የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • በፍርድ ዙፋኑ ፊት የምትቀርበው እንዴት ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—1995 | ጥቅምት 15
    • በፍርድ ዙፋኑ ፊት የምትቀርበው እንዴት ነው?

      “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል።”—ማቴዎስ 25:31

      1–3. ትክክለኛ ፍርድ በማግኘት ረገድ ብሩህ አመለካከት እንድንይዝ የሚያደርገን ምንድን ነው?

      ‘ተፈረደበት ወይስ ተፈረደለት?’ ብዙዎች ፍርድ ቤት ቀርቦ ሲታይ ስለ ነበረ አንድ ጉዳይ ሲሰሙ የሚጠይቁት ጥያቄ ይህ ነው። ዳኞችና ሕግ አዋቂዎች ሐቀኞች ለመሆን ይሞክሩ ይሆናል፤ ሆኖም ብዙውን ጊዜ ትክክለኛ ፍርድ ይሰጣሉን? በፍርድ ቤቶች ስለሚፈጸመው የፍርድ መጓደልና አድልዎ አልሰማችሁምን? በሉቃስ 18:1–8 ላይ ከሚገኘው የኢየሱስ ምሳሌ ለመገንዘብ እንደምንችለው እንዲህ ዓይነቱ የፍርድ መጓደል አዲስ ነገር አይደለም።

      2 ሰዎች በሚሰጡት ፍርድ የደረሰብህ ነገር ምንም ይሁን ምን ኢየሱስ ምን ብሎ ሐሳቡን እንዳጠቃለለ ልብ በል፦ “እግዚአብሔር . . . ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? እላችኋለሁ፣ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?”

      3 አዎን፣ በመጨረሻ ይሖዋ አገልጋዮቹ ፍትሕ እንዲያገኙ ያደርጋል። በተለይ በአሁኑ ጊዜ የምንኖረው በዚህ የነገሮች ሥርዓት “የመጨረሻ ቀን” ውስጥ ስለሆነ ኢየሱስም በጉዳዩ ውስጥ ይገባበታል። ይሖዋ በቅርቡ ክፋትን ከምድር ላይ ጠራርጎ ለማጥፋት በኃያል ልጁ ይጠቀማል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ 2 ተሰሎንቄ 1:7, 8፤ ራእይ 19:11–16) ብዙውን ጊዜ የበጎችና የፍየሎች ምሳሌ ተብሎ ከሚጠራው ኢየሱስ ከሰጣቸው ከመጨረሻዎቹ ምሳሌዎች አንዱ በሆነው ምሳሌ ላይ ኢየሱስ ስለሚጫወተው ሚና ማስተዋል ልናገኝ እንችላለን።

      4. ከዚህ በፊት የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ የሚፈጸምበትን ጊዜ የተረዳነው እንዴት ነበር? ሆኖም በአሁኑ ጊዜ በዚህ ምሳሌ ላይ ትኩረት የምናደርገው ለምንድን ነው? (ምሳሌ 4:18)

      4 ይህ ምሳሌ ኢየሱስ በ1914 ንጉሥ ሆኖ በዙፋኑ ላይ ስለ መቀመጡ እንደሚናገርና ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በበጎች ለተመሰሉት ሰዎች ዘላለማዊ ሕይወት፣ በፍየሎች ለተመሰሉት ሰዎች ደግሞ ዘላለማዊ ጥፋት የሚያሰጥ ፍርድ በመፍረድ ላይ እንዳለ ከረጅም ጊዜ በፊት ተረድተን ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ምሳሌ እንደገና መመርመሩ ምሳሌው ስለሚፈጸምበት ጊዜና ስለሚገልጸው ነገር አዲስ ግንዛቤ አስገኝቷል። ይህ አዲስ ግንዛቤ የስብከት ሥራችንን አስፈላጊነትና ሰዎች የሚሰጡትን ምላሽ ወሳኝነት ያጠናክራል። ምሳሌውን በጥልቅ ለመረዳት የሚያስችል መሠረት እንዲኖረን መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋና ኢየሱስ በንጉሥነታቸውና በፈራጅነታቸው የሚያከናውኑትን ነገር በተመለከተ ምን እንደሚገልጽ እንመልከት።

      ይሖዋ በታላቅ ፈራጅነቱ የሚያከናውነው ተግባር

      5, 6. ይሖዋ ንጉሥም ዳኛም እንደሆነ አድርገን መመልከታችን ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

      5 ይሖዋ ከፍጥረታቱ ሁሉ የበላይ ሆኖ አጽናፈ ዓለምን ይገዛል። መጀመሪያና መጨረሻ ስለሌለው “የዘላለም ንጉሥ” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:17 አዓት ፤ መዝሙር 90:2, 4፤ ራእይ 15:3) ሕጎችን ወይም ሥርዓቶችን የማውጣትና የማስፈጸም ሥልጣን አለው። ይሁን እንጂ ሥልጣኑ ዳኝነትንም ይጨምራል። ኢሳይያስ 33:22 “እግዚአብሔር ፈራጃችን ነው፣ እግዚአብሔር ሕግን ሰጪያችን ነው፣ እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው” ይላል።

      6 የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋ የተለያዩ የፍርድ ጉዳዮችን ተመልክቶ እንደሚፈርድ ከረጅም ጊዜ በፊት ተገንዝበው ነበር። ለምሳሌ ያህል “የምድር ሁሉ ፈራጅ” የሰዶምና የገሞራን ክፋት ካመዛዘነ በኋላ ነዋሪዎቹ ጥፋት እንደሚገባቸው ከመፍረዱም በላይ ያን የጽድቅ ፍርድ አስፈጽሟል። (ዘፍጥረት 18:20–33፤ ኢዮብ 34:10–12) ይሖዋ ምን ጊዜም ፍርዶቹን የሚያስፈጽም ጻድቅ ዳኛ እንደሆነ ማወቃችን ምንኛ ሊያጽናናን ይገባል!

      7. ይሖዋ ከእስራኤል ጋር በነበረው ግንኙነት የዳኝነት ተግባር ያከናወነው እንዴት ነው?

      7 በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ይሖዋ አንዳንድ ጊዜ በቀጥታ ፍርድ ይሰጥ ነበር። በዚያ ወቅት ብትኖር ኖሮ አንድ ፍጹም የሆነ ዳኛ የፍርድ ጉዳዮችን እንደሚመለከት በማወቅህ አትጽናናም ነበርን? (ዘሌዋውያን 24:10–16፤ ዘኁልቁ 15:32–36፤ 27:1–11) በተጨማሪም አምላክ ለፍርድ የሚያገለግሉ ጥሩ የአቋም ደረጃዎችን የያዙ “የፍርድ ውሳኔዎችን” ሰጥቷቸዋል። (ዘሌዋውያን 25:18, 19 አዓት ፤ ነህምያ 9:13፤ መዝሙር 19:9, 10፤ 119:7, 75, 164፤ 147:19, 20) እሱ “የምድር ሁሉ ፈራጅ” ስለሆነ ጉዳዩ ሁላችንንም ይነካናል።—ዕብራውያን 12:23

      8. ዳንኤል ከዚህ ጉዳይ ጋር የሚዛመድ ምን ራእይ ተመልክቷል?

