የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት አስተምሩ
    መጠበቂያ ግንብ—1991 | ጥር 15
    • በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት አስተምሩ

      “በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት ከማስተማር ዝንፍ አላልኩም።”​—ሥራ 20:20 ባይንግተን ትርጉም

      1. አንድ የካቶሊክ ቄስ የይሖዋ ምስክሮች ስለሚያደርጉት የቤት ወደ ቤት አገልግሎት ውጤታማነት ምን ብለዋል?

      ዘ ፕሮቪደንስ ሳንደይ ጆርናል የተባለው ጋዜጣ በጥቅምት 4, 1987 እትሙ ላይ “ካቶሊኮች ወንጌልን ከቤት ወደ ቤት እየወሰዱ ነው” የሚል ርዕስ አውጥቶ ነበር። ጋዜጣው እንደዘገበው ይህ ሥራ የተጀመረበት ዋና ዓላማ “ከቀዘቀዙ ምዕመናን አንዳንዶቹን መልሶ ለማንቃት ነው።” በፀጋ ሰበካ የወንጌላዊነት ሥራ ዲሬክተር የሆኑት ቄስ ጆን አላርድ የሚከተለውን እንደተናገሩ ተገልጾአል፦ “ብዙ ትችት እንደሚቀሰቀስ የታወቀ ነው። ሰዎች ‘እንደ ይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት መሄድ ጀመሩ’ ይሉናል። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ከዚህ ሥራቸው የተሳካ ውጤት አግኝተዋል። በዚህ ክፍለ ሀገር [በሮድ ደሴት ዩ.ኤስ.ኤ.] ወደ ማንኛውም የመንግሥት አዳራሽ ብትሄዱ ከዚህ ቀደም ካቶሊኮች በነበሩ ሰዎች የተሞሉ ጉባዔዎች እንደምታገኙ እርግጠኛ ነኝ።”

      2. ምን ተገቢ ጥያቄ ይነሳል?

      2 አዎ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት በሚያደርጉት አገልግሎት በደንብ ታውቀዋል። ይሁን እንጂ ከቤት ወደ ቤት የሚሄዱት ለምንድ ነው?

      ሐዋርያዊው ዘዴ

      3. (ሀ) ኢየሱስ ለተከታዮቹ ምን ሥራ ሰጥቶአል? (ለ) የጥንቶቹ የኢየሱስ ተከታዮች የተሰጣቸውን ሥራ የፈጸሙት በምን ዋነኛ ዘዴ ነበረ?

      3 ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ የሚከተለውን ከፍተኛ ትርጉም ያለው ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፦ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጓቸው። እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴዎስ 28:19, 20) ይህ ሥራ የሚከናወንበት ዋነኛ መንገድ በ33 እ.ዘ.አ. ከዋለው የጴንጠቆስጤ በዓል በኋላ በግልጽ ታወቀ። “ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው [ከቤት ወደ ቤት] ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተውም ነበር።” (ሥራ 5:42) ሃያ ዓመት ከሚያክል ጊዜ በኋላም ሐዋርያው ጳውሎስ ከቤት ወደ ቤት ያገለግል ነበር። በኤፌሶን ከተማ ይኖሩ ለነበሩ ሽማግሌዎች “በጉባዔም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም” ሲል ያሳሰበው በዚህ ምክንያት ነበር።​—ሥራ 20:20

      4. ሥራ 5:42 እና ሥራ 20:20 የኢየሱስ ተከታዮች ስብከት ከቤት ወደ ቤት የሚዳረስ መሆኑን ይገልጻሉ ለማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

      4 በሥራ 5:42 ላይ “ከቤት ወደ ቤት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ካትኦይኮን ነው። እዚህ ላይ ካታ የተባለው ቃል በየ__ የሚል ትርጉም አለው። ስለዚህ የደቀመዛሙርቱ ስብከት በየቤቱ ይዳረስ ነበር ማለት ነው። ራንዶልፍ ኤ ዬገር ስለ ሥራ 20:20 ሲያብራሩ የሚከተለውን ጽፈዋል። ጳውሎስ “በሕዝባዊ ስብሰባዎችም [ዴሞሲያ] ሆነ ከቤት ወደ ቤት ([ካታ] የተባለው ጠቃሽ አመልካች ያለበት መስተዋድድ ተጨምሮበታል) አስተምሮአል። ጳውሎስ ሶስት ዓመት ለሚያክል ጊዜ በኤፌሶን ከተማ ኖሮ ነበር። እያንዳንዱን ቤት ጎብኝቶ ነበር፣ ወይም ቢያንስ ቢያንስ ለሁሉም ሰው ሰብኮ ነበር። (ሥራ 20 ቁጥር 26) ይህም ከቤት ወደ ቤት የሚደረገውም ሆነ በሕዝባዊ ስብሰባዎች የሚደረገው ወንጌላዊ ሥራ ትክክል ለመሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ ነው።”

      5. ጳውሎስ በሥራ 20:20 ላይ የተናገረው ለሽማግሌዎች ስለተደረገ ማህበራዊ ጥየቃ ወይም ስለ እረኝነት ጥየቃ ነበር ለማለት የማይቻለው ለምንድን ነው?

      5 በሉቃስ 8:1 ላይም ካታ በተመሳሳይ ትርጉም ተሠርቶበታል። ኢየሱስ “ከከተማ ወደ ከተማ፣ ከመንደር ወደ መንደር” እንደሰበከ ይናገራል። ጳውሎስ በሥራ 20:20 ላይ የተጠቀመው ካትኦይኩስ የሚለውን የብዙ ቁጥር ነው። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህንን ቃል “በቤታችሁ ውስጥ” ብለው ተርጉመዋል። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ለሽማግሌዎች ማህበራዊ ጥየቃ ወይም ለእምነት ባልደረቦቹ የእረኝነት ጥየቃ ስለማድረጉ ብቻ መናገሩ አልነበረም። ምክንያቱም “ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንሥሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች” መሰከርሁ ብሎአል። (ሥራ 20:21) የእምነት ባልደረቦቹ ቀድሞውኑ ንሥሐ ገብተው በኢየሱስ አምነዋል። ስለዚህ የሐዋርያት ሥራ 5:42ም ሆነ 20:20 የሚናገሩት “ከቤት ወደ ቤት” ወይም ከበር ወደ በር ለማያምኑ ሰዎች ስለመስበክ ነው።

      ምትክ የማይገኝለት ዘዴ ነው

      6. ጳውሎስ በኤፌሶን ስለፈጸመው የስብከት ሥራ ምን ተብሎአል?

