የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት ምንድን ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—2015 | ኅዳር 1
    • ወታደሮች፣ ታንኮች እና የጦር አውሮፕላኖች

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

      አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት ምንድን ነው?

      ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ ትሰጣለህ? ብዙ ሰዎች አምላክ ጦርነትን እንደሚደግፍ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች አምላክ በጥንት ዘመን አንዳንድ አገልጋዮቹን በጦርነት እንዲካፈሉ መመሪያ መስጠቱን ማስረጃ አድርገው የሚያቀርቡ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባም ቢሆን የዚህን እውነተኝነት ያረጋግጣል። ሌሎች ደግሞ የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ጠላቶቻቸውን እንዲወዱ እንዳስተማረ ይገልጻሉ። (ማቴዎስ 5:43, 44) በመሆኑም አምላክ በአንድ ወቅት ስለ ጦርነት የነበረው አመለካከት እንደተለወጠና በዛሬው ጊዜ ጦርነትን እንደማይደግፍ ይሰማቸዋል።

      አንተስ ምን ይሰማሃል? አምላክ ጦርነትን ይደግፋል? ከሆነስ በዛሬው ጊዜ ግጭቶች ሲካሄዱ ከየትኛው ወገን ጎን ይቆማል? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘትህ ስለ ጦርነት ባለህ አመለካከት ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ጦርነትን እንደሚደግፍ እንዲሁም አንተ የምትደግፈውን ወገን እንደሚያግዝ ብታውቅ እንደምትደሰት ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም የአንተ ወገን ድል እንደሚቀናው እርግጠኛ ነህ። በሌላ በኩል ደግሞ አምላክ የሚደግፈው በተቃራኒ ወገን ያለውን ሠራዊት እንደሆነ ብታውቅ ምን ይሰማሃል? በጉዳዩ ላይ ያለህን አቋም እንደገና ማጤን እንዳለብህ ሊሰማህ ይችላል።

      ይሁንና አንድ ወሳኝ ጉዳይ አለ፦ አምላክ ስለ ጦርነት ያለውን አመለካከት ማወቅህ ለእሱ ባለህ አመለካከት ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። የሰው ልጆች በሚያካሂዱት ጦርነት የተነሳ ክፉኛ ከተጎዱት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ከሆንክ ለሚከተሉት ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ ማወቅ እንደምትፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም፦ አንዳንዶች እንደሚሰማቸው አምላክ ጦርነትን ይወዳል? ሰዎች በጦርነት እንዲሠቃዩ ይፈቅዳል? ወይም ጦርነት እንዲካሄድ ያበረታታል? አሊያም በጦርነት እጁን ባያስገባም ሌሎች ሲጨቆኑ ዝም ብሎ ያያል?

      መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መልስ የዚህ ፍጹም ተቃራኒ መሆኑን ስታውቅ ልትገረም ትችላለህ። እንዲያውም አምላክ ጥንትም ሆነ ዛሬ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት ፈጽሞ አልተለወጠም። በጥንት ዘመንም ሆነ ኢየሱስ ምድር ላይ በኖረበት በመጀመሪያው መቶ ዘመን አምላክ ስለ ጦርነት ምን አመለካከት እንደነበረው መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን እንመልከት። እንዲህ ማድረጋችን አምላክ በዛሬው ጊዜ ስለ ጦርነት ምን አመለካከት እንዳለው እንዲሁም ጦርነት ወደፊትም ይቀጥል እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ ይረዳናል።

  • አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት—በጥንት ዘመን
    መጠበቂያ ግንብ—2015 | ኅዳር 1
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት ምንድን ነው?

      አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት—በጥንት ዘመን

      ቀይ ባሕር ፈርዖንንና ሠራዊቱን ሲውጣቸው

      ሕዝቡ በጭቆና ቀንበር ሥር ወድቋል። እፎይታ ለማግኘት በተደጋጋሚ ወደ አምላክ ቢጸልዩም ወዲያውኑ መፍትሔ አላገኙም። እነዚህ ሰዎች የአምላክ ሕዝብ የነበሩት እስራኤላውያን ናቸው። ሲጨቁናቸው የነበረው ደግሞ ኃያሉ የግብፅ ብሔር ነው። (ዘፀአት 1:13, 14) አምላክ፣ ከግብፅ የጭቆና ቀንበር እስኪያላቅቃቸው ድረስ እስራኤላውያን ለብዙ ዓመታት መጠበቅ አስፈልጓቸዋል። በመጨረሻም አምላክ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ ደረሰ። (ዘፀአት 3:7-10) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ግብፃውያንን የተዋጋው አምላክ ራሱ እንደሆነ ይናገራል። በግብፅ ላይ አውዳሚ መቅሰፍቶችን በተከታታይ ያወረደ ከመሆኑም ሌላ የግብፅ ንጉሥንና ሠራዊቱን ቀይ ባሕር ውስጥ አሰጠማቸው። (መዝሙር 136:15) ይሖዋ አምላክ ለሕዝቡ ሲል “ኃያል ተዋጊ” መሆኑን አሳየ።—ዘፀአት 15:3, 4

      አምላክ ራሱ ግብፃውያንን የተዋጋ መሆኑ ጦርነትን በደፈናው እንደማይቃወም ያሳያል። እንዲያውም ሕዝቡ የሆኑት እስራኤላውያን እንዲዋጉ የፈቀደባቸው ጊዜያት ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ እጅግ ክፉ የነበሩትን ከነአናውያንን እንዲወጉ አዟቸው ነበር። (ዘዳግም 9:5፤ 20:17, 18) አምላክ፣ ጨቋኝ የነበሩትን ፍልስጤማውያን እንዲዋጋ የእስራኤል ንጉሥ ለነበረው ለዳዊት መመሪያ ሰጥቶታል። አልፎ ተርፎም ዳዊት ድል እንዲቀዳጅ የሚያስችለውን የጦር ስልት ነግሮታል።—2 ሳሙኤል 5:17-25

      እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት አንዳንድ የክፋትና የጭቆና ድርጊቶች የእስራኤላውያንን ሕልውና ስጋት ላይ ሲጥሉ አምላክ ሕዝቡንና እውነተኛውን አምልኮ ከአደጋ ለመጠበቅ ሲል እስራኤላውያን እንዲዋጉ ፈቅዶላቸዋል። ይሁን እንጂ በአምላክ ትእዛዝ ስለተካሄዱት እንዲህ ያሉ ጦርነቶች ቀጥሎ የቀረቡትን ሦስት ቁልፍ ነጥቦች ልብ በል፦

      1. በጦርነቱ ላይ ማን መሰለፍ እንዳለበት የሚወስነው አምላክ ራሱ ነበር። በአንድ ወቅት አምላክ ለእስራኤላውያን “እናንተ ይህን ጦርነት መዋጋት አያስፈልጋችሁም” ብሏቸዋል። ለምን? አምላክ ራሱ ስለሚዋጋላቸው ነው። (2 ዜና መዋዕል 20:17፤ 32:7, 8) በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ ከተጠቀሰው ጋር በሚመሳሰሉ ሌሎች በርካታ ወቅቶችም እሱ ራሱ ተዋግቶላቸዋል። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ አምላክ በጥንቷ እስራኤል የነበሩት ሕዝቦቹን እሱ በሚደግፋቸው ጦርነቶች ላይ እንዲዋጉ አዟቸው ነበር፤ ለምሳሌ ያህል የተስፋይቱ ምድር ይዞታቸውን ለማስከበርና ከጥቃት ለመከላከል በሚደረጉ ጦርነቶች ተካፍለዋል።—ዘዳግም 7:1, 2፤ ኢያሱ 10:40

      2. ጦርነቱ መቼ መካሄድ እንዳለበት የሚወስነው አምላክ ራሱ ነበር። የአምላክ አገልጋዮች፣ ጭቆናና ክፋት ይፈጽሙ የነበሩትን በዙሪያቸው ያሉ ሕዝቦች ለመዋጋት አምላክ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ በትዕግሥት መጠበቅ አስፈልጓቸዋል። አምላክ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በራሳቸው ውሳኔ ጦርነት እንዲያካሂዱ አይፈቀድላቸውም ነበር። በራሳቸው ተነሳሽነት ወደ ጦርነት በገቡባቸው ወቅቶች የአምላክን ድጋፍ አጥተዋል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያሳየው እስራኤላውያን አምላክ ሳይፈቅድ ጦርነት ሲያካሂዱ አብዛኛውን ጊዜ ለሽንፈት ተዳርገዋል።a