      8 ይህን ጉዳይ በተመለከተ አንድ “የዓይን ምሥክር” የሰጠው ምሥክርነት አለን። ነቢዩ ዳንኤል መንግሥታትን ወይም ነገሥታትን የሚያመለክቱ አስፈሪ አራዊትን በራእይ ተመልክቶ ነበር። (ዳንኤል 7:1–8, 17) ከዚህም በላይ “ዙፋኖችም እስኪዘረጉ ድረስ አየሁ፣ በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ . . . ነበረ” ብሏል። (ዳንኤል 7:9) ዳንኤል ዙፋኖችንና ‘በዘመናት የሸመገለው [ይሖዋ] ተቀምጦ ’ እንደተመለከተ ልብ በል። ‘ዳንኤል እዚህ ላይ እየመሠከረ ያለው አምላክ መንገሡን ነውን?’ በማለት ራስህን ጠይቅ።

      9. በዙፋን ላይ ‘የመቀመጥ’ አንዱ ትርጉም ምንድን ነው? ምሳሌዎችን ስጥ።

      9 መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጊዜ በእንዲህ ዓይነቱ አነጋገር ስለሚጠቀም አንድ ሰው በዙፋን ላይ እንደ “ተቀመጠ” ስናነብ ይህ ሰው ነገሠ ብለን እናስብ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ “[ዘምሪ] ንጉሥም በሆነ ጊዜ፣ በዙፋኑም በተቀመጠ ጊዜ . . .” በማለት ይናገራል። (1 ነገሥት 16:11፤ 2 ነገሥት 10:30፤ 15:12፤ ኤርምያስ 33:17) አንድ መሲሐዊ ትንቢት “በዙፋኑም ላይ ተቀምጦ ይነግሣል” ይላል። ስለዚህ ‘በዙፋን ላይ መቀመጥ’ መንገሥ ማለት ሊሆን ይችላል። (ዘካርያስ 6:12, 13፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ይሖዋ በዙፋን ላይ እንደ ተቀመጠ ንጉሥ ተደርጎ ተገልጿል። (1 ነገሥት 22:19፤ ኢሳይያስ 6:1፤ ራእይ 4:1–3) እሱ “የዘላለም ንጉሥ” ነው። ሆኖም አንድ የተለየ የሉዓላዊነቱን ገጽታ በሚያረጋግጥበት ወቅት በአዲስ መልክ በዙፋን ላይ የተቀመጠ ያህል ንጉሥ ሆነ ሊባል ይችላል።—1 ዜና መዋዕል 16:1, 31፤ ኢሳይያስ 52:7፤ ራእይ 11:15–17፤ 15:3፤ 19:1, 2, 6

      10. የእስራኤላውያን ነገሥታት ዋንኛ ተግባር ምን ነበር? በምሳሌ አስረዳ።

      10 ይሁን እንጂ በጣም አስፈላጊው ነጥብ የሚከተለው ነው፦ የጥንት ነገሥታት ዋና ተግባር ክሶችን መስማትና ፍርድ መስጠት ነበር። (ምሳሌ 29:14) ሁለት ሴቶች ‘ሕፃኑ የእኔ ነው’ ብለው በተከራከሩ ጊዜ ሰሎሞን የሰጠውን ጥበብ የተሞላበት ፍርድ አስታውስ። (1 ነገሥት 3:16–28፤ 2 ዜና መዋዕል 9:8) ከመንግሥታዊ ሕንፃዎቹ አንዱ “የሚፈርድበት ዙፋን ያለበት” ሲሆን ሕንፃው “ፍርድ ቤት” ተብሎም ይጠራ ነበር። (1 ነገሥት 7:7) ኢየሩሳሌም ‘ዙፋኖች ለፍርድ የተቀመጡባት’ ቦታ እንደሆነች ተደርጋ ተገልጻለች። (መዝመር 122:5) ‘በዙፋን ላይ መቀመጥ’ ማለት መፍረድ ማለትም ጭምር እንደሆነ የተረጋገጠ ነው።—ዘጸአት 18:13፤ ምሳሌ 20:8

      11, 12. (ሀ) በዳንኤል ምዕራፍ 7 ላይ ይሖዋ በዙፋን ላይ ስለ መቀመጡ የሚናገረው ሐሳብ ትርጉም ምንድን ነው? (ለ) ሌሎች ጥቅሶች ይሖዋ ለፍርድ እንደ ተቀመጠ የሚያረጋግጡት እንዴት ነው?

      11 አሁን ዳንኤል ‘በዘመናት የሸመገለው ተቀምጦ ’ ወዳየበት ትዕይንት እንመለስ። ዳንኤል 7:10 በዚህ ላይ ሲያክል “ፍርድም ሆነ፣ መጻሕፍትም ተገለጡ” ይላል። አዎን፣ በዘመናት የሸመገለው ስለ ዓለም አገዛዝና የሰው ልጅ የተባለው ለመግዛት ብቃት ያለው ስለ መሆኑ ፍርድ ለመስጠት ተቀምጦ ነበር። (ዳንኤል 7:13, 14) ከዚያም ‘በዘመናት የሸመገለው መጣ፤ ለልዑል ቅዱሳንም ተፈረደላቸው ’ የሚል እናነባለን። እነዚህ ቅዱሳን ከሰው ልጅ ጋር ለመግዛት ብቁ እንደሆኑ ተፈረደላቸው። (ዳንኤል 7:22) በመጨረሻም ይህ ‘ችሎት’ የፍርድ ጉዳዮችን ‘ማየቱን በመቀጠል’ በመጨረሻው የዓለም ኃያል መንግሥት ላይ በየነበት።—ዳንኤል 7:26a

      12 በዚህም ምክንያት ዳንኤል አምላክ ‘በዙፋን ላይ ተቀምጦ’ መመልከቱ አምላክ ፍርድ ለመስጠት መምጣቱን ያመለክታል። ቀደም ሲል ዳዊት “[ይሖዋ ሆይ] ፍርዴንና በቀሌን አድርገህልኛልና፤ ጽድቅን እየፈረድህ በዙፋንህ ላይ ተቀመጥህ” በማለት ዘምሮ ነበር። (መዝሙር 9:4, 7) በተጨማሪም ኢዩኤል “አሕዛብ ይነሡ፣ ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆም ይውጡ፤ በዙሪያ ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ እፈርድ ዘንድ [እኔ ይሖዋ] በዚያ እቀመጣለሁና” በማለት ጽፏል። (ኢዩኤል 3:12፤ ከኢሳይያስ 16:5 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስና ጳውሎስ ሰዎች ክሶችን ለመስማትና ፍርድ ለመስጠት በተቀመጡባቸው ቦታዎች ለፍርድ ቀርበው ነበር።b—ዮሐንስ 19:12–16፤ ሥራ 23:3፤ 25:6

      የኢየሱስ ሥልጣን

      13, 14. (ሀ) የአምላክ ሕዝቦች ኢየሱስ እንደ ነገሠ ምን ማረጋገጫ አላቸው? (ለ) ኢየሱስ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው መቼ ነው? ኢየሱስ ከ33 እዘአ ጀምሮ በመግዛት ላይ ያለው በምን መንገድ ነው?

