የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ሕያው በሆነ አምላክ ማመን ትችላለህን?
    መጠበቂያ ግንብ—1997 | ጥቅምት 1
    • ግራ የተጋባች ሴት “የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ አይገባኝም” ብላለች። ልጆቹ ይማሩበት ከነበረው ትምህርት ቤት ውጪ ከአበቦች ጋር የተቀመጠ አንድ ካርድ የደረሰው መከራ ያስከተለውን ሐዘን ይገልጻል። በካርዱ ላይ የተጻፈው “ለምን?” የሚል አንድ ቃል ብቻ ነበር። የደንብሌን ካቴድራል ቄስ መልስ ሲሰጡ “ምንም ማብራሪያ ለመስጠት አይቻልም። ይህ ለምን እንደተከሰተ መልስ ለመስጠት አንችልም” ብለዋል።

      ይህ ከተፈጸመ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በዚያው ዓመት በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ታዋቂ የነበረ አንድ ወጣት ቄስ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደለ። ቸርች ታይምስ የተባለ ጽሑፍ የሊቨርፑሉ አቡን “የአምላክን በር ለምን? ለምን? በሚሉ ጥያቄዎች ስለመደብደብ” ሲናገሩ በድንጋጤ የተዋጠ አንድ ጉባኤ ያዳምጣቸው እንደነበር ዘግቧል። እኚህ ቄስም ቢሆኑ ሕያው ከሆነ አምላክ የተገኙ የሚያጽናኑ ቃላትን ለመናገር አልቻሉም።

      ታዲያ እኛ ማመን ያለብን በምንድን ነው? ሕያው በሆነ አምላክ ለማመን የሚያስችል ጥሩ ምክንያት አለ። ይህ ደግሞ ከላይ የተነሱትን ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችል ቁልፍ ነው። ቀጥሎ በሚገኘው ርዕስ ውስጥ የቀረበውን ማስረጃ እንድትመለከት እንጋብዝሃለን።

  • ሕያው አምላክ የሆነውን ይሖዋን እወቅ
    መጠበቂያ ግንብ—1997 | ጥቅምት 1
    • ሕያው አምላክ የሆነውን ይሖዋን እወቅ

      በህንድ የሚኖሩት ዶክተር ኤስ ራዳክሪሽናን የሂንዱ እምነትና ሌሎች የሃይማኖት ሥርዓቶች ስለ አምላክ ያላቸውን አመለካከት በማነጻጸር እንደሚከተለው ብለዋል:- “የዕብራውያን አምላክ የተለየ ነው። ሕያው የሆነና በታሪክ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግ፣ በማደግ ላይ ባለው በዚህ ዓለም ውስጥ የሚታዩትን ለውጦችና አጋጣሚዎች በትኩረት የሚከታተል አምላክ ነው። ከእኛ ጋር የሐሳብ ግንኙነት የሚያደርግ እውን አካል ነው።”

      በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው አምላክ ስም በዕብራይስጥ ሲጻፍ יהוה ሲሆን፣ ብዙውን ጊዜ “ይሖዋ” ተብሎ ተተርጉሟል። እሱ ከሁሉም አማልክት የላቀ ነው። ስለ እሱ ምን እናውቃለን? በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ከነበሩ ሰዎች ጋር ግንኙነት ያደርግ የነበረው እንዴት ነው?

      ይሖዋና ሙሴ “ፊት ለፊት”

      ሙሴ ቃል በቃል አምላክን ባያየውም በይሖዋና በአገልጋዩ በሙሴ መካከል የነበረው መቀራረብ ግን “ፊት ለፊት” የሆኑ ያህል ነበር። (ዘዳግም 34:​10፤ ዘጸአት 33:​20) ሙሴ ወጣት በነበረበት ጊዜ ልቡ በወቅቱ በግብጽ ባርነት ሥር ከነበሩት እስራኤላውያን ጋር ነበር። ለፈርዖን ቤት ኑሮ ጀርባውን በመስጠት “ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ።” (ዕብራውያን 11:​25) በዚህ ምክንያት ይሖዋ ለሙሴ ብዙ መብቶችን ሰጥቶታል።