      6 አቢል አቦት ሊቨርሞር በ1844 ሐዋርያት ሥራ 20:20 ላይ ስለሚገኘው የጳውሎስ ቃል ሲያብራሩ እንዲህ ጽፈዋል፦ “ታላቁን ሥራውን በየቤቱ ለግለሰቦች በማድረስና የሰማይን እውነት ለኤፌሶን ሰዎች ቃል በቃል በየጎጆአቸውና በየልባቸው ተሸክሞ በመውሰድ በትጋት ይፈጽም ነበር እንጂ በሕዝባዊ ስብሰባዎች ንግግር በማድረግ ብቻ በቃኝ ብሎ ሌሎቹን የመስበኪያ መሣሪያዎች አልተወም።” በቅርብ ጊዜ እንደተገለጸው “ወንጌልን ከቤት ወደ ቤት መስበክ ከመጀመሪያ ጀምሮ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ተለይተው የታወቁበት ሥራ ነበር። (ከሥራ 2:46 እና 5:42 ጋር አወዳድር). . . . [ጳውሎስ] በኤፌሶን ይኖሩ ለነበሩ አይሁዳውያንም ሆን ለአሕዛብ የነበረበትን ኃላፊነት በሚገባ ስለተወጣ እነዚህ ሰዎች ቢጠፉ የሚያመካኙበት ሰበብ አይኖራቸውም።”​—ዘ ዌስልያን ባይብል ኮሜንተሪ ጥራዝ 4 ገጽ 642-3

      7. አምላክ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጉትን ከቤት ወደ ቤት አገልግሎት ተቀብሎታል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

      7 ለተሰበሰበ ሕዝብ ንግግር ማድረግ ምሥራቹን በማሳወቅ ረገድ የራሱ ቦታ ቢኖረውም በየበራፉ ሰዎችን በግል ለማነጋገር ምትክ ሊሆን አይችልም። በዚህ ረገድ ምሑሩ ጆሴፍ አዲሰን አሌክሳንደር “ቤተክርስቲያን የቤተክርስቲያንና የቤት ውስጥን ስብከት የሚተካ ወይም የሚተካከል ዘዴ አልፈለሰፈችም” ብለዋል። ምሑሩ ኦ.ኤ.ሒልስ እንዳሉት “በሕዝብ ስብሰባ ማስተማርና ከቤት ወደ ቤት ማስተማር ጎን ለጎን መሄድ ይገባቸዋል።” የይሖዋ ምሥክሮች በሣምንታዊ የሕዝብ ስብሰባዎች በሚሰጡ የሕዝብ ንግግሮች አማካኝነት ትምህርት ይሰጣሉ። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከቤት ወደ ቤት የማዳረሱ ሐዋርያዊ ዘዴ ጥሩ ውጤት ስለማስገኘቱ በቂ ማስረጃ አላቸው። ይሖዋም ይህን ሥራ እንደሚደግፈው የተረጋገጠ ነው። ምክንያቱም በዚህ አገልግሎት አማካኝነት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከፍ ወዳለው የአምልኮ ቦታው በየዓመቱ እንዲጎርፉ በማድረግ ላይ ነው።​—ኢሳይያስ 2:1-4፤ 60:8, 22

      8. (ሀ) ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው አገልግሎት ውጤታማ ስለሆነበት ምክንያት ምን ተብሎአል? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች በየደጃፉ በሚያደርጉት ስብከትና በሌሎቹ ምሥክርነት የመስጠት ሥራዎች ረገድ ከጳውሎስ ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?

      8 ሌላ ባለሥልጣን “ሰዎች በአብያተ ክርስቲያናት ደጆች ከሚሰጣቸው ትምህርት ይልቅ በቤታቸው ደጃፍ የሚሰጣቸውን ትምህርት ማስታወስ ይቀላቸዋል” ብለዋል። ጳውሎስም አዘውትሮ በየደጃፉ በመሄድ ጥሩ የአገልጋይነት አርዓያ ትቶልናል። “በምኩራቦችና በገበያ ቦታዎች በመስበክና ዲስኩር በማድረግ ብቻ በቃኝ ብሎ አያውቅም” ሲሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ኤድዊን ደብልዩ ራይስ ጽፈዋል። “ሁልጊዜ ከቤት ወደ ቤት በትጋት ያስተምር ነበር። በኤፌሶን ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ለመመለስ ከክፋት ጋር ከቤት ወደ ቤት፣ እጅ ለእጅ፣ ፊት ለፊት ተጋድሎአል።” የይሖዋ ምሥክሮች በየደጃፉ ከሰዎች ጋር በነፍስ ወከፍ መነጋገር ውጤታማ መሆኑን ተገንዝበዋል። ከዚህም በላይ ተመላልሶ መጠየቅ ያደርጋሉ። ከተቃዋሚዎች ጋር እንኳን ቢሆን በምክንያታዊነት ሊወያዩ ከፈለጉ ለመነጋገር ፈቃደኞች ናቸው። ልክ እንደ ጳውሎስ ናቸው። ኤፍ ኤን ፔሉቤት ስለ ጳውሎስ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የጳውሎስ ሥራ በስብሰባዎች ብቻ የተወሰነ አይደለም። ጠያቂ ሰው ወይም ፍላጎት ያለው ወይም ተቃዋሚ እንኳን ቢሆን ስለ ሃይማኖት ለመነጋገር ፈቃደኛ የሆነ ሰው ሲያገኝ በነፍስ ወከፍ እያነጋገረ በየቤቱ ይዘዋወር እንደነበረ አያጠራጥርም።”

      ሽማግሌዎች ግንባር ቀደም መሆን ይኖርባቸዋል

      9. ጳውሎስ ለሽማግሌዎች ምን ምሳሌ ትቶአል?

      9 ጳውሎስ ለሽማግሌዎች ምን ምሳሌ ትቶአል? ደፋርና ታከተኝ የማይሉ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የምሥራቹን የሚሰብኩ መሆን እንደሚገባቸው አመልክቶአል። ጄ ግሌንትዎርዝ በትለር በ1879 እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ጳውሎስ በሚሰብክበት ጊዜ አደጋ ይደርስብኛል ወይም ሰዎች ምን ይሉኛል ብሎ እንዳላሰበ [የኤፌሶን ሽማግሌዎች] አሳምረው ያውቁ ነበር። አስፈላጊ የሆነውን እውነት ከመናገር ወደኋላ አላለም። ለተወሰነ የእውነት ገጽታ የተለየ አድልዎ ሳያሳይ ለመመገብ ወይም ለማነጽ የሚያስፈልገውን ሁሉና፣ ይህንንም ብቻ ይመክር ነበር። የአምላክን ምክር ሁሉ በሙላትና በጥራት ይናገር ነበር። ይህን የክርስትና እውነት በትጋትና በግለት የማሳየትና የማስተማር ልማዱን በጢራኖስ ትምህርት ቤትና በሌሎች የደቀመዛሙርት መሰብሰቢያ ቦታዎች ሳይወስን ባገኘው ቤት ሁሉ ያዳርስ ነበር። ከዕለት እስከ ዕለት ከቤት ወደ ቤትና ከነፍስ ወደ ነፍስ የክርስቶስን በመሰለ ፍላጎትና ናፍቆት አስደሳቹን ምሥራች ያዳርስ ነበር። ለየትኛውም የሰዎች ክፍልና ነገድ፣ ጠላት ለሆኑ አይሁዳውያንም ሆነ፣ ለአሽሟጣጭ ግሪኮች የስብከቱ ዋና መልዕክት ሕይወት አዳኝ የሆኑትን እውነቶች በሙሉ የሚያጠቃልለው ወደ እግዚአብሔር ንሥሐ መግባትና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ብቻ ነበር።”

      10, 11. (ሀ) በክርስቲያናዊ አገልግሎት ረገድ ጳውሎስ ከኤፌሶን ሽማግሌዎች ምን ይጠብቅ ነበር? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሽማግሌዎችም ጭምር የጳውሎስን አርዓያ በመከተል እንዴት ባለው አገልግሎት ይካፈላሉ?

