የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • sg ጥናት 10 ገጽ 49-54
  • የማስተማርን ችሎታ ማዳበር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የማስተማርን ችሎታ ማዳበር
  • ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ‘ለማስተማር ጥበብህ’ ትኩረት ስጥ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህን ልብ ለመንካት ጣር
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1993
  • እውቀት በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት ደቀ መዛሙርት ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1996
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት አድርገው እንዲጠመቁ መርዳት—ክፍል ሁለት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
ለተጨማሪ መረጃ
ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
sg ጥናት 10 ገጽ 49-54

ጥናት 10

የማስተማርን ችሎታ ማዳበር

1-3. ማስተማር ምን ነገሮችን ያጠቃልላል? እንዴት ያሉ የማስተማር አጋጣሚዎችን እናገኛለን?

1 እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ታላላቅ አስተማሪዎቻችን አድርገን የምንመለከተው ይሖዋ አምላክንና ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። እንደ መዝሙራዊው “ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ” ብለን እንጸልያለን። (መዝ. 143:10) በተጨማሪም ኢየሱስን “መምህር ሆይ” ብለው ይጠሩት የነበሩትን የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን የመሰለ ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል። በእርግጥም ኢየሱስ ታላቅ አስተማሪ ነበር። የተራራ ስብከቱን እንደፈጸመ “ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፤ . . . እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና።” (ማቴ. 7:28, 29) ታላላቆቹ አስተማሪዎች ይሖዋና ኢየሱስ ናቸው። እኛም እነርሱን ለመምሰል እንፈልጋለን።

2 ማስተማር መዳበር የሚያስፈልገው ችሎታ ነው። የማስተማር ሥራ አንድ ነገር መቼ፣ እንዴት፣ ለምን፣ የት እና ምን እንደተደረገ መግለጽን የሚያጠቃልል ነው። ማንኛውም ክርስቲያን በተለይ ኢየሱስ “እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ሲል የሰጠውን ትዕዛዝ ለመፈጸም የማስተማር ችሎታውን ማዳበር ይኖርበታል። (ማቴ. 28:19, 20) ይህ ሥራ ችሎታ የሚጠይቅ መሆኑን ሐዋርያው ጳውሎስ “በትዕግሥትና በጥሩ የማስተማር ዘዴ አጥብቀህ ምከር” በማለት ለጢሞቴዎስ ከሰጠው ምክር ለመረዳት ይቻላል። — 2 ጢሞ. 4:2 አዓት

3 ሌሎችን የምናስተምርባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። ወላጆች ልጆቻቸውን የማስተማር ግዴታ አለባቸው። የምሥራቹ አዋጅ ነጋሪዎች በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት ፍላጎት ያላቸውን አዳዲስ ሰዎች ማስተማር ይኖርባቸዋል። አዳዲስ አስፋፊዎችን ማሠልጠን አስፈላጊ የሚሆንባቸው ጊዜያት አሉ። ብዙ ወንድሞች ደግሞ በአገልግሎት ስብሰባም ሆነ በሕዝብ ንግግር ላይ የሚገነባ ንግግር ይሰጣሉ። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የሚካፈሉ ተማሪዎች በሙሉ በአስተማሪነት ረገድ ያደረጉትን እድገት ለማሳየት ልባዊ ጉጉት ሊኖራቸው ያስፈልጋል። በዚህ የማስተማር አገልግሎት የመካፈል ችሎታህን ባዳበርክ መጠን እውነተኛ እርካታና የጥረትህን ዋጋ ታገኛለህ። ለአንድ ሰው የአምላክን ቃል አስተምሮ ጥሩ መንፈሳዊ እድገት ሲያሳይ የመመልከትን ያህል የሚያስደስት ነገር የለም።

4, 5. ትምህርት በምንሰጥበት ጊዜ በማንና በምን ላይ እንመካለን?