      ሙሴ የፈርዖን ቤተሰብ አባል እንደመሆኑ መጠን ‘የግብፆችን ጥበብ ሁሉ ተምሯል።’ (ሥራ 7:​22) ይሁን እንጂ የእስራኤልን ሕዝብ ለመምራት ትሕትናን፣ ታጋሽነትንና ገርነትን ማዳበር ያስፈልገው ነበር። ሙሴ በምድያም እረኛ ሆኖ በኖረባቸው 40 ዓመታት ይህን ሲያደርግ ቆይቷል። (ዘጸአት 2:​15-22፤ ዘኁልቁ 12:​3) ምንም እንኳ ይሖዋ ማንም ሊያየው ባይችልም ራሱንና ዓላማዎቹን ለሙሴ ገልጾለታል፤ እንዲሁም አምላክ በመላእክቱ አማካኝነት አሥሩን ትእዛዛት ሰጥቶታል። (ዘጸአት 3:​1-10፤ 19:​3–20:​20፤ ሥራ 7:​53፤ ዕብራውያን 11:​27) መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርም ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር ፊት ለፊት ከሙሴ ጋር ይነጋገር ነበር” ሲል ይገልጻል። (ዘጸአት 33:​11) እንዲያውም ይሖዋ ራሱ “እኔ አፍ ለአፍ በግልጥ እናገረዋለሁ” ብሏል። ሙሴ ከማይታየው፣ ነገር ግን ሕያው ከሆነው አምላኩ ጋር እንዴት ያለ ውድ የሆነ የቅርብ ዝምድና ነበረው!​—⁠ዘኁልቁ 12:​8

      ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ የቀድሞ ታሪክ ጨምሮ ከሕጉ ደንብ ጋር የተያያዙ ዝርዝር ጉዳዮችን ጽፏል። በተጨማሪም የዘፍጥረት መጽሐፍን የመጻፍ ታላቅ መብት አግኝቶ ነበር። የመጽሐፉ የኋለኛው ክፍል ታሪክ በራሱ ቤተሰብ በትክክል ይታወቅ ስለነበር በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ ታሪኩን ለመመዝገብ ቀላል ነበር። ይሁን እንጂ ሙሴ የሰውን የቀድሞ ታሪክ የሚገልጹ ዝርዝር ሐሳቦችን ያገኘው ከየት ነው? ሙሴ በቀድሞ አባቶቹ ተጠብቀው የቆዩ ጥንታዊ ሰነዶች ሊኖሩትና እነሱን እንደ ምንጭ አድርጎ ተጠቅሞባቸው ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ከይሖዋ በቀጥታ በቃል ወይም በመለኮታዊ ራእይ የተላለፈለትን ዝርዝር ሐሳብ ተቀብሎ ይሆናል። በተለያዩ ዘመናት የኖሩ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ሰዎች ሙሴ ከአምላኩ ጋር የተቀራረበ ዝምድና እንደነበረው ከረዥም ጊዜ በፊት ተገንዝበው ነበር።

      ይሖዋ ለኤልያስ ሕያው አምላክ ነበር

      ይሖዋ ለነቢዩ ኤልያስም ሕያው አምላክ ነበር። ኤልያስ በዋነኛው የከነዓናውያን አምላክ ማለትም በበዓል አምላኪዎች ከፍተኛ ጥላቻና ተቃውሞ ቢደርስበትም ለንጹሕ አምልኮ በመቅናት ይሖዋን አገልግሏል።​—⁠1 ነገሥት 18:​17-40