      10 ስለዚህ ጳውሎስ ከኤፌሶን ሽማግሌዎች ምን ይጠብቅ ነበር ለማለት ይቻላል? ምሑሩ ኢ ኤስ ያንግ ሐዋርያው የተናገረውን ቃል በራሳቸው ቋንቋ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፣ “ከሁሉም ዐይነት ሰዎች ጋር፣ ከአይሁዳውያንም ሆነ ከአሕዛብ ጋር ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ደከምኩ እንጂ ሰው በተሰበሰበበት ብቻ በመናገር አልተወሰንኩም። ለሁሉም አይነት ሰዎች የሰበክሁት አጠቃላይ መልዕክት ’ወደ እግዚአብሔር ንሥሐ መግባትና በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነበር።’” ደብልዩ ቢ ራይሌ ደግሞ የጳውሎስን ቃል በሌላ አነጋገር ሲጽፉ እንዲህ ብለዋል፣ “ትርጉሙ ግልጽ ነው፤ ’እኔ የጀመርኩትን እንድትቀጥሉ፣ እኔ ያደረግኩትን እንድታደርጉና እኔ ያስተማርኩትን እንድታስተምሩ እጠብቅባችኋለሁ። በተጨማሪም እኔ የተቃወምኩትን እንድትቃወሙ፣ እኔ እንዳደረግኩ በየመንገዱና ከቤት ወደ ቤት በያደባባዩም እንድታስተምሩና ለአይሁድም ሆነ ለግሪክ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ንሥሐ መግባትንና በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን እንድትመሰክሩ እጠብቅባችኋለሁ። ዋነኞቹ መሠረታዊ ነገሮች እነዚህ ናቸውና።”

      11 ጳውሎስ በሥራ ምዕራፍ 20 ላይ እንደ እርሱ ሽማግሌዎች የነበሩት ወንድሞች ከቤት ወደ ቤት የሚሄዱ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲሆኑ ይጠብቅባቸው እንደነበረ ማመልከቱ እንደነበረ ግልጽ ነው። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ሽማግሌዎች በዚህ ረገድ ለተቀሩት የጉባኤ አባሎች ጥሩ አርዓያ በመሆን ግንባር ቀደም መሆን ነበረባቸው። (ከዕብራውያን 13:17 ጋር አወዳድር) ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮችም እንደ ጳውሎስ ለአሕዛብ ሁሉ ስለ አምላክ መንግሥት፣ ወደ አምላክ ንሥሐ ስለመግባትና በኢየሱስ ክርስቶስ ስለማመን እየተናገሩ ከቤት ወደ ቤት ይሰብካሉ። (ማርቆስ 13:10፤ ሉቃስ 24:45-48) በዘመናዊዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚገኙ የተሾሙ ሽማግሌዎችም በዚህ ረገድ ግንባር ቀደም እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል።​—ሥራ 20:28

      12. አንዳንድ የቀድሞ ሽማግሌዎች ምን ለማድረግ እምቢተኞች ሆነዋል? በአሁኑ ጊዜ ግን ሽማግሌዎች በየትኛው ሥራ በግምባር ቀደምትነት ይሰማራሉ?

      12 ቻርልስ ቴዝ ራስል አሁን የይሖዋን መንግሥት የሚያውጅ መጠበቂያ ግንብ የተባለውንና ያን ጊዜ የጽዮን መጠበቂያ ግንብና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ ይባል የነበረውን መጽሔት በ1879 ማተም ጀመረ። ራስልና ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የመንግሥቱን መልእክት ሐዋርያዊውን ዘዴ በመጠቀም ይናገሩ ነበር። ይሁን እንጂ ቆየት ባሉት ዓመታት አንዳንድ የጉባኤ ሽማግሌዎች የመመስከር ኃላፊነታቸውን ቸል አሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ምስክር እንዲህ በማለት ጽፎአል፣ “ክርስቲያኖች ጽሑፎች ይዘው ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት በተለይም እሁድ እሁድ በሚደረገው ሥራ መካፈል እንደሚኖርባቸው ማስታወቂያ እስከተነገረበት እስከ 1927 ድረስ ሁሉም ነገር በደህና ይቀጥል ነበር። በአባላት ምርጫ የተሾሙት ሽማግሌዎች ተቃወሙትና የጉባኤ አባላት በሙሉ በዚህ ሥራ በምንም ዓይነት እንዳይካፈሉ ለመከልከል ሞከሩ።” ከጊዜ በኋላ ከቤት ወደ ቤት በመስበክ ሥራ የማይካፈሉ ሁሉ በሽምግልና የማገልገል መብታቸው ተወሰደባቸው። ዛሬም ቢሆን በሽምግልናና በዲቁና የሚያገለግሉ ሁሉ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው የምሥክርነት ሥራና በሌሎቹ የክርስቲያናዊ አገልግሎት መስኮች በግንባር ቀደምትነት እንዲካፈሉ ይጠበቅባቸዋል።

      እያንዳንዱ ክርስቲያን ምሥክር ነው

      13. (ሀ) ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ባይሰሙም እንኳን ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) ጳውሎስ ከሕዝቅኤል ጋር የሚመሳሰለው በምን መንገድ ነው?

      13 ክርስቲያኖች ሁሉ የመንግሥቱን መልእክት ሰዎች በአድናቆት ባይቀበሉትም እንኳን በይሖዋ እርዳታ ከቤት ወደ ቤት መስበክ ይኖርባቸዋል። ሕዝቅኤል የአምላክ ጉበኛ እንደመሆኑ መጠን ሰዎች ቢሰሙትም ባይሰሙትም ማስጠንቀቅ ነበረበት። (ሕዝቅኤል 2:5-7፤ 3:11, 27፤ 33:1-6) ኢ ኤም ብሌይክሎክ ሕዝቅኤልንና ጳውሎስን በማነፃፀር የሚከተለውን ጽፈዋል፤ “[ጳውሎስ በሥራ ምዕራፍ 20 ላይ ከተናገረው] በኤፌሶን ስለተከናወነው አገልግሎት በግልጽ ለመረዳት እንችላለን። የሚከተለውን አስተውሉ፣ በመጀመሪያ ደረጃ ጳውሎስ ታማኝ ነበር። በሰዎች ዘንድ ለመወደድ ወይም ዝና ለማትረፍ የሚፈልግ ሰው አልነበረም። ልክ እንደ ሕዝቅኤል በጉበኝነት ሥራ ላይ የተመደበ ስለነበረ የሥራ ግዴታውን በቅንዓትና ከሚናገረው ቃል ጋር በሚስማማ ጠባይ ፈጽሞአል። በሁለተኛ ደረጃ ፍቅራዊ አዛኝነት ነበረው። ምንም ዓይነት ስሜት የሌለው የጥፋት መልእክት አድራሽ አልነበረም። በሶስተኛ ደረጃ ደከመኝ የማይል ወንጌላዊ ነበር። በአደባባይም ሆነ ከቤት ወደ ቤት በከተማዎችም ሆነ በየገጠሩ ወንጌልን ሰብኮአል።”

      14. በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ራሱን ለይሖዋ አምላክ የወሰነ ሁሉ የመመስከር ኃላፊነት የተጣለበት ለምንድን ነው?