4 በይሖዋ መታመን። ጥሩ የምሥራቹ አስተማሪ ለመሆን ከሚያስፈልጉት ነገሮች ትልቁ በይሖዋ ላይ መታመን ነው። በይሖዋ መመካት፣ የእርሱን እርዳታ መጠየቅና በሁሉም ነገር ይሖዋን ማሰብ አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 3:5, 6) ኢየሱስ እንኳ “ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም” ብሎአል። (ዮሐ. 7:16) በጽሑፍ በሰፈሩት ንግግሮቹ ላይ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከግማሽ ከሚበልጡት በቀጥታ ጠቅሶአል ወይም ሐሳባቸውን ገልጾአል። ስለዚህ ሌሎችን በምታስተምርበት ጊዜ ኢየሱስ እንዳደረገው በአምላክ የእውነት ቃል ላይ መመካት ይኖርብሃል። ለሚቀርብልህ ጥያቄ ሁሉ መልስ የምትሰጠው ከአምላክ ቃል መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ሰዎች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን የሚያስፈልጋቸውን ዕውቀት የሚያገኙበት ዋነኛው መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። — 2 ጢሞ. 3:16

5 በይሖዋ ላይ የምትታመን ከሆነ ብቃት እንደሌለህ ሆኖ ሊሰማህ አይገባም። ይሖዋ በእውነት ቃሉ ውስጥ የተገለጸውን ዓላማውን እንድናስተውል ይረዳናል። ስለነዚህ እውነቶች ያለህን ዕውቀት ለሌሎች ካካፈልክ ይሖዋ ይደግፍሃል። “እኔ ማስተማር የምችል ሰው አይደለሁም” በማለት ወደኋላ ማለት አይገባህም። በይሖዋ ላይ ብትተማመንና በጸሎት ብትጠይቀው ጥሩ አስተማሪ ለመሆን ትችላለህ። — 2 ቆሮ. 3:5

6–8. ጥሩ አስተማሪ በመሆን ረገድ ዝግጅት ምን ድርሻ አለው?

6 ዝግጅት። የምታስተምረውን ርዕሰ ጉዳይ በሚገባ ማወቅን ሊተካ የሚችል ነገር የለም። ሌላ ሰው ከማስተማርህ በፊት አንተ ራስህ ትምህርቱን በግልጽ መረዳት ይኖርብሃል። (ሮሜ 2:21) የዕውቀት አድማስህ እየሰፋ በሄደ መጠን የአስተማሪነት ችሎታህም በዚያው መጠን ይሻሻላል። ቢሆንም ያለህ ዕውቀት ከጥቂት መሠረታዊ እውነቶች ያላለፈም ቢሆን አስተማሪ ልትሆን ትችላለህ። ስለምታውቀው ነገር ተናገር። ትናንሽ ልጆች እንኳ ከወላጆቻቸው የተማሩአቸውን እውነቶች ለትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ሊያስተምሩ ይችላሉ። ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የማስተማር ችሎታህን እንድታዳብር ሊረዳህ ይችላል።

7 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምትመራ ወይም ንግግር የምትሰጥ ከሆነ መጀመሪያ ትምህርቱን በመደገፍ የቀረቡትን ምክንያቶች በግልጽ ተረዳ። ነገሩ ለምን እንደዚያ እንደሆነ ለመረዳት ሞክር። ሐሳቦቹን በራስህ አነጋገር ለመግለጽ ሞክር። የቀረቡት የጥቅስ ማስረጃዎች እንዲገቡህ አድርግ። አንድን ነጥብ ለማስረዳት በጥቅሶቹ እንዴት እንደምትጠቀም ተዘጋጅ።

8 ሌላው የዝግጅታችን ገጽታ ተማሪው በቀድሞ ሃይማኖቱ ምክንያት በአእምሮው ውስጥ ሊነሱበት የሚችሉትን ጥያቄዎች ግምት ውስጥ አስገብቶ በቅድሚያ መዘጋጀት ነው። ይህም ከተማሪው ሁኔታ ጋር የሚስማማ ትምህርት ለማዘጋጀት ይረዳሃል። ያለውን እውቀትና ማስተዋል በቅድሚያ ማወቅህ አዲስ እውቀት ለመስጠትና ወደፊት እንዲራመድ ለመርዳት የሚያስችልህን ሁኔታ ያመቻችልሃል። ሌላው ተማሪ ደግሞ በአስተዳደጉ ምክንያት ለየት ያለ ጥያቄ ሊጠይቅህ ስለሚችል ሌላ ዓይነት ዝግጅት ማድረግ ሊያስፈልግህ ይችላል። ስለዚህ ተማሪህን በሚገባ ማወቅህ በዝግጅትህ ረገድ ሊረዳህ ይችላል።

9. ተማሪዎች በራሳቸው አነጋገር መልስ እንዲሰጡ እንዴት ማበረታት ይቻላል?

