ርኅሩኅ እረኞች ሆነው ግልገሎቹን ይጠብቃሉ
ከሰው ጋር ተቀራርበው ከሚኖሩት እንስሳት ሁሉ እንደ በግ ያለ ለማዳ እንሰሳ የለም። አብዛኛዎቹ እንስሳት ምግብ ፈልጎ ለማግኘትና ከሚያድኗቸው ፍጥረታት ለማምለጥ አስፈላጊው ጥንካሬና የተፈጥሮ እውቀት አላቸው። በግ ግን የተለየች እንስሳ ናት። ከአዳኝ አውሬዎች ለሚመጣባት ጥቃት የተጋለጠች ናት። ራስዋን ከጥቃት የመከላከል አቅሙ የላትም። አንዲት በግ እረኛ ከሌላት ትፈራለች እንዲሁም ትሸበራለች። ከመንጋው ከተለየች በቀላሉ ትባዝናለች። እንግዲያው ታዛዥ የሆኑት በጎች ከእረኛቸው ያለመለየት ስሜት የሚያሳዩባቸው ጥሩ ምክንያቶች አሏቸው። ያለ እርሱ የመኖር ዕድላቸው የመነመነ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በጎችን የዋህ፣ በሌሎች የተጎሳቆሉና መከታ የሌላቸውን ሰዎች በምሳሌያዊ መንገድ ለማመልከት የሚጠቀምባቸው በእነዚህ ዓይነተኛ ባሕሪዎች የተነሳ ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ አንድ እረኛ ለድካሙ የሚያገኘው ዋጋ የሚገባው ነው። የሚያሳልፈው ሕይወት ቀላል አይደለም። ለሙቀትም ሆነ ለብርድ የተጋለጠ ነው፤ እንቅልፍ አልባ የሆኑ ሌሊቶችንም ያሳልፋል። ብዙውን ጊዜ ራሱን ለአደጋ በማጋለጥ መንጋውን ከአደገኛ አውሬዎች መጠበቅ አለበት። አንድ እረኛ በጎቹ ሳይለያዩ አብረው እንዲውሉ ማድረግ ስላለበት ብዙ ጊዜውን የባዘነ ወይም የጠፋ በግ በመፈለግ ያሳልፋል። የታመሙትንና የተጎዱትን ማከም አለበት። የደከሙትንና አቅም የሌላቸው የበግ ጠቦቶች መሸከም አለበት። በቂ የሆነ ምግብና ውኃ ስለመኖሩ ሁልጊዜ ማሰብ ይኖራል። የመንጋውን ደህንነት ለማረጋገጥ ሙሉ ሌሊት በሜዳ ማደር ለአንድ እረኛ ያልተለመደ ነገር አይደለም። እረኝነት ውጣ ውረድ የተሞላበት ሕይወት ስለሆነ ቆራጥ፣ ትጉህና ብልህ የሆነ ሰውን አገልግሎት ይጠይቃል። ከሁሉም በላይ በእርሱ ጥበቃ ሥር በአደራ ለተሰጠው መንጋ ልባዊ የሆነ አሳቢነት የማሳየት ቸሎታ ሊኖረው ይገባል።
የአምላክን መንጋ እንደ እረኛ ሆኖ መጠበቅ
መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ሕዝብ እንደ ታዛዥ በጎች በእነርሱ ላይ የተሾሙትን ደግሞ እንደ እረኞች አድርጎ ይገልጻቸዋል። ይሖዋ ራሱ ‘የነፍሳችን እረኛና ጠባቂ’ ነው። (1 ጴ ጥሮስ 2:25) ‘መልካሙ እረኛ’ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያው ጴጥሮስን ‘ግልገሎቼን አሰማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጎቼን አሰማራ’ ባለው ጊዜ በጎቹ ርኅራኄ የተሞላበት ጥበቃ እንዲያገኙ ያለውን ፍላጎት ገልጿል። (ዮሐንስ 10:11፤ 21:15–17) ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ‘የአምላክን ጉባኤ እንደ እረኞች ሆነው እንዲጠብቁ’ ከበድ ያለ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። (ሥራ 20:28) መንፈሳዊ እረኞች ሆነው የሚያከናውኑት ሥራ ከአንድ ጥሩ የበጎች እረኛ የሚፈለጉት ባሕርያት ይኸውም ቆራጥነት፣ ብልህነት፣ ትጋት በተለይ ደግሞ ለመንጋው ደህንነት ልባዊ የሆነ አሳቢነት ማሳየትን ይጠይቃል።