      14 አምላክ በዘመናዊ አገልጋዮቹ ላይ ያፈሰሰው በረከትና ብልጽግና የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው በመጠራታቸው የተደሰተባቸው መሆኑን ያረጋግጣል። (ኢሳይያስ 43:10-12) ከዚህም በላይ ኢየሱስ ለተከታዮቹ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሎ ስለነበር የክርስቶስም ምሥክሮች ናቸው። (ሥራ 1:8) ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በመፀለይ ራሱን ለይሖዋ የወሰነ ሁሉ የመመስከር ኃላፊነት አለበት።

      15. ስለጥንቶቹ ክርስቲያኖች የመመስከር ሥራ ምን ተብሎአል?

      15 ስለ ምሥክርነት ሥራ የሚከተለው ተብሎአል፣ “መላውን ቤተክርስቲያን የሚመለከት ሥራ ነበር። የጥንቱ ቤተክርስቲያን ሚሲዮናዊ ሥራ ለሴቶች ሚሲዮናዊ ማኅበር ወይም ለውጭ አገር ሚሲዮናዊ ቦርድ የተተወ ኃላፊነት አልነበረም። የመመስከር ሥራ እንደ ሽማግሌዎች፣ ዲያቆናት ወይም ሐዋርያት ለመሰሉት የሙያ ሰዎች ብቻም የተተወ አልነበረም። . . . በዚያ የጥንት ዘመን መላው ቤተክርስቲያን ሚስዮናዊ ነበር። የጥንቱ ቤተክርስቲያን ሚስዮናዊ ፕሮግራም በሁለት እምነቶች ላይ የተመሠረተ ነበር። (1) የቤተክርስቲያን ዋነኛ ሥራ ወንጌልን በዓለም በሙሉ ማዳረስ ነው። (2) ይህን ሥራ የመፈጸም ኃላፊነት የተጫነው በመላው የክርስቲያን ማኅበረሰብ ላይ ነው።”​—ጄ ኸርበርት ኬን

      16. የሕዝበ ክርስትና ጸሐፊዎች እንኳን ስለ ክርስቲያኖችና ስለ ምሥክርነት ሥራ ምን ነገር አምነዋል?

      16 የዘመናችን የሕዝበ ክርስትና ፀሐፊዎች ከመንግሥቱ መልእክቱ ጋር የማይስማሙ ቢሆንም አንዳንዶቹ ክርስቲያኖች የመመስከር ግዴታ እንዳለባቸው ያምናሉ። ለምሳሌ ያህል ኦስካር ኢ ፎይክት ሁሉም አገልጋይ ነው በተባለው መጽሐፋቸው “ማንም ካህን አምላክ ለእያንዳንዱ አማኝ የሰጠውን አገልግሎት ሊፈጽም አይችልም። የሚያሳዝነው ግን ለብዙ መቶ ዓመታት በቤተክርስቲያን ውስጥ ተስፋፍቶ በኖረው የተሳሳተ አስተሳሰብ ምክንያት የ500 ምዕመናን ሥራ ለአንድ ካህን ብቻ መተው ነው። በጥንቱ ቤተክርስቲያን ግን እንዲህ አልነበረም። ያመኑ ሁሉ በየደረሱበት ቃሉን ይሰብኩ ነበር።”

      17. የምሥክርነቱ ሥራ በጥንት ክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ስለነበረው ቦታ ምን ሊባል ይችላል?

      17 በጥንት ክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ የመመስከሩ ሥራ ከፍተኛ ቦታ ይሰጠው ነበር። በዘመናችን የይሖዋ ምሥክሮችም እንዲሁ ነው። የሐርቫርድ ዩኒቨርስቲው ኢድዋርድ ካልድዌል ሙር የሚከተለውን ጽፈዋል፣ “በአጠቃላይ የመጀመሪያዎቹ ሶስት መቶ ዓመታት የክርስትና እንቅስቃሴ እምነቱን ለማስፋፋት ይታይ በነበረው ከፍተኛ ግለትና ፍላጎት ተለይቶ ይታወቃል። የክርስትና ምኞትና ፍላጎት ወንጌላዊነት፣ የመዳንን መልእክት መናገር ነበር። . . . ይሁን እንጂ በጥንቱ ዘመን የኢየሱስን ትምህርትና እምነት በማስፋፋት ረገድ ሚስዮናውያን ተብለው ሊጠሩ የሚችሉ ሰዎች ያበረከቱት ድርሻ በጣም አነስተኛ ነበረ። ከተለያየ የሥራ መስክ፣ ከተለያየ የኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ የተለያዩ ሰዎች የሥራ ውጤት ነበር። በራሳቸው ተሞክሮ ደኅንነት እንደሚያስገኝ ያመኑበትን ያንን የውስጣዊ ሕይወት ምሥጢር፣ ያንን አዲስ ዓይነት የዓለም አመለካከት እስከ ሮማ መንግሥት የመጨረሻ ድንበር አደረሱት። . . . [የጥንቱ ክርስትና] የዚህ ዓለም ሥርዓት እንደሚጠፋ ጥልቅ እምነት ነበረው። አዲስ የሆነ የዓለም ሥርዓት በድንገት በተአምር እንደሚቋቋም ያምን ነበር።”

      18. የፖለቲካ መሪዎች በሕልማቸው እንኳን ከሚያስቡት በጣም የሚበልጠው ታላቅ ተስፋ ምንድን ነው?

      18 የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት በመመስከርና በሌሎቹ የአገልግሎት ዘዴዎቻቸው አማካኝነት አድማጮቻቸውን የአምላክ ቃል ወደገባለት አዲስ ዓለም በደስታ ይመራሉ። በዚህ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖረው ፍጻሜ የሌለው ሕይወት አዲስ ዓለም አቀፍ ሥርዓት እንገነባለን የሚሉ ሰዎች በሕልማቸው እንኳን ከሚያስቡት በጣም የበለጠ ይሆናል። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:1-4) ሁሉም ሰው በአምላክ አዲስ ዓለም ውስት ለመኖር ይፈልጋል ብሎ ለማሰብ ይቻላል። ይሁን እንጂ ይህን የሚፈልጉት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። ቢሆንም የይሖዋ አገልጋዮች የዘላለም ሕይወት የሚፈልጉ ሰዎችን ለማስተማር ስለሚጠቀሙባቸው አንዳንድ ጥሩ ዘዴዎች ቀጥለን እንመልከት።

  • ለዘላለም ሕይወት ዝንባሌ ያላቸውን መፈለግ
    መጠበቂያ ግንብ—1991 | ጥር 15
    • ለዘላለም ሕይወት ዝንባሌ ያላቸውን መፈለግ

      “ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ አመኑ።”​—ሥራ 13:48

      1. ይሖዋ የሰውን ልብ በሚመለከት ምን ችሎታ አለው?

      ይሖዋ አምላክ ልብን ማንበብ ይችላል። ይህም ነቢዩ ሣሙኤል የእሴይን ልጅ በእሥራኤል ላይ ንጉሥ እንዲሆን ሊቀባው በሄደ ጊዜ በግልጽ ታይቶአል። ሣሙኤል ኤልያብን እንዳየ “በእውነት [ይሖዋ (አዓት)] የሚቀባው በፊቱ ነው አለ። [ይሖዋ (አዓት)] ግን ሣሙኤልን ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ [ይሖዋ (አዓት)] አያይምና ናቅሁት። ሰው ፊትን ያያል፣ [ይሖዋ (አዓት)] ግን ልብን ያያል አለው።” በዚህም መሠረት ሣሙኤል ለይሖዋ ልብ የተስማማውን ዳዊትን እንዲቀባ ታዘዘ።​—1 ሳሙኤል 13:13, 14፤ 16:4-13

      2. በሰው ምሳሌያዊ ልብ ውስጥ ምን ነገር ተተክሎ ይገኛል? ስለዚህስ ጉዳይ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ምን እናነባለን?

