባትም ወደ ቀትር ሳይቃረብ አይቀርም። ኢየሱስ ከኢየሩሳሌም ውጭ ወደሚገኘው ጎልጎታ ወደሚባል ሥፍራ ተወሰደ። ኢየሱስ እጆቹና እግሮቹ በትልልቅ ምስማር በእንጨት ላይ ተቸነከሩ። ከዚያም እንጨቱ ወደ ላይ ቀጥ ብሎ ሲቆም የሰውነቱ ክብደት የተቸነከረበትን ቀዳዳ ሲተረትረው የተሰማውን ስቃይ በቃላት መግለጽ ያዳግታል። ኢየሱስና ሁለቱ ወንጀለኞች ሲሰቀሉ ለማየት ብዙ ሕዝብ ተሰብስቧል። ብዙዎቹ ኢየሱስን ይሳደቡ ነበር። የካህናት አለቆችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች “ሌሎችን አዳነ፣ ራሱን ሊያድን አይችልም” በማለት ዘበቱበት። ሌላው ቀርቶ ወታደሮቹና የተሰቀሉት ሁለት ወንጀለኞች ሳይቀር በኢየሱስ ላይ ተሳለቁ።—ማቴዎስ 27:41-44
እኩለ ቀን ሲሆን ኢየሱስ ለተወሰነ ጊዜ ተሰቅሎ ከቆየ በኋላ በድንገት መለኮታዊ ምንጭ ያለው አስፈሪ ጨለማ ለሦስት ሰዓታት ያህል ምድሪቱን ሸፈናት።a አንደኛው ወንጀለኛ አብሮት የተሰቀለውን እንዲገስጽ ያነሳሳው ይህ ሳይሆን አይቀርም። ከዚያም ወደ ኢየሱስ ዞር ብሎ “በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” ሲል ለመነው። በሞት አፋፍ ላይ እያለ ምንኛ የሚደነቅ እምነት አሳይቷል! ኢየሱስ ‘እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ’ ሲል መለሰለት።—ሉቃስ 23:39-43
ከሰዓት በኋላ ወደ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ኢየሱስ ሕይወቱ ሊያልፍ መቃረቡን ሲያውቅ “ተጠማሁ” አለ። ከዚያም በከፍተኛ ድምፅ “አምላኬ አምላኬ፣ ስለ ምን ተውኸኝ?” ሲል ጮኸ። ኢየሱስ፣ የዳዊትን ቃላት ጠቅሶ ሲናገር ንጹሕ አቋሙ እስከ መጨረሻው ድረስ እንዲፈተን አባቱ ከለላውን ከእርሱ ላይ ያነሳ ያህል ተሰምቶት ነበር። አንድ ሰው ሆምጣጤ ውስጥ የተነከረ ስፖንጅ ወደ አፉ አመጣለት። ኢየሱስ ጥቂት ሆምጣጤ ከጠጣ በኋላ እያቃተተ “ተፈጸመ” አለ። ከዚያም በከፍተኛ ድምፅ “አባት ሆይ፣ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” ካለ በኋላ ራሱን አዘንብሎ ሞተ።—ዮሐንስ 19:28-30፤ ማቴዎስ 27:46፤ ሉቃስ 23:46፤ መዝሙር 22:1
የከሰዓት በኋላው ጊዜ ሊገባደድ ተቃርቦ ስለነበር ፀሐይ ጠልቃ ሰንበት (ኒሳን 15) ከመጀመሩ በፊት ኢየሱስን ለመቅበር የችኮላ ዝግጅት ተደረገ። በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረው እውቁ የሳንሄድሪን አባል የአርማትያሱ ዮሴፍ ኢየሱስን እንዲቀብር ተፈቀደለት። በኢየሱስ ላይ እምነት እንዳለው በስውር የተናገረው ሌላው የሳንሄድሪን አባል ኒቆዲሞስ ደግሞ 33 ኪሎ ግራም የሚመዝን ከርቤና የእሬት ቅልቅል በመስጠት ትብብር አደረገ። የኢየሱስን አካል በአቅራቢያው በሚገኝ አዲስ መቃብር ውስጥ በጥንቃቄ አስቀመጡት።
እንደገና ሕያው ሆነ!
