የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ታሪኩ እውነት ነው?
    መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016 | ቁጥር 2
    • የኢየሱስን አስከሬን ከመከራው እንጨት ላይ ሲያወርዱት፤ ደቀ መዛሙርቱ ከርቀት ሆነው ሲመለከቱ

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ኢየሱስ የተሠቃየውና የሞተው ለምንድን ነው?

      ታሪኩ እውነት ነው?

      በ33 ዓ.ም. በጸደይ ወቅት የናዝሬቱ ኢየሱስ ተገደለ። ኢየሱስ፣ ሕዝብን ለዓመፅ አነሳስቷል የሚል የሐሰት ክስ የተሰነዘረበት ሲሆን በጭካኔ ከተገረፈ በኋላ በእንጨት ላይ ተቸነከረ። የሞተውም እጅግ ተሠቃይቶ ነው። ይሁን እንጂ አምላክ ከሞት አስነሳው፤ ከ40 ቀን በኋላም ወደ ሰማይ አረገ።

      ይህ አስገራሚ ዘገባ ተመዝግቦ የሚገኘው፣ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት (በተለምዶ አዲስ ኪዳን ይባላሉ) ውስጥ ባሉት አራት ወንጌሎች ላይ ነው። ሆኖም ይህ ዘገባ እውነት ነው? ይህ አግባብነት ያለውና በቁም ነገር ሊታሰብበት የሚገባ ጥያቄ ነው። ምክንያቱም ዘገባው እውነት ካልሆነ የክርስትና እምነት ዋጋ ቢስ ይሆናል፤ በገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋም እንዲሁ ምኞት ብቻ ሆኖ ይቀራል። (1 ቆሮንቶስ 15:14) በሌላ በኩል ደግሞ ዘገባው እውነት ከሆነ አንተን ጨምሮ መላው የሰው ዘር ብሩህ ተስፋ አለው ማለት ነው። ታዲያ የወንጌል ዘገባዎች እውነት ናቸው ወይስ ልብ ወለድ?

      ማስረጃዎቹ ምን ያሳያሉ?

      በምናብ ከተፈጠሩ አፈ ታሪኮች በተለየ መልኩ የወንጌል ጸሐፊዎች፣ ትክክለኛ ዘገባ ለማስፈር ከፍተኛ ጥረት እንዳደረጉና ለእያንዳንዱ ዝርዝር ጉዳይ ትኩረት እንደሰጡ ከዘገባው ማየት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል፣ በዘገባዎቹ ላይ የብዙ ቦታዎች ስም የተጠቀሰ ሲሆን ከእነዚህ አብዛኞቹን አሁንም ሄዶ መጎብኘት ይቻላል። በዘገባዎቹ ላይ የተጠቀሱት ሰዎች በገሃዱ ዓለም ላይ የነበሩ ናቸው፤ ይህንንም የዓለም ታሪክ ምሁራን አረጋግጠዋል።—ሉቃስ 3:1, 2, 23

      በመጀመሪያውና በሁለተኛው መቶ ዘመን የኖሩ የዓለም ታሪክ ጸሐፊዎች ኢየሱስን በጽሑፎቻቸው ላይ ጠቅሰውታል።a የተገደለበትን መንገድ በተመለከተ በወንጌል ዘገባዎች ላይ የሰፈረው ሐሳብ፣ በዘመኑ ሮማውያን የሞት ቅጣት ከሚፈጽሙበት መንገድ ጋር ይስማማል። በተጨማሪም ዘገባዎቹ በማስረጃ የተደገፉና ሐቀኝነት የሚንጸባረቅባቸው ናቸው፤ እንዲያውም ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የአንዳንዶቹ ድክመት እንኳ በወንጌሎች ላይ ተካቷል። (ማቴዎስ 26:56፤ ሉቃስ 22:24-26፤ ዮሐንስ 18:10, 11) እነዚህ ሁሉ ማስረጃዎች፣ የወንጌል ጸሐፊዎች ስለ ኢየሱስ ያሰፈሩት ዘገባ እውነተኛና ትክክለኛ እንደሆነ በሚገባ ያሳያሉ።

      ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ ምን ማለት ይቻላል?