      2 እያንዳንዱ ሰው አንድ አይነት ዋነኛ ዝንባሌ ይኖረዋል። በምሳሌያዊ ልቡ ውስጥ ሥር የሰደደ ዝንባሌ ይኖረዋል። (ማቴዎስ 12:34, 35፤ 15:18-20) በዚህም ምክንያት “በልቡ ግን ሠልፍ ነበረ” የሚል ቃል እናነባለን። (መዝሙር 55:21) “የግልፍተኝነት ዝንባሌ ያለው ሰው ብዙ በደል ይፈጽማል” (አዓት) ይላል። በተጨማሪም “እርስ በርሳቸው የመለያየት ዝንባሌ ያላቸው ባልንጀራሞች አሉ፣ ይሁን እንጂ ከወንድም የበለጠ የሚጠጋ ወዳጅ አለ” የሚል ቃል እናነባለን። (ምሳሌ 18:24፤ 29:22 አዓት) ብዙ ሰዎች በጥንትዋ የጵስድያ አንጾኪያ ይኖሩ እንደነበሩት አንዳንድ አሕዛብ መሆናቸው ያስደስታል። ስለ ይሖዋ የደኅንነት ዝግጅት ሲሰሙ ደስ አላቸው። [የይሖዋንም (አዓት)] ቃል አከበሩ። ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ አመኑ። [የይሖዋም (አዓት)] ቃል በአገሩ ሁሉ ተስፋፋ።”​—ሥራ 13:44-48

      አማኞች ልበ ንጹሐን ናቸው

      3, 4. (ሀ) ልበ ንጹሐን እነማን ናቸው? (ለ) ልባቸው ንጹሕ የሆኑ አምላክን የሚያዩት እንዴት ነው?

      3 እነዚህ የአንጾኪያ አማኞች የተጠመቁ ክርስቲያኖች ሆኑ። በታማኝነት የጸኑትም “ልባቸው ንጹሕ የሆኑ ደስተኞች ናቸው፤ አምላክን ያዩታልና” የሚለውን የኢየሱስ ቃል በራሳቸው ላይ ሊጠቅሱ ይችላሉ። (ማቴዎስ 5:8 አዓት) ይሁን እንጂ “ልባቸው ንጹሕ የሆኑ” እነማን ናቸው? አምላክንስ የሚያዩት እንዴት ነው?

      4 ልበ ንጹሐን የተባሉት በውስጣቸው ንጹሕ የሆኑት ናቸው። የአድናቆት፣ የፍቅር፣ የፍላጎትና የዓላማ ንጽሕና አላቸው። (1 ጢሞቴዎስ 1:5) አምላክ ለፍጹም አቋም ጠባቂዎች የሚያደርግላቸውን ሁሉ ለመመልከት ስለሚችሉ አምላክን ያያሉ። (ከዘፀዓት 33:20፤ ኢዮብ 19:26፤ 42:5 ጋር አወዳድር) እዚህ ላይ “ማየት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “በዓይነ ልቡና ማየት፣ ማስተዋል፣ ማወቅ” የሚል ትርጉም አለው። ኢየሱስ የአምላክን ባሕርይ ፍጹም በሆነ ሁኔታ ስላንፀባረቀ “ልባቸው ንፁሕ” ሆኖ በክርስቶስና ኃጢአት በሚያስተሠርየው መሥዋዕቱ ያመኑ፣ የኃጢአት ሥርየት ያገኙና ተቀባይነት ያለው አምልኮ ለአምላክ ለማቅረብ የቻሉ ሁሉ የአምላክን ባሕርይ ለማየት ችለዋል። (ዮሐንስ 14:7-9፤ ኤፌሶን 1:7) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ትንሣዔ አግኝተው አምላክንና ክርስቶስን ፊት ለፊት ማየት ሲችሉ አምላክን ማየታቸው የመጨረሻውን ከፍተኛ ደረጃ ይይዛል። (2 ቆሮንቶስ 1:21, 22፤ 1 ዮሐንስ 3:2) ይሁን እንጂ ልባቸው ንጹሕ የሆኑ ሁሉ በትክክለኛ ዕውቀትና በእውነተኛ አምልኮ አማካኝነት አምላክን ለማየት ይችላሉ። (መዝሙር 24:3, 4፤ 1 ዮሐንስ 3:6፤ 3 ዮሐንስ 11) በሰማይ ወይም በገነቲቱ ምድር የዘላለም ህይወት ለማግኘት ጥሩ ዝንባሌ አላቸው።​—ሉቃስ 23:43፤ 1 ቆሮንቶስ 15:50-57፤ 1 ጴጥሮስ 1:3-5

      5. አንድ ሰው የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ተከታይና አማኝ ሊሆን የሚችለው እንዴት ብቻ ነው?

      5 ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ የሌላቸው ሁሉ አማኞች አይሆኑም። ማመን አይቻላቸውም። (2 ተሰሎንቄ 3:2) ለመማር ፈቃደኛ ያልሆነና በልብ ውስጥ ያለውን ለማየት የሚችለው ይሖዋ ያልሳበው ማንኛውም ሰው የኢየሱስ ተከታይ ለመሆን አይችልም። (ዮሐንስ 6:41-47) እርግጥ ነው የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ በሚሰብኩበት ጊዜ በማንም ሰው ላይ አስቀድመው አይፈርዱም። የሰዎችን ልብ ለማንበብ ስለማይችሉ የስብከታቸውን ውጤት አፍቃሪ ለሆነው አምላክ ይተዋሉ።

      6. (ሀ) ከቤት ወደ ቤት ከሰዎች ጋር ግንባር ለግንባር ተገናኝቶ ስለመነጋገር ምን ተብሎአል? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች ለዘላለም ሕይወት በትክክል ያዘነበሉ ሰዎችን ፈልገው እንዲያገኙ የሚረዳቸው ምን ዝግጅት ተደርጎላቸዋል?

      6 አንድ ምሑር የሚከተለውን በማለት ጥሩ ሐሣብ ሰጥተዋል፣ “[ጳውሎስ] በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት እየሄደ እውነትን አስተምሮአል። ከመድረክ ብቻ ሳይሆን ከሰዎች ጋር በግል እየተገናኘ ክርስቶስን ሰብኮአል። ሰዎችን ለመንካት ከግለሰቦች ጋር ግንባር ለግንባር ከመገናኘት የበለጠ ዘዴ አይኖርም።” (ኦገስት ቫን ሪን) እንደ ቲኦክራቲክ አገልግሎት ትምህርት ቤት መምሪያ፣ ከቅዱሳን ጽሑፎች ምክንያቱን ማስረዳት፣ የመንግሥት አገልግሎታችን የመሰሉት ጽሑፎች የይሖዋ ምሥክሮች ንግግር እንዲያደርጉና በመስክ አገልግሎታቸው ከሰዎች ጋር ተገናኝተው በሚነጋገሩበት ጊዜ ጥሩ ውጤት እንዲያገኙ ይረዱአቸዋል። በተጨማሪም በአገልግሎት ስብሰባ የሚታዩት ትዕይንቶችና በቲኦክራቲክ አገልግሎት ትምህርት ቤት የሚሰጠው ምክር በጣም ይጠቅማቸዋል። በዚህ ትምህርት ቤት የሚካፈሉ ሁሉ ስለ ጥሩ መግቢያ፣ ስለ ትክክለኛ የጥቅስ አጠቃቀም፣ ስለ ምክንያታዊ አቀራረብ፣ አሳማኝ የመከራከሪያ ነጥብ ስለማቅረብ፣ ስለ ምሳሌ አጠቃቀም፣ ጥሩ መደምደሚያ ስለማቅረብና ስለመሳሰሉት የጥሩ ንግግር ባሕርያት ጠቃሚ ማሰልጠኛ ይሰጣቸዋል። የአምላክ ሕዝቦች ለዘላለም ሕይወት ጥሩ ዝንባሌ ያላቸውን በሚፈልጉበት ጊዜ የበለጠ ውጤት እንዲያገኙ የሚያስችላቸውን ይህን ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደሚያጠናክረው እንመልከት።