እሁድ በማለዳ መግደላዊት ማርያምና ሌሎች ሴቶች ገና ሳይነጋ ወደ ኢየሱስ መቃብር መጡ። ሆኖም መቃብሩ የተከደነበት ድንጋይ ተንከባልሎ ከቦታው መንቀሳቀሱ አስገራሚ ነው! ይባስ ብሎም መቃብሩ ባዶ ነው! መግደላዊት ማርያም ለጴጥሮስና ለዮሐንስ ለመንገር እየሮጠች ሄደች። (ዮሐንስ 20:1, 2) ገና ከመሄዷ አንድ መልአክ ለተቀሩት ሴቶች ተገለጠላቸው። መልአኩ “እናንተስ አትፍሩ” አላቸው። በተጨማሪም “ፈጥናችሁም ሂዱና:- ከሙታን ተነሣ፣ እነሆም፣ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው” ሲል አሳሰባቸው።—ማቴዎስ 28:2-7
በጥድፊያ እየሄዱ ሳለ ኢየሱስን ራሱን አገኙት! “ሄዳችሁ . . . ለወንድሞቼ ተናገሩ” አላቸው። (ማቴዎስ 28:8-10) በኋላም መግደላዊት ማርያም መቃብሩ አጠገብ ሆና እያለቀሰች ሳለ ኢየሱስ ተገለጠላት። በደስታ ከመፈንደቋም በላይ ይህን የምሥራች ለሌሎች ደቀ መዛሙርት ለማብሰር በፍጥነት ሄደች። (ዮሐንስ 20:11-18) እንዲያውም በዚያ ታሪካዊ እሁድ ዕለት ኢየሱስ ከሞት ስለ መነሳቱ ምንም ጥርጣሬ እንዳይኖር ለማድረግ ለተለያዩ ደቀ መዛሙርቱ አምስት ጊዜ ተገለጠላቸው!
ጉዳዩ አንተን የሚመለከተው እንዴት ነው?
ከ1,966 ዓመታት በፊት የተፈጸሙ ክንውኖች በዚህ በ21ኛው መቶ ዘመን ደፍ ላይ የምትገኘውን አንተን እንዴት ሊመለከት ይችላል? አንድ የእነዚህ ክንውኖች የዓይን ምሥክር እንዲህ ሲል ገልጿል:- “በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፣ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።”—1 ዮሐንስ 4:9, 10
የክርስቶስ ሞት “ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ” የሆነው በምን መንገድ ነው? የእርሱ ሞት ማስተሰሪያ የሆነው ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖር ስለሚያስችል ነው። የመጀመሪያው ሰው አዳም በአምላክ ላይ በማመፁ ምክንያት ለዘሮቹ የኃጢአትና የሞት ቅርስ አስተላልፏል። በአንጻሩ ደግሞ ኢየሱስ ሕይወቱን ለሰው ልጆች ኃጢአትና ሞት የቤዛ ዋጋ አድርጎ በመክፈል አምላክ ምሕረትና ሞገስ እንዲያሳይ የሚያስችል መሠረት ጥሏል። (1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6) አንተም ኃጢአት በሚያስተሰርየው የኢየሱስ መሥዋዕት ላይ እምነት በማሳደር ከኃጢአተኛው አዳም ከወረስከው ኩነኔ ነፃ ልትወጣ ትችላለህ። (ሮሜ 5:12፤ 6:23) እንዲህ ማድረግህ አፍቃሪ ከሆነው ሰማያዊ አባትህ ከይሖዋ አምላክ ጋር የግል ዝምድና የመመሥረት አስደናቂ አጋጣሚ ይከፍትልሃል። በአጭር አባባል ኢየሱስ የከፈለው ከፍተኛ መሥዋዕት ማብቂያ የሌለው ሕይወት ሊያስገኝልህ ይችላል።—ዮሐንስ 3:16፤ 17:3
ሐሙስ ሚያዝያ 1 ምሽት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር በዓለም ዙሪያ በብዙ ሺህ በሚቆጠሩ ቦታዎች በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ እነዚህና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ይብራራሉ። አንተም እንድትገኝ ተጋብዘሃል። በአካባቢህ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን በዓል ለማክበር የሚሰበሰቡበትን ቦታና ሰዓት በደስታ ይነግሩሃል። ስብሰባው ላይ መገኘትህ ኢየሱስ ሰው ሆኖ ባሳለፈው የመጨረሻ ቀን አፍቃሪው አምላካችንና ውድ ልጁ ላደረጉልን ነገር ያለህን አድናቆት እንደሚያሳድግልህ ጥርጥር የለውም።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኢየሱስ የሞተው ሙሉ ጨረቃ በሚታይበት ወቅት ስለሆነ ጨለማው በፀሐይ ግርዶሽ ሳቢያ የተከሰተ ሊሆን አይችልም። የፀሐይ ግርዶሽ ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ የሚቆይ ሲሆን የሚከሰተውም ጨረቃ በምድርና በፀሐይ መካከል በምትሆንበት አዲስ ጨረቃ በሚታይበት ወቅት ነው።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ግራፍ/ሰንጠረዥ]
የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ
ኒሳን 33 እዘአ ክንውኖች ታላቅ ሰውb
14 ሐሙስ ምሽት የማለፍ በዓል ተከበረ፤ ኢየሱስ የሐዋርያቱን እግር አጠበ፤ ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ወጣ፤ ክርስቶስ የሞቱን መታሰቢያ በዓል አቋቋመ (በዚህ ዓመት ሐሙስ፣ ሚያዝያ 1 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ይከበራል)፤ ሐዋርያቱን ተለይቷቸው ለሚሄድበት ጊዜ ለማዘጋጀት መከራቸው 113 አን. 2 እስከ 117 አን. 1
ከእኩለ ሌሊት እስከ ማለዳ ከጸለዩና የምሥጋና መዝሙሮች ከዘመሩ በኋላ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ ሄዱ፤ ኢየሱስ በከፍተኛ ጩኸትና እንባ ጸለየ፤ የአስቆሮቱ ይሁዳ ብዙ ሰዎች ይዞ መጥቶ ኢየሱስን አሳልፎ ሰጠ፤ ኢየሱስ ታስሮ ወደ ሐና ሲወሰድ ሐዋርያቱ ሸሹ፤ በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት እንዲቀርብ ወደ ሊቀ ካህኑ ቀያፋ ተወሰደ፤ ሞት ተፈረደበት፤ ሰደቡት እንዲሁም ደበደቡት፤ ጴጥሮስ ኢየሱስን ሦስት ጊዜ ካደ 117 እስከ 120
አርብ ጠዋት ጠዋት ኢየሱስ በድጋሚ በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ቀረበ፤ ወደ ጲላጦስ ተወሰደ፤ ወደ ሔሮድስ ተላከ፤ ወደ ጲላጦስ ተመለሰ፤ ኢየሱስ ተገረፈ፣ ተሰደበ እንዲሁም ተደበደበ፤ ጲላጦስ ግፊት ሲበዛበት እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው፤ ጠዋት ረፋዱ ላይ በሞት ሊቀጣ ወደ ጎልጎታ ተወሰደ 121 እስከ 124
ከእኩለ ቀን እስከ ከሰዓት በኋላ አጋማሽ ከእኩለ ቀን ጥቂት ቀደም ብሎ ተሰቀለ፤ ኢየሱስ በሚሞትበት ጊዜ ከቀትር አንስቶ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ጨለማ ሆነ፤ ከፍተኛ ርዕደ መሬት ተከሰተ፤ የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከሁለት ተቀደደ 125,126
ከሰዓት አመሻሹ ላይ የኢየሱስ አስከሬን ሰንበት ከመጀመሩ በፊት በአትክልት ቦታ በሚገኝ መቃብር እንዲያርፍ ተደረገ 127 አን. 1-7
15 አርብ ምሽት ሰንበት ጀመረ
ቅዳሜ ጲላጦስ የኢየሱስ መቃብር በወታደሮች እንዲጠበቅ ፈቃድ ሰጠ 127 አን. 8-9
16 እሁድ ማለዳ ላይ የኢየሱስ መቃብር ባዶ ሆኖ ተገኘ፤ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ (1) ሰሎሜን ዮሐናንና የያዕቆብ እናት ማርያምን ጨምሮ ለሴት ደቀ መዛሙርቱ፤ (2) ለመግደላዊት ማርያም፤ (3) ለቀለዮጳና ለጉዞ ጓደኛው፤ (4) ለስምኦን ጴጥሮስ፤ (5) አንድ ላይ ተሰብስበው ለነበሩ ሐዋርያትና ለሌሎች ደቀ መዛሙርት ተገለጠላቸው 127 አን. 10 እስከ 129 አን. 10
[የግርጌ ማስታወሻ]
b እዚህ ላይ የተጠቀሱት ቁጥሮች እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው በተባለው መጽሐፍ ላይ የሚገኙትን ምዕራፎች ያመለክታሉ። የኢየሱስን የመጨረሻ አገልግሎት በተመለከተ ቅዱስ ጽሑፋዊ መግለጫዎችን በዝርዝር የያዘ ሰንጠረዥ ለማግኘት “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና ጠቃሚ ነው” (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ገጽ 290ን ተመልከት። እነዚህ መጻሕፍት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተሙ ናቸው።