      3. ረዓብ እና ቤተሰቦቿ በኢያሪኮ ፍርስራሽ መካከል ቆመው

        አምላክ በከነአናውያን ላይ ጦርነት እንዲታወጅ ቢያዝም እንደ ረዓብና ቤተሰቦቿ የመሰሉ አንዳንድ ግለሰቦች ከሞት እንዲተርፉ አድርጓል

        አምላክ ክፉዎችን ጨምሮ በሰዎች ሞት አይደሰትም። ይሖዋ አምላክ የሕይወት ምንጭና የሰው ዘር ፈጣሪ ነው። (መዝሙር 36:9) በመሆኑም ሰዎች ሲሞቱ የማየት ፍላጎት የለውም። የሚያሳዝነው ግን ሌሎችን ለመጨቆን አልፎ ተርፎም ለመግደል በክፋት የሚያሴሩ ሰዎች አሉ። (መዝሙር 37:12, 14) አምላክ እንዲህ ዓይነቱን ክፋት ለማስቆም በክፉዎች ላይ ጦርነት እንዲካሄድ የፈቀደባቸው ጊዜያት አሉ። ያም ሆኖ እስራኤላውያን እንደዚህ ባሉት ጦርነቶች እንዲካፈሉ ባደረገባቸው ዘመናት በሙሉ እስራኤላውያንን ለሚጨቁኑት ጭምር “መሐሪ” እና “ለቁጣ የዘገየ” መሆኑን አሳይቷል። (መዝሙር 86:15) ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን ከአንዲት ከተማ ጋር ጦርነት ከመግጠማቸው በፊት የከተማዋ ነዋሪዎች አቋማቸውን የሚለውጡበትና ጦርነቱ መቅረት የሚችልበት አጋጣሚ ለመስጠት “የሰላም ጥሪ” እንዲያስተላልፉ አምላክ ደንግጎ ነበር። (ዘዳግም 20:10-13) በዚህ መንገድ አምላክ ‘በክፉው ሰው ሞት ደስ እንደማይሰኝ ይልቁንም ክፉው ሰው አካሄዱን አስተካክሎ በሕይወት እንዲኖር እንደሚፈልግ’ አሳይቷል።—ሕዝቅኤል 33:11, 14-16b

      ቀደም ሲል እንዳየነው አምላክ በጥንት ዘመን ጦርነትን የተለያዩ የጭቆናና የክፋት ድርጊቶችን ለማስቆም የሚያስችል ትክክለኛ መንገድ አድርጎ ተመልክቶታል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ጦርነት መቼ መካሄድ እንዳለበትና በጦርነቱ ማን መካፈል እንደሚኖርበት የመወሰን መብት ያለው አምላክ እንጂ ሰዎች አልነበሩም። ይሁንና አምላክ ጦርነት እንዲካሄድ ሲፈቅድ ደም እንደተጠማ የሚጠቁም ዝንባሌ ታይቶበታል? በጭራሽ፤ እሱ ዓመፅን ይጠላል። (መዝሙር 11:5) ለመሆኑ አምላክ፣ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎቱን በጀመረበት በአንደኛው መቶ ዘመን ለጦርነት የነበረው አመለካከት ተለውጦ ይሆን?

      a ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት እስራኤላውያን አምላክ ከአማሌቃውያንና ከከነዓናውያን ጋር እንዳይዋጉ የሰጣቸውን ትእዛዝ ጥሰው ጦርነት በገጠሙ ጊዜ ተሸንፈዋል። (ዘኁልቁ 14:41-45) ከብዙ ዓመታት በኋላ ደግሞ ታማኙ ንጉሥ ኢዮስያስ የአምላክን ፈቃድ ሳይጠይቅ ጦርነት ገጥሞ ነበር፤ ይህ በችኮላ የወሰደው እርምጃ ሕይወቱን አሳጥቶታል።—2 ዜና መዋዕል 35:20-24

      b እስራኤላውያን ከከነአናውያን ጋር ጦርነት ከመግጠማቸው በፊት የሰላም ጥሪ አላስተላለፉም ነበር። ለምን? ምክንያቱም ከነአናውያን ክፉ አካሄዳቸውን ማስተካከል የሚችሉበት 400 ዓመታት ነበራቸው። እስራኤላውያን ጦርነት ሊገጥሟቸው በመጡበት ጊዜ ከነአናውያን በክፉ አቋማቸው ቀጥለው ነበር። (ዘፍጥረት 15:13-16) ስለዚህ ሙሉ በሙሉ መጥፋት ነበረባቸው። ይሁን እንጂ በግለሰብ ደረጃ አካሄዳቸውን የለወጡ ከነአናውያን ከጥፋት ተርፈዋል።—ኢያሱ 6:25፤ 9:3-27

  • አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት—በመጀመሪያው መቶ ዘመን
    መጠበቂያ ግንብ—2015 | ኅዳር 1
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት ምንድን ነው?

      አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት—በመጀመሪያው መቶ ዘመን

      ሕዝቡ በጭቆና ቀንበር ሥር ወድቋል። በቀድሞ ዘመን እንደኖሩት አባቶቻቸው ሁሉ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያንም በወቅቱ ከነበረው የሮም የጭቆና ቀንበር ነፃ እንዲያወጣቸው በተደጋጋሚ ወደ አምላክ ጸልየው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ከዚያም ስለ ኢየሱስ ሰሙ። ታዲያ በትንቢት የተነገረለት መሲሕ እሱ ይሆን? በዚህ ጊዜ በሮማውያን ጭቆና ይደርስባቸው የነበሩ በርካታ አይሁዳውያን ኢየሱስ ‘እስራኤልን ነፃ እንደሚያወጣ’ ጠብቀው ነበር። (ሉቃስ 24:21) ሆኖም ከጭቆና ነፃ አልወጡም። ይባስ ብሎም በ70 ዓ.ም. የሮም ሠራዊት መጥቶ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን አወደመ።

      ይህ የሆነው ለምንድን ነው? አምላክ ጥንት እንዳደረገው ለአይሁዳውያን ያልተዋጋላቸው ለምንድን ነው? ወይም ደግሞ ከጭቆና ቀንበር ነፃ ለመውጣት እንዲዋጉ ያልፈቀደላቸው ለምንድን ነው? አምላክ ለጦርነት የነበረው አመለካከት ተለውጦ ይሆን? በፍጹም። ይሁን እንጂ ከአይሁዳውያን ጋር በተያያዘ የተደረገ ጉልህ ለውጥ አለ። አይሁዳውያን የአምላክ ልጅ የሆነውን ኢየሱስን መሲሕ አድርገው አልተቀበሉትም። (የሐዋርያት ሥራ 2:36) በመሆኑም በብሔር ደረጃ ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ልዩ ዝምድና አጡ።—ማቴዎስ 23:37, 38

      የአይሁድ ብሔርና ተስፋይቱ ምድር ከዚህ በኋላ መለኮታዊ ጥበቃ ማግኘታቸው አበቃ። በተጨማሪም አይሁዳውያን ጦርነት ቢያካሂዱ ውጊያው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው ወይም እሱ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው መናገር አይችሉም። ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ሥጋዊ እስራኤላውያን የአምላክን ሞገስ ያገኙ በነበረበት ጊዜ የሚፈስላቸው በረከት ከእነሱ ተወስዶ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘የአምላክ እስራኤል’ ተብሎ ለተጠራው በአዲስ መልክ ለተቋቋመው መንፈሳዊ ብሔር ተሰጠ። (ገላትያ 6:16፤ ማቴዎስ 21:43) በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችን ያቀፈው ጉባኤ መንፈሳዊ የአምላክ እስራኤል ሆነ። በመሆኑም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች “አሁን ግን የአምላክ ሕዝብ ናችሁ” ተብለዋል።—1 ጴጥሮስ 2:9, 10

      ታዲያ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች “የአምላክ ሕዝብ” ተደርገው ስለተቆጠሩ አምላክ እነሱን ከሮማውያን ጭቆና ነፃ ለማውጣት ተዋግቶላቸዋል? አሊያም በሚጨቁናቸው ብሔር ላይ ጦርነት እንዲያካሂዱ ፈቅዶላቸው ነበር? በጭራሽ። ለምን? በአምላክ ትእዛዝ የሚደረግን ጦርነት በተመለከተ ባለፈው ርዕስ ላይ እንዳየነው፣ እንዲህ ዓይነቱ ውጊያ መቼ መካሄድ እንዳለበት የሚወስነው አምላክ ራሱ ነው። አምላክ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ክርስቲያኖች አልተዋጋላቸውም ወይም እንዲዋጉ አልፈቀደላቸውም። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ አምላክ ክፋትንና ጭቆናን በጦርነት ለማስወገድ የመረጠበት ጊዜ አይደለም።