      ሐሳብ የሚቀሰቅስ መግቢያ

      7. ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራ ስብከቱ የተጠቀመባቸው የመግቢያ ቃላት ስለ ጥሩ መግቢያ ምን ያስተምሩናል?

      7 ከቤት ወደ ቤት ለመመስከር የሚዘጋጁ ሁሉ ፍላጎት ስለሚቀሰቅስ መግቢያ ከኢየሱስ ምሳሌ ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ። ኢየሱስ የተራራ ስብከቱን ሲከፍት “ደስተኛ” የሚለውን ቃል ዘጠኝ ጊዜ ተጠቅሞበታል። ለምሳሌ ያህል “ለሚያስፈልጋቸው መንፈሣዊ ነገሮች ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው፤ የሰማያት መንግሥት የእነርሱ ናትና። . . . የዋሆች ደስተኞች ናቸው፣ ምድርን ይወርሳሉና” ብሎአል። (ማቴዎስ 5:3-12 አዓት) ዐረፍተ ነገሮቹ ቀጥተኛና ግልጽ ነበሩ። ይህ መግቢያ የአድማጮቹን ፍላጎት ቀስቅሶና አነሳስቶ እንደነበረ አያጠራጥርም። ደስተኛ ለመሆን የማይፈልግ ሰው ሊኖር አይችልምና።

      8. ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ለመነጋገሪያ ርዕሳችን እንዴት ያለ መግቢያ መጠቀም ይገባናል?

      8 ከቤት ወደ ቤት በምናደርገው አገልግሎት የምንጠቀምበት መነጋገሪያ ርዕስ ሁልጊዜ በሚገነባና በሚጥም መንገድ መቅረብ ይኖርበታል። ነገር ግን ማንኛችንም ብንሆን የሚያስደነግጥ መግቢያ መጠቀም አይገባንም። ለምሳሌ “ከላይኛው ዓለም መልእክት ይዤልዎት መጥቼአለሁ” በሚልና ይህን በመሰለ መግቢያ መጠቀም ተገቢ አይደለም። እርግጥ ምሥራቹ ከላይ ከሰማይ የመጣ ነው። ቢሆንም እንዲህ ያለው መግቢያ የምናነጋግረው ባለቤት ጤነኛ መሆናችንን እንዲጠራጠርና በተቻለ ፍጥነት ከእኛ ለመላቀቅ እንዲፈልግ ሊያደርገው ይችላል።

      በአምላክ ቃል እንደሚገባ መጠቀም

      9. (ሀ) በምናገለግልበት ጊዜ ጥቅሶችን እንዴት ማስተዋወቅ፣ ማንበብና ማብራራት ይገባናል? (ለ) ኢየሱስ በጥያቄዎች እንዴት እንደተጠቀመ ለማሳየት ምን ምሳሌ ተጠቅሶአል?

      9 መድረክ ላይ ሆነን በምንናገርበት ጊዜ ጥቅሶችን በሚገባ ማስተዋወቅ፣ በተገቢ ቦታ ላይ ጠበቅ አድርጎ ማንበብ፣ ትርጉሙን በግልጽና በትክክል ማብራራት እንደሚገባን ሁሉ በመስክ አገልግሎታችንም እንደዚያው ማድረግ አለብን። ባለቤቱ በጥቅሶቹ ስለተገለጹት ነጥቦች እንዲያስብ የሚያደርጉት ጥያቄዎች መጠየቅም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በዚህም ላይ የኢየሱስ ዘዴ ትምህርት ይሰጠናል። አንድ ጊዜ የሙሴን ሕግ በደንብ የሚያውቅ ሰው “መምህር ሆይ፣ የዘላለምን ህይወት እንድወርስ ምን ላድርግ” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም መልሶ “በሕግ የተጻፈው ምንድር ነው? እንዴትስ ታነባለህ?” አለው። ሰውዬው ሊመልሰው የሚችል ጥያቄ እንደሆነ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። “[ይሖዋ (አዓት)] አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህም፣ በፍጹም ኃይልህም፣ በፍጹም አሳብህም ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ” በማለት በትክክል መለሰለት። ይህን በመመለሱም ኢየሱስ አመሰገነው። በዚህም ምክንያት ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ ተቻለ።​—ሉቃስ 10:25-37

      10. በመነጋገሪያ ርዕሳችን ረገድ ምን ነገር ማስታወስ ይኖርብናል? ባለቤቶችን ጥያቄ በምንጠይቅበት ጊዜ ከምን መቆጠብ ይኖርብናል?

      10 ከቤት ወደ ቤት በመሄድ የሚመሰክሩ ሁሉ አጠቃላይ መልዕክት አድርገው የሚጠቀሙበትን መነጋገሪያ ርዕስ ጎላ አድርገው መግለጽና የሚናገሩትን ለማብራራት የሚጠቅሱአቸውን ጥቅሶች ለምን እንደጠቀሱ ግልጽ ማድረግ ይገባቸዋል። ምሥክሩ የሰዎችን ልብ ለመንካት ስለሚሞክር ሰዎቹን የሚያሳፍር ጥያቄ ከመጠየቅ መቆጠብ ይኖርበታል። በአምላክ ቃል በምንጠቀምበት ጊዜ ሁሉ ’ንግግራችን በጸጋና በጨው የተቀመመ ይሁን።’​—ቆላስይስ 4:6

      11. የተሳሳተ አስተያየት ለማረም በጥቅሶች በመጠቀም ረገድ ኢየሱስ በሠይጣን በተፈተነ ጊዜ ያደረገው እንዴት ምሳሌ ይሆነናል?