በአምላክ ነቢይ በሕዝቅኤል ዘመን በእሥራኤል ውስጥ የይሖዋን ሕዝብ ፍላጎቶች እንዲያሟሉ የተሾሙት እረኞች ሥራቸውን በሚገባ አልተወጡም ነበር። አብዛኛው የአምላክ መንጋ እውነተኛ አምልኮን በመተው እጅግ ተንገላቷል። (ሕዝቅኤል 34:1–10) በጊዜያችን የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የክርስቲያን ጉባኤ ተብለው በዘልማድ ለሚጠሩት ሕዝቦች እረኞች እንደሆኑ አድርገው ይናገራሉ፤ ሆኖም ሕዝበ ክርስትና ያለባት መንፈሳዊ ሕመም ቀሳውስቱ ኢየሱስ በምድር ሳለ የነበሩትን ሕዝቡን ቸል ያሉትንና ያጎሳቆሉትን ክፉዎቹን አስመሳዮች እንደሚመስሉ ያረጋግጣል። የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ መሪዎች ‘ለበጎቹ እንደማይገደው እረኛ ያልሆነ ሞያተኛ ናቸው። (ዮሐንስ 10:12, 13) በምንም ዓይነት መንገድ የአምላክን መንጋ ለመጠበቅ ፈቃደኞች፣ ችሎታው ያላቸው ወይም ብቁዎች አይደሉም።
ለመንጋው የሚጨነቁ እረኞች
ኢየሱስ የይሖዋ አምላክን መንጋ ለሚጠብቁ ሁሉ ፍጹም ምሳሌ ትቶላቸዋል። በሁሉም ሁኔታዎች ሥር ለደቀ መዛሙርቱ አፍቃሪ፣ ደግ፣ ርኅሩኅና ረዳታቸው ነበር። በራሱ ተነሳስቶ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ፈልጎ ለማግኘት ጥሯል። ምንም እንኳ ኢየሱስ ብዙውን ጊዜ ሥራ ይበዛበትና ይደክመው የነበረ ቢሆንም ችግራቸውን ለማዳመጥና ማበረታቻ ለመስጠት ጊዜ ይመድብ ነበር። ነፍሱን ለእነርሱ አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑ የላቀውን የፍቅር መግለጫ የሚያሳይ ነበር። — ዮሐንስ 15:13
በአሁኑ ጊዜ ሁሉም የተሾሙ የጉባኤ ሽማግሌዎች እንዲሁም ዲያቆናት ለመንጋው ይህ ኃላፊነት አለባቸው። ስለዚህም እነዚህ ኃላፊነት ያለባቸው ብዙዎቹ ሰዎች በሌላ አገር ቁሳዊ ጥቅሞች ማግኘት የሚችሉ ቢሆኑም እንኳ ጉባኤዎችን አለበቂ እርዳታና የበላይ ጥበቃ ጥለውት አይሄዱም። ‘በአስጨናቂ ጊዜያት’ ስለምንኖር መንጋው ማበረታቻና መመሪያ ያስፈልገዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) በየጊዜው የሚያጋጥም አደጋ ስላለ አንዳንዶች ‘የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ በሚዞረው’ በሰይጣን ወጥመድ ሊያዙ ይችላሉ። (1 ጴጥሮስ 5:8) ክርስቲያን እረኞች ‘ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን መገሰጻቸው፣ ድፍረት የሌላቸውን ማጽናታቸውና ለደካሞች መትጋታቸው’ ዛሬ ከምን ጊዜውም ይበልጥ አስፈላጊ ነው። (1 ተሰሎንቄ 5:14) ሚዛናቸውን መጠበቅ ያቃታቸው ሰዎች ከመንጋው እንዳይወጡ ለመጠበቅ ከተፈለገ እረኞቹ ዘወትር ንቁ መሆን ያስፈልጋቸዋል። — 1 ጢሞቴዎስ 4:1
እረኛው አንድ በግ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ማወቅ የሚችለው እንዴት ነው? በጣም ግልጽ ሆነው ከሚታዩት ምልክቶች አንዳንዶቹ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አለመገኘት፣ በመስክ አገልግሎት ተሳትፎ አለማድረግና ከሌሎች የመራቅ አዝማሚያዎች ናቸው። የበጎቹን አቋምና የአነጋገር ሁኔታ በጥንቃቄ በማስተዋል ድክመታቸውን መለየት ይቻላል። ሌሎችን ወደ መተቸት ሊያዘነብሉ ይችላሉ፤ ይህም ምናልባት