የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 1/1 ገጽ 5-8
  • አዲስ ፍጥረቶች ተወለዱ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አዲስ ፍጥረቶች ተወለዱ
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “የአዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር” መፈጠር
  • ‘የአዲስ ሰማይና የአዲስ ምድር’ አጀማመር
    በሕይወት ተርፎ ወደ አዲስ ምድር መግባት
  • አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር
    ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!
  • በትንቢት እንደተነገረው ሁሉን አዲስ ማድረግ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • መንግሥቲቱ ድል ትቀዳጃለች!
    “መንግሥትህ ትምጣ”
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 1/1 ገጽ 5-8

አዲስ ፍጥረቶች ተወለዱ

ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን አንድ ጊዜ “ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም” ብሎ ነበር። (መክብብ 1:9) ይህ ኣባባል እኛ ለምንኖርበት ግዑዝ ዓለም ይሠራል፤ ነገር ግን የይሖዋ መንፈሳዊ ፍጥረቶች ለሚገኙበት እጅግ ሰፊ ለሆነው መንፈሳዊ ዓለምስ ይሠራልን? በዚህ የመንፈሳዊ ፍጥረቶች ዓለም ከሰሎሞን የሚበልጠው፣ እንዲያውም ከሰሎሞን ብቻ ሳይሆን በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው ተወዳዳሪ የሌለው አዲስ ፍጥረት ሆኖአል። ይህ የሆነው እንዴት ነበር?

ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ በ29 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በዮርዳኖስ ወንዝ በመጥምቁ ዮሐንስ ለመጠመቅ ራሱን አቀረበ። “ከተጠመቀም በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆም ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤ እነሆም ድምፅ ከሰማያት መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ።” (ማቴዎስ 3:16, 17) በመሆኑም ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ተቀብቶ የመጀመሪያው አዲስ ፍጥረት ሆነ። በኋላም በእርሱ መስዋዕታዊ ሞት አማካኝነት በአምላክና በተመረጡ የሰዎች ቡድን መካከል ለተቋቋመው አዲስ ኪዳን መካከለኛ ሆነ። እነዚህ የተመረጡ ሰዎች እያንዳንዳቸው ከኢየሱስ ጋር በሰማያዊት መንግሥቱ ለመግዛት የሚጠባበቁ ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው ለመሆን በአምላክ መንፈስ የተወለዱ “አዲስ ፍጥረት” ሆኑ።—2 ቆሮንቶስ 5:17፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6፤ ዕብራውያን 9:15

እነዚህ የተቀቡና በመንፈስ የተወለዱ ክርስትያኖች ባለፉት በመቶ የሚቆጠሩ ዓመታት በሙሉ ራሱ አዲስ ፍጥረት የሆነው የእውነተኛው ክርስቲያን ጉባኤ አባላት በመሆን ከክርስቶስ ጋር አንድ ወደመሆን ሲሰባሰቡ ቆይተዋል። ሐዋርያው ጴጥሮስ “እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ” በማለት እንደተናገረው አምላክ ይህን የክርስቲያን ጉባኤ ለአንድ ዓላማ ከዚህ ዓለም ጠርቶ አውጥቶታል። (1 ጴጥሮስ 2:9) የመጀመሪያ የአምላክ አዲስ ፍጥረት እንደሆነው እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ከእርሱ በኋላ የመጣው ይህ አዲስ ፍጥረትም የምሥራቹን የመስበክ ተቀዳሚ ግዴታ አለበት። ( ሉቃስ 4:18, 19) በመጨረሻ ቁጥራቸው 144, 000 የሚሆኑት የአዲሱ ፍጥረት ኣባሎች በተናጠል “ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው” መልበስ አለባቸው። (ኤፌሶን 4:24፤ ራእይ 14:1, 3) ይህም በገላትያ 5:22, 23 ላይ የተገለጹትን የመንፈስ ፍሬዎች” እንዲኮተኩቱና የመጋቢነት ሥራቸውንም በታማኝነት እንዲያጠናቅቁ ይጠይቅባቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 4:2፤ 9:16

በዘመናችንስ ይህ አዲስ ፍጥረት ምን ሆነ? የመጽሐፍ ቅዱስ የጊዜ ሰሌዳ እንደሚያሳየው በ1914 “የዓለም መንግሥት ለጌታችንና [ለይሖዋና አዓት] ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፣ ለዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል” የሚሉት የራእይ 11:15 ቃላት ፍጻሜያቸውን አገኙ። ክርስቶስ እንደነገሰ የወሰደው የመጀመሪያ እርምጃ ሰይጣንንና አጋንንት መላእክቱን ከሰማይ ወደ ምድር አካባቢ ወርውሮ መጣል ነበር። ይህም በመጀመሪያው የዓለም ጦርነትና አብረውት በመጡት መከራዎች መልክ የተከሰተውን ወዮታ አምጥቷል።—ራእይ 12:9, 12, 17