      13 ይሖዋ ንጉሥም ዳኛም ነው። ኢየሱስስ? የኢየሱስን ልደት ያበሰረው መልአክ “ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤. . . ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም” ብሏል። (ሉቃስ 1:32, 33) ኢየሱስ የዳዊት ሥርወ መንግሥት ዘላለማዊ ወራሽ ይሆናል። (2 ሳሙኤል 7:12–16) ዳዊት “እግዚአብሔር ጌታዬን፦ ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው። እግዚአብሔር የኃይልን በትር ከጽዮን ይልክልሃል፤ በጠላቶችህም መካከል ግዛ” ስላለ ኢየሱስ የሚገዛው ከሰማይ ሆኖ ነው።—መዝሙር 110:1–4

      14 ይህ የሚሆነው መቼ ነው? ኢየሱስ ሰው በነበረበት ወቅት ንጉሥ ሆኖ አልገዛም። (ዮሐንስ 18:33–37) በ33 እዘአ ሞቶ ከተነሣ በኋላ ወደ ሰማይ አረገ። ዕብራውያን 10:12 “እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ” ይላል። ኢየሱስ ምን ሥልጣን ነበረው? “[አምላክ] ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይ . . . በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው . . . ከሁሉም በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው።” (ኤፌሶን 1:20–22) ኢየሱስ በዚያ ወቅት በክርስቲያኖች ላይ ንጉሣዊ ሥልጣን ስለ ነበረው ጳውሎስ “እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፣ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ሥርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን” በማለት ሊጽፍ ችሏል።—ቆላስይስ 1:13፤ 3:1

      15, 16. (ሀ) ኢየሱስ በ33 እዘአ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ አልሆነም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ በአምላክ መንግሥት ላይ መግዛት የጀመረው መቼ ነው?

      15 ሆኖም በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በአሕዛብ ላይ ንጉሥና ዳኛ አልሆነም። በአምላክ መንግሥት ላይ ንጉሥ ሆኖ የሚሾምበትን ጊዜ እየተጠባበቀ በአምላክ አጠገብ ተቀምጦ ነበር። ጳውሎስ ስለ እሱ “ከመላእክት፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ ከቶ ለማን ብሎአል?” ሲል ጽፏል።—ዕብራውያን 1:13

      16 የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ በማይታዩት ሰማያት የአምላክ መንግሥት ገዢ በሆነበት በ1914 በመጠባበቅ የሚያሳልፈው ጊዜ እንዳለቀ የሚጠቁሙ ብዙ መረጃዎችን አሳትመው አውጥተዋል። ራእይ 11:15, 18 “የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፣ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣል።” “አሕዛብ ተቆጡ፣ ቁጣህም መጣ” ይላል። አዎን፣ ብሔራት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት እርስ በርሳቸው በመዋጋት ቁጣቸውን ገልጸዋል። (ሉቃስ 21:24) ከ1914 ጀምሮ ያየናቸው ጦርነቶች፣ የመሬት መንቀጥቀጦች፣ መቅሠፍቶች፣ የምግብ እጥረቶች እና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች ነገሮች ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደሆነና የመጨረሻው የዓለም ፍጻሜ መቃረቡን ያረጋግጣሉ።—ማቴዎስ 24:3–14

      17. እስካሁን ድረስ የትኞቹን ቁልፍ ነጥቦች ተረድተናል?

      17 ትንሽ ለመከለስ ያህል፦ አምላክ በዙፋን ላይ ንጉሥ ሆኖ ተቀምጧል ሊባል ይችላል፣ ሆኖም በሌላ መንገድ ደግሞ በዙፋኑ ላይ ለፍርድ ሊቀመጥ ይችላል። በ33 እዘአ ኢየሱስ በአምላክ ቀኝ የተቀመጠ ሲሆን አሁን ደግሞ የመንግሥቱ ንጉሥ ሆኗል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ የሚገኘው ኢየሱስ በዳኝነት ሥራ እያገለገለ ነውን? ከዚህም በላይ በተለይ በዚህ ጊዜ ይህ ጉዳይ ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው?

      18. ኢየሱስ ዳኛም ጭምር እንደሚሆን ምን ማረጋገጫ አለ?

      18 ፈራጆችን የመሾም መብት ያለው ይሖዋ የእርሱን የአቋም ደረጃዎች ያሟላውን ኢየሱስን ለዳኝነት መርጦታል። ኢየሱስ በመንፈሳዊ ሕያው የሆኑ ሰዎችን በተመለከተ ሲናገር “ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም” ባለ ጊዜ ይህን አሳይቷል። (ዮሐንስ 5:22) ሆኖም ኢየሱስ በሕያዋንና በሙታን ላይ ስለሚፈርድ ፍርዱ ከዚህ የበለጠ ነገርንም ይጨምራል። (ሥራ 10:42፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:1) ጳውሎስ በአንድ ወቅት “[አምላክ] ቀን ቀጥሮአልና፣ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል” ብሏል።—ሥራ 17:31፤ መዝሙር 72:2–7

      19. ኢየሱስ በዳኝነት ተቀምጧል ብሎ መናገር ትክክል የሚሆነው ለምንድን ነው?

      19 ታዲያ የተወሰነ የዳኝነት ሥልጣን ይዞ በክብራማ ዙፋን ላይ ተቀምጧል ብለን መደምደማችን ትክክል ይሆናልን? አዎን። ኢየሱስ ለሐዋርያት “እናንተስ የተከተላችሁኝ፣ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ ፣ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 19:28፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ የመንግሥቱ ንጉሥ ቢሆንም እንኳ በማቴዎስ 19:28 ላይ የተጠቀሰው ተጨማሪ ሥራው በሺው ዓመት ለዳኝነት በዙፋን ላይ መቀመጥን ይጨምራል። በዚያን ጊዜ በመላው የሰው ዘር ማለትም በጻድቁም ሆነ በኃጢአተኛው ላይ ይፈርዳል። (ሥራ 24:15) ከዘመናችን ጋር በሚዛመዱትና ሕይወታችንን በሚነኩት የኢየሱስ ምሳሌዎች ላይ ስናተኩር ይህን ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው።

      ምሳሌው ምን ይላል?

      20, 21. የኢየሱስ ሐዋርያት የጠየቁት ዘመናችንን የሚመለከት ጥያቄ የትኛው ነው? ይህስ ወደ የትኛው ጥያቄ ይመራል?

      20 ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሐዋርያቱ “‘እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ? የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምን ይሆናል?’ ብለው ጠየቁት።” (ማቴዎስ 24:3 አዓት) ኢየሱስ ‘መጨረሻው ከመምጣቱ’ በፊት በምድር ላይ የሚፈጸሙትን በጣም አስፈላጊ የሆኑ ሁኔታዎች አስቀድሞ ተናገረ። ይህ መጨረሻ ከመምጣቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ብሔራት “የሰው ልጅን በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል።”—ማቴዎስ 24:14, 29, 30

      21 የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ በእነዚህ ብሔራት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ምን ዋጋ ይቀበላሉ? “የሰው ልጅ በከብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል” በማለት ከሚጀምረው ስለ በጎችና ፍየሎች ከሚናገረው ምሳሌ መልሱን ለማግኘት እንሞክር።—ማቴዎስ 25:31, 32

      22, 23. የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ በ1914 መፈጸም አለመጀመሩን የሚያመለክቱት የትኞቹ ነጥቦች ናቸው?