      የእስራኤል ንጉሥ የነበረው አክዓብና ሚስቱ ኤልዛቤል ኤልያስን ሊገድሉት ፈልገው ነበር። ኤልያስ ለሕይወቱ ስለ ፈራ በሙት ባሕር ምዕራብ ወደምትገኘው ቤርሳቤህ ሸሽቶ ሄደ። እዚያም በምድረ በዳ ከመቅበዝበዙም በላይ እንዲሞት ጸለየ። (1 ነገሥት 19:​1-4) ይሖዋ ኤልያስን ትቶት ነበርን? ታማኝ ስለሆነው አገልጋዩ ማሰቡን አቁሞ ነበር ማለት ነውን? ኤልያስ እንደዚህ ተሰምቶት ከነበረ ተሳስቷል! ከጊዜ በኋላ ይሖዋ “ኤልያስ ሆይ፣ በዚህ ምን ታደርጋለህ?” በማለት በቀስታ ጠየቀው። ከመለኮታዊው ኃይል አስደናቂ መግለጫ በኋላ “ኤልያስ ሆይ፣ በዚህ ምን ታደርጋለህ? የሚል ድምፅ [እንደገና] ወደ እርሱ መጣ።” ይሖዋ ለኤልያስ ያለውን አሳቢነት በግልጽ ያሳየው ታማኝ አገልጋዩን ለማበረታታት ሲል ነበር። አምላክ ኤልያስ እንዲፈጽመው የሚፈልገው ብዙ ሥራ ነበረው፤ እሱም ለቀረበለት ጥሪ በደስታ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥቷል! ኤልያስ የተሰጠውን የሥራ ድርሻ በታማኝነት በማከናወን የሕያው አምላኩን የይሖዋን ስም አስቀድሷል።​—⁠1 ነገሥት 19:​9-18

      ይሖዋ የእስራኤልን ሕዝብ ከተዋቸው በኋላ በምድር ላይ ከሚገኙት አገልጋዮቹ ጋር በቀጥታ መነጋገሩን አቁሟል። ነገር ግን ይህ ለእነርሱ የነበረው አሳቢነት ቀንሷል ማለት አይደለም። በእሱ አገልግሎት ላይ የሚገኙትን ሰዎች በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት መምራቱንና ማጠንከሩን ቀጥሏል። ለምሳሌ ያህል ቀደም ሲል ሳውል ተብሎ ይጠራ የነበረውን ሐዋርያው ጳውሎስን እንውሰድ።

      መንፈስ ቅዱስ ለጳውሎስ የሰጠው አመራር

      ሳውል የተወለደው ስመ ጥር በሆነችው የኪልቅያ ከተማ በጠርሴስ ነበር። ወላጆቹ ዕብራውያን ቢሆኑም በትውልዱ ሮማዊ ዜጋ ነበር። ይሁን እንጂ የሳውል አስተዳደግ ጥብቅ የነበረውን የፈሪሳውያንን ትምህርት የተከተለ ነበር። ከጊዜ በኋላ በኢየሩሳሌም ታዋቂ የሕግ መምህር በነበረው “በገማልያል እግር አጠገብ” የመማር አጋጣሚ አግኝቶ ነበር።​—⁠ሥራ 22:​3, 26-28

      ሳውል ለአይሁድ እምነት የነበረው የተሳሳተ ቅንዓት በኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ላይ በተካሔደው አረመኔያዊ ዘመቻ ተካፋይ እንዲሆን አድርጎታል። የመጀመሪያው ክርስቲያን ሰማዕት በሆነው በእስጢፋኖስ መገደል እንኳን ሳይቀር ተስማምቷል። (ሥራ 7:​58-60፤ 8:​1, 3) ምንም እንኳ አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ እንዲሁም አንገላች የነበረ ቢሆንም ‘ሳያውቅ ባለማመን ስላደረገው ነገር ምሕረትን አግኝቷል።’​—⁠1 ጢሞቴዎስ 1:​13

      ሳውል ይህን እንዲያደርግ ያነሳሳው አምላክን ለማገልገል የነበረው ልባዊ ፍላጎት ነው። ሳውል ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ ላይ ክርስትናን ከተቀበለ በኋላ ይሖዋ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቅሞበታል። ሐናንያ የተባለ የቀድሞ ክርስቲያን ደቀ መዝሙር ሳውልን እንዲረዳው ከሙታን ከተነሣው ክርስቶስ መመሪያ ተቀብሎ ነበር። ከዚያ በኋላ ጳውሎስ (ሳውል ክርስቲያን ከሆነ በኋላ የተጠራበት ሮማዊ ስሙ) በአውሮፓና በትንሹ እስያ አንዳንድ ክፍሎች ረዥምና ፍሬያማ አገልግሎት እንዲያከናውን የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ መርቶት ነበር።​—⁠ሥራ 13:​2-5፤ 16:​9, 10

