-
‘እሱ አስቀድሞ ወዶናል’ወደ ይሖዋ ቅረብ
-
-
“አምላክ ፍቅር ነው”
15. መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን የፍቅር ባሕርይ በተመለከተ ምን ይላል? ይህን አገላለጽ ለየት የሚያደርገውስ ምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
15 መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎቹ የይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያት በተለየ መልኩ ስለ ፍቅር የሚናገረው አንድ ነገር አለ። ቅዱሳን መጻሕፍት ‘አምላክ ኃይል ነው’ ወይም ‘አምላክ ፍትሕ ነው’ ወይም ደግሞ ‘አምላክ ጥበብ ነው’ አይሉም። ይሖዋ እነዚህ ባሕርያት አሉት፤ የእነዚህ ባሕርያት ዋነኛ ምንጭ እሱ ከመሆኑም በላይ በጥበብ፣ በፍትሕም ሆነ በኃይል ረገድ አቻ የለውም። አራተኛውን ባሕርይ በተመለከተ ግን “አምላክ ፍቅር ነው” የሚል ጠለቅ ያለ ትርጉም ያለው አነጋገር ተጠቅሶ እናገኛለን።b (1 ዮሐንስ 4:8) ይህ ምን ማለት ነው?
16-18. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ፍቅር ነው” የሚለው ለምንድን ነው? (ለ) በምድር ላይ ካሉ ፍጥረታት ሁሉ የሰው ልጅ የይሖዋን የፍቅር ባሕርይ ለመግለጽ ተስማሚ ምሳሌ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
16 “አምላክ ፍቅር ነው” ሲባል “አምላክ ማለት ፍቅር ማለት ነው፤ ፍቅር ማለት አምላክ ማለት ነው” እንደማለት ያህል እንደሆነ አድርገን ማሰብ አይኖርብንም። ይሖዋን እንደ አንድ ረቂቅ የሆነ ባሕርይ አድርገን ልንወስደው አይገባም። ከፍቅር በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ስሜቶችና ባሕርያት ያሉት አምላክ ነው። ይሁንና ፍቅር የይሖዋ ዋነኛ ባሕርይ ነው። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ ይህን ጥቅስ አስመልክቶ ሲናገር “አምላክ ሁለንተናው ፍቅር ነው፤ ፍቅር ማንነቱ ነው” ብሏል። ነጥቡን በዚህ መንገድ ጠቅለል አድርጎ መግለጽ ይቻላል፦ የይሖዋ ኃይል ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ያስችለዋል። ፍትሑና ጥበቡ ደግሞ ድርጊቱን ይመሩለታል። ለድርጊት የሚያነሳሳው ግን ፍቅር ነው። በተጨማሪም ሌሎቹን ባሕርያቱን የሚጠቀምባቸው ፍቅሩን በሚያንጸባርቅ መንገድ ነው።
17 ብዙውን ጊዜ ይሖዋ የፍቅር ተምሳሌት እንደሆነ ተደርጎ ይነገራል። በመሆኑም በመሠረታዊ ሥርዓት ስለሚመራው የፍቅር ዓይነት ማወቅ ከፈለግን ስለ ይሖዋ መማር ያስፈልገናል። እርግጥ ነው፣ ሰዎችም ይህን ግሩም ባሕርይ ያንጸባርቃሉ። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ይሖዋ የፍጥረት ሥራዎቹን እያከናወነ በነበረበት ወቅት ልጁን “ሰውን በመልካችን እንደ አምሳላችን እንሥራ” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 1:26) በምድር ላይ ካሉት ፍጥረታት ሁሉ የማፍቀር ችሎታ ያላቸውና በዚህ ረገድ አምላካቸውን መምሰል የሚችሉት ሰዎች ብቻ ናቸው። ይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያቱን ለመግለጽ የተለያዩ ፍጥረታትን ምሳሌ አድርጎ እንደተጠቀመ አስታውስ። ይሁንና ጎላ ብሎ የሚታየውን ባሕርይውን ማለትም ፍቅሩን ለመግለጽ ምሳሌ አድርጎ የተጠቀመው በምድር ላይ ካሉት ፍጥረታት ሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠውን የሰውን ልጅ ነው።—ሕዝቅኤል 1:10
-
-
‘እሱ አስቀድሞ ወዶናል’ወደ ይሖዋ ቅረብ
-
-
b ከዚህ ጋር ተመሳሳይ አገላለጽ የሚጠቀሙ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ። ለምሳሌ ያህል “አምላክ ብርሃን ነው” እና “አምላካችን የሚባላ እሳት ነው” የሚሉ ጥቅሶች እናገኛለን። (1 ዮሐንስ 1:5፤ ዕብራውያን 12:29) ይሁን እንጂ እነዚህ አገላለጾች ይሖዋን የሚያነጻጽሩት ከቁሳዊ ነገሮች ጋር በመሆኑ ዘይቤያዊ አነጋገሮች መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርብናል። ይሖዋ ቅዱስና ጻድቅ ስለሆነ በብርሃን ሊመሰል ይችላል። “ጨለማ” ወይም ርኩሰት በእሱ ዘንድ የለም። ኃይሉን በመጠቀም ማጥፋት የሚችል በመሆኑም ከእሳት ጋር ሊመሳሰል ይችላል።
-