      ስለዚህ በጥንት ዘመን እንደነበሩት የአምላክ አገልጋዮች ሁሉ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችም አምላክ ክፋትንና ጭቆናን ለማስወገድ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ መጠበቅ ነበረባቸው። እስከዚያው ድረስ በጠላቶቻቸው ላይ በራሳቸው ተነሳሽነት ጦርነት እንዲያካሂዱ አልፈቀደላቸውም። ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠው ትምህርት ላይ ይህን ግልጽ አድርጓል። ለምሳሌ ያህል፣ ተከታዮቹ በጦርነት እንዲካፈሉ አላዘዛቸውም፤ ከዚህ ይልቅ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ ጸልዩ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 5:44) ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሩሳሌም በሮም ሠራዊት ጥቃት እንደሚሰነዘርባት ትንቢት ሲናገር ደቀ መዛሙርቱ ከተማዋ ውስጥ ቆይተው እንዲዋጉ ሳይሆን እንዲሸሹ አዟቸዋል፤ እነሱም ይህን ትእዛዝ አክብረዋል።—ሉቃስ 21:20, 21

      በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት በጻፈው መልእክት ላይ “ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ከዚህ ይልቅ ‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ’ ይላል ይሖዋ” ብሏል። (ሮም 12:19) እዚህ ላይ ጳውሎስ የጠቀሰው በዘሌዋውያን 19:18 እና በዘዳግም 32:35 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን አምላክ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት የተናገረውን ሐሳብ ነው። ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው አምላክ በጥንት ዘመን ለሕዝቡ የተበቀለበት አንደኛው መንገድ በጠላቶቻቸው ላይ ጦርነት ሲያካሂዱ እነሱን በመርዳት ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ እንደሚያሳየው አምላክ ለጦርነት ያለው አመለካከት አልተለወጠም። በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ቢሆን አምላክ ጦርነትን ለአገልጋዮቹ ሲል ለመበቀል እንዲሁም የተለያዩ የጭቆናና የክፋት ድርጊቶችን ለማስቆም የሚያስችል ትክክለኛ መንገድ አድርጎ ተመልክቶታል። ሆኖም በጥንት ዘመን እንደነበረው ሁሉ በዚህ ጊዜም እንዲህ ዓይነቱ ጦርነት መቼ መካሄድና ማን መዋጋት እንዳለበት የሚወስነው እሱ ራሱ ነበር።

      ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አምላክ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ክርስቲያኖች እንዲዋጉ አልፈቀደላቸውም። ስለ ዘመናችንስ ምን ማለት ይቻላል? አምላክ በዛሬው ጊዜ እንዲዋጉ የፈቀደላቸው ሕዝቦች አሉ? ወይስ ይህ ወቅት ለአገልጋዮቹ ሲል ጣልቃ ገብቶ የሚዋጋበት ጊዜ ነው? አምላክ በዛሬው ጊዜ ጦርነትን እንዴት ይመለከተዋል? የዚህ ተከታታይ ርዕስ የመጨረሻ ክፍል ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

  • አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት—በዛሬው ጊዜ
    መጠበቂያ ግንብ—2015 | ኅዳር 1
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት ምንድን ነው?

      አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት—በዛሬው ጊዜ

      በዛሬው ጊዜ ሰዎች በጭቆና ቀንበር ሥር ወድቀዋል። ብዙዎች እረፍት ለማግኘት በተደጋጋሚ ወደ አምላክ የሚጮኹ ሲሆን ‘እፎይታ የምናገኝበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ ያሳስባቸዋል። ታዲያ እነዚህ ሰዎች እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙትን ጩኸት አምላክ ይሰማል? በሌላ በኩል፣ ከሚደርስባቸው ጭቆና ለመገላገል ጦርነትን እንደ አማራጭ ስለሚከተሉ ሰዎች ምን ማለት ይቻላል? አምላክ፣ የሚያካሂዱት ጦርነት ተገቢ እንደሆነ በመቁጠር ጥረታቸውን ይደግፋል?

      በአርማጌዶን ኢየሱስና መላእክቱ ነጭ ፈረሶች እየጋለቡ

      አርማጌዶን ጦርነቶችን ሁሉ የሚያስወግድ ጦርነት ይሆናል

      በመጀመሪያ፣ የሚከተለውን እውነታ ማወቃችን ሊያጽናናን ይችላል፦ አምላክ በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ያለውን መከራ ያያል፤ ደግሞም እርምጃ መውሰዱ አይቀርም። (መዝሙር 72:13, 14) በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘መከራ ለሚቀበሉ ሰዎች እረፍት እንደሚሰጣቸው’ ቃል ገብቷል። ይህ የሚሆነው መቼ ነው? “ጌታ ኢየሱስ ከኃያላን መላእክቱ ጋር ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ . . . አምላክን በማያውቁትና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ለሚገልጸው ምሥራች በማይታዘዙት ላይ የበቀል እርምጃ ይወስዳል።” (2 ተሰሎንቄ 1:7, 8) ኢየሱስ የሚገለጠው ወደፊት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ያንን ጊዜ ‘ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ታላቅ ቀን’ ወይም አርማጌዶን በማለት ይጠራዋል።—ራእይ 16:14, 16

      ወደፊት በሚካሄደው በዚያ ጦርነት ላይ አምላክ ክፉዎችን ለመዋጋት የሚጠቀመው ሰዎችን ሳይሆን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስንና ሌሎች ኃያላን መንፈሳዊ ፍጥረታትን ነው። ይህ የሰማይ ሠራዊት ማንኛውንም ዓይነት ጭቆና ያስወግዳል።—ኢሳይያስ 11:4፤ ራእይ 19:11-16

      ዛሬም አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት አልተለወጠም። አሁንም ቢሆን አምላክ ጦርነትን የሚያየው ጭቆናና ክፋትን ለማስቆም የሚያስችል ትክክለኛ መንገድ አድርጎ ነው። ይሁን እንጂ በታሪክ ዘመናት በሙሉ እንደታየው እንዲህ ዓይነቱ ጦርነት መቼ መካሄድና ማን መዋጋት እንዳለበት የሚወስነው አምላክ ራሱ ነው። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው አምላክ ወደፊት በሚያካሂደው ጦርነት ክፋትን ለማስቆምና ጨቋኞችን ለመበቀል ወስኗል፤ በጦርነቱ ላይ የሚዋጋው ደግሞ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እንግዲያው በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ የሚካሄዱት ጦርነቶች፣ የቱንም ያህል ተገቢ ቢመስሉም የአምላክ ድጋፍ የላቸውም።

      ይህን በምሳሌ ለማስረዳት፣ አባታቸው በሌለበት መጣላት የጀመሩ ሁለት ወንድማማቾችን ለማሰብ ሞክር። እነዚህ ልጆች መጣላታቸውን አቁመው አባታቸውን በስልክ አናገሩት። አንደኛው ልጅ ጠቡን የጀመረው ወንድሙ እንደሆነ ሲገልጽ ሌላኛው ደግሞ ወንድሙ መጥፎ ነገር እንዳደረገበት ይናገራል። ሁለቱም አባታቸው እነሱን እንደሚደግፍ በማሰብ ስሞታ አሰሙ። ይሁን እንጂ አባታቸው ሁለቱንም ከሰማ በኋላ ቤት መጥቶ እስኪያስታርቃቸው ድረስ መጣላት እንዲያቆሙ ነገራቸው። ወንድማማቾቹ ለተወሰነ ጊዜ ከጠበቁት በኋላ በድጋሚ መጣላት ጀመሩ። አባትየው ቤት ሲደርስ ልጆቹ መመሪያውን ባለማክበራቸው ሁለቱንም ቀጣቸው።