ይህም በምድር ላይ የቀሩት የአዲሱ ፍጥረት ቀሪዎች “ለአሕዛብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ [የተቋቋመችው] የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” በማለት ኢየሱስ ትንቢት የተናገረለትን ሥራ በመፈጸም ሥራ መካፈል እንዳለባቸው እንደ ማሳሰቢያ ሆኖ አገልግሏል። ይህ “መጨረሻ” ምንድን ነው? ኢየሱስ በመቀጠል “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። እነዚህ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር። ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ” በማለት ገልጿል።—ማቴዎስ 24:3-14, 21, 22

የይሖዋ መንፈስ ከአዲሱ ፍጥረቱ የቀሩትን ቅቡዓን በዚች ምድር ላይ ተደርጎ በማያውቅ መጠን በሚካሄደው በዚህ በጣም ሠፊ የሆነ የስብከት ዘመቻ እንዲጠመዱ አነሳስቶአቸዋል። የእነዚህ ቀናተኛ የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር በ1919 ከነበረው ጥቂት ሺህ ተነስቶ በ1930ዎቹ አጋማሽ ላይ 50,000 ያህል ወደመሆን ደርሶአል። በትንቢት እንደተነገረው “ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ።”—ሮሜ 10:18

ለመዳን የሚሰበሰቡት የአዲሱ ፍጥረት ቀሪዎች ብቻ ይሆናሉን? አይደለም። ምክንያቱም በመጨረሻ መኖሪያቸው ሰማይ የሚሆነው መንፈሳዊ እሥራኤላውያንን ብቻ ሳይሆን “አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች” የሆኑ ሌሎችም ጭምር ተሰብስበው እስኪጠናቀቁ ድረስ የአምላክ መላእክት የታላቁን መከራ ነፋሳት እንደሚይዙ ትንቢቱ ይናገራል። የእነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ዕጣ ፈንታስ ምንድነው? የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው “ከታላቁ መከራ” ይወጣሉ።—ራእይ 7:1-4, 9, 14

ደስ የሚለው ነገር 229 ከሚያክሉ አገሮች የተሰባሰቡት ከ4,500,000 በላይ የሆኑት እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ተግተው በመሥራት ላይ ያሉ ምስክሮች በመሆን በቁጥር በጣም ጨምረዋል። ባለፈው ዓመት ሚያዝያ 17 ቀን በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ላይ የተገኙት 11,431,171 ተሰብሳቢዎች ቁጥር እንደሚያመለክተው አሁንም ገና የሚመጡ ሰዎች አሉ። ከእነዚህ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ውስጥ ከወይኑና ከቂጣው ምሳሌ በመካፈል የአዲሱ ፍጥረት ቀሪዎች ክፍል ነን ባይ የሆኑት 8, 683 ብቻ ነበሩ። በዚህ ዘመን የሚካሄደውን ሠፊ የስብከት ሥራ ለመፈጸም እጅግ ብዙ ሰዎች የሆኑት በሚልዮን የሚቆጠሩ ከጎናቸው ቆመው በኅብረት እየሠሩ ነው። (ሶፎንያስ 3:9) ከዚያም በላይ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች ለመጠገን እሥራኤላውያን ያልሆኑ ናታኒም ከካህናት ጋር ኣብረው እንደሠሩ ሁሉ ከእጅግ ብዙ ሰዎች መካከል ጥሩ ሥልጠና ያገኙ ሰዎች ከመንፈሳዊ እሥራኤል ቅቡዓን የአስተዳደር አካል ጋር ጎን ለጎን በመሆን በአስተዳደርና በሌሎችም የኃላፊነት ሥራዎች ላይ እየሠሩ ነው።—ነህምያ 3:22-26

“የአዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር” መፈጠር

ይህ የማሰባሰብ ሥራ ከፍተኛ በሆነ ደስታ ታጅቦአል። ልክ ይሖዋ ይሆናል እንዳለው ተፈጽሞአል። “እነሆ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፤ የቀደሙትን አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም። ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘላለም ሐሤት አድርጉ፣ እነሆ ኢየሩሳሌምን ለሐሤት፣ ሕዝብዋንም ለደስታ እፈጥራለሁና። እኔም በኢየሩሳሌም ደስ ይለኛል፣ ከዚያም ወዲያ የልቅሶ ድምፅና የዋይታ ድምፅ አይሰማባትም።” (ኢሳይያስ 65:17-19) ይሖዋ የፈጠራቸው አዲስ ሰማያት በመጨረሻ በኢየሱስ ክርስቶስና ባለፉት 19 መቶ ዓመታት ከሰው ልጆች መካከል በተውጣጡት ትንሣኤ ያገኙ 144, 000 ሰዎች ተሟልቶ ይቋቋማል። ይህ አዲስ ሰማይ ቃል በቃል በኢየሩሳሌም ላይ ከገዛ ከማንኛውም ምድራዊ መስተዳድር ከሰሎሞን ዘመንም እንኳን ሳይቀር እጅግ በጣም የተለየ ክብራማ መስተዳድር ነው። ይህ አዲስ ሰማይ በራእይ ምዕራፍ 21 ላይ ከአንፀባራቂ ውበቷ ጋር የተገለጸችውን ሰማያዊት ከተማ አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን የሚጨምር ይሆናል።

አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የክርስቶስ መንፈሳዊ ሙሽራ ስትሆን እርሷም ሞተው መንፈሳዊ ትንሣኤ ካገኙ በኋላ ወደ ሰማይ ሄደው ከሙሽራው ጋር የሚተባበሩትን 144, 000 ቅቡዓን ተከታዮቹን ታመለክታለች። እነዚህ የኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮች በራእይ 21:1-4 ላይ “ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ” በመባል የተገለጹ ሲሆን ይህም ማለት በዚህች ምድር ላይ ላሉት የሰው ልጆች በረከትን ለማምጣት አምላክ ይጠቀምባቸዋል ማለት ነው። በዚህም መንገድ “እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ” የሚለው ትንቢት ይፈጸማል።

አምላክ ይህን አዲስ ሰማይ በመፍጠሩ ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን እንችላለን! ይህ የአምላክ መንግሥታዊ ዝግጅት የሰው ልጆችን በጣም ረዥም ለሆነ ጊዜ ሲያሰቃዩ እንደኖሩት ምግባረ ብልሹ አገዛዞች አላፊና ጠፊ ሳይሆን ዘላለማዊና ዘላቂ ይሆናል። አዲስ ፍጥረትና መንፈሳዊ ዘሮቻቸው የሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች አምላክ ቀጥሎ በሰጠው ተስፋ ሐሤት ያደርጋሉ:- “እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ከፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ እንዲሁ ዘራችሁና ስማችሁ ጸንተው ይኖራሉ።”—ኢሳይያስ 66:22

አዲስ ምድር የሚጀምረው በእነዚህ የአዲስ ፍጥረት ቅቡዓን ዘሮች በሆኑት ሰዎች ነው። አዲስ ምድር አዲስ የሆነ ፈሪሃ አምላክ ያለው በምድር ላይ የሚኖር የሰው ልጆች ኅብረተሰብ ነው። በዛሬው ጊዜ በሰብአዊው ኅብረተሰብ መካከል ያለው ጥላቻ፣ ወንጀል፣ ዓመፅ፣ እምነት አጉዳይነትና የፆታ ብልግና በጎ አድራጊ በሆነው አዲስ ሰማይ አመራር ሥር በሚሠራ አዲስ የምድር ኅብረተሰብ ሙሉ በሙሉ መቀየር የሚያስፈልገው መሆኑን በማያሻማ መንገድ ያረጋግጣል። ይሖዋም ይህን ለማድረግ አቅዶአል። አዲስ ሰማያትን እንደፈጠረ ሁሉ የሰላማዊው አዲስ የዓለም ኅብረተሰብ እምብርት እንዲሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎችን በማሰባሰብ አዲስ ምድርንም እየፈጠረ ነው። “ከታላቁ መከራ” በሕይወት የሚተርፈው ይህ ኅብረተሰብ ብቻ ይሆናል።—ራእይ 7:14

ከታላቁ መከራ ቀጥሎ ምን ይመጣል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን? ኢየሱስ አዲሱን ምድር የሚገዙትን አዲስ ሰማያት ለማዋቀር የመጀመሪያዎቹ ለሆኑት ሐዋርያቱ ሲናገር “እውነት እላችኋለሁ፣ እናንተስ የተከተላችሁኝ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለቱ ዙፋን ላይ ትቀመጣላችሁ” በማለት ቃል ገብቶላቸዋል። (ማቴዎስ 19:28) የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም 144,000 አባሎች በሙሉ ከኢየሱስ ጋር በሰው ልጆች ላይ አብረው ይፈርዳሉ። በዚያን ጊዜ ሰብአዊው ኅብረተሰብ የተመሠረተባቸው ራስ ወዳድነትና ጥላቻ በፍቅር ይተካሉ። የጎሣ የዘርና የብሔርተኝነት ችግሮች ይወገዳሉ። ትንሣኤም የምንወዳቸውን የሞቱብንን ሰዎች በየተራ ወደ ሕይወት መልሶ ያመጣቸዋል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ታማኝ የሰው ልጆች ወደ ገነትነት በተለወጠች ምድር ላይ ለዘላለም በመኖር ከፍ ወዳለ የኑሮ ደረጃ የተሻገረ አንድ ትልቅ ቤተሰብ ይሆናሉ።

ይህም ተምኔታዊ አስተሳሰብ ወይም ልብ ወለድ ተረት አይደለም። ‘እንደ ተስፋ ቃሉ የምንጠብቃቸው ጽድቅ የሚኖርባቸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ዘላቂነት ያላቸው ፍጥረቶች ይሆናሉ! (2 ጴጥሮስ 3:13) በእርግጥ ይህ ተስፋ “እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” ባለውና “እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው” በማለት ጨምሮ ቃል በገባው አምላክ የተሰጠ አስደናቂና ዕጹብ ድንቅ የሆነ ተስፋ ነው።—ራእይ 21:5

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