9 ጥያቄዎች። ጥሩ አስተማሪ በመሆን ረገድ ጥያቄዎች በጣም ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታሉ። ይህንንም ኢየሱስ በተደጋጋሚ በተግባር አሳይቷል። (ሉቃስ 10:36) ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምትመራበት ጊዜ በጽሑፉ ላይ በሰፈሩት ጥያቄዎች በመጠቀም የኢየሱስን ምሳሌ ልትከተል ትችላለህ። ይሁን እንጂ በደንብ አጣርተህ የምታስተምር ከሆነ ተማሪው መልሶቹን ከመጽሐፉ ብቻ ቢያነብ በቂ እንደሆነ አድርገህ በመቁጠር አታልፍም። ተማሪው ከመጽሐፉ በቀጥታ አንብቦ የሚመልስ ከሆነ መልሶቹን በራሱ አነጋገር እንዲገልጽ የሚያደርገው ተጨማሪ ጥያቄ ልትጠይቀው ትችላለህ። አንዳንድ ጊዜ “መልሱ ትክክል ነው፤ ግን እንዴት በራስህ አነጋገር ልትገልጸው ትችላለህ?” ብለህ መጠየቅ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል።

10. በመሪ ጥያቄዎች እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ግለጽ።

10 በተጨማሪም መሪ ጥያቄዎችን መጠየቅ ለማስተማር ጠቃሚ እንደሆነ ልትገነዘብ ትችላለህ። መሪ ጥያቄዎች የሚባሉት ሰውዬው ቀደም ብሎ የሚያውቃቸውን ነገሮች መሠረት በማድረግ ከዚህ በፊት ወዳላሰበበት መደምደሚያ እንዲደርስ ለማድረግ የምትጠቀምባቸው ጥያቄዎች ናቸው። (ማቴ. 17:25, 26፤ 22:41–46) ‘ይህ ሰው ይህንና ያንን ያውቃል። ምክንያታዊ ቅደም ተከተላቸውን የጠበቁ ጥያቄዎችን ብጠይቀው ደግሞ ትክክለኛው መደምደሚያ ላይ ሊደርስ ይችላል። መሪ የሆኑትን ጥያቄዎች ትቼ በቀጥታ ዋናውን ጥያቄ ብጠይቀው ግን የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ይደርሳል’ ብለህ ታስባለህ ማለት ነው። በሌላ አነጋገር ተማሪው ትክክለኛው መልስ ላይ ሊያደርሰው የሚችል እውቀት ቢኖረውም እዚህ መልስ ላይ ለመድረስ እርዳታ ያስፈልገዋል። እርግጥ ከዚህ ሁሉ የሚቀልለው መልሱን በቀጥታ መናገር ነው። በመሪ ጥያቄዎች ብትጠቀም ግን መልሱን የተናገረው ተማሪው ራሱ ስለሆነ መልሱ የበለጠ ተቀባይነት ይኖረዋል። በተጨማሪም የማሰብ ችሎታውን ያዳብርለታል። ጥያቄዎችህ በምክንያታዊ አስተሳሰብ ደረጃ በደረጃ ወደ ትክክለኛው መደምደሚያ ያደርሱታል። ይህም ውሎ አድሮ በጣም ከፍተኛ የሆነ ጥቅም የሚያስገኝለት ይሆናል።

11. በአመለካከት ጥያቄዎች እንዴት መጠቀም ይቻላል?

11 አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የአመለካከት ጥያቄ መጠየቅ ተፈላጊ ሊሆን ይችላል። በእነዚህ ጥያቄዎች አማካኝነት ተማሪው በአንድ የተወሰነ ጉዳይ ላይ ምን ዓይነት እምነት እንዳለው ለማወቅ ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል አምላክ ስለ ምንዝር ያወጣው ሕግ ምን እንደሆነ ልትጠይቀው ትችላለህ። ምንዝር መጥፎ እንደሆነ የሚገልጽ ጥቅስ ሊጠቅስ ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ተማሪው ከሰጠው መልስ ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማልን? ራሱ ነገሩን እንደዚያ አድርጎ ይመለከተዋልን? ስለ ምንዝር ራሱ ምን ዓይነት አስተሳሰብ እንዳለው ለማወቅ አንድ ጥያቄ ልትጠይቅ ትችላለህ። “ምንዝር ብንፈጽም ወይም ባንፈጽም ምን ልዩነት ያመጣል?” ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ። ከሚሰጠው መልስ በምን ረገድ ተጨማሪ እርዳታ ሊሰጠው እንደሚያስፈልግ ልትገነዘብና አስፈላጊውን እርዳታ ልትሰጠው ትችላለህ። የአመለካከት ጥያቄዎች የተማሪዎችህን ልብ ለመንካት ያስችሉሃል።

12, 13. ከቤት ወደ ቤት በምናገለግልበት ጊዜም ይሁን መድረክ ላይ ሆነን ንግግር በምንሰጥበት ጊዜ በጥያቄዎች መጠቀም ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?