      ዛሬስ ይኸው የመንፈስ ቅዱስ አመራር ተለይቶ ሊታወቅ ይችላልን? አዎን፣ ሊታወቅ ይችላል።

      አምላክ የለም የሚለው እምነት ይሖዋ ለሰዎች እንዳያስብ አያደርገውም

      ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሁለተኛ ፕሬዚዳንት ነበር። ቀደም ሲል የይሖዋ ምሥክሮች ይታወቁበት በነበረው ስም መሠረት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ሆኖ በ1906 ከተጠመቀ ከአንድ ዓመት በኋላ የማኅበሩ የሕግ ጠበቃ ሆኖ እንዲሠራ ተደረገ። በጥር 1917 ደግሞ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ሆነ። ነገር ግን ይህ ወጣት ጠበቃ በአንድ ወቅት በአምላክ መኖር የማያምን ሰው ነበር። እንዲህ ያለ ንቁ ክርስቲያን የይሖዋ አገልጋይ እንዲሆን የገፋፋው ምንድን ነው?

      ራዘርፎርድ በሐምሌ 1913 ዩ ኤስ ኤ ውስጥ በማሳቹሴትስ ክፍለ ሀገር በስፕሪንግፊልድ ከተማ ተደርጎ በነበረው ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበር የአውራጃ ስብሰባ ላይ ሊቀ መንበር በመሆን አገልግሏል። በከተማው የሚገኝ ዘ ሆምስቴድ የተባለ ጋዜጣ ዜና አጠናቃሪ ለራዘርፎርድ ቃለ መጠይቅ አድርጎለት የነበረ ሲሆን የሰጠውም መልስ የአውራጃ ስብሰባው ዋና ዋና ክፍሎች በወጡበት ጽሑፍ ላይ እንደገና ታትሟል።

      ራዘርፎርድ ለማግባት ባሰበበት ጊዜ የባፕቲስት ሃይማኖትን እምነት ይከተል እንደነበረና ሊያገባት ያሰባት ሴት ግን የፕሪስቢቴሪያን ሃይማኖት ተከታይ እንደነበረች ተናግሯል። የራዘርፎርድ ፓስተር “እሷ ስላልተጠመቀች ወደ ሲኦል እሳት እንደምትገባና እሱ ግን በመጠመቁ ምክንያት በቀጥታ ወደ ሰማይ እንደሚሄድ ሲነግሩት ነገሮችን በሚገባ ማመዛዘን የሚችለው አእምሮው ይህን ለመቀበል አሻፈረኝ ስላለ አምላክ የለም ባይ ሆነ።”

      ራዘርፎርድ ሕያው በሆነ አምላክ ላይ እምነት ለመገንባት ብዙ ዓመታት የፈጀ ጥልቅ ጥናት ማድረግ አስፈልጎታል። “አእምሮን ሊያረካ የማይችል ነገር ልብንም ለማርካት አይችልም” የሚል መሠረት ይዞ እንደተነሳ ተናግሯል። ክርስቲያኖች “የሚያምኑባቸው ቅዱሳን ጽሑፎች እውነት መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው” በማለት ራዘርፎርድ ከገለጸ በኋላ “የቆሙበትን መሠረት ሊያውቁት ይገባል” ሲል አክሎ ተናግሯል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17ን ተመልከት።

      አዎን፣ ዛሬም እንኳን ቢሆን በአምላክ መኖር የማያምን ወይም ስለ አምላክ መኖር አለመኖር በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም የሚል አንድ ሰው ቅዱሳን ጽሑፎችን ሊመረምር፣ በይሖዋ አምላክ ላይ እምነቱን ሊገነባና ከእርሱም ጋር ጠንካራ የሆነ የግል ዝምድና ሊያዳብር ይችላል። አንድ ወጣት በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በታተመውና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ካጠና በኋላ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ይህን ጥናት በጀመርኩበት ጊዜ በአምላክ አላምንም ነበር፤ ይሁን እንጂ አሁን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት የነበረኝን አስተሳሰብ ፍጹም እንደለወጠው ልገነዘብ ችያለሁ። ይሖዋን ማወቅና በእርሱም ማመን ጀምሬአለሁ።”