የቅሬታ ስሜት እንዳደረባቸው ሊያመለክት ይችላል። ጭውውታቸው በመንፈሳዊ ግቦች ላይ ከመሆን ይልቅ ቁሳዊ ሃብትን በመከታተል ላይ ከመጠን በላይ ያተኮረ ሊሆን ይችላል። በጥቅሉ ግለት፣ ብሩህ አመለካከትና ደስታ የጎደላቸው መሆኑ እምነታቸው ተዳክሟል ማለት ሊሆን ይችላል። ከባድ ኀዘን የሚነበብበት የፊት ገጽታ ተቃዋሚ በሆኑ ዘመዶች ወይም በዓለማዊ ጓደኞች ግፊት እንዳደረባቸው የሚያሳይ ምልክት ሊሆን ይችላል። እረኛው እነዚህን ምልክቶች በማስተዋል ምን ዓይነት እርዳታ እንደሚያስፈልግ ለመገምገም ሊጥር ይችላል።
ክርስቲያን እረኞች አንድን መሰል አማኝ ለመርዳት ወደ ቤቱ በሚሄዱበት ጊዜ ዋነኛ ዓላማቸውን በአእምሮአቸው ውስጥ ማስቀመጥ ያስፈልጋቸዋል። የእረኝነት ጉብኝት የባጥ የቆጡ የሚወራበት የማኅበራዊ ኑሮ ጥየቃ አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ ወንድሞቹን ይጎበኝ የነበረው ‘መጽናት እንዲችሉ መንፈሳዊ ስጦታ ለማካፈልና እርስ በእርስ ለመጽናናት’ ነበር። (ሮሜ 1:11, 12) ይህን ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል።
በመጀመሪያ ግለሰቡን በጥንቃቄ ገምግም፤ መንፈሳዊ ሁኔታውም ምን እንደሚመስል ለማወቅ ሞክር። ይህን መሠረት በማድረግ ምን ዓይነት መመሪያ፣ ማበረታቻ ወይም ምክር ይበልጥ ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል አስብበት። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ “የሚሠራ” ስለሆነ ዋነኛ የምክር ምንጭ መሆን ይኖርበታል። (ዕብራውያን 4:12) በጎች ስለገጠሟቸው ልዩ ችግሮች ማብራሪያ የሚሰጡ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶችን ርዕሶች ማየት ይቻላል። የሚያነቃቁና አእምሮን የሚያድሱ ተሞክሮዎችን በይሖዋ ምስክሮች የዓመት መጽሐፍ ላይ ማግኘት ይቻላል። ዋናው ዓላማ ‘ሰውየውን ለማነጽ የሚጠቅም’ መንፈሳዊ ነገር ለማካፈል ነው። — ሮሜ 15:2
ገንቢ የሆነ እረኝነት
ቃል በቃል የበጎችን መንጋ የሚጠብቅ አንድ እረኛ በጎቹ ጥበቃና እንክብካቤ ለማግኘት በእሱ እንደሚመኩ ያውቃል። አብዛኛውን ጊዜ አስጊ ሁኔታዎች የሚመጡት ከመባዘን፣ በበሽታ፣ ከመዛል፣ ከጉዳትና ከአዳኝ አውሬዎች ነው። በተመሳሳይም መንፈሳዊ እረኛ የመንጋውን ደህንነት የሚፈታተኑትን አስጊ የሆኑ መሰል ሁኔታዎችን መገንዘብና እነርሱን ለመቋቋም መፍትሔ መፈለግ አለበት። ብዙ ጊዜ የሚያጋጥሙ አንዳንድ ችግሮችና በመንፈሳዊ የሚገነባ ሐሳብ ለወንድሞች ለማካፈል ምን ሊባል እንደሚቻል የሚገልጹ ጥቆማዎች ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል።
(1) በቀላሉ እንደሚታለለው በግ ሁሉ አንዳንድ ክርስቲያኖችም ምንም ጉዳት የማያስከትሉና አስደሳች መስለው በሚታዩ መስህብነት ባላቸው ነገሮች በመታለል ከአምላክ መንጋ ወጥተው ይባዝናሉ። ከፍቀረ ንዋይ፣ ከመዝናኛ ወይም ከመደሰቻዎች ጋር የተያያዙ ግቦችን በመከታተል ሊሳቡና አልፎ ተርፎም ሊኮበልሉ ይችላሉ። (ዕብራውያን 2:1) ለእንዲህ ዓይነት ግለሰቦች የጊዜውን አጣዳፊነት፣ ወደ ይሖዋ ድርጅት ተጠግቶ የመኖርን አስፈላጊነትና የመንግሥቱን ፍላጎቶች በሕይወት ውስጥ የማስቀደምን አንገብጋቢነት ማሳሰብ ይቻላል። (ማቴዎስ 6:25–33፤ ሉቃስ 21:34–36፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:8–10) በግንቦት 15, 1984 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 8–11 ላይ ባለው “ሚዛንህን ጠብቅ — እንዴት?” በሚለው ርዕስ ላይ ለዚህ የሚረዳ ምክር ይገኛል።