      11 በተለይ ተመላልሶ መጠየቅ በምናደርግበት ጊዜ ቅዱሳን ጽሑፎች ምንና ለምን እንደሚሉ በማሳየት የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ማስተካከል ሊያስፈልግ ይችላል። ኢየሱስም ሰይጣንን አሳፍሮ ለመመለስ እንዲሁ ማድረግ አስፈልጎት ነበር። ሠይጣን “መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፣ እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሱሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔርስ ልጅ ከሆንህ ወደ ታች [ራስን የመግደል ያህል ከመቅደሱ ጫፍ] ወርውር” አለው። ሠይጣን የጠቀሰው የመዝሙር 91:11, 12 ጥቅስ የአምላክ ሥጦታ የሆነውን ሕይወት አደጋ ላይ መጣልን አይደግፍም። ኢየሱስም ሕይወቱን ሆን ብሎ አደጋ ላይ በመጣል ይሖዋን መፈታተን ተገቢ አለመሆኑን በመገንዘብ “[ይሖዋ (አዓት)] አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል” ሲል ለሠይጣን መልሶአል። (ማቴዎስ 4:5-7) እርግጥ ሠይጣን እውነት ፈላጊ አይደለም። ምክንያታዊ የሆኑ ሰዎች ግን መንፈሣዊ እድገታቸውን የሚያሰናክልባቸው የተሳሳተ አስተያየት ሲገልጹ የአምላክ ቃል አገልጋይ ቅዱሳን ጽሑፎች ምን እንደሚሉና ምን ማለታቸው እንደሆነ በዘዴ ማሳየት ይኖርበታል። ይህ ሁሉ ’በአምላክ ቃል በሚገባ የመጠቀም’ ክፍል ነው። ይህም በቲኦክራቲክ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጡት በጣም ጠቃሚ የሆኑ ትምህርቶች አንዱ ነው።​—2 ጢሞቴዎስ 2:15

      ለማሳመን መጣር ተገቢ ቦታ አለው

      12, 13. በአገልግሎታችን በማሳመን ችሎታችን መጠቀም ትክክል የሚሆነው ለምንድን ነው?

      12 ለማሳመን መጣር በክርስቲያናዊ አገልግሎት ውስጥ ተገቢ ቦታ አለው። ለምሳሌ ጳውሎስ የሥራ ባልደረባው የነበረውን ጢሞቴዎስን በተማረውና “እንዲያምን በተደረገው” ነገር እንዲጸና መክሮት ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:14 አዓት) በቆሮንቶስም ጳውሎስ “በየሰንበቱ በምኩራብ ውስጥ ንግግር ያደርግና አይሁድንም ሆነ የግሪክ ሰዎችን ለማሳመን ይጥር ነበር።” (ሥራ 18:1-4 አዓት) በኤፌሶንም ‘ንግግር ያደርግና ስለ አምላክ መንግሥት ያሳምን ነበር።’ (ሥራ 19:8) በሮማ በቤት ውስጥ ታስሮ በነበረበት ጊዜ ሐዋርያው ሰዎችን ወደ እርሱ ይጠራና ‘ሊያሳምናቸው እየጣረ’ ምሥክርነት ይሰጣቸው ነበር። አንዳንዶችም አማኞች ሆነዋል።​—ሥራ 28:23, 24

      13 እርግጥ ነው፣ ምሥክሩ ምንም ያህል ለማሳመን ቢጥር አማኞች የሚሆኑት ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸው ብቻ ናቸው። በዘዴ የቀረበ አሳማኝ ምክንያትና ግልጽ ማብራሪያ እንዲያምኑ ሊገፋፋቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ምን ተጨማሪ ነገር እንዲያምኑ ሊረዳቸው ይችላል?

      ምክንያታዊና አሳማኝ መሆን

      14. (ሀ) ምክንያታዊና የተያያዘ ንግግር ማቅረብ ምን ማድረግን ይጠይቃል? (ለ) አሳማኝ መከራከሪያ ነጥብ ለማቅረብ ምን ማድረግ ያስፈልጋል?

      14 በቲኦክራቲክ አገልግሎት ትምህርት ቤት ትኩረት ከሚሰጥባቸው የጥሩ ንግግር ባሕርያት አንዱ ምክንያታዊና የተያያዘ ሐሣብ ያለው ንግግር ማቅረብ ነው። ይህም ቁልፍ ሐሳቦችንና አግባብነት ያላቸውን ነጥቦች በሙሉ በምክንያታዊ ቅደም ተከተል ማስቀመጥን ይጠይቃል። በተጨማሪም አሳማኝ መከራከሪያ ነጥብ ማቅረብ ያስፈልጋል። ለዚህም በመጀመሪያ ጥሩ መሠረት መጣልና አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ ያስፈልጋል። ከዚህ ተነጥሎ የማይታየው ደግሞ የጋራ መስማሚያ ነጥብ ይዞ መወያየት፣ ፍሬ ሐሳቡን በሚገባ የማብራራትና ለሰውየው ምን ትርጉም እንዳለው የማስረዳት ጉዳይ ነው። በዚህም ረገድ ቅዱሳን ጽሑፎች ጥሩ መምሪያ ይሰጡናል።

      15. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ በማርስ ኮረብታ ላይ ንግግር ባደረገ ጊዜ የአድማጮቹን ትኩረት የሳበውና ሁሉም የሚስማሙበት ነጥብ ያስጀመረው እንዴት ነው? (ለ) የጳውሎስ ንግግር ምክንያታዊና የተያያዘ የሆነው እንዴት ነው?

      15 እነዚህ የንግግር ባሕርያት ሐዋርያው ጳውሎስ በማርስ ኮረብታ ላይ ባደረገው እውቅ ንግግሩ በግልጽ ታይተዋል። (ሥራ 17:22-31) መግቢያው የአድማጮቹን ትኩረት ከመሳቡም በላይ በጋራ የሚስማሙበት ነጥብ አስጀምሯል። “የአቴና ሰዎች ሆይ፣ እናንተ በሁሉ ነገር አማልክትን እንደምትፈሩ እመለከታለሁ” አላቸው። በዚህ አባባሉ ያመሰገናቸው መስሎ እንደታያቸው አያጠራጥርም። ጳውሎስ “ለማይታወቅ አምላክ” ስለተሠራ መሠዊያ ከነገራቸው በኋላ ምክንያታዊ፣ አሳማኝና ሐሳቡ ያልተቆራረጠ ንግግሩን አቀረበ። ይህ ያላወቁት አምላክ “ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ” እንደሆነ ገለጸላቸው። እርሱ ግን እንደ አቴናና እንደ ሌሎቹ የግሪክ አማልክት ሰው በሠራው መቅደስ አይኖርም ወይም በሰው እጅ አይገለገልም። ሐዋርያው በመቀጠል አምላክ ሕይወት እንደሰጠንና እርሱን በጭፍን እንድንፈልግ እንዳላደረገ አመለከተ። ከዚያም በጣኦት አምልኮ ድንቁርና ያለፈውን ጊዜ በትዕግሥት ተመልክቶ ያሳለፈው ፈጣሪያችን ’በየቦታው ያሉትን ሰዎች ንሥሐ እንዲገቡ እንደሚጠይቅ’ ገለጸ። ይህም በቅደም ተከተሉ መሠረት ’ከሙታን አስነስቶ ባዘጋጀው ሰው እጅ አምላክ የምድርን ነዋሪዎች በሙሉ እንደሚፈርድ’ወደሚገልጸው ነጥብ አደረሰው። ጳውሎስ “የኢየሱስንና የትንሣዔውን ወንጌል” ይሰብክ ስለነበረ እነዚህ የአቴና ሰዎች ይህ ፈራጅ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚሆን ያውቁ ነበር።​—ሥራ 17:18

      16. የአንድ ክርስቲያን አገልግሎት ጳውሎስ በማርስ ኮረብታ ባደረገው ንግግርና በቲኦክራቲክ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በሚያገኘው ሥልጠና እንዴት ይነካል?