      “ሞኝ ሰው” እና አምላክ

      ዶክተር ጄምስ ሄስቲንግስ ኤ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል በተባለ መጽሐፍ ላይ እንዲህ ብለዋል:- “የትኛውም የብሉይ ኪዳን [የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች] ጸሐፊ የአምላክን መኖር ለማብራራት ወይም ለማስረዳት አስቦ አያውቅም። የጥንቱ ዓለም የአምላክን መኖር የሚክድ ወይም አምላክ መኖሩን የሚያረጋግጡ የማሳመኛ ነጥቦች የሚያስፈልጉት አልነበረም። በአምላክ መኖር ማመን ለሰው ልጅ አእምሮ ተፈጥሯዊ የሆነና ለሁሉም ሰዎች ደግሞ የተለመደ ነገር ነበር።” በእርግጥ ይህ በዚያ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች በሙሉ አምላካዊ ፍርሃት ነበራቸው ማለት አይደለም። እውነታው ከዚያ የተለየ ነበር። በመዝሙር 14:​1 እና 53:​1 ላይ “ሰነፍ” ወይም እንደ ኪንግ ጄምስ ቨርሽን “ሞኝ” በልቡ “አምላክ የለም ይላል” የሚል ሐሳብ እናገኛለን።

      የአምላክን መኖር የሚክደው ይህ ሞኝ ሰው ምን ዓይነት ሰው ነው? ምንም እውቀት የሌለው ደንቆሮ ሰው አይደለም። ከዚህ ይልቅ ናቫል የሚለው የዕብራይስጥ ቃል የሥነ ምግባር ጉድለትን ያመለክታል። ፕሮፌሰር ኤስ አር ድራይቨር ዘ ፓረሌል ሶልተር በተባለ ጽሑፍ ላይ ችግሩ “የመረዳት ድክመት ሳይሆን ለሥነ ምግባርና ለሃይማኖት ቸልተኛ መሆን፣ ደንታቢስነት ወይም ግዴለሽነት ነው” ብለዋል።

      መዝሙራዊው በመቀጠል ይህ አመለካከት ያስከተለውን የሥነ ምግባር ውድቀት ሲገልጽ “በሥራቸው ረከሱ፣ ጎሰቆሉ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም” ብሏል። (መዝሙር 14:​1) ዶክተር ሄስቲንግስ ሲያጠቃልሉ “አምላክ ከሰዎች አእምሮ ውስጥ መጥፋቱ እንዲሁም ጥፋተኞች ሳይቀጡ መቅረታቸው ሰዎች ብልሹዎች እንዲሆኑና አስከፊ ሥራዎችን እንዲፈጽሙ አድርጓቸዋል።” አምላካዊ ያልሆኑ መመሪያዎችን በግልጽ በመቀበል ሕያው የሆነውን አምላክ ገሸሽ ያደርጉታል፤ በእርሱም ተጠያቂ ለመሆን አይፈልጉም። ይሁን እንጂ ይህን የመሰለው አመለካከት መዝሙራዊው ከ3,000 ዓመታት በፊት እነዚህን ቃላት በጻፈበት ጊዜ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም የሞኝነትና የስንፍና አስተሳሰብ ነው።

      ሕያው ከሆነው አምላካችን የተሰጡን ማስጠንቀቂያዎች

      አሁን በመጀመሪያው ርዕስ ላይ ወዳነሳናቸው ጥያቄዎች እንመለስ። ብዙ ሰዎች በዚህ ዓለም ላይ ያለውን መከራ ሲመለከቱ ሕያው አምላክ አለ የሚለውን ሐሳብ ለመቀበል የሚቸገሩት ለምንድን ነው?

      መጽሐፍ ቅዱስ ‘በእግዚአብሔር የተላኩ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የተናገሩትን’ የጽሑፍ መረጃ ይዟል። (2 ጴጥሮስ 1:​21) ሕያው አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋ ሊገልጽልን የሚችለው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች ከማይታይና የሰዎችን አስተሳሰብ የመምራትና የመቆጣጠር ኃይል ካለው ሰይጣን ዲያብሎስ ከተባለ ክፉ ፍጡር እንድንጠነቀቅ ያሳስበናል። ነገሩን በምክንያታዊነት ካሰብነው ሕያው አምላክ መኖሩን የማናምን ከሆነ ሕያው የሆነ ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ጭምር ይኖራል ብለን እንዴት ልናምን እንችላለን?

      ሐዋርያው ዮሐንስ ‘ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ዓለሙን ሁሉ እያሳተ እንዳለ’ በመንፈስ አነሳሽነት ጽፏል። (ራእይ 12:​9) ከጊዜ በኋላ ዮሐንስ “ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን” ብሏል። (1 ዮሐንስ 5:​19) እነዚህ መግለጫዎች ዮሐንስ ራሱ በወንጌሉ ላይ የመዘገባቸውን “የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም አንዳች የለውም” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት ያንጸባርቃሉ።​—⁠ዮሐንስ 14:​30

      ይህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት ዛሬ ሰዎች ካላቸው እምነት ጋር እጅግ የተራራቀ ነው! ካቶሊክ ሄራልድ “በአሁኑ ጊዜ ስለ ዲያብሎስ ማውራት ጊዜ ያለፈበት ነገር ነው። ተጠራጣሪ የሆነውና በሳይንስ የመጠቀው ይህ ያለንበት ዘመን ሰይጣንን በጡረታ አግልሎታል” ብሏል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሊገድሉት ይፈልጉ ለነበሩ ሰዎች በግልጽ እንዲህ ብሏቸዋል:- “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ።”​—⁠ዮሐንስ 8:​44

      መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ስላለው ኃይል የሚሰጠው ማብራሪያ ምክንያታዊ ነው። አብዛኛዎቹ ሰዎች በሰላምና በስምምነት የመኖር ምኞት እያላቸው ዓለም ለምን በጥላቻ፣ በጦርነትና በደንብሌን በተፈጸመው ዓይነት (በገጽ 3 እና 4 ላይ የተጠቀሰው) ዓላማ የሌለው የዓመፅ ድርጊት እንደተቀሰፈች በግልጽ ይናገራል። ከዚህም በላይ ልንዋጋው የሚገባን ጠላት ሰይጣን ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ የሰውን ዘር ለማሳሳትና ለማሰቃየት ከረዥም ጊዜ በፊት ከሰይጣን ጋር ሕብረት ስለፈጠሩ አጋንንት ማለትም ስለ ክፉ መንፈሳዊ ፍጥረቶች ጭምር ማስጠንቀቂያ ይሰጠናል። (ይሁዳ 6) ኢየሱስ ክርስቶስ በእነዚህ መናፍስታዊ ኃይላት ብዙ ጊዜ ቢፈተንም ሊያሸንፋቸው ችሏል።​—⁠ማቴዎስ 12:​22-24፤ ሉቃስ 9:​37-43

      እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ይህችን ምድር ከክፋት የማጥራትና በመጨረሻም የሰይጣንና የአጋንንቱን እንቅስቃሴዎች የማስወገድ ዓላማ አለው። ስለ ይሖዋ ያለን እውቀት በተስፋዎቹ ላይ ጽኑ እምነት እንዲኖረን ሊያደርገን ይችላል። እንዲህ ብሏል:- “ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይሆንም። እኔ፣ እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ነኝ፣ ከእኔም ሌላ የሚያድን የለም።” በእርግጥ ይሖዋ እሱን ለሚያውቁት፣ ለሚያመልኩትና ለሚያገለግሉት ሁሉ ሕያው የሆነ አምላክ ነው። መዳን የምናገኘው ከእሱ ብቻ ነው።​—⁠ኢሳይያስ 43:​10, 11

      [በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ሙሴ በመንፈስ አነሳሽነት ዘፍጥረት 1:​1ን ሲጽፍ የሚያሳይ የ18ኛው መቶ ዘመን ቅርጽ

      [ምንጭ]

      From The Holy Bible by J. Baskett, Oxford

      [በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ኢየሱስ ክርስቶስ የአጋንንትን ኃይል ብዙ ጊዜ አሸንፏል

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