(2) አንድ እረኛ ለታመሙ በጎች ህክምና ማድረግ ያስፈልገዋል። በተመሳሳይም መንፈሳዊ እረኞች በሕይወታቸው ውስጥ በገጠሟቸው መጥፎ ነገሮች ሳቢያ በመንፈሳዊ የታመሙትን ክርስቲያኖች መርዳት አለባቸው። (ያዕቆብ 5:14, 15) ሥራ አጥተው፣ ከባድ የጤና ችግር ደርሶባቸው ወይም በቤተሰብ ሕይወታቸው ውስጥ ችግሮች ገጥመዋቸው ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ከአምላክ ሕዝብ ጋር ለመቀራረብ ወይም ለመንፈሳዊ ምግብ ያላቸው ፍላጎት እምብዛም ሊሆን ይችላል። ይህም ከሰው መራቅንና ተስፋ መቁረጥን ያስከትላል። ይሖዋ እንደሚያስብላቸውና በአስቸጋሪ ጊዜያት እንደሚደግፋቸው ማረጋገጫ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። (መዝሙር 55:22፤ ማቴዎስ 18:12–14፤ 2 ቆሮንቶስ 4:16–18፤ 1 ጴጥሮስ 1:6, 7፤ 5:6, 7) በሰኔ 1, 1980 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 12–15 ላይ የሚገኘውን “እንደ ክርስቲያን መጠን ወደፊት አሻግሮ መመልከት” የሚለውን ርዕስ መከለሱም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
(3) እረኛው የዛሉትን በጎች ነቅቶ መከታተል አለበት። አንዳንዶቹ ለብዙ ዓመታት በይሖዋ አገልግሎት የታመኑ ሆነው የጸኑ ናቸው። ከብዙ ፈተናዎችና መከራዎች ጋር ታግለዋል። ጠንክሮ በመሥራት ረገድ የመዛል ምልክቶችን ያሳያሉ፤ አልፎ ተርፎም በስብከቱ ሥራ የመትጋትን አስፈላጊነት በተመለከተ ያደረባቸውን ጥርጣሬ ይገልጹ ይሆናል። መንፈሳቸው እንዲያንሰራራ ማድረግና ኢየሱስ ክርስቶስን በመምሰል አምላክን በሙሉ ልብ በማገልገል ለሚገኙት ደስታዎችና በረከቶች አድናቆታቸውን ማደስ ያስፈልጋል። (ገላትያ 6:9, 10፤ ዕብራውያን 12:1–3) ይሖዋ የታማኝነት አገልግሎታቸውን እንደሚገነዘብና ወደፊት ለእርሱ ምስጋና ለሚደረጉት እንቅስቃሴዎች ሊያበረታቸው እንደሚችል እንዲገነዘቡ ልንረዳቸው እንችል ይሆናል። (ኢሳይያስ 40:29, 30፤ ዕብራውያን 6:10–12) በ14–109 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 10–18 ላይ በተብራራው “መልካምን ሥራ ለመሥራት አትታክት” በሚለው ርዕስ ላይ ያሉትን ሐሳቦች ማካፈሉ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
(4) ጉዳት እንደደረሰባቸው በጎች ሁሉ አንዳንድ ክርስቲያኖችም መጥፎ ምግባር መስሎ በታያቸው ነገር ተጎድተዋል። ሆኖም ሌሎችን ይቅር የምንል ከሆነ የሰማዩ አባታችንም በሚያስፈልገን ጊዜ ይቅርታ ያደርግልናል። (ቆላስይስ 3:12–14፤ 1 ጴጥሮስ 4:8) አንዳንድ ወንድሞች ወይም እኅቶች ተገቢ መስሎ ያልታያቸው ምክር ወይም ተግሣጽ ተሰጥቷቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ሁላችንም ከመንፈሳዊ ምክርና ተግሣጽ ጥቅም ልናገኝ እንችላለን፤ ይሖዋ የሚያፈቅራቸውን እንደሚገሥጽ ማወቁም የሚያጽናና ነው። (ዕብራውያን 12:4–11) ሌሎች ደግሞ ብቁ እንደሆኑለት የሚሰማቸውን የአገልግሎት መብት ባለማግኘታቸው ያደረባቸው ቅሬታ በእነርሱና በጉባኤው መካከል ልዩነት እንዲፈጥር ይፈቅዱለታል። ከይሖዋ ድርጅት ብንርቅ መዳንና እውነተኛ ደስታ ለማግኘት የምንሄድበት ሌላ ቦታ የለም። (ከዮሐንስ 6:66–69 ጋር አወዳድር።) ነሐሴ 15, 1988 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 28–30 ላይ “ክርስቲያናዊ አንድነታችንን መጠበቅ” በሚለው ርዕስ ላይ ከዚህ ጋር የተያያዙ ጠቃሚ ሐሳቦችን ማግኘት ይቻላል።
(5) በጎች ከአዳኝ አውሬዎች መጠበቅ አለባቸው። ልክ እንደዚሁም አንዳንዶች ከማያምኑ ዘመዶች ወይም የሥራ ጓደኞች ተቃውሞና ዛቻ ሊደርስባቸውና ሊደናገጡ ይችላሉ። ለአምላክ የሚሰጡትን አገልግሎት እንዲቀንሱ ወይም በክርስቲያናዊ አገልግሎት የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንዲያቋርጡ ለማድረግ ግፊቶች በሚመጡበት ጊዜ የአቋም ጽናታቸው ሊፈተን ይችላል። ሆኖም ተቃውሞው አዲስ ነገር እንዳልሆነና የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን ከሚያሳዩት ማስረጃዎች አንዱ መሆኑን መገንዘብ እንዲችሉ ሲደረግ ጥንካሬ ያገኛሉ። (ማቴዎስ 5:11, 12፤ 10:32–39፤ 24:9፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:12) የታመኑ ከሆኑ ይሖዋ በፍጹም እንደማይተዋቸውና ላሳዩት ጽናት ዋጋ እንደሚሰጣቸው ማስገንዘቡ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 4:7–9፤ ያዕቆብ 1:2–4, 12፤ 1 ጴጥሮስ 5:8–10) በ4–103 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 8–12 ላይ ያለው “ስደት ቢኖርም በደስታ መጽናት” የሚለው ርዕስ ተጨማሪ ማበረታቻ ይሰጣል።
እረኞች ሆይ፣ ኃላፊነቶቻችሁን ተወጡ
የአምላክ መንጋ የሚያስፈልጓቸው ነገሮች ብዙ ናቸው፤ ተገቢ ክትትል ማድረግም ቀላል ሥራ አይደለም። በመሆኑም ክርስቲያን እረኞች ርኅሩኅ፣ ከልብ የሚያስቡና ለመርዳት ዝግጁዎች መሆን አለባቸው። ትዕግሥትና አስተዋይነት በጣም አስፈላጊ ናቸው። አንዳንድ ግለሰቦች ምክርና ተግሣጽ ያስፈልጋቸዋል፤ ሌሎች ግን ይበልጥ የሚጠቀሙት ከማበረታቻ ነው። በአንዳንድ ሁኔታዎች ለተወሰኑ ጊዜያት በግል ቀርቦ ማነጋገሩ ሊበቃ ይችላል፤ በሌሎች ሁኔታዎች ግን ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል። በማንኛውም ሁኔታ ዋነኛው ዓላማ ግለሰቡ ጥሩ የጥናት ልምድ እንዲኖረው፣ በጉባኤ ስብሰባዎች እንዲገኝ ወይም ዘወትር እንዲሰበሰብና በክርስቲያናዊ አገልግሎት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚያነሳሳው በመንፈሳዊ የሚገነባ መመሪያ ወይም ፍቅራዊ የሆነ ምክር ለማካፈል ነው። መሰል አማኞችን ለመርዳትና የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ምንም እክል ሳያጋጥመው መፍሰስ እንዲችል መንገድ እንዲከፍቱ ለማስቻል የሚረዱ ዋና ዋና መንገዶች እነዚህ ናቸው።