12 በተጨማሪም ጥያቄዎች ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት በጣም ይጠቅማሉ። ለምሳሌ ያህል የቤቱ ባለቤት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲገባው በተሻለ ሁኔታ ለመርዳት እንድትችል አስተሳሰቡን ለማወቅ ትፈልግ ይሆናል። በተጨማሪም የራሱን አስተያየት እንዲናገር አጋጣሚ ቢሰጠው አንተ የምትናገረውን ለማዳመጥ የበለጠ ፍላጎት ስለሚኖረው ጥያቄዎችን ጠይቀህ የራሱን ሐሳብ እንዲገልጽ ፍቀድለት።

13 መድረክ ላይ ሆነህ ንግግር በምትሰጥበት ጊዜም እንኳ ጥያቄዎችን ጠይቀህ መልስ እንዲሰጥህ የምትጠባበቅበት ጊዜ ይኖራል። ስለዚህ አድማጮች መልስ እንዲሰጡ ትጋብዛለህ። ይሁን እንጂ መልስ የማይጠበቅባቸው ጥያቄዎች መጠየቅ አስፈላጊ የሚሆንባቸው ጊዜያት ይኖራሉ። እንደነዚህ ያሉት ጥያቄዎች የሚጠየቁት የማሰብ ችሎታን ለመቀስቀስ ነው እንጂ አድማጮች መልስ እንዲሰጡባቸው አይደለም። (ሉቃስ 12:49–51) መልሱን የምትሰጠው አንተ ራስህ ነህ። ተከታታይ ጥያቄዎችን ከጠየቅህ በኋላ በመጨረሻ ላይ መልሳቸውን ለመስጠት የምትፈልግበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። የምትጠይቃቸው ጥያቄዎች ዓይነት በአድማጮችህና በምትሰጠው ትምህርት ላይ የተመካ ነው።

14, 15. ምሳሌ መስጠትና ዋና ዋና ሐሳቦችን መደጋገም ለምን ዓላማ ያገለግላሉ?

14 ምሳሌዎች። ከዋነኞቹ የኢየሱስ የማስተማሪያ ዘዴዎች አንዱ በምሳሌዎች መጠቀም ነበር። ዛሬም ቢሆን ክርስቲያን አስተማሪዎች በተመሳሳይ ጥሩ የሆኑ ትምህርቶች በአድማጮቻቸው አእምሮ ውስጥ እንዲቀረጹ ለማድረግ ከኑሮና ከሕይወት ተሞክሮ በተገኙ ምሳሌዎች ይጠቀማሉ። (ማቴ. 13:34, 35) ከበድ ያሉና የተወሳሰቡ ምሳሌዎች ለመከታተል የሚያስቸግሩ ከመሆናቸውም በላይ ልታስረዳ ያሰብከውን ነጥብ ሊያጨልሙት ይችላሉ። በያዕቆብ መልእክት ውስጥ ብዙ ምሳሌዎች ቀርበዋል። የባሕር ሞገድ፣ የመርከብ መልሕቅ፣ የፈረስ ልጓም፣ መስተዋት ወዘተ ተጠቅሰዋል። እነዚህ ምሳሌዎች ሁሉ የተወሰዱት በጣም ከተለመዱ የሕይወት ገጽታዎች ነው። ንቁ የሆነ አስተማሪ የሚሰጣቸው ምሳሌዎች ለተማሪው ሁኔታ፣ ዕድሜ፣ ሃይማኖት፣ ባሕልና ወዘተ የሚስማሙ መሆናቸውን ያረጋግጣል። ንግግር ወይም ዲስኩር በምታደርግበት ጊዜም ሆነ አንድን ግለሰብ በምታስተምርበት ጊዜ በምሳሌዎች ልትጠቀም ትችላለህ።

15 መደጋገም። መድረክ ላይ ሆነህ ንግግር የምትሰጥም ሆንክ በግል ቤት ውስጥ አንድን ግለሰብ የምታስተምር ጥሩ አስተማሪ ለመሆን መደጋገም በጣም አስፈላጊ ነው። ቁልፍ የሆኑ ቃላት፣ ሐረጎችና በተለይ ጥቅሶች በተማሪህ አእምሮ ውስጥ እንዲቀረጹ ለማድረግ መጣር ይኖርብሃል። የተማሪ ንግግር የምታቀርብ ከሆነ የምታነጋግረውን ባለቤት የክለሣ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ዋና ዋና ነጥቦችን ጎላ ለማድረግ ትችላለህ። ይህን በማድረግህም ተማሪው ዋናውን ሐሳብ መረዳቱን ማረጋገጥ ትችላለህ። ኢየሱስ “ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን?” ሲል እንደጠየቀው ታደርጋለህ ማለት ነው። — ማቴ. 13:51

16. አንድ ተናጋሪ ጥሩ አስተማሪ ከሆነ ንግግሩን ካዳመጥክ በኋላ ምን ነገሮችን ለማስታወስ ትችላለህ?