      ኢየሱስ በአንድ ወቅት የነበረ ሰው መሆኑና መሞቱ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ቢያገኝም ከሞት መነሳቱን ግን የሚጠራጠሩ ሰዎች አሉ። የኢየሱስ ሐዋርያትም እንኳ ጌታቸው ትንሣኤ እንዳገኘ መጀመሪያ ሲነገራቸው አላመኑም ነበር። (ሉቃስ 24:11) ይሁን እንጂ እነዚህም ሆኑ ሌሎች ደቀ መዛሙርቱ፣ ትንሣኤ ያገኘውን ኢየሱስን በተለያዩ ወቅቶች ካዩት በኋላ የነበራቸው ጥርጣሬ በሙሉ ተወገደ። እንዲያውም ኢየሱስ ትንሣኤ ካገኘ በኋላ ከ500 ለሚበልጡ የዓይን ምሥክሮች የተገለጠበት ጊዜ አለ።—1 ቆሮንቶስ 15:6

      ደቀ መዛሙርቱ ሊታሰሩና ሊገደሉ እንደሚችሉ እያወቁ፣ ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን ለሁሉም ሰው ሌላው ቀርቶ እሱን ላስገደሉት ሰዎች እንኳ በድፍረት አውጀዋል። (የሐዋርያት ሥራ 4:1-3, 10, 19, 20፤ 5:27-32) እነዚያ ሁሉ ደቀ መዛሙርት፣ ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ ፍጹም እርግጠኞች ባይሆኑ ኖሮ የዚህን ያህል በልበ ሙሉነት ይናገሩ ነበር? እንዲያውም ክርስትና በዚያ ዘመንም ሆነ ዛሬ ባለው ዓለም ላይ ይህን ያህል ተጽዕኖ እንዲያሳድር ያደረገው ኢየሱስ ትንሣኤ ማግኘቱ ነው።

      ስለ ኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ የሚገልጹት የወንጌል ዘገባዎች፣ ተአማኒ ታሪካዊ መዛግብት መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉትን መሥፈርቶች በሙሉ አሟልተዋል። ዘገባዎቹን በትኩረት ማንበብህ ታሪኩ እውነት መሆኑን እንድታምን ያደርግሃል። ኢየሱስ የሞተውና የተነሳው ለምን እንደሆነ ስትገነዘብ ደግሞ እምነትህ ይበልጥ ይጠናከራል። የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ጉዳይ ያብራራል።

      a በ55 ዓ.ም. ገደማ የተወለደው ታሲተስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “[ክርስቲያኖች] ለሚለው ስም መገኛ የሆነው ክርስቱስ [ክርስቶስ] በጢባርዮስ የንግሥና ዘመን ከአስተዳዳሪዎቻችን አንዱ በነበረው በጳንጥዮስ ጲላጦስ እጅ ከፍተኛ የሆነ ቅጣት ተቀብሏል።” በተጨማሪም ስዊቶኒየስ (አንደኛው መቶ ዘመን)፣ አይሁዳዊው የታሪክ ምሁር ጆሴፈስ (አንደኛው መቶ ዘመን) እንዲሁም የቢቲኒያ አገረ ገዢ የነበረው ትንሹ ፕሊኒ (ሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ) ኢየሱስን ጠቅሰውታል።

      ዓለማዊ ምንጮች ሰፋ ያለ ዘገባ ያልያዙት ለምንድን ነው?