እንዲህ ዓይነቱን እርዳታ የሚሰጡ እረኞች ለመንጋው እጅግ ጠቃሚ የሆነ አገልግሎት ያከናውናሉ። (11–106 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 13–16 ተመልከት።) መንፈሳዊ እረኞች ለሚያከናውኑት ነገር መንጋው ከፍተኛ ግምት ይሰጣል። አንድ የቤተሰብ ራስ እንዲህ ዓይነቱን እርዳታ ከተቀበለ በኋላ እንዲህ ሲል ገለጸ:- ‘በእውነት ውስጥ ለ22 ዓመታት ከቆየን በኋላ በፍቅረ ነዋይ ወደ ዓለም ተሳብን። ብዙ ጊዜ በስብሰባዎች ላይ መገኘት እንፈልግ ነበር፤ ሆኖም ልናደርገው የማንችለው ነገር መስሎ ታየን። ከሰይጣን ዓለምም ጋር መጣጣም አልቻልንም። ስለዚህ ሙሉ በሙሉ ተለይተን ከሁለት የወደቀ ዛፍ ሆነን ነበር። ይህም ብስጭትና ጭንቀት ላይ ጣለን። የሚያበረታቱ ቃላት አስፈልገውን ነበር። አንድ ሽማግሌ ሊጠይቀን መጣና በቤታችን ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግልን ያቀረበልንን ጥያቄ በደስታ ተቀበልነው። አሁን ዋስትና ወዳለው የይሖዋ ድርጅት ተመልሰናል። የሚሰማኝን ደስታ መግለጽ ያዳግተኛል!’
የባዘኑትና ተሰፋ የቆረጡት ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን በመንፈሳዊ ሲያንሰራሩና ሲነቃቁ ለታላቅ ደስታ ምክንያት የሚሆን ነገር ይኖራል። (ሉቃስ 15:4–7) የይሖዋ ሕዝብ ‘በማሰማሪያው ውስጥ እንዳለ መንጋ’ በአንድነት ሲሰባሰቡ ይሖዋ ለሕዝቡ ያለው ዓላማ ከግቡ ይደርሳል። (ሚክያስ 2:12) በዚህ ዋስትና ባለው ማረፊያ በመልካሙ እረኛ በኢየሱስ ክርስቶስ እርዳታ ‘ለነፍሳቸው ዕረፍት ያገኛሉ።’ (ማቴዎስ 11:28–30) በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ አንድ አካል የተደራጀው መንጋ ከተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ጎን ለጎን መመሪያ፣ ማጽናኛና ጥበቃ ያገኛል።
በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ በዚህ የእረኝነት እንቅስቃሴ አማካኝነት ጥንት ቃል ከገባው ነገር ጋር የሚስማማ ፍቅራዊ የሆነ ሥራ እያከናወነ ነው። “እኔ ራሴ በጎቼን እሻለሁ እፈልግማለሁ . . . ከተበተኑት ስፍራ ሁሉ አድናቸዋለሁ . . . የጠፋውንም እፈልጋለሁ . . . የተሰበረውንም እጠግናለሁ የደከመውንም አጸናለሁ።” (ሕዝቅኤል 34:11–16) ይሖዋ እረኛችን መሆኑን ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው! — መዝሙር 23:1–4
የአምላክን መንጋ ለመጠበቅ በተዘጋጁት መለኮታዊ ዝግጅቶች የተነሳ እንደ ይሖዋ አገልጋዮች መጠን “በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁም፤ አቤቱ፣ አንተ ብቻህን በእምነት አሳድረኸኛልና” በማለት ዳዊት የተሰማው ዓይነት ስሜት ሊሰማን ይችላል። (መዝሙር 4:8) አዎን፤ የይሖዋ ሕዝቦች በፍቅራዊ ጥበቃው ደህንነት ይሰማቸዋል፤ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ግልገሎቹን ርኅሩኅ እረኞች ሆነው ስለሚጠብቁም አመስጋኞች ናቸው።
[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Potter’s Complete Bible Encyclopedia