      22 ኢየሱስ በ1914 በንጉሣዊ ሥልጣኑ ላይ እንደ ተቀመጠ ከብዙ ጊዜ በፊት ተረድተን ነበር፤ ታዲያ ይህ ምሳሌ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመፈጸም ላይ ነውን? ማቴዎስ 25:34 ኢየሱስን እንደ ንጉሥ አድርጎ ስለሚገልጸው ይህ ምሳሌ ከ1914 ጀምሮ መፈጸም ጀምሯል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው። ይሁን እንጂ ከዚያ ጊዜ በኋላ ወዲያውኑ የተሰጠው ፍርድ ምን ነበር? “በአሕዛብ ሁሉ” ላይ ፍርድ አልተሰጠም። ከዚህ ይልቅ ‘የእግዚአብሔር ቤት’ ነን በሚሉት ላይ ትኩረቱን አድርጓል። (1 ጴጥሮስ 4:17) ከሚልክያስ 3:1–3 ጋር በሚስማማ መንገድ ኢየሱስ እንደ የይሖዋ መልእክተኛ በመሆን በምድር ላይ በቀሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ላይ ፍርድ በመስጠት ምርመራ አካሂዷል። በተጨማሪም በሐሰት “የእግዚአብሔር ቤት” ነኝ በምትለዋ በሕዝበ ክርስትና ላይ ፍርድ የሚሰጥበት ጊዜ ነበር።c (ራእይ 17:1, 2፤ 18:4–8) ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜ ወይም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ አሕዛብን ሁሉ በጎችና ፍየሎች ናችሁ በማለት የመጨረሻ ፍርድ ለመስጠት እንደተቀመጠ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም።

      23 ኢየሱስ በምሳሌው ውስጥ የሚያከናውነውን ተግባር ከመረመርን በመጨረሻ በአሕዛብ ሁሉ ላይ ሲፈርድ እንመለከተዋለን። ምሳሌው ባለፉት አሥርተ ዓመታት የሞቱት ሰዎች ሁሉ ዘላለማዊ ሞት ወይም ሕይወት እየተፈረደባቸው ወይም እየተፈረደላቸው ይህ ፍርድ ለብዙ ዓመታት እንደሚቀጥል አያመለክትም። በቅርብ ዓመታት የሞቱ አብዛኞቹ ሰዎች ወደ ሰው ልጆች ተራ መቃብር የሄዱ ይመስላል። (ራእይ 6:8፤ 20:13) ሆኖም ምሳሌው ኢየሱስ በሕይወት የሚኖሩትንና የፍርድ ውሳኔውን የሚቀበሉትን “አሕዛብን ሁሉ” የሚዳኝበትን ጊዜ ይገልጻል።

      24. የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼ ነው?

      24 በሌላ አባባል ይህ ምሳሌ የሰው ልጅ በክብሩ የሚመጣበትን የወደፊት ጊዜ ያመለክታል። በዚያን ጊዜ በሕይወት በሚኖሩ ሰዎች ላይ ለመፍረድ ይቀመጣል። የሚሰጠው ፍርድ ባሳዩት ባሕርይ ላይ የተመሠረተ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ‘በጻድቁና በኃጢአተኛው መካከል ያለው ልዩነት’ በግልጽ ይታያል። (ሚልክያስ 3:18) ፍርዱ የሚሰጠውም ሆነ የሚፈጸመው በአንድ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በግለሰቦች ላይ በሚታየው ነገር መሠረት ትክክለኛ የፍርድ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል።—በተጨማሪም 2 ቆሮንቶስ 5:10ን ተመልከት።

      25. የሰው ልጅ በክብራማ ዙፋን መቀመጡን በተመለከተ ማቴዎስ 25:31 የሚገልጸው ምንድን ነው?

      25 ይህም ማለት በማቴዎስ 25:31 ላይ እንደ ተገለጸው ኢየሱስ ‘በክብሩ ዙፋን ላይ ተቀምጦ’ የሚሰጠው ፍርድ ይህ ኃያል ንጉሥ ወደፊት በአሕዛብ ላይ ፍርድ ለመስጠትና ያን ፍርድ ለማስፈጸም የሚቀመጥበትን ጊዜ ያመለክታል። አዎን፣ በማቴዎስ 25:31–33, 46 ላይ ኢየሱስን በተመለከተ የተገለጸው የፍርድ ትዕይንት በመግዛት ላይ ያለው በዘመናት የሸመገለው ንጉሥ የዳኝነት ተግባሩን ለማከናወን መቀመጡን ከሚናገረው በዳንኤል ምዕራፍ 7 ላይ ካለው ትዕይንት ጋር የሚመሳሰል ነው።

      26. ይህን ምሳሌ በተመለከተ ምን አዲስ ግንዛቤ ተገኝቷል?

      26 የበጎቹንና የፍየሎቹን ምሳሌ በዚህ መንገድ መረዳት በበጎቹና በፍየሎቹ ላይ ፍርድ የሚሰጠው ወደፊት እንደሆነ ያሳያል። በማቴዎስ 24:29, 30 ላይ የተጠቀሰው “መከራ” ከፈነዳና የሰው ልጅ ‘በክብሩ ከመጣ’ በኋላ የሚፈጸም ነገር ነው። (ከማርቆስ 13:24–26 ጋር አወዳድር።) ከዚያ በኋላ በጠቅላላው የነገሮች ሥርዓት መጨረሻ ወቅት ኢየሱስ ችሎት ላይ ተቀምጦ ለአንዳንዶቹ ሲፈርድላቸው በሌሎች ላይ ደግሞ የጥፋት ፍርድ ይበይንባቸዋል።—ዮሐንስ 5:30፤ 2 ተሰሎንቄ 1:7–10

      27. የኢየሱስን የመጨረሻ ምሳሌ በማወቅ ረገድ ስለምን ነገር ፍላጎት ሊያድርብን ይገባል?

      27 ይህም የኢየሱስ ምሳሌ የሚፈጸምበትን ማለትም በበጎቹና በፍየሎቹ ላይ ፍርድ የሚሰጥበትን ጊዜ በተመለከተ ያለንን ግንዛቤ ከፍ ያደርግልናል። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት የምንሰብከውን እኛን የሚነካን እንዴት ነው? (ማቴዎስ 24:14) ሥራችንን አቅልለን እንድንመለከት ያደርገናል ወይስ ከባድ ኃላፊነት ይጥልብናል? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እኛ በጉዳዩ እንዴት እንደምንነካ እንመለከታለን።

  • የበጎቹና የፍየሎቹ የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—1995 | ጥቅምት 15
    • የበጎቹና የፍየሎቹ የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው?

      “እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል።” —ማቴዎስ 25:32

      1, 2. የበጎቹንና የፍየሎቹን ምሳሌ ለማወቅ ፍላጎት ሊያድርብን የሚገባው ለምንድን ነው?

      ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥም በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ አስተማሪ ነበር። (ዮሐንስ 7:46) ከማስተማሪያ ዘዴዎቹ አንዱ በምሳሌዎች መጠቀም ነበር። (ማቴዎስ 13:34, 35) እነዚህ ምሳሌዎች ቀላል ቢሆኑም ጥልቅ መንፈሳዊና ትንቢታዊ እውነቶችን በማስተላለፍ ረገድ ኃይለኛ ናቸው።

      2 ኢየሱስ በሰጠው የበጎችና የፍየሎች ምሳሌ ላይ “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ” በማለት አንድ የተለየ ሥልጣን ይዞ እርምጃ የሚወስድበትን ጊዜ ጠቁሟል። (ማቴዎስ 25:31) ኢየሱስ “እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ? የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምን ይሆናል?” ለሚለው ጥያቄ የሰጠውን መልስ የደመደመው በዚህ ምሳሌ ስለሆነ ይህ ነገር የማወቅ ፍላጎት ሊያሳድርብን ይገባል። (ማቴዎስ 24:3 አዓት) ይሁን እንጂ ይህ ለእኛ ምን ትርጉም ይኖረዋል?

      3. ኢየሱስ ቀደም ሲል ባቀረበው ንግግሩ ላይ ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ ወዲያውኑ ምን ይሆናል ብሎ ነበር?

      3 ኢየሱስ ታላቁ መከራ ከፈነዳ “በኋላ ወዲያው” እንደሚከሰቱ የምንጠብቃቸውን አስደንጋጭ ሁኔታዎች አስቀድሞ ተናግሯል። በዚያን ጊዜ “የሰው ልጅ ምልክት” ይታያል ብሏል። ይህ ሁኔታ “የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ” የሚያዩትን “የምድር ወገኖች” በከፍተኛ ደረጃ ይነካል። የሰው ልጅ “ከመላእክቱ” ጋር ይመጣል። (ማቴዎስ 24:21, 29–31)a የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ የሚፈጸመው እንዴት ነው? ዘመናዊ መጽሐፍ ቅዱሶች በምዕራፍ 25 ውስጥ ያስቀምጡት እንጂ ይህ ምሳሌ ኢየሱስ ለቀረበለት ጥያቄ የሰጠው መልስ ክፍል ሲሆን በክብሩ ስለሚመጣበት ጊዜ ተጨማሪ ማብራሪያ የሚገኝበትና “በአሕዛብ ላይ” በመፍረድ ሥራው ላይ የሚያተኩር ነው።—ማቴዎስ 25:32

      በምሳሌው ውስጥ የተገለጹት

      4. በበጎቹና በፍየሎቹ ምሳሌ መጀመሪያ ላይ ስለ ኢየሱስ የተጠቀሰው ምንድን ነው? ሌሎችስ እነማን ተጠቅሰዋል?

      4 ኢየሱስ ምሳሌውን የጀመረው ‘የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ’ በማለት ነው። “የሰው ልጅ” ማን እንደሆነ ሳታውቅ አትቀርም። የወንጌል ጸሐፊዎች ብዙውን ጊዜ የሰው ልጅ የሚለውን አጠራር ኢየሱስን ለመግለጽ ይጠቀሙበታል። ኢየሱስ ራሱ እንኳ ራሱን የሰው ልጅ ብሎ የጠራው “የሰው ልጅ የሚመስል” “ግዛትና ክብር መንግሥትም” ለመቀበል በዘመናት ወደ ሸመገለው እንደ ቀረበ የሚገልጸውን የዳንኤል ራእይ በአእምሮው ይዞ እንደ ነበረ አያጠራጥርም። (ዳንኤል 7:13, 14፤ ማቴዎስ 26:63, 64፤ ማርቆስ 14:61, 62) በዚህ ምሳሌ ውስጥ በዋነኛነት የተጠቀሰው ኢየሱስ ቢሆንም ሌሎችም አሉ። በማቴዎስ 24:30, 31 ላይ እንደ ተገለጸው ቀደም ሲል በዚህ ንግግሩ ውስጥ የሰው ልጅ ‘በኃይልና በብዙ ክብር ሲመጣ’ መላእክት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ተናግሮ ነበር። በተመሳሳይም የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ ኢየሱስ ‘በክብሩ ዙፋን ላይ’ ለፍርድ ‘ሲቀመጥ’ መላእክት ከእሱ ጋር እንደሚኖሩ ያሳያል። (ከማቴዎስ 16:27 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ ዳኛውና መላእክቱ በሰማይ ስለሆኑ በምሳሌው ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎች በሰማይ ናቸውን?

      5. የኢየሱስን “ወንድሞች” ለይተን ልናውቃቸው የምንችለው እንዴት ነው?

      5 ምሳሌውን ስንመለከት ለይተን ልናውቃቸው የሚገቡን ሦስት ቡድኖች እንዳሉ እንረዳለን። ከበጎችና ከፍየሎች በተጨማሪ የሰው ልጅ በጎቹንና ፍየሎቹን ለማወቅ ወሳኝ የሆነውን ሦስተኛውን ቡድን አክሏል። ኢየሱስ የዚህ ሦስተኛ ቡድን አባላት መንፈሳዊ ወንድሞቹ እንደሆኑ ገልጿል። (ማቴዎስ 25:40, 45) ኢየሱስ “የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፣ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነው” ስላለ እነዚህ ሰዎች የእሱ እውነተኛ ተከታዮች መሆን ይኖርባቸዋል። (ማቴዎስ 12:50፤ ዮሐንስ 20:17) ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ በማድረግ ጳውሎስ “የአብርሃም ዘር” ክፍልና የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆኑ ክርስቲያኖች ጽፏል። ጳውሎስ እነዚህን ሰዎች የኢየሱስ “ወንድሞች” እና ‘የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች’ በማለት ጠርቷቸዋል።—ዕብራውያን 2:9 እስከ 3:1፤ ገላትያ 3:26, 29

      6. ከኢየሱስ ወንድሞች ውስጥ “ከሁሉ የሚያንሱ” የተባሉት እነማን ናቸው?

      6 ኢየሱስ ከእነዚህ ወንድሞቹ ውስጥ ‘ከሁሉ የሚያንሱትን’ የጠቀሰው ለምንድን ነው? እነዚህ ቃላት ሐዋርያት ቀደም ሲል እሱ ሲናገር የሰሙትን ነገር ያስተጋባሉ። ኢየሱስ ከእሱ በፊት በመሞቱ ምክንያት ምድራዊ ተስፋ ያለውን መጥምቁ ዮሐንስን ሰማያዊ ሕይወት ከሚያገኙት ሰዎች ጋር ሲያነጻጽር “ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል” ብሏል። (ማቴዎስ 11:11) ወደ ሰማይ ከሚሄዱት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እንደ ሐዋርያት በጉባኤ ውስጥ ትልቅ ቦታ ሲኖራቸው ሌሎቹ ደግሞ አነስተኛ ቦታ ሊኖራቸው ይችላል። ሆኖም ሁሉም የኢየሱስ መንፈሳዊ ወንድሞች ናቸው። (ሉቃስ 16:10፤ 1 ቆሮንቶስ 15:9፤ ኤፌሶን 3:8፤ ዕብራውያን 8:11) ስለዚህ አንዳንዶቹ በምድር ላይ ሳሉ ከቁጥር የማይገቡ ቢመስሉም እንኳ ወንድሞቹ ስለ ነበሩ በጥሩ ሁኔታ መያዝ ነበረባቸው።

      በጎቹና ፍየሎቹ እነማን ናቸው?