      ኢየሱስ በዓለም ላይ ካሳደረው ከፍተኛ ተጽዕኖ አንጻር በዘመኑ የነበሩ ምንጮች (ከመጽሐፍ ቅዱስ ሌላ) ሰፋ ያለ ዘገባ እንደሚይዙ መጠበቅ ይኖርብናል? አይኖርብንም። ምክንያቱም አንደኛ ነገር፣ ወንጌሎች ከተጻፉ 2,000 ዓመት ገደማ ሆኗቸዋል። በዚያ ዘመን ከተዘጋጁ ሌሎች ጽሑፎች መካከል እስከ ዘመናችን ተጠብቀው የቆዩት በጣም ጥቂት ናቸው። (1 ጴጥሮስ 1:24, 25) ከዚህም ሌላ ኢየሱስ ብዙ ተቃዋሚዎች ነበሩት፤ በመሆኑም ሰዎች በእሱ እንዲያምኑ የሚያደርግ ነገር ይጽፋሉ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው።

      ከሐዋርያቱ አንዱ የሆነው ጴጥሮስ የኢየሱስን ትንሣኤ በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ እሱን በሦስተኛው ቀን አስነሳው፤ ከዚያም ለሰዎች እንዲገለጥ አደረገው፤ የተገለጠው ግን ለሁሉም ሰው ሳይሆን አምላክ አስቀድሞ ለመረጣቸው ምሥክሮች ይኸውም ከሞት ከተነሳ በኋላ አብረነው ለበላንና ለጠጣን ለእኛ ነው።” (የሐዋርያት ሥራ 10:40, 41) ኢየሱስ ለሁሉም ሰው ያልተገለጠው ለምንድን ነው? የኢየሱስ ጠላቶች የሆኑት የሃይማኖት መሪዎች ከሞት መነሳቱን ሲሰሙ ይህ ዜና እንዳይሰራጭ ለማድረግ ሴራ እንደጠነሰሱ የማቴዎስ ዘገባ ይነግረናል።—ማቴዎስ 28:11-15

      ታዲያ ኢየሱስ ትንሣኤው ሚስጥር ሆኖ እንዲቀር ይፈልግ ነበር ማለት ነው? በፍጹም፤ ምክንያቱም ጴጥሮስ በመቀጠል እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ እሱን በሕያዋንና በሙታን ላይ ፈራጅ አድርጎ እንደሾመው ለሰዎች እንድንሰብክና በተሟላ ሁኔታ እንድንመሠክር አዘዘን።” እውነተኛ ክርስቲያኖች በዚያ ዘመን ይህን አድርገዋል፤ አሁንም እንዲህ እያደረጉ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 10:42

  • ኢየሱስ የተሠቃየውና የሞተው ለምንድን ነው?
    መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016 | ቁጥር 2
    • የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች በገነት ውስጥ

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

      ኢየሱስ የተሠቃየውና የሞተው ለምንድን ነው?

      “በአንድ ሰው [በአዳም] አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ።” —ሮም 5:12

      አዳምና ሔዋን የተከለከለውን ፍሬ ሲመለከቱ፤ አዳምና ሔዋን አርጅተው፤ የሬሳ ሣጥን ወደ መቃብር ሲወሰድ

      “ለዘላለም መኖር ትፈልጋለህ?” ተብለህ ብትጠየቅ ምን መልስ ትሰጣለህ? አብዛኞቹ ሰዎች ለዘላለም መኖር እንደሚፈልጉ ቢናገሩም ይህ የሕልም እንጀራ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሞት ያለ ነገር እንደሆነና ማንም ሰው መሞቱ እንደማይቀር ይናገራሉ።

      ይሁንና ጥያቄው ለወጥ ተደርጎ “መሞት ትፈልጋለህ?” ተብለህ ብትጠየቅስ? ጤናማ የሆነ ማንኛውም ሰው መሞት አይፈልግም። ይህ ምን ያሳያል? መከራና ችግር ቢደርስብንም እንኳ ተፈጥሯዊው ፍላጎታችን በሕይወት መኖር ነው። አምላክ ሰዎችን ሲፈጥራቸው በሕይወት የመኖር ፍላጎት እንዲኖራቸው እንዳደረገ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። “ዘላለማዊነትን በልባቸው ውስጥ አኑሯል” ይላል።—መክብብ 3:11

      ይሁንና ሰዎች ለዘላለም እየኖሩ አይደለም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ደግሞስ አምላክ ሁኔታውን ለማስተካከል ያደረገው ነገር አለ? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መልስ የሚያጽናና ሲሆን ኢየሱስ የተሠቃየውና የሞተው ለምን እንደሆነ ለመረዳትም ያስችለናል።

      ሰዎች ለዘላለም የማይኖሩት ለምንድን ነው?

      የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ምዕራፎች፣ አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ይኸውም ለአዳምና ለሔዋን ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንደሰጣቸው ይነግሩናል፤ እንዲህ ያለ ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለባቸውም ገልጾላቸዋል። ዘገባው ቀጥሎም አዳምና ሔዋን፣ አምላክን ሳይታዘዙ በመቅረታቸው ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንዳጡ ይናገራል። ታሪኩ የተቀመጠው ለመረዳት ቀላል በሆነ መንገድ በመሆኑ አንዳንዶች ተረት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ እንደ ወንጌል ዘገባዎች ሁሉ የዘፍጥረት መጽሐፍም እውነተኛ ታሪክ እንደሆነ የሚያሳይ ማስረጃ አለ።a

      አዳም ሳይታዘዝ መቅረቱ ምን አስከተለ? መጽሐፍ ቅዱስ “በአንድ ሰው [በአዳም] አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ” የሚል መልስ ይሰጣል። (ሮም 5:12) አዳም አምላክን ባለመታዘዙ ኃጢአት ሠርቷል። በዚህ ምክንያት ለዘላለም የመኖር አጋጣሚውን ያጣ ሲሆን ውሎ አድሮም ሞተ። እኛም የእሱ ዘሮች በመሆናችን ኃጢአትን ከእሱ ወርሰናል። በዚህም የተነሳ ለሕመም፣ ለእርጅናና ለሞት ተዳርገናል። የምንሞተው ለምን እንደሆነ የሚገልጸው ይህ ሐሳብ፣ በዛሬው ጊዜ ልጆች ከወላጆቻቸው በዘር ስለሚወርሷቸው ነገሮች ሳይንስ ከደረሰበት ግንዛቤ ጋር ይስማማል። ይሁንና አምላክ ሁኔታውን ለማስተካከል ያደረገው ነገር አለ?

      አምላክ ምን አድርጓል?

      አምላክ፣ አዳም ለዘሮቹ ያሳጣቸውን ነገር ይኸውም ለዘላለም የመኖርን አጋጣሚ የሰው ልጆች እንዲያገኙ የሚያስችል ዝግጅት አድርጓል፤ ይህም ዋጋ መክፈል ጠይቆበታል። አምላክ ይህን ያደረገው እንዴት ነው?

      መጽሐፍ ቅዱስ በሮም 6:23 ላይ “የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነው” ይላል። ይህም ሲባል ሞት የኃጢአት ውጤት ነው ማለት ነው። አዳም ኃጢአት ስለሠራ ሞተ። እኛም ኃጢአት ስለምንሠራ የኃጢአት ደሞዝ ከሆነው ሞት አናመልጥም። ይሁንና ኃጢአተኞች የሆንነው በራሳችን ጥፋት አይደለም፤ ስንወለድ ጀምሮ ኃጢአተኞች ነን። ስለዚህ አምላክ በፍቅር ተገፋፍቶ ልጁ ኢየሱስ ‘የኃጢአትን ደሞዝ’ ስለ እኛ እንዲሸከምልን ዝግጅት አደረገ። ይህ ዝግጅት የሚሠራው እንዴት ነው?

      የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች በገነት ውስጥ

      የኢየሱስ ሞት ደስተኞች ሆነን ለዘላለም እንድንኖር መንገድ ከፍቶልናል

      ኃጢአትንና ሞትን የወረስነው አንድ ሰው ይኸውም ፍጹም የነበረው አዳም ባለመታዘዙ ምክንያት በመሆኑ፣ ከኃጢአት ደሞዝ ነፃ እንድንወጣ እስከ ሞት ድረስ ታዛዥ የሆነ አንድ ፍጹም ሰው ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጉዳይ ሲያብራራ “በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደሆኑ ሁሉ በአንዱ ሰው መታዘዝም ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ” ይላል። (ሮም 5:19) እዚህ ላይ የተጠቀሰው ‘አንድ ሰው’ ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ ሰማይን ትቶ ወደ ምድር በመምጣት ፍጹም ሰውb ሆኖ ስለ እኛ ሞተ። በዚህም የተነሳ በአምላክ ዘንድ እንደ ጻድቅ ሆነን መቆጠር እንዲሁም ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ማግኘት ችለናል።

      ኢየሱስ የተሠቃየውና የሞተው ለምንድን ነው?

      ታዲያ ኢየሱስ እኛን ከኃጢአት ደሞዝ ነፃ ለማውጣት መሞት ያስፈለገው ለምንድን ነው? ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ፣ የአዳም ዘሮች ለዘላለም እንዲኖሩ መፍቀዱን የሚገልጽ አዋጅ ማውጣት አይችልም ነበር? እንዲህ የማድረግ ሥልጣን እንዳለው ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ እንዲህ ቢያደርግ የኃጢአት ደሞዝ ሞት እንደሆነ በግልጽ ያስቀመጠውን ሕግ መጣስ ይሆንበታል። ይህ ሕግ ደግሞ ሳይመች ሲቀር፣ ሊሰረዝ ወይም ሊለወጥ የሚችል ተራ ደንብ አይደለም። ፍትሕ እንዲኖር ይህ ሕግ በጣም አስፈላጊ ነው።—መዝሙር 37:28

      አምላክ በዚህ ረገድ ፍትሐዊ የሆነውን እርምጃ ባይወስድ ኖሮ ‘በሌሎች ነገሮችም እንዲሁ ያደርግ ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ የሰው ልጆችን ሊያሳስባቸው ይችል ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ‘ከአዳም ዘሮች መካከል የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ብቁ የሆኑት እነማን እንደሆኑ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ይወስን ይሆን? የገባውን ቃል እንደሚፈጽም እምነት ሊጣልበት ይችላል?’ የሚሉት ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ። አምላክ፣ እኛ መዳን እንድናገኝ ያደረገው ዝግጅት የፍትሕ መሥፈርቱን የተከተለ መሆኑ ምንጊዜም ትክክል የሆነውን እንደሚያደርግ ዋስትና ይሰጠናል።

      አምላክ፣ ኢየሱስ መሥዋዕት ሆኖ እንዲሞት ማድረጉ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንዲከፈትልን አስችሏል። በዮሐንስ 3:16 ላይ የሚገኘውን ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ ልብ በል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” በመሆኑም የኢየሱስ ሞት፣ የአምላክ ፍትሕ ዝንፍ የማይል እንደሆነ ያሳያል፤ ከዚህ ይበልጥ ደግሞ አምላክ ለሰዎች ያለው ታላቅ ፍቅር መግለጫ ነው።