      16 እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ በማርስ ኮረብታ ላይ ከቤት ወደ ቤት እየሄደ እየመሰከረ አልነበረም። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ከዚህ ንግግሩና በቲኦክራቲክ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ማሠልጠኛ የመስክ አገልግሎታቸውን የሚያጠናክርላቸው ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ። የጳውሎስ ምክንያታዊ አቀራረብና አሳማኝ ክርክር አንዳንድ አቴናውያን አማኞች እንዲሆኑ እንደገፋፋቸው ሁሉ ይህ ሁሉ እርዳታ ውጤታማ አገልጋዮች እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።​—ሥራ 17:32-34

      ትምህርት ሰጪ በሆኑ ምሳሌዎች መጠቀም

      17. በአገልግሎት እንዴት ባሉ ምሳሌዎች መጠቀም ይገባል?

      17 በተጨማሪም ቲኦክራቲክ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የአምላክ አገልጋዮች በቤት ወደ ቤት የምሥክርነት ሥራቸውና በሌሎቹ የአገልግሎት መስኮች በጥሩ ምሳሌዎች እንዲጠቀሙ ይረዳቸዋል። ዋና ዋና ነጥቦችን አጠንክሮ ለመግለጽ ቀላልና የሚጥም ምሳሌ መጠቀም ይገባል። ምሳሌዎቹ ከተለመዱ ሁኔታዎች የተወሰዱ መሆን አለባቸው። ለምን እንደጠቀሳቸውም ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል። የኢየሱስ ምሳሌዎች እነዚህን ብቃቶች በሙሉ የሚያሟሉ ነበሩ።

      18. ማቴዎስ 13:45, 46 በአገልግሎት ሊጠቅም የሚችለው እንዴት ነው?

      18 ለምሳሌ የሚከተለውን የኢየሱስ ቃል እንመልከት። “መንግሥተ ሰማያት መልካምን ዕንቁ የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች። ዋጋዋም እጅግ የበዛ አንዲት እንቁ ባገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት።” (ማቴዎስ 13:45, 46) እዚህ ላይ እንቁ የተባለው ኦይስተር በሚባለውና በሌሎች መሰል የባሕር ፍጥረታት ሽፋን ውስጥ የሚገኝ ጌጥ ነው። ውድ ዋጋ ያላቸው ግን አንዳንዶቹ ብቻ ናቸው። ነጋዴው የዚህን እንቁ ከፍተኛ ዋጋ ለማወቅ የሚያስችለው አስተዋይነት ስለነበረው ይህን አንድ እንቁ ለማግኘት ያለውን ሁሉ ለመሸጥ ፈቃደኛ ሆነ። ተመላልሶ መጠየቅ ወይም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምናደርግበት ጊዜ የአምላክን መንግሥት ከልቡ የሚያደንቅ ሰው እንደዚህ ነጋዴ እንደሚያደርግ ለማስገንዘብ በዚህ ምሳሌ ለመጠቀም እንችላለን። እንዲህ ያለው ሰው መንግሥቱ ማንኛውም ዓይነት መሥዋዕት ሊከፈልለት እንደሚገባ በመገንዘብ በሕይወቱ ውስጥ የመጀመሪያውን ደረጃ ይሰጠዋል።

      በቀስቃሽ መደምደሚያ ማጠቃለል

      19. ከቤት ወደ ቤት በምናገለግልበት ጊዜ መደምደሚያችን ለባለቤቱ ምን ሊያሳየው ይገባል?

      19 በተጨማሪም የአምላክ ሕዝቦች በቲኦክራቲክ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የአንድ ንግግር ወይም የአንድ ውይይት መደምደሚያ ከአጠቃላዩ መልዕክት ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ ሊኖረው እንደሚገባና አድማጮቹ ምን እንደሚያደርጉ የሚያስገነዝብና እርምጃም እንዲወስዱ የሚያነሳሳ መሆን እንደሚኖርበት ይማራሉ። ከቤት ወደ ቤት በምናገለግልበት ጊዜ ባለቤቱ ምን እንዲያደርግ እንደሚፈለግበት በግልጽ ማወቅ ይኖርበታል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ እንዲወስድ ወይም ተመላልሶ መጠየቅ እንዲደረግለት ፈቃደኛ እንዲሆን እንደምንፈልግ በግልጽ ማሳወቅ ያስፈልገናል።

      20. በማቴዎስ 7:24-27 ላይ ምን ጥሩ የቀስቃሽ መደምደሚያ ምሳሌ እናገኛለን?

      20 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ የተጠቀመበት መደምደሚያ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። በቀላሉ ሊገባ በሚችል ምሳሌ በመጠቀም የተናገራቸውን ቃላት በሥራ ላይ ማዋል የጥበብ መንገድ መሆኑን ገልጾአል። እንዲህ በማለት ደመደመ፣ “ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ፣ ጎርፍም መጣ፣ ነፋስም ነፈሰ፣ ያንም ቤት ገፋው። በዓለት ላይም ስለተመሰረተ አልወደቀም። ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሰራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ፣ ጎርፍም መጣ፣ ነፋስም ነፈሰ፣ ያንም ቤት መታው፣ ወደቀም። አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።” (ማቴዎስ 7:24-27) የአምላክ አገልጋዮች የሚያነጋግሩአቸውን ባለቤቶች ለተግባር መቀስቀስ እንደሚገባቸው የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ነው።

      21. ውይይታችን ምን ነገር አስረድቶናል? ይሁን እንጂ ምን ነገር መገንዘብ ይኖርብናል?

      21 ከላይ የተመለከትናቸው ነጥቦች ቲኦክራቲክ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ብዙ ሰዎች ብቃት ያላቸው የመንግሥቱ ሰባኪዎች እንዲሆኑ እንዴት እንደሚረዳቸው ያሳያሉ። እርግጥ ብቃታችን በአንደኛ ደረጃ የሚገኘው ከአምላክ ነው። (2 ቆሮንቶስ 3:4-6) በተጨማሪም አገልጋዩ ምንም ያህል ከፍተኛ ብቃት ቢኖረው አንድ ሰው አምላክ በኢየሱስ በኩል ካልሳበው በስተቀር አማኝ ሊሆን አይችልም። (ዮሐንስ 14:6) ቢሆንም የአምላክ ሕዝቦች ለዘላለም ሕይወት በትክክል ያዘነበለ ልብ ያላቸውን በሚፈልጉበት ጊዜ ይሖዋ በሰጣቸው ዝግጅት ሁሉ መጠቀም ይገባቸዋል።

      መልስህ ምን ይሆናል?

      ◻ “ልበ ንጹሐን” እነማን ናቸው? አምላክንስ የሚያዩት እንዴት ነው?

      ◻ ከቤት ወደ ቤት አገልግሎታችን የመንግሥቱን መልእክት በምናስተዋውቅበት ጊዜ ስለምን ነገሮች ማሰብ ይኖርብናል?

      ◻ በምናገለግልበት ጊዜ የአምላክን ቃል በሚገባ ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

      ◻ በመስክ አገልግሎት ምክንያታዊና አሳማኝ አቀራረብ እንዲኖረን የሚረዳን ምንድን ነው?

      ◻ በመስክ አገልግሎት ስለምንጠቀምበት ምሳሌ ምን ማሰብ ይገባል?

      ◻ ምሥክርነት በምንሰጥበት ጊዜ የምንጠቀምበት መደምደሚያ ምን ዓላማ ማከናወን ይኖርበታል?

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