16 የሚያስተምሩ ንግግሮች። ብዙ ትምህርት ያገኘህባቸውን ንግግሮች በአድናቆት ታስታውሳለህ። ስለዚህ አንዳንድ ተናጋሪዎች ጥሩ አስተማሪዎች የሆኑበትን ምክንያት አስተውል። ንግግራቸውን ለማስታወስ ቀላል የሆነበትን ምክንያት ተገንዘብ። ንግግራቸው የተጣደፈ አይደለም። አድማጮች የሚመልሱአቸውን ጥያቄዎች ወይም የማሰብ ችሎታቸውን ብቻ የሚቀሰቅሱና መልስ የማይጠበቅባቸውን ጥያቄዎች ይጠይቃሉ። ቁልፍ ጥቅሶችን አውጥተህ እንድትመለከትና በሚያነቡበት፣ በሚያብራሩበትና ዋና ዋና ሐሳቦቹን በሚያጎሉበት ጊዜ እንድትከታተል ይጋብዛሉ። ሥዕላዊ መግለጫዎችን የሚጠቀሙ ተናጋሪዎችም አሉ። በማንኛውም ጊዜ ቢሆን በአጭሩ ነካ ነካ የተደረጉ በርካታ ነጥቦችን ከማስታወስ ይልቅ በሚገባ የተብራሩ ጥቂት ነጥቦችን ማስታወስ እንደሚቀልል ትገነዘባለህ። ጥሩ የማስተማር ዘዴዎች በሚገባ ከተሠራባቸው ንግግሩን የሚያዳምጡ ሰዎች የንግግሩን መልእክት፣ ዋና ዋናዎቹን ነጥቦችና ጎላ ብለው የተብራሩ አንድ ወይም ሁለት ጥቅሶችን አስታውሰው ለመናገር ይችላሉ።

17, 18. ሰዎች በታላላቆቹ አስተማሪዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የምናደርገው እንዴትና ለምንድን ነው?

17 ትኩረታቸውን በታላላቆቹ አስተማሪዎች ላይ እንዲያደርጉ መርዳት። ክርስቲያን አስተማሪ እንደመሆንህ መጠን በማንኛውም ጊዜ አድማጮችህ የሕይወት ሁሉ ምንጭ ይሖዋ አምላክ መሆኑንና ኢየሱስ ክርስቶስም ሕይወትና በረከት የሚገኝበት የይሖዋ ወኪል መሆኑን ምን ጊዜም እንዲያስታውሱ ማድረግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብሃል። (ዮሐ. 17:3) ለእነዚህ ሁለት ታላላቅ አስተማሪዎች የጋለ አድናቆት እንዲያድርባቸው ለማድረግ መጣር ያስፈልጋል።

18 ጥሩ የማስተማር ችሎታ ማዳበር ስትጀምር ፍቅር የሚኖረውን ድርሻ መገንዘብ ትጀምራለህ። አንድ ተማሪ ይሖዋ አምላክን ሲያፈቅር በታማኝነት ያገለግለዋል። ስለዚህ ጥናት በምትመራበት ጊዜ ተስማሚ የሆኑ ነጥቦች ሲያጋጥሙህ አምላክ ለኃጢአተኛው የሰው ዘር ምን እንዳደረገና ምን በማድረግ ላይ እንዳለ አስገንዝበው። የአምላክን ጥበብ፣ ፍትሕ፣ ፍቅርና ኃይል ጎላ አድርገህ ግለጽለት። እነዚህ ባሕርያት በሙሉ አንድ ላይ ተቀናጅተው ታዛዥ ለሆነው የሰው ልጅ በርካታ ጥቅሞችን አስገኝተዋል። ተማሪው ቀና ልብ ካለው ከጊዜ በኋላ ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ የመቆም ስሜትና ስሙንም በሚያስከብር ሥራ ለመካፈል ጠንካራ ፍላጎት ያድርበታል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