      ይሁንና ኢየሱስ በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ በተገለጸው መንገድ የተሠቃየውና የሞተው ለምንድን ነው? ኢየሱስ በጣም ከባድ በሆነ ፈተና ሥር አልፎ ታማኝነቱን መጠበቁ፣ ዲያብሎስ የሰው ልጆች መከራ ሲደርስባቸው ለአምላክ ታማኝ እንደማይሆኑ የተናገረው ሐሳብ ስህተት መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጧል። (ኢዮብ 2:4, 5) ሰይጣን ፍጹም የነበረውን አዳምን ኃጢአት እንዲሠራ ማድረግ ስለቻለ፣ ሰዎች ፈተና ቢደርስባቸው ለአምላክ ታማኝ እንደማይሆኑ የሰነዘረው ሐሳብ እውነት ሊመስል ይችላል። ያም ሆኖ ልክ እንደ አዳም ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ ከባድ መከራ ቢደርስበትም ለአምላክ ታዛዥ ሆኗል። (1 ቆሮንቶስ 15:45) በዚህ መንገድ ኢየሱስ፣ አዳምም ቢፈልግ ኖሮ አምላክን ለመታዘዝ ሊመርጥ ይችል እንደነበረ አረጋግጧል። ኢየሱስ መከራ ሲደርስበት በመጽናት እኛም ልንከተለው የሚገባ አርዓያ ትቶልናል። (1 ጴጥሮስ 2:21) አምላክ፣ ልጁ ኢየሱስ ፍጹም ታዛዥነት በማሳየቱ፣ በሰማይ የማይሞት ሕይወት በመስጠት ወሮታውን ከፍሎታል።

      የኢየሱስ ሞት አንተን የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

      ኢየሱስ መሞቱ እውነት ነው። የእሱ ሞት፣ ለዘላለም ሕይወት መንገድ ከፍቷል። ታዲያ ለዘላለም መኖር ትፈልጋለህ? ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገን እንዲህ በማለት ገልጿል፦ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ አለባቸው።”—ዮሐንስ 17:3

      የዚህ መጽሔት አዘጋጆች፣ እውነተኛ አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋ እና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መማርህን እንድትቀጥል ያበረታቱሃል። በአካባቢህ የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድ ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው። በተጨማሪም www.pr2711.com/am የተሰኘውን ድረ ገጻችንን በመጎብኘት ጠቃሚ መረጃ ማግኘት ትችላለህ።

      a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 በተባለው መጽሐፍ ገጽ 922 ላይ “ዘ ሂስቶሪካል ካራክተር ኦቭ ጀነስስ” የሚለውን ንዑስ ርዕስ እንዲሁም በጥር 1, 2011 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 4 ላይ የወጣውን “ኤደን ገነት በእውን የነበረ ቦታ ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት፤ ሁለቱም ጽሑፎች በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ናቸው።

      b አምላክ የልጁን ሕይወት ከሰማይ ወደ ማርያም ማህፀን በማዛወር ማርያም እንድትፀንስ አድርጓል፤ ኢየሱስ ከማርያም ኃጢአት እንዳይወርስ ደግሞ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ተከላክሎለታል።—ሉቃስ 1:31, 35

      በመታሰቢያው በዓል ላይ ቂጣው ሲዞር

      ‘ይህን ሁልጊዜ አድርጉት’

      ኢየሱስ ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠቱ በፊት በነበረው ምሽት ከታማኝ ሐዋርያቱ ጋር እያለ የሞቱን መታሰቢያ በዓል አቋቋመ። ለሐዋርያቱ “ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አላቸው። (ሉቃስ 22:19) በመላው ዓለም ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ይህን መመሪያ በመታዘዝ የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ በየዓመቱ ያከብራሉ። ባለፈው ዓመት በበዓሉ ላይ 19,862,783 ሰዎች ተገኝተው ነበር።

      በዚህ ዓመት የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ የሚከበረው ረቡዕ፣ መጋቢት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. (መጋቢት 23, 2016) ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ነው። ከቤተሰብህና ከጓደኞችህ ጋር በበዓሉ ላይ ተገኝታችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን ንግግር እንድታዳምጡ በአክብሮት ተጋብዛችኋል። ንግግሩ፣ የኢየሱስ ሞት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ለአንተ ምን ጥቅም እንዳለው ያብራራል። በስብሰባው ላይ ለመገኘት ክፍያ አይጠየቅም፤ ሙዳየ ምጽዋትም አይዞርም። በዓሉ የሚከበርበትን ሰዓትና ቦታ ለማወቅ በአካባቢህ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች መጠየቅ አሊያም www.pr2711.com/am የተባለውን ድረ ገጻችንን መመልከት ትችላለህ።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