      በዛሬው ጊዜም እርስ በርስ የሚዋጉ ብሔራት ብዙውን ጊዜ አምላክ ከእነሱ ጎን እንዲቆም ይጸልያሉ። አምላክ ግን የትኛውንም ወገን አይደግፍም። ከዚህ ይልቅ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ” እንዲሁም “ራሳችሁ አትበቀሉ” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ሮም 12:17, 19) ከዚህም በላይ የሰው ልጆች እሱ በአርማጌዶን የሚወስደውን እርምጃ ‘በትዕግሥት መጠበቅ’ እንዳለባቸው ተናግሯል። (መዝሙር 37:7 የግርጌ ማስታወሻ) ብሔራት፣ አምላክ እርምጃ እስኪወስድ ድረስ ከመጠበቅ ይልቅ ጦርነትን አማራጭ ሲያደርጉ አምላክ ድርጊታቸውን በእብሪት የተወሰደ የኃይል እርምጃ አድርጎ ስለሚመለከተው በሁኔታው አይደሰትም። በመሆኑም አምላክ በአርማጌዶን ጦርነት ቁጣውን ይገልጻል፤ እንዲሁም ‘ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ በማስወገድ’ በብሔራት መካከል የሚካሄደው ግጭት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ ያደርጋል። (መዝሙር 46:9፤ ኢሳይያስ 34:2) በእርግጥም አርማጌዶን ጦርነቶችን ሁሉ የሚያጠፋ ጦርነት ይሆናል።

      የጦርነት መወገድ የአምላክ መንግሥት ከሚያመጣቸው ብዙ በረከቶች መካከል አንዱ ነው። ኢየሱስ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም” በሚለው የታወቀ ጸሎቱ ላይ ስለዚህ መንግሥት ተናግሯል። (ማቴዎስ 6:10) የአምላክ መንግሥት ጦርነትን ብቻ ሳይሆን የጦርነት ዋነኛ መንስኤ የሆነውን ክፋትን ጭምር ያስወግዳል።a (መዝሙር 37:9, 10, 14, 15) የኢየሱስ ተከታዮች የአምላክ መንግሥት የሚያመጣውን በረከት በጉጉት መጠበቃቸው አያስገርምም።—2 ጴጥሮስ 3:13

      ሰዎች በገነት ውስጥ አስደሳች ሕይወት ይመራሉ

      ይሁንና የአምላክ መንግሥት መከራን፣ ጭቆናንና ክፋትን በሙሉ እስኪያስወግድ የምንጠብቀው ለምን ያህል ጊዜ ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ ማግኘታቸው የምንኖረው በዚህ የነገሮች ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀናት’ ውስጥ እንደሆነ ይጠቁማል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5)b በቅርቡ የአምላክ መንግሥት በአርማጌዶን ጦርነት አማካኝነት የመጨረሻዎቹ ቀናት እንዲደመደሙ ያደርጋል።

      ቀደም ብሎ እንደተገለጸው ለመጨረሻ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ጦርነት የሚጠፉት ‘ስለ ጌታችን ኢየሱስ ለሚገልጸው ምሥራች የማይታዘዙ’ ሰዎች ይሆናሉ። (2 ተሰሎንቄ 1:8) ይሁን እንጂ አምላክ ክፉዎችን ጨምሮ በማንም ሰው ሞት እንደማይደሰት አስታውስ። (ሕዝቅኤል 33:11) አምላክ በዚህ የመጨረሻ ጦርነት “ማንም እንዲጠፋ ስለማይፈልግ” ፍጻሜው ከመምጣቱ በፊት በአሁኑ ጊዜ ስለ ጌታችን ኢየሱስ የሚገልጸው ምሥራች “ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር” እንዲሰበክ እያደረገ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:8, 9፤ ማቴዎስ 24:14፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) አዎን፣ በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያካሂዱት ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ አማካኝነት ሰዎች አምላክን ማወቅ፣ ስለ ኢየሱስ ለሚገልጸው ምሥራች መታዘዝና በሕይወት ተርፈው ጦርነት የማይኖርበትን ጊዜ ማየት የሚችሉበት አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል።

      a በተጨማሪም የአምላክ መንግሥት፣ የሰው ዘር ጠላት የሆነውን ሞትን ያጠፋል። በዚህ መጽሔት ላይ “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው” በሚለው ርዕስ ሥር እንደተገለጸው አምላክ በታሪክ ዘመናት በሙሉ በተደረጉት ጦርነቶች ያለቁትን ጨምሮ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰዎች ከሞት ያስነሳል።

      b የመጨረሻዎቹን ቀናት አስመልክቶ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ተመልከት።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