የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
በፓራጉዋይ ራቅ ብለው የሚገኙ ቀበሌዎችን ማዳረስ ፍሬ አስገኘ
የፓራጉዋይ የመጠበቂያ ግንብ ማህበር ቅርንጫፍ ቢሮ በክልሎቹ በሙሉ የመንግሥቱን የምሥራች መስበክ አስፈላጊ መሆኑን ሙሉ በሙሉ ተገንዝቧል። (ሥራ 1:8) አምላክ በመጪው ታላቅ መከራ ይህን ክፉ ሥርዓት ከማጥፋቱ በፊት ሰዎች ሁሉ ስለ መንግሥቱ ለመማርና ይሖዋን ለማገልገል የሚችሉት አሁን ነው። (ማቴዎስ 24:21, 22) ለጉባኤዎች ባልተመደቡ ቀበሌዎች የሚኖሩ ሰዎችን ለመርዳት ምን በመደረግ ላይ እንዳለ የሚከተሉት ተሞክሮዎች ያሳያሉ። ቅርንጫፍ ቢሮው የሚከተለውን ሪፖርት ልኮአል።
ለጉባኤ ያልተመደቡ ቀበሌዎችን በሙሉ በጊዜያዊ ልዩ አቅኚዎች አማካኝነት ለማዳረስ ዝግጅት ተደረገ። በ1990 የአገልግሎት ዓመት ከህዳር እስከ ጥር በነበሩት ወራት 39 ወንድሞችና እህቶች በጠቅላላው እስካሁን አንድም የመንግሥት አስፋፊ ያልነበረባቸውን መቶ ትላልቅና ትናንሽ ከተሞች አዳርሰዋል። 6,119 መጻሕፍትን፣ 4,262 ትናንሽ መጻሕፍትንና 5,144 መጽሔቶችን ለማደል ችለዋል። በተገኘውም ውጤት አዳዲስ የአስፋፊዎች ቡድን በመቋቋም ላይ ይገኛል።
◻ አንዲት ሴት ለጉባኤ ባልተመደበ ቀበሌ ከምታገለግል አንዲት አቅኚ እህት በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተሰኘውን መጽሐፍ ተቀበለች። አቅኚዋ መጽሐፍ ቅዱስ ልታስጠናት ፈቃደኛ መሆኗን ስትገልጽላት ሴትየዋም ግብዣውን በደስታ ተቀበለች። አቅኚዋ ልታስጠናት በተመለሰች ጊዜ ወይዘሮዋን ብቻ ሳይሆን የሴቲቱ ቤተሰቦች፣ ጓደኞችና ጎረቤቶች ለጥናቱ ተዘጋጅተው ሲጠብቋት አገኘች! ሴትየዋ ጥናቱ በጣም ጥሩ እንደሆነና ይሖዋ የሰጠው ተስፋና በረከት አስደናቂ እንደሆነ በመንገር ጠርታቸው ኖሯል። ይህን የምሥራች ከዚህ በፊት ከማንም ሰው ሰምታው ስለማታውቅ ጎረቤቶቿና ወዳጆቿም መስማት እንደሚኖርባቸው ተሰምቷታል።
አቅኚዋ ጥናቱን በመራች ቁጥር በጥናቱ ላይ ብዙ ሰዎች ከመገኘታቸው የተነሳ መለስተኛ ጉባኤ መሰለ። እነዚህ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ብዙ ጥያቄዎች ይጠይቁና በጥናቱም ይካፈሉ ነበር። አቅኚዋ ቀበሌውን እንዳዳረሰች ከጓደኞቿ ጋር ወደሌላ አካባቢ እንደምትሄድ በገለጸች ጊዜ ያች ወይዘሮ በመጨነቅ እነሱ እንዴት እንደሚሆኑ ጠየቀች። በአቅራቢያው በሚገኝ ጉባኤ ያሉ ወንድሞች ጥናቱን እንዲቀጥሉላቸው ዝግጅት ተደረገ። አሁን እነዚህን ፍላጎት ያሳዩ በግ መሰል ሰዎች ለመርዳት ልዩ አቅኚዎች ተመድበዋል።
◻ አንዲት አቅኚ እህት በሌላ ለጉባኤ ባልተመደበ ቀበሌ ከቤት ወደ ቤት ስትሄድ አሥር ዓመት ከሚሆን ጊዜ በፊት ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተሰኘውን መጽሐፍ ያገኘ ሰው አገኘች። ሰውየው ከዚያ ጊዜ ወዲህ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በምንም ዓይነት መንገድ ሳይገናኝ ቆይቷል። ይሁን እንጂ እሱ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እያለ የሚጠራው ይሖዋ ብቻ እውነተኛ አምላክ እንደሆነና ሱ ብቻ መመለክ እንዳለበት አውቋል። በራሱ አነሳሽነት ለሚያውቀው ሰው ሁሉ ስለ ይሖዋ ሲናገር ቆይቷል። እንዲያውም በየሳምንቱ ሶስት ኪሎሜትር የእግር መንገድ እየተጓዘ ስለአምላክ የሚነግራቸው ፍላጎት ያሳዩ ባልና ሚስት ነበሩ። ምክንያቱንም በራሱ አነጋገር ሲገልጽ “እኔ እየሄድኩ ካልጎበኘኋቸው ይሐዋን ይረሱታል” አለ። ከእነዚህ ባልና ሚስት በተጨማሪ ይህ ፍላጎት ያለው ሰው ስለሰበከላቸው ብቻ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው የሚፈልጉ ሌሎች አሥር የሚሆኑ ሰዎች ነበሩ።
የሚደንቀው ነገር አቅኚዋ ይህን ሰው ከማግኘቷ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ አንድ የአካባቢው ቄስ ካጀቡት ሰዎች ጋር የድንግል ምስል ይዞ ወደቤቱ ሊገባ ሲል በምስሎች እንደማያምን በማስረዳት እንዳይገባ ከልክሎት ነበር። ቄሱ እጅግ ተናዶ ነበር። ሰውየው ያን ዕለት ማታ ይሖዋ እንዲረዳው ጸለየ። ስለዚህ አቅኚዋ ስታገኘው ምን ያህል ስሜቱ እንደተቀሰቀሰና እንደተደሰተ ለመገመት ትችላላችሁ። ወዲያውኑም ሥርዓት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ ዝግጅት ተደረገ። ሰውየውም ከቲኦክራቲካዊው ድርጅት ጋር በመተባበር ዕድገት ማሳየቱን ቀጥሎአል።
ወንድሞች በእነዚህ ለጉባኤ ባልተመደቡ ቀበሌዎች ሠፊ ምሥክርነት ለመስጠት ሲጥሩ በፓራጉዋይ ያለውን መከር የመሰብሰብ ሥራ ይሖዋ በእርግጥ እየባረከው ነው።—ማቴዎስ 24:14