      7, 8. ኢየሱስ በጎቹን በተመለከተ ምን ብሏል? በመሆኑም እነሱን በተመለከተ ምን መደምደሚያ ላይ ልንደርስ እንችላለን?

      7 በበጎች ላይ የሚሰጠውን ፍርድ በተመለከተ እንዲህ የሚል እናነባለን፦ “[ኢየሱስም] በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ እናንተ የአባቴ ብሩካን፣ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፣ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፣ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፣ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፣ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፣ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና። ጻድቃንም መልሰው ይሉታል፦ ጌታ ሆይ፣ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን? ንጉሡም መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል።”—ማቴዎስ 25:34–40

      8 ክብርና ሞገስ አግኝተው በኢየሱስ ቀኝ ለመቆም ብቁ እንደሆኑ የተፈረደላቸው በጎች አንድን የሰዎች ቡድን እንደሚያመለክቱ ግልጽ ነው። (ኤፌሶን 1:20 የ1980 ትርጉም፤ ዕብራውያን 1:3) ለዚህ የበቁት ምን ስላደረጉ ነው? ይህን ያደረጉትስ መቼ ነው? ኢየሱስ በታመመበትም ሆነ በታሰረበት ወቅት እሱን በመርዳት በደግነት፣ በአክብሮትና በልግስና ምግብ፣ መጠጥ እንዲሁም ልብስ እንደ ሰጡት ተናግሯል። በጎቹ እነዚህን ነገሮች ለኢየሱስ እንዳላደረጉለት ሲናገሩ መንፈሳዊ ወንድሞቹ የሆኑትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች መርዳታቸው እሱን የረዱት ያህል እንደሚቆጠር ኢየሱስ ገለጸላቸው።

      9. ምሳሌው በሺው ዓመት ውስጥ የማይፈጸመው ለምንድን ነው?

      9 በሺው ዓመት ውስጥ ቅቡዓን የሚራቡ፣ የሚጠሙ፣ የሚታመሙ ወይም የሚታሰሩ ሰብዓዊ ፍጥረታት ስለማይሆኑ ይህ ምሳሌ በዚያን ጊዜ የሚፈጸም አይደለም። ሆኖም ብዙዎቹ በዚህ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ወቅት እነዚህ ችግሮች ደርሰውባቸዋል። ሰይጣን ወደ ምድር ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ በእነሱ ላይ ትችት፣ ሥቃይና ሞት በማምጣት ቀሪዎቹን የቁጣው ልዩ ኢላማ አድርጓቸዋል።—ራእይ 12:17

      10, 11. (ሀ) በጎቹ ለኢየሱስ ወንድሞች አንድ ዓይነት ደግነት ያደረጉ ሰዎችን በሙሉ ያካትታሉ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ያልሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በጎቹ እነማንን ያመለክታሉ?

      10 ኢየሱስ ከወንድሞቹ ለአንዱ ትንሽ ቁራሽ ወይም አንድ ብርጭቆ ውኃ በመስጠት አነስተኛ ደግነት ያሳየ ሰው ሁሉ ከበጎቹ እንደ አንዱ ለመሆን ይበቃል ማለቱ ነበርን? እንዲህ ዓይነቱ የደግነት ተግባር ሰብዓዊ ደግነት ሊሆን እንደሚችል አሌ ባይባልም በዚህ ምሳሌ ላይ የተጠቀሱትን በጎች የሚመለከት ሌላ ነገር ያለ ይመስላል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ከወንድሞቹ ለአንዱ አንድ ዓይነት የደግነት ተግባር የፈጸሙ አምላክ የለም ባዮችን ወይም ቀሳውስትን መጥቀሱ እንዳልነበር የተረጋገጠ ነው። በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ በጎቹን ሁለት ጊዜ “ጻድቃን” በማለት ጠርቷቸዋል። (ማቴዎስ 25:37, 46) ስለዚህ በጎቹ በአንድ የተወሰነ ጊዜ ውስጥ የክርስቶስ ወንድሞችን በትጋት የረዷቸውንና በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም ለማግኘት የሚያስፈልገውን እምነት ያሳዩ ሰዎችን ማመልከት ይኖርባቸዋል።

      11 ለበርካታ መቶ ዘመናት እንደ አብርሃም የመሳሰሉ ብዙ ሰዎች በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም አግኝተዋል። (ያዕቆብ 2:21–23) ኖኅ፣ አብርሃምና ሌሎች ታማኝ ሰዎች በአምላክ መንግሥት ሥር በገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ከሚወርሱት “ሌሎች በጎች” መካከል ናቸው። በቅርቡ ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ የሌሎች በጎች አባላት ከቅቡዓን ጋር “አንድ መንጋ” በመሆን እውነተኛውን አምልኮ ይዘዋል። (ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 7:9) እነዚህ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች የክርስቶስ ወንድሞች የመንግሥቱ አምባሳደሮች እንደሆኑ ስለሚገነዘቡ በሰብዓዊም ይሁን በመንፈሳዊ መንገድ ይረዷቸዋል። ኢየሱስ ሌሎች በጎች በምድር ላይ ላሉት ወንድሞቹ የሚያደርጉትን ነገር ለእሱ እንዳደረጉለት አድርጎ ይቆጥረዋል። ከእነዚህ መካከል ኢየሱስ በአሕዛብ ላይ ለመፍረድ በሚመጣበት ወቅት በሕይወት የሚኖሩት በጎች እንደሆኑ ይፈረድላቸዋል።

      12. በጎቹ ለኢየሱስ ደግነት ስለማድረጋቸው ጥያቄ ያቀረቡት ለምን ሊሆን ይችላል?

      12 ታዲያ በአሁኑ ጊዜ ከቅቡዓን ጋር ሆነው ምሥራቹን የሚሰብኩትና እነሱን የሚረዷቸው ሌሎች በጎች ከሆኑ “ጌታ ሆይ፣ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህስ?” ብለው የሚጠይቁት ለምንድን ነው? (ማቴዎስ 25:37) ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ይህ ምሳሌ ነው። ኢየሱስ በዚህ ምሳሌ አማካኝነት ለመንፈሳዊ ወንድሞቹ ያለውን ጥልቅ አሳቢነት፣ ለእነሱ እንደሚያዝንና የእነሱን መከራ እንደሚካፈል አሳይቷል። ኢየሱስ ከዚህ ቀደም ሲል “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፣ እኔን የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 10:40) ኢየሱስ በዚህ ምሳሌ ላይ ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ተጠቅሞ አንድ ሰው ለወንድሞቹ የሚደረገው ነገር (ጥሩም ይሁን መጥፎ) ወደ ሰማይ እንደሚደርስ አሳይቷል፤ ነገሩ በሰማይ ለእሱ የተደረገለት ያህል ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ እዚህ ላይ በሚፈረድላቸውም ሆነ በሚፈረድባቸው ሰዎች ላይ አምላክ የሚሰጠውን ፍርድ ተገቢና ፍትሐዊ እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ በማስቀመጥ የይሖዋ የፍርድ መመዘኛ አጉልቷል። ፍየሎቹ ‘በዓይናችን ብናይህ ኖሮ እንረዳህ ነበር’ የሚል ሰበብ ማቅረብ አይችሉም።

      13. ፍየል መሰሎቹ ሰዎች ኢየሱስን “ጌታ” ብለው የጠሩት ለምን ሊሆን ይችላል?

      13 በዚህ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ፍርድ የሚሰጥበትን ጊዜ ከተረዳን የፍየሎቹ ማንነት ግልጽ ይሆንልናል። ይህ የሚሆነው “የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፣ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፣ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር . . . ሲመጣ ያዩታል” የሚለው ትንቢት በሚፈጸምበት ወቅት ነው። (ማቴዎስ 24:29, 30፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ከሚመጣው መከራ በሕይወት የሚተርፉ የንጉሡን ወንድሞች ይጠሉ የነበሩ ሰዎች ዳኛው እንዲያድናቸው “ጌታ ሆይ” በማለት በተስፋ መቁረጥ ስሜት ይጠሩታል።—ማቴዎስ 7:22, 23፤ ከራእይ 6:15–17 ጋር አወዳድር።

      14. ኢየሱስ በጎቹንና ፍየሎቹን የሚፈርድባቸው በምን መሠረት ነው?

      14 ይሁን እንጂ ኢየሱስ የሚሰጠው ፍርድ የቀድሞ ቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች፣ አምላክ የለም ባዮች ወይም ሌሎች ሰዎች በተስፋ መቁረጥ ስሜት በሚናገሩት ነገር ላይ የተመሠረተ አይሆንም። (2 ተሰሎንቄ 1:8) ከዚህ ይልቅ ዳኛው የልብን ሁኔታና ሰዎች “ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ [ወንድሞቹ] ለአንዱ” እንኳ ያደረጓቸውን የቀድሞ ተግባራት ይመረምራል። በምድር ላይ የቀሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ቁጥር እየቀነሰ መሄዱ እሙን ነው። ይሁን እንጂ “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሆኑት ቅቡዓን መንፈሳዊ ምግብና መመሪያ ማቅረባቸውን እስከቀጠሉ ድረስ “ከሕዝብ፣ ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ” የተውጣጡት “እጅግ ብዙ ሰዎች” እንዳደረጉት ሁሉ ወደፊት በግ ሊሆኑ የሚችሉት ሰዎች ለባሪያው ክፍል መልካም የማድረግ አጋጣሚ አላቸው።—ራእይ 7:9, 14

      15. (ሀ) ብዙዎች ፍየል መሰል ሰዎች እንደሆኑ ያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) አንድ ሰው በግ ነው ወይም ፍየል ነው ብለን መፍረድ የሌለብን ለምንድን ነው?

      15 ሰዎች የክርስቶስን ወንድሞችና ከእነሱ ጋር እንደ አንድ መንጋ ሆነው የተባበሩትን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች በጎች የያዟቸው በምን መንገድ ነው? ብዙ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ በክርስቶስ ወኪሎች ላይ ጥቃት ባይፈጽሙም ሕዝቦቹን በፍቅር አልያዟቸውም። ፍየል መሰሎቹ ሰዎች ክፉውን ዓለም በመምረጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የመንግሥቱን መልእክት ሲሰሙ አልተቀበሉትም። (1 ዮሐንስ 2:15–17) እርግጥ በመጨረሻ ፍርድ እንዲሰጥ የተሾመው ኢየሱስ ነው። እኛ ማን በግ እንደሆነና ፍየል እንደሆነ የመፍረድ መብት አልተሰጠንም።—ማርቆስ 2:8፤ ሉቃስ 5:22፤ ዮሐንስ 2:24, 25፤ ሮሜ 14:10–12፤ 1 ቆሮንቶስ 4:5

      የእያንዳንዱ ቡድን የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው?

      16, 17. የበጎቹ የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው?

      16 ኢየሱስ ለበጎቹ ሲፈርድላቸው “እናንተ የአባቴ ብሩካን፣ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት [“ከተመሠረተበት” አዓት] ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” ብሏቸዋል። “ኑ” የሚለው ግብዣ እንዴት ያለ ሞቅ ያለ ግብዣ ነው! የሚመጡት ወዴት ነው? ወደ ዘላላም ሕይወት ነው። ይህም “ጻድቃን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ” በሚለው የማጠቃለያ ሐሳቡ ላይ ተገልጿል።—ማቴዎስ 25:34, 46

      17 ኢየሱስ በመክሊቶቹ ምሳሌ ላይ ከእሱ ጋር በሰማይ የሚገዙት ሰዎች ምን እንደሚፈለግባቸው አሳይቷል፤ ሆኖም በዚህ ምሳሌ ላይ የገለጸው የመንግሥቱ ዜጎች ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ነው። (ማቴዎስ 25:14–23) በጎቹ ለኢየሱስ ወንድሞች የሙሉ ልብ ድጋፍ በመስጠታቸው ምክንያት የመንግሥቱን ምድራዊ ግዛት ይወርሳሉ። አምላክ ሊቤዡ ለሚችሉ ሰዎች “ዓለም ከተመሠረተበት” ጊዜ ጀምሮ ያዘጋጀላቸውን በገነት ምድር ውስጥ የመኖር ተስፋ ያገኛሉ።—ሉቃስ 11:50, 51

      18, 19. (ሀ) ኢየሱስ በፍየሎቹ ላይ ምን ፍርድ ይሰጣል? (ለ) ፍየሎቹ ዘላለማዊ ሥቃይ እንደማይደርስባቸው እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

      18 ይህ በፍየሎቹ ላይ ከሚሰጠው ፍርድ ምንኛ የተለየ ነው! “በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል፦ እናንተ ርጉማን፣ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፣ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፣ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፣ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፣ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና። እነርሱ ደግሞ ይመልሱና፦ ጌታ ሆይ፣ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን አላገለገልንህም? ይሉታል። ያን ጊዜ፦ እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም ብሎ ይመልስላቸዋል።”—ማቴዎስ 25:41–45

      19 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይህ አነጋገር ፍየል መሰል የሆኑት ሰዎች የማይሞቱ ነፍሳት በመሆን በዘላለም እሳት ይሠቃያሉ ማለት እንዳልሆነ ያውቃሉ። ይህ በፍጹም ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ሰዎች ነፍሳት ናቸው እንጂ በውስጣቸው የማይሞቱ ነፍሳት የላቸውም ። (ዘፍጥረት 2:7 አዓት ፤ መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4) ዳኛው በፍየሎቹ ላይ “የዘላለም እሳት” በመበየኑ ወደፊት የመኖር ተስፋ የሌለው ጥፋት ይደርስባቸዋል። ይህ ፍርድ ለሰይጣንና ለአጋንንቱ ጭምር ዘላለማዊ ጥፋት ያስከትልባቸዋል። (ራእይ 20:10, 14) ስለዚህ ይሖዋ የሾመው ዳኛ ሁለት ተቃራኒ ፍርዶችን ይሰጣል። በጎቹን “ኑ” የሚላቸው ሲሆን ፍየሎቹን ደግሞ “ከእኔ ሂዱ” ይላቸዋል። በጎቹ “የዘላለም ሕይወት” ያገኛሉ። ፍየሎቹ “የዘላለም ቅጣት” ይቀበላሉ።—ማቴዎስ 25:46b

      ይህ ለእኛ ምን ትርጉም ይኖረዋል?

      20, 21. (ሀ) ክርስቲያኖች ምን በጣም አስፈላጊ የሆነ ሥራ አላቸው? (ለ) በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ ያለው የመለያየት ሥራ የትኛው ነው? (ሐ) የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ መፈጸም ሲጀምር የሰዎች ሁኔታ ምን ይሆናል?

      20 ኢየሱስ ስለ መገኘቱና ስለ ሥርዓቱ መደምደሚያ ምልክት የሚሆነውን ነገር ሲናገር የሰሙት አራቱ ሐዋርያት ብዙ የሚያስቡባቸው ጉዳዮች ነበሯቸው። ነቅተው መጠበቅ ያስፈልጋቸው ነበር። (ማቴዎስ 24:42) በተጨማሪም በማርቆስ 13:10 ላይ የተጠቀሰውን የምሥክርነቱን ሥራ ማከናወን ነበረባቸው። በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ሥራ በትጋት እየተካፈሉ ነው።

      21 ታዲያ ስለ በጎቹና ፍየሎቹ ምሳሌ ያገኘነው ይህ ተጨማሪ ማስተዋል ለእኛ ምን ትርጉም ይኖረዋል? በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ሚናቸውን እየለዩ ነው። አንዳንዶች ‘ወደ ጥፋት በሚወስደው ሰፊ መንገድ’ ላይ ሲሆኑ ሌሎች ‘ወደ ሕይወት በሚወስደው ጠባብ መንገድ’ ላይ ለመቆየት እየጣሩ ነው። (ማቴዎስ 7:13, 14) ይሁን እንጂ ኢየሱስ በበጎቹና በፍየሎቹ ላይ የመጨረሻውን ፍርድ የሚሰጥበት በምሳሌው ውስጥ የተገለጸው ጊዜ ገና ወደፊት ይጠብቀናል። የሰው ልጅ የዳኝነት ተግባሩን ለማከናወን ሲመጣ ብዙ እውነተኛ ክርስቲያኖች የሆኑ ራሳቸውን የወሰኑ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ‘የታላቁ መከራን’ የመጨረሻ ክፍል አልፈው ወደ አዲሱ ዓለም ለመግባት ብቁ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ፍርድ ይሰጣል። ይህ ተስፋ በአሁኑ ጊዜ ሊያስደስታቸው ይገባል። (ራእይ 7:9, 14) በሌላ በኩል ከ“አሕዛብ ሁሉ” መካከል በጣም ብዙ ሰዎች እንደ ልበ ደንዳና ፍየሎች ሆነዋል። እነዚህ ሰዎች “ወደ ዘላለም ቅጣት . . . ይሄዳሉ።” ይህ ለምድር እንዴት ያለ እፎይታ ያመጣል!

      22, 23. ምሳሌው የሚፈጸመው ወደፊት ቢሆንም የስብከቱ ሥራ በአሁኑ ጊዜ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      22 በምሳሌው ውስጥ የተገለጸው ፍርድ ወደፊት በቅርብ ጊዜ የሚፈጸም ቢሆንም እንኳ አሁን አንድ በጣም ወሳኝ የሆነ ነገር እየተከናወነ ነው። እኛ ክርስቲያኖች ሰዎች በሁለት ወገን እንዲለዩ የሚያደርገውን ሕይወት አድን መልእክት በማወጅ ላይ ነን። (ማቴዎስ 10:32–39) ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “የጌታን [“የይሖዋን” አዓት] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና። እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?” (ሮሜ 10:13, 14) የአምላክን ስምና የመዳንን መልእክት በማሳወቅ ለሕዝብ የምንሰጠው አገልግሎት ከ230 በላይ በሆኑ አገሮች ውስጥ ተዳርሷል። አሁንም ቢሆን ይህን ሥራ በግምባር ቀደምነት የሚመሩት ቅቡዓን የክርስቶስ ወንድሞች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጉ ሌሎች በጎች ከእነሱ ጋር ተባብረዋል። በተጨማሪም በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎች በኢየሱስ ወንድሞች ለሚታወጀው መልእክት አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ላይ ናቸው።

      23 ከቤት ወደ ቤት ወይም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ስለምንሰብክ ብዙዎች መልእክታችን ይደርሳቸዋል። ሌሎች በማናውቀው መንገድ ስለ ይሖዋ ምሥክሮችና እኛ ስለምንወክለው ነገር ሊሰሙ ይችላሉ። ኢየሱስ ፍርድ የሚሰጥበት ጊዜ ሲደርስ ማኅበረሰቡን ተጠያቂ የሚያደርገውና ቤተሰብን ግምት ውስጥ የሚያስገባው ምን ያህል ነው? ይህን ያህል ነው ብለን ለመናገር አንችልም፤ ስለ ጉዳዩ አስቀድሞ መገመትም ፋይዳ አይኖረውም። (ከ1 ቆሮንቶስ 7:14 ጋር አወዳድር።) በአሁኑ ጊዜ ብዙዎች ጆሮ ዳባ ልበስ ብለዋል፣ የአምላክን ሕዝቦች ይተቻሉ ወይም በቀጥታ ያሳድዳሉ። ስለዚህ ይህ ወሳኝ ጊዜ ነው፤ እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ እንደ ፍየሎች አድርጎ ከሚፈርድባቸው ሰዎች መካከል ሊሆኑ ይችላሉ።—ማቴዎስ 10:22፤ ዮሐንስ 15:20፤ 16:2, 3፤ ሮሜ 2:5, 6

      24. (ሀ) ግለሰቦች ለስብከቱ ሥራችን አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ይህ ጥናት አንተ በግልህ ለአገልግሎት ምን ዓይነት ዝንባሌ እንድትይዝ ረድቶሃል?

      24 ደስ የሚለው ግን በርካታ ሰዎች የአምላክን ቃል በማጥናትና የይሖዋ ምሥክሮች በመሆን አዎንታዊ ምላሽ እየሰጡ ነው። በአሁኑ ጊዜ ፍየሎች ከሚመስሉት አንዳንዶቹ ተለውጠው በግ መሰል ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ዋናው ነጥብ አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡትና የክርስቶስን ወንድሞች በትጋት የሚረዱት ሰዎች ኢየሱስ ፍርድ ለመስጠት በዙፋኑ ላይ በሚቀመጥበት በቅርብ ጊዜ ውስጥ በቀኙ ለመሰለፍ መሠረት የሚሆንላቸውን ነገር ካሁኑ በማሳየት ላይ መሆናቸው ነው። እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ጊዜም ሆነ ወደፊት መባረካቸውን ይቀጥላሉ። ስለዚህ ይህ ምሳሌ ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን ይበልጥ በቅንዓት እንድናከናውን ሊገፋፋን ይገባል። ጊዜው ሳያልቅ የመንግሥቱን ምሥራች ለማወጅ የምንችለውን ያህል ለመሥራት እንፈልጋለን። ይህን ካደረግን ሌሎች አዎንታዊ ምላሽ መስጠት የሚችሉበትን አጋጣሚ እንፈጥርላቸዋለን። በዚያን ጊዜ ሰዎች እንዲጠፉም ሆነ እንዲድኑ ፍርድ የመስጠት ሥልጣን ያለው ኢየሱስ ነው።—ማቴዎስ 25:46